የልጅ አመራር
ምዕራፍ 32—ባህሪይ እንዴት እንደሚቀረጽ
በትጋትና በማይታክት ጥረት የተገኘ—ባህርይ እንዲሁ በአጋጣሚ አይመጣም። በአንድ ጊዜ በቁጣ ስሜት መገንፈል እና በአንድ የተሳሳተ አቅጣጫ በተደረገ እርምጃ የሚወሰን አይደለም። ባህሪይ ወደ ክፉም ሆነ ወደ መልካምነት ይቀረጽ ዘንድ ምክንያት የሚሆነው የድርጊት ድግግሞሽ ነው፡፡ ትክክለኛ ባህሪይ ሊቀረጽ የሚችለው በትጋት፣ በማይታክት ጥረት፣ እያንዳንዱን በአደራ የተሰጡንን ተሰጥኦዎችን እና ችሎታዎችን ለእግዚአብሔር ክብር ይውል ዘንድ በማሻሻል ብቻ ነው። ብዙዎች ይህን ከማድረግ ይልቅ ስሜት አሊያም ሁኔታዎች ወደሚመሯቸው ቦታዎች ሁሉ ይዋልሉ ዘንድ ለራሳቸው ይፈቅዳሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት ጥሩ ቁሳዊ ነገር ስለሌላቸው አይደለም፣ ነገር ግን በወጣትነታቸው እግዚአብሔር በጣም የተሻለውን እንዲሰሩ እንደሚፈልግ ስለማያውቁ ነው፡፡289 CGAmh 155.1
ለእግዚአብሔር እና ለባልጀሮቻችን የመጀመሪያ ኃላፊነታችን ራስን በማሻሻል ውስጥ ይገኛል፡፡ የቻልነውን ያህል መልካም ስራ መስራት እንድንችል ፈጣሪ የሰጠን ችሎታዎች ሁሉ በከፍተኛ የፍጹምነት ደረጃ መዳበር አለበት። ባህሪያችንን ለማፅዳትና ለማንጻት ጉድለቶቻችንን ለማየት እና ለማስተካከል እና በባህሪያችን ውስጥ ጥሩ የሆነውን ለማሻሻል የሚያስችለን ክርስቶስ የሚሰጠን ጸጋ ያስፈልገናል፡፡2 CGAmh 155.2
አምላክ የሰጠንን ኃይሎች ማጎልመስ—እያንዳንዱ ሰው በከፍተኛ ሁኔታ የባህሪይው ስነ-ሕንጻ ምሑር ነው፡፡ በየቀኑ መዋቅሩ ወደ መጠናቀቅ ይቃረባል። ሕንፃችን በዘላለማዊ ዐለት ላይ እንደተመሰረተ ለማየት እንዴት እንደምንገነባ መጠንቀቅ እንዳለብን የእግዚአብሔር ቃል ያስጠነቅቀናል። ሥራችን ልክ ባለበት ሁኔታ የሚታይበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ለዚህም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ጠቀሜታ ባህሪይን ለመቅረጽ ሁሉም ሰው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሀይሎች ለማዳበር ጊዜው አሁን ነው፡፡ CGAmh 155.3
ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝ ማመን ለባህሪይ ጥንካሬ እና ጽናትን ይሰጣል። በክርስቶስ እውነተኛ እምነት ያላቸው የእግዚአብሔር ዐይን በእነርሱ ላይ መሆኑን፣ የሰዎች ሁሉ ፈራጅ የግብረ-ገብን ዋጋ እየመዘነ መሆኑን፣ የሰማይ ፍጡራንም ምን ዓይነት ባህሪይ እየተቀረጸ እንዳለ እየተመለከቱ መሆናቸውን በማስታወስ በአዕምሮአቸው መሻታቸውን የገዙ ይሆናሉ፡፡290 CGAmh 156.1
በእያንዳንዱ ኩነት ተጽዕኖ ያድርበታል—እያንዳንዱ የህይወት ኩነት፣ ጥቃቅን ቢሆንም እንኳን፣ ባህሪይን በመቅረጽ ረገድ የራሱ ተጽዕኖ አለው፡፡ መልካም ባሕርይ ከዓለማዊ ሐብት ይልቅ እጅግ ውድ ነው፣ እርሱንም የመቅረጽ ተግባርም ሰዎች ሊሳተፉበት ከሚሰማሩበት ተግባራት እጅግ የላቀው ነው፡፡ CGAmh 156.2
በሁኔታዎች የተፈጠሩ ባህሪያት የሚለዋወጡ እና ወጥነት የሚጎላቸው—ማለትም እጅግ የሚቀራረኑ ናቸው፡፡ ባለቤቶቻቸው በህይወት ውስጥ የላቀ ግብ ወይም ዓላማ የላቸውም፡፡ በሌሎች ሰዎች ባህሪይ ላይ ክቡር ተጽዕኖ የላቸውም፡፡ እነርሱ ዓላማ ቢስ እና ኃይል አልባ ናቸው፡፡ 291 CGAmh 156.3
የእግዚአብሔርን ምሳሌ በመከተል ፍጹም ይሆናል—እግዚአብሔር ከፊታችን በተቀመጠው ምሳሌ መሠረት ባህሪይን እንድንገነባ ዘንድ ይጠብቅብናል፡፡ ጸጋን በጸጋ ላይ በመጨመር፣ በተሰጠን መመሪያ መሠረት ደካማ ነጥቦቻችንን ፈልገን በማረም ጡቡን በጡብ ላይ ማኖር አለብን፡፡ በቤቱ ግድግዳዎች ላይ ስንጥቅ ሲታይ፣ ስለ ሕንፃው አንድ ነገር የተሳሳተ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በባህሪያችን ግንባታ ውስጥ ስንጥቆች ብዙውን ጊዜ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ጉድለቶች ካልታረሙ በቀር አደገኛ አውሎ ነፈስ ሲገፋው ቤቱ ይወድቃል። 292 CGAmh 156.4
እርሱ የማረጋገጫ ማህተሙን የሚያሳርፍባቸውን ባህሪያትን እንድንገነባ ዘንድ እግዚአብሔር ብርታትን፣ የማመዛዘን ኃይልን እና ጊዜን ይሰጠናል፡፡ በመጨረሻም በሰው እና በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበረውን ተመጣጠኝ መዋቅርን፣ ጥሩ ቤተመቅደስን፣ ይዞ መቅረብ ይችል ዘንድ የእርሱ የሆነውን እያንዳንዱን ልጅ በንጹህ፣ የተከበረ ተግባር ክቡር ባህሪይን መገንባት ይችል ዘንድ ይመኛል፡፡ CGAmh 156.5
ባህሪያችን ስንገነባ በክርስቶስ ላይ መገንባት አለብን፡፡ እርሱ አስተማማኝ መሠረት- ማለትም ፍጹም የማይነቃነቅ መሠረት ነው፡፡ የፈተና እና የመከራ ዐውሎ ነፋስ ከዘላለማዊ ዓለት ጋር የተጣበቀውን ህንፃ ሊያንቀሳቀስ አይችልም። CGAmh 157.1
ለጌታ ውብ ወደ ሆነ ህንፃ ማደግ የሚፈልግ ኃይሎቹን በሙሉ ማጎልበት አለበት፡፡ ባህሪይ ስምሙ ሆኖ ሊዳብር የሚችለው ተሰጥኦዎችን በአግባቡ ስንጠቀም ብቻ ነው። ስለዚህ በቃሉ እንደተነገረው ወርቅን፣ ብርን፣ የከበሩ ድንጋዮችን— ማለትም የእግዚአብሔርን የሚያነጸ እሳትን መቋቋም የሚችሉ ቁሶችን ወደ መሠረቱ እናመጣለን፡፡ በባህሪያችን ግንባታ ክርስቶስ ምሳሌያችን ነው፡፡ 293 CGAmh 157.2
ፈተናን መቋቋም አለብን—የዳንኤል ሕይወት የተቀደሰ ባህርይ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ መንፈሳዊ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም ለሁሉም፣ በተለይም ለወጣቶች ትምህርት ያቀርባል፡፡ የእግዚአብሔርን መስፈርቶች በጥብቅ ማክበር ለአካል እና ለአእምሮ ጤና ጠቃሚ ነው። 294 CGAmh 157.3
የዳንኤል ወላጆች ከልጅነቱ ጀምሮ ጥብቅ መሻትን የመግዛትን ልማድን አስተምረውታል፡፡ በልማዶቹ ሁሉ ከተፈጥሮ ሕግጋት ጋር መጣጣም እንዳለበት፤ ምግብና መጠጥ አካሉ፣ አእምሮው እና የተፈጥሮ ግብረ-ገቡ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረው እና ለችሎታዎቹም በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ እንደሚሆን፤ ሁሉንም እንደ እግዚአብሔር ስጦታዎች ስለሚቆጥራቸውና በምንም ዓይነት መንገድ ማቀጨጭና ማዳከም እንደሌለበት ያስተምሩት ነበር። በዚህ ትምህርት የተነሳ የእግዚአብሔር ህግ በአእምሮው ውስጥ ከፍ ተደርገው፣ በልቡም ተከብረው ነበር፡፡ ዳንኤል በተማረከበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ ክቡር ለሆነው ታላቅነት፣ ለግብዝነት እና ለአረማዊነት ራሱን እንዲያላምድ የሚያደረገው ከባድ መከራ ውስጥ እያለፈ ነበር፡፡ በእርግጥም መሻትን ለመግዛት፣ ለታታሪነት እና ለታማኝነት ሕይወት ብቁ የሚያደርገው እንግዳ ትምህርት ቤት! እናም እርሱን በከበበው የክፋት አየር ውስጥ ያለ ምግባረ-ብልሹነት ኖሯል፡፡ CGAmh 157.4
ዳንኤል እና ጓደኞቹ ገና በልጅነታቸው የትክክለኛውን ስልጠና እና ትምህርት ጥቅም አግኝተዋል፣ ነገር ግን እነዚህ አጋጣሚዎች ብቻ እነርሱ የነበራቸውን አቋም ሊያመጣላቸው አይችልም ነበር፡፡ ለራሳቸው እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ— ማለትም መጻኢ ሕይወታቸው በራሳቸው አካሄድ ላይ የሚደገፍበት ጊዜ መጣ፡፡ ከዚያም በልጅነት ለተሰጣቸው ትምህርቶች ታማኝ ለመሆን ወሰኑ፡፡ የጥበብ መጀመሪያ የሆነው እግዚአብሔርን መፍራት ለታላቅነታቸው መሠረት ነበር። መንፈሱ እያንዳንዱን እውነተኛ ዓላማ እና እያንዳንዱን የከበረ ውሳኔ አጠናከረ፡፡ 295 CGAmh 158.1
ዓላማው ከፍ ያለ መሆን አለበት—ዛሬ ወጣቶች ዳንኤል እንደ ጸና መጽናት ቢፈልጉ፣ እያንዳንዱ መንፈሳዊ ጅማት እና ጡንቻ እንዲዘረጋ ማድረግ አለባቸው፡፡ እነርሱ ጀማሪዎች ብቻ ሆነው እንዲኖሩ ጌታ አይፈልግም፡፡ በርሱ ላይ ተራምደው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይወጡ ዘንድ የመሰላሉ ጫፍ ላይ እንዲደርሱ እርሱ ይፈልጋል፡፡ 296 CGAmh 158.2
ወጣቱ የዚህን የባህሪይ ግንባታ አስፈላጊነት በአግባቡ ቢያደንቁ፣ በእግዚአብሔር ፊት የምርመራ ፈተና በሚቋቋም መልኩ ሥራቸውን የማከናወንን አስፈላጊነት ይመለከቱ ነበር፡፡ እጅግ ተራው እና ደካማው ሰው፣ ፈተናን ለመቋቋም በትጋት በመጣር እና ጥበብን ከላይ በመፈለግ፣ አሁን የማይቻል ወደ ሚመስሉ ከፍታዎች ሊደርስ ይችላል፡፡ እነዚህ ስኬቶች ጥቃቅን ኃላፊነቶችን ለመወጣት ታማኝ ለመሆን ያለ ቆራጥ ዓላማ ሊመጡ አይችሉም። ጠማማ ባህሪዎች ይበረቱ ዘንድ እንዳይተው የማያቋርጥ ክትትል ይጠይቃል። ወጣቱ የግብረ-ገብ ኃይል ሊኖረው ይችላል፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣው የእኛ ምሳሌ ለመሆን እና ለሁሉም ወጣቶች እና በሁሉም ዕድሜ ክልል ላሉት መለኮታዊ እርዳታን ለመስጠት ነው። 297 CGAmh 158.3
ምክር እና ተግሣጽ ተቀባይነት ማግኘት አለባቸው—በባህሪይ፣ በልማዶች እና በተግባር ላይ ጉድለት ያላቸው ሰዎች ምክርን እና ተግሣጽን መቀበል አለባቸው። ይህ ዓለም የእግዚአብሔር ቤተ ሙከራ ነው፣ እናም በሰማያዊው ቤተመቅደስ ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ድንጋይ ሁሉ ለጌታ ሕንጻ ገጣሚ ይሆን ዘንድ የተፈተነ እና የከበረ እስከሚሆን ድረስ የተጠረበ እና የተስተካከለ መሆን አለበት። ነገር ግን ለመሠልጠን እና ለመማር አሻፈረኝ የምንል ከሆነ፣ ልክ እንዳልተጠረቡ እና እንዳልተስተካከሉ፣ በመጨረሻም ፋይዳ ቢስ ሆኖ እንደሚጣሉ ድንጋዮች እንሆናለን፡፡298 CGAmh 158.4
በባህሪዎ ግንባታ ውስጥ እጅግ ብዙ ስራ መከናወን አለበት፣ እርስዎ ሻካራ ድንጋይ ስለሆኑ በእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ውስጥ አንድ ሥፍራ ከመያዝዎ በፊት የተጠረበና የተስተካከለ መሆን አለብዎ፡፡ እርሱ ለእርስዎ ያለውን ሥፍራ ለመሙላት እስከሚዘጋጁ ድረስ እግዚአብሄር የባህሪዎን ሹል ጫፎች በመዶሻ እና በመሮ ቢያስወግድ አይግረሞት፡፡ ይህንን ሥራ ማከናወን የሚችል ማንም ሰብአዊ ሰው የለም፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው በእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እናም አንድ የማይጠቅምን ምት እንደማይማታ እርግጠኛ ይሁኑ፡፡ ምቶቹ በሙሉ ለዘለአለማዊ ደስታዎ የሚሆኑ የፍቅር ምት ናቸው። ድክመቶችዎን ያውቃል፣ እናም ለመጠገን እንጂ ለማፍረስ አይሰራም፡፡12 CGAmh 159.1