የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
የጀምስ ኋይት ጤንነት መመለስ
ከብዙ ዓመታት በፊት (1865)፣ Amh2SM 306.1
ባለቤቴ በባትል ክሪክ ከባድ ኃላፊነቶችን ተሸክሞ በነበረ ጊዜ፣ የስራው ጫና በአካሉ ላይ መታየት ጀመረ፡፡ ጤንነቱ በፍጥነት ተለየው፡፡ በመጨረሻም በአካልም ሆነ በአእምሮ ከመድከሙ የተነሣ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም ነበር፡፡ ጓደኞቼ፣ «ሚስስ ኋይት፣ ባለቤትሽ በሕይወት መኖር አይችልም” አሉኝ፡፡ ጤንነቱ እንዲያገግም የበለጠ ምቹ ወደሆነ ቦታ ልወስደው ወሰንኩ፡፡ እናቱ፣ «ኤለን፣ ቤት ሆነሽ ለቤተሰብሽ መጠንቀቅ አለብሽ» አለችኝ፡፡ Amh2SM 306.2
እኔም መልሼ፡- «እናቴ፣ ያ ጠቢብ አእምሮ ሙሉ በሙሉ ሥራውን እንዲያቆም በፍጹም አልፈቅድም፡፡ የባለቤቴን አእምሮ ለማዳን ከእግዚአብሔር ጋር እሰራለሁ፣ እግዚአብሔርም ከእኔ ጋር ይሰራል» አልኳት፡፡ Amh2SM 306.3
ለጉዟችን ገንዘብ ለማግኘት ምንጣፎቼን አንስቼ ሸጥኳቸው፡፡ …ምንጣፎቼን በመሸጥ በተገኘው ገንዘብ ሽፍን ሰረገላ ገዛሁና በሰረገላው ውስጥ አባት እንዲተኛበት ፍራሽ በማስቀመጥ ለጉዞ ተዘጋጀን፡፡ ከነበረን ብቸኛው የአሥራ አንድ አመት ዊሊ ጋር በመሆን ሚሽጋን ወደነበረው ወደ ራይት ጉዞአችንን ጀመርን፡፡ Amh2SM 306.4
በጉዞ ላይ እያለን ዊሊ ከፈረሶቹ መካከል በአንዱ አፍ ውስጥ ልጓም ለማድረግ ቢሞክርም አልቻለም ነበር፡፡ ባለቤቴን «እጅህን በትካሻዬ ላይ አድርግና ሄደን ልጓሙን በፈረሱ አፍ አድርግ» አልኩት፡፡ Amh2SM 306.5
እሱም እንዴት ማድረግ እንደምችል አይታየኝም አለኝ፡፡ እኔም «ትችላለህ፣ ተነስና ና” አልኩት፡፡ እንዳዘዝኩት አደረገና ልጓሙን በፈረሱ አፍ ውስጥ ማድረግ ቻለ፡፡ በሚቀጥለው ጊዜም ማድረግ እንዳለበት አወቀ፡፡ Amh2SM 306.6
ያለማቋረጥ ባለቤቴ እንደዚህ ያሉ ትንንሽ ነገሮችን እንዲሠራ አደረግኩት፡፡ ፀጥ ብሎ እንዲቀመጥ አልፈቀድኩለትም፣ ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን እንዲሰራ ለማድረግ ሞከርኩ፡፡ በጤና ተቋሞቻችን ውስጥ ያሉት ሐኪሞች እና ረዳቶች መከተል ያለባቸው እቅድ ይህ ነው፡፡ የሕመምተኞች አእምሮ ባሉበት ሁኔታ ላይ በማዘን የሚያሳልፉበት ጊዜ እንዳይኖር በስራ እንዲጠመድ በማድረግ በዚህ መስመር ደረጃ በደረጃ፣ ደረጃ በደረጃ ምሯቸው፡፡ Amh2SM 306.7
የአካልና የአእምሮ ስራ ተደፋፈረ Amh2SM 307.1
ብዙ ጊዜ ወንድሞች ምክርን በመፈለግ ወደ እኔ ይመጡ ነበር፡፡ ባለቤቴ ማንንም ማየት አይፈልግም ነበር፡፡ ሰዎች ሲመጡ ወደ ሌላ ክፍል መሄድን በጣም ይፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን ማንም መምጣቱን ከመገንዘቡ በፊት እንግዳውን ወደ እርሱ አመጣና «ባለቤቴ ሆይ፣ ይህ ወንድም ጥያቄ ለመጠየቅ የመጣ ነው፣ አንተ ከእኔ በተሻለ ሁኔታ ጥያቄውን መመለስ ስለምትችል ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ” እለው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ማድረግ የሚችለው ሌላ አማራጭ አልነበረውም ነበር፡፡ በክፍሉ ውስጥ ሆኖ ጥያቄውን መመለስ ነበረበት፡፡ በዚህና በሌሎች ብዙ መንገዶች አእምሮውን እንዲያሰራ አደረግኩት፡፡ አእምሮውን እንዲጠቀም ባይደረግ ኖሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ አእምሮው ሥራውን ያቆም ነበር፡፡ Amh2SM 307.2
ባለቤቴ በየቀኑ የእግር ጉዞ ያደርግ ነበር፡፡ በክረምት ወቅት አሰቃቂ የሆነ የበረዶ ማዕበል ስለወረደ በዚያ ውስጥ ወደ ውጭ መውጣት እንደማይችል አሰበ፡፡ እኔ ወደ ወንድም ሩት ሄድኩና «ወንድም ሩት፣ ትርፍ ጥንድ ቦቲዎች አሉህ ወይ?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ Amh2SM 307.3
እሱም «አዎን» በማለት መለሰልኝ፡፡ Amh2SM 307.4
እኔም «ዛሬ ጧት መዋስ ብችል ደስ ይለኛል» አልኩት፡፡ ቦቲ ጫማዎቹን አድርጌ በመውጣት በበረዶው ውስጥ ሲሶ ማይል ያህል ርቀትን ተጓዝኩ፡፡ ከዚያም ተመለስኩና ባለቤቴን የእግር ጉዞ እንድናደርግ ጠየቅኩት፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የአየር ንብረት ውስጥ መውጣት እንደማይችል ነገረኝ፡፡ እኔም «ትችላለህ፣ የእኔን ዱካ እየተከተልክ መሄድ ትችላለህ” አልኩት፡፡ ለሴት ትልቅ አክብሮት የነበረው ሰው ነበር፤ እኔ የሄድኩበትን መንገድ ባየ ጊዜ ሴት በበረዶ ውስጥ መሄድ ከቻለች እሱም መሄድ እንደሚችል አሰበ፡፡ በዚያ ጧት የተለመደውን የእግር ጉዞ አደረገ፡፡ Amh2SM 307.5
በጸደይ ወራት ውስጥ መተከል ያለባቸው የፍራፍሬ ዛፎችና መዘጋጀት ያለበት የአትክልት ቦታ ነበር፡፡ ልጄን «ዊሊ፣ እባክህን ሶስት መቆፈሪያዎችንና ሶስት መቧጠጫዎችን ግዛ፡፡ ከእያንዳንዱ ሶስት ሶስት መግዛትህን እርግጠኛ ሁን» አልኩት፡፡ እቃዎቹን ባመጣልኝ ጊዜ ከመቆፈሪያዎቹ መካከል አንዱን እሱ እንዲወስድና ሌላኛውን ለአባቱ እንዲሰጥ ነገርኩት፡፡ እኔም አንዱን ወሰድኩና ሥራ ጀመርን፤ ምንም እንኳን እጄ ውኃ ቢቋጥርም በቁፋሮው መራኋቸው፡፡ አባት ብዙ መሥራት ባይችልም ከእኛ ጋር አብሮ ተንቀሳቀሰ፡፡ ባለቤቴን ወደ ጤንነት ለመመለስ ከእግዚአብሔር ጋር ለመተባበር የሞከርኩት በእነዚህ መንገዶች ነበር፡፡ እነሆ ጌታም ባረከን! Amh2SM 307.6
ለመንዳት በምሄድበት ጊዜ ሁሉ ባለቤቴን ይዤ እሄድ ነበር፡፡ በማንኘውም ሥፍራ ለስብከት ስሄድም ይዤው እሄድ ነበር፡፡ ቋሚ የሆኑ ተከታታይ ስብሰባዎች ነበሩኝ፡፡ እየሰበክሁ ሳለሁ ወደ አግዳሚ ወንበር ሄዶ እንዲቀመጥ ማሳመን አልቻልኩም ነበር፡፡ በመጨረሻ ከብዙ ወራት በኋላ እንዲህ አልኩት፣ «ዛሬ ወደ አግዳሚ ወንበር ሂደህ ልትቀመጥ ነው» አልኩት፡፡ ለመሄድ ፈቃደኛ ባይሆንም አልተሸነፍኩለትም ነበር፡፡ ወደ አግዳሚ ወንበሩ አብሮኝ እንዲሄድ አደረግኩት፡፡ ያን ቀን ለሕዝቡ ተናገረ፡፡ ምንም እንኳን የተሰበሰብንበት ቤት በማያምኑ ሰዎች የተሞላ ቢሆንም ግማሽ ሰዓት ያህል ያለማቋረጥ አለቅስ ነበር፡፡ በልቤ ውስጥ ደስታና ምስጋና ሞልቶ እየፈሰሰ ነበር፡፡ ድል እንደተገኘ አወቅኩ፡፡ Amh2SM 307.7