የልጅ አመራር

36/85

ምዕራፍ 34—ባህሪይ የሚበላሽባቸው መንገዶች

ወላጆች የጥፋትን ዘር ሊዘሩ ይችላሉ—የተሳሳቱ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥፋት የሚያመጣባቸውን ትምህርቶች እያስተማሩ ነው፣ እንዲሁም ለራሳቸውም እግሮች እሾህ እየዘሩ ናቸው…፡፡ ወላጆች በእጅጉ የልጆቻቸውን መጻኢ ደስታ በእጃቸው ይዘዋል። የእነዚህን ልጆች ባህሪይ የመቅረጽ ወሳኝ ሥራ በእነርሱ ላይ የተጣለ ነው፡፡ በልጅነት ጊዜ የተሰጣቸው መመሪያዎች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ይከተላቸዋል፡፡ ወላጆች ከበቀለ በኋላ ለመልካምም ሆነ ለክፉ ፍሬ የሚያፈራ ዘር ይዘራሉ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለደስታ ወይም ለስቃይ ሊያበቁ ይችላሉ፡፡311 CGAmh 166.1

በማሞላቀቅ ወይም የብረት በትር ሕግ—ልጆች ብዙውን ጊዜ ከልጅነታቸው ጀምሮ ይሞላቀቃሉ፣ በዚህም ሳቢያ የተሳሳቱ ልማዶች ይተከላሉ። ወላጆቹ ለጋ የሆነ ተክልን ሲያጣምሙ ቆይተዋል፡፡ በስልጠና ሂደት ውስጥ ባህሪያቸው ወደ መበላሸት ወይም ሚዛናዊ እና መልካም ወደ መሆን ያድጋል፡፡ ብዙዎች በማሞላቀቅ ጽንፍ ሲሳሳቱ ሌሎች ግን ወደ ተቃራኒው ጽንፍ ሄደው ልጆቻቸውን በብረት በትር ይገዟቸዋል። ከእነዚህ አንዳቸውም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ እየተከተሉ አይደሉም፣ ሁለቱም የሚያስፈራ ሥራ በመስራት ላይ ናቸው፡፡ እነርሱ የልጆቻቸውን አእምሮ እየቀረጹ ናቸው፣ ይህን ስለማድረጋቸውም በእግዚአብሔር ቀን መልስ መስጠት አለባቸው። ዘላለማዊነት በዚህ ምድር ሕይወት የተከናወኑ ስራዎችን ውጤት ያሳያል፡፡ 312 CGAmh 166.2

ለእግዚአብሔር ማሠልጠን ያለመቻል—ልጆቻቸው የጌታን መንገድ እንዲጠብቁ፣ እርሱ ያዘዛቸውን እንዲያደርጉ፣ ልጆቻቸውን ማሠልጠን ባለመቻላቸው፣ ወላጆች አንድ ከባድ ግዴታን ችላ ይላሉ፡፡313 CGAmh 166.3

አንዳንድ [ልጆች] የሻቸውን እንዲያደርጉ ይተዋሉ፤ ሌሎች በጥፋታቸው ተገኝተው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ነገር ግን ጥቂት ትህትና፣ ደስተኛነት፣ እና የአድናቆት ቃላት ይሰጣቸዋል።314 CGAmh 167.1

አቤት እናቶች በእርጋታ እና በቆራጥነት የልጆቻቸውን ሥጋዊ የግልፍተኝነት ስሜቶችን ለማሰልጠን እና ለመቆጣጠር በጥበብ ብቻ ቢሰሩ ኖሮ ምን ያህል ኃጢአት በእምቡጥነቱ በተቀጨ፣ እና ምን ያህል አያሌ የቤተ ክርስቲያን መከራዎች ባልተከሰቱ ነበር! …ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ ከማሰልጠን እና በወጣትነታቸው ለባለሥልጣን እንዲገዙ ከማስተማር ችል በማለታቸው ብዙ ነፍሳት ለዘላለም ይጠፋሉ። ስህተቶችን በዝምታ ማለፍ እና ግልፍተኝነትን መታገስ በክፋት ሥር ምሳርን የሚያስቀምጥ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ነፍሳትን የሚያጠፋ ነው፡፡ አቤት፣ ወላጆች ለዚህ አስፈሪ ችላ ባይነት ለእግዚአብሔር ምን ምላሽ ይሰጣሉ! 315 CGAmh 167.2

ኃጢአትን ቀለል አድርገው የማየት ችላ ባይነት—ሰይጣን አእምሯቸውን እና ልባቸውን ለመቆጣጠር እና የእግዚአብሄርን መንፈስ ከውስጣቸው ለማውጣት እየጣረ ስለሆነ ልጆች ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ንቁ እንክብካቤ እና ምሪት ይፈልጋሉ፡፡ የዚህ ዘመን ወጣት አስፈሪ ሁኔታ በመጨረሻው ቀን ውስጥ እየኖርን ስለ መሆኑ ጠንካራ ምልክቶች አንዱ ነው፣ ሆኖም ግን የብዙዎች ጥፋት ዱካ ሲታይ በቀጥታ በወላጆች የተሳሳተ አመራር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። ተግሳጽ ላይ የማጉረምረም መንፈስ ሥር እየሰደደ የመጣ ሲሆን ያለ መታዘዝን ፍሬ እያፈራ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው እያሳዩ ባሉት ባህሪዎች ደስተኞች ባይኑም እንኳ፣ እነርሱ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸውን ስህተቶች ግን ማየት አልቻሉም…፡፡ CGAmh 167.3

በኃጢያት እና በወንጀል ላይ የለውን ቸልተኝነት እና በክርስቲያን ነን ባዮች ቤተሰቦች ውስጥ ያለውን የዚህን ነገር መኖር አስከፊነት ለመለየት ያለመቻል እና መዘግየትን እግዚአብሔር ያወግዛል።316 CGAmh 168.1

በገደብ እጦት—ልጆቻቸውን በአግባቡ ስለማይድቧቸው እና ስለማይመሯቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ በምግበረ ብልሹነት፣ ልቅ ግብረ-ገብ እና በህይወት ኃላፊነቶች ላይ አነስተኛ ትምህርት ይዘው እያደጉ ናቸው፡፡ በስሜቶቻቸው፣ በጊዜያቸው፣ በአዕምሮ ችሎታዎቻቸው እንዳሻቸው እንዲኖሩ ልቅ ተለቅቀዋል፡፡ በእነዚህ ችላ በተባሉ ተሰጥዎች ሳቢያ የጎደፈው የእግዚአብሔር ሥራ በአባቶችና እናቶች ደጃፍ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የመጋቢነት ኃላፊነት ያላቸው፣ በእነርሱ ኃላፊነት ሥር የሆኑት ነፍሳት ኃይላቸውን ሁሉ ለፈጣሪያቸው ክብር እንዲያሻሽሉ የማብቃት የተቀደሰ ኃላፊነትን የሰጣቸው ምን ሰበብ ያቀርባሉ? 317 CGAmh 168.2

ወላጆች ልጆቻቸውን እንደሚወዱ አስበው ነበር፣ ነገር ግን እጅግ የከፋ ጠላቶቻቸው መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ እነርሱ ክፋት ልቅ እንዲተው አድርገዋል። ልጆቻቸው ኃጢያትን እንዲንከባከቡ ፈቅደዋል፣ የሳደገውን ሰለባ ብቻ ሳይሆን ያገኛቸውን በሙሉ የሚነድፍ እፉኝት እንደ መውደድ እና እንደ መንከባከብ ነው። 318 CGAmh 168.3

ጉልህ ስህተቶችን ችላ ማለት—የግብረ-ገብ ደረጃዎችን ከፍ ለማድረግ እና የልጆቻቸውን ስህተቶች ለማረም እግዚአብሔርን በመፍራት ከልባቸው እና ከነፍሳቸው ይሰሩ ዘንድ ሸክሞችን ከሚሸከሙ ሰዎች ጋር ከመተባበር ይልቅ ብዙ ወላጆች “ልጆቼ ከሌሎች ልጆች የባሱ አይደሉም” ሲሉ ሕሊናቸውን ያረጋጋሉ። ልጆቻቸው እንዳይከፉና ተስፋ የመቁረጥ እርምጃ እንዳይወስዱ፣ እግዚአብሔር የሚጠላቸውን ጉልህ ስህተቶች ለመደበቅ ይሻሉ፡፡ የአመጽ መንፈስ ልባቸው ውስጥ ካለ፣ በማሞላቀቅ እንዲያድግ ከመፍቀድ ይልቅ አሁን መቆጣጠሩ እጅግ የተሻለ ነው፡፡ ወላጆች ኃላፊነታቸውን ቢወጡ፣ ከዚህ የተለዩ ሁኔታዎችን እናያለን፡፡ ከእነዚህ ወላጆች መካከል ብዙዎቹ ከአምላክ ወደ ኋላ ያፈገፈጉ ናቸው። የሰይጣንን ዘዴዎች ለመረዳትና ወጥመዶቹን ለመቋቋም ከእርሱ የሆነ ጥበብ የላቸውም፡፡ 319 CGAmh 168.4

ለልጆች የተለየ ትኩረት መስጠት እነ ማሞላቀቅ—ወላጆች ዘወትር ለትናንሽ ልጆቻቸው የተለየ ትኩረት ይሰጣሉ፣ ያሞላቅቋቸውማል፣ ምክንያቱም በዚህ መንገድ እነርሱን መያዝ ቀላል መስሎ ይታያቸዋል፡፡ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ መተው በልባቸው ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚነሱ ሥርዓት አልባ ዝንባሌዎችን ከማገድ ይልቅ የተሻለ ሥራ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የፈሪ እርምጃ ነው፡፡ ያልተገቱ ዝንባሌዎቻቸው ወደ ፍጹም መጥፎ ምግባር ያደጉባቸው እነዚህ ልጆች በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ዘለፋና ሀፍረትን የሚያመጡበት ጊዜ ስለሚመጣ በዚህ አይነት ሁኔታ ከኃላፊነት መሸሽ ክፉ ነገር ነው፡፡ ለፈተናዎቹ ሳይዘጋጁ፣ መደናገርና ችግሮችን ለመቋቋም ብርታት ሳይኖራቸው፤ ስሜታዊ ሆነው፣ ሌሎችን በኃይል ለመቆጣጠር፣ ሥርዓት አልበኛ ሆነው፣ ወደ የዕለቱ የውጥረት ሕይወት ይወጣሉ፡፡ 320 CGAmh 169.1

የከንቱ ዘር በመዝራት—የትም ብንሄድ ያለማስተዋል ልጆች ሲሞላቀቁ፣ ልዩ ትኩረት ሲሰጣቸው እና ሲወደሱ እንመለከታለን፡፡ ይህም ከንቱዎች፣ አይናውጣዎች እና ትዕቢተኞች ያደርጋቸዋል። መጻኢ ጊዜን ሳያስቡ፣ በእነርሱ ኃላፊነት ስር ያሉትን ወጣቶች በሚያሞጋግሱ እና በሚያሞላቅቁ ጥበብ በጎደላቸው ወላጆች እና አሳዳጊዎች አማካይነት በሰው ልጅ ልብ ውስጥ የከንቱነት ዘሮች በቀላሉ ይዘራሉ፡፡ የራስ ፍላጎት እና ኩራት መላእክትን ወደ አጋንንትነት የለወጧቸው እና የሰማይንም በሮች በላያቸው ላይ የዘጉ ክፋቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ወላጆች፣ ባለማስተዋል፣ ልጆቻቸውን የሰይጣን ወኪሎች እንዲሆኑ በደንብ እያሠለ ጠኗቸው ነው፡፡ 321 CGAmh 169.2

ለታዳጊ ልጆች ባሪያ በመሆን—ከትምህርታቸው እና ስልጠናቸው ጋር በሚስማማ መልኩ፣ ልጆች ራሳቸውን በማስደሰት፣ በመዝናናት እና እራሳቸውን በማሞጋገስ ሲኖሩ፣ ምን ያህል የሚለፉ፣ ሸክም የበዛባቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ባሪያዎች ሆነዋል። ወላጆች ለመሰብሰብ ግድየለሾች የሚሆኑበትን መከር በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ይዘራሉ፡፡ በዚህ ስልጠና ውስጥ፣ በአስር፣ በአስራ ሁለት፣ ወይም በአስራ ስድስት ዓመታቸው፣ ልጆች እራሳቸውን እጅግ ጥበበኞች እንደ ያስባሉ፣ ልዩ ችሎታዎች እንዳላቸው ያስባሉ፣ በወላጆቻቸውም ቁጥጥር ሥር እንዳይሆኑ እጅግ አዋቂዎች እንደሆኑ፣ እና የየዕለት የሕይወት ግዴታዎችን ለመወጣት ራሳቸውን እንዳያዋርዱ ከፍ ያሉ እንደሆኑ ይቆጥራሉ። የተድላ ፍቅር አእምሯቸውን ይቆጣጠራል፤ እናም ራስ ወዳድነት፣ ትዕቢት እና አመፅ በህይወታቸው ውስጥ መራራ ውጤት ያመጣል፡፡ የሰይጣንን ማታለያዎች ይቀበሉና በዓለም ላይ ታላቅ ታይታን ለመፍጠር ያልተቀደሱ ምኞት ይንከባከባሉ፡፡ 322 CGAmh 169.3

የተሳሳተ ፍቅር እና ርህራሄ—ወላጆች ለእግዚአብሔር ቅዱስ ህግ ታዛዥ መሆንን አደጋ ላይ በመጣል ለልጆቻቸው ተገቢ ከሆነው በላይ ፍቅር ሊያሳዩ ይችላሉ። በዚህ ፍቅር በመመራት፣ ልጆቻቸው የተሳሳቱ ስሜቶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመፍቀድ እና እግዚአብሔር እንዲሰጡ ያዘዛቸውን መመሪያ እና ተግሣጽ በመተው ለእግዚአብሔርን ሳይታዘዙ ይቀራሉ፡፡ ወላጆች በዚህ መንገድ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ችላ ሲሉ የራሳቸውን እና የልጆቻቸውን ነፍስ አደጋ ላይ ይጥላሉ፡፡ 323 CGAmh 170.1

ታዛዥነትን እንደ መስፈርት በመፈለግ ረገድ የሚታይ ድክመት፣ የሐሰት ፍቅር እና ርህራሄ—ማሞላቀቅና አለመገደብ ጥበብ ነው የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ— መላእክትን የሚያሳዝን ነገር ግን ሰይጣንን ደስ የሚያሰኝ የሥልጠና አካል ነው፣ ምክንያቱም በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ወደ ራሱ መስመር ስለሚያስገባ ነው፡፡ ለዚህም ነው እርሱ የወላጆችን ዓይን የሚያሳውረው፣ የማስተዋል ችሎታቸውን የሚያደነዝዘው እና አዕምሯቸውን ግራ የሚያደናግረው፡፡ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው አስደሳች፣ ተወዳጅ፣ ታዛዥ እና ተንከባካቢ እንዳልሆኑ ይመለከታሉ፤ ሆኖም ግን ልጆቻቸው ሕይወታቸውን አስደሳች እንዳይሆን ለማድረግ፣ ልባቸውን በሐዘን ለመሙላት በቤታቸው ውስጥ ይሰበሰባሉ እናም ሰይጣን ነፍሶችን ወደ ጥፋት በማምራት ለመማረክ የሚጠቀምበትን ቁጥር ይጨምራሉ።14 CGAmh 170.2

ታዛዥነትን እንደ መስፈርት መጠየቅ አለመቻል—አመስጋኝ የሆኑ ልጆች ተመግበው እና ለብሰው ሳይታረሙ እንዲሄዱ ሲፈቀድላቸው፣ በክፉ መንገዳቸው ለመቀጠል ድፍረት ያገኛሉ፡፡ እናም ወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲንከባከቧቸው እና መታዘዝን እንደ መስፈርት ባይጠይቁ፣ እነርሱም ክፉ ሥራዎቻቸውን ይጋራሉ፡፡ እንደነዚህ ያሉት ልጆች ልክ የአመጽ መንገድን ለመከተል እንደመረጡ እንደ ሌሎች ሰዎች፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመቆየት ሌሎችን የሚበክሉ ናቸው፡፡ በዚህ ክፉ ዘመን እያንዳንዱ ክርስቲያን ክፉን፣ ዓመፀኛ የሆኑትን የልጆች ሰይጣናዊ ድርጊቶችን በማውገዝ ጸንቶ መቆም አለበት። ክፉ ወጣቶች የሰለም አዋኪና የጓደኞቻቸው ምግባረ ብልሹነት መንስኤ እንደ ሆኑ እንጂ ደግ እና ታዛዥ ተደርጎ መታየት የለባቸውም። 324 CGAmh 171.1

ልጆች የራሳቸውን አስተሳሰብ እንዲከተሉ በመፍቀድ—በሕብረተሰቡ ውስጥ ተስፋፍቶ ያለው ተጽዕኖ ወጣቶች የየራሳቸውን የአዕምሮአቸውን ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ እንዲከተሉ መፍቀድ ነው፡፡ 325 CGAmh 171.2

እነርሱ [ወላጆች] የልጆቻቸውን ፍላጎት በማርካት እና የራሳቸውን ዝንባሌ እንዲከተሉ በመፍቀድ ፍቅራቸውን ሊያገኙ እንደሚችሉ ያስባሉ። እንዴት ያለ ስህተት ነው! በዚህ መንገድ ተሞላቅቀው ያደጉ ልጆች ምኞቶቻቸውን የመይገቱ፣ በባህሪያቸው የማይሸነፉ፣ ራስ ወዳዶች፣ አስቸጋሪዎች እና ሌሎችን በኃይል መግዛት የሚፈልጉ፣ ለራሳቸውና እና በአካባቢያቸው ላሉት ሁሉ እርግማን የሚሆኑ ናቸው፡፡17 CGAmh 171.3

የተሳሳቱ አመለካከቶች እንዲኖሩ በመፍቀድ—የልጅነት ትምህርቶች መልካምም ሆነ መጥፎ፣ በቀላሉ የሚቀሰሙ አይሆኑም። በወጣትነት ውስጥ ባህሪይ የሚገነባው ለበጎ ወይም ለክፉ ነው፡፡ ቤት ውስጥ ውዳሴ እና የሐሰት ሽንገላ ሊኖር ይችላል፣ በዓለም ውስጥ እያንዳንዱ የራሱን ዋጋ ይዞ ይቆማል። ሁሉም የቤት ባለሥልጣናት የሚረቱለት የተሞላቀቀ ሰው፣ በየዕለቱ በሀፍረት ለሌሎች የመረታት ግዴታ የተጋለጠ ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ አይነት ሁኔታ በእነዚህ ተግባራዊ የሕይወት ትምህርቶች እውነተኛ ስፍራቸውን ይማራሉ፡፡ በትችቶች፣ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች፣ እና ከበላዮቻቸው በሚደመጥ ግልጽ ቋንቋ፣ ብዙውን ጊዜ ትክክለኛውን ደረጃቸውን የሚያገኙ እና ተገቢውን ስፍራቸውን ለመረዳትና ለመቀበል ራሳቸውን የሚያዋርዱ ይሆናሉ። ነገር ግን ይህ በውስጡ ለማለፍ ከባድ እና አላስፈላጊ መከራ ሲሆን በልጅነታቸው ተገቢ ሥልጠና በማግኘት መወገድ ይችል ነበር፡፡ CGAmh 171.4

ከእነዚህ በአግባቡ ካልተገሩ አብዛኞቹ በሕይወታቸው ውስጥ ስኬትን ማግኘት በሚችሉበት ሥፍራ በመውደቅ ከዓለም ጋር በተቃራኒ ዓለማ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ስለማታሞላቅቃቸው እና ስለማትንከባከባቸው ዓለም ቂም እንደያዘችባቸው በመቁጠር ያድጉና በዓለም ላይ ቂም በመየዝ እና እምተኛ በመሆን ይበቀሏታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች የሌላቸውን ትህትና እንዲኖራቸው ያስገድዳቸዋል፤ ነገር ግን ይህ ተፈጥሮ ከለገሰቻቸው ጸጋ ጋር አይጣጣምላቸውም፣ እውነተኛ ባህሪያቸውም ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ እንደሚገለጥ የተረጋገጠ ነው፡፡ CGAmh 172.1

ከእነርሱ ጋር ከተገናኙት ጋር ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያስተምሯቸው ለምንድን ነው? 326 CGAmh 172.2

ለማኅበረሰቡ የተሰጡ እንዲሆኑ አድርገው ማሠልጠን—ልጆች ለማኅብረሰቡ የተሰጡ እንዲሆኑ ተደርገው ሊሰለጥኑ አይገባም። ለሞሎክ ሊሠዉ አይገባቸውም፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆን አለባቸው፡፡ ወላጆች በተጽዕኖአቸው ሥር ላሉት ነፍሳት መዳን እንዲሠሩ በክርስቶስ ርህራሄ መሞላት አለባቸው። አእምሯቸው በፍጹም በዓለም ፋሽኖችና እና ልማዶች እንዲመሰጡ ማድረግ የለባቸውም። ልጆቻቸው ፓርቲዎችን፣ ኮንሰርቶችን እና ጭፈራዎችን እንዲካፈሉ፣ እንዲደግሱ እና ድግስ ላይ እንዲገኙ ሊያስተምሯቸው አይገባም፣ ምክንያቱም አሕዛቦች በዚህ መንገድ ይሄዳሉ፡፡ 327 CGAmh 172.3

የራስ ወዳድነት ደስታ ፍላጎት እንዲኖር በመፍቀድ—ወጣቶች የስኬት ምንነት ትክክለኛውን አስተሳሰብ በህይወታቸው ቢጀምሩ፣ ለህብረተሰቡ በረከት እና ለእግዚአብሔር ሥራ ክብር ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ወጣቶች አሉ፡፡ ነገር ግን በምክንያታዊነት እና በመርህ ከመመራት ይልቅ ለክፉ ዝንባሌ ራሳቸውን እንዲሰጡ የሰለጠኑ እና የራስ ወዳድነት ፍላጎቶችን በመንከባከብ፣ ደስታን በዚህ አይነት መንገድ ለማግኘት በማሰብ እራሳቸውን ለማስደሰት ብቻ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን በራስ ወዳድነት ጎዳና ደስታን መሻት መከራን ስለሚያመጣ ዓላማቸውን ለማሳካት ተስኗቸዋል፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ፋይዳ ቢሶች፣ በእግዚአብሔርም ሥራ ላይ ፋይዳ ቢሶች ናቸው፡፡ በዚህ ዓለምም ሆነ በመጻኢው ዓለም ተስፋቸው እጅግ የመነመነ ነው፣ ምክንያቱም ራስ ወዳድነት በተሞላበት ደስታ ፍለጋ፣ ይህንንም ሆነ መጪውን ዓለም ያጣሉ። 328 CGAmh 172.4

ቤት ውስጥ ኃይማኖተኝነት ባለመኖሩ ሳቢያ—አባቶችና እናቶች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ዝርዝር እና ክልከላዎችን ያውቁ ዘንድ ትጉህ የቅዱሳን ጽሑፎች ተማሪዎች ናቸው ተብሎ በሚታሰብባቸው የክርስቲያን ቤቶች ተብዬዎች ውስጥ፣ የቃሉን መመሪያ በመከተል እና ልጆችን በጌታ መንገድ በማሰልጠንና በተግሳጽ በማሰደግ ረገድ ችላ ባይነት ይንጸባረቃል። ክርስቲያን ነን የሚሉ ወላጆች ቤት ውስጥ ሃይማኖተኛነትን አይለማመዱም። አባቶች እና እናቶች ርካሽ እና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በመድረስ ረክተው ሳሉ ቤት ውስጥ የክርስቶስን ባሕርይ እንዴት መወከል ይችላሉ? የሕያው እግዚአብሔር ማኅተም የሚርፈው በባህሪያቸው የክርስቶስን ምሳሌ በሚያሳዩ ላይ ብቻ ነው። 329 CGAmh 173.1

ወላጆች እግዚአብሔርን ቢታዘዙት ኖሮ—ጌታ የወላጆችን የተሳሳተ መመሪያ አያጸድቅም፡፡ በዛሬው ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆች ከአምላክ ዓላማ ውጭ ሆነው እየኖሩና እየሠሩ የጠላትን ሰራዊት ቁጥር እጅግ እያበዙ ናቸው፡፡ እነርሱ የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ያልተቀደሱ ናቸው፤ ነገር ግን ኃጢአቱ በወላጆቻቸው ደጃፍ ላይ ነው፡፡ ክርስቲያን ወላጆች ሆይ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች ወላጆቻቸው ቤትን በጥበብ ማስተዳደር ባለመቻላቸው ምክንያት በኃጢአታቸው እየጠፉ ናቸው፡፡ ወላጆች ክብሩ በደመና አምድ ለተሸፈነ፣ ለማይታየው የእስራኤል ሠራዊት መሪ ቢታዘዙ፣ አሁን በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ያለው የደስታ እጦት ባልታየ ነበር። 330 CGAmh 173.2