ታላቁ ተጋድሎ

9/45

ምዕራፍ ፮—ኸስ እና ጀሮም

በቦኸሚያ ወንጌሉ የተተከለው ቀደም ብሎ በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገደማ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉሞ፣ ሕዝባዊ አምልኮ በቋንቋቸው ይደረግ ነበር። የጳጳሱ ኃይል እየበረታ ሲሄድ ግን በዚያው ልክ የእግዚአብሔር ቃል እየተሰወረ ሔደ። “የነገሥታትን ክብር ማዋረድ” ሥራዬ ብሎ የተያያዘው ግሪጎሪ 7ኛ ሰዎችን በባርነት ስር ለማድረግ ወደ ኋላ የሚል አልነበረም፤ በመሆኑም በቦኸሚያውያን ቋንቋ ሕዝባዊ አምልኮን የሚከለክል አዋጅ እንዲወጣ አደረገ። “በማይታወቅ ቋንቋ አምልኮ መካሄዱ እግዚአብሔርን አስደስቶታል፣ ስለሆነም ይህን ደንብ ቸል ማለት ለብዙ ክፋቶችና ኑፋቄዎች መነሳት ምክንያት ሆኖአል” በማለት ሊቀ-ጳጳሱ አወጀ።-Wylie, b. 3, ch. 1። ሕዝቡን ጨለማ ውጦት እንዲቀር፣ የእግዚአብሔር ቃል ብርሐን እንዲዳፈን ሮም ደነገገች። ቤተ ክርስቲያን ተጠብቃ እንድትቆይ ግን እግዚአብሔር ሌሎች ልዑኮችን አዘጋጅቶ ነበር። ቀድሞ ይኖሩበት ከነበረው ከፈረንሳይና ኢጣሊያ አገር ተሰደው ወደ ቦኸሚያ የመጡ ብዙ ዋልደንሶችና አልቢጀንሶች ነበሩ። በግላጭ ማስተማር ባይደፍሩም በድብቅ ግን የማያቋርጥ ጥረት ያደርጉ ነበር። በዚህም እውነተኛው እምነት ተጠብቆ ከምዕተ ዓመት ወደ ምዕተ ዓመት ይተላለፍ ነበር። GCAmh 74.1

ከኸስ ዘመን በፊት በቤተክርቲያንዋ የነበረውን ብልሹነትና የሰዎችን ያለቅጥ አባካኝነት በግልጽ የተቃወሙ ሰዎች በቦኸሚያ ተነስተው ነበር። ጥረታቸው መጠነ ሰፊ ፍላጎትን አስነሳ። የስልጣን ተዋረዱ ፍርሃት ስላደረበት የወንጌሉን ደቀ-መዛሙርት በመቃወም ማሳደድ እንዲጀመርባቸው ተደረገ። ተባረው በዋሻዎችና በተራራዎች መሃል እንዲያመልኩ ከተገደዱ በኋላ ብዙዎች በወታደሮች እየታደኑ ተገድለዋል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ከሮማዊያን አምልኮ ያፈነገጡ ሁሉ በእሳት እንዲቃጠሉ አዋጅ ወጣ። ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው ቢሰጡም የዓላማቸውን ድል መንሳት ግን በተስፋ ወደፊት ይመለከቱ ነበር። “ድነት የሚገኘው በተሰቀለው አዳኝ በማመን ብቻ” እንደሆነ ያስተማረ ከእነዚህ መካከል አንድ ሰው ሲሞት እንዲህ ተናገረ፣ “የእውነት ጠላቶች ቁጣ አሁን አሸንፎናል፤ ለዘላለም ግን አይሆንም፤ ሰይፍ ወይም ስልጣን ሳይኖረው ከዚህ ተራ ሕዝብ መሃል አንድ ሰው ይነሳል፤ ተቃዋሚዎቹም ያሸንፉት ዘንድ ከቶ አይቻላቸውም” አለ።-Ibid., b. 3, ch. 1። የሉተር ዘመን ገና ሩቅ ነበር። ሮምን በመቃወም ምስክርነቱ አሕዛብን የሚያናውጥ ሰው ግን እየተነሳ ነበር። GCAmh 74.2

ጆን ኸስ ትውልዱ ከድሃ ቤተሰብ ነበር፤ ገና በህፃንነቱ አባቱ በመሞቱ ጉዲፈቻ ሆነ። በጣም ሐይማኖተኛዋ እናቱ ትምህርትንና እግዚአብሔርን መፍራት ከሐብት ሁሉ አስበልጣ ዋጋ በመስጠት እነዚህን ቅርሶች ወደ ልጅዋ ለማስተላለፍ ተግታ ሰራች። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በክፍለ ሐገራዊው ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ በፕራግ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በእርዳታ እንዲማር ፈቅዶለት በዚያ ተመዘገበ። ወደ ፕራግ ባደረገው ጉዞ እናቱ አብራው ነበረች። ባሏ የሞተባት፣ ደሃ ሴት በመሆንዋ ለልጅዋ የምታበረክትለት ዓለማዊ ስጦታ አልነበራትም። ሆኖም ወደ ታላቋ ከተማ እየተቃረቡ ሲሔዱ አባት በሌለው ወጣት ጎን ተንበርክካ የሰማይ አባታቸው ይባርከው ዘንድ ተማፀነች። ያቺ እናት ፀሎትዋ በእንዴት አይነት ሁኔታ እንደሚመለስ ያስተዋለችው ነገር አልነበረም። GCAmh 74.3

በዩኒቨርሲቲው ብዙም ሳይቆይ በማያባራ ልፋቱና ፈጣን እድገቱ ምክንያት ኸስ ታዋቂነትን እያተረፈ መጣ። ኩነኔ የሌለበት ሕይወቱና ትሁትና አሸናፊ ፀባዩ በሁሉም ስፍራ አክብሮትን አተረፈለት። የሮማዊቷ ቤተ ክርስቲያን ጥብቅ ልባዊ ተከታይ ነበር፤ ቤተ ክርስቲያንዋ እንደምትሰጥ የምትመሰክረውን መንፈሳዊ በረከትም በመሻት በእውነት የሚተጋ ነበር። በአንድ የኢዮቤልዩ በዓል ቀን ኃጢአቱን ለመናዘዝ ሄደ። ከተራገፈው ሳንዱቁ የቀሩትን የመጨረሻዎቹን ጥቂት ሳንቲሞች ከከፈለ በኋላ ቃል ከተገባው የኃጢአት ስርየት ተካፋይ ይሆን ዘንድ ሰልፉን ተቀላቀለ። የኮሌጅ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ቅስናውን ጀመረ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም እውቅናን በማትረፍ ወዲያው በንጉሡ መቀመጫ፣ በቤተመንግሥት ውስጥ መሥራት ጀመረ። በተማረበት ዩኒቨርሲቲም እንደ ፕሮፌሰር፣ በኋላም ሃላፊ ሆኖ አገለገለ። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያ ተራ የእርዳታ ተማሪ የነበረ ሰው የሃገሩ ኩራት ሆነ፤ ስሙም በመላው አውሮፓ ገናና ሆነ። GCAmh 75.1

ኸስ የተሐድሶውን ሥራ የጀመረው ግን በሌላ መስክ ነበረ። የቅስናን ትምህርት ለብዙ ዓመታት ከወሰደ በኋላ የቤተልሔም ፀሎት ቤት ሰባኪ እንዲሆን ተደረገ። የዚህ ፀሎት ቤት መሥራች፣ መጽሐፍ ቅዱሳት በሕዝቡ ቋንቋ ይሰበኩ ዘንድ ድጋፍ የሚያደርግ፣ አስፈላጊነቱም እጅግ እንደሆነ የሚናገር ነበር። ይህንን ድርጊት ሮም አጥብቃ የምትቃወም ቢሆንም በቦኸሚያ ሙሉ ለሙሉ አልተቋረጠም ነበር። ነገር ግን ታላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ድንቁርና ነበር፤ በሁሉም የሕብረተሰብ መደቦችም እጅግ አሰቃቂ ርኩሰቶች ይፈፀሙ ነበር። ኸስም ለነገ ሳይል እነዚህን ክፋቶች አወገዘ፤ በተደጋጋሚ የሚናገራቸው የእውነትና የንጽህና መርሆዎች በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ተግባራዊ እንዲሆኑ ተማፀነ። GCAmh 75.2

ወደ በኋላ ከኸስ ጋር ቅርብ ግንኙነት የመሰረተው የፕራግ ነዋሪ የነበረው ጀሮም ከእንግሊዝ ሲመለስ የዋይክሊፍን ጽሁፎች ይዞ ተመለሰ። በዋይክሊፍ ትምህርቶች ምክንያት የተለወጠችው የእንግሊዝ ንግስት የቦኸሚያ ልዕልት ስለነበረች የተሐድሶ አራማጁ ሥራዎች በርሷ ተፅዕኖ ለትውልድ ሃገርዋ በስፋት ተሰራጭተው ነበር። እነዚህን ሥራዎች ኸስ በትኩረት አነበበ፤ የፃፋቸው ሰው ልባዊ ክርስቲያን እንደሆነ አምኖ በመቀበል [ዋይክሊፍ] ሲያራምዳቸው የነበሩትን ተሐድሶዎች በአዎንታ ወደ መቀበል አጋደለ። በዚያን ጊዜ ባያስተውለውም ኸስ ከሮም አርቆ የሚወስደውን ጎዳና ተያይዞት ነበር። GCAmh 75.3

በዚህ ጊዜ ገደማ፣ ብርሃኑን ቀደምታ የተቀበሉ፣ ሁለት እንግዳ ምሁራን፣ በዚህ ሩቅ አገር አስተምህሮውን ያስፋፉ ዘንድ ከእንግሊዝ ሐገር ወደ ፕራግ መጡ። ከጅምሩ በሊቀ-ጳጳሱ የበላይነት ላይ ያነጣጠረ ግልጽ ጥቃት በመሰንዘራቸው ብዙም ሳይቆዩ በሹማምንቱ ዝም እንዲሉ ቢደረጉም፣ የመጡበትን ዓላማ ለመተው ፈቃደኛ አልነበሩምና ወደ ሌሎች አማራጮች ፊታቸውን አዞሩ። የጥበብ ሰዎችም (አርቲስቶችም)፣ ሰባኪዎችም በመሆናቸው ስልታቸውን መጠቀም ጀመሩ። ለሕዝብ ክፍት በሆነ ስፍራ ሁለት ስዕሎችን ሳሉ። በአንደኛው ስዕል ላይ በጉዞ ብዛት የተቦጫጨቀ ልብስ የለበሱ፣ በባዶ እግራቸው የሚራመዱ ደቀ መዛሙርት የሚከተሉት “የዋህ ሆኖ በአህያ ላይ…ተቀምጦ” [ማቴ 21÷5] የነበረው የሱስ ወደ የሩሳሌም ሲገባ ይታይ ነበር። በአንፃሩ ሁለተኛው ስዕል ደግሞ ሊቀ-ጳጳሱ በውድ መጎናፀፊያው አሸብርቆ፣ ሶስትዮሽ ዘውድ ደፍቶ፣ በጳጳሳዊ አጀብ ተከቦ፣ እፁብ ድንቅ በሚባል ሁኔታ በተሸለመው ፈረሱ ላይ ሆኖ በሚያንፀባርቅ ውበት ያጌጡትን ቀሳውስትና የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናትን አስከትሎ፣ መለከት ነፊዎችን ከፊቱ አሰልፎ የሚያሳይ ነበር። GCAmh 75.4

የሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት የሳበ ስብከት በዚህ ሥፍራ ነበር። ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ ስዕሎቹን ይመለከት ነበር። ፍሬ ነገሩን ማንም ይስተው ዘንድ አልተቻለውም። በጌታው በክርስቶስ የዋህነትና ትህትና እና የጌታ ባሪያ ነኝ ብሎ በሚመሰክረው በሊቀ-ጳጳሱ ኩራትና እብሪት መካከል ያለው ልዩነት ብዙዎችን ያስገርም ጀመር። ታላቅ ሕዝባዊ ብጥብጥ በፕራግ ተነሳ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ለደህንነታቸው ሲሉ መልቀቃቸው አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንግዶቹ ከዚያ ስፍራ ሄዱ። ያስተማሩት ትምህርት ግን የሚረሳ አልነበረም። ስዕሎቹ በኸስ አእምሮ ላይ ጥልቅ አግራሞትን የጫሩ ነበሩና መፅሐፍ ቅዱስንና የዋይክሊፍን ፅሁፎች በበለጠ እንዲመረምር ተመራ። በዋይክሊፍ የተነገሩትን ሁሉንም የተሐድሶ ትምህርቶች ለመቀበል ገና ዝግጁ ያልነበረ ቢሆንም ትክክለኛው የሊቀ-ጳጳሱ ባህርይ የበለጠ ጥርት ብሎ ታየው፤ በበለጠ ቁጭትም የስልጣን ተዋረዱን ኩራት፤ ማሳካት የሚሻውን ጥልቅ ፍላጎትና ብልሹነት አወገዘ። GCAmh 76.1

በፕራግ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ብጥብጥ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጀርመን ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ስለተገደዱ በእነርሱ አማካኝነት ብርሐኑ ከቦኸሚያ ወደ ጀርመን አገርም ገባ። ብዙዎቹ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቁት በኸስ አማካኝነት ነበር። ወደ አባት አገራቸው ሲመለሱም ወንጌሉን በተኑት። GCAmh 76.2

በፕራግ የተሰራው ሥራ ወሬ ወደ ሮም ደረሰ፤ ሳይቆይም በሊቀ-ጳጳሱ ፊት ይቀርብ ዘንድ ለኸስ መጥሪያ ደረሰው። ትዕዛዙን ማክበር ማለት ለእርግጥ ሞት ራሱን ማጋለጥ ነበር። የቦኸሚያ ንጉሥና ንግስት፣ ዩኒቨርሲቲው፣ የልዑላን አባላትና የመንግሥት ሹማምንት በአንድ ላይ በመተባበር ኸስ በፕራግ መቅረት እንዲፈቀድለት፣ በሮም የሚሰጠው መልስ በምክትሉ አማካኝነት እንዲሆን የሚጠይቅ ደብዳቤ ለሊቀ-ጳጳሱ ፃፉ። ሊቀ-ጳጳሱም ይህንን ጥያቄያቸውን በአዎንታ በመመለስ ፈንታ ኸስን ወደ መዳኘትና ወደ መኮነን በማምራት የፕራግን ከተማም በእግድ ስር አደረጋት። GCAmh 76.3

በዚያ ዘመን እንዲህ አይነቱ ፍርድ ሲወሰን መጠነ ሰፊ ድንጋጤ ይፈጥር ነበር። ይህንን የፍርድ ሂደት የሚያጅቡት ሥነ ሥርዓቶች፣ ሊቀ-ጳጳሱን፣ ራሱ እግዚአብሔርን የሚወክል አድርጎ በሚያየው፣ የሰማይንና የሲኦልን ቁልፍ የያዘ፤ ጊዜያዊም (ምድራዊም) ሆነ መንፈሳዊ (ዘላለማዊ) ፍርድ መስጠት ይችላል ብሎ በሚያምነው ሕዝብ ላይ ፍርሃት እንዲነዙ ተደርገው የተዘጋጁ ነበሩ። እግድ ለተጣለበት የአገር ክፍል የሰማይ በሮች እንደሚዘጉበት፤ ሊቀ-ጳጳሱ ባሻው ጊዜ ማዕቀቡ እስኪነሳ ድረስ በዚያ አካባቢ የሚሞቱ ሰዎች ከተድላና ደስታ መኖሪያቸው [ከገነት] ተከልክለው እንደሚቆዩ ይታመን ነበር። የዚህ አሰቃቂ ጥፋት ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ሁሉም የሐይማኖቱ ስነ-ስርዓቶች ይቋረጡ ነበር፤ አብያተ ክርስቲያናት ይዘጉ ነበር፤ ጋብቻዎችም የሚፈፀሙት በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ነበር። የሞቱት ሰዎች የተቀደሰ መቀበሪያ መሬት ተከልክለው፣ የሚገባቸው የቀብር ፍትሃት ሳይደረግላቸው፣ በመስክ ወይም በጉድጓድ ውስጥ ይቀበሩ ነበር። እንዲህም የሰዎችን ምናብ የሚስቡ እርምጃዎችን በመውሰድ ሮም የሰዎችን ንቃተ-ህሊና ለመቆጣጠር ጥረት ታደርግ ነበር። GCAmh 76.4

የፕራግ ከተማ በረብሻ ተናወጠች። ብዙ የህብረተሰቡ ክፍል ለሚወርድባቸው መቅሰፍት ተጠያቂው ኸስ እንደሆነ አድርገው በማውገዝ ለሮም የበቀል እርምጃ ተላልፎ እንዲሰጥ ጠየቁ። የተነሳውን ማዕበል ፀጥ ለማሰኘት የተሐድሶ አራማጁ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ተወለደበት ጎጥ ፈቀቅ አለ። በፕራግ ለተለያቸው ጓደኞቹ የጻፈው ደብዳቤ፦ “ከመካከላችሁ ፈቀቅ ያልኩት የክርስቶስን ፈለግ በመከተል ነው፤ ክፉ የሚያስቡ በራሳቸው ላይ ዘላለማዊ ኩነኔ እንዳያመጡ እድሉን ለማጥበብ፣ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ደግሞ የስደትና የመከራቸው ምክንያት ላለመሆን ነው። በተጨማሪም እግዚአብሔርን የማይፈሩ ቀሳውስት ረዘም ላለ ጊዜ የጌታ ቃል እንዳይሰበክ ሊከለክሉ ይችላሉ የሚለው ፍራቻዬም ከእናንተ እንድርቅ አድርጎኛል። መለኮታዊ እውነትን እክድ ዘንድ አይደለም እናንተን የተውኳችሁ፤ በእግዚአብሔር እርዳታ ለእውነቱ ለመሰዋት ፈቃደኛ ነኝ” የሚል ነበር።-Bonnechose, The Reformers Before the Reformation, vol.1, ገጽ 87። ኸስ ሥራውን አላቆመም፤ በየገጠሩ እየተዘዋወረ በተመስጦ ለሚያዳምጠው ጉባኤ ይሰብክ ነበር። በመሆኑም ወንጌሉን ለመገደብ ሊቀ-ጳጳሱ የፈፀመው ድርጊት እንዲያውም የበለጠ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆነ፤ “ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና።” [2ኛ ቆሮ 13÷8]። GCAmh 77.1

‘’በዚህ የሕይወቱ ክፍል የኸስ አእምሮ የሚያሳምም የግጭት ትዕይንት ቀጠና ይመስል ነበር። ቤተ ክርስቲያንዋ አስደንጋጭ በሚባሉ ክስተቶች ልታዳክመው ብትሞክርም ከዚህ በፊት የእርስዋን ስልጣን በግልጽ ተቃውሞ አያውቅም ነበር። ለእርሱ እስካሁን ድረስ የሮም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሚስት፣ ሊቀ-ጳጳሱ ደግሞ የእግዚአብሔር ተወካይና ቄስ ገበዝ (vicar) ነበር። ኸስ ሲዋጋ የነበረው የስልጣንን አላግባብ መጠቀም እንጂ የእምነቱን መሰረታዊ መርሆዎች አልነበረም። ይህ ደግሞ በህሊናው መጠይቅና በገባው መጠን ባገኘው እምነት መካከል መሪር ግጭት አስነሳበት። እርሱ እንደሚያምነው፣ ስርዓቱ ትክክልና ስህተት መሥራት የማይቻለው ከሆነ፣ አልታዘዝም ይል ዘንድ ውስጡ የሚያስገድደው ታዲያ ለምንድን ነው? እርስዋን መታዘዝ ኃጢአት እንደሆነ ተረዳ፤ ግን ስህተት መሥራት ለማይቻላት ቤተ ክርስቲያን መታዘዝ ለምን ወደ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሊያመራ ቻለ? መፍትሔ ሊያገኝለት የማይችለው ችግር ሆነበት። በየሰዓቱ እየተመላለሰ የሚያሰቃየው ጥርጣሬ ይህ ነበር። አጠጋግቶም ቢሆን ሊደርስበት የቻለው መፍትሔ፦ በክርስቶስ ዘመን እንደ ነበረው የቤተ ክርስቲያንዋ ካህናት እርጉም ከመሆናቸው የተነሳ ህጋዊ የሆነውን ስልጣናቸውን ህገ-ወጥ ለሆነ ተግባር ያውሉት እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ያ እየተደገመ እንደሆነ ያሰበበት ሁኔታ ነበር። ይህም ህሊናን መግዛት ያለባቸው የተስተዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ናቸው የሚለውን አባባል ለራሱ ምሪትም ሆነ ለሰዎች ለማስተማር ጥቅም ላይ እንዲያውለው መራው፤ በሌላ አባባል፣ ብቸኛው ስህተት የሌለበቱ መሪ፣ በመፅሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚናገረው እግዚአብሔር እንጂ በቀሳውስቱ አማካኝነት የምትናገረው ቤተ ክርስቲያን አይደለችም ማለት ነው።”-Wylie, b. 3, ch. 2። GCAmh 77.2

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በፕራግ የተነሳው አለመረጋጋት ቀዝቀዝ ሲል ኸስ ወደ ቤተልሔም ፀሎት ቤት ተመልሶ በበለጠ ቅንዓትና ጀግንነት የእግዚአብሔርን ቃል መስበክ ተያያዘው። ጠላቶቹ ንቁና ብርቱ ቢሆኑም ንግስቲቱና በርካታ ልዑላን ጓደኞቹ ነበሩ። ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብም ከእርሱ ጋር ወግኖ ቆመ። በንጽህና ከፍ ከፍ የሚያደርጉትን ትምህርቶቹንና የተቀደሰ ሕይወቱን፣ ከሚያቆረቁዘው የሮማውያኑ አስተምህሮ፣ ከሚያራምዱትም ንፉግነትና ወራዳነት ጋር በማነጻጸር በኸስ ጎን መቆማቸውን ብዙዎች እንደክብር ይቆጥሩት ነበር። GCAmh 77.3

እስከዚህ ጊዜ ድረስ ኸስ ብቻውን ይለፋ ነበር፤ አሁን ግን በእንግሊዝ በነበረበት ጊዜ የዋይክሊፍን ትምህርት የተቀበለው ጀሮም የተሐድሶ ሥራውን ተቀላቀለ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ሁለቱ በሕይወታቸው የተቆራኙ ሆኑ፤ በሞታቸውም የሚለያዩ አልነበሩም። GCAmh 78.1

ተወዳጅነትን የሚያተርፉ ባህርያት ማለትም አንፀባራቂ ተሰጥኦ፣ አንደበተ ርዕቱነትና እውቀት፤ ቁንጮ ሆኖ ዲግሪውን የጨረሰው የጀሮም ጥሪቶች ነበሩ። ሆኖም እውነተኛ የባህርይ ጥንካሬን ባካተቱ ክህሎቶች ግን ኸስ የላቀ ነበር። የተረጋጋ የማመዛዘን ችሎታው ግንፍል የሚል መንፈስ የነበረው የጀሮም መግቻ ሆኖ ያገለግል ነበረ፤ ጀሮም ከልብ በመነጨ ትህትና ለኸስ ተገቢውን ዋጋ በመስጠት ምክሩን በአዎንታ ይቀበል ነበር። በተቀናጀው ጥረታቸው ተሐድሶው በተሻለ ፍጥነት መስፋፋት ጀመረ። GCAmh 78.2

የሮምን አብዛኛዎቹን ስህተቶች በመግለጥ በእነዚህ በተመረጡ ሰዎች ላይ ታላቅ የብርሐን ጮራ እንዲያንፀባርቅ የአምላክ ፈቃድ ሆነ። ለዓለም ሊሰጥ ያለውን ሁሉንም ብርሐን ግን አልተቀበሉም ነበር። በእነዚህ አገልጋዮቹ አማካኝነት እግዚአብሔር ሕዝቡን ከሮማዊነት ጨለማ እያወጣ ነበረ። ነገር ግን መጠነ ሰፊና ታላላቅ መሰናክሎችን ማለፍ ነበረባቸው፤ እናም መሸከም በሚችሉት መጠን፣ ደረጃ በደረጃ እግዚአብሔር መራቸው። ሁሉንም ብርሐን በአንድ ጊዜ ይቀበሉ ዘንድ የተዘጋጁ አልነበሩም። በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች የቀትር የፀሐይ ብርሐን በሙላት ወገግ ቢል እንደሚሆኑት ሁሉ፣ [ሙሉው እውነት] ቢቀርብላቸው ኖሮ ፊታቸውን እንዲዞሩ ያደርጋቸው ነበር። ስለዚህ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን በሚያገኝበት መጠን፣ እግዚአብሔር ለመሪዎቹ ጥቂት በጥቂት፣ ይገልጽላቸው ነበር። ሕዝቡን ወደ በለጠና ጥልቅ ተሐድሶ የሚመሩ፣ በየክፍለ ዘመኑ ወደፊት የሚነሱ ታማኝ አገልጋዮች ፈለጉን ተከትለው ይነሱ ዘንድ ነበራቸው። GCAmh 78.3

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረው የምዕመናን ክፍፍል አሁንም ቀጠለ። ሶስት ሊቀ-ጳጳሳት የበላይነትን ለመቆናጠጥ ሲፋለሙ፣ ፀባቸው የክርስቲያኑን ዓለም በወንጀልና በሽብር ውስጥ ከተተው። የስድብ ውርጅብኝ ማዥጎድጎዳቸው አልበቃ ብሎአቸው ወደ ዘመናዊ መሳሪያዎች ፊታቸውን በማዞር እያንዳንዳቸው የጦር መሳሪያ መግዛትና ወታደሮች ማሰባሰብ ጀመሩ። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ገንዘብ ማስፈለጉ አጠያያቂ አልነበረም፤ በመሆኑም ስጦታዎች፣ ቢሮዎችና የቤተ ክርስቲያንዋ ንብረቶች በሙሉ ለሽያጭ ቀረቡ። ቀሳውስቱም የበላይ አለቆቻቸው የሚያደርጉትን በመከተል የራሳቸውን ስልጣን አደራጅተው ተቀናቃኞቻቸውን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ በአብያተ ክርስቲያናት ቢሮዎች መካከል ንግድ የማካሄድ፣ ስርየትን በገንዘብ የመሸጥና ጦርነት የማወጅ ተግባር ላይ ተሰማሩ። የኃይማኖት ሽፋን በመሰጠታቸው ምክንያት እንዳልተፈጸሙ የሚታለፉትን ርኩሰቶች፣ በየቀኑ እየጨመረ በሚሄድ ድፍረት ኸስ ጮክ ባለ ድምጽ ያወግዛቸው ጀመር። ሕዝቡም ክርስትናን አደጋ ላይ የጣሉት ሰቆቃዎች መንስኤዎች የሮማውያኑ መሪዎች እንደሆኑ አድርገው በግልጽ ከሰሷቸው። GCAmh 78.4

አሁንም እንደገና የፕራግ ከተማ ወደ ደም አፋሳሽ ብጥብጥ ልትገባ ጠርዝ ላይ የደረሰች መሰለች። እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ “እሥራኤልን የምትገለባብጥ” [1ኛ ነገስት 18÷17] አንተ ነህ ተብሎ የእግዚአብሔር አገልጋይ ውንጀላ ቀረበበት። ከተማዋ እንደገና ታገደች፤ ኸስም ወደተወለደበት መንደሩ ሄደ። በተወደደችው ቤተልሔም የፀሎት ቤቱ በታማኝነት ይነገር የነበረው ምስክርነት ወደ ፍፃሜ መጣ። ለእውነት ምስክር ትሆን ዘንድ ነፍሱን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት በሰፊ መድረክ ላይ ለመላው ክርስትና የሚናገርበት ጊዜ ደረሰ። GCAmh 79.1

አውሮፓን ያምታታውን ርኩሰት ለመፈወስ ጠቅላላ ስብሰባ በኮንስታንስ ተጠራ። ስብሰባው የተጠራው በንጉሥ ሲጅስመንድና ከሶስቱ ተቃናቃኝ ሊቀ-ጳጳሳት በአንዱ በዮሐንስ 23ኛ ጠያቂነት ነበር። በእርግጥ ይህ የስብሰባ ጥሪ ሊቀ-ጳጳስ ዮሐንስ የሚፈልገው አልነበረም፤ ምክንያቱም ባህርይውና የአቋም መመሪያው ብልሹ ከመሆናቸው የተነሳ፣ በዚያን ዘመን የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ግብረ-ገብነት እጅግ የላሸቀ ደረጃ በመድረሱ በራሱ የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት ቢገመገም እንኳ በእግሩ መቆም እንደማይችል ያውቅ ስለነበረ ነው። የንጉሥ ሲጅስመንድን ትዕዛዝ ይቃወም ዘንድ ግን አልቻለም። GCAmh 79.2

ስብሰባው ማከናወን ያለበት ዋና ግቦች፣ በቤተ ክርስቲያን ያለውን የመከፋፈል መንፈስ መፈወስና ኑፋቄን ከስሩ መመንገል ነበር። ሁለቱ የሊቀ-ጳጳሱ ተቃዋሚዎችና የአዲሱ አመለካከት ዋና መሪና አስፋፊ ጆን ኸስ በተሰብሳቢዎቹ ፊት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተላለፈ። ሁለቱ የጳጳሱ ተቀናቃኞች ለደህንነታቸው በመስጋት በአካል ሳይመጡ በልዑካኖቻቸው አማካኝነት ተወክለው ቀረቡ። ሊቀ-ጳጳስ ዮሐንስ የስብሰባው አቀናባሪ እንደሆነ መስሎ ቢቀርብም የመጣው ግን ብዙ ጥርጣሬ በውስጡ ይዞ ነበር። ዘውዱ ለደረሰበት ውርደት፣ እንዲሁም ጳጳስነትን ለመቆናጠጥ ሲል ለፈፀማቸው ወንጀሎች ተጠያቂ በማድረግ ከስልጣኔ ሊያወርደኝ ንጉሡ በሚስጥር አስቧል በማለት ፈርቶ ነበር። ያም ሆኖ ወደ ኮንስታንስ ከተማ የገባው በታላቅ አጀብ ተከቦ፣ ከከፍተኛ የኃይማኖት መሪዎች ጋር የቤተመንግሥት ነዋሪዎችን አስከትሎ ነበር። የከተማዋ የኃይማኖት አለቆች፣ ባለስልጣናትና እጅግ ብዙ የከተማዋ ሕዝብ የእንኳን ደህና መጣህ አቀባበል አደረጉለት። በአራት አጥቢያ ዳኞች የተያዘ የወርቅ ጥላ በላዩ ላይ ነበረ። አጀቡ በፊቱ ይተም ነበር፤ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና የልዑላን ያሸበረቁ አልባሳት የበለጠ ድምቀት ሰጥተውት ነበር። GCAmh 79.3

በዚህን ጊዜ ሌላ መንገደኛ ወደ ኮንስታንስ እየተቃረበ ነበር። ኸስ የተጋረጠበትን አደጋ በውል ያውቅ ነበር። ሁለተኛ እንደማይገናኙ አድርጎ ጓደኞቹን ተሰናብቶ የጀመረው ጉዞ ወደ መቃጠያ ስፍራው የሚመራው እንደሆነ እያሰበ ጉዞውን ተያያዘው። ከቦኸሚያው ንጉሥ የሰላም መንገድ ማረጋገጫ (የይለፍ)፣ ከዚያም በጉዞው ላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ከሲጅስመንድ ለደህንነቱ ማረጋገጫ ቢሰጠውም ዝግጅት ያደረገው ግን እሞታለው በሚል እሳቤ ነበር። GCAmh 79.4

በፕራግ ለሚገኙት ጓደኞቹ በተፃፈ ደብዳቤ እንዲህ አለ፦ “የደህንነት ማረጋገጫ ከንጉሡ ተሰጥቶኝ፣ ገዳይ የሆኑ በርካታ ጠላቶችን ለመገናኘት መሄዴ ነው…. በመድሃኒቴ በኃያሉ እግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ እተማመናለሁ። እቋቋማቸው ዘንድ፣ ሚዛናዊነትን የተላበሰ ጥንቃቄና ጥበብን በአፌ ይሞላ ዘንድ፣ ፈተናን፣ ወህኒን፣ አስፈላጊም ከሆነ አሰቃቂ ሞትን በድፍረት እገናኝ ዘንድ እንዲቻለኝ፤ በእርሱ እውነት ብርታት ይሆንልኝ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ይለግሰኝ ዘንድ እግዚአብሔር ፅኑ ፀሎታችሁን እንደሚሰማ አምናለሁ። የሱስ ክርስቶስ ለሚወዳቸው ሲል መከራን ተቀበለ፤ እርሱ ምሳሌ ስለተወልን እኛ ለራሳችን ድነት ስንል ሁሉንም ነገር በፅናትና በትዕግስት ማለፋችን የሚያስደንቅ ነገር ነውን? እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ እኛ ደግሞ የርሱ የእጅ ሥራዎች፤ እርሱ ጌታ ነው እኛም ባሪያዎቹ፤ እርሱ የዓለም ገዢ ነው፣ እኛ ደግሞ የተናቅን ጠፊዎች ነን። እርሱ ግን ተሰቃዬ! ታዲያ የኛ መሰቃየት በተለይም ለመንጻታችን ከሆነልን ለምን እንሰቃይ ዘንድ አይገባንም? ስለዚህ የተወደዳችሁ ሆይ የእኔ መሞት ለክብሩ የሚሆን አንዳች ነገር ካለው በቶሎ እንዲፈጸም፤ በላዬ የሚወርዱትን መከራዎቼን ያለመንገዳገድ (አቋሜ ሳይናወጥ) መሸከም እችል ዘንድ እርሱ እንዲያስችለኝ ፀልዩልኝ። ወደ እናንተ ተመልሼ መምጣቴ የተሻለ ከሆነም ወንድሞቼ ቢከተሉት ነቀፋ የሌለው ምሳሌ ትቼ ማለፍ ይቻለኝ ዘንድ፤ አንድስ እንኳ የወንጌሉን የእውነት ቃል ሳልሸፍን ያለ እድፍ መመለስ እንድችል ወደ እግዚአብሔር እንፀልይ። ስለዚህ ምናልባት የእኔን ፊት በፕራግ እንደገና ፈጽሞ አታዩት ይሆናል። የማይገባኝን ክብር ሰጥቶ ሃያሉ አምላክ ወደ እናንተ ይመልሰኝ ዘንድ ፈቃዱ ከሆነ ግን በሕጉ እውቀትና ፍቅር በፀናች ልብ ወደ ፊት እንገሰግስ ዘንድ ይገባናል።”-Bonnechose, vol. 1, ገጽ 147, 148። GCAmh 79.5

የወንጌሉ ደቀ መዝሙር ይሆን ዘንድ ወደተለወጠ ወደ አንድ ካህን ኸስ በፃፈው ደብዳቤ፣ ውድና ያማረ ልብስ በመልበሱ ይሰማው የነበረውን ደስታ እየኮነነ፣ በእርባና ቢስ ሞያ ሰዓታትን ሲያባክን የነበረበትን ተግባራት እያወገዘ፣ [ኸስ ራሱ ድሮ የሰራውን] በጥልቅ ትህትና ስለራሱ ስህተቶች ሲናገር ይስተዋላል። ከዚያም እነዚህን ልብን የሚነኩ ተግሳፆች አከለበት፦ “የሀብት ንብረትና የቤተ ክርስቲያን ስልጣን ማካበት ሳይሆን የነፍሳት መዳንና የእግዚአብሔር ክብር አእምሮህን ይሙላው። ከነፍስህ ይልቅ ቤትህን እንዳታስጌጥ ተጠንቀቅ፤ ከሁሉም በላይ መሻትህን ለመንፈሳዊ ህንፃ አውለው። ለድሆች ትሁትና የተሰጠህ ሁን፤ በመብልም ውልህን አትሳት፤ ሕይወትህን ማስተካከል አቅቶህ ከመጠን በላይ መፈለግን መተው ካልቻልክ እኔ እንደሆንኩት ሁሉ በእጅጉ ትዋረዳለህ….ከህፃንነትህ ጀምረህ ትምህርቴን እየተቀበልክ ስላደግህ አስተምህሮዬን ታውቃለህ፤ ስለዚህ ለአንተ ተጨማሪ መፃፍ ጥቅም የለውም። ስወድቅ በተመለከትከኝ ግብዝነት ግን እንዳትመስለኝ በጌታችን ምሕረት እለምንሃለሁ”፤ በደብዳቤው ሽፋን ላይ ይህንን ጨመረበት፦ “ወዳጄ ሆይ እንደሞትኩ እርግጠኛ ከመሆንህ በፊት ይህንን እትም [ደብዳቤ] እንዳትከፍተው እማፀንሃለሁ።”-Ibid., vol. 1, ገጽ 147, 148። GCAmh 80.1

ኸስ በጉዞው ላይ በሄደበት ሁሉ አስተምህሮው እንደተስፋፋ የሚጠቁሙ ምልክቶችን አስተዋለ። አላማውም በመልካም ተቀባይነትን እንዳገኘ ተመለከተ። ሕዝቡ ሊገናኘው ወደርሱ ይጥለቀለቅ ነበር። በአንዳንድ ከተሞችም የአጥቢያ ዳኞች በመንገዶቻቸው ሆነው ይገናኙት ነበር። GCAmh 80.2

ኮንስታንስ ሲደርስ ለኸስ ሙሉ ነፃነት ተሰጠው። ከንጉሠ ነገሥቱ የጉዞ የደህንነት ማረጋገጫ በተጨማሪ የጥበቃ ማረጋገጫ ከራሱ ከሊቀ-ጳጳሱ ተሰጠው። ሆኖም እነዚህ ጠንካራና ተደጋጋሚ አዋጆች ተጥሰው በሊቀ-ጳጳሱና በአበይት የኃይማኖት መሪዎች ትዕዛዝ ተይዞ አስከፊ ወደ ሆነ የምድር እስር ቤት ተወረወረ። GCAmh 80.3

ለኸስ የሰጠውን ቃል በመስበር የፈጸመው ሸፍጥ ለራሱም ምንም ሳይጠቅመው፣ ሊቀ-ጳጳሱም ወዲያው ወደዚያው እስር ቤት ተጣለ። Ibid., vol, ገጽ 247። ከነፍስ ማጥፋት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመነገድ እና ከምንዝር በተጨማሪ እጅግ የረከሱ፣ “በስም ይጠሩ ዘንድ እጅግ የሚቀፉ” ወንጀሎችን ፈጽሞ መገኘቱ በጉባኤው ፊት ተረጋገጠበት። በመጨረሻም ጉባኤው ራሱ ወስኖበት ዘውዱ ከራሱ ላይ ተነስቶ ወደ እስር ቤት ገባ። ተቃዋሚ ሊቀ-ጳጳሳቱም ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ተደርገው በምትካቸው አዲስ ሊቀ-ጳጳስ ተመረጠ። GCAmh 80.4

ሊቀ-ጰጳሱ የሰራው ወንጀል ኸስ በቀሳውስቱ ላይ ከሰነዘረው፣ ተሐድሶም እንዲያደርጉ ከጠየቀበት ክስ ፈፅሞ የላቀ ቢሆንም፣ ጳጳሱን ከስልጣን ያወረደው ያው ራሱ ጉባኤ የተሐድሶ አራማጁን ይጨፈልቅ ዘንድ እርምጃ ወሰደ። የኸስ እስር ቤት መግባት በቦኸሚያ ታላቅ ቁጣን ቀሰቀሰ። ይህንን የጭካኔ ድርጊት ኃያላን ልዑላን በጉባኤው ፊት ተቃወሙ፤ ንጉሠ ነገሥቱም ለኸስ የሰጠው የይለፍ ፈቃድ እንዲጣስ ባለመፈለጉ በተሐድሶ አራማጁ ላይ የተሰጠውን ውሳኔ ተቃወመው። ነገር ግን የተሐድሶ አራማጁ ጠላቶች እጅግ አደገኛና የማያወላውሉ ነበሩ። ንጉሠ ነገሥቱ ተገቢነት የሌለው ጥላቻው እንዲያንሰራራ በመኮትኮት፣ ፍርሃቱን በመጠቀምና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያለውን ቀናኢነት በመጥቀስ ያግባቡት ጀመር። “ከመናፍቅ ጋር እምነቱን አንድ ያለማድረግ ሙሉ ነፃነት ያለው” መሆኑን በማውሳት መጠነ ሰፊ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ የጉባኤው ስልጣን ከንጉሠ ነገሥቱ በላይ ስለሆነ “ከገባው ቃል [ኸስ ነፃ እንዲሆን ንጉሡ ከሰጠው የይለፍ ቃል] ነፃ ሊያደርገው እንደሚችል” ተናገሩ - Jacques Lenfant, History of the Council of Constance, vol. 1, ገጽ 516፤ በዚህም አሸናፊነትን ተቀዳጁ። GCAmh 81.1

በህመምና በእስር ተዳክሞ፣ በእስር ቤቱ ካለው ርጥበት አዘል መጥፎ አየር የተነሳ የያዘው ትኩሳት ለሞት ሊያበቃው ደርሶ፣ በመጨረሻ ኸስ በጉባኤው ፊት ቀረበ። በሰንሰለት ተጠፍሮ፣ ስልጣኑና የእምነት ቃሉ ከአደጋ ይጠብቀው ዘንድ ቃል ገብቶ በነበረው ንጉሠ ነገሥት ፊት ቆመ። በረጅም ጊዜ የፍርድ ሂደት ቆይታው ንቅንቅ ሳይል እውነትን ጠበቀ፤ በተሰበሰቡት የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ባለስልጣናት ፊት የስልጣን መዋቅሩ የሚፈጽመውን ብልሹነት በፍጹም ሃቀኝነት ተቃወመ። አስተምህሮውን ይክድ እንደሆን፣ ያለዚያ ሞት እንደሚጠብቀው ተነግሮት፣ እንዲመርጥ ሲጠየቅ የሰማዕትነትን ዕጣ ፈንታ መረጠ። GCAmh 81.2

የእግዚአብሔር ፀጋ አጽንቶ አቆመው። ከመጨረሻው ቅጣቱ በፊት ባሳለፋቸው የስቃይ ሳምንታት ሰማያዊ ሰላም ነፍሱን ሞልቶት ነበር። “ይህንን ደብዳቤ”፣ አለ ለአንድ ጓደኛው ሲጽፍ፣ “የምጽፈው እጄ በሰንሰለት ታስሮ የሞት ፍርድ ነገ እንደሚፈፀምብኝ በመጠባበቅ ነው….ወደፊት በሚመጣው በአስደሳቹና ሰላማዊው ሕይወት፣ በክርስቶስ እርዳታ እንደገና ስንገናኝ በፈተናዎቼና በመከራዬ ውስጥ እግዚአብሔር እንዴት እንደረዳኝ፣ ጌታ እንዴት ራሱን በምሕረት እንደገለፀልኝ ያኔ ይገባሃል።” ብሎ ፃፈ።-Bonnechose, vol. 2, ገጽ 67። GCAmh 81.3

በእስር ቤት ጽልመት ውስጥ ሆኖ የእውነተኛውን እምነት ድል ወደፊት ተመለከተ። በህልሙ፣ ያገለግልበት በነበረው ፕራግ በሚገኘው የፀሎት ቤት ተመልሶ ሊቀ-ጳጳሱና ጳጳሳቱ በግድግዳው ላይ እርሱ የሳላቸውን የክርስቶስን ስዕሎች ፈግፍገው ሲያጠፉት ተመለከተ። ባየው ነገር እጅግ ተረብሾ ነበር፤ የጠፉትን ስዕሎች ለመተካት ብዙ ሰዓሊያን መጥተው በብዛትና በተሻለ ቀለም ሲስሏቸው በሚቀጥለው ቀን ሲመለከት ግን ሃዘኑ ወደ ደስታ ተለወጠ። ሰዓሊያኑ ሥራቸውን ሲጨርሱ በዙሪያቸው በጉጉት ለተሰበሰበ ሕዝብ እንዲህ ብለው ጮሁ፦ “አሁን ሊቀ-ጳጳሳትና ጳጳሳት ይምጡ! ከእንግዲህ ሊያጠፉአቸው ፈጽሞ አይችሉም።” ህልሙን እያሰላሰለ ተሐድሶ አራማጁ፦ “የክርስቶስ ምስል ፈጽሞ እንደማይጠፋ እርግጠኛ ነኝ፤ ያጠፉት ዘንድ ምኞታቸው ነው፤ ከእኔ በላቁ ሰባኪዎች አማካኝነት ግን እንደገና አዲስ ሆኖ በሰዎች ልብ ውስጥ ይታተማል” አለ።-D’Aubigné, b. 1, ch. 6። GCAmh 81.4

ለመጨረሻ ጊዜ ኸስ በጉባኤው ፊት ቀረበ። ንጉሠ ነገሥቱ፣ የግዛቱ ልዑላን፣ የንጉሣውያን ምክትሎች፣ የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት፣ ጳጳሳት፣ ካህናትና የቀኑን ክስተት ለመመልከት የመጣ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ያለበት እጅግ ደማቅና ታላቅ ጉባኤ ነበር። በረጅም ዘመኑ ትንቅንቅ ውስጥ የህሊና ነፃነት የሚረጋገጥበትን የመጀመሪያውን ታላቅ መስዋዕትነት ለመመልከት ከሁሉም የክርስትና ዓለማት ሰዎች ተሰብስበው ነበር። GCAmh 82.1

የመጨረሻ ውሳኔውን እንዲያደርግ ሲጠየቅ፤ ኸስ እምነቱን እንደማይክድ ተናገረ፤ የገባው ቃል በአሳፋሪ ሁኔታ በተጣሰው ንጉሠ ነገሥት ላይ ዘልቆ የሚገባውን አስተያየቱን አነጣጥሮ፣ “በሕዝቡ እምነትና እዚህ በተገኘው በንጉሠ ነገሥቱ ጥበቃ ስር ” ሆኖ በራሱ ፈቃድ በጉባኤው ፊት እንደቀረበ ተናገረ።-Bonnechose, vol. 2, ገጽ 84። የጉባኤው ሁሉ አይን ሲያርፍበት የሲጅስመንድ ፊት ደም መሰለ። GCAmh 82.2

ውሳኔ ያረፈበት ጉዳይ ስለነበር የማዋረድ ሥነ ሥርዓቱ ተጀመረ። ጳጳሳቱ እንደ ቀሳውስት ልማድ እስረኛቸውን አለበሱት፤ የቅስና ካባውን ሲያጠልቅ ሳለ፦ “ሄሮድስ በጲላጦስ ፊት ሲያቀርበው ጌታችን የሱስ ክርስቶስ ነጭ የፌዝ መጎናፀፊያ እንዲለብስ ተደርጎ ነበር” አለ።-ibid., vol. 2, ገጽ 86። አሁንም እንደገና እንዲክድ ሲያባብሉት ወደ ሕዝቡ ዘወር ብሎ፣ “ታዲያ በምን ፊቴ ሰማያትን ልመልከት? ያልተበረዘውን ወንጌል የሰበኩላቸውን እጅግ በርካታ ሰዎች እንዴት አድርጌ ልመልከታቸው? የለም አይሆንም፤ ለሞት ከተሰጠው ከዚህ ጎስቋላ አካል ይልቅ ለመዳናቸው የበለጠ ክብር እሰጣለሁ።” የቅስና ልብሱን አንድ በአንድ እያወለቀ እያንዳንዱ ጳጳስ የድርሻውን ሥነ ሥርዓት ሲፈጽም እርግማን ያወርድ ነበር። በመጨረሻም አስፈሪ የመናፍስት ምስሎች የተሳሉበት “ሊቀ-መናፍቅ” የሚል ጽሁፍ የተጻፈበት የቄስ ዘውድ በራሱ ላይ አስቀመጡ። “ለእኔ ስትል የሾህ አክሊል ለጫንከው፣ ኦ ጌታ የሱስ ሆይ፣ ስለ አንተ ይህንን የውርደት ዘውድ አጠልቃለሁ” በማለት ተናገረ። GCAmh 82.3

በእንዲህ ሁኔታ በለበሰ ጊዜ ቀሳውስቱ ነፍሱን ለሰይጣን አሳልፈው ሰጡ። ኸስ ወደ ሰማይ እየተመለከተ፣ “አንተ ዋጅተኸኛልና መንፈሴን ለእጆችህ አደራ እሰጣለሁ” ሲል ጮኸ።-Wylie, b. 3, ch. 7። GCAmh 82.4

በዚህ ጊዜ ለመንግሥታዊ ባለስልጣናት ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ ወደሚገደልበት ስፍራ ተወሰደ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ሰዎች፣ ቀሳውስትና ጳጳሳት በውድና አንፀባራቂ ልብሳቸው፣ እንዲሁም የኮንስታንስ ነዋሪ በአጠቃላይ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። ከማቃጠያው ግንድ ጋር ከታሰረ በኋላ፣ እሳቱን ለማቀጣጠል ሁሉም ነገር ዝግጁ ሲሆን፣ አሁንም በድጋሜ ስህተቱን በመቀበል ራሱን እንዲያድን ለሰማዕቱ ጥያቄ ቀረበለት። “ምን አይነት ስህተት” አለ ኸስ፣ ” ነው የማርመው? የምንም ነገር ጥፋተኛ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ። የፃፍኩትና የተናገርኩት ከኃጢአትና ከጥፋት ነፍሳትን ለማዳን በማሰብ እንደሆነ ይመሰክርልኝ ዘንድ እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ስለሆነም የፃፍኩትንና የተናገርኩትን ያንን እውነት፣ በጥልቅ ሐሴት፣ በደሜ አረጋግጠዋለሁ” አለ።-Ibid., b. 3, ch. 7። GCAmh 82.5

በዙሪያው እሳት ሲቀጣጠል “የዳዊት ልጅ የሱስ ሆይ ማረኝ” እያለ መዘመር ጀመረ፤ አንደበቱ ለዘላለም እስኪዘጋ ድረስ መዘመሩን ቀጠለ። GCAmh 83.1

ባሳየው የሚደነቅ ጀግንነት ጠላቶቹ እንኳ ሳይቀሩ ተገርመው ነበር። አንድ ቀናኢ-ጳጳስ ስለ ኸስና ብዙም ሳይቆይ ስለ ሞተው ጀሮም መስዋዕትነት ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “የመጨረሻ ሰዓታቸው ሲቃረብ ንቅንቅ በማይል አቋም አእምሮአቸውን ሞልተውት ነበር። ወደ ጋብቻ ድግስ እንደሚሄዱ አይነት ለእሳቱ ተዘጋጅተው ነበር። የስቃይ ጩኸት ፈጽሞ አላሰሙም። ነበልባሉ እየተንቀለቀለ ወደ ላይ ሲወጣ የውዳሴ መዝሙሮችን ይዘምሩ ነበር። የእሳቱ ብርታት ዝማሬያቸውን ያስቆመው ዘንድ አልተቻለውም።”-Ibid., b. 3, ch. 7። GCAmh 83.2

የኸስ ሰውነት ሙሉ በሙሉ በእሳት ተቃጥሎ ሲያልቅ፤ አመዱ ያረፈበት አፈር ጭምር ተሰብስቦ ወደ ራይን ወንዝ ተጣለ፤ እንዲህም ወደ ውቅያኖሱ ተወሰደ። አሳዳጆቹ የመሰከራቸውን እውነቶች ከሥራቸው መንግለው እንዳጠፉ በማሰብ በከንቱ ዋተቱ። በዚያ ቀን ወደ ባህር የተወሰዱት የአመድ ትቢያዎች በዓለም ሃገራት ሁሉ እንደተበተኑ ዘሮች እንደሚሆኑ ጭራሽ ያለሙት ነገር አልነበረም። ይህ [ዘር] ገና ባልታወቁ ስፍራዎች ጭምር ለእውነት ምስክሮች የሚሆን የተትረፈረፈ ምርት እንደሚያስገኝ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። በኮንስታንስ ጉባኤ አዳራሽ ውስጥ የተናገረው ድምጽ፣ ያስተጋባው ጩኸት፣ ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ የሚያስተጋባ ማሚቶ የቀሰቀሰ ነበር። ኸስ ሞተ፣ ነፍሱን የሰጠላቸው እውነቶች ግን ይጠፉ ዘንድ አልቻሉም። የእምነቱና የጽናቱ ምሳሌነት፣ ግርፋትና ሞትን ተጋፍጠው በጽናት ለእውነት ይቆሙ ዘንድ አእላፋትን የሚያበረታታ ይሆናል። የእርሱ ግድያ የሮምን አረመኔያዊ ሸፍጠኝነት ለዓለም አሳይቷል። የእውነት ጠላቶች ማስተዋል ቢሳናቸውም ያጠፉት ዘንድ በከንቱ የሚደክሙበትን ዓላማ በእርግጥ እያስፋፉት ነበር። GCAmh 83.3

አሁንም ሌላ የማቃጠያ ስፍራ በኮንስታንስ ይዘጋጅ ዘንድ ነበረው። የሌላ ምስክር ደም ስለ እውነት መመስከር አለበት። ኸስ ወደ ጉባኤው ሲሄድ ጀሮም ሲሰናበተው ጠንካራና ፈቀቅ የማይል እንዲሆን ከመከረው በኋላ አደጋ የሚገጥመው ከሆነ ፈጥኖ እንደሚደርስለት ነግሮት ነበር። የተሐድሶ መሪውን መታሰር እንደሰማ፣ ታማኙ ደቀ መዝሙር የገባውን ቃል ለመፈፀም ወዲያውኑ ተዘጋጄ። ያለ የይለፍ ፈቃድ አንድ አጋር ብቻ አስከትሎ ወደ ኮንስታንስ አቀና። እዚያ በደረሰ ጊዜም ኸስን የማዳን ምንም አይነት መንገድ እንደሌለና ራሱን ለአደጋ እንዳጋለጠ ተረዳ። ከከተማዋ ኮብልሎ ወደ መጣበት አገሩ ሲመለስ ተያዘ፣ በወታደሮች ቁጥጥር ስር ሆኖ እግሮቹ በሰንሰለት ተጠፍረው ወደ ኮንስታንስ ተመለሰ። በጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀርብ፣ ለተሰነዘሩበት ውንጀላዎች መልስ ለመስጠት ሲሞክር፣ “ከእርሱ ጋር ወደ እሳት! ወደ እሳት!” የሚል ጩኸት ነበር የተመለሰለት።-Bonnechose, vol. 1, ገጽ 234። ከባድ ስቃይ እንዲደርስበት ተደርጎ ክፉኛ ተጠፍሮ ታስሮ ወደ ጨለማ የምድር እስር ቤት ውስጥ ተጥሎ ዳቦና ውሃ ብቻ ይሰጠው ነበር። ጥቂት ወራት ከታሰረ በኋላ የጭካኔ እሥራቱ በጀሮም ላይ ያመጣው በሽታ በሕይወቱ ላይ አደጋ ሆነ፤ እንዳያመልጣቸው [እንዳይሞት] በመስጋት ጠላቶቹ ሁኔታውን በጥቂቱ ቢያሻሽሉለትም፤ ለአንድ ዓመት በእስር ቆየ።የኸስ መሞት ጳጳሳውያኑ የጠበቁትን ውጤት ሳያስገኝላቸው ቀረ። ተሰጥቶት የነበረው የይለፍ ፈቃድ በመጣሱ ምክንያት የቁጣ ማዕበል ተቀስቅሶ ስለነበር የተሻለውን አማራጭ ለመውሰድ ጉባኤው በመወሰን ጀሮምን ከማቃጠል ይልቅ የሚቻል ከሆነ ተገድዶ እንዲክድ እንዲደረግ ውሳኔ ላይ ተደረሰ። በጉባኤው ፊት እንዲቀርብ ከተደረገ በኋላ እምነቱን እንዲክድ ያለዚያም እንደሚቃጠል አማራጩ ቀረበለት። ካለፈበት የእርስ ቤት ስቃይ ጋር ሲነጻጸር እስሩ በጀመረበት ሰሞን ሞት ቢመጣለት ኖሮ እንደ ምሕረት በቆጠረው ነበር። አሁን ግን በእስር ቤቱ አሰቃቂ ሁኔታ ተጎሳቁሎ፣ በልብ ሰባቂ ሃሳብና ጭንቀት ተገርፎ፣ በህመም ተዳክሞ፣ ከጓደኞቹ በመለየቱና በኸስ መሞት ክፉኛ ልቡ ተሰብሮ፣ አእምሮአዊ ጥንካሬው ሰልሎ፣ ከጉባኤው ጋር ለመስማማት ፈቃደኝነቱን ገለጸ። የካቶሊክን እምነት ለመከተል ቃል በመግባት የዋይክሊፍንና የኸስን አስተምህሮዎች ጉባኤው ማውገዙን ተቀበለ፤ እነርሱ ካስተማሯቸው “ቅዱስ እውነቶች” በስተቀር አስተምህሮአቸውን ለማውገዝ ተስማማ። -Ibid., vol. 2, ገጽ 141። GCAmh 83.4

ይህንን ቀላል መንገድ በመጠቀም የህሊናውን ጩኸት ዝም ለማሰኘትና ሞትን ለማምለጥ ጀሮም አጥብቆ ለፋ። በእስር ቤት በብቸኝነት ውስጥ ሆኖ ግን ምን እንዳደረገ ቁልጭ ብሎ ታየው። ኸስ ያሳየውን ጥንካሬና ታማኝነት እያሰበ፣ በአንፃሩ የራሱን በእውነት ላይ የፈጸመውን ክህደት በጥልቀት አሰላሰለ። ለእርሱ ሲል በመስቀል ላይ የሞተውን፣ ያገለግለው ዘንድ ቃል የገባለትን መለኮታዊ ጌታ ያስብ ጀመረ። ከመካዱ በፊት በዚያ ሁሉ ስቃይ ውስጥ ሆኖ እንኳ በእግዚአብሔር እርዳታ መጽናናትን ያገኝ ነበር፤ አሁን ግን ፀፀትና ጥርጥር ነፍሱን ይገርፈው ጀመር። ከሮም ጋር ሰላም ከመሆኑ በፊት ተጨማሪ ክህደት መፈፀም እንደሚገባው ያውቃል። የጀመረው መንገድ የሚደመደመው ሙሉ በሙሉ እምነቱን በመካድ ከመሆን አይዘልም። አቅዋም ወሰደ፦ የጥቂት ጊዜ ስቃይ ለማምለጥ ብሎ አምላኩን አይክድም። GCAmh 84.1

ብዙም ሳይቆይ እንደገና በጉባኤው ፊት ቀረበ። እጅ መስጠቱ ፈራጆቹን አላረካቸውም። የደም ጥማታቸው በኸስ ሞት ምክንያት የበለጠ ተንቀልቅሎ ለአዲስ ተጠቂዎች ይንጫጫ ነበር። ጀሮም ሕይወቱን ለማትረፍ ያለው አማራጭ ያለምንም ገደብ፣ ሙሉ በሙሉ እውነትን መካድ ብቻ ነበር። እርሱ ግን እምነቱን በአደባባይ መስክሮ ወደ እሳት በመሄድ ሰማዕት ወንድሙን ለመከተል ወስኖ ነበር። GCAmh 84.2

ቀደም ሲል የሰጠውን የክህደት ቃል እንደማይቀበለው ከተቃወመ በኋላ፣ እንደ ሟች ሰው መከላከያውን ያቀርብ ዘንድ ዕድል እንዲሰጠው አስረግጦ ጠየቀ። የንግግሩን ተፅዕኖ በመፍራት ለተሰነዘሩበት ክሶች እውነታነት አዎንታውን ወይም እምቢታውን ብቻ እንዲያሳውቅ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወተወቱ። ጀሮም ግን ይህን አይነቱን ጭካኔና ፍርደ-ገምድልነት ተቃወመ። “ለሶስት መቶ አርባ ቀናት በሚያስፈራው ወህኒ ቤታችሁ ዘግታችሁኝ ኖራችኋል” አለ፦ “ቆሻሻ በሞላበት ከባድ ጉዳት በሚያስከትልና በሚገማ ሽታ፣ የሁሉም ነገር እጥረት ባለበት ቦታ ነበርሁ። ከዚያም አውጥታችሁ በፊታችሁ አቆማችሁኝ፤ አደገኛ ጠላቶቼ ለሆኑት ጆሮአችሁን በመስጠት እኔን ለመስማት እምቢ አላችሁ። ጠቢብ ሰዎችና በእርግጥም የዓለም ብርሐን ከሆናችሁ ትክክለኛ ፍርድን በመቃወም ኃጢአት እንዳትሰሩ ተጠንቀቁ። እኔ ደካማ ሟች ነኝ፤ የሕይወቴም ጠቃሚነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ትክክለኛ ያልሆነ ፍርድ እንዳትሰጡም የምለምናችሁ ከእኔ ይልቅ ለእናንተ የበለጠ በማሰብ ነው።”-Ibid., vol. 2, ገጽ 146, 147። GCAmh 84.3

በመጨረሻም ጥያቄው አዎንታን አገኘ፤ እውነትን የሚቃረን ወይም ጌታውን የማይመጥን አንዳች ነገር እንዳይናገር፣ ሃሳቡንና ንግግሩን መለኮታዊ መንፈስ ይቆጣጠር ዘንድ በፈራጆቹ ፊት ተንበርክኮ ፀለዬ። ለመጀመሪያዎቹ ደቀ-መዛሙርት እግዚአብሔር የተናገረው የተስፋ ቃል በጉባኤው ፊት ለጀሮም በዚያ ቀን ተፈፀመለት፤ “ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ…. አሳልፈው ሲሰጡአችሁ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንደምትናገሩ አትጨነቁ። በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩት እናንተ አይደላችሁምና።” [ማቴ 10÷18-20]። የጀሮም ንግግር በጠላቶቹ ዘንድ እንኳ ሳይቀር መገረምንና አድናቆትን አተረፈ። ለማንበብ ቀርቶ ማየት እንኳ በማይችልበት ሁኔታ በከባድ አካላዊ ስቃይና አእምሮአዊ ጭንቀት ለአንድ ሙሉ ዓመት በእስር ቤት ሲማቅቅ ኖረ። ክርክሩን ያቀረበበት ግልጽነትና ጥንካሬ ግን ጸጥታ የሰፈነበት የማጥናት እድል አግኝቶ የተዘጋጀ ያስመስለው ነበር። ፍርድ በሚያጣምሙ ዳኞች ምክንያት የተወገዙትን የቅዱስ ሰዎችን ረዥም ዝርዝር ይመለከቱ ዘንድ የሚያዳምጡትን ጠቆማቸው። በጊዜያቸው የነበረውን ሕዝብ ከፍ ከፍ ለማድረግ የጣሩ፣ የተወገዙና የተጣሉ፣ ሆኖም ከዘመናት በኋላ ክብር የተገባቸው እንደሆኑ የሚነገርላቸው በእያንዳንዱ ትውልድ የሚነሱ ሰዎች አሉ። ክርስቶስም ራሱ ወንጀል እንደሰራ ተደርጎ በኃጥእ ሸንጎ ተፈርዶበታል። GCAmh 85.1

ጀሮም አቋሙን ባስተባበለበት ጊዜ በኸስ ላይ የተወሰነው ፍርድ ፍትሐዊ እንደሆነ ተቀብሎ ሊያፀድቀው ተስማምቶ ነበር። አሁን ደግሞ፣ ያንን በማለቱ ንስሐ በመግባት ለሰማዕቱ ንጽህናና ቅድስና ምስክርነት ሰጠ። “ጆን ኸስን ከህጻንነቱ ጀምሮ አውቀዋለሁ፤” አለ፤ “እጅግ ግሩም፣ ሀቀኛና ጻድቅ ሰው ነበር። ከጥፋት ነፃ ቢሆንም ቅሉ ተፈረደበት…. እኔም እንዲሁ - እኔም ለመሞት ዝግጁ ነኝ። አንድ ቀን ማንም በማያታልለው በታላቁ እግዚአብሔር ፊት ቀርበው ስለ አስመሳይ ባህሪያቸው መልስ በሚሰጡት ጠላቶቼና የሃሰት ምስክሮቼ በተዘጋጀልኝ ስቃይ ምክንያት ወደ ኋላ አላፈገፍግም።’’-Bonnechose, vol. 2, ገጽ 151። GCAmh 85.2

እውነትን በመካዱ ምክንያት ራሱን ሲወቅስ ጀሮም ቀጠለ፦ “ከወጣትነቴ ጀምሮ ከሰራኋቸው ኃጢአቶች ሁሉ ይልቅ በዚህ ገዳይ ስፍራ በዋይክሊፍና በጌታዬ፣ በፃድቁ ሰማዕት በጆን ኸስ ላይ የተሰጠውን በኃጢአት የተሞላ ፍርድ እንደ ማጽደቄ አእምሮዬን የከበደውና በአሳዛኝ ፀፀት ውስጥ የከተተኝ ክስተት የለም። አዎ፣ [ይህንን ኃጢአቴን] ከልቤ እናዘዛለሁ፤ የሞት ፍርሃት በያዘኝ ጊዜ አስተምህሮአቸውን ሳወግዝ በአሳፋሪ ሁኔታ መንቀጥቀጤን በታላቅ ድንጋጤና መሸማቀቅ እናገረዋለሁ። ስለዚህ እግዚአብሔር በደሌን ሁሉ፣ በተለይም ከሁሉም በላይ አሰቃቂ የሆነውን ይህንን ኃጢአቴን፣ ይቅር እንዲለኝ እለምነዋለሁ። ወደ ፈራጆቹ እየጠቆመ ፈርጠም ብሎ፣ “በዋይክሊፍና በኸስ ላይ የፈረዳችሁባቸው የቤተ ክርስቲያንዋን አስተምህሮ ስላናጉ ሳይሆን፤ የመሪዎችን አሳፋሪ ድርጊት፣ ልታይ ልታይ ባይነታቸውንና እብሪታቸውን እንዲሁም የጳጳሳትንና የቀሳውስትን ርኩሰቶች ሁሉ፣ ሲኦል የሚገባቸው የብልግና ተግባር እንደሆኑ አድርገው ስላወገዟቸው ነው። እነርሱ እውነት እንደሆኑ ያረጋገጧቸውና ሊካዱ የማይችሉትን ነገሮች ሁሉ፣ የማስበውና የምናገረው ልክ እንደነርሱው ነው።” GCAmh 85.3

ንግግሩ ተቋረጠ፤ ጳጳሳቱ በቁጣ እየተንቀጠቀጡ “ምን አይነት ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው የምንፈልገው?” “ከሁሉም መናፍቃን በላይ ግትር የሆነው እርሱ ይወገድ!” በማለት ጮኹ። GCAmh 86.1

ለተፈጠረው ውሽንፍር ደንታ ሳይሰጥ በጠንካራ ንግግር ቀጠለ፡ “እንዴ! ለመሞት ይፈራል ብላችሁ ታስባላችሁ? ከሞት በላይ አስከፊ በሆነ አሰቃቂ የምድር ውስጥ ወህኒ ቤታችሁ ለአንድ ዓመት ሙሉ ዘግታችሁኛል። ከቱርካዊ፣ ከአይሁድና ከጣዖት አምላኪ በላይ ጨክናችሁብኛል፤ ገና በሕይወት እያለሁ ስጋዬ ከላዬ ላይ በስብሶ አጥንቴ ቀርቷል፤ ሆኖም አላማርርም፤ እንጉርጉሮ የሰውን ልብና መንፈስ ያሳምማልና። በአንድ ክርስቲያን ላይ ይህ አይነት ታላቅ ጭካኔ ሲፈጸም ግን መገረሜን ከመናገር እቆጠብ ዘንድ አይቻለኝም።”-Ibid., vol. 2, ገጽ 151-153። GCAmh 86.2

አሁንም እንደገና የቁጣው ማዕበል ገነፈለ፤ ጀሮምም በፍጥነት ወደ እስር ቤቱ ተወሰደ። ሆኖም የተናገራቸው ቃላት በጥልቀት የነካቸው፣ ያድኑትም ዘንድ የሚሹ የተወሰኑ ሰዎች በጉባኤው ወስጥ ነበሩ። የቤተ ክርስቲያን ልዑካን ወደ ታሰረበት ሄደው ከጎበኙት በኋላ ለጉባኤው ጥያቄ የአዎንታ መልስ እንዲሰጥ ገፋፉት። ለሮም ያለውን ተቃውሞ የሚተው ከሆነ እጅግ የሚያጓጉ እድሎች በወሮታነት የእርሱ እንደሚሆኑ ተነገረው። ነገር ግን ጌታው[ክርስቶስ] የዓለም ክብር በፊቱ ሲቀርብለት እንዳደረገው ሁሉ ጀሮምም በአቋሙ ፀና። GCAmh 86.3

“እንደተሳሳትሁ ከቅዱስ መጻሕፍት አረጋግጡልኝና፣” አለ፣ “አቋሜን በይፋ እለውጣለሁ (እክዳለሁ)።” GCAmh 86.4

“መፅሐፍ ቅዱሳት!” አለ ከከሳሾቹ አንዱ፤ “ሁሉም ነገር ፍርድ የሚያገኘው እነሱን መሰረት አድርጎ ነው? ቤተ ክርስቲያን ካልተረጎመቻቸው (ካላብራራቻቸው) ማን ሊያስተውላቸው ይችላል?” GCAmh 86.5

“የሰዎች ወጎችና ልማዶች ከአዳኛችን ወንጌል የተሻለ የእምነት እርባና አላቸውን?” ሲል ጀሮም መለሰ። “ጳውሎስ መልእክት ለላከላቸው ሰዎች ሲፅፍ ‘መጻሕፍትን መርምሩ’ እንጂ የሰዎችን ልማድ አድምጡ አላላቸውም።” GCAmh 86.6

“መናፍቅ!” ነበር መልሱ፣ “እስካሁን ስለለመንኩህ ተፀፀትሁ። የምትገፋፋው በሰይጣን እንደሆነ አያለሁ” አለው።-Wylie, b. 3, ch. 10። GCAmh 86.7

ብዙም ሳይቆይ ጥፋተኛ እንደሆነ ተበየነበት። ኸስ ሕይወቱን ወደ ሰጠበት ወደዚያው ስፍራ ተወሰደ። ፊቱ በደስታና በሰላም ፈክቶ በዝማሬ ወደፊት ተራመደ። እይታው በክርስቶስ ላይ ተተክሎ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ ሞት የአስፈሪነቱን ኃይል አጥቷል። ገዳዩ የተቆለለውን ማገዶ ለማቀጣጠል ከኋላው ሲቀርብ ሰማዕቱ በጩኸት፣ “ና፤ በድፍረት ወደፊት ና፤ እሳቱን በፊት ለፊቴ አያይዘው፤ ብፈራ ኖሮ እዚህ አልገኝም ነበር” አለው። GCAmh 86.8

እሳቱ እየተንቀለቀለ በዙሪያው ሲወጣ፣ የመጨረሻ ቃላቱ የፀሎት ቃላት ነበሩ፦ “ጌታ ሆይ፣ ሁሉን ቻይ አባት” በማለት አቃሰተ፤ “አቤቱ ማረኝ፤ ሁልጊዜ እውነትህን እንደወደድሁ ታውቃለህና ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር በል”-Bonnechose, vol. 2, ገጽ 168። ላንቃው ተዘጋ፣ ከንፈሮቹ ግን በፀሎት ይንቀሳቀሱ ነበር። GCAmh 87.1

እሳቱ ሥራውን ሲጨርስ የሰማዕቱ አመድና አመዱ ያረፈበት አፈር ተሰብስቦ በኸስ ላይ እንደተደረገው ሁሉ ወደ ራይን ወንዝ ተጣለ። የእግዚአብሔር ታማኝ ብርሐን ተሸካሚዎች በዚህ ሁኔታ ተቀፀፉ። ያወጁአቸው እውነቶች ብርሐን፣ የጀግንነት ምሳሌነታቸው ጮራ ግን ሊጠፋ አልቻለም። በዓለም ላይ ጎህ እየቀደደ ሊመጣ ያለውን፣ ጅማሮውም እየታየ የነበረውን ያንን ቀን ለማስቆም የሚሞክሩ ሰዎች፣ ፀሐይ የተፈጥሮ ኡደቷን ከመከተል ተገድባ ወደ ኋላ እንድትመለስ ቢሞክሩ ሳይሻላቸው አይቀርም። GCAmh 87.2

የኸስ መሰዋት በቦኸሚያ የቁጣንና የድንጋጤን ነበልባል አቀጣጥሎ ነበር። በቀሳውስቱ ተንኮልና በንጉሠ ነገሥቱ ክህደት ሳቢያ ወጥመድ ውስጥ እንደገባ የአገሩ ሕዝብ በሙሉ አወቀ። የእውነት ታማኝ አስተማሪ እንደነበር (በቦኸሚያውያን) ከታወጀ በኋላ ሞት የፈረደበት ጉባኤ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰሰ። አሁን ከቀድሞው ይልቅ አስተምህሮዎቹ የበለጠ ትኩረት ይስቡ ጀመር። በጳጳሳዊ አዋጆች አማካኝነት የዋይክሊፍ ጽሁፎች እንዲቃጠሉ ተደርገው ነበር። በዚህ ጊዜ ከቃጠሎ የተረፉት ጽሁፎች ከተደበቁበት እንዲወጡ ተደርገው ከ[ሙሉው] መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ወይም ሰዎች ማግኘት ከቻሏቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፋዮች ጋር ተቀናጅተው ተጠኑ፤ በመሆኑም ብዙ ሰዎች የተሐድሶውን እምነት ይቀበሉ ዘንድ ተመሩ። GCAmh 87.3

የኸስ ገዳዮች የሞተለት አላማው ድል ሲነሳ በዝምታ ማየት አልተቻላቸውም። ሊቀ-ጳጳሱና ንጉሠ-ነገሥቱ ተባብረው፣ እንቅስቃሴውን ለመደቆስ አቅደው፣ የሲጅስመንድ ሰራዊት በቦኸሚያ ላይ በኃይል ተንቀሳቀሰ። GCAmh 87.4

ሆኖም የሚታደጋቸው ተነሳ፤ ጦርነቱ እንደጀመረ ሙሉ በሙሉ አይነስውርነት የገጠመው ቢሆንም በዘመኑ ከነበሩ ጄነራሎች መካከል በጀግንነቱ የሚጠቀሰው ዚስካ የቦኸሚያዊያን መሪ ነበር። በእግዚአብሔር እርዳታና በተልዕኮአቸው ፃድቅነት በመተማመን፣ እነዚያ ሕዝቦች፣ ሊጋፈጣቸው ከሚችለው አደገኛ ሰራዊት ተወዳዳሪ የሌለውን፣ ኃያል ጦር መመከት ቻሉ። ንጉሠ-ነገሥቱ በተደጋጋሚ አዳዲስ ሰራዊት እያሰለፈ ቦኸሚያን ለመውረር ቢሞክርም ውርደት ተከናነበ። ኸሳውያኖቹ ከሞት ፍርሃት በላይ ሆነው የሚቋቋማቸው ሊገኝ አልቻለም። ጦርነቱ ከተጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጀግናው ዚስካ ሞተ፤ በምትኩም እንደርሱ ደፋርና ብልሃተኛ፣ እንዲያውም በአንዳንድ ነገሮች ከዚስካ የሚሻል መሪ የነበረው ጀነራል ፕሮኮፒየስ ተነሳ። GCAmh 87.5

አይነ ስውሩ የጦር ሰው እንደሞተ ሲረዱ የቦኸሚያ ጠላቶች ያጡትን ሁሉ ለመተካት ትክክለኛ ጊዜው እንደደረሰና ዕድል ፊቷን ወደነርሱ እንዳዞረች አሰቡ። ሊቀ-ጳጳሱ በኸሳዊያን ላይ የኃይማኖት ጦርነት(crusade) አወጀ፤ አሁንም እንደገና እጅግ አያሌ ሰራዊት በፍጥነት በቦኸሚያ ላይ ዘመተ፤ ሆኖም አሰቃቂ ሽንፈትን ተጎነጨ። አሁንም እንደገና ሌላ የኃይማኖት ጦርነት ታወጀ። በጳጳሳዊ ግዛት ስር ካሉ የአውሮፓ አገሮች በጠቅላላ ወታደር፣ ገንዘብና የጦር መሣሪያ ተሰበሰበ። መናፍቃን ኸሳውያንን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚደመስሱ እርግጠኛ ሆነው እልፍ አዕላፋት ወደ ጳጳሳዊ ሰንደቅ ዓላማ ጎረፉ። እንደሚያሸንፍ ተማምኖ ግዙፍ ጦር ወደ ቦኸሚያ ገባ። ሕዝቡም ለመመከት ወደዚያ ገሰገሰ። የሚለያቸው አንድ ወንዝ በመካከላቸው አስኪቀር ድረስ ሁለቱ ሰራዊት ተቀራረቡ። የተባበሩት ጦር በቁጥር እጅግ ይበልጥ ነበር፤ ሆኖም ጠሩ በድፍረት በመገስገስ ኸሳውያንን በማጥቃት ፈንታ፣ ተመስጦ ውስጥ የገባ አይነት ሆኖ በዝምታ ቦኸሚያውያንን ይመለከታቸው ነበር። ከዚያም በድንገት ምስጢራዊ ፍርሃት በሰራዊቱ ላይ ወደቀ፤ ምንም ጥቃት ሳይደርስበት በማይታይ ኃይል እንደሚጠረግ አይነት ያ ኃያል ጦር መፈረካከስና መበታተን ጀመረ። አያሌ ቁጥር ያለው ሕዝብ በኸሳውያን ተገደለ፤ የሚሸሸውን ጦር እየተከተሉ ያጠቁት ኸሳውያን ስፍር ቁጥር የሌለው ምርኮ ሰበሰቡ፤ ይህ ጦርነት ቦኸሚያውያንን በማደህየት ፈንታ ባለፀጋዎች አደረጋቸው።- Wylie b. 3, ch. 17። GCAmh 87.6

ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአዲስ ሊቀ-ጳጳስ አሁንም እደገና ሌላ የመስቀል ጦርነት ታቀደ። እንደባለፈው ሁሉ ጦረኞችና ቁሳቁሶች ከመላው ጳጳሳዊ አውሮፓ ተሰበሰበ። በዚህ አደገኛ እቅድ እንዲሳተፉ ለመገፋፋት እጅግ በርካታ ማታለያዎች በሥራ ላይ ውለው ነበር። በጣም አሰቃቂ የሚባል ወንጀል የፈፀመ እያንዳንዱ ወታደር ኃጢአቱ ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚባልለት ማረጋገጫ ይሰጠው ነበር። በጦርነት የሚሞቱ የተትረፈረፈ ሽልማት በሰማይ እንደሚያገኙ፣ በሕይወት የሚተርፉትም ከጦርነቱ ብዙ ሃብትና ክብር እንደሚያገኙ ቃል ተገባላቸው። እንደገና ብዙ ሰራዊት ተመልምሎ ድንበር በማቋረጥ ወደ ቦኸሚያ ገባ። ኸሳውያኑ ሆን ብለው ወደኋላ በማፈግፈግ፣ ወራሪዎቹ ገስግሰው ወደ ገጠሩ የሃገራቸው ክፍል ጠልቀው እስኪገቡ ድረስ፣ እንዲያውም ጦርነቱን አሸንፈናል ብለው ድላቸውን መቁጠር እስኪጀምሩ ድረስ ከፊታቸው ፈረጠጡ። በመጨረሻም የፕሮኮፒየስ ጦር ቆመ፤ ከዚያም ወደ ኋላ በመመለስ ለመዋጋት ገሰገሰ። በዚህ ጊዜ የተባበሩት ጦር የሰሩትን ስህተት በማስተዋል የጦርነቱን መጀመር በሰፈሩበት ቦታ ሆነው ይጠባበቁ ነበር። ወደእነርሱ የሚገሰግሰው የጦር ድምጽ ከሩቅ ሲሰማ፣ ኸሳውያኑ ገና በዓይን እንኳ ሳይታዩ ድንገተኛ ድንጋጤ በጦሩ ላይ ወደቀ። ልዑላን፣ ጀነራሎችና ተራው ወታደር መሳሪያቸውን እየጣሉ በየአቅጣጫው ይፈረጥጡ ጀመር። የወራሪው መሪ የነበረው የጳጳሱ ተወካይ በሽብር ተውጦ፣ ውጥንቅጡ የወጣውን ወታደር እንደገና ለማሰለፍ ቢጥርም ድካም ትርፉ ሆኖ ቀረ። ልፋቱ ከንቱ ሆኖ እርሱ ራሱ በሚኮበልለው ወታደር ማዕበል ተጠረገ፤ በቀላሉ የተገኘው ትልቅ ድል ተጠናቀቀ፤ አሁንም ብዛት ያለው ምርኮ በአሸናፊዎች እጅ ወደቀ። GCAmh 88.1

ለሁለተኛ ጊዜ ተወዳዳሪ ከሌላቸው፣ ከሃያላኑ የአውሮፓ ሃገራት ተሰብስቦ የተላከው ጀግና፣ ጦረኛ የሆነው፣ ለውጊያ የሰለጠነናው በሚገባ የታጠቀው ጦር፣ አንድ ጥቃት ሳይደርስበት፣ ትንሽና እስካሁን ድረስ ደካማ ከምትባል አገር በወጡ መካቾች ፊት እግሬ አውጪኝ አለ። ይህ የመለኮታዊ ኃይል መገለጽ ነበር። ወራሪዎቹ ከተፈጥሮ አቅም በላይ በሆነ ኃይል በፍርሃት ተመቱ። የፈርኦንን ሰራዊቱን በቀይ ባህር ያሰጠመ እርሱ፤ በጌዴዎንና በሶስት መቶዎች ፊት የሚዲያን ጦር እንዲሸሽ አድርጎ የእብሪተኛውን የአሶርን ጦር በአንድ ሌሊት የፈጀ እርሱ፤ የጨቋኙን ሐይል ያሽመደምድ ዘንድ በድጋሜ እጁን ዘረጋ። “በዚያ የሚያስፈራ ነገር ሳይኖር እጅግ ፈሩ። እግዚአብሔር በአንተ ላይ የሰፈሩትን አጥንት በትኖአልና፣ አሳፈርኻቸው፣ እግዚአብሔር ንቆአቸዋልና።” [መዝ 53÷5]። GCAmh 88.2

የጳጳሳዊ መሪዎች በኃይል ወረው የመግዛት ተስፋቸው ሲሟጠጥ በመጨረሻ ወደ ሰላማዊ ድርድር (ዲፕሎማሲ) ፊታቸውን አዞሩ። የህሊና ነፃነት ለቦኸሚያውያን እንደሚሰጥ የሚያትት፣ ሆኖም ለሮም ኃይል አሳልፎ በመስጠት በእርግጥ የከዳቸው አስታራቂ ሃሳብ ውስጥ ገቡ። ከሮም ጋር ሰላም ለመፍጠር ቦኸሚያውያኑ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል፦ ነፃ የመፅሐፍ ቅዱስ ስብከት፤ በቅዱስ ቁርባን ሁሉም ምዕመን ዳቦውንና ወይኑን [ሥጋውንና ደሙን] የማግኘት መብት እንዲኖረውና አምልኮም በአገሩ ቋንቋ እንዲካሄድ፣ የኃይማኖት መሪዎች ከሁሉም መንግሥታዊ ቢሮዎችና የስልጣን ተዋረድ እንዲገለሉ፤ እንዲሁም ወንጀል ሲፈፀም መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች በኃይማኖት ባለስልጣናትና በተራው ምዕመን ላይ ስልጣን እንዲኖራቸው የሚሉ ነበሩ። የመተርጎም ስልጣኑ፣ ማለትም እነዚህ አራት ቅድመ ሁኔታዎች በትክክል ምን ማለት እንደሆኑ ገለጻ የማድረግ መብቱ የቤተ ክርስቲያን መሆን እንዳለበት አሳውቀው በመጨረሻ ጳጳሳዊ መሪዎቹ እነዚህን አራት አንቀጾች ተቀበሏቸው። በዚህ መሰረት ስምምነት ላይ ተደረሰ። በኸሳውያን [የቅድመ ሁኔታ] አንቀጾች ላይ የራስዋን ትርጉም (ፍካሬ) በመጫን፣ ሮም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳደረገችው ሁሉ የራስዋን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይቻላታልና፣ ትርጉማቸውን በማጣመም በጦርነት ልታገኘው ያልቻለችውን መብት በማታለልና በማጭበርበር ማሳካት ቻለች።-Wylie b. 3, ch. 18። GCAmh 88.3

ነጻነታቸውን እንደነጠቃቸው የገባቸው ብዙ የቦኸሚያ ሰዎች ስምምነቱን አንቀበልም አሉ። ልዩነትና ክፍፍል በመካከላቸው ተነስቶ ወደ እርስ በእርስ ጥልና ደም መፋሰስ አመራ። በዚህ ግጭት ታላቁ ፕሮኮፒየስ ተገደለ፣ የቦኸሚያ የነጻነት መብቶችም በዚያው አብረው ጠፉ። GCAmh 89.1

ኸስንና ጀሮምን የከዳው ሲጅስመንድ አሁን የቦኸሚያም ንጉሥ ሆነ፣ የቦኸሚያውያንን መብት ሊያስጠብቅ ቢምልም ጳጳሳዊ ሥርዓትን መገንባቱን ተያያዘው። ለሮም ታዛዥ በመሆኑ ግን ያተረፈው ነገር የለም። የሃያ ዓመታት ሕይወቱ በፍጋትና በአደገኛ ሁኔታዎች የተሞላ ነበር። በረጅምና እርባና ቢስ ትግል ወታደሩ ተመናምኖና ሃብቱ ተሟጦ ነበር። ግዛቱን በእርስ በርስ ጦርነት ጠርዝ ላይ ትቶ፣ ለወራሾቹ የተበላሸ ስም አስቀርቶ፣ አንድ ዓመት ከገዛ በኋላ ሞተ። GCAmh 89.2

ብጥብጥ፣ ጥልና ደም መፋሰስ ቀጠለ። የውጪ ኃይላት ቦኸሚያን እንደገና ወረሯት፤ የውስጣዊ መከፋፈሉ የሕዝቡን ትኩረት ሰረቀው። ለወንጌሉ ታማኝ ሆነው የቆሙቱ ደም አፍሳሽ ስደት ስር ወደቁ። የቀድሞ ባልንጀሮቻቸው ከሮም ጋር ስምምነት አድርገው ስህተቶችዋን ጭልጥ አድርገው ሲጠጡ ሳለ በጥንታዊቷ ኃይማኖት የፀኑት የተለየ ቤተ ክርስቲያን በማቋቋም “የተባበሩት ወንድሞች” በማለት ራሳቸውን ሰየሙ። ይህ ድርጊታቸው ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ውግዘትን አመጣባቸው፤ ሆኖም ንቅንቅ ሳይሉ ቀሩ። በጫካዎችና በዋሻዎች ውስጥ በመደበቅ በህብረት ለማምለክና በአንድነት የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ይሰባሰቡ ነበር። GCAmh 89.3

እውነትን የሚከተሉ እዚህም እዚያም ተበታትነው የተረፉ አማኞች እንዳሉ ወደ ተለያዩ ሐገራት በስውር በሚልኳቸው መልክተኞች አማካኝነት ተረዱ። እነርሱ እንደሚደርስባቸው ሁሉ የስደት ኢላማ የሆኑ እዚህ ከተማ ጥቂት፣ እዛኛው ከተማም ጥቂት አማኞች እንዳሉ ተገነዘቡ። መሰረቱን በመጽሐፍ ቅዱስ ያደረገ በአልፕስ ተራሮች መካከል አንድ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን መኖሩንም ተረዱ። ይህን መረጃ በታላቅ ደስታ ተቀበሉት፤ ከዋልደንሳውያን ክርስቲያኖች ጋርም የግንኙነት መስመር ተከፈተ።-Wylie, b. 3, ch. 19። GCAmh 89.4

ቦኸሚያውያን በጽልመት ሰዓት፣ ንጋትን እንደሚጠባበቁ ሰዎች ዓይናቸውን ወደ አድማስ አዙረው፣ በስደት ሌሊታቸው ውስጥ ሆነው በወንጌሉ እንደ ፀኑ ይጠብቁ ነበር። “ዕጣቸው በክፉ ዘመን ላይ ወደቀች፤ ሆኖም መጀመሪያ በኸስ የተነገረውንና በጀሮም የተደገመውን፣ ጎህ ከመቅደዱ በፊት አንድ መቶ ዓመት ያህል ማለፍ እንዳለበት የሚያወሳውን ቃል አስታወሱ። እነዚህ ቃላት ለኸሳውያኑ፣ በባርነት ለነበሩት ጎሳዎች [እሥራኤላዊያን] እንደተነገሩት እንደ ዮሴፍ ቃላት ነበሩ፦ ‘እኔ እሞታለሁ፣ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል”’። በ1470 ዓ.ም. ገደማ ስደት ቆመ፤ የአንፃራዊ ብልጽግና ዘመንም ሆነ፤ “ምዕተ ዓመቱ ሲገባደድ በቦኸሚያና በሞራቪያ ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ ‘የተባበሩት ወንድሞች’ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ።-Ezra Hall Gillet, Life and Times of John Huss, vol. 2, ገጽ 570። የእሳት ነበልባልንና የሰይፍን ስለት አምልጠው ኸስ አስቀድሞ የተናገረውን የዚያን ቀን አጥቢያ ያዩ ዘንድ የተፈቀደላቸው ቅሬታዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም።” Wylie, b. 3, ch. 19። GCAmh 90.1