የልጅ አመራር
ምዕራፍ 33—ባህሪይ በመቅረጽ ሂደት የወላጅ ኃላፊነት
መለኮታዊ ተልእኮ ለወላጆች—የልጆቻቸውን ባህሪይ በመለኮታዊው ምሳሌ መሠረት ይቀርጹ ዘንድ እግዚአብሔር ለወላጆች ሥራቸውን ሰጥቷቸዋል፡፡ በእርሱ ጸጋ ሥራውን ማከናወን ይችላሉ፤ ነገር ግን ፈቃድን ለመምራት እና ስሜቶችን ለመግታት ከጽናት እና ቆራጥነት ያላነሳ ትዕግስት እና ጥንቃቄ ይጠይቃል። የተተወ እርሻ እሾህና አረምን ያበቅላል። ለጥቅም ወይም ለውበት መከርን መሰብሰብ የሚፈልግ ሰው በመጀመሪያ መሬቱን ማዘጋጀት እና ዘሩን መዝራት አለበት፣ ከዚያም የለጋዎቹን ቡቃያዎች ዙሪያ ቆፍሮ አረሙን ያስወግዳል መሬቱንም የለሰልሳል፣ እናም ብርቅዎቹ እፅዋቶች ይበለጽጉ እና ልፋቱን በጥሩ ሁኔታ ይከፍሉታል። 299 CGAmh 160.1
የባህርይ ግንባታ ለሰው ልጆች በአደራ የተሰጠ እጅግ አስፈላጊ ስራ ነው፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት የዚህ ጉዳይ ትጉህ ጥናት የዛሬውን ያህል ፍጹም አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም ነበር፡፡ ከዚህ በፊት የነበረ ትውልድ ይህን ያህል እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲጋፈጥ በጭራሽ ጥሪ ተደርጎለት አያውቅም ነበር፤ ከዚህ በፊት የነበሩ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ዛሬ እንደተጋረጣቸው አይነት ከፍተኛ አደጋ በጭራሽ ተጋፍጠው አያውቁም ነበር፡፡2 CGAmh 160.2
ወላጆች፣ የልጆቻችሁን ባህሪዎች ከእግዚአብሔር ቃል መመሪያዎች ጋር ስምሙ በሆነ መልኩ የማዳበር ስራችሁ ይኸውላችሁ፡፡ ዘላለማዊ ጥቅሞች እዚህ ውስጥ ስለ ተካተቱ ይህ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የልጆቻችሁ ባህርይ ግንባታ ከእርሻችሁ ይልቅ አስፈላጊ ነው፣ ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ይልቅ አስፈላጊ ነው ወይም ማንኛውንም ንግድ ከመምራት የበለጠ አስፈላጊ ነው፡፡ 300 CGAmh 160.3
ቤት፣ ለባህሪይ ግንባታ እጅግ ተመራጭ ሥፍራ—የቤተክርስቲያን ትምህርት ቤትም ሆነ ኮሌጅ በቤት ውስጥ ትክክለኛው መሠረት ላይ የልጆችን ባህሪይ የመገንባትን ያህል እድሎችን አይሰጥም። 301 CGAmh 161.1
ጠማማ ባህሪዎች መቃናት አለባቸው—በዚህ የምድር ሕይወት ጠማማ ባህሪይን የማያስተካክሉ ሰዎች በመጻኢ የሕያውነት ሕይወት ተካፋይነት የላቸውም፡፡ አቤት፣ የወጣቱ መቃናት ምን ያህል አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወላጆች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ልጆቻቸውን ለእግዚአብሔር የማሠልጠን የተቀደሰ ኃላፊነት በእነርሱ ላይ የተጣለ ነው፡፡ ትናንሽ ልጆቻቸው ሰማይ ቤት ለመግባት የሚያስችሏቸውን ባህሪያትን እንዲመሰርቱ የመርዳት ሥራ ለእነርሱ ተሰጥቷቸዋል፡፡5 CGAmh 161.2
ወላጆች፣ እዚህ ላይ ስህተት አትስሩ—ወላጆች፣ ለክርስቶስ ስትሉ የልጆቻችሁን ባህሪዎች ለዚህ ጊዜ እና ለዘለአለም የመቅረፅ፣ እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነ ሥራችሁ ላይ ስህተት አትስሩ፡፡ በታማኝነት መመሪያን ከመስጠት ችላ የማለት ወይም ስህተት በሚሰሩበት ጊዜ ዓይኖቻችሁ ጉድለቶቻቸውን ከማየት የሚሰውር ብልሃት የጎደለው ፍቅር እና ተገቢውን መግቻ ከመስጠት የሚከለክላችሁ ከበኩላችሁ ያለ ስህተት ጥፋታቸውን ያረጋግጣል፡፡ አካሄዳችሁ ለእያንዳንዱ መጻኢ ተግባራቸው የተሳሳተ አቅጣጫ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ምን መሆን እንዳለባቸው እና ለክርስቶስ፣ ለሰዎች እና ለራሳቸውም ነፍስ ምን መሥራት እንዳለባቸው ትወስኑላቸዋለችሁ፡፡ CGAmh 161.3
ልጆቻችሁን በሐቀኝነት እና በታማኝነት ይያዟቸው። በድፍረት እና በትዕግስት ይስሩ። የትኛውንም መስቀል አትፍሩ፣ ምንም ጊዜን እና ጉልበትን፣ ሸክም ወይም መከራን አታጥፉ፡፡ የልጆቻችሁ እጣ ፈንታ የሥራችሁን ሁኔታ ይመሰክራል፡፡ ለክርስቶስ ያላችሁ ታማኝነት ከሌላ ከማንኛውም መንገድ በተሻለ በልጆቻችሁ ሚዛናዊ ባህሪይ ሊገለፅ ይችላል፡፡ እነርሱ በገዛ ደሙ የተገዙ የክርስቶስ ንብረት ናቸው፡፡ የእነርሱ ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ በኩል ከሆነ፣ ሌሎች የሕይወትን መንገድ እንዲያገኙ የሚረዱ ከእርሱ ጋር አብሮ ሰራተኞች ይሆናሉ፡፡ አምላክ የሰጣችሁን ሥራ ችላ ብትሉ፣ ጥበብ የጎደለው አስተዳደጋችሁ ከክርስቶስ ተለይተው የጨለማ መንግስትን ከሚያጠናክሩ ክፍል ውስጥ ያደርጋቸዋል። 302 CGAmh 161.4
ንፁህ ቤት፣ ነገር ግን ልጆች ያልሰለጠኑ— ልጆቿ ጎዳና ላይ እንዲሮጡ እና የጎዳና ትምህርት እንዲቀስሙ ተለቅቀው ሳሉ፣ በጥልቀት የሚመለከቱ ዓይኖቿ በቤትዋ ውስጥ ከእንጨት ከተሰሩ ዕቃዎች ጋር የማይጣጣመውን ማንኛውንም አይነት ጉድለት ማስተዋል የምትችል እና በመደበችው ሰዓት ቤቷን በጥንቃቄ የምታጸደ እና ይህንንም ዘወትር አካልና መንፈሳዊ ጤንነትን መስዋዕት በማድረግ የምታከናውን እናት አይቻለሁ፡፡ እነዚህ ልጆች ባለጌ፣ ራስ ወዳድ ፣ ረባሽ እና የማይታዘዙ ሆነው ያድጉ ነበር፡፡ እናት ምንም እንኳን የሚረዳትን ሰው ብትቀጥርም፣ ልጆቿን በአግባቡ ለማሰልጠን ጊዜ እስኪያጥራት ድረስ የቤት ሥራዎች ላይ በጣም የተጠመደች ነበረች፡፡ እስከነ ባህሪይ እንከኖቻቸው፣ ሥርዓት አልባ እና ያልሰለጠኑ ሆነው እንዲያድጉ ትተዋቸዋለች። ነገር ግን የእናት ምርጫ በትክክለኛው አቅጣጫ ጥቅም ላይ አለመዋሉ ፣ ወይም የልጆቿን አእምሮ እና ምግባር ለመቅረጽ እና ሚዛናዊ ባህሪይ እና ተወዳጅ ጸባይ እንዲኖራቸው የማድረጉ አስፈላጊነትን ማየት ትችል እንደ ነበር ሊሰማን ይችላል፡፡ CGAmh 162.1
እናት የመጀመሪያ ትኩረት የተሰጠቻቸው ነገሮች ሁለተኛ ደረጃ እንዲኖራቸው ብታደርግ ኖሮ የልጆቿን አካላዊ፣ አእምሯዊና ግብረ-ገባዊ ሥልጠና ወሰን የሌለው ወሳኝነት እንዳለው ትቆጥር ነበር። የእናትነትን ኃላፊነት የሚወስዱ ሰዎች ልጆች ተወዳጅ ባህሪይ እና ንጹህ ግብረ-ገብ፣ የተሻለ ምርጫ እና አስደሳች ባህሪይ ይኖራቸው ዘንድ ለማስተማር በእግዚአብሄር እና በልጆቻቸው እጅግ የከበረ ግዴታ ሥር እንዳሉ ሊሰማቸው ይገባል፡፡ 303 CGAmh 162.2
በእግዚአብሔር መንፈስ ብቻ—ወደ የክብር በሮች ለመግባት ህይወታችንን እና ባህሪያችንን መቅረጽ እንደምንችል እናስባለን? እኛ አንችልም፡፡ በእኛ እና በልጆቻችን ላይ በሚሠራው በእግዚአብሔር መንፈስ ላይ ዘወትር ጥገኞች ነን፡፡304 CGAmh 162.3
ወላጆች በቤተሰቦቻቸው ውስጥ የተለያዩ ሁኔታዎችን ከተመለከቱ እራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ቀድሰው ይስጡ እና ጌታ በቤታቸው ውስጥ ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ ይፈጥራል፡፡ 305 CGAmh 163.1
የእግዚአብሔር እና የእናንተ ድርሻ—ክርስቲያን ወላጆች፣ እንድትነቁ እለምናችኋለሁ…፡፡ ጌታ እንዲሰራላችሁ በመጠበቅ ግዴታዎቻሁን ችላ ብትሉ እና ኃላፊነታችሁ ላይ ብትለግሙ ተስፋ ትቆርጣላችሁ፡፡ ማድረግ የምትችሉትን ሁሉ በታማኝነት ከፈጸማችሁ፣ ልጆቻችሁን ወደ ኢየሱስ አምጡ እና በቅንነት፣ በጽናትም ስለ እነርሱ ምልጃ አቅርቡ፡፡ ጌታ ረዳታችሁ ይሆናል፤ ከጥረቶቻችሁ ጋር ይሠራል፤ በኃይሉም ድልን ታገኛላችሁ…። CGAmh 163.2
ወላጆች እግዚአብሔር እንደሚፈልግባቸው አይነት ፍላጎትን ለልጆቻቸው በሚያሳዩበት ጊዜ ጸሎታቸውን ይሰማል፣ ከጥረታቸውም ጋር ይሠራል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ወላጆች እንዲሠሩ የተወላቸውን ሥራ ለመስራት አያቅድም፡፡ 306 CGAmh 163.3
ፈጣሪ ይረዳችኋል—እናቶች ሆይ፣ በሥራችሁ ላይ የአጽናፈ ሰማይ ፈጣሪ እንደሚረዳችሁ አስታውሱ፡፡ በእርሱ ብርታት እና በስሙ፣ ልጆቻችሁ አሸናፊዎች እንደሚሆኑ መምራት ትችላላችሁ። ብርታት ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር እንዲመለከቱ አስተምሯቸው። ጸሎታቸውን እንደሚሰማ ንገሯቸው፡፡ ክፉን በመልካም እንዲያሸንፉ አስተምሯቸው። ከፍ የሚያደርግ እና የከበረ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ አስተምሯቸው። ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንዲሆኑ ምሯቸው፣ ከዚያም ፈተና ለመቋቋም ብርታት ይኖራቸዋል፡፡ ከዚያም የአሸናፊዎችን ሽልማት ይቀበላሉ፡፡307 CGAmh 163.4
ርህሩሁ ቤዛችሁ ጸሎታችሁን ለመስማት እና በህይወት ትግባራችሁ ውስጥ የምትፈልጉትን ድጋፍ ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ ሆኖ በፍቅር እና በሀዘኔታ ይመለከታችኋል፡፡ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ገርነት፣ እምነት፣ እና ልግስና የክርስቲያን ባሕርይ አካላት ናቸው። እነዚህ ውድ ጸጋዎች የመንፈስ ፍሬዎች ናቸው፡፡ እነርሱ የክርስቲያን አክሊል እና ጋሻ ናቸው። 308 CGAmh 163.5
ለተሳሳቱ ሰዎች የማበረታቻ ቃል—ልጆቻቸውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሲያሠለጥኗቸው የነበሩ ሰዎች ተስፋ መቁረጥ አያስፈልጋቸውም፤ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው እውነተኛውን የመታዘዝ መንፈስ ይፈልጉ እና እርሱ ስር ነቀል ተሃድሶዎችን ያደርጉ ዘንድ ያስችላቸዋል፡፡ የራሳችሁን ልምዶች አዳኝ መርሆዎች ከሆኑት የእግዚአብሔር ቅዱስ ህግ ጋር ስታስማሙ ልጆቻችሁ ላይ ተጽዕኖ ታሳርፋላችሁ፡፡309 CGAmh 164.1
አንዳንድ ልጆች የወላጅ ምክርን አይቀበሉም—ወላጆች ልጆቻቸው ልባቸውን ለእግዚአብሔር ይሰጡ ዘንድ እያንዳንዱን ልዩ አጋጣሚና ትምህርት ለመስጠት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ነገር ግን ልጆቹ በብርሃን ለመጓዝ አሻፈረኝ ይሉ ይሆናል፣ እናም በክፉ አካሄዳቸው በሚወዷቸው እና ይድኑ ዘንድ በሚናፍቅ የወላጆቻቸው ልብ ላይ መጥፎ ሀሳቦችን ይጥላሉ። CGAmh 164.2
ሕፃናትን የኃጢያት እና አለመታዘዝ ጎዳና እንዲከተሉ የሚፈታተናቸው ሰይጣን ነው…፡፡ በብርሃን ለመመላለስ አሻፈረኝ ካሉ፣ ፈቃዳቸውን እና መንገዳቸውን ለእግዚአብሔር ለማስረከብ ፈቃደኛ ካልሆኑ እና ንስሃ ባለመግባት የኃጢያትን ጎዳና መከተላቸውን ከቀጠሉ፣ በፍርድ ቀን የነበሯቸው ብርሃን እና ልዩ አጋጣሚዎች ሊፈርዱባቸው ይቆማሉ፣ ምክንያቱም በብርሃን ስላልሄዱና ወዴት ይሄዱ እንደ ነበረ ስለማያውቁ ነው፡፡ ሰይጣን እየመራቸው ነው፣ በአለም ውስጥም ርዕሰ ጉዳይ ይሆናሉ። ሰዎች እንዲህ ይላሉ፣ “ለምን፣ እነዚያን ልጆች ተመልከቱአቸው! ወላጆቻቸው በጣም ሃይማኖተኞች ናቸው፣ ነገር ግን ከልጆቼ ይልቅ መጥፎዎች እንደሆኑ ትመለከታላችሁ፣ ስለዚህ እኔ ክርስቲያን ተብዬ መጠራት አልፈልግም፡፡” በዚህ መንገድ ጥሩ መመሪያን የሚያገኙ ነገር ግን የማይቀበሉ ልጆች ፈረሃ እግዚአብሔር በሌላቸው ሰዎች ፊት ወላጆቻቸውን በማሳፈር እና በማወረድ ነቀፋ ላይ ይጥሏቸዋል፡፡ በተጨማሪም እነርሱ በሚያሳዩት መጥፎ አካሄድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ላይ ነቀፋ ያመጣሉ፡፡ 310 CGAmh 164.3
ወላጆች ሆይ፣ ይህ የእናንተ ሥራ ነው—ወላጆች ሆይ፣ በልጆቻችሁ ውስጥ ትዕግሥትን፣ ጽናትንና እውነተኛ ፍቅርን ማበልጸግ የእናንተ ስራ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ልጆች በትክክል ስትይዟቸው ለንጹህ እና እጅግ ሚዛናዊ ባህሪዎች መሠረት እንዲጥሉ እየረዳችኋቸው ነው፡፡ አንድ ቀን በገዛ ቤተሰቦቻቸው ውስጥ የሚከተሏቸውን መርሆዎችን አዕምሯቸው ውስጥ እያሳደጋችሁ ነው። በጥሩ ሁኔታ የተመሩ የጥረቶቻችሁ ውጤት እነርሱ ቤተሰቦቻቸውን በጌታ መንገድ በሚመሩበት ጊዜ ይታያል፡፡15 CGAmh 165.1