የልጅ አመራር

15/85

ክፍል 5—ሌሎች መሠረታዊ ትምህርቶች

ምዕራፍ 13—ራስን መቆጣጠር

ልጆችን ለኑሮና ለኃላፊነቶቹ ማዘጋጀት— እናት እንድትንከባከብ የተሰጧትን ልጆች ስትመለከት፣ እነርሱን የማስተማር ታላቁ ዓለማና ግብ ምንድነው? ስትል በጭንቀት ልትጠይቅ ትችላለች፡፡ እነርሱን ለኑሮና ለኃላፊነቶቹ ብቁ ማድረግ፣ በዓለም ውስጥ ለተከበረ ደረጃ ብቁ እንዲሆኑ፣ መልካም ያደርጉ ዘንድ፣ ባልንጀሮቻቸውን ይጠቅሙ ዘንድ፣ በመጨረሻም የጻድቃንን ሽልማት ለማግኘት ነውን? ይህ ከሆነ፣ ሊማሩ የሚገባቸው የመጀመሪያው ትምህርት ራስን መቆጣጠር ነው፤ ምክንያቱም ማንም ያልተገራ፣ አንገተ-ደንዳና ሰው ስኬትን በዚህ ዓለም ላይ ወይም ሽልማትን በሚቀጥለው ተስፋ ሊያደርግ አይችልም፡፡ 141 CGAmh 85.1

ልጅን እንዲረታ ያሰልጥኑት—ትናንሽ ልጆች፣ አንድ አመት ሳይሆናቸው በፊት፣ ስለ እነርሱ የሚወራውን ይሰማሉ፣ ይረዳሉም፣ በምን ያህል መጠን እንደሚሞላቀቁም ያውቃሉ፡፡ እናቶች፣ ልጆቻችሁ ለመሻቶቻችሁ ይረቱ ዘንድ ማሰልጠን አለባችሁ፡፡ ልጆቻችሁን የምትቆጣጠሩ እና እንደ እናት ክብራችሁን የምትጠብቁ ከሆነ ይህ ጉዳይ መገኘት አለበት፡፡ እናንት ከልጆቻችሁ የምትጠብቁትን ነገር ልጆቻችሁ ወዲያው ያውቃሉ፣ ፍቃዳቸው የእናንተን ፈቃድ የሚያሸንፍበትንም ጊዜ ያውቃሉ፣ እጅግ ድልም ያደርጋሉ፡፡ 142 CGAmh 85.2

ሕግን በልጅ እጅ አሳልፎ መስጠትና እንዲመራ በመተው፣ የተሳሳቱ ልማዶች እንዲያድጉ መፍቀድ እጅግ ከባድ ጫካኔ ነው፡፡ 143 CGAmh 85.3

የራስ ወዳድነት ምኞቶች አይርኩ—ወላጆች ጠንቃቆች ካልሆኑ፣ የትናንሽ ልጆቻቸውን ፍላጎት ለማርካት ሲሉ የራሳቸውን እንዲተው እስኪያደርግ ድረስ ትኩረት እንዲፈልጉና አጋጣሚን እንዲያገኙ በሚመራቸው አይነት መንገድ ይይዟቸዋል፡፡ ልጆች ወላጆች አንድ ነገር እንዲያደርጉላቸው፣ ምኞታቸውን እንዲያረኩላቸው ጥሪ ያቀርቡላቸዋል፣ ወላጆችም ይህን ማድረጋቸው ራስ ወዳድነትን በልጆቻው ውስጥ ቢያሰርጽም እንኳ የምኞታቸውን ይሰጧቸዋል፡፡ ነገር ግን ወላጆች ይህን በማድረጋቸው ልጆቻቸው ላይ ስህተት መፈጸማቸው ነው፣ ከዚያም በኋላ በልጁ ሕይወት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተማሯቸውን ተጽዕኖዎችን ለመቀልበስ እንዴት ከባድ እንደሆነ ይመለከታሉ፡፡ ልጆች ገና በለጋነታቸው ከራስ ወዳድነት የመነጩ ምኞቶችን ማርካት እንደሌለባቸው መማር አለባቸው፡፡ 144 CGAmh 85.4

ልጆች የሚያለቅሱበት ምንም ነገር አይሰጣቸው—እናት አሁንም አሁንም መደጋገማ ማድረግ ያለባት አንድ የከበረ ትምህርት ቢኖር ልጅ አዛዥ አለመሆኑን ነው፤ እርሱ ገዥ አይደለም፣ ነገር ግን የእርሷ ፈቃድና የእርሷ ምኞት የበላይ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ራስን መቆጣጠርን ታስተምራቸዋለች፡፡ ሩህሩህ ልባችሁ ይህን ለማድረግ እጅግ ቢመኝም እንኳ፣ የሚያለቅሱበት አንዳችም ነገር እንዳይሰጣቸው፣ ምክንያቱም አንድ ጊዜ በማልቀስ ድል ካገኙ ይህ እንዲደገም ይጠብቃሉ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ጦርነቱ ይበልጥ ከባድ ይሆናል፡፡ 145 CGAmh 86.1

የቁጣ ስሜት እንዲንጸባረቅ ፍጹም አይፍቀዱ—ከእናት የመጀመሪያ ተግባራት ውስጥ አንዱ የጨቅላ ልጇን ሰሜት መገደብ ነው፡፡ ልጆች ቁጣን እንዲያንጸባርቁ ሊፈቀድላቸው አይገባም፤ አንድ ለጥቅማቸው የማይሆን ነገር ስለተከለከሉ፣ ወለል ላይ ራሳቸውን እንዲጥሉ፣ እንዲጋጩና እንዲያለቅሱ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው የቁጣን ስሜት እንዲያንጸባርቁ ሲያሞላቅቋቸው እያየሁ እጨነቅ ነበር፡፡ እናቶች ይህን በቁጣ መገንፈልን መታገስ ያለባቸው እና በልጁም ባህሪይ ላይ ግድየለሽ መሆን ያለባቸው ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን ክፋት አንድ ጊዜ ፈቃድ ካገኘ፣ ይደገማል፣ ድግግሞሹም ባህሪይ ይሆናል፣ ስለዚህም የልጁ ባህሪይ ክፉ ቅርጽ ይይዛል፡፡ 146 CGAmh 86.2

ክፉ መንፈስ መቼ መገሰጽ እንዳለበት—አብዘኛውን ጊዜ ትናንሽ ልጆች ፍላጎታቸው በማናቸውም መንገድ ጣልቃ ከተገባባቸው ራሳቸውን ሲጥሉና ሲያቅሱ አያለሁ፡፡ ጠላት የልጆቻችንን አዕምሮ ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋል፣ ነገር ግን በራሱ ፈቃድ እንዲቀርጻቸው እንፈቅድለታለን? እነዚህ ትናንሽ ልጆች የትኛው መንፈስ ተፅዕኖ እያደረገባቸው እንደሆነ መለየት አይችሉም፣ ስለዚህ በእነርሱ ፈንታ በአስተዋይነትና በነጻነት ውሳኔ የመስጠት ኃይልን መለማመድ የወላጆች ኃላፊነት ነው፡፡ ልማዳቸው በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ክፉ ዝንባሌዎች መገታት አለባቸው፣ አዕምሮም ብርሃንን በመደገፍ መነቃቃት አለበት፡፡ ልጁ በማናቸውም ጥረት ራሱን እንዲገዛ መበረታታት አለበት፡፡ 147 CGAmh 87.1

“በቤተልሔም መዝሙሮች” ይጀምሩ —እናቶች በእቅፎቻቸው ያሉ ሕጻናትን ትክክለኛውን መርኾዎች እና ልማዶችን ማስተማር አለባቸው፡፡ ራሶቻቸውን ከወላል ጋር እንዲያጋጩ ሊፈቅዱላቸው አይገባም፡፡… እናቶች ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ያስተምሯቸው፡፡ ከቤተልሔም መዝሙር ይጀምሩ፡፡ ይህ ለስላሳ ዜማ የፀጥታ የማስፈን ተጽዕኖ አለው፡፡ በእነዚህ ለስለስ ያሉ ዜማዎች ስለ ክርስቶስና ስለ ፍቅሩ ይዘምሩላቸው፡፡ 8 CGAmh 87.2

ማወላወል ወይም ውሳኔ አለመስጠት አያስፈልግም—የልጁ ጠማማ ስሜት በተቻለ ፍጥነት መገደብ አለበት፤ ይህ ተግባር በዘገየ ቁጥር ለመፈጸም ይበልጥ አዳጋች ይሆናል፡፡ ፈጣንና በቀላሉ የሚነካ ባህሪይ ያላቸው ልጆች የቤተሰብ የተለየ ጥንቃቄ ያሻቸዋል፡፡ እነርሱ በተለየ ሁኔታ ነገር ግን በጽናት መያዝ አለባቸው፤ በወላጆች በኩል በእነርሱ ጉዳይ ማወላወል ወይም ውሳኔ አለመስጠት አያስፈልግም፡፡ ልዩ ስህተቶቻቸውን መቆጣጠር የሚችሉበትን የተፈጥሮ ባህሪያት በጥንቃቄ መንከባከብና ማጎልበት ተገቢ ነው፡፡ በቀላሉ የሚነካ እና ጠማማ ባህርይን ማሞላቀቅ ልጁን የመጥፋት ውጤት ይኖረዋል፡፡ ስህተቶቹ ከዕድሜው ጋር እየበረቱ፣ የአዕምሮውን ዕድገት እየገታ፣ እና መልካምና የተከበረ የባህሪይውን ሚዛን እየጣለ ይመጣል፡፡ 148 CGAmh 87.3

የወላጆች ራስን የመቆጣጠር ምሳሌ በጣም አስፈላጊ ነው—አንዳንድ ወላጆች ራሳቸውን መቆጣጠር አይችሉም፡፡ የራሳቸውን ክፉ የምግብ ፍላጎቶች ወይም በቀላሉ የሚነካ ስሜታቸውን መቆጣጠር አይችሉም፤ ስለዚህ ልጆቻቸውን የምግብ ፍላጎትን ስለ መካድ እና ራስን ስለመቆጣጠር ማስተማር አይችሉም፡፡ 149 CGAmh 88.1

ወላጆች ልጆቻቸውን ራስን መቆጣጠርን ማስተማርን የሚመኙ ከሆነ፣ እነርሱ መጀመሪያ የዚያ ባህሪይ ቅርጽ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የወላጆች ጥላቻና ስህተት ፈላጊነት ባህሪይ በልጆች ውስጥ ችኩልነትን፣ በቀላሉ የሚነካ ስሜትን ያበረታታል፡፡ 150 CGAmh 88.2

ለመልካም ሥራ አይታክቱ—ወላጆች በቤታቸው ይሰሩ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሥራ እንዳይሰሩ ለምቾትና ለደስታ ከፍተኛ ፍቅር አላቸው፡፡ ወጣቶች ቤት ውስጥ በአግባቡ የሰለጠኑ ቢሆን ኖሮ፣ በዚህ ጊዜ ወጣቶች ላይ የሚታየውን አስደንጋጭ ክፋት ባላየን ነበር፡፡ ወላጆች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሥራ መሥራት ቢጀምሩ እና ልጆቻቸውን ራስን መግዛትን፣ ራስን መካድን፣ ራስን መቆጣጠርን በመህርህ እና በምሳሌ ቢያስተምሯቸው፣ የእግዚአብሔርን ማረጋገጫ ለማግኘት ሲሉ፣ ኃላፊነታቸውን በሚፈልጉበት ጊዜ በክርስቶስ ትምህርት ቤት ውስጥ የከበረ ትምህርት ያገኙ ነበር፡፡ ትዕግስትን፣ ይቅር ባይነትን፣ ፍቅርን እና የዋህነትን ይማሩ ነበር፤ እነዚህም ልጆቻቸውን ማስተማር ያለባቸው ዋና ዋና ትምህርቶች ናቸው፡፡ CGAmh 88.3

የወላጆች የግብረ-ገብ ኃይል ከተነቃቃ በኋላ፣ ችላ የተባለውን ተግባራቸውን በታደሰ ኃይል ሲጀምሩ፣ በዚህ ሥራ ላይ ተስፋ መቁረጥ ወይም ራሳቸውን ለመስተጓጎል መፍቀድ የለባቸውም፡፡ እጅግ አያሌ ሰዎች መልካምን ለማድረግ ይታክታሉ፡፡ ያልተጠበቁ አስቸኳይ ነገሮችን ለመግጠም ከባድ ጥረት፣ ዘላቂ ራስን መቆጣጠርን፣ እና የተትረፈረፈ ጸጋ እና ዕውቀትን እንደሚጠይቅ ሲያውቁ፣ ተስፋ ይቆርጡና ትግሉን ያቆማሉ፣ የነፍሳት ጠላትም በራሱ ጎዳና እንዲቀጥል ይተውታል፡፡ ከቀን ወደ ቀን፣ ከወር ወደ ወር፣ ከዓመት ወደ ዓመት፣ የልጅዎ ባህሪይ እስኪቀረጽ ድረስ እና ልማዱ በትክክለኛው መንገድ እስኪጸና ድረስ፣ ሥራው መቀጠል አለበት፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ቤተሰብዎ በልልነት፣ ባልተገራ አቅጣጫ እንዲቀጥል መተው የለብዎትም፡፡ 151 CGAmh 88.4

ራስዎን መቆጣጠርን በጭራሽ አይተው—በጭራሸ ራሳችንን መቆጣጠርን መተው የለብንም፡፡ ሁልጊዜ ፍጹም ምሳሌነትን እንጠብቅ፡፡ ትዕግስት በማጣት እና በብስጭት መናገር ወይም መናደድ— ባንናገርም እንኳ፣ ኃጢአት ነው፡፡ በትክክል ክርስቶስን በመወከል ጠቃሚ በመሆን መጓዝ አለብን፡፡ የቁጣ ንግግር ልክ ባልጩትን እንደሚገጭ ባልጩት ነው፡ በአንድ ጊዜም የቁጣ ስሜትን ያቀጣጥላል፡፡ CGAmh 89.1

በጭራሽ እንደ ለውዝ ጨጎጊት አይሁኑ፡፡ ቤት ውስጥ ሻካራ፣ እና በሚሰቀጥጥ ድምጽ የተነገረ ቃል መጠቀምን ለራስዎ አይፍቀዱ፡፡ ሰማያዊ እንግዶችን ቤትዎ መጋበዝ አለብዎ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ እርሱና የሰማይ መልዓክት ከእናነት ጋር እንዲቆዩ ማድረግ አለብዎ፡፡ የሕይወትን ብርሃን በዙሪያዎ ላሉት ለማሳየት የክርስቶስን ጽድቅ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅድስና፣ የቅድስናን ውበት መቀበል አለብዎ፡፡ 13 CGAmh 89.2

“ትዕግስተኛ ሰው” ይላል ጠቢቡ ሰው፣ “ከኃያል ሰው ይሻላል፤ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማን ከሚወስድ ሰው ይሻላል፡፡” ስሜታቸውን ላለመግዛት ሲፈተኑ የአዕምሮን ሚዛን የሚጠብቁ ወንዶችና ሴቶች የጦር ሠራዊትን ለጦር እና ድል ለመንሳት ከሚመራ የጦር መሪ ይልቅ በእግዚአብሔር እና በሰማይ መልዓክት ፊት ከፍ ተደርገው ይታያሉ፡፡ አንድ የተከበረ ንጉሰ ነገስት በአልጋው ላይ በሞት አፋፍ ሳለ አንዲህ ሲል ተናገረ፣ “ድል ካደረግኋቸው መካከል አንድ አሁን መጽናናትን የሚሰጠኝ ነገር አለ፣ እርሱም አስቸጋሪ ስሜቴ ላይ ያገኘሁት ድል ነው፡፡” አሌክሰንደር እና ቄሳር ራሳቸውን ድል ከመንሳት ይልቅ ዓለምን ድል መንሳት ቀሏቸው አግኝተዋል፡፡ ከአንዱ አገር ሌላውን አገር ድል ከነሱ በኋላ — አንዳቸው “መሻትን ያለመግዛት፣ ሌለኛው ለምኞት እብደት ሰለባ” በመሆን ወድቀዋል፡፡ 152 CGAmh 89.3