የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ያለ ልምምድ
የእግዚአብሔርን ተቋማት እየበከለ ያለውን መንፈስ በተመለከተ ትልቅ ጥንቃቄ መወሰድ አለበት፡፡ እነዚህ ተቋማት የተቋቋሙት ራስን መስዋዕት በማድረግ፣ ራሳቸውን የካዱ የእግዚአብሔር ሰዎች በሰጡአቸው ስጦታዎች እና ራስ ወዳድነት በሌለው የእግዚአብሔር ባርያዎች አገልግሎት ነበር፡፡ ከተቋማዊ አገልግሎት ጋር የተገናኘ እያንዳንዱ ነገር የሰማይን ፊርማ መያዝ አለበት፡፡ የእግዚአብሔር ተቋማት ቅድስና ስሜት መደፋፈርና መጎልበት አለበት፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሉአላዊነት በመቀበል ልባቸውን በእርሱ ፊት ዝቅ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሁሉም ራስን በመካድ መርሆዎች መሰረት መኖር አለባቸው፡፡ እንደ እውነተኛ፣ ራሱን መስዋዕት እንደሚያደርግ ሰራተኛ፣ መንፈሳዊ ፋኖሱ ተወልውሎ እየነደደ፣ እየሰራ ያለውን ድርጅት ፍላጎቶች ለማራመድ ራስ ወዳድነት በሌለበት ሁኔታ ይጥራል፣ የከበረ ልምምድ ይኖረውና «በእርግጥ እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው» ማለት ይችላል፡፡ ችሎታውን፣ አገልግሎቱንና የማይደክም ንቃትን ለእግዚአብሔር ተቋም ለመስጠት በመፍቀዱ በከፍተኛ ደረጃ የታደለ መሆኑ ይሰማዋል፡፡ {2SM 176.4} Amh2SM 176.4
በሶስተኛው መልአክ መልእክት ጅምር ላይ ተቋማችንን የመሰረቱት እና በእነርሱ ውስጥ የሰሩት ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ራስ ወዳድነት በሌለበት ሀሳብ ተነሳስተው ነበር፡፡ ይሰሩት ለነበረው ከባድ ሥራ ይሰጣቸው የነበረው ራሳቸውን ለመደገፍ እንኳን የማይበቃ እጅግ ዝቅተኛ ክፍያ ነበር፡፡ ነገር ግን ልቦቻቸው በአገልግሎት ፍቅር የተጠመቁ ነበሩ፡፡ በሙሉ ልብ የሚሰጥ ልግስና ከሰራተኞች አለቃ መንፈስ ጋር በነበራቸው የቀረበ ግንኙነት ግልጽ ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ በተቻለ መጠን ብዙ ሰራተኞች የእውነትን መስፈርቶች በአዳዲስ ቦታዎች መትከል እንዲችሉ ከፍተኛ የሆነ ቁጠባን ተለማመዱ፡፡ {2SM 177.1} Amh2SM 177.1
ነገር ግን ከጊዜ ጋር ለውጥ መጣ፡፡ እንደዚያ ጊዜ የመስዋዕትነት መንፈስ አይታይም፡፡ በአንዳንድ ተቋሞቻችን የጥቂት ሰራተኞች ደሞዝ ምክንያት ሊሰጠው ከሚችል በላይ ተጨምሯል፡፡ ይህ ከፍተኛ ደሞዝ የሚሰጣቸው ሰዎች ከሌሎች የሚበልጥ ችሎታ ስላላቸው ሊከፈላቸው እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ችሎታቸውንና መክሊቶቻቸውን የሰጠው ማን ነው? ከደሞዝ ጭማሪ ጋር ቀስ በቀስ ጣዖት የሆነው የመመኘት መንፈስም መጣና መንፈሳዊነት እየቀነሰ ሄደ፡፡ ጉልህ የሆኑ ክፋቶች ቀስ ብለው ገቡና እግዚአብሔር ክብሩን አጣ፡፡ ይህን ለከፍተኛ ደሞዝ የሚደረገውን መስገብገብ የተመለከቱ የብዙ ሰዎች አእምሮዎች በጥርጣሬና በአለማመን እርሾ ተመረዙ፡፡ እንደ ክፉ እርሾ እንግዳ የሆኑ መርሆዎች በመላው አማኞች ውስጥ ተሰራጩ፡፡ ብዙዎች ራሳቸውን መካድን ተዉ፣ ጥቂት የማይባሉትም አስራታቸውንና ስጦታቸውን ከለከሉ፡፡ {2SM 177.2} Amh2SM 177.2
እግዚአብሔር በገዛ ፈቃዱ በቅዱስ ሥራው ውስጥ በልብ ውስጥ ተጀምሮ ወደ ውጭ መስራት ያለበት ተሃድሶ እንዲመጣ ጥሪ አቀረበ፡፡ በጭፍንነት ለአገልግሎታቸው ከፍተኛ ግምት መስጠታቸውን የቀጠሉ አንዳንድ ሰዎች ተወገዱ፡፡ ሌሎች ለእነዚያ ተሰጥቶ የነበረውን መልእክት ተቀብለው ልባቸውን ሙሉ ለሙሉ ለዓላማው በመስጠት ወደ እግዚአብሔር ተመለሱና የምኞት መንፈስን መጥላትን ተማሩ፡፡ በተቻላቸው መጠን በራሳቸው ፈቃድ ደሞዛቸውን በመቀነስ በሕዝብ ፊት ትክክለኛ የሆነ ምሳሌን ለማስቀመጥ ጥረት አደረጉ፡፡ እግሮቻቸው በከፍተኛ ብልጠት በተዘጋጁ በአንዳንድ ፈተናዎች ተጠራርገው እንዳይወሰዱ ለማዳን ከአእምሮና ከልብ ሙሉ በሙሉ መለወጥ ያነሰ ነገር እንደማያስፈልግ ተገነዘቡ፡፡ {2SM 177.3} Amh2SM 177.3