የልጅ አመራር

16/85

ምዕራፍ 14—ፀጥታ እና አክብሮት

ተገቢ ያልሆነ ጫጫታ እና ሁከትን መግታት—አንዲትም እናት አዕምሮዋ በብዙ ነገሮች እንዲጨናነቅ መፍቀድ የለባትም...፡፡ ፈቃድ ቢያገኙ ልምድ ከሌለው እና ከአላዋቂ ልቦቻቸው የሚመነጨውን እያንዳንዱን ስሜት የሚከተሉትን ትናንሽ ልጆቿን በታላቅ ትጋት እና በቅርብ ንቁነት መንከባከብ አለባት። በደስታ በተሞላ መንፈሳቸው ቤት ውስጥ ከፍተኛ ጫጫታ እና ሁከት ይፈጥራሉ፡፡ ይህ መከልከል አለበት። ልጆች እነዚህን ነገሮች ላለማድረግ የተማሩ ከሆነ ደስተኞች ይሆናሉ ፡፡ ጎብኚዎች በሚመጡበት ጊዜ ፀጥተኛ እና አክባሪ መሆን እንዳለባቸው መማር አለባቸው፡፡ 153 CGAmh 91.1

በቤት ውስጥ ፀጥታ ይንገስ —አባቶች እና እናቶች ፣… ልጆችዎ ለህግ እንደሚገዙ ያስተምሯቸው፡፡ ልጆች ስለሆኑ በቤቱ ውስጥ እንደ ምኞታቸው ረብሽ የመፍጠር መብት አለን ብለው እንዲያስቡ አይፈቅዱላቸው ፡፡ የቤት ውስጥ ውበት እንዳይጠፋ ጥበብ የተሞላቸው ህጎች እና መመሪያዎች መውጣት እና ተግባራዊ መሆን አለባቸው። 154 CGAmh 91.2

ወላጆች ልጆቻቸው እንዲጮኹና እንዲያለቅሱ በመፍቀዳቸው ትልቅ ስህተት ይሰራሉ፡፡ ግድየለሾችና ሁካተኞች እንዲሆን ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ እነዚህ የማያስደስቱ ባህሪያት በልጅነታቸው እድሜ ቁጥጥር ሥር ካልዋሉ በስተቀር፣ በኃይማኖት እና በሥራ ሕይወት ውስጥ በርትተውና አድገው ልጆች ከራሳቸው ጋር ይወስዱታ፡፡ ልጆች ቤት ውስጥ ጸጥ እንዲሉ ሲማሩ ደስተኞች ይሆናሉ፡፡ 155 CGAmh 91.3

ልምድ ያላቸውን ሰዎች ውሳኔ አክብሮት እንዲሰጡ አስተምሯቸው—ልጆች ልምድ ያላቸውን ሰዎች ውሳኔዎችን ማክበር እንደሚገባቸው መማር አለባቸው፡፡ አስተሳሰባቸው ከቤተሰቦቻቸው እና ከመምህራኖቻቸው አስተሳሰቦች ጋር ይስማማ ዘንድ መማር እና የእነርሱን ምክሮች የመጠበቅን ትክክለኛነት እንዲመለከቱ መመሪያ ማግኘት አለባቸው፡፡ ከዚያም ይመራቸው ከነበረ እጅ ተለይተው ሲሄዱ ባህሪያቸው በንፋስ እንደሚናወጥ ሸምበቆ አይሆንም፡፡ 156 CGAmh 91.4

የወላጅ ግድየለሽነት አክብሮት ማጣትን ያበረታታል—ልጆች በራሳቸው ቤት ውስጥ አክብሮት የማይሰጡ፣ የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ እና ነጭናጫ ከሆኑ፣ የእነርሱ ኃጢአት በወላጆቻቸው በር ላይ ትሆናለች፡፡ 157 CGAmh 92.1

እናት… በእናትነት ክብር ቤተሰቧን በጥበብ መምራት አለባት፡፡ በቤት ውስጥ ያላት ተጽዕኖ የላቀ፤ ቃሏም ሕግ መሆን አለበት፡፡ እርስዋ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ያለች ክርስቲያን ከሆነች፣ ልጆቿ ለሰዎች አክብሮት እንዲኖራቸው ማድረግ ትችላለች፡፡ ከልጆችዎ በእርግጥ ምን እንደምትፈልጉ ይንገሯቸው፡፡ 158 CGAmh 92.2

ወላጆች ሥልጣናቸውን ሳይጠብቁ ሲቀሩ፣ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ፣ ለመምህራን ወይም ለርዕሰ-መምህሩ ተገቢ የሆነ አክብሮት አይኖራቸውም፡፡ ሊኖራቸው የሚገባውን አክብሮት ቤት ውስጥ አልተማሩም፡፡ አባትና እናት ከልጆች ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ነበሩ፡፡ 159 CGAmh 92.3

ያልተገራ የነውረኛነት ውጤት—ለልጆቻችሁ አክብሮትን አሳዩአቸው፣ አንድም አክብሮት የጎደለውን ቃል እንዲናገሯችሁ አትፍቀዱ፡፡ 160 CGAmh 92.4

ጥበበኛ የወጣትነት አመለካከት—ጥበበኛና የተባረከ ወጣት የሚባለው ያ ወላጆች ካሉት እነርሱን መመልከትን ተግባሩ የሚያደርግ፣ ከሌሉት አሳዳጊውን ወይም ከእርሱ ጋር የሚኖሩትን እንደ አማካሪ፣ እንደ አጽናኝ እና በአንዳንድ ሁኔታዎችም እንደ የበላዮቹ የሚመለከታቸው እና በቤቱ ውስጥ ያሉ ክልከላዎችን በመታዘዝ ለመኖር የሚፈቅድ ወጣት ነው፡፡ 161 CGAmh 92.5

አክብሮት በከፍተኛ ጥንቃቄ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል [ማሳሰቢያ: ይህ ርዕስ ሙሉ በሙሉ እንዴት እንደቀረበ ለመመልከት፣ ምዕራፍ 80፣ “ቅዱስ ለሆነ ነገር ሊሰጠው የሚገባ አክብሮት” የሚለውን ይመልከቱ] — አክብሮት በከፍተኛ ጥንቃቄ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ነው፡፡ እያንዳንዱ ልጅ ለእግዚአብሔር እውነተኛ አክብሮትን ማሳየት እንዳለበት መማር አለበት፡፡ 162 CGAmh 93.1

ልጆቻችንን ከዓለም፣ ከቤተ ክርስቲያን እና ከቤተሰብ ጋር በትክክለኛው የግንኙነት ደረጃ ላይ ልናስቀምጣቸው እንደሚገባ እንድንገነዘብ እግዚአብሔር ይመኛል፡፡ ከቤተሰብ ጋር ሊኖራቸው የሚገባ ግንኙነት ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት የመጀመሪያው ነጥብ ነው፡፡ ለእርስ ባርሳቸው ትሁታን እና ለእግዚአብሔርም ትሁት እንዲሆኑ እናስተምራቸው፡፡ “ለእግዚአብሔር ትሁት መሆን አለባቸው ስትይ ምን ማለትሽ ነው? ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ፡፡” ለሰማዩ አባታችን አክብሮት መስጠትን እና በእኛ ፈንታ ክርስቶስ ያደረገልንን ታላቁና ቁጥር ስፍር ያሌላውን መስዋዕትነትን ማድነቅን መማር አለባቸው ማለቴ ነው…፡፡ ወላጆች እና ልጆች የሰማይ መልአክት ከእነርሱ ጋር ይገናኙ ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ጥብቅ ግንኙነት መጠበቅ አለባቸው፡፡ እነዚህ መልዕክተኞች ኃጢአት እና ለእግዚአብሔር ትሁት ያለመሆን በበዛበት አያሌ ቤቶች ውስጥ አይገቡም፡፡ ከቃሉ የሰማይን መንፈስ በመውሰድ እዚህ ታች ወደ ሕይወታችን እናምጣው፡፡ 163 CGAmh 93.2

አክብሮትን እንዴት ማስተማር እንዳለብን— ወላጆች ቅዱስ ገጾች ላይ ባሉ የተለያዩ ዕውቀቶች ልጆቻቸውን መማረክ ይችላሉ፣ ይህን ማድረግም አለባቸው፡፡ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእግዚአብሔር ቃል መማረክ ከፈለጉ ግን፣ ራሳቸውም በእርሱ መማረክ ይገባቸዋል፡፡ እግዚአብሔር እስራኤልን ሲያዝ “ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድ ስትሄድ፣ ስትተኛም ስትነሳም አጫውቱአቸው፡፡” (ዘዳግም 11፡19) ሲል ስለ ቃሉ እንደተናገረው ከአስተምህሮው ጋር የተላመዱ መሆን አለባቸው፡፡ ልጆቻቸው እግዚአብሔርን እንዲወዱትና እንዲያከብሩት የሚመኙ በቃሉና በፍጥረት ሥራዎቹ እንደተገለጠው ስለ መልካምነቱ፣ ስለ ግርማው እና ስለ ኃይሉ መናገር አለባቸው፡፡ 164 CGAmh 93.3

አክብሮት በታዛዥነት ይገለጣል—እውነተኛ አክብሮት በታዛዥነት እንደሚገለጥ ልጆች ይመልከቱ፡፡ እግዚአብሔር አላስፈለጊ የሆነውን ምንም ነገር አላዘዘም፣ እንዲሁም እርሱ ለተናገራቸው ቃላት ታዛዥነትን እንደ ማሳየት እርሱን እጅግ የሚያስደስት አክብሮት የሚገለጥበት ሌላ መንገድ የለም፡፡ 165 CGAmh 94.1