ታላቁ ተጋድሎ
ምዕራፍ ፭—ጆን ዋይክሊፍ
ከተሐድሶው በፊት የነበሩት የመፅሐፍ ቅዱሳት ቅጅዎች እጅግ አናሳ ነበሩ። ቃሉ ሙሉ በሙሉ ይጠፋ ዘንድ ግን እግዚአብሔር አልፈቀደም። እውነቶቹ ለዘላለም ተደብቀው ሊኖሩ የሚችሉ አልነበሩም። የብረት መዝጊያዎችን ከፍቶ፣ የወህኒ ቤት በሮችን ወለል አርጎ ባርያዎቹን ነጻ ማውጣት የቻለው ጌታ የሕይወትንም ቃል በቀላሉ መክፈት ይቻለው ነበር። በተለያዩ በአውሮፓ አገሮች ያሉ ሰዎች እንደተደበቀ መዝገብ እውነትን ይፈልጉ ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስ ተነሳሱ። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተመርተው፣ ቅዱሳት ገጾችን በጥልቅ ፍላጎት ማንበብ ጀመሩ። የያዘውን ብርሐን ከማወቃቸው የተነሳ በራሳቸው ላይ የሚያመጣውን መዘዝ ለመቀበል ዝግጁ ሆኑ። ሁሉም ነገር ጥርት ብሎ ባይታያቸውም ለረጅም ጊዜ ተቀብረው የነበሩ ብዙ እውነቶችን ይረዱ ዘንድ ግን አቅርቦት ነበር። የስህተትንና የአጉል አምልኮን ሰንሰለት እየበጣጠሱ፣ ለረጅም ጊዜ በባርነት የቆዩት ተነስተው ነፃነታቸውን እንዲያውጁ ጥሪ እንዲያስተላልፉ እንደ ሰማይ ልዑካን ወደ ፊት ገሰገሱ። GCAmh 61.1
ከዋልደንሶች በስተቀር፣ የእግዚአብሔር ቃል የተማሩት ሰዎች ብቻ በሚረዱት ቋንቋ ተቆልፎ ለዘመናት ኖሯል። ሆኖም በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳት በራሳቸው ቋንቋ ተተርጉመው የሚያነቡበት ሰዓት ደረሰ። ዓለም እኩለ ሌሊቱን አልፎአል። የጽልመት ሰዓታት እያለቁ፣ በብዙ ሃገራት የንጋት ምልክት መታየት ጀመረ። GCAmh 61.2
በእንግሊዝ ሃገር በአሥራ አራተኛው ክፍለ ዘመን “የተሐድሶ የንጋት ኮከብ” ብቅ አለ። ጆን ዋይክሊፍ ለእንግሊዝ ብቻ ሳይሆን ለመላው ክርስትና የተሐድሶ ፈር ቀዳጅ ሆነ። ሮምን በመቃወም ማሰማት የቻለው ታላቁ ድምፅ እንደገና ፀጥ ማለት የሚችል አልነበረም። ያ ተቃውሞ የግለሰቦችን፣ የአብያተ ክርስቲያናትንና የአገራትን ነፃነት የሚያውጀውን የትግል በር ከፈተ። GCAmh 61.3
ዋይክሊፍ ሁሉን አቀፍ ትምህርት የተማረ ሲሆን፣ ለእርሱ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነበር። በኮሌጅ በጠንካራ ክርስትናው፣ በአስደናቂ ችሎታውና የትምህርት ብቃቱ የታወቀ ነበር። ለትምህርት ካለው ከፍተኛ ጥማት የተነሳ ሁሉንም አይነት የትምህርት ዘርፎች ማወቅ ፈለገ። በትምህርታዊ ፍልስፍና፣ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና፣ በፍትሐ-ብሔር ሕግ፣ በተለይም በራሱ ሃገር ሕግ ሰለጠነ። በኋላ ባከናወናቸው አገልግሎቶቹ ላይ የእነዚህ ቀደምት ስልጠናዎች ጥቅም ግልጽ ነበረ። ግምታዊ ፍልስፍናን ጠለቅ አድርጎ ማወቁ የነበረበትን መሰረታዊ ስህተቶች ማጋለጥ እንዲችል ረዳው። ብሔራዊና ሐይማኖታዊ ሕግ በማጥናቱም ለሰብዓዊና ለሐይማኖታዊ ነጻነት ለሚደረገው ታላቅ ፍልሚያ ዝግጁ እንዲሆን ጠቀመው። ከእግዚአብሔር ቃል የሚገኙትን መሳሪያዎች እየደገነ ሳለ በትምህርት ቤቶች የሚቀርቡትን ትምህርቶችና መምህራን የሚጠቅሟቸውን ዘዴዎች ማወቅ ቻለ። የእውቀቱ ጥራትና ጥልቀት፣ እንዲሁም የጉብዝናው ኃይል በወዳጆቹም ሆነ በጠላቶቹ አክብሮትን አተረፈለት፣ በአገሪቱ ካሉ ቀዳሚ ምሁራን አንዱ መሆን በመቻሉም ደጋፊዎቹ በደስታ ይመኩበት ነበር። በአንጻሩ ደግሞ [ዋይክሊፍ ምሁር ከመሆኑ የተነሳ] ጠላቶቹ የዚህን የተሐድሶ ደጋፊ የአላዋቂነት ድክመት በማጉላት የተሐድሶው እንቅስቃሴ ነቀፋ የሚሰነዘርበት እንደሆነ ያሳዩ ዘንድ አልተቻላቸውም። GCAmh 61.4
ገና በኮሌጅ እያለ ዋይክሊፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። በጥንት ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በጥንታዊ ቋንቋ ተጽፎ በነበረበት ዘመን ላልተማረው መደብ የተዘጋው የእውነት ምንጭ፣ ምሁራን ማግኘት ይችሉ ነበር። ስለሆነም እንደ ተሐድሶ አራማጅ፣ የዋይክሊፍ የወደፊት ሥራ ተመቻችቶ ነበር። ትምህርት ያገኙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል አጥንተው፣ የተገለጸውን የነጻ ጸጋውን ታላቅ እውነት አግኝተው ነበር። ከአስተምህሮዎቻቸውም ይህንን እውነት በማሰራጨት፣ ሌሎችም ወደነዚህ ሕያው መዛግብት ፊታቸውን እንዲያዞሩ መርተዋል። GCAmh 62.1
ዋይክሊፍ ትኩረቱ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሲዞር፣ በትምህርት ቤት የነበረውን ጥንቁቅና የተሟላ የመሆን ችሎታውን በመጠቀም መጽሐፉን ይመረምር ጀመር። ከዚህም በፊት የትምህርት ቤቱ ጥናቱ፣ ወይም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሊያረካው ያልቻለ ታላቅ ጥማት ነበረበት። በከንቱ ድካም ሲፈልገው የነበረውን ግን ከእግዚአብሔር ቃል አገኘው። ከዚህ [መጽሐፍ] ውስጥ የድነት እቅድ ተገልጾለት ተመለከተ። የሰው ብቸኛ ጠበቃ ክርስቶስ እንደሆነ አስተዋለ። ለክርስቶስ አገልግሎት ራሱን በማስረከብ የደረሰባቸውን እውነቶች ለማወጅ ቆርጦ ተነሳ። GCAmh 62.2
ከተሐድሶው በኋላ እንደ ነበሩት ሁሉ፣ ዋይክሊፍ ሥራውን ሲጀምር ወዴት እንደሚያደርሰው አያውቅም ነበር። ሆነ ብሎ እያወቀ የሮም ተቃዋሚ ሆኖ አልተነሳም ነበር። ለእውነት የነበረው መሰጠት ግን ከሃሰት ጋራ ጥል ከማንሳት በቀር ወደ ሌላ ሊመራው አልቻለም። የጳጳሳዊውን ሥርዓት ስህተት የበለጠ ሲረዳ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በበለጠ ቆራጥነት ለማቅረብ ተገፋፋ። ሮም ለሰው ወግና ባህል ስትል የእግዚአብሔርን ቃል እንደጣለች አስተዋለ። የሮም ቀሳውስት የሰሩትን መጽሐፍ ቅዱሳትን የማጥፋት ወንጀል ያለፍርሃት በመክሰስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለሕዝቡ እንዲሰጥና በቤተ ክርስቲያንም ያለው ስልጣን እንዲታደስ ጠየቀ። ቅንና ግሩም አስተማሪ፣ አንደበተ-ርቱዕ ሰባኪም ነበር፤ የእለት ተእለት ሕይወቱ የሚመሰክረውን በተግባር የሚያሳይ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ፣ የአሳማኝ ምክንያቱ ኃይል፣ የሕይወቱ ንጽህና፣ እንዲሁም የማይታጠፈው ጉብዝናውና ሃቀኝነቱ ሕዝባዊ አድናቆትንና ልበ ሙሉነትን አተረፈለት። በሮም ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመውን ርኩሰት በማየታቸው ብዙዎች በቀድሞው እምነታቸው እርካታ አጥተው ስለነበር በዋይክሊፍ የተገለጹትን እውነቶች በታላቅ ደስታ ተቀበሉዋቸው። ሆኖም የተሐድሶ አራማጁ ተጽእኖ ከራሳቸው እየበለጠ መምጣቱን ሲረዱ፣ የጳጳሳዊው ሥርዓት መሪዎች በቁጣ መገንፈል ጀመሩ። GCAmh 62.3
ዋይክሊፍ ስህተቱን ለይቶ የሚያውቅ ብልህ ሰው ነበር። በሮም የፀደቁትን በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ያለ ፍርሃት ተቃወመ። የንጉሡ መንፈሳዊ መሪ(ቄስ) በመሆን ሊቀ-ጳጳሱ ከእንግሊዝ ገዢ የሚጠይቀውን ግብር በመቃወም፣ ሊቀ-ጳጳሱ ይገባኛል የሚለው፣ በዓለማዊ መሪዎች ላይ ያለው የበላይነት ስልጣን ከምክንያታዊነትም ሆነ ከተገለጠው እውነት አንጻር ተገቢ እንዳልሆነ ቁልጭ አድርጎ አሳየ። የሊቀ-ጳጳሱ ይገባኛል መጠይቆች ከፍተኛ ንዴትን ቀስቅሰው ስለነበረ የዋይክሊፍ አስተምህሮዎች በአገሪቱ ቀንደኛ ምሁራን ላይ ተጽእኖ ማሳደር ቻሉ። ንጉሡና ሹማምንቱ አንድ በመሆን የሊቀ-ጳጳሱን ምድራዊ ስልጣንና ይገባኛል የሚለውን ግብር ተቃወሙ። በዚህም ምክንያት በእንግሊዝ አገር በጳጳሳዊ የበላይነት ስልጣን ላይ ውጤታማ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ። GCAmh 62.4
የተሐድሶ አራማጁ ረዥምና ቆራጥ የተቃውሞ ትግል ካወጀባቸው ጥፋቶች አንዱ ደግሞ የምፅዋተኛ መነኮሳት ጉዳይ ነበረ። ከእነዚህ እንግሊዝን የወረሩ መነኮሳት በአገሪቱ የታላቅነትና የብልጽግና ገጽታ ላይ ጉዳት ያስከተሉ ነበሩ። ኢንዱስትሪ፣ ሥነ-ትምህርትና ግብረ-ገብነት በአጠቃላይ ይህ አውዳሚ ተጽእኖ ተሰምቷቸው ነበር። የመነኮሳቱ ሥራ ፈትነትና ልመና በሕዝቡ ገቢ ላይ ከፍተኛ ጫና ከማሳደሩም በላይ የሥራ ጠቀሜታ ንቀት እንዲደርስበት አደረገ። የወጣቶች ባህርይና የሥነ-ምግባር ደረጃ ወረደ፤ ተበላሸም። በመነኮሳት ተጽእኖ ምክንያት ብዙዎች ወደ ገዳም እንዲገቡና የምንኩስና ሕይወት እንዲኖሩ ተገፋፉ። ይህ የሚፈጸመው ደግሞ ያለወላጆቻቸው ፈቃድ ከመሆኑም በላይ ራሳቸውም በውል ሳያውቁት፣ ያለፈቃዳቸውም ነበር። የገዳም ሥርዓት መጠይቆች ከልጅነት ፍቅርና ከሃላፊነት ግዴታዎች በላይ እንደሆኑ በመናገር ከቀደምት የሮም ቤተ ክርስቲያን አባቶች አንዱ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በለቅሶና በእንጉርጉሮ አባትህ ደጃፍህ ላይ ቢወድቅ፣ እናትህም የተሸከመችበትን ገላዋን፣ የጠባሀቸውንም ጡቶች ብታሳይህ እንኳ፣ በእግርህ ረግጠህ አልፈሃቸው ቀጥታ ወደ ክርስቶስ ና።” “በዚህ አስከፊ ኢ-ሰብአዊነት” ብሎ ሉተር በኋላ እንደጠራው “ከክርስቲያኑና ከሰው ይልቅ ጨካኙንና ተኩላውን በሚያበረታታና በሚያሞግስ” ድርጊት ወላጆቻቸውን በመቃወም የልጆች ልብ እንደ ብረት እንዲጠነክር ያደረገ ነበር።-Barnas Sears, The Life of Luther, ገጽ 70, 69። በዚህም አካሄዳቸው የጳጳሳዊ መሪዎች እንደ ቀድሞዎቹ ፈሪሳውያን በወግና ባህላቸው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ዋጋ አሳጡት። ቤቶች ባዶ ሆኑ፤ ወላጆችም የወንድና የሴት ልጆቻቸውን አብሮነት ተነፈጉ። GCAmh 63.1
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንኳን ሳይቀሩ በዚህ የመነኮሳት የሃሰት ማብራሪዎች ተታለው ፈለጋቸውን እንዲከተሉ ተገፋፉ። ሕይወታቸውንም ባዶ እንዳደረጉና በወላጆቻቸውም ላይ ጥልቅ ሃዘን ማምጣታቸውን ከተመለከቱ በኋላ ብዙ ተማሪዎች ከዚህ ድርጊታቸው ተጸጽተዋል። ሆኖም አንድ ጊዜ በወጥመድ ከተጠፈሩ በኋላ ነጻነታቸውን እንደገና ማግኘት የማይታሰብ ነበር። የመነኮሳቱን ተጽእኖ በመፍራት ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመላክ ተቆጥበው ነበር። በዝነኞቹ የትምህርት ማዕከሎች የሚስተዋል የተሳታፊዎች ቁጥር መቀነስ ይታይ ነበር። ትምህርት ቤቶቹ እየኮሰሱ ሔደው ድንቁርና ተስፋፋ። GCAmh 63.2
ለእነዚህ መነኮሳት ሊቀ-ጳጳሱ ኑዛዜን የመስማት የኃጢአት ይቅርታም የመስጠት ስልጣን ሰጥቶ ነበር። ይህም የታላቅ ርኩሰት ምንጭ ሆነ። ትርፍ ከማጋበስ ወደኋላ የማይሉ መነኮሳት ፍትሐት (ስርየት) ለመስጠት ዝግጁ ከመሆናቸው፣ ወዲያውኑ ሁሉም ዓይነት ወንጀለኞች ወደ እነርሱ ይጎርፉ ጀመር። ውጤቱም እጅግ መጥፎ የሚባሉ፣ ብልሹ ስነምግባሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲስፋፉ አደረገ። ህሙማንና ደካሞች ከስቃያቸው ጋር እየተተዉ፣ የምስኪኖቹን ችግር ማቃለል የሚችሉት ስጦታዎች፣ የታዘዙትን የማያመጡትን እየኮነኑ፣ ምጽዋት እንዲለግሱ ከዛቻ ጋር ለሚጠይቁት መነኮሳት ተበረከቱ። ምንም የሌላቸው እንደሆኑ ቢናገሩም የመነኮሳቱ ሃብት ያለማቋረጥ እያደገ ሄዶ የሚያማምሩ ህንፃዎቻቸው እና የቅንጦት ጌጣጌጦቻቸው፣ የእነርሱ ብልጽግና የሕዝቡን መደህየት የበለጠ አጉልተው የሚያሳዩ ነበሩ። እነዚህ መነኮሳት፣ በቅንጦት እና በፌሽታ እየተቀማጠሉ፣ ራሳቸው ከመውጣት ይልቅ አስደናቂ ወጎችን፣ አፈ-ታሪኮችንና ቀልዶችን እየደጋገሙ በመንገር ሕዝቡ በበለጠ እንዲታለል የሚያደርጉ ያልተማሩ ሰዎችን ወደ ሕዝቡ ይልኩ ነበር። መነኮሳቱ በአጉል አምልኮ የሰከረውን ሕዝብ ጨምድደው በመያዝ ሐይማኖታዊ ሃላፊነት ማለት የሊቀ-ጳጳሱን የበላይነት መቀበል፣ ቅዱሳንን ማምለክና ለመነኮሳት ስጦታ መለገስን እንደሚያካትት፤ እነዚህም ተግባራት ሰማይ ለመግባት በቂ እንደሆኑ በማስተማር ሕዝቡ እንዲያምንና እንዲቀበል ይገፋፉት ነበር። GCAmh 63.3
የተማሩ፣ ቅዱስ ሐይማኖተኛ ሰዎች በገዳም ሥርዓት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ቢጥሩም አልተሳካላቸውም ነበር። ዋይክሊፍ ግን በተሻለ መረዳት፣ ስርዓቱ ራሱ የሃሰት በመሆኑ መውደቅ እንዳለበት በማወጅ ክፋትን ከስር መሰረቱ ይመታ ጀመር። ውይይት እና ጥያቄዎች መቀስቀስ ጀመሩ። የሊቀ-ጳጳሱን የኃጢአት ይቅርታ አድራጊነት በንዋይ እየሸጡ፣ መነኮሳት አገር ላገር ሲዞሩ ሳለ፣ ብዙዎች ይቅርታን በገንዘብ የማግኘታቸው ጉዳይ እያጠራጠራቸው፣ ይቅርታን ከሮም ሊቀ-ጳጳስ ይልቅ ከእግዚአብሔር ለምን እንደማይለምኑ መጠየቅ ጀመሩ። ስስታቸው ፈጽሞ ሊረካ በማይችለው፣ በዝባዥ መነኮሳት ተግባር ምክንያት የመንቃት ደወል የሰሙ ጥቂቶች አልነበሩም። “የሮም ቀሳውስት እና መነኮሳት፣” አሉ ሕዝቡ፣ “እንደ ነቀርሳ እየበሉን ነው፤ እግዚአብሔር ሊያድነን ይገባል፣ ያለበለዚያ ሕዝቡ ይጠፋል።”እነዚህ መነኮሳት አፍቅሮተ-ነዋያቸውን ለመሸፈን ሲጥሩ፤ የሱስ እና ደቀ መዛሙርቱም እርዳታ ያገኙ የነበሩት ሕዝቡ በሚለግሳቸው ስጦታ እንደነበር በማውሳት፣ እነርሱም የአዳኙን ፈለግ እየተከተሉ እንደሆነ ለማብራራት ሲሞክሩ ይታዩ ነበር። ይህ የመነኮሳት አስተምህሮ ጭራሽ ወደማይፈልጉት ውጤት አመራ - መነኮሳቱ የሚናገሩት እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን ራሱ ማጥናት ጀመረ - ይህም ሮም ከምንም በላይ ፈጽማ የማትፈልገው ውጤት ነበር። ሮም ለመደበቅ አላማዬ ብላ የያዘችው ጉዳይ ቢሆንም የሰዎች አእምሮ ወደ እውነት ምንጭ ይመራ ጀመር። GCAmh 64.1
ዋይክሊፍ ከመነኮሳቱ ጋር ወደ ትልቅ አተካራ ከመግባት ይልቅ የሕዝቡ አእምሮ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ እና ወደ ምንጩ የሚገፋፋውን፣ መነኮሳቱን የሚቃረነውን ትምህርት በበራሪ ጽሁፍ መልክ እያዘጋጀ ይበትን ነበር። በሊቀ-ጳጳሱ የሚፈጸመው ኃጢአት የማስተሰርየት ወይም የውግዘት (ከአባልነት የማስወገድ) ተግባር ተራ ቄሶች ከሚፈጽሙት ተመሳሳይ ሥራ የተለየ እንዳልሆነና የእግዚአብሔርን ኩነኔ በራሱ ላይ ካላመጣ በስተቀር ማንም ሰው ሊወገዝ እንደማይችል አስተማረ። የሚሊዮኖች ነፍሳት የታሰሩበትን፣ ሊቀ-ጳጳሱ ያቆመውን የመንፈሳዊና የዓለማዊ ሰፊ የግዛት መዋቅር ለማንኮታኮት ከዚህ የተሻለ ዘዴ አልነበረም። GCAmh 64.2
እያኮተኮተ ካለው ሮም የእንግሊዝን ንጉሣዊ አገዛዝ መብቶች ለማስከበር ይችል ዘንድ ዋይክሊፍ እንደገና ጥሪ ቀረበለት። የንጉሣዊ አምባሳደር ሆኖ ከሊቀ-ጳጳሱ ልኡካን ጋራ እየተሰበሰበ በኔዘርላንድ ሁለት ዓመት ቆየ። በዚያም ቆይታው ከፈረንሳይ ከኢጣሊያና ከስፔን ከመጡ የኃይማኖት መሪዎች ጋር በቅርበት ተገናኘ፤ ከመጋረጃው በስተጀርባ ያሉ ብዙ ነገሮችን፣ በተለይም በእንግሊዝ ቢቀር ኖሮ ተደብቀው ሊቀሩ የሚችሉ ብዙ ምስጢራትን መረዳት ቻለ። የጥረቱ አመርቂ ውጤት መሰረት የሆኑትን ብዙ ነገሮች ቀሰመ። የስርዓቱን ትክክለኛ ባህርይና ዓላማ ከእነዚህ የጳጳሳዊ ልዑካን ማወቅ ቻለ። ወደ እንግሊዝ በመመለስ የቀድሞውን ትምህርቱን በግልጽና በተሻለ ፍላጎት በማከናወን ስስት፣ ክብርና ማታለል የሮም አምላኮች እንደሆኑ አወጀ። GCAmh 64.3
ዋይክሊፍ ስለ ሊቀ-ጳጳሱና ስለ [ገንዘብ] ሰብሳቢዎቹ ከበራሪ ወረቀቶቹ በአንዱ ሲገልጻቸው እንዲህ ብሏል፦ “የድሃውን መተዳደሪያ ከመሬታችን ይወስዳሉ፤ ለኃይማኖታዊ ሥርዓት ማስኬጃና ለመንፈሳዊ ጉዳዮች በብዙ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ከመንግሥት ካዝና ይሰበስባሉ። ይህም ስርየትን የመሸጥ የከሃዲነት እርግማን ነው፤ ሁሉም ክርስትና የእርሱን ክህደት እንዲያረጋግጥና እንዲያስቀጥልም የሚያደርግ ነው። መንግሥታችን ትልቅ የወርቅ ቁልል እንዳለው የማያጠራጥር ቢሆንም ከዓለማዊውና ከትዕቢተኛው የቄስ ገንዘብ ሰብሳቢ በቀር ሌላ ማንም የወሰደ የለም። ከጊዜ በኋላም ይህ የወርቅ ክምችት ማለቁ አይቀርም፤ ምክንያቱም ከምድራችን ሁሉንም ገንዘብ እየሟጠጠ በመውሰድ የቤተ ክርስቲያንን ቁሳቁስና ስርየትን በማሻሻጥ የእግዚአብሔርን እርግማን ያመጣብናል እንጂ ምንም ወደኛ የሚመልሰው ነገር የለውም።”-John Lewis, History of the Life and Sufferenigs of J. Wicliff, ገጽ 37። GCAmh 65.1
ወደ እንግሊዝ እንደተመለሰ በሉተርወርዝ የቤተ ክርስቲያን ገቢዎች ጉዳይ አስተዳዳሪ ይሆን ዘንድ በንጉሡ ተቀጠረ። ይህ መሆኑ ደግሞ ዋይክሊፍ በሚያደርገው ግልጽና ቀጥተኛ አነጋገር ቢያንስ ንጉሡ እንዳልተቀየመ የሚያረጋግጥለት ነበር። የፍርድ ቤትን አሰራር በማስተካከልና የሃገሪቱን ኃይማኖት ቅርጽ በማስያዝ ረገድ የዋይክሊፍ ተጽእኖ ሚና ነበረው። GCAmh 65.2
ብዙም ሳይቆይ የሊቀ-ጳጳሱ ነጎድጓድ ይወርድበት ጀመር። ሶስት አዋጆች ወደ እንግሊዝ ተላኩ። የኑፋቄ አስተማሪውን ድምጽ ፀጥ የሚያሰኙ ወሳኝና ወዲያውኑ የሚፈጸሙ ትእዛዞች ለዩኒቨርሲቲው፣ ለንጉሡና ለቀሳውስቱ ተላኩ። (Augustus Neander, General History of the Christian Religon and Church, period 6, sec. 2, pt. 1, par. 8። ሆኖም እነዚህ ትእዛዞች ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ እዚያው ያሉት ቀሳውስት ካላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት የተነሳ ለፍርድ በፊታቸው ይቀርብ ዘንድ ለዋይክሊፍ መጥሪያ ሰጥተውት ነበር። ነገር ግን በግዛቷ ካሉት ኃያላን ልዑላን መካከል ሁለቱ ከዋይክሊፍ ጋር ወደ ልዩ ፍርድ ቤቱ አብረው ሄዱ። ህንጻውን የከበበውና እየተግተለተለ የሚገባው ሕዝብ ዳኞቹን ስላስፈራራቸው፣ የፍርድ ሂደቱን ለጊዜው እንዲያራዝሙት ስላስገደዳቸው፣ በሰላም እንዲለቀቅ ተፈቀደለት።ከትንሽ ጊዜ በኋላም እርጅናውን በመጠቀም ተሐድሶ አራማጁ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ቀሳውስቱ ተጽእኖ ያደርጉበት የነበረው ንጉሥ ኤድዋርድ 3ኛ ሞተ፤ ለዋይክሊፍ ይቆምለት የነበረው ሰው የመንግሥቱ እንደራሴ ሆነ። GCAmh 65.3
ነገር ግን የሊቀ-ጳጳሱ ትእዛዛት መድረስ መናፍቁ እንዲያዝና እንዲታሰር የማያወላዳ ግዴታን በመላው እንግሊዝ ላይ የጫነ ነበር። እነዚህ አካሄዶች በቀጥታ ወደ ማቃጠያ ስፍራ የሚመለክቱ ነበሩ። ዋይክሊፍ በቅርቡ የሮም የበቀል እርምጃ ተጠቂ እንደሚሆን የተረጋገጠ ጉዳይ መሰለ። ሆኖም ለቀድሞው ባርያው “አትፍራ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ” [ዘፍ 15÷1] ያለ እርሱ፣ ባርያውን ይጠብቅ ዘንድ እጁን ዘረጋ። ሞት መጣ፤ ሆኖም ለተሐድሶ አራማጁ ሳይሆን ያጠፋው ዘንድ ላወጀበት ለሊቀ-ጳጳሱ ነበር። ግሪጎሪ 11ኛ ሲሞት ለዋይክሊፍ ፍርድ የተሰበሰቡ የኃይማኖት መሪዎች ሁሉ ተበታተኑ። GCAmh 65.4
ተሐድሶው የመስፋፋትና የማደግ ዕድል ያገኝ ዘንድ ጣልቃ በመግባት፣ ድርጊቶችን በማጨናገፍ እግዚአብሔር ይሰራ ነበር። የግሪጎሪን ሞት ተከትሎ ሁለት የሚቀናቀኑ ሊቀ-ጳጳሳት ተመረጡ። ራሳቸውን ስህተት ሊሰሩ የማይችሉ አድርገው የሚናገሩ፣ አንዱ ለአንዱ እንዲታዘዝ የሚጠይቁ፣ ሁለት ተቃራኒ ኃይላት ተነሱ። ተቃዋሚያቸውን በሚዘገንን እርግማን እየኮነኑ፣ የሚደግፉአቸውን ደግሞ የሰማይን ሽልማት ተስፋ እየሰጡ፣ አንደኛው ሊቀ-ጳጳስ ከሌላኛው ጋር ጦርነት ሲያደርግ፣ ይረዱአቸው ዘንድ በየፊናቸው የእምነቱን ተከታዮች ይጎሰጉሱ ነበር። ይህ ክስተት የጳጳሳዊ ስርዓቱን ኃይል ክፉኛ አዳከመው። ተቃራኒ ጎራዎች ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ እርስ በርስ ሲጋጩ፣ በዚህ መሃል ዋይክሊፍ እፎይ የሚልበት ጊዜ አገኘ። ኩነኔና ውንጀላ ከአንዱ ሊቀ-ጳጳስ ወደ ሌላው ሲመላለስ፣ ተቃራኒ አቋማቸውን ለመደገፍ ሲባል የደም ጎርፍ ወረደ። ወንጀልና አሉባልታ ቤተ ክርስቲያንዋን አጥለቀለቃት። በዚህ ጊዜ የተሐድሶ አራማጁ ፀጥታ በሰፈነበት በሉተርወርዝ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ፣ ሰዎች ከሚፎካከሩ ሊቀ-ጳጳሳት ይልቅ ወደ ሰላም አለቃው ወደ የሱስ ይመለከቱ ዘንድ ተግቶ ይሰራ ነበር። GCAmh 66.1
በአባላቱ መካከል የነበረው ልዩነት የፈጠረው ጥላቻና ምግባረ ብልሹነት ሕዝቡ በርግጥም ጳጳሳዊው ሥርዓት ምን ዓይነት እንደሆነ እንዲያይ ዕድል በመፍጠሩ፣ ለተሐድሶ መንገድ አመቻቸ። “የሊቀ-ጳጳሳት ክፍፍል” በሚል ባሳተመው በራሪ ወረቀት አንደኛው ሊቀ-ጳጳስ ሌላኛውን የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው በማለት የሚኮንንበት ንግግር እውነት ስለመሆን አለመሆኑ ሕዝቡ እንዲመረምር ጠየቀ። “ርኩስ መንፈስ” አለ፣ “በአንደኛው ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ሊቀ-ጳጳሳት ውስጥ አለ፤ ይህም ሰዎች በቀላሉ፣ በየሱስ ስም አማካኝነት ሁለቱንም እንዲያሸንፏቸው ያደርጋል።”-R. Vaughan, Life and Opinions of John de Wicliffe, vol. 2, p, 6። GCAmh 66.2
ዋይክሊፍ ጌታው እንዳደረገው ሁሉ ወንጌልን ለድሆች ይሰብክ ነበር። በሉተርወርዝ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ባሉት ሰዎች ቤት ብቻ ብርሃኑ መግባቱ ስላላረካው ወደ እያንዳንዱ የእንግሊዝ ክፍል እንዲስፋፋ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። ይህንንም ለማሳካት እውነትን የሚያፈቅሩትን፣ ያወቁትን እውነት ከማስፋፋት የበለጠ ነገር አለ ብለው የማያስቡትን፣ ጥብቅ ሐይማኖተኛና ቀላል የሆኑ ሰባኪዎችን አደራጀ። በገበያ ስፍራዎች፤ በታላላቅ የከተማ መንገዶች፤ በገጠር መንገዶች፣ በሁሉም ስፍራ በመሄድ አስተማሩ። ወደ ሽማግሌዎች፣ ወደ ህሙማንና ወደ ምስኪኖች በመድረስ የፀጋውን መልካም ዜና አበሰሩላቸው። GCAmh 66.3
በኦክስፎርድ የስነ መለኮት ጥናት ፕሮፌሰር እንደመሆኑ በዩኒቨርሲቲው አዳራሾች የእግዚአብሔርን ቃል ይሰብክ ነበር። በስሩ ለነበሩት ተማሪዎች እውነትን በታማኝነት ይናገር ስለነበር፣ “የወንጌሉ ዶክተር” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት ነበር። ነገር ግን የሕይወት ዘመኑ ታላቅ ሥራ የነበረው፣ መጽሐፍ ቅዱሳትን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ መተርጎሙ ነበር። እያንዳንዱ በእንግሊዝ ያለ ሰው የእግዚአብሔርን ግሩም ሥራ በተወለደበት ቋንቋ ያነብ ዘንድ ያለውን ፍላጎት፣ “እውነቱና የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም” በሚለው ሥራው ገለፀ። GCAmh 66.4
ሆኖም በድንገት ጥረቱ ሁሉ ቆመ። ገና ስድሳ ዓመት እንኳ ያልሞላው ቢሆንም ፋታ የሌለው ሥራው፣ ጥናቱና የጠላቶቹ ጥቃት ጉልበቱን ክፉኛ በዝብዞት፣ ያለ እድሜው አረጀ፤ በአደገኛ በሽታም ተመታ። ይህ ክስተት ለኃይማኖት ሰዎቹ [ለካቶሊኮቹ] ከፍተኛ ደስታ አመጣ። በቤተ ክርስቲያንዋ ላይ ያመጣውን ክፋት አምርሮ እንደሚፀፀት በማሰብ ንስሐ ሲገባ ለማዳመጥ ወደ ክፍሉ ፈጥነው መጡ። ከአራቱ ሐይማኖቶች የተወከሉ ሰዎች ከአራት የመንግሥት ሹሞች ጋር ሆነው ከሞት አፋፍ ላይ ነው በተባለው ሰው ዙሪያ ተሰበሰቡ። “ሞት በከንፈሮችህ ላይ ነው” አሉ፤ “በጥፋትህ ተፀፀት፤ እዚህ በቆምንበትም እኛን ለመጉዳት የተናገርከው ሁሉ ስህተት እንደነበር ተናገር” አሉት። የተሐድሶ አራማጁ በዝምታ ካዳመጣቸው በኋላ፣ ከተኛበት ቀና እንዲያደርገው ረዳቱን ጠይቆ፣ የተናገረው ስህተት እንደነበር ተረድቶ የመመለስ ንግግሩን የሚጠብቁትን ትኩር ብሎ ተመለከተና ሁሌም ድንጋጤ በሚፈጥርባቸው ኃይለኛ ድምፁ ፈርጠም ብሎ “በእርግጥ አልሞትም፤ እኖራለሁ፤ የመነኮሳቱን የክፋት ሥራም እናገራለሁ።” አለ-D’Aubigné, b. 17, ch. 7፤ መነኮሳቱ አፍረውና ደንግጠው በፍጥነት ከክፍሉ ወጡ። GCAmh 66.5
ዋይክሊፍ የተናገራቸው ቃላት እውን ሆኑ። ሰማይ የወከለውን፣ ሕዝቡን ነጻ የሚያወጣውን፣ የእውቀት ብርሐን የሚፈነጥቅላቸውን፣ ወደ እምነትም የሚያመጣቸውን፣ ሮምን ለመቃወም ተወዳዳሪ የሌለው መሳሪያ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ለአገሬው ሕዝብ ያስጨብጥ ዘንድ በሕይወት ኖረ። ይህንን ሥራ ለመፈጸም እጅግ በርካታ መሰናክሎች መታለፍ ነበረባቸው። ዋይክሊፍ በህመም እየደከመ መጣ፤ የቀሩት የሥራ ዘመናቱ ጥቂት ዓመታት ብቻ እንደሆኑ አወቀ፤ መጋፈጥ ያለበትን የተቃራኒ ኃይልም ተመለከተ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል ተስፋዎች በመደገፍ ፈጽሞ ተስፋ ሳይቆርጥ ወደፊት ቀጠለ። የአዕምሮውን ብስለትና የካበተ ልምዱን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለዚህ የተለየ ሥራው በእግዚአብሔር አቅርቦት ተጠብቆና ተዘጋጅቶ ከሥራዎቹ ሁሉ የሚበልጠውን ተግባሩን ያከናውን ዘንድ ቆየ። ክርስትና በሁሉም ስፍራ ሲበጣበጥ ሳለ የተሐድሶ መሪው ሉተርወርዝ ባለው ቤቱ ተቀምጦ፣ በውጪ ለሚነፍሰው ማዕበል ጆሮውን ሳይሰጥ ትኩረቱን ሁሉ ለተመረጠበት ሥራ አደረገ። GCAmh 67.1
በመጨረሻም ሥራው ተጠናቀቀ! የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ተተርጉሞ ቀረበ። የእግዚአብሔር ቃል ለእንግሊዝ አገር ተከፈተ። አሁን የተሐድሶ አራማጁ እስርም ሆነ ማቃጠያ ሥፍራውን አይፈራም። መቼም ሊጠፋ የማይገባው መብራት በእንግሊዛውያን እጅ አስገብቷል። ለሀገሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በመስጠቱ በጦርነት ከተገኙት ታላላቅ አንጸባራቂ ድሎች ይልቅ የክፋትንና የድንቁርናን ሰንሰለት ለመበጠስ፣ አገሩንም ነጻ በማውጣት ከፍ ከፍ ለማድረግ የተሻለ ሥራ ሰርቷል። GCAmh 67.2
የህትመት ሥራው እንዴት እንደተከናወነ በውል ባይታወቅም መጽሐፍ ቅዱስን ለማባዛት ግን አዝጋሚና እልህ አስጨራሽ ሥራዎች መከናወን እንደነበረባቸው መገመት አያዳግትም። መጽሐፉን ለማግኘት ከነበረው ታላቅ ጉጉት የተነሳ በመጻፉ ሥራ ላይ ብዙዎች ተሳታፊ ሆነዋል፤ ያም ሆኖ የነበረውን ጥያቄ ለማሟላት አስቸጋሪ ነበር። በሐብት የበለፀጉት አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱሱን ሙሉውን ሲፈልጉ፣ ሌሎች ደግሞ የተወሰነውን ክፍል ብቻ ይገዙ ነበር። በብዙ አጋጣሚዎች፣ ብዙ ቤተሰቦች አንድ ላይ ተባብረው አንድ ቅጂ ይገዙ ነበር። እናም ብዙም ሳይቆይ የዋይክሊፍ መጽሐፍ በየቤቱ ገባ። GCAmh 67.3
ሰዎች ያመዛዝኑ ዘንድ የቀረበላቸው ተማፅኖ ለጳጳሳዊው አስተምህሮ ከነበራቸው የምን-ግዴ አይነት ተቀባይነት ቀሰቀሳቸው። በዚህ ጊዜ ዋይክሊፍ ልዩ የሆነውን የፕሮቴስታንት አስተምህሮ ማስተማር ጀመረ፤ መዳን በክርስቶስ በማመን እንደሆነና መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው እውነት (ስህተት ሊኖርበት የማይችል) እንደሆነ ሰበከ። ይሰብኩ ዘንድ በተለያየ ስፍራ ባሰማራቸው ሰዎች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስና የተሐድሶ መሪው ተጨማሪ ጽሁፎች ተሰራጩ። እጅግ ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ የእንግሊዝ ግማሽ ሕዝብ የዚህ አዲስ እምነት ተከታይ ሆነ። GCAmh 67.4
የመጽሐፍ ቅዱሳት ብቅ ማለት የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት ላይ ጭንቀትና ስጋት ፈጠረ። አሁን መሳሪያቸው ፋይዳ-ቢስ የሆነበት፣ ከዋይክሊፍ በላይ የሆነ ኃይለኛ ወኪል ተጋርጦባቸዋል። ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋ ከአሁን በፊት ተተርጉሞ ስለማያውቅ በእንግሊዝ አገር መጽሐፍ ቅዱስን የሚከለክል ሕግ አልነበረም። ሕግ የወጣውና በጥብቅ የተተገበረውም ከዚያ ጊዜ በኋላ ነበረ። የቀሳውስቱ ጥረት ቢኖርም እንኳ [ሕግ ከመውጣቱና ተግባራዊ ከመሆኑ] በፊት የእግዚአብሔርን ቃል ለማሰራጨት የተወሰነ ጊዜ ተገኝቶ ነበር። GCAmh 68.1
አሁንም እንደገና የጳጳሳዊው መሪዎች የተሐድሶ አራማጁን ድምጽ ዝም ለማሰኘት ሴራ መከሩ፤ በሶስት ፍርድ ሸንጎዎች ፊት በተከታታይ ቢቀርብም ያሰቡት አልሆነላቸውም። መጀመሪያ የቀሳውስት ስብሰባ ካደረጉ በኋላ፣ የዋይክሊፍ ጽሁፎች ተቀባይነት የሌላቸው እንዲሆኑ በማወጅ ወጣቱን ንጉሥ ሪቻርድ 2ኛን ከጎናቸው በማሰለፍ የተወገዙትን አስተምህሮዎች ይዞ የተገኘ ሁሉ ወደ እስር ቤት እንዲገባ የሚያዝ ንጉሣዊ አዋጅ ማግኘት ቻሉ። GCAmh 68.2
ከቤተ ክርስቲያን የተላለፈውን መመሪያ በመቃወም ዋይክሊፍ ለተወካዮች ምክር ቤት (ለፓርላማው) ይግባኝ አለ። በብሔራዊው መማክርት ፊት ያለ ፍርሃት ቆሞ ያለውን የስልጣን ተዋረድ በመቃወም በቤተ ክርስቲያን የተደነገጉትን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ጥፋቶች በተሐድሶ እንዲታረሙ ጠየቀ። ተአማኒነትን በተላበሰ ኃይለኛ ንግግር የጳጳሳዊውን ሥርዓት የስልጣን ንጥቂያና ብልሹ አስተዳደር ዘረዘረ። በጠላቶቹ መካከል ግራ መጋባት ሆነ። የዋይክሊፍ ደጋፊዎችና ወዳጆቹ ሮማዊነትን በግልጽ እንዲቀበሉ ተገደው ስለነበር፣ የተሐድሶ መሪው አርጅቶና ብቻውን ሆኖ፣ ለተባበረው የንጉሣዊና ጳጳሳዊ ስልጣን እጅ መስጠቱ አይቀሬ ነው ተብሎ በብዙሃኑ ተጠብቆ ነበር። ሆኖም በዚያ ፈንታ ጳጳሳውያን ተሸናፊ ሆነው ራሳቸውን አገኙት። የተወካዮች ምክር ቤትም ልብን ሰብቆ በሚገባው የዋይክሊፍ ንግግር ተነሳስቶ ለማሳደድና ለማሰር የወጣውን አዋጅ ሻረ፤ የተሐድሶ አራማጁም እንደገና ነጻነቱን ተቀዳጀ። GCAmh 68.3
በግዛቱ ካለው ጠቅላይ ሐይማኖታዊ ልዩ ፍርድ ቤት እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ ቀረበ። በዚህ ስፍራ ለኑፋቄ ቦታ አይሰጥም። አሁን በመጨረሻ ጊዜ ሮም አሸናፊነትን ስትቀዳጅ፣ የለውጥ አራማጁ ሥራ እንዲቆም ይደረጋል። ጳጳሳውያን ያሰቡት ይህንን ነበር። እቅዳቸው ከተሳካ፣ ዋይክሊፍ ያለው አማራጭ አስተምህሮው ስህተት እንደሆነ አምኖ መናገር ወይም ከፍርድ ቤቱ ሲወጣ ቀጥታ ወደ መቃጠያ ስፍራ ማምራት ነበር። GCAmh 68.4
ዋይክሊፍ ግን ያፈገፍግ (አቋሙን ይለውጥ) ዘንድ አልተቻለውም፤ [አስተምህሮውን] ይሸፍን ዘንድ አልሆነለትም። ያለምንም ፍርሃት በአስተምህሮው ጎን በመቆም የከሳሾቹን ውንጀላ አስተባበለ። ራሱን፣ ስልጣኑንና በፊቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመርሳት በመለኮታዊ ፍርድ ቤት ፊት አድማጮቹን ሰብስቦ ማደነጋገሪያቸውንና ማታለያቸውን ሁሉ በዘላለማዊ እውነት ሚዛን ላይ አስቀመጠው። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተሰበሰቡበት አዳራሽ ውስጥ መኖሩ ይታወቅ ነበር። እግዚአብሔር የመኖሩ ምልክት በአድማጮቹ ላይ ነበረ። ቦታውን ለመልቀቅ ኃይል ያነሳቸው መሰሉ። ከጌታ የፍላጻ ኮሮጆ እንደሚወጡ ቀስቶች የለውጥ አራማጁ ቃላት ልባቸውን ይበሱ ጀመር። በርሱ ላይ የሰነዘረበትን የኑፋቄ ወንጀል፣ በሚያሳምን ኃይል መልሶ ወደ እነርሱ ወረወረው። ለምንድነው ስህተታቸውን ማሰራጨት የፈለጉት? ጠየቀ፦ ለትርፍና በእግዚአብሔር ፀጋ ለመነገድ ነው አለ። GCAmh 68.5
“ከማን ጋር የምትከራከሩ (ማንን የምትገዳደሩ) ይመስላችኋል?” አለ መጨረሻ ላይ፤ ወደ መቃብሩ ከተቃረበ ሽማግሌ ጋር ነውን? አይደለም ከእውነት ጋር እንጂ፤ ከእናንተ በላይ ኃያል ከሆነው ከሚያሸንፋችሁ እውነት ጋር ነው” ካለ በኋላ ከስብሰባው ወጣ፤ ከከሳሾቹ አንድስ እንኳ ያስቆመው ዘንድ የሞከረ አልነበረም።-Wylie, b. 2, ch. 13። GCAmh 69.1
የዋይክሊፍ ሥራ ወደ መገባደዱ ነበር። ለረጅም ጊዜ በእጁ የያዘው የእውነት ሰንደቅ ዓላማ ከእጁ የሚወድቅበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር፤ ሆኖም በወንጌሉ ምስክርነት የሚቆምበት አንድ ተጨማሪ ሥራ ነበረው። እውነት፣ የስህተት ግዛት ጠንካራ ምሽግ ከሆነው ስፍራ መታወጅ ነበረበት። የቅዱሳንን ደም በተደጋጋሚ ባፈሰሰችው በሮም ፍርድ ቤት ይቀርብ ዘንድ ዋይክሊፍ መጥሪያ ደረሰው። የተጋረጠበት አደጋ ምን እንደሆነ በውል ቢያውቅም፣ የእጅ መንቀጥቀጥ በሽታ ንውጠት ጉዞውን የማይሞከር ከማድረጉ በቀር መጥሪያውን ተቀብሎ መሄዱ አይቀርም ነበር። በአካል ቀርቦ ለሮም ቃሉን ባይሰጥም በደብዳቤ መናገር ይችል ነበር። ይህንንም ለማድረግ ወሰነ። GCAmh 69.2
ከሚኖርበት የቤተ ክርስቲያኑ መጠለያ ሆኖ በአነጋገር አክብሮት ያለው፣ በመንፈስም ክርስትናን የተላበሰ ሆኖም የጳጳሳዊውን ሥርዓት ታይታና ኩራት የሚነቅፍ ደብዳቤ ለሊቀ-ጳጳሱ ጻፈ። እንዲህም አለ፦ “እውነት እላለው፣ የያዝሁትን እውነት ለእያንዳንዱ ሰው በተለይም ለሮም ጳጳስ ከፍቼ ስገልጽ ደስታ ይሰማኛል። እኔ ትክክልና እውነት እንደሆነ የተቀበልኩትን እምነት እርሱም በፈቃዱ እንደሚቀበለው ስህተትም ቢኖርበት እንደሚያስተካክለው ተስፋ አለኝ። በመጀመሪያ የክርስቶስ ወንጌል የእግዚአብሔር ሕግ ሙሉ አካል እንደሆነ አምናለሁ… በዚህ ምድር የክርስቶስ ወኪል ነው እንደመባሉ ከሰዎች ሁሉ በላይ የሮም ሊቀ-ጳጳስ ለዚህ የወንጌል ሕግ ይገዛል ብዬ እጠብቃለሁ። ምክንያቱም በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል ታላቅነት ማለት ዓለማዊ ክብርና ዝናን ያቀፈ ሳይሆን የክርስቶስን ሕይወትና ባህርይ መምሰልና በትክክል መከተል ነበር… ክርስቶስ በዚህ ምድር ሐይማኖታዊ ሕይወቱ፣ ዓለማዊ ሹመትንና ክብርን የጠላና ንቆ የተወ፣ እጅግም መጻተኛ (የድኆች ድኃ) የነበረ ሰው ነበር። GCAmh 69.3
“ማንም አማኝ ራሱን ሊቀ-ጳጳሱን፣ ወይም ከቅዱሳን ሰዎች አንዱን መከተል አይኖርበትም፤ ሊቀ-ጳጳሱ ክርስቶስን መከተል በቻለበት መጠን እነርሱም ጌታ የሱስ ክርስቶስን መከተል እንጂ። ጴጥሮስና የዘብዴዎስ ልጆች የክርስቶስን ፈለግ መከተልን በተጻረረ ሁኔታ ዓለማዊ ክብር ሲሹ ጥፋት ሰሩ፤ ስለሆነም ከእነዚያ ስህተቶቻቸው ጋር እንከተላቸው ዘንድ አይገባንም። GCAmh 69.4
“ስለዚህ ክርስቶስ፣ በተለይም የእርሱ ሐዋርያት እንዳደረጉት ሁሉ ሊቀ-ጳጳሱም ምድራዊ ሹመቱንና ስልጣኑን ለዓለማዊ ገዥ ትቶ፣ የኃይማኖት መሪዎችን በብቃት ማንቀሳቀስና ማበረታታት ይኖርበታል። GCAmh 70.1
“ከእነዚህ ነጥቦች በአንዱ አጥፍቼ ከሆነና ለማስተካከል የእኔ መሰዋት አስፈላጊ ከሆነ ራሴን በትህትና ለሞት አስረክባለሁ፤ እንደ ፈቃዴና እንደ ምኞቴ ማድረግ ብችል ኖሮ በእርግጥ በሮም ጳጳስ ፊት እቀርብ ነበር። ጌታ ግን በተቃራኒው ጎበኘኝ፤ ከሰዎች ይልቅ እግዚአብሔርን መታዘዝ እንዳለብኝ አስተማረኝ።” GCAmh 70.2
ሲያጠቃልልም እንዲህ አለ፦ “እርሱና በስሩ ያሉ የኃይማኖት አባቶች፣ በሕይወትና በባህርይ ጌታ የሱስ ክርስቶስን ይከተሉ ዘንድ፣ ሕዝቡንም በትክክል ያስተምሩና ሕዝቡም በተመሳሳይ ሁኔታ ይከተላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደጀመረው የሊቀ-ጳጳሱን ልብ እንዲያነሳሳ ወደ አምላክ እንጸልይ” አለ።-Hohn Foxe, Acts and Monuments, vol. 3, ገጽ 49, 50። GCAmh 70.3
እንዲህም በማድረጉ ዋይክሊፍ ለሊቀ-ጳጳሱና ለተከታዮቹ የክርስቶስን የዋህነትና ትህትናን በማንጸባረቅ፣ በእርሱና ተወካዮቹ ነን ብለው በሚናገሩለት ጌታ መካከል ያለውን ልዩነት ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለክርስትናው ዓለም ቁልጭ አድርጎ አሳየ። GCAmh 70.4
የታማኝነቱ ዋጋ የሕይወቱ መስዋእትነት እንደሚሆን ዋይክሊፍ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። ንጉሡ፣ ሊቀ-ጳጳሱና በሥሩ ያሉት ጳጳሳቱ በመተባበር ሞቱን ለማቀናጀት ተነሱ፤ በጥቂት ወራት ውስጥም ወደ መቃጠያ ስፍራው እንደሚያመራ እርግጥ መሰለ። ጽናቱ ግን በፍጹም አልተናወጠም ነበር። “የሰማእትነትን ዘውድ ከሩቅ ስለመጠበቅ ለምን ታወራላችሁ?” አለ፤ “ለሚንቦጠረሩት የኃይማኖት መሪዎች የክርስቶስን ወንጌል ስበኩ፤ ሰማዕትነት አያመልጣችሁም። ምን! በሕይወት እያለሁ ዝም ልል? በፍጹም አላደርገውም! አውሎ ነፋሱ ይውረድ፤ መምጣቱን እጠባበቃለሁ።”-D’Aubgné, b. 17, ch. 8። GCAmh 70.5
የእግዚአብሔር ጥበቃ ግን አሁንም ባርያውን ከለለው። እድሜውን ሙሉ በጀግንነት ለእውነት የቆመ ሰው፣ የሕይወቱን የየቀን አደጋ የተጋፈጠ ጀግና፣ እውነትን በሚጻረሩ ሰዎች ጥላቻ ምክንያት ሊወድቅ አልቻለም። ዋይክሊፍ ራሱን ለመጠበቅ አስቦ አያውቅም፤ አምላክ ግን ከለላው ሆኖ ቆይቷል። አሁን ደግሞ ጠላቶቹ እንደሚይዙት እርግጠኛ በሆኑበት ሰዓት፣ የእግዚአብሔር እጅ እነሱ ፈጽሞ ሊደርሱበት ወደማይችሉት ስፍራ ወሰደው። በሉተርወርዝ ቤተ ክርስቲያን የቁርባን አገልግሎት በሚያቀርብበት ጊዜ በመንቀጥቀጥ በሽታው ተመቶ ወደቀ፤ በጥቂት ጊዜያት ውስጥም ሕይወቱ አለፈች። GCAmh 70.6
እግዚአብሔር ለዋይክሊፍ ሥራ ሰጥቶት ነበር፤ የእውነትንም ቃል በአፉ አስቀመጠ፤ ይህም ቃል ወደ ሕዝቦቹ ይመጣ ዘንድ በዙሪያው ቅጥር ሰራለት፤ ለታላቁ የተሐድሶ ሥራ መሰረት እስኪጣል ድረስ ሕይወቱ ተጠበቀች፣ ሥራውም ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ ተደረገ። GCAmh 70.7
ዋይክሊፍ የመጣው በግርዶሽ ከተሰወረው የጨለማው ዘመን ነበር። ከቀደመው ሥራቸው የተነሳ የተሐድሶውን አሰራር መልክ ያስይዘው ዘንድ የሚረዱት፣ ከእርሱ በፊት የነበሩ ሰዎች አላገኘም። ልክ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ የተለየ ተልዕኮ ለማሳካት ተወልዶ፣ የአዲስ ዘመን ፈር ቀዳጅ ሆነ። ያም ሆኖ የደረሰበት እውነት ሙሉ እና የተቀናጀ ስለነበር እርሱን ተከትለው የተነሱት ተሐድሶ አራማጆች ሊበልጡት ያልቻሉ፣ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከመቶ ዓመት በኋላ እንኳ ሊደርሱበት ያልቻሉት ነበር። መሰረቱ ሰፊ እና ጥልቅ፤ መዋቅሩም ብርቱና ትክክል ስለነበር ከእርሱ በኋላ የመጡት [ከቆመበት ቀጠሉ እንጂ] የፈረሰውን እንደገና የመሥራት ተግባር ማከናወን አላስፈለጋቸውም። GCAmh 70.8
የሰዎችን የማሰብ ችሎታና ህሊና ነጻ ለማውጣት፣ ድል ተቀዳጅታ ከቆየችው ሮም እስር አሕዛብን ለማስፈታት፣ ዋይክሊፍ መርቆ የከፈተው ታላቁ እንቅስቃሴ ምንጩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አገኘ። ከአሥራ አራተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እንደ የሕይወት ውሃ ለዘመናት ሲፈስ የነበረው የበረከት ጅረት መነሻ ምንጭ ይህ ነበር። ዋይክሊፍ ቅዱስ መጻሕፍትን፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ መገለጫ፣ በቂ የእምነትና የተግባር መመሪያ አድርጎ እንዲሁ በእምነት ተቀበለ። የሮም ቤተ ክርስቲያን መለኮታዊ፣ ስህተት ልትሰራ የማትችል፣ ባለስልጣን በመሆንዋ፣ ለአንድ ሺህ ዓመት የቆየውን አስተምህሮዎችዋንና ልምድዋን ያለ ምንም ጥያቄ በአክብሮት እንዲቀበል ተደርጎ ነበር የተማረው። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል ያደምጥ ዘንድ ከዚህ ሁሉ ፈቀቅ አለ። ሰዎች እውቅና ይሰጡት ዘንድ ያበረታታ የነበረውም ስለዚህ ስልጣን ነበር። ቤተ ክርስቲያንዋ በሊቀ-ጳጳሱ በኩል እንድትሰበክ በመደረግ ፋንታ፣ በቃሉ አማካኝነት የሚናገረው የእግዚአብሔር ድምጽ ብቸኛውና ትክክለኛው ስልጣን እንደሆነ አወጀ። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍጹም ፈቃድ ገላጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ብቸኛ ተርጓሚውም መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በማስረዳት፣ እያንዳንዱ ሰው አስተምህሮውን በማጥናት፣ ሊሰራ የተገባውን ራሱ ማወቅ እንደሚችል አስተማረ። በዚህም የሰዎችን አእምሮ ከሮምና ከሊቀ-ጳጳሱ ወደ እግዚአብሔር ቃል መለሰ። GCAmh 71.1
ዋይክሊፍ ከታላላቆቹ የተሐድሶ አራማጆች መካከል አንዱ ነበር። በአስተሳሰብ ችሎታው ስፋት፣ ፍንትው ካለው አመለካከቱ፣ እውነቱን በመጠበቅ ረገድ ከነበረው ፍንክች የማይል አቋምና ለማስከበርም ከነበረው ድፍረት አንጻር፣ ከእርሱ በኋላ ከመጡት ውስጥ የሚወዳደረት አሉ ማለት ይከብዳል (የሚወዳደሩት ምናልባት በጣም ጥቂት ቢኖሩ ነው)። የሕይወት ንጽህናው፣ በጥናትና በሥራ የነበረው ኧህ የማይል ትጋቱ፣ ፈጽሞ የማይደለለው ስብዕናው፣ ክርስቶስ መሰል ፍቅሩና ለአገልግሎቱ የነበረው ታማኝነት የተሐድሶ አራማጆችን ጀማሪ ማንነት የሚገልጹ ባህርያት ነበሩ። ይህንን ማከናወን የቻለው በዘመኑ የነበረውን የእውቀት ጽልመትና የስነ-ምግባር ብልሹነት አሸንፎ በመውጣት ነበር። GCAmh 71.2
የዋይክሊፍ ሕይወት፣ የቅዱስ መጻሕፍት የማስተማርና የመለወጥ ኃይል ምስክር ነው። መሆን የቻለውን እንዲሆን ያደረገው መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። የመገለጡን ታላቅ እውነቶች ለመረዳት የሚደረግ ጥረት ለሁሉም ብልቶች ጥንካሬና እድሳት ይለግሳል፤ አእምሮን ያሰፋል፤ መረዳትን ይስላል፤ ሚዛናዊነትን ያጎመራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማንኛውም ሌላ ጥናት ሊያደርገው በማይችል ሁኔታ እያንዳንዱን አስተሳሰብ፣ ስሜትና ምኞት ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ የዓላማ ጽናትን፣ ትዕግስትን፣ ጀግንነትንና ጽናትን ያላብሳል፤ ባህርይን ያነጥራል፤ ነፍስንም ይቀድሳል። በቅንነትና በአክብሮት የሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የደቀ-መዝሙሩን አእምሮ ከዘላለማዊው ህሊና ጋር በቀጥታ በማገናኘት፣ እጅግ የተዋጣለት ከሚባል የሰዎችን ፍልስፍና መሰረት ካደረገ ስልጠና ይልቅ ጠንካራ እና የተሻለ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ሰዎችን ለዓለም ያበረክታል። “የቃልህ ፍቺ ያበራል” ይላል መዝሙረኛው፤ “ህጻናትንም አስተዋዮች ያደርጋል። [መዝ 119÷130]። GCAmh 71.3
በዋይክሊፍ የተሰጡ አስተምህሮዎች መስፋፋታቸውን ቀጠሉ፤ ዋይክሊፋውያን እና ሎላርዶች በመባል የሚታወቁት ተከታዮቹ የእንግሊዝን አገር ማካለል ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎችም ስፍራዎች በመበተን የወንጌሉን እውቀት አሰራጩ። በዚህ ጊዜ መሪያቸው ስለሌለ ከበፊቱ ይልቅ በበለጠ ቅንዓት አስተማሪዎች ሥራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፤ ብዙ ሕዝብም ትምህርታቸውን ለመስማት ይጎርፍ ጀመር። GCAmh 72.1
ከንጉሣውያን ዘር አንዳንዶች፣ የንጉሡ ሚስት ሳትቀር ከተለወጡት ሰዎች መካከል ነበሩ። በተለያዩ ስፍራዎች ሊስተዋል የሚችል የሰዎች የባህርይ ለውጥ ይታይ ነበር፤ የጣዖት አምልኮ ምልክቶች (የሮማዊነት ምሳሌ) ሁሉ ከአብያተ ክርስቲያናቱ ተወገዱ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ መሪያቸው ይሆን ዘንድ በደፈሩት ሁሉ ላይ ጭካኔ የተሞላበት የማሳደድ ማዕበል በድንገት ተደፋባቸው። የእንግሊዝ ነገሥታት የሮምን ድጋፍ በማግኘት ግዛታቸውን ለማጠናከር ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ የተሐድሶ አራማጆችን ለመሰዋት አላቅማሙም ነበር። በእንግሊዝ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቃጠሎ አዋጅ በወንጌሉ ደቀ መዛሙርት ላይ ታወጀባቸው። ሰማዕትነት፣ሰማዕትነትን ተከተለ፤ የእውነት ጠበቆች ህገ-ወጥ ተደርገው ሲገረፉ፣ ጩኸታቸውን ማሰማት የቻሉት ወደ ፀባኦት ጌታ ጆሮ ብቻ ነበር። የቤተ ክርስቲያን ጠላቶችና የግዛቱም ከሃዲዎች ሆነው ቢሰደዱም በድሆች ደሳሳ ጎጆዎች ውስጥ በመጠለል፣ በአብዛኛውም በጎሬዎችና በዋሻዎች በመደበቅ፣ በምስጢር ቦታዎች ማስተማራቸውን ቀጠሉ። በቁጣ የገነፈለ ስደት ቢኖርም የተረጋጋ፣ ሐይማኖተ-ጠንካራ፣ ቅንና ታጋሽ የሆነ የተስፋፋውን የእምነት ብልሹነት የሚቃወም ጥረት ለምዕተ ዓመታት መነገሩን ቀጠለ። በዚያን ቀደምት ጊዜ የነበሩ ክርስቲያኖች፣ ስለ እውነት የነበራቸው እውቀት ከፊል ቢሆንም የእግዚአብሔርን ቃል መውደድና መታዘዝ ተምረው ነበር። ለዚህም ሲሉ በትእግስት ስቃይን ተቀበሉ፤ በሐዋርያት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ብዙዎች ለክርስቶስ ሥራ ሲሉ ዓለማዊ ጥሪታቸውን ሁሉ አጡ። GCAmh 72.2
በቤታቸው ይኖሩ ዘንድ የተፈቀደላቸው እነርሱ የተሰደዱትን ወንድሞች በደስታ ያስጠጓቸው ነበር፤ ከዚያም እነርሱ ሲባረሩ ከህብረተሰቡ የመገለልን ዕጣ ፈንታ በፀጋ ይቀበሉት ነበር። እውነት ነው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ በአሳዳጆቻቸው ቁጣ ደንግጠው ሐይማኖታቸውን በመሰዋት ነጻነታቸውን ያገኙ፣ የጸጸትን መጎናጸፊያ ለብሰው ከእስር ቤት የወጡና ሲያደርጉት የነበረው ስህተት እንደሆነ ያወጁ ነበሩ። በአንጻሩ ደግሞ ቁጥራቸው ጥቂት ያልነበረ፣ “በመከራውም ይካፈሉ” ዘንድ የተገባቸው ሆነው በመቆጠራቸው ሃሴት የሚያደርጉ፣ በግርፋትና በነበልባል መሃል፣ በ“ሎላርድ ህንጻ” ውስጥ፣ እንዲሁም በወህኒ ቤት ውስጥ ሆነው ያለፍርሃት እውነትን የመሰከሩ፣ የተመሰከረለት አስተዳደግ የነበራቸው፣ የዋህና ራሳቸውን ያዋረዱ ሰዎች ነበሩበት። GCAmh 72.3
ዋይክሊፍ በሕይወት እያለ የሚፈልጉትን ማድረግ ተስኖአቸው ነበርና፣ መቃብር ውስጥ በዝምታ ማረፉ የነበራቸውን ጥላቻ ሊያበርደው አልቻለም። በኮንስታንስ በነበረው ስብሰባ አዋጅ ታውጆ፣ ከሞተ አርባ አመት ካለፈው በኋላ መቃብሩ ተቆፍሮ አጥንቱ ከወጣ በኋላ ተሰብስቦ ተቃጥሎ አመዱ በአቅራቢያው በሚገኝ ወንዝ ተጣለ። “ወንዙ” አለ አንድ ጸሐፊ፣ “አመዱን ወደ አቮን ወሰደው፣ ከአቮንም ወደ ሰቨርን፣ ከሰቨርን ደግሞ ወደ ጠባባብ ሐይቆች፣ ከዚያም ወደ ዋናው ውቅያኖስ ገባ፤ በመሆኑም የዋይክሊፍ አመድ በዓለም ዙሪያ የተበተነው የራሱ አስተምህሮ አርማ ነው” አለ። የክፉ ሥራቸው ትርጉም ምን እንደሆነ ጠላቶቹ በውል አልተገነዘቡትም ነበር።-T. Fuller, Church History of Britain, b. 4, sec. 2, par. 54። GCAmh 72.4
የቦኸሚያው ጆን ኸስ የሮማዊነትን ብዙዎቹን ስህተቶች እንዲያወግዝና ወደ ተሐድሶ ሥራም እንዲገባ የተመራው በዋይክሊፍ ጽሁፎች አማካኝነት ነበር። በእነዚህ በዘመን ርቀት እጅግ በተነጣጠሉ ሁለት መቶ ዓመታት፣ የእውነት ዘር ተዘራ። ሥራው ከቦኸሚያ ወደ ሌላ ስፍራዎች ተስፋፋ። የሰዎች አዕምሮ ለረጅም ጊዜ ተረስቶ ወደ ነበረው ወደ እግዚአብሔር ቃል ተመራ። መለኮታዊ እጅ ለታላቁ ተሐድሶ መንገዱን እያዘጋጀ ነበረ። GCAmh 73.1