የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

240/349

ምዕራፍ 31—የግል ልምምዶች

የሳንባ ምችን በማከም ረገድ የቀድሞ ልምምድ

በ1864 ዓ.ም የክረምት ወቅት ልጄ ዊሊ ከሳንባ ምች የተነሣ ድንገተኛና ኃይለኛ የሆነ ትኩሳት ያዘው፡፡ ከዚህ በሽታ የተነሣ ታላቁን ልጃችንን በቅርቡ ስለቀበርነው ዊሊም ይሞትብን ይሆናል ብለን በጣም ተጨንቀን ነበር፡፡ ሐኪምን ላለማማከር፣ ነገር ግን ውኃን በመጠቀምና ስለ ሕጻኑ እግዚአብሔርን በመለመን ራሳችን ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ወሰንን፡፡ እምነት ያላቸውን ጥቂት ሰዎች በጸሎት እንዲተባበሩን ጠየቅናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን መገኘትና በረከት ጣፋጭ ማረጋገጫ አገኘን፡፡ Amh2SM 304.1

በሚቀጥለው ቀን ዊሊ በጣም ታሞ ነበር፡፡ ይቃዥ ነበር፡፡ ሳናግረው የሚያይ ወይም የሚሰማ አይመስልም ነበር፡፡ ልቡ በትክክል አይመታም ነበር፣ ነገር ግን ያለማቋረጥ የተረበሸ መርገብገብ ይታይበት ነበር፡፡ ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር መመልከታችንን፣ በራሱ ላይ ውኃን በደንብ መጠቀማችንንና ያለማቋረጥ ሳንባውን በውኃ መጫናችንን ቀጠልን፡፡ ብዙም ሳይቆይ ከዚህ በፊት እንደነበረው ወደ ህሊናው ተመለሰ፡፡ በቀኝ ጎኑ በኩል ከባድ ሕመም ይሰማው ስለነበር ለአፍታ እንኳን በዚያ ጎኑ መተኘት አልቻለም ነበር፡፡ ይህ ሕመም የቀነሰው እንደ ትኩሳቱ መጠን የውኃውን ሙቀት በመቀያየር በቀዝቃዛ ውኃ በመጫን ነበር፡፡ እጆቹና እግሮቹ ሞቃት ሆነው እንዲቆዩ ለማድረግ በጣም ጥንቃቄ አድርገን ነበር፡፡ Amh2SM 304.2

ችግሩ በሰባተኛ ቀን ያበቃል ብለን ጠብቀን ነበር፡፡ ልጁ በሕመም ላይ በነበረባቸው ቀናት ውስጥ ምንም እረፍት ስላላገኘን በአራተኛውና በአምስተኛው ሌሊቶች ሌሎች ሰዎች እንዲጠነቀቁለት አሳልፈን ለመስጠት ተገደድን፡፡ ባለቤቴና እኔ በአምስተኛው ቀን በጣም ተጨነቅን፡፡ ሕጻኑ ንጹህ ደም ያስታውክና በጣም ያስል ነበር፡፡ ባለቤቴ አብዛኛውን ሰዓት በጸሎት ያሳልፍ ነበር፡፡ በዚያን ሌሊት ልጃችንን በጣም ጥንቁቅ በሆኑ እጆች ውስጥ ተውን፡፡ ከመተኛታችን በፊት ባለቤቴ ረዥምና ልባዊ የሆነ ጸሎት ጸለየ፡፡ በድንገት የጸሎት ሸክም ለቀቀውና የሆነ ድምጽ «ሂድና ተኛ፣ ለልጁ እኔ እጠነቀቃለሁ” የሚለው መሰለው፡፡ Amh2SM 304.3

እኔ አሞኝ ብተኛም ከጭንቀት የተነሣ ለበርካታ ሰዓታት መተኛት አልቻልኩም ነበር፡፡ የአየር እጥረት አስጨነቀኝ፡፡ እየተኛን የነበረው ትልቅ ክፍል ውስጥ ቢሆንም ተነሳሁና ወደ ትልቁ አዳራሽ የሚመራውን በር ስከፍት ወዲያውኑ ፋታ አገኘሁና ብዙም ሳይቆይ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡ ልምድ ያለው ሐኪም በልጄ አጠገብ ቆሞ አንዱን እጅ በልጄ ላይ አድርጎ በሌላኛው እጁ ደግሞ የልብ ምቱን እየለካ እያንዳንዱን እስትንፋስ እየተከታተለ እንደሆነ አለምኩ፡፡ ወደ እኛ ዞር ብሎ «ችግሩ አልፏል፡፡ እጅግ አስከፊ የሆነው ሌሊት አልፏል፡፡ አሁን እንደገና ማገገም የሚያስፈልገው ጎጂ የሆነ የመድሃኒት ተጽእኖ ስለሌበት ቶሎ ይሻለዋል፡፡ ከአካል ክፍሎች ቆሻሻን ለማስወገድ ተፈጥሮ የከበረ ሥራዋን ሰርታለች” ብሎ ነገረኝ፡፡ እንዴት እንደደከመኝ፣ ለመተንፈስ የነበረብኝን ጭንቀት እና በር ከከፈትኩ በኋላ ያገኘሁትን እረፍት ነገርኩት፡፡ Amh2SM 305.1

እንዲህ አለኝ፣ «ለአንቺ እረፍት የሰጠው ለልጅሽም እረፍት ይሰጠዋል፡፡ አየር ያስፈልገዋል፡፡ ከመጠን በላይ ሙቀት እንዲያገኝ አድርጋችሁታል፡፡ ከምድጃው የሚመጣው የሞቀ አየር ጎጂ ነው፤ በመስኮቶቹ መጋጠሚያ ባሉ ክፍተቶች የሚገባው አየር ባይኖር ኖሮ መርዝ ይሆንና ሕይወትን ያጠፋ ነበር፡፡ ከምድጃ የሚወጣ ሙቀት የአየርን ሕይወት ሰጭነት ከማጥፋቱም በላይ ሳንባዎችን ያዳክማል፡፡ ክፍሉ ከመጠን በላይ እንዲሞቅ ከመደረጉ የተነሳ የልጁ ሳንባዎች ደክመው ነበር፡፡ የታመሙ ሰዎች ከበሽታ የተነሣ አቅም ያጡ ስለሆኑ ዋና የአካል ክፍሎቻቸው በሽታን ለመቋቋም እንዲችሉ ብርታት ሰጭ የሆነውን አየር ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ አየርና ብርሃን በጣም በሚያስፈልጉባቸው ጊዜያቶች አደገኛ ጠላት የሆኑ ይመስል ወደ ሕመምተኛው ክፍል እንዳይገቡ ይደረጋሉ፡፡ Amh2SM 305.2

ይህ ሕልምና የባለቤቴ ልምምድ ለሁለታችንም መጽናኛ ነበር፡፡ በማለዳ ልጃችን እረፍት የለሽ ሌሊት እንዳሳለፈ አወቅን፡፡ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከፍተኛ ትኩሳት ያለበት ይመስል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ትኩሳቱ ለቀቀውና ከድካም በስተቀር የተሻለው መሰለ፡፡ አምስት ቀናት በቆየው የሕመም ወቅት ከአንድ ትንሽ ብስኩት በስተቀር ሌላ ምንም ነገር አልበላም ነበር፡፡ በፍጥነት ተሻለውና ከዚህ በፊት ለበርካታ ዓመታት ከነበረው በበለጠ ሁኔታ ጤንነቱ የተሻለ ሆነ፡፡ ይህ ልምምድ ለእኛ ጠቃሚ ነው፡፡ Spiritual Gifts, vol. 4 (first section), pp. 151-153 (1864). Amh2SM 305.3