መልዕክት ለወጣቶች

266/511

የባሕርይ ታላቅነት ምልክቶች

ዳንኤልና ጓደኞቹ በሶስቱ ዓመት የስልጠና ጊዜያቸው የአመጋገብ ቁጥብነታቸውን፣ ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነትና ሁልጊዜ በእርሱ ኃይል መደገፍን ቀጥለውበት ነበር፡፡ ያገኙት እውቀትና ችሎታ በንጉሡ የሚፈተንበት ጊዜ ሲመጣ በመንግሥቱ ውስጥ ለማገልግል ከሌሎቹ እጩዎች ጋር ተመረመሩ፡፡ ነገር ግን «ከእነዚያ ሁሉ መካከል እንደ ዳንኤል፣ እንደ አናኒያ፣ እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛሪያ ያለ ማንም አልተገኘም፡፡» ነገሮችን ለማየት የነበራቸው ማስተዋል፣ ትክክለኛ ቋንቋ የመምረጥ ችሎታቸውና ሰፊ እውቀታቸው የአእምሮ ኃይላቸውን ጥንካሬና ብርታት ገለጸ፡፡ ስለዚህ በንጉሡ ፊት ቆሙ፡፡ «ንጉሡ በጠየቃቸው በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስመተኞች ሁሉ እነርሱ እጅግ በልጠው አገኛቸው፡፡” MYPAmh 158.1

እግዚአብሔር ሁልጊዜ ትክክል የሆኑትን ያከብራል፡፡ ታላቁ ንጉሥ በወረራ ከያዛቸው አገሮች ሁሉ ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣቶች በባቢሎን ተሰብስበው ነበር፡፡ ከእነዚህ ሁሉ መካከል የዕብራውያን ምርኮኞች ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡ ቀጥ ያለ አቋማቸው፣ ጽኑ የሆነ የሚነጥር አከሄዳቸው፣ ብሩህ ፊታቸው፣ ያልደበዘዘ ግንዛቤያቸው፣ ያልተበከለ ትንፋሻቸው ሁሉ ተፈጥሮ ለሕጎችዋ የሚታዘዙትን የምታከብር መሆኑን የሚገልጹ የባሕርይ ታላቅነት ምልክቶች ነበሩ፡፡ MYPAmh 158.2