ታላቁ ተጋድሎ

10/45

ምዕራፍ ፯—የሉተር ከሮም ጋር መለያየት

ቤተ ክርስቲያንን ከጳጳሳዊ ጽልመት አውጥተው ወደ ንጹህ ኃይማኖት ይመሩ ዘንድ ከተጠሩ መካከል በቀደምትነት የሚጠቀሰው ማርቲን ሉተር ነበረ። ቀናኢ፣ ጽኑና የተሰጠ የሆነው፣ እግዚአብሔርን ከመፍራት በቀር ሌላ ፍርሃት የማያውቀው፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ በስተቀር የኃይማኖት መሰረት ይሆን ዘንድ ለሌላ ለምንም ነገር እውቅና የማይሰጠው ሉተር ለዘመኑ የሚገጥም ሰው ነበር። በእርሱ በኩል እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶና ለዓለም የእውቀት ብርሐን የሚሆን ታላቅ ሥራ አከናወነ። GCAmh 91.1

እንደ መጀመሪያዎቹ የወንጌል ፋና ወጊዎች ሁሉ ሉተርም በድሃ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ነበር። የልጅነቱን ጊዜ ያሳለፈው በድሃ የጀርመን ጪሰኛ ቤት ውስጥ ነበር። አባቱ የማዕድን አውጪ ሰራተኛ ነበረና በየቀኑ እየለፋ ከሚያገኘው ገቢ ለትምህርት ቤቱ ይከፍልለት ነበር። የአባቱ ምኞት የሕግ ሰው እንዲሆን ነበር፤ ሆኖም በብዙ መቶ ዓመታት ውስጥ በጣም በዝግታ ሲያድግ የነበረው የታላቁ ቤተ መቅደስ ግንበኛ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር አቅዶለት ነበር። ችግር፣ ድህነት እንዲሁም ጥብቅ ስነ-ሥርዓት፣ ዘላለማዊው ጥበብ ሉተርን ለሕይወቱ አስፈላጊ ተልዕኮ ያዘጋጀበት ትምህርት ቤት ነበሩ። GCAmh 91.2

የሉተር አባት ጠንካራና ንቁ አእምሮ የነበረው፤ የሚደነቅ ባህርይ የተላበሰ፤ ታማኝ፣ ቆራጥና ቀና ሰው ነበር። የመጣው ቢመጣ ለሃላፊነቱ የገባውን ቃል የማያጥፍ አይነት ሰው ነበር። የሚያስደንቀው ማስተዋሉ የምንኩስና መዋቅሩን በጥርጣሬ እንዲመለከተው አድርጎት ነበር። ከእርሱ ፈቃድ ዉጪ ሉተር ገዳም ሲገባ እጅግ አዝኖ ነበር። እናም ከልጁ ጋር እንደተጣላ፣ ሳይታረቅ ለሁለት ዓመት ቆየ፤ ከታረቁ በኋላም ቢሆን የነበረው አቋም አልተቀየረም ነበር። GCAmh 91.3

የሉተር ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ነበሩ። በእግዚአብሔር እውቀትና በክርስትና ስነ-ምግባር ልምምድ ያንፁአቸው ዘንድ ይጥሩ ነበር። ልጁ የእግዚአብሔርን ስም እንዲያስታውስ፤ አንድ ቀን የጌታ እውነት እንዲስፋፋ የሚያግዝ ይሆን ዘንድ ሉተር እየሰማ አባቱ ዘወትር ፀሎት ያደርግ ነበር። የጥረት-ግረት ኑሮአቸው እንዲያጣጥሙት የፈቀደላቸው እያንዳንዱ የስነ-ምግባራዊ ወይም አእምሮአዊ እድገት ዕድል በወለጆቻቼው በጉጉት ይዳብር ነበር። ልጆቻቸውን ለቅስድናና ለጥቅም ያዘጋጁ ዘንድ ጥረታቸው ቅንና ትጋት የተላበሰ ነበር። ከቆራጥነታቸውና ከባህርያቸው ጥንካሬ የተነሳ አንዳንዴ ከመጠን ያለፈ ሃይለኝነት ይንጸባረቅባቸው ነበር። ሆኖም የተሐድሶ አራማጁ እራሱ በአንዳንድ ሁኔታዎች ወላጆቹ ስህተት ይሰሩ እንደነበር ቢያውቅም ስነ-ስርዓታቸውን ከሚኮንነው ይልቅ የሚያወድሰው ይበልጥ ነበር። GCAmh 91.4

ገና በልጅነቱ እንዲማር በተላከበት ቦታ ጭካኔ፣ አንዳንዴም ሁከት ጭምር አጋጥሞታል። የወላጆቹ ድህነት እጅግ ስር የሰደደ ከመሆኑ የተነሳ ወደሚማርበት ሌላ ከተማ ሲሄድ ምግብ ለማግኘት ለተወሰነ ጊዜ ከቤት ቤት እየዞረ መዘመር ግዴታ ሆኖበት ነበር። ብዙ ጊዜም ይርበው ነበር። በዚያን ጊዜ ተንሰራፍቶ የነበረው ጽልመት የተላበሰው የኃይማኖት አጉል አምልኮ አስተሳሰብ በፍርሃት ሞልቶት ነበር። ስለወደፊቱ የጨለማ ዘመን ሲያስብ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ፤ እግዚአብሔር ፍንክች የማይል፣ ይቅርታ የማያደርግ ፈራጅና ጨካኝ ፈላጭ ቆራጭ እንጂ ቸር ሰማያዊ አባት እንዳልሆነ ዘወትር በፍርሃት በማሰብ፣ ማታ ማታ ወደ መኝታው ሲገባ በሃዘን በተሞላ ልብ ይጋደም ነበር። በከባድና በበርካታ ተስፋ መቁረጦች ውስጥ ቢሆንም ሉተር ነፍሱን ወደሳባት የስነ-ምግባርና የእውቀት ምጥቀት የላቀ ደረጃ ለመድረስ በቆራጥነት ወደፊት ይገፋ ነበር። GCAmh 91.5

ለእውቀት ይጠማ ነበር፤ ቅንና የተግባራዊነት ባህርይ የተላበሰው አእምሮው፣ ከታይታና ጥልቀት ከሌለው ነገር ይልቅ ጠንካራ መሰረት ያለውንና ጠቃሚውን እንዲመኝ መራው። በአሥራ ስምንት ዓመቱ ወደ ኤርፈርት ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ሁኔታዎቹ የተሻሉ፣ የወደፊት ተስፋዎቹም ከቀደመው ዘመኑ ይልቅ የፈኩ ነበሩ። በቁጠባና በጥረት ብቃትን ያተረፉት ወላጆቹ የሚያስፈልገውን ሁሉ ማሟላት ቻሉ። የብልህ ጓደኞቹ ተጽዕኖ የቀድሞውን የጽልመት ልምዱን በጥቂቱም ቢሆን ቀንሶለታል። ለጥልቅ አስተሳሰባቸው ከፍተኛ ዋጋ እየሰጠ፣ የጠቢቦቹን ጥበብ እየቀሰመ፣ የተዋጣላቸው የሚባሉ ፀሐፊያንን መዛግብት በትጋት አጠና። በድሮዎቹ መምህራኑ ጥብቅ ሥነ-ሥርአት ሥር በነበረበት ጊዜ እንኳ አንዳች የተለየ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን አሳይቶ ነበር። አሁን ሁኔታዎች ሲመቻቹ፣ በመልካም ተፅዕኖ ስር ሲሆን፣ አእምሮው በፍጥነት ጎለበተ። የማስታወስ ችሎታው፣ ንቁ አይነ-ህሊናው፣ ጠንካራ የማገናዘብ ችሎታዎቹና ደከመኝ የማይለው ጥረቱ ብዙም ሳይቆይ ከጓደኞቹ መካከል የቁንጮነትን ሥፍራ እንዲይዝ ረዳው። የሚማረው ትምህርት መረዳቱን አጎመራው፤ የአዕምሮው ገቢራዊነትና ቶሎ ነገሮችን የማስተዋል ችሎታው በሕይወቱ ለሚገጥመው ተቃርኖ እያዘጋጁት ነበር። GCAmh 92.1

እግዚአብሔርን መፍራት በሉተር ልብ ውስጥ ይኖር ነበረ፤ ይህም ለዓላማው ፅኑ እንዲሆንና በእግዚአብሔርም ፊት ራሱን በጥልቀት እንዲያዋርድ መራው። ምን ጊዜም በመለኮታዊ እርዳታ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ይሰማው ነበር፤ እያንዳንዷን ቀን የሚጀምረው በፀሎት ነበር፤ ለምሪት እና ለድጋፍ በእያንዳንዷ ትንፋሹ በልቡ ልመና ያቀርብ ነበር። “በደንብ መፀለይ” ይላል ሁልጊዜ፣ “የጥናት የተሻለው ክፋይ ነው።”-D’Aubigné, b. 2, ch. 2። GCAmh 92.2

አንድ ቀን በዩኒቨርሲቲው ቤተ መፃሕፍት ውስጥ መፃሕፍትን ሲያገላብጥ ሳለ ሉተር በላቲን ቋንቋ የተፃፈ መፅሐፍ ቅዱስ አገኘ። እንደዚህ አይነት መፅሐፍ ከዚያን ጊዜ በፊት ፈፅሞ አይቶ አያውቅም ነበር። ስለመኖሩ ራሱ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። በሕዝባዊ አምልኮ ጊዜ ተከፍተው ሲነበቡ የሰማው የተወሰኑትን የወንጌልና የሐዋርያት መልእክት መፅሐፍትን ሲሆን፣ መፅሐፍ ቅዱስ ማለት እነዚህን ብቻ የያዘ እንደሆነ አድርጎ ያስብ ነበር። አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉውን የእግዚአብሔር ቃል ተመለከተ። አክብሮታዊ ፍርሃትና መደነቅ ተደባልቆበት የተቀደሱትን ገፆች ከፈታቸው፤ “ኦ! እንደዚህ አይነቱን መፅሐፍ እግዚአብሔር ለራሴ ቢሰጠኝ” ለማለት በየመሐሉ እያቋረጠ፣ ልቡ በኃይልና በፍጥነት እየመታ፣ የሕይወትን ቃላት ራሱ አነበበ።-Ibid., b. 2, ch. 2። መላዕክት ከጎኑ ነበሩ፤ ከእግዚአብሔር ዙፋን የወጣው የብርሐን ጮራ የተከበረውን እውነት ያስተውል ዘንድ ተላከ። እግዚአብሔርን እንዳያሳዝን ሁሌም ይፈራ ነበር፤ አሁን ግን በደንብ የገባው የኃጢአተኝነት ሁኔታው ከምንጊዜውም በላይ በጥልቀት ተሰማው። GCAmh 92.3

ከኃጢአት ነፃ፣ ከእግዚአብሔርም ጋር ሰላም ለመሆን ካለው ልባዊ ፍላጎት የተነሳ በመጨረሻ ወደ ገዳም ለመግባትና የምንኩስና ሕይወት ለመምራት ወሰነ። በዚህ ስፍራ እጅግ ተራ የተባሉ ሥራዎችን መሥራት፣ ቤት ለቤት እየዞረ መለመን ነበረበት፤ ክብርና ሙገሳ ከምንም በላይ በሚናፈቁበት የእድሜ ክልል በነበረበት ሰዓት እነዚህ እዚህ ግባ የማይባሉ የሥራ ሃላፊነቶች የተፈጥሯዊ ስሜቱን በጥልቀት የሚያዋርዱ ነበሩ። ሆኖም በኃጢአቱ ምክንያት ይህ መሆን ያለበት አስፈላጊ ተግባር መሆኑን በማመን ውርደቱን በትዕግስት ችሎ ኖረ። GCAmh 93.1

በቀን ውስጥ መሥራት ካለበት ሥራ የምትተርፈውን እያንዳንዷን ደቂቃ ለጥናት ይጠቀምባት ነበር፤ እንቅልፉን ትቶ፣ ለሚቀምሳት ትንሽ መብል በሚያጠፋው ጊዜ እንኳ ቅር ይሰኝ ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናቱ ከምንም በላይ ደስተኛ ነበር። በገዳሙ ከግድግዳ ጋር በሰንሰለት የታሰረ መጽሐፍ ቅዱስ አግኝቶ ነበርና ብዙ ጊዜ በዚያ ስፍራ ይቆይ ነበር። የኃጢአት መረዳቱ እየጠለቀ ሲሄድ፣ በራሱ ጥረት ይቅርታንና ሰላምን ለማግኘት ጣረ። በጥረት፣ በፆም፣ በአዳር ፀሎት፣ ራስን በማሰቃየት፣ የገዳም ኑሮ ሊያላቅቀው ያልቻለውን ተፈጥሮአዊ ክፋት ለመቆጣጠር እጅግ ጥብቅና የማያወላዳ ሕይወት ይመራ ነበር። በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ያገኝ ዘንድ የሚያስችለውን የልብ ንጽህና ለማግኘት ሊከፍለው ያልተዘጋጀበት መስዋዕትነት አልነበረም። “በጣም የተሰጠሁ መነኩሴ ነበርኩ፤” አለ በኋላ፦ “የሕጎቼን ደንቦች ለመፈፀም መናገር ከምችለው በላይ በጥብቅ አክብሬአለሁ። መነኩሴ በምንኩስና ሥራው ሰማይ መግባት ቢችል ኖሮ ያለ ምንም ጥርጥር መብቱ ይኖረኝ ነበር። በዚያ ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ብቀጥል ኖሮ ስጋዬን ለማስገዛት የምፈጽማቸውን ተግባራት ለሞት እስኪያበቁኝ ድረስ እገፋባቸው ነበር።” ብሏል።-Ibid., b. 2, ch. 3። ከዚህ ስቃይ አምጪ ስነ-ሥርዓት የተነሳ ጉልበቱ ተሟጠጠ፤ ከዚያ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ማገገም ላልቻለበት ራስን የሚያስት ድንገተኛ የሰውነት መኮማተር በሽታ ተጋለጠ። ሆኖም በጥረቱ ሁሉ በሸክም የዛለችው ነፍሱ፣ ረፍት ታገኝ ዘንድ አልተቻላትም። በመጨረሻም ተስፋ ወደ መቁረጥ አፋፍ ደረሰ። GCAmh 93.2

ጥረቱ ሁሉ ከንቱ እንደሆነ በሚሰማው ሰዓት እግዚአብሔር ለሉተር ጓደኛና ረዳት አስነሳ። ጥብቅ ሐይማኖተኛው ስታውፒትዝ የእግዚአብሔርን ቃል ለሉተር አእምሮ ከፈተለት፤ ራሱን ከማየት አይኑን እንዲያነሳ፤ የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ ምክንያት ስለሚመጣው ዘላለማዊ ቅጣት ማሰላሰል እንዲያቆምና ወደ ኃጢአት አስተሰርይው አዳኙ፣ ወደ የሱስ እንዲመለከት መከረው። “ኃጢአትህን እየቆጠርህ ራስህን ከምታሰቃይ፣ በተቤዤህ ክንድ ላይ ራስህን አኑር። በፃድቅ ሕይወቱ፣ በሞቱ ሥርየት፣ በእርሱ እመን። የእግዚአብሔርን ልጅ አዳምጠው። መለኮታዊ ተቀባይነትን ታገኝ ዘንድ እርሱ ሰው ሆነ።” “አስቀድሞ የወደደህን እርሱን ውደደው።”-Ibid., b. 2, ch. 3። እንዲህና እንዲህ ብሎ ይህ የምሕረት መልዕክተኛ ተናገረ። ቃላቱ በሉተር አእምሮ ላይ ጥልቅ ተፅዕኖ አሳደሩ። ለረጅም ጊዜ ዋጋ ሲሰጣቸው ከነበሩት ስህተቶች ጋር ሲታገል ከቆየ በኋላ፣ እውነቱን መጨበጥ ቻለ፣ ለተናወጠችው ነፍሱም ሰላም ወረደላት። GCAmh 93.3

ሉተር ቄስ ሆኖ ሲቀባ በዊተንበርግ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ይሆን ዘንድ ከገዳም እንዲወጣ ተጠራ። በዚህ ስፍራ መፅሐፍ ቅዱሳት መጀመሪያ በተፃፉበት ቋንቋ ያጠና ጀመር። መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ጀመረ፤ መዝሙረ ዳዊት፣ ወንጌላቱና የሐዋርያቱ መልእክቶች በደስታ በብዛት ለተሰበሰቡ ሰዎች መብራራት ጀመሩ። ጓደኛውና የበላዩ የነበረው ስታውፒትዝ መድረክ ላይ ወጥቶ እንዲሰብክ ገፋፋው። በክርስቶስ ፈንታ ቆሞ ለሰዎች ይሰብክ ዘንድ የማይገባው እንደሆነ በመቁጠር ሉተር አመነታ። ከረዥም ትግል በኋላ በጓደኞቹ ተማፅኖ ተሸነፈ። በዚህ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱሳት እውቀት ታላቅ ሊቅ ሆኖ ነበር፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ ነበረ። በአንደበተ-ርዕቱነቱ አድማጮቹ ተማረኩ፤ እውነቱን ያቀረበበት ግልጽነትና ኃይል አሳመናቸው፣ የጋለ መንፈሱም ልባቸውን አቀለጠው። GCAmh 93.4

ሉተር እስካሁን የጳጳሳዊው ቤተ ክርስቲያን ታማኝ ልጅ ነበር፤ ከዚህ ውጪ ሌላ ሊሆን የሚችለው ይኖራል ብሎ አስቦም አያውቅም። በእግዚአብሔር አቅርቦት ሮምን ይጎበኝ ዘንድ ተመራ። በመንገዱ በሚገኙ ገዳማት እያደረ ጉዞውን በእግሩ ቀጠለ። ኢጣሊያ ውስጥ በነበረ ገዳም ባየው ሃብት፣ ዕፁብ ድንቅነትና ድሎት ምክንያት በመገረም ተዋጠ። መነኮሳቱ ከፍተኛ ገንዘብ እየተሰጣቸው፣ እጅግ በተዋበ ቤት እየኖሩ፣ ውድና ያሸበረቀ ልብስ እየለበሱ፣ በሚያስደንቅ የምግብ ገበታ ላይ ይመገቡ ነበር። ሉተር በሚያሳምም አሉታዊ መጠራጠር ይህንን ክስተት ከራሱ የራስን መካድና የስቃይ ሕይወት ጋር አነፃፀረው። አዕምሮው ግራ መጋባት ጀመረ። GCAmh 94.1

በመጨረሻም ባለ ሰባት ኮረብታዎችዋን ከተማ ከሩቅ ተመለከተ። በልባዊ ስሜት በምድር ተደፍቶ እየሰደገ “ቅድስት ሮም፣ ሰላም እልሻለሁ!” አለ።-Ibid., b. 2, ch. 6። ወደ ከተማዋ ገብቶ አብያተ ክርስቲያናትን ጎበኘ፣ በቀሳውስትና በመነኮሳት የሚደጋገመውን አስደናቂ ታሪክ(ተረት) አዳመጠ፤ አስፈላጊውን ሥርዓተ-አምልኮም አከናወነ። በሚያየው ነገር ሁሉ በመገረምና በድንጋጤ ይሞላ ነበር። በሁሉም የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት ዘንድ፣ ከላይ እስከታች ድረስ፣ ኃጢአት እንደሰረጸ ተመለከተ፤ የብልግና ቀልዶችን ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይሰማ ነበር፤ በቁርባን ሥርዓት ጊዜ ጭምር የሚሰማው አሳዛኝ ብልግናና ንቀት በፍርሃት ሞላው፤ ከመነኮሳቱና ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ቆይታ ብኩንነትንና ወራዳነትን አስተዋለ። ወደ የትኛውም አቅጣጫ ቢዞር፣ በቅድስና ስፍራ ንቀትና ስድብ ተገናኘው። “በጣም የሚገርም ነው፤” አለ ሲጽፍ፤ “ምን አይነት ኃጢአትና ግፍ ነው በሮም የሚፈፀመው፤ ካልታየና ካልተሰማ በስተቀር ማመን አይቻልም። ‘ሲኦል የሚባል ሥፍራ ካለ፣ ሮም የተመሠረተችው (የተገነባችው) በእርሱ ላይ ነው።’ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሮም ሁሉም አይነት ኃጢአት የሚከማችባት፣ ዲካ የሌላት ጉድጓድ ናት።”-Ibid., b. 2, ch. 6። GCAmh 94.2

አዳኛችን ከሮማ ፍርድ ቤት ሲወጣ እየተራመደ ወረደበት የተባለውን፤ በተዓምር ከየሩሳሌም ወደ ሮም ተወሰደ የተባለለትን፣ “የጲላጦስ ደረጃ” በመባል የሚታወቀውን ደረጃ በጉልበቱ ተንበርክኮ ለወጣ ሁሉ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያደርግ ሊቀ-ጳጳሱ በቅርቡ አዋጅ አውጥቶ ነበር። ሉተር አንድ ቀን እነዚህን ደረጃዎች በመሰጠት ሲወጣ ሳለ በድንገት ነጎድጓድ የሚመስል ድምጽ “ፃድቅ በእምነት ይኖራል” [ሮሜ 1÷17] የሚል ድምጽ የተናገረው መሰለው። በሃፍረትና በፍርሃት ውስጥ ሆኖ ከተንበረከከበት በፍጥነት ተነስቶ በችኮላ ከዚያ ቦታ ሄደ። ያ ጥቅስ በነፍሱ ላይ የነበረው ኃይል ፈፅሞ አልጠፋም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለደህንነት ሲባል የሰውን ሥራ ተስፋ ማድረግ ስህተት እንደሆነ፣ ክርስቶስ በፈጸመው ሥራም ቋሚ እምነት ይኖረው ዘንድ አስፈላጊነቱ የበለጠ ግልጽ እየሆነለት መጣ። አይኖቹ ተከፍተዋል፤ ለጳጳሳዊ ሥርዓት ከንቱ እምነትም(ማታለያም) ፈጽመው አይዘጉም። ከሮም ፊቱ ዘወር ሲል [ወደ አገሩ ሲመለስ]፣ ልቡም ጭምር ዘወር ብሎ ነበር፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መለያየቱ እየሰፋ ሄዶ ከጳጳሳዊ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነት በሙሉ እስኪያቋርጥ ድረስ ቀጠለ። GCAmh 94.3

ከሮም ከተመለሰ በኋላ ሉተር ከዊተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በስነ-መለኮት ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪውን አገኘ። በዚህ ጊዜ አግኝቶት በማያውቅ ነፃነት የሚወደው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማተኮር ዕድል አገኘ። የሊቀ-ጳጳሳቱን አባባሎችና አስተምህሮዎች(dogmas) ሳይሆን፣ እድሜውን ሙሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ ለማጥናትና በታማኝነት ለመስበክ ለራሱ ቃል ገብቶ ነበር። መነኩሴና ፕሮፌሰር ብቻ መሆኑ ቀርቶ ህጋዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋጅ ነጋሪ ሆነ። ለእውነት የተጠሙና የተራቡ የእግዚአብሔርን መንጎች ይመግብ ዘንድ የተጠራ ጠባቂ ነበር። በተቀደሱት መፃሕፍት ውስጥ ከተቀመጡት በስተቀር ክርስቲያኖች ሌላ አስተምህሮዎች ይቀበሉ ዘንድ እንደማይገባቸው አስረግጦ ተናገረ። እነዚህ ቃላት የጳጳሳዊ ሥርዓት የበላይነት መሰረትን ክፉኛ መቱት። የተሐድሶውን ዋና መርህ የያዙ ነበሩ። GCAmh 95.1

የሰውን ፅንሰ ሃሳብ ከእግዚአብሔር ቃል በላይ ከፍ ከፍ ማድረግ ያለውን አደጋ አስተዋለ። የመምህራንን በግምት ላይ የተመሠረተ እምነተ-ቢስነትን ያለ አንዳች ፍርሃት ነቀፈ፤ ለረዥም ጊዜ በሰዎች ላይ የመቆጣጠር ተፅዕኖ አስፍኖ የኖረውን ፍልስፍናና የስነ-መለኮት ትምህርት ተቃወመ። እንደዚህ ያሉት አስተምህሮዎች እርባና-ቢስ መሆናቸው ሳያንስ ጎጂም እንደሆኑ በግልጽ በማውገዝ፣ የሰዎችን አእምሮ ከአደናጋሪና አሳሳች ፈላስፋዎችና የኃይማኖት አስተማሪዎች በመመለስ በነብያትና በሐዋርያት የተቀመጡትን ዘላለማዊ እውነቶች አድማጮች ይጨብጡ ዘንድ ጣረ። GCAmh 95.2

ቃሉን ለመስማት በቋፍ ለነበረው አያሌ ሕዝብ የሚናገረው መልእክት እጅግ የከበረ ነበር። ከአሁን በፊት እንዲህ አይነት ትምህርት ወደ ጆሮአቸው አልገባም። የክርስቶስ ፍቅር የምሥራች፣ በሚያነፃው ደሙ አማካኝነት የሚገኘው ስርየትና ሰላም ልባቸውን በደስታ አሞቀው፤ ዘላለማዊ ተስፋ በልባቸው ፀነሰ። ጮራው ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ የሚደርስ፣ እስከ ዓለም ፍፃሜም ፍካቱ እየጨመረ የሚሄድ የብርሐን ችቦ በዊተንበርግ ተቀጣጠለ። GCAmh 95.3

ብርሐንና ጨለማ ግን ስምሙ ይሆኑ ዘንድ አይቻላቸውም። በእውነትና በሃሰት መካከል ሊገቱት የማይቻል ግጭት አለ። አንዱን መደገፍና ማጽናት ሌላውን ማጥቃትና መገልበጥ ነው። አዳኛችን ራሱ፦ “ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።” [ማቴ 10÷34] ብሏል። ተሐድሶውን ከጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሉተር እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ከፊት ሆኖ አይመራኝም፤ ወደ ፊት ይገፋኛል እንጂ። የራሴ ድርጊቶች አለቃ አይደለሁም። አርፌ በሰላም ብኖር ደስ በተሰኘሁ፤ ነገር ግን ወደ ብጥብጦችና አብዮቶች መሃል እወረወራለሁ።”-D’Aubigné, b. 5, ch. 2። አሁን ወደ ፉክክሩ ሊገፋፋ ያለበት ጊዜ ነበር። GCAmh 95.4

የሮም ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ፀጋ የንግድ ልውውጥ አካሂዳበታለች። የገንዘብ ለዋጮች ገበታዎች [ማቴ 21÷12] ከመሰዊያዎችዋ አጠገብ ተደርድረው፣ አየሩ በገዥዎችና በሻጮች ጫጫታ ተሞልቶ ነበር። የቅዱስ ጴጥሮስን ቤተ ክርስቲያን በሮም ለመሥራት በሚል ምክንያት ገንዘብ ለማሰባሰብ ሲባል የኃጢአት ይቅርታ [ቲኬቶች] በገንዘብ ይሸጡ ዘንድ በሊቀ-ጳጳሱ ስልጣን ለግብይት በግልጽ ቀርበው ነበር። በኃጢአት ደመወዝ የማዕዘን ድንጋይ ተጥሎ፣ ፣ ለወንጀል በተከፈለ ዋጋ፣ እግዚአብሔር ይመለክበት ዘንድ ቤተ መቅደስ ሊሰራ ነበር። ነገር ግን ለሮም ግዝፈት የተነደፈው መንገድ ለስልጣንዋና ለታላቅነትዋ ገዳይ የሆነ ጉዳት ተንኳሽ ሆነ። ቆራጥና እጅግ ውጤታማ የሆኑትን የጳጳሳዊ ሥርዓት ጠላቶች ያስነሳው፣ የጳጳሳዊውን ዙፋን ወዳነጋነገው፣ ባለሶስት ኮከቡን የሊቀ-ጳጳሱን ዘውድ ከጭንቅላቱ ላይ ወዳንሸራተተው ጦርነት እንዲያመራ ያደረገው ይህ ነበር። GCAmh 95.5

በጀርመን አገር የኃጢአት ስርየትን [ቲኬቶች] እንዲሸጥ በሕግ ተሹሞ የነበረው ስሙ ቴትዘል የሚባል ሰው በሕብረተሰብና በእግዚአብሔር ሕግ ላይ እጅግ ወራዳ ተግባራትን እንደፈፀመ ክስ የቀረበበት ሰው ነበር። ነገር ግን የሚገባው ቅጣት ሳይጣልበት የሊቀ-ጳጳሱን ገንዘብ የመሰብሰብና ሌሎች ቅንነት የጎደላቸው ንድፈ-ሥራዎችን እንዲያስፋፋ ተቀጠረ። አፍጥጠው የወጡ ውሸቶችን በታላቅ ድፍረት በመደጋገም፣ ያልተማረ፣ ነገሮችን አምኖ ለመቀበል ዝግጁ የሆነና በአጉል አምልኮ የሚያምን ሕዝብን ለማታለል ግሩም አፈ-ታሪኮችን (ተረቶችን) ይናገር ነበር። የእግዚአብሔር ቃል በውስጣቸው ቢኖር ኖሮ እንደዚያ ባልታለሉም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የተደበቀው እነርሱን በጳጳሳዊ ስልጣን ቁጥጥር ስር በማድረግ የአልጠግብ-ባይ መሪዎችን ስልጣንና ኃይል ለማስፋት ነበር። (See John C. L. Gieseler, A Compendium of Ecclesiastical History, per. 4, sec. 1, par. 5)። GCAmh 96.1

ቴትዘል ወደ አንድ ከተማ ሲገባ፣ መልክተኛው በፊቱ እየሄደ፣ “የእግዚአብሔር እና የቅዱስ አባታችን [የሊቀ-ጳጳሱ] ፀጋ በደጃፋችሁ ናት” እያለ ይጮህ ነበር።-D’Aubigné, b. 3, ch.1። ሕዝቡም ይህንን አስመሳይ የስድብ ሰው፣ ከሰማይ ወደ እነርሱ የወረደ፣ እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነ አድርገው ይቀበሉት ነበር። አስከፊው ህገ-ወጥ ልውውጥ በቤተ ክርስቲያን ይዘጋጅና ቴትዘል ወደ መድረክ ወጥቶ ኃጢአትን የማስተሰርየት ሽያጭ [ቲኬቶች] በእግዚአብሔር ከተሰጡ ስጦታዎች ሁሉ በላይ እንደሆነ በመናገር ምስጋና ያቀርባል። የይቅርታ የምስክር ወረቀቶቹን የገዛ፣ ወደፊት ሊሰራው ካሰበው ኃጢአት ሁሉ ነፃ እንደሚያደርገው፣ በተጨማሪም “ንስሐ መግባት እንኳ የግድ አስፈላጊ እንዳልሆነ” ያውጅ ነበር። ከዚያም በላይ፣ የሚያድለው የኃጢአት ይቅርታ በሕይወት ያሉትን ብቻ ሳይሆን የሞቱትን እንደሚያድን ለአድማጮቹ በመተረክ፤ ለሞተው ሰው የተከፈለችው ሳንቲም በደረቱ ሥር ባቃጨለችበት ቅጽበት በጊዜያዊ [ማሰቃያ] ስፍራው (purgatory) የነበረች ነፍሱ ወደ ሰማይ ጉዞዋን ታቀናለች ይል ነበር። (See K. R. Hagenbach, History of the Reformation, vol. 1, ገጽ 96)። GCAmh 96.2

ስምዖን ማጉስ የሐዋርያትን ተዓምራት የመሥራት ኃይል ለመግዛት በጠየቀበት ጊዜ ጴጥሮስ ያለው እንዲህ ነበር፦ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ” [የሐዋ ሥራ 8÷20]። የቴትዘል አቅርቦት ግን በጓጉ ሺዎች ዘንድ ተቀባይነት አገኘ። ብርና ወርቅ ወደ ግምጃ ቤቱ ጎረፈ። ንስሐ መግባትን፣ እምነትን እንዲሁም ኃጢአትን ለመቋቋምና ለማሸነፍ ትጉህ ጥረትን ከሚጠይቅ ይልቅ በገንዘብ መገዛት የሚችል ድነት በቀላሉ የሚገኝ ነበር። GCAmh 96.3

የኃጢአት ማስተሰርያ [ሽያጭ] አስተምህሮ በሮማ ቤተ ክርስቲያን ባሉ የተማሩና ሐይማኖተኛ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። ከምክንያትና ከመገለጥ ጋር እጅግ ተፃራሪ በሆኑ የአስመሳይነት ተግባራት የማያምኑ ብዙ ሰዎች ነበሩ። በዚህ የኃጢአት ንግድ ላይ ድምጹን ያሰማ ዘንድ የደፈረ አንድም የቤተ ክርስቲያን መሪ አልነበረም፤ የሰዎች አዕምሮ ግን መረበሽና ረፍት ማጣት ይታይበት ጀምሮ ነበር፤ ለቤተ ክርስቲያኑ መንጻት ሲል እግዚአብሔር በሆነ መሳሪያ በኩል ሊሰራ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችል እንደሁ ብለው ብዙዎች በጥልቅ ፍላጎት ይጠይቁ ነበር። GCAmh 97.1

ሉተር አሁንም ድረስ ፈጽሞ ዝንፍ የማይል የጳጳሳዊ ሥርዓት ደጋፊ ቢሆንም እንኳ የኃጢአት ማስተሰርየት ሥራ አጫፋሪዎች በነበራቸው በስድብ የተሞሉ ግምታዊ አስተሳሰቦች ግን በታላቅ ድንጋጤ ይሞላ ነበር። የራሱ ቤተ ክርስቲያን አባላት የሆኑ ብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የምስክር ወረቀት ገዝተው ነበር፤ ከልባቸው ተፀፅተው፣ ሊለወጡ ፍላጎት ስለነበራቸው ሳይሆን የኃጢአት ይቅርታ የምስክር ወረቀት በመግዛታቸው ስርየትን ያገኙ ዘንድ ተስፋ አድርገው ብዙም ሳይቆዩ ወደ ፓስተራቸው እየመጡ የተለያየ ኃጢአታቸውን መናዘዝ ጀመሩ። ሉተር ስርየት (ፍትሐት) እንደማይፈጽምላቸው ከነገራቸው በኋላ፣ ኃጢአታቸውን ተናዘው ሕይወታቸውን የማያድሱ ከሆነ በኃጢአታቸው እንደሚጠፉ አስጠነቀቃቸው። በታላቅ ግራ መጋባት ውስጥ ሆነው ወደ ቴትዘል በመመለስ እርሱ የሰጣቸውን የስርየት የምስክር ወረቀት የንስሐ አባቱ አልቀበልም እንዳለ ስሞታ በማቅረብ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ በድፍረት ብራቸው እንዲመለስላቸው ጥያቄ አቀረቡ። መነኩሴው በንዴት ተንቀጠቀጠ፣ እጅግ ዘግናኝ የሆኑ እርግማኖችን እያዥጎደጎደ፣ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ እሳት እያስነደደ “ፈጽመው ቅዱስ የሆኑትን የርሱን የስርየት ቲኬቶች ለመገዳደር የሚደፍሩትን መናፍቃን ያቃጥል ዘንድ” በሊቀ-ጳጳሱ እንደታዘዘ አወጀ።-D’Aubigné, b. 3, ch. 4። GCAmh 97.2

በዚህ ጊዜ እንደ የእውነት ተጋዳይ ሆኖ ሉተር ሥራውን በድፍረት ተያያዘው። ልባዊና ጠንከር ያለ የማስጠንቀቂያ ድምጹ ከመድረክ ይሰማ ነበር። የኃጢአትን አስከፊ ባህርይ በሕዝቡ ፊት በመግለጽ ሰው በራሱ ሥራ የኃጢአትን ኩነኔነት ሊቀንስ ወይም ከቅጣቱ ሊያመልጥ ፈጽሞ የማይቻለው እንደሆነ አስተማረ። ወደ እግዚአብሔር ንስሐ ከመግባትና በክርስቶስ ከማመን በስተቀር ኃጢአተኛውን ሊያድነው የሚችል ምንም ነገር የለም። የክርስቶስ ፀጋ ሊገዛ አይችልም፤ የነጻ ስጦታ ነው። የስርየት [የምስክር ወረቀቶቹን] ሕዝቡ እንዳይገዙ፤ ነገር ግን በእምነት ወደ ተሰቀለው አዳኝ እንዲመለከቱ መከራቸው። ድነትን በራሱ ለማግኘት ያለፈበትን፣ ራሱን በማዋረድና የንስሐ መግቢያ ቅጣት በማከናወን በከንቱ የደከመበትን ተሞክሮውን በማውሳት ራሱን ከመመልከት አይኑን አንስቶ በክርስቶስ ሲያምን ሰላምና ደስታ እንዳገኘ ለሚያዳምጡት አረጋገጠላቸው። GCAmh 97.3

ቴትዘል ንግዱንና የረከሰ አስመሳይነቱን ቀጥሎ ሳለ እነዚህን በአደባባይ የሚፈፀሙ አግባብነት የሌላቸው ተግባራት በተሻለና በተሳካ ሁኔታ ይቃወም ዘንድ ሉተር ወሰነ። ይህንን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ብዙም ሳይቆይ ተፈጠረ። የዊተንበርግ የግንብ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጥንታዊ የሞቱ ቅዱሳን ሐውልቶችን የያዘ ነበር፤ በተወሰኑ የበዓል ቀናት ሰዎች እንዲጎበኟቸው ይደረግ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ቤተ ክርስቲያንዋን ለሚጎበኙና ኃጢአታቸውን ለሚናዘዙ ሁሉ ሙሉ የኃጢአት ስርየት ይሰጣቸው ነበርና በእነዚህ የበዓል ቀናት ብዙ ሕዝብ ወደዚህ ስፍራ ይሰበሰብ ነበር። ከሁሉም የሚበልጠው ክብረ በዓል “የሁሉም ቅዱሳን” በዓል እየተቃረበ ነበር። በዓሉ አንድ ቀን ሲቀረው ሉተር ወደዚያ ስፍራ የሚጎርፈውን ሕዝብ ተቀላቅሎ ከሄደ በኋላ የኃጢአት ይቅርታ [ሽያጭን] አስተምህሮን የሚነቅፉ፣ የጥናት ውጤቶቹ የነበሩትን፣ ዘጠና አምስት ነጥቦችን በሮቹ ላይ ለጠፋቸው። የነዚህን ጽሁፎች እውነትነት ለማስረዳት በሚቀጥለው ቀን በዩኒቨርሲቲው ለመገኘት ፈቃደኝነቱን ገለፀ፤ ለነዚህ ነጥቦች ተቃውሞ ለማሰማት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲመጡ፣ ሃሳቦቹ እውነት እንደሆኑ እንደሚያረጋግጥም ተናገረ። GCAmh 97.4

ያቀረባቸው ነጥቦች በሁሉም ዘንድ ትኩረትን መሳብ ቻሉ። በሁሉም አቅጣጫ ተነበቡ፤ ተደገሙ፤ ተደጋገሙ። በዩኒቨርሲቲውና በመላ ከተማዋ ታላቅ ሽብር ተፈጠረ። በእነዚህ ጽሁፎች ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ስልጣን፣ ቅጣቱንም የማስቀረት ሥራ ለሊቀ-ጳጳሱም ሆነ ለማንም ሰው ያልተሰጠ እንደሆነ ተመልክቶ ነበር። በሰዎች መሰረተ ቢስ አስተሳሰብ ተመስርቶ ገንዘብ ለመሰብሰብ የተቀናጀ፣ የሐሰት ማታለያዎቹን የሚያምኑ ነፍሳትን ለማጥፋት የሚጠቀምበት የሰይጣን የማታለያ መሳሪያ፣ ሁሉም ከእውነት የራቀ የማጭበርበሪያ ንድፍ እንደሆነ ያሳይ ነበር። የክርስቶስ ወንጌል ለቤተ ክርስቲያን ተወዳዳሪ የሌለው ቅርስዋ እንደሆነ በግልጽ በማመልከት በንስሐና በእምነት ለሚሹት ሁሉ፣ በወንጌሉ ውስጥ የተገለፀው የእግዚአብሔር ፀጋ በነፃ የተሰጠ እንደሆነ ያትት ነበር። GCAmh 98.1

የሉተር ጥናታዊ ፅሁፍ ውይይት የጋበዘ ቢሆንም ማንም ደፍሮ የመከራከር ጥያቄውን የተቀበለ አልነበረም። ያነሳቸው ጥያቄዎች በጥቂት ቀናት ጀርመንን ሲያዳርሱ፣ በጥቂት ሳምንታት ደግሞ በመላው የክርስትናው ዓለም አቃጨሉ። በቤተ ክርስቲያን የተንሰራፋውን አሰቃቂ ኃጢአት በማየት እጅግ ያዝኑ የነበሩ፣ ከመባባስ ለመግታት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያላወቁ፣ ታማኝ ሮማውያን እነዚህን ሃሳቦች በታላቅ ደስታ አነበቧቸው፤ በውስጣቸውም የእግዚአብሔር ድምጽ እንዳለበት አስተዋሉ። ከሮም እምብርት የሚወጣውን፣ በፍጥነት እየሰፋ የሚሄደውን የከፋ የኃጢአት ማዕበል ለመግታት እግዚአብሔር በቸርነቱ እጁን እንደሰደደ ተሰማቸው። በሚያሳልፈው ውሳኔ ላይ ይግባኝ የማለትን መብት የማይሰጥ እብሪተኛ ኃይልን የሚያስቆም በመገኘቱ ዳኞችና ልዑላን በስውር ሐሴት አደረጉ። GCAmh 98.2

ነገር ግን ኃጢአት አፍቃሪውና በመላምት (በአጉል እምነት) የተያዘው ሕዝብ፣ ፍርሃቱ እንዲቀዘቅዝ ያደርጉት የነበሩት አስመሳይ ማጭበርበሪያዎች ተጠራርገው ሲወሰዱ በታላቅ ድንጋጤ ተዋጠ። ወንጀልን የማጽደቅ ተግባራቸው የተቋረጠባቸው፣ ትርፋቸው አደጋ ላይ መውደቁን የተመለከቱ በማጭበርበር የተካኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተቆጡ፣ አስመሳይ ባህሪያቸውን ደግፈው ለማቆየት ተንቀሳቀሱ። የተሐድሶ አራማጁ የሚገናኛቸው መራር ወንጃዮች አሉት። አንዳንዶቹ በጥድፊያና ቅጽበታዊ በሆነ ስሜት ያደረገው ነው በማለት ከሰሱት። ሌሎች ደግሞ በመላምት እምነት ወንጀል በመክሰስ ከእብሪቱና ከግትርነቱ የተነሳ እንጂ በእግዚአብሔር ታዞ እንዳልሆነ ተናገሩ። መልስ ሲሰጥም፣ “የሆነ ኩራት መልክ ሳይታይበትና ጥልን ይቀሰቅሳል ተብሎ ክስ ሳይቀርብበት አዲስ ሃሳብ የሚያመጣ እንደሌለ ማን የማያውቅ አለ? ክርስቶስና ሁሉም ሰማዕታት የተገደሉት ለምንድን ነው? የኖሩበትን ዘመን ጥበብ በእብሪት የሚያንቋሽሹ ሆነው ስለታዩ፤ የድሮ አስተሳሰቦችን ደጋፊዎችን መጀመሪያ ሳያማክሩ አዲስ እውነቶች ይዘው ብቅ ስላሉ ነው” አለ። በመቀጠልም፦ “እኔ እያደረግሁት ያለሁት በእግዚአብሔር ምክር እንጂ በሰው ጥበብ የሚተገበር አይደለም። ሥራው የእግዚአብሔር ከሆነ ማን ሊያስቆመው ይችላል? ካልሆነም ደግሞ ማን ወደ ፊት ሊገፋው ይችላል? የእኔ ፈቃድ ሳይሆን፣ የእነርሱም ሳይሆን፣ የኛም ሳይሆን፣ በሰማይ ያለህ ቅዱስ አባት! - የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ።-Ibid., b. 3, ch. 6። GCAmh 98.3

ሉተር ሥራውን ይጀምር ዘንድ የተነሳሳው በእግዚአብሔር መንፈስ ቢሆንም ያለ ከባድ ተጋድሎ ግን ወደፊት ያራምደው ዘንድ የሚቻል አልነበረም። የጠላቶቹ ነቀፌታ፣ ዓላማውን አጣሞ የመወከል፣ ትክክለኛ ያልሆነ ተንኮለኛ ሸሮችን በባህርይውና በሃሳቦቹ ላይ የመለጠፍ ድርጊታቸው እንደሚያቃቅት ጎርፍ ያህል ተወረወረበት። ያለ ውጤትም አልቀሩም። በቤተ ክርስቲያንና በትምህርት ቤት ያሉ መሪዎች በተሐድሶ ጥረቱ ላይ በደስታ እንደሚተባበሩ እርግጠኛ ሆኖ ነበር። በከፍተኛ ቦታ ላይ የተቀመጡት ሰዎች የሚሰጡት ማበረታቻ ደስታና ተስፋ ችሮት ነበር። በብርሐን የተሞላ የቤተ ክርስቲያን ቀን ሊጀምር እንደሆነ በመጠባበቅ በደስታ ወደፊት ይመለከት ነበር። ነገር ግን ማበረታቻው ወደ ነቀፋ፣ ውግዘት ተቀይሯል። የቤተ ክርስቲያንም ሆነ የመንግሥት ታላላቅ ባለስልጣናት ስለጥናቱ እውነትነት አምነው ነበር፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ እነዚህን እውነቶች መቀበል ታላላቅ ለውጦችን እንደሚያስከትል ተረዱ። ሕዝቡ እንዲማርና እንዲታደስ ማድረግ፣ መላ የሮምን ስልጣን ማጣጣል፣ ወደ ጎተራዋ የሚፈሱትን በሺዎች የሚቆጠሩ ጅረቶች ማቋረጥ፣ ብሎም የጳጳሳዊ መሪዎችን የአባካኝነትና የቅንጦት አንዋንዋር በከፍተኛ ደረጃ መቀልበስ ማለት ነው። በተጨማሪም ሃላፊነት የሚሰማቸው ፍጡራን እንደሆኑ እንዲያስቡና በተግባርም እንዲገልጡ፣ ለድነታቸውም ወደ ክርስቶስ ብቻ እንዲመለከቱ ሰዎችን ማስተማር፣ የሊቀ-ጳጳሱን ዙፋን መገልበጥ ቀጥሎም የራሳቸውን [የሹሞቹን] ስልጣን መደምሰስ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን እውቀት እምቢ አሉ፤ ወደ ብርሐን ያመጣቸው ዘንድ የላከውን ሰው በመቃወምም ክርስቶስንና እውነትን ይፃረሩ ዘንድ ተሰለፉ። GCAmh 99.1

በዓለም ተወዳዳሪ የሌላቸውን ኃይላት ተቃውሞ የቆመ አንድ ሰው እርሱ ብቻ ነውና ሉተር ራሱን ሲመለከት በፍርሃት ተርበደበደ። የቤተ ክርስቲያንን ስልጣን ለመቃወም በርግጥም በእግዚአብሔር ስለመመራቱ አንዳንድ ጊዜ ይጠራጠር ነበር። “የምድር ነገሥታትና ዓለም ሁሉ በፊቱ የሚንቀጠቀጡለትን የሊቀ-ጳጳሱን ግርማዊነት እቃወም ዘንድ”፣ አለ ሲጽፍ፣ “እኔ ማን ነበርሁ?” “በነዚያ ሁለት ዓመታት እንዴት እንደተሰቃየሁ፣ እንዴት እንደተከፋሁ ይባስ ብሎም እንዴት ወደ ተስፋ መቁረጥ አዘቅት በተደጋጋሚ እንደገባሁ ማንም ሊያውቅልኝ አይችልም።”-Ibid., b. 3, ch. 6። ፈጽሞ ተስፋ-ቢስ ይሆን ዘንድ ግን አልተተወም ነበር። የሰው እርዳታ ሲቀር ወደ እግዚአብሔር ብቻ ተመለከተ፤ ሁሉን በሁሉ በሆነው ኃያል ክንድ ፍጹም ከአደጋ ነፃ ሆኖ መደገፍ እንደሚችልም ተማረ። GCAmh 99.2

ሉተር የተሐድሶው አጋር ለሆነ ሰው ሲጽፍ፦ “በማጥናት ወይም በአዕምሮ ብስለታችን (በማገናዘብ ችሎታችን) መጽሐፍ ቅዱስን ልንረዳው አይቻለንም። ስለዚህ የመጀመሪያው ሥራህ መሆን ያለበት በፀሎት መጀመር ነው። ቃሉን በትክክል መረዳት ትችል ዘንድ በበዛ ምህረቱ እግዚአብሔር እንዲያስችልህ አጥብቀህ መለመን ይገባሃል። ቃሉን ከፃፈው ከራሱ በቀር ያንን ቃል የሚተረጉም ሌላ ማንም የለም። ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ [ዮሐ 6÷45] በማለት ራሱ ተናግሯል። ከጥናትህና ከማስተዋል ችሎታህ ምንም አትጠብቅ፤ እንዲሁ በእግዚአብሔር፣ በመንፈሱም ምሪት ታመን። ይህንን ፈትኖ የደረሰበት ሰው ሲነግርህ እመን።” ብሏል።-Ibid., b. 3, ch. 7። ለዚህ ዘመን የሚያስፈልጉትን የከበሩ እውነቶች ለሌሎች ያዳርሱ ዘንድ እግዚአብሔር እንደጠራቸው ለሚሰማቸው ሁሉ እዚህ ላይ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት አለ። እነዚህ እውነቶች የሰይጣንንና እርሱ የሸረባቸውን ተረቶች የሚወዱትን ሰዎች ጥላቻ መቀስቀሳቸው አይቀርም። ከጨለማ ኃይላት ጋር በሚደረገው ትንቅንቅ ከማስተዋል ችሎታ ጥንካሬና ከሰው ጥበብ የበለጠ አንዳች የሚያስፈልግ ነገር አለ። GCAmh 99.3

ጠላቶቹ ስለ ወግና ባህል ሲሟገቱ፣ ስለ ሊቀ-ጳጳሱ ማረጋገጫዎችና ስለ ስልጣኑ ሲናገሩ፣ ሉተር የተጋፈጣቸው በመጽሐፍ ቅዱስና፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነበር። እዚህ ውስጥ መልስ ሊሰጡባቸው ያልቻሉአቸው የመከራከሪያ ነጥቦች ነበሩ፤ በመሆኑም የወግ አጥባቂነትና የአጉል እምነት ባሪያ የነበሩ ሁሉ፣ አይሁዳውያን የክርስቶስን ደም ለማፍሰስ እንዳጨበጨቡ እነርሱም የሉተር ደም እንዲፈስ ጮሁ። “እርሱ መናፍቅ ነው” አሉ የሮም ተቆርቋሪዎች፤ “ተጨማሪ አንድ ሰዓት በሕይወት እንዲቆይ መፍቀድ ኃጢአት ነው!” “ወንጀለኛ ወደሚገደልበት በፍጥነት መወሰድ ይገባዋል!”-Ibid., b. 3, ch. 9። ሉተር ግን የንዴታቸው ተጠቂ አልሆነም። እግዚአብሔር እንዲሰራው የሚፈልገው ሥራ ነበርና የሰማይ መላዕክት ይጠብቁት ዘንድ ተላኩ። ነገር ግን ከሉተር የከበረውን እውነት የተቀበሉ ብዙዎች የሰይጣን ቁጣ ቁጫኝ መውጫ ተደረጉ፤ ለእውነት ሲሉ ያለፍርሃት የግርፋትና የሞት ሰለባ ሆኑ። GCAmh 100.1

የሉተር ትምህርቶች በመላው ጀርመን የሚገኙ አስተዋይ ሰዎችን ሁሉ መማረክ ቻሉ። ከስብከቶቹና ከፅሁፎቹ የሚወጣው ጮራ ሽዎችን እየቀሰቀሰ በብርሐን አጎናፀፈ። ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ጊዜ ተጠፍራበት የነበረው የሞተ ወግ አጥባቂነት እየለቀቀ በቦታው ሕያው የሆነ እምነት ይተካ ጀመር። በሮማዊነት የአጉል አምልኮ ላይ ብዙዎች በየቀኑ አመኔታቸው እየተሸረሸረ ነበር። የጭፍን ጥላቻ መሰናክሎች እየተወገዱ ነበር። ሉተር እያንዳንዱን አስተምህሮና መጠይቅ የመረመረበት የእግዚአብሔር ቃል በሁለት ወገን እንደተሳለ ሰይፍ የሕዝቡን ልብ ይሰነጥቅ ነበር። በሁሉም ስፍራ ለመንፈሳዊ እድገት ፍላጎት መነቃቃት ይታይ ነበር። ለብዙ ዘመናት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ለጽድቅ መራብና መጠማት ይንፀባረቅ ነበር። ለረጅም ጊዜ ወደ ፍጡር ስነ-ሥርዓትና የምድራዊ አማላጆች ሲመራ የኖረው የሰዎች አይን፣ በፀፀትና በእምነት ወደ ተሰቀለው፣ ወደ ክርስቶስ መመለስ ጀመረ። GCAmh 100.2

ይህ መጠነ ሰፊ መነቃቃት የጳጳሳዊ ሥርዓት ባለስልጣናትን ፍራቻ ይልቅ አባባሰው። ሉተር ለቀረበበት የኑፋቄ ክስ መልስ ይሰጥ ዘንድ ወደ ሮም እንዲሄድ መጥሪያ ደረሰው። ትዕዛዙ ጓደኞቹን በድንጋጤ ሞላቸው። የክርስቶስ ሰማዕታትን ደም ጠጥታ በሰከረችው፣ በምግባረ-ብልሹዋ ከተማ የሚጋረጥበት አደጋ ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ወደ ሮም የመሄዱን ጉዳይ አጥብቀው በመቃወም በዚያው በጀርመን እንዳለ ምርመራ እንዲካሄድበት ጠየቁ። GCAmh 100.3

በመጨረሻ ይህ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ጉዳዩን የሚሰማ ልዑክ ሊቀ-ጳጳሱ ወከለ። ሊቀ-ጳጳሱ ለልዑኩ ባስተላለፋቸው መመሪያዎች ሉተር መናፍቅ ተብሎ ከወዲሁ እንደተወሰነበት ተናገረ። ስለዚህም ልዑኩ ሉተርን “በመወንጀል ያለምንም መዘግየት ራሱን እንዲያስረክብ” ማድረግ እንዳለበት ትዕዛዝ ተላለፈለት። በአቋሙ ፀንቶ ከቆመና ልዑኩ በአካል ሊይዘው ካልቻለ ደግሞ “በመላው ጀርመን አገር ህገ-ወጥ እንደሆነ እንዲያውጅበት፣ ከርሱ ጋር ቁርኝት ያላቸውን ያጠፋ፣ ይረግምና ከቤተ ክርስቲያን አባልነት ይሰርዝ ዘንድ” ስልጣን ተሰጠው። -Ibid., b. 4, ch. 2።በተጨማሪም የመጣውን ቸነፈራዊ ኑፋቄ ከስሩ መንግሎ ለመጣል ይቻል ዘንድ ሉተርንና ደጋፊዎቹን ይዞ ለሮም የበቀል እርምጃ ለማስረከብ ቸል ያለ፣ ከንጉሡ በስተቀር፣ በመንግሥት ወይም በቤተ ክርስቲያን ማንኛውንም ስልጣን የያዘም ቢሆን ከቤተ ክርስቲያን አባልነት እንዲያገለው ሊቀ-ጳጳሱ ለልዑኩ ትዕዛዝ አስተላለፈ። GCAmh 100.4

የጳጳሳዊ ሥርዓት እውነተኛ መንፈስ እዚህ ላይ ቁልጭ ብሎ ታየ። በፅሁፉ ውስጥ ቅንጣት የክርስትና መርህ፣ አንድ የተለመደ ፍትሐዊነት እንኳ አይታይም ነበር። ሉተር ከሮም እጅግ እርቆ ስለነበር ለማብራራት ወይም አቋሙን ለማስረዳት ዕድል አልነበረውም። ሆኖም ጉዳዩ ሳይመረመር መናፍቅ እንደሆነ በደፈናው ታወጀበት፤ በአንድ ቀን ማሳሰቢያ ተሰጥቶት፣ በዛው ቀን ተወንጅሎ፣ ተፈርዶበት ተኮነነ። ይህ ሁሉ የተደረገው፣ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በመንግሥት ላይ ብቸኛ ጠቅላይ-የበላይ የሆነ፣ ስህተት ይሰራ ዘንድ የማይቻለው ስልጣን፣ ቅዱስ አባት፣ አድርጎ ራሱን በሾመው አማካይነት ነበር። GCAmh 101.1

ሉተር የሚያጽናና እና የሚመክር እውነተኛ ጓደኛ ባስፈለገው በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሜላንክተንን ወደ ዊተንበርግ ላከለት። ገና በዕድሜ ወጣት፣ ትሁትና ዓይናፋር ባህርይ የነበረው የሜላንክተን ሚዛናዊ አስተሳሰብ፣ ጥልቅ እውቀትና የሚያሸንፈው አንደበተ ርቱዕነቱ ከባህርይው ንፅህናና ቀጥተኛነት ተዳምሮ የሁሉንም አድናቆትና ክብር አትርፎለት ነበር። የክህሎቶቹ አንፀባራቂነት ከባህርይው ጨዋነት ልቆ አይታይም ነበር። ብዙም ሳይቆይ የወንጌሉ ልባዊ ደቀ-መዝሙር ሆነ፤ የሉተርም ታማኝ ጓደኛና፣ ወሳኝ ደጋፊ ሆነ፤ ጨዋነቱ፣ ጥንቃቄውና ፍንክች አይበሌነቱ የሉተር ድፍረትና ጉልበት አሟይ ኃይል ሆነ። የእነርሱ ተቀናጅቶ መሥራት ለተሐድሶው ጥንካሬ ጨመረለት፤ ለሉተርም ታላቅ የመጽናኛ ምንጭ ሆነለት። GCAmh 101.2

የችሎቱ ቦታ አውግስበርግ እንዲሆን ተወስኖ፣ የተሐድሶ አራማጁ ወደዚያ ስፍራ ለመሄድ ጉዞውን በእግር ጀመረ። የምር የሆኑ ፍራቻዎች በእርሱ ዙሪያ ይነገሩ ነበር። በመንገድ ላይ ተይዞ እንደሚገደል ግልጽ ማስፈራሪያ ተሰንዝሮበት ስለነበር ወደዚያ ስፍራ በእግር እንዳይሄድ ጓደኞቹ ለመኑት። ዊተንበርግን ለቆ፣ ለተወሰነ ጊዜ ደህንነቱን በደስታ ሊጠብቁለት ወደሚችሉ፣ ወደ እነርሱ ሄዶ እንዲቆይ ጭምር ለመኑት። ነገር ግን እግዚአብሔር ካስቀመጠው ስፍራ (ኃላፊነት) ይለቅ ዘንድ አልተቻለውም። ማዕበሎች ቢመቱት እንኳ እውነትን ይጠብቅ ዘንድ በታማኝነት መቀጠል ይኖርበታል፤ ንግግሩ፦ “እኔ ልክ እንደ ኤርሚያስ የጥልና የንትርክ ሰው ነኝ፤ ሆኖም ማስፈራሪያቸውን የበለጠ በጨመሩ ቁጥር ደስታዬን ያበዙታል …. ክብሬንና መልካም ስሜን ቀዳደው ጥለውታል። የቀረኝ የተቆሳቆለው አካሌ ነው፤ ይውሰዱት፤ ሕይወቴን በጥቂት ሰዓታት ያሳጥሩታል። ነፍሴን እንደሆነ ግን አያገኟትም። የክርስቶስን ቃል ለዓለም ያደርስ ዘንድ የቆረጠ እርሱ ሞትን በእያንዳንዷ ሰዓት መጠበቅ አለበት።”-Ibid., b. 4, ch. 4። GCAmh 101.3

የሉተር አውግስበርግ የመድረስ ዜና ለጳጳሳዊው ልዑክ ታላቅ እርካታ ሆነ፤ የዓለምን ትኩረት የሳበው አስቸጋሪ መናፍቅ በሮም ስልጣን ስር የወደቀ መሰለ፤ ማምለጥ እንደሌለበትም ልዑኩ ወሰነ። የተሐድሶ አራማጁ የይለፍ ለራሱ ማመቻቸት አልቻለም ነበር፤ በልዑኩ ፊት የይለፍ ሳይዝ እንዳይቀርብ ጓደኞቹ አስጠንቅቀውት ራሳቸው ከንጉሠ ነገሥቱ ሊያመጡለት ወሰኑ። የልዑኩ ሃሳብ፣ ከቻለ ሉተር አቋሙን እንዲክድ ማድረግ፤ ካልሆነ ደግሞ ወደ ሮም እንዲወሰድ በማድረግ የኸስንና የጀሮምን ዕጣ ፈንታ ማስጎንጨት ነበር። ስለሆነም ምሕረት ያደርግንኛል ብሎ እንዲያምንና፤ ያለ የይለፍ እንዲገኝ በወኪሎቹ አማካኝነት ሉተርን ለማግባባት ጣረ። የተሐድሶ አራማጁ ይህን ሃሳብ አጥብቆ ተቃወመው። የንጉሠ ነገሥቱ ጥበቃ እንዳለው የሚያረጋግጥለት ወረቀት ከያዘ በኋላ ብቻ ነበር በሊቀ-ጳጳሱ እንደራሴ ፊት የቀረበው። GCAmh 101.4

በመርሃ-ግብር ደረጃ ሮማውያኑ ትሁት መስለው በመቅረብ ሉተርን ለማሸነፍ ወስነው ነበር። ልዑኩ ከእርሱ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ከፍተኛ የሆነ ወዳጅነትን አንፀባርቆ ነበር። ነገር ግን ሉተር ያለ አንዳች ማመንታት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ስልጣን እጁን እንዲሰጥ፤ ያለምንም ክርክር ወይም ጥያቄ እያንዳንዱን ጉዳይ (ነጥብ) እንዲተው ጠየቀ። እየመረመረው የነበረውን ሰው ባህርይ በትክክል እንዳልገመተ የሚያሳይ ነበር። ሉተርም በመልሱ ለቤተክርስቲያንዋ ያለውን አክብሮት በመግለፅ ለእውነት ያለውን ፅኑ ፍላጎት፣ ከአስተማረው ውስጥም አንዳች የተቃውሞ ነገር ቢኖር ሁሉንም ለመመለስ ያለውን ዝግጁነት፣ እንዲሁም በአስተምህሮዎቹ ላይ ውሳኔ ይሰጡ ዘንድ ለጥቂት አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች ለማስረከብ እንደሚስማማ ተናገረ። ስህተት እንደተገኘበት ሳያረጋግጥ ጥፋተኛ መሆኑን እንዲናዘዝ የሚጠይቀውን የሊቀ ጳጳሱን ሹም አካሄድ ግን ተቃወመ። GCAmh 102.1

የመጣው ብቸኛ የአጸፋ መልስ፦ “[በፊት የነበረኝን አቋም] ትቻለሁ በል፣ ትቻለሁ በል” የሚል ነበር። የተሐድሶ አራማጁም አቋሙን በመጽሐፍ ቅዱስ የተደገፈ መሆኑን በማመልከት እውነቱን እንደማይክድ ተናገረ። ሉተር ላቀረበው ክርክር የሚመልሰው ሲያጣ፣ ለተሐድሶ አራማጁ የመናገር ዕድል ሳይሰጠው የነቀፋ፣ የሹፈትና የሽንገላ መዓት፣ ከወግና ከባህል እንዲሁም ከአባቶች አባባል ጋር እየቀላቀለ የነገር ማዕበል አወረደበት። ስብሰባውን መቀጠሉ ፍሬ ቢስ እንደሆነ በመመልከት፣ ከልብ የመነጨ ባይሆንም ሉተር መልሱን በጽሁፍ እንዲያቀርብ በመጨረሻ ተፈቀደለት። GCAmh 102.2

“ይህንን በማድረግ” አለ ሉተር ለአንድ ጓደኛው ሲጽፍ፦ “ተጨቋኙ እጥፍ አትራፊ ይሆናል። አንደኛ፣ የተፃፈው ነገር ሌሎች ፍርድ ይሰጡበት ዘንድ መቅረብ ይችላል፤ ሁለተኛ፣ እብሪተኛና ለፍላፊ፣ ማን አለብኝ የሚለውን ሰው ፍርሃት በመጠቀም፣ ከተቻለም በህሊናው ላይ በመሥራት፣ እኔ ነኝ የበላይ በሚል ቋንቋ ሊያሸንፍህ በሚሞክረው ፈላጭ ቆራጭ ዘንድ ተፅዕኖ ለማሳደር የተሻለ ዕድል ይገኛል።”-Martyn, The Life and Times of Luther, ገጽ 271, 272። GCAmh 102.3

በሚቀጥለው ቃለ-ምልልስ ሉተር ግልጽ፣ እጥር ምጥን፣ ፈርጠም ያሉ፣ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተደገፉ አመለካከቶቹን አቀረበ። ይህንን ጽሁፍ ጮክ ብሎ ካነበበው በኋላ ለቤተ-ክህነት መሪው አስረከበው፤ ነገር ግን መሪው ወረቀቱን በንቀት ወደጎን በማሽቀንጠር የማይረቡ ቃላትና የእርባና ቢስ ጥቅሶች ጥርቅም እንደሆነ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ሉተር ሙሉ ለሙሉ ስሜቱ ተቀስቅሶ ጅንኑን የቤተ-ክህነት መሪ በራሱ ሜዳ - በቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችና ወጎች ላይ - በመገናኘት የነበሩትን ግምታዊ አስተሳሰቦች አንኮታኮተበት። GCAmh 102.4

የቤተ-ክህነት መሪው የሉተር ምክንያታዊነት (አመክንዮ) ሊመለስ የማይችል መሆኑን ሲረዳ ራሱን መቆጣጠር አቅቶት፣ በቁጣ ገንፍሎ “ጥፋተኛ ነኝ በል፤ ያለበለዚያ ጉዳይህን ያውቁ ዘንድ ሃላፊነት በተሰጣቸው ዳኞች ፊት ትቆም ዘንድ ወደ ሮም እልክሃለሁ። አንተንና የሚደግፉህን ከአባልነት አስወግዳችኋለሁ፤ ፊት የሚሰጡህን ሁሉ ከቤተ ክርስቲያንዋ አባርራቸዋለሁ” በማለት ተናገረ። በመጨረሻም የኩራትና የንዴት ቅላጼ ባለው ድምጽ፦ “ትቻለሁ በል፣ ያለዚያ ደግመህ አትምጣ” አለው።-D’Aubigné, London ed., b. 4, ch. 8። GCAmh 103.1

ጥፋተኛ ነኝ ብሎ የመመለስ ዕድል ከእርሱ እንደማይጠበቅ በሚገልጽ ሁኔታ ሉተር ከጓደኞቹ ጋር በፍጥነት ከዚያ ወጣ። የቤተ ክህነት መሪው ያቀደው ይህ አልነበረም። በኃይል አስፈራርቼ ሉተርን አንበረክከዋለሁ በማለት ራሱን ደልሎ ነበር። በዚህ ጊዜ ከደጋፊዎቹ ጋር ብቻውን የቀረው መሪ ያቀደው ሳይሆንለት በመቅረቱ እጅግ ቅር ተሰኝቶ አይኑ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ያማትር ነበር። GCAmh 103.2

በዚህ ገጠመኝ የሉተር ጥረቶች ያለ መልካም ውጤት አልቀሩም። ተሰብስቦ የነበረው ብዙ ሕዝብ ሁለቱን ሰዎች የማወዳደር ዕድል አግኝቶ ስለነበር በሁለቱ ሰዎች የተንፀባረቀውን መንፈስ ሕዝቡ በራሱ ልብ እንዲለው፤ በተጨማሪም የቋማቸው ጥንካሬና እውነትነት እንዲገነዘበው ማድረግ ተችሎ ነበር። እንዴት ያለ ልዩነት ነበር! የተሐድሶ አራማጁ ተራ፣ ትሁትና ከዓላማው የማይነቃነቅ ሆኖ በእግዚአብሔር ጥንካሬ የቆመ፤ እውነትን ከጎኑ ያሰለፈ ነበር፤ በአንጻሩ የሊቀ-ጳጳሱ ወኪል ራሱን ያዋደደ፣ ፈላጭ ቆራጭ፣ ጅንንና ሚዛናዊነት የጎደለው፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድስ እንኳ መከራከሪያ ያልጠቀሰ፤ ነገር ግን “ጥፋተኛነትህን አምነህ ተመለስ፤ ያለዚያ ወደ ሮም ተልከህ ቅጣትህን ትቀበላለህ” በሚል የጮኸ ነበር። GCAmh 103.3

ሉተር [እንዳይነካ] የሚያዝ የይለፍ ቢኖረውም ሮማውያኑ ግን ይዘው ለማሰር ሴራ እየጠነሰሱበት ነበር። በዚያ መቆየቱ የሚያመጣው ጥቅም እንደሌለና ሳይዘገይ ወደ ዊተንበርግ እንዲመለስ ጓደኞቹ ገፋፉት። ማከናወን የሚፈልጋቸው ነገሮችም በጥብቅ ሚስጥርነት በመያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ተስማሙ። በዚህም መሰረት ጎህ ከመቅደዱ በፊት አጥቢያ ዳኛው ካዘጋጀለት አንድ መንገድ ጠቋሚ ጋር ሆኖ በፈረስ ጉዞውን ጀመረ። መጥፎ ነገር ሊከሰት ይችላል በሚል ብዙ ፍርሃት፣ ፀጥ ባለው የከተማዋ ጨለማ መንገዶች በምስጢር ጉዞውን ቀጠለ። ንቁና ጨካኝ የነበሩት ጠላቶች ጥፋቱን እያቀዱለት ነበር። የተዘጋጀለትን ወጥመድ ማምለጥ ይችል ይሆን? እነዚያ ጊዜያት የጭንቀትና የልባዊ ፀሎት ጊዜያት ነበሩ። በከተማዋ ግንብ ወደ ትንሽ በር ደረሰ፤ ተከፈተችለትና ከመሪው ጋር ያለምንም መዘግየት አለፈ። ከከተማዋ ቅጥር በደህና ከወጡ በኋላ ኮብላዮቹ በፍጥነት ይገሰግሱ ጀመር፤ ወኪሉ ስለ ሉተር መሄድ ከመስማቱ በፊት፣ ሉተር አሳዳጆቹ ሊደርሱበት ከሚችሉበት ክልል ውጪ ሆኖ ነበር። ሰይጣንና ልዑካኑ ተሸነፉ። በቁጥጥራቸው ስር እንደሆነ የተማመኑት ሰው፣ ወፍ ከአዳኞችዋ ወጥመድ አፈትልካ እንደምትበር ከእጃቸው አመለጠ። GCAmh 103.4

የሉተርን ማምለጥ ዜና ሲሰማ የቤተ-ክህነት መሪው በግርምትና በንዴት ጦፈ። ይህንን የቤተ ክርስቲያን በጥባጭ፣ በጥበብና በፅናት በመያዝ ታላቅ ክብር ለመቀበል ቋምጦ ነበር። ተስፋው ሳይሆን ቀረ። ንዴቱን ለሳክሶኒው መራጭ (የሳክሶኒ ግዛት የሕዝብ ወኪል የሆነ) ለፍሬዴሪክ በፃፈው ደብዳቤ ላይ በማንፀባረቅ፣ ሉተርን አምርሮ በማውገዝ፣ ፍሬዴሪክ ሉተርን ይዞ ወደ ሮም እንዲልከው፣ ወይም ከሳክሶኒ ግዛት በኃይል እንዲያስወግደው ጠየቀ። GCAmh 103.5

ሉተር መከላከያውን ሲያቀርብ፣ ወኪሉ ወይም ሊቀ-ጳጳሱ ስህተቱን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያሳዩት ተገዳደራቸው። የእርሱ አስተምህሮዎች የእግዚአብሔርን ቃል የሚፃረሩ ሆነው ከተገኙ በእርግጠኝነት መሳሳቱን አምኖ እንደሚቀበል ቃል ገባ። ለእንደዚህ አይነት ቅዱስ ተልዕኮ ይሰቃይ ዘንድ የተገባው ሆኖ በመገኘቱ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረበ። GCAmh 104.1

መራጩ ስለ ተሐድሶ አስተምህሮዎች ገና ብዙም እውቀት አልነበረውም፤ ነገር ግን በሉተር ቃላት ግልጽነት፣ ተአማኒነትና ኃይል በመነካት የተሐድሶ አራማጁ ስህተት እንደተገኘበት እስኪረጋገጥ ድረስ ይጠብቀው ዘንድ ፍሬደሪክ ወሰነ። ለልዑኩ ጥያቄ መልስ ሲጽፍ እንዲህ አለ፦ “ዶ/ር ማርቲን በአውግስበርግ በፊትህ ቀርቦ ስለነበር እርካታ ሊሰማህ ይገባል። ጥፋተኛ እንደሆነ ሳታሳምነው፣ በደለኛ ነኝ ብሎ እንዲያምን ለማድረግ ትጥራለህ ብለን አልጠበቅንም ነበር። በእኛ ግዛት ስር ያሉ አንዳቸውም የተማሩ ሰዎች የማርቲን አስተምህሮ ለእግዚአብሔር ክብር የሌለው፣ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ወይም መናፍቃዊ ስለመሆኑ የነገሩን ነገር የለም፤ በመሆኑም ሉተርን ወደ ሮም የመላክ ወይም ከግዛቶቻችን የማባረር እርምጃን መቃወም ግድ ይሆንብናል።”-D’aubigné, b. 4, ch. 10። GCAmh 104.2

በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ውስጥ የስነ-ምግባር ገደቦች ውድቀት እንደተንሰራፋ መራጩ አስተዋለ። ታላቅ የተሐድሶ ሥራ ያስፈልግ ነበር። ሰዎች ለእግዚአብሔር መጠይቅ እውቅና ሰጥተው ከታዘዙ፣ በእውቀት የዳበረ ስነ-ልቦና የሚያሳድረውን ተፅዕኖ የሚከተሉ ከሆነ፣ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት የሚደረገው የተወሳሰበና ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ አደረጃጀት አስፈላጊ አይሆንም። ሉተር ይህንን ዓላማ ለማሳካት እየለፋ እንደሆነ ተገነዘበ፤ የተሻለ ተፅዕኖ በቤተ ክርስቲያን እየተስተዋለ በመምጣቱ በስውር ደስ ይለው ነበር። GCAmh 104.3

በዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርነቱም ሉተር እጅግ የተዋጣለት ዝነኛ ሰው እንደሆነ አስተዋለ። ሉተር የጥናት ውጤቱን ከግንብ በተሰራው ቤተ ክርስቲያን ላይ ከለጠፈ ጀምሮ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ቢሆንም በሁሉም ቅዱሳን ክብረ-በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር በጣም ቀንሶ ነበር። ሮም ለአምልኮ የሚመጡ ሰዎችንና ስጦታዎችን አጣች፤ በምትኩ ግን ወደ ዊተንበርግ በሚመጡ ሰዎች ቦታው ተያዘ፤ ታሪካዊ ቅርሶቿን ለማድነቅ በሚመጡ የኃይማኖት ተጓዦች ሳይሆን በተማሪዎች የትምህርት አዳራሾችዋ ተሞሉ። የሉተር ፅሁፎች በሁሉም ስፍራ ለመጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ፍላጎትን ቀስቅሰው ነበር። ከመላው የጀርመን አገር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ስፍራዎች ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ይጎርፉ ጀመር። ዊተንበርግን ለመጀመሪያ የሚያዩ ወጣቶች ልክ “በጥንት ጊዜ ከጽዮን ተራራ እንደወጣ ሁሉ የእውነት ብርሐን ከዊተንበርግ ተንፀባርቆ እሩቅ አገራትን ይደርስ ዘንድ ስላደረገ እጃቸውን ወደ ሰማይ አንስተው እግዚአብሔርን ይባርኩ” ነበር።-Ibid., b. 4, ch. 10። GCAmh 104.4

በዚህ ጊዜም ሉተር ከሮማዊነት ስህተቶች የተለወጠው ገና በከፊል ነበር። የሊቀ-ጳጳሱን አዋጆችና መተዳደሪያ ደንቦች(ህገ-ካቶሊክ) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲያወዳድር ሳለ ግን በመገረም ተሞላ። “የሊቀ-ጳጳሳትን አዋጆች እያነበብኩ ነው” አለ “እናም…. ሊቀ-ጳጳሱ ራሱ የክርስቶስ ተቃዋሚ ይሁን ወይም የእርሱ ሐዋርያ የማውቀው ነገር የለም። ክርስቶስ በእነርሱ ዘንድ በስህተት ተወክሎ፣ ስቅለቱም እንዲሁ ነው የሚታየው።”-Ibid., b. 5, ch. 1። እንደዚህም ሆኖ ሉተር አሁንም የሮም ቤተ ክርስቲያን ደጋፊ ነበር፤ ከህብረትዋም ራሴን እነጥላለሁ የሚል ሃሳብም ፈጽሞ በውስጡ አልነበረም። GCAmh 105.1

የተሐድሶ አራማጁ ጽሁፎችና አስተምህሮዎች ክርስትናን በተቀበለ አገር ሁሉ እየተስፋፉ ነበር። ዜናው ወደ ስዊዘርላንድና ሆላንድ ተሰራጨ። የጽሁፎቹ ቅጅዎች ፈረንሳይና ስፔይን መድረስ ቻሉ። በእንግሊዝ አገር የእርሱ ትምህርቶች እንደ የሕይወት ቃል ተቀባይነት አገኙ። ለቤልጅየምና ለኢጣልያም እውነቱ ደርሷቸዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሞት ከሚመስል ህሊናዊ መስለል [አፍዝዝ አደንግዝ] እየነቁ የእምነትን ሕይወት ደስታና ተስፋ ማጣጣም ጀመሩ። GCAmh 105.2

በሉተር ጥቃት ሮም የበለጠ እየተበሳጨች መጣች፤ የተወሰኑ አክራሪ ተቃዋሚዎቹ፣ በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ዶክተሮች ሳይቀር፣ አመፀኛውን መነኩሴ የገደለ ኃጢአት አይኖርበትም በማለት አውጀው ነበር። አንድ ቀን በካፖርቱ ስር ሽጉጥ የደበቀ እንግዳ ሰው የተሐድሶ አራማጁን ጠጋ ብሎ እንዲህ ብቻውን ለምን እንደሚሔድ ይጠይቀዋል። “በእግዚአብሔር እጆች ውስጥ ነኝ” አለ ሉተር፣ “እርሱ ረዳቴና ጠባቂዬ ነው። ሰው ምን ያደርገኛል?” አለው፤ እንግዳው ሰው እነዚህን ቃላት እንደሰማ ልክ ከሰማይ መላዕክት ፊት የቆመ ያህል ፊቱ ገርጥቶ ከእርሱ ሸሸ። GCAmh 105.3

ሮም ሉተርን ለማጥፋት ቆርጣ ተነስታለች፤ እግዚአብሔር ግን ከለላው ሆነ። አስተምህሮዎቹ በሁሉም ስፍራ ተሰሙ። በገዳማት፣ በጎጆዎች፣ በልዑላን መኖሪያ ቤተ-መንግሥቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በነገሥታት መኖሪያ አዳራሾች ሁሉ ተሰራጨ፤ የተፈሩና የተከበሩ ሰዎችም ጥረቱን ለመደገፍ በየአቅጣጫው ተነሱ። GCAmh 105.4

በዚህ ጊዜ ነበር ሉተር የኸስን ሥራዎች ሲያነብ፣ ፅድቅ በኃይማኖት፣ እርሱ ራሱ ከፍ ለማድረግና ለማስተማር ሲሻው የነበረው አስተምህሮ በቦኸሚያ የተሐድሶ አራማጅ ተይዞ የነበረ እምነት እንደሆነ የተረዳው። “ሁላችንም” አለ ሉተር፦ “ጳውሎስ፣ አውገስቲንና እኔም ጭምር ሳናውቀው ኸሳውያን ነበርን።” “እውነት ለዓለም ከመቶ ዓመት በፊት ተሰብኮ፣ እንዲቃጠል ሆኖአልና” ቀጠለ፣ “እግዚአብሔር በእርግጥ ምድርን በፍርድ ይጎበኛታል።”-wylie, b. 6, ch. 1። GCAmh 105.5

በክርስትና ተሐድሶ ጉዳይ ሉተር ለጀርመን ንጉሠ ነገሥትና መሳፍንት ባቀረበው ተማፅኖ፣ ሊቀ-ጳጳሱን በተመለከተ ሲናገር፦ “የክርስቶስ ወኪል ተብሎ የሚጠራው እርሱ ማንም ንጉሠ ነገሥት ሊስተካከለው የማይችል ግርማ ተጎናጽፎ መመልከት አስፀያፊ ነው። ይህ የተዋረደውንና ምስኪኑን የሱስን፤ ወይስ ትሁቱን ቅዱስ ጴጥሮስን ለመወከል ነው? ሊቀ-ጳጳሱ የዓለም ጌታ ነው ይላሉ! እንደሚወክለው በጉራ የሚናገርለት ክርስቶስ ግን፣ ‘መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም’ አለ [ዮሐ 18÷36]። ወኪል የሚያስተዳድረው ግዛት አለቃው ከሚገዛው ወሰን ሊሰፋ ይችላልን?”-D’Aubigné, b. 6, ch. 3። GCAmh 105.6

ስለ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ እንዲህ ብሎ ፃፈ፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት ብሎም በወጣቶቻችን ልብ ውስጥ ለመቅረጽ ትጉህ ጥንቃቄ መውሰድ ካልቻሉ በስተቀር ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሲኦል የሚመሩ ሰፊ በሮች ሆነው እንዳይገኙ እጅግ እፈራለሁ። መጽሐፍ ቅዱሳት የሕይወት መመሪያ ባልተደረጉበት ቦታ ልጁን ያስገባ ዘንድ ማንንም አልመክርም። የእግዚአብሔር ቃል በትጋት የማይጠናበት እያንዳንዱ ተቋም መበላሸቱ አይቀርም።”-Ibid., b. 6, ch. 3። GCAmh 106.1

ይህ ተማፅኖ በመላው ጀርመን በፍጥነት ተሰራጨ፤ በሕዝቡ ዘንድም ከባድ ተፅዕኖ ማሳደር ቻለ። አገሪቱ ተነጋነገች፤ እልፍ አዕላፋትም በተሐድሶው ሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ለመሰለፍ ተነሱ። የሉተር ተቃዋሚዎች የበቀል እሳት እየለበለባቸው፣ የማያዳግም እርምጃ ይወሰድበት ዘንድ ሊቀ-ጳጳሱን ወተወቱት። አስተምህሮዎቹ ወዲያውኑ እንዲወገዙ አዋጅ ወጣ። የተሐድሶ አራማጁና ደጋፊዎቹ እምነታቸውን ይክዱ ዘንድ ስልሳ ቀን ተሰጣቸው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የማይመለሱ ከሆነ ከቤተ ክርስቲያን አባልነት እንደሚሰረዙ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። GCAmh 106.2

ያ ለተሐድሶው አስከፊ ችግር ነበር። የሮም ከቤተ ክርስቲያን የማግለል ብይን ንጉሠ ነገሥታትን በፍርሃት ያርበደበደ፣ ኃያል መንግሥታትን በሃዘንና በባዶነት ሲሞላ የኖረ፣ ለብዙ መቶ ዓመታት የቆየ፣ ተግባር ነበር። መርገሙ የወደቀባቸው ሁሉ በሁሉም ስፍራ በታላቅ ፍርሃትና ስጋት ይታዩ ነበር። ከባልንጀሮቻቸው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው እንደ ህገ-ወጦች ተቆጥረው ለፍጅት ይታደኑ ነበር። በዙሪያው ሊፈነዳ ስለተቃረበው ኃይለኛ ማዕበል ሉተር መረዳት የሌለው አልነበረም። ነገር ግን ክርስቶስ ረዳቱና ጥበቃው እንደሆነ በመተማመን ፀንቶ ቆመ። በሰማዕትነት ድፍረትና እምነት እንዲህ ፃፈ፦ “ስለሚሆነው ነገር አላውቅም፣ ለማወቅም ግድ የለኝም።” “ማዕበሉ በየትኛውም ስፍራ ሊደርስብኝ ይችላል፤ እኔ ግን አልፈራም። አንዲት ቅጠል እንኳ ያለ አባታችን ፈቃድ ተቀንጥሳ አትወድቅም። ለእኛማ ምን ያህል ይጠነቀቅልን ይሆን! ይህ ቃል፣ ለኛ ሥጋ የሆነው ቃል፣ ራሱ ሞቶአልና፣ ለእርሱ ቃል መሞት ቀላል ነገር ነው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ እርሱ ከኛ በፊት ባለፈበት ማለፋችን ደግሞ እርሱ ወዳለበት ያደርሰናል፤ ለዘላለም ከእርሱ ጋር እንኖራለን።”-Ibid., 3d London ed., Walther, 1840, b. 6, ch. 9። GCAmh 106.3

ጳጳሳዊ አዋጅ ሲደርሰው ሉተር፦ “ቅድስና የሌለው፣ ሐሰትም ነውና እጠላዋለሁ፣ እቃወመዋለሁም… በዚህ አዋጅ የተወገዘው ክርስቶስ ራሱ ነው።” “ተወዳዳሪ ለሌለው ዓላማ ስል ወደፊት ሊገጥመኝ በሚችለው ስቃይ ኩራት ይሰማኛል። ከወዲሁ የበለጠ ነፃነት ይሰማኛል፤ ምክንያቱም አሁን ሊቀ-ጳጳሱ የክርስቶስ ተቃዋሚ እንደሆነ፣ ዙፋኑም የራሱ የሰይጣን ዙፋን እንደሆነ አውቄአለሁ”አለ።-D’Aubigné, b. 6, ch. 9። GCAmh 106.4

ሆኖም የሮም ትዕዛዝ ውጤት-አልባ አልነበረም። እስር፣ ግርፋትና ሰይፍ፣ መታዘዝን በኃይል ማስፈፀም የሚችሉ ውጤታማ መሳሪያዎች ነበሩ። ደካሞችና በአጉል እምነት የተጠመዱ ሁሉ በሊቀ-ጳጳሱ አዋጅ ይንቀጠቀጡ ነበር፤ በአብዛኛው ለሉተር ሃዘኔታ ቢንፀባረቅም፣ ብዙዎች ግን የተሐድሶው ተልዕኮ ውድ ሕይወትን አደጋ ላይ ለመጣል የሚበቃ ምክንያት እንዳልሆነ ይሰማቸው ነበር። ሁሉም ነገር እንደሚያመለክተው የተሐድሶ አራማጁ ሥራ በቅርብ የሚቋረጥ ይመስል ነበር። GCAmh 106.5

ሉተር ግን አሁንም ፍርሃት የለሽ ነበረ። ሮም ውግዘቶችዋን አወረደችበት፤ እንደሚገደል ወይም ተገዶ እጅ እንደሚሰጥ [አስተምህሮውን እንደሚክድ] ተማምኖ ዓለም የሚሆነውን ይመለከት ነበር። ነገር ግን በከፍተኛ ኃይል የበደለኝነትን ፍርድ ወደርስዋ መልሶ በኃይል ወረወረው፤ እርስዋን ለዘላለም ለመተው ያለውን አቋም በአደባባይ ተናገረ።ተማሪዎች፣ ዶክተሮችና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በተሰበሰቡበት፣ የሊቀ-ጳጳሱን ትዕዛዝ ከቀኖና ሕጎች፣ ከአዋጆችና የጳጳሳዊ ሥርዓትን ስልጣን ከሚያስጠብቁ የተወሰኑ ጽሁፎች ጋር ሉተር በሕዝቡ ፊት በእሳት አቃጠለው። “ጠላቶቼ መጽሐፎቼን በማቃጠል”፣ አለ ሉተር፣ “በአንዳንዶች አእምሮ ላይ የእውነትን ተልዕኮ ማቁሰል፣ ብሎም ነፍሳትን ማጥፋት ተሳክቶላቸዋል። በዚህ ምክንያት እኔ ደግሞ የእነርሱን መጻሕፍት አቃጥላለሁ። ከባድ ትግል አሁን ተጀመረ። እስካሁን ከሊቀ-ጳጳሱ ጋር እየተባበርኩ ነበር፤ አሁን ግን ግልጽ ጦርነት አውጃለሁ። ይህንን ሥራ በእግዚአብሔር ስም ጀምሬአለሁ፤ እኔ በሌለሁበት፣ በእርሱ ኃይል ይጠናቀቃል።”-Ibid, b. 6, ch. 10። GCAmh 107.1

የተነሳበት ዓላማ ደካማ ነው ብለው ለሚጎነትሉት፣ ለጠላቶቹ ዘለፋ በሚሆን አነጋገር ሉተር ሲመልስ፣ “ይህንን አስፈላጊ ሥራ እፈጽም ዘንድ የመረጠኝ እግዚአብሔር እንዳልሆነ ማን ያውቃል፣ እነዚህ አጉተምታሚዎች ያንን ባለመፍራት እኔን መጥላታቸው እግዚአብሔርን ራሱን እየጠሉት ቢሆንስ? ብቻዬን እንደሆንሁ ይናገራሉ፤ አይደለሁም፤ ያህዌ ከእኔ ጋር ነው። እነርሱ እንደሚያስተውሉትማ፣ ከግብፅ በተወጣበት ጊዜ ሙሴ ብቻውን ነበር፤ በንጉሥ አሃብ ዘመን ኤልያስ ብቻውን ነበር፤ ኢሳይያስ በየሩሳሌም ብቻውን ነበር፤ ሕዝቅኤል በባቢሎን ብቻውን ነበር። ሮም ሆይ ይህንን አድምጪ፦ ነብይ ይሆንለት ዘንድ እግዚአብሔር ሊቀ-ካህንን ወይም የታወቀ ዝነኛ ሰውን በጭራሽ መርጦ አያውቅም። የተዋረዱና የተናቁ ሰዎችን፣ እንዲያውም ባንድ ወቅት በግ ጠባቂውን አሞጽን፣ መረጠ። ቅዱሳን ህይዎታቸውን በሚያስከፍል አደጋ ውስጥ ሆነው ነገሥታትን፣ ልዑላንን፣ ወስላታ ቀሳውስትንና ጠቢባንን ለመገሰጽ ተገደዋል።” “እኔም ራሴ ነብይ ነኝ እያልኩ አይደለም፤ ይህንን ግን እላለሁ፣ በጨቋኞቹ በኩል ቁጥራቸው የበዛ [ሰዎች]፣ የመደብ ደረጃ፣ ሃብትና የማላገጫ ደብዳቤዎች እያሉ፣ እኔ ብቻየን በመሆኔ፣ በዚህ ምክንያት ሊፈሩ ይገባቸዋል። አዎ ብቻዬን ነኝ፤ ሆኖም ሳልናወጥ ቆሜያለሁ፤ ምክንያቱም ከእኔ ጎን ለጎን የእግዚአብሔር ቃል አብሮኝ አለና፤ በኩራት የሚናገሩለት ብዛት ያለው ቁጥር ቢኖራቸውም፣ ይህ [ከእኔ ጋር ያለው] ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል ከእነርሱ ጋር አይደለም።”-Ibid, b. 6, ch. 10። GCAmh 107.2

ይህም ሁሉ ሆኖ የመጨረሻውን ከቤተ ክርስቲያን የመለየት ውሳኔውን ለማድረግ ሉተር ከራሱ ጋር ጭንቅ የሆነ ትግል ማካሄድ ነበረበት። በዚህ ጊዜ ገደማ ነበር እንዲህ የፃፈው፦ “ልክ እንደሆነ ተደርጎ በልጅነት የተቀረጸን ነገር ለመተው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር ይሰማኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ከጎኔ ቢሆንም እንኳ ሊቀ-ጳጳሱን ብቻዬን ተቃውሜ ለመቆምና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው! ለማለት መድፈሬ ትክክል ነው ብዬ ራሴን ለማሳመን በምን ያህል ህመም ውስጥ አለፍኩ! የልብ ፈተና ያልሆነብኝ ምን አለ! ከጳጳሳዊ ደጋፊ ከንፈር የማይጠፋውን፦ “አንተ ብቻ ነህ ጠቢብ? ሌላው ሁሉ ስህተተኛ ሊሆን ይችላል? ጥፋተኛው ራስህ ብትሆንና፣ በስህተትህ ተሳትፈው ብዙ ነፍሳት ለዘላለም ቢኮነኑስ እንዴት ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ስንት ጊዜ በምሬት ራሴን ጠይቄዋለሁ! “ክርስቶስ፣ መሳሳት በማይቻለው ቃሉ ልቤን አጠንክሮ ያሉብኝ መጠራጠሮች እስኪወገዱልኝ ድረስ ከራሴና ከሰይጣን ጋር እንዲህ እታገል ነበርሁ።”-Martyn, ገጽ 372, 373። GCAmh 107.3

ሉተር ስህተቱን አምኖ ካልተመለሰ በስተቀር ከቤተ ክርስቲያን እንደሚያገልለው ሊቀ-ጳጳሱ አስጠንቅቆት ነበር፤ ይህ ዛቻ አሁን እውን ሆነ። ከሮማዊ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ለመጨረሻ ጊዜ መለያየቱን የሚናገር አዲስ አዋጅ ወጣ፤ ሉተር በሰማይ የተረገመ እንደሆነ የሚናገር፣ አስተምህሮውንም የሚቀበሉትን ሁሉ በተመሳሳይ እርግማን የሚኮንን አዋጅ ወጣ። ታላቁ ፍጥጫ ሙሉ በሙሉ ተጀመረ። GCAmh 108.1

በእነርሱ ዘመን መነገር ያለበትን፣ ለዚያ ጊዜ አስፈላጊ የሆነውን የተለየ መልእክት እንዲናገሩ እግዚአብሔር የሚገለገልባቸው ሁሉ፣ ተቃውሞ ዕጣ ፈንታቸው ይሆናል። ለዚያ ጊዜ የተለየ አስፈላጊነት የነበረው ወቅታዊ እውነት በሉተር ዘመን ነበር፤ ለቤተ ክርስቲያንዋ ዛሬም ወቅታዊ እውነት አለ። ሁሉን ነገር እንደ ፈቃዱ ማድረግ የሚቻለው እርሱ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሰዎችን ለማስቀመጥ፣ እንዲያገለግሉ ለተቀመጡበት ሁኔታዎችና ለኖሩበት ዘመናቸው ገጣሚ የሚሆን የተለየ ኃላፊነት ለመስጠት እግዚአብሔር ፈቃደኛ ነው። ለሚሰጣቸው ብርሐን ዋጋ የሚሰጡ ከሆነ፣ ሰፊ እውነት በፊታቸው ይከፈታል። ነገር ግን ዛሬ፣ ሉተርን የተቃወሙ የጳጳሳዊ ሥርዓት ደጋፊዎች ለእውነት፣ ያኔ ከነበራቸው ፍላጎት የተሻለ መሻት በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ አይታይም። እንደ ቀድሞ ዘመናት ሁሉ ዛሬም ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የሰዎችን ፅንሰ ሐሳቦችና ወግ ልማዶች የመቀበል ዝንባሌ አለ። ለዚህ ዘመን ያለውን ወቅታዊ እውነት የሚያቀርቡ እነርሱ፣ ያለፉት የተሐድሶ አራማጆች ከነበራቸው ተቀባይነት የተሻለ ተቀባይነት እናገኛለን ብለው መጠበቅ የለባቸውም። በእውነትና በሐሰት፣ በክርስቶስና በሰይጣን መካከል ያለው ታላቁ ተቃርኖ(ተጋድሎ) የዚህ ዓለም ታሪክ ሊዘጋ በተቃረበ ቁጥር እየጨመረ የሚሄድ ነው። GCAmh 108.2

የሱስ ለደቀ-መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ።” [ዮሐ 15÷19-20]። በሌላ በኩልም ደግሞ ጌታችን በግልጽ ተናግሯል፦ “ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩባችሁ ወዮላችሁ!፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኛ ነብያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።” [ሉቃ 6÷26]። ካለፉት ዘመናት በተሻለ ሁኔታ የዓለም መንፈስ፣ ዛሬ፣ ከክርስቶስ መንፈስ ጋር ስምሙ አይደለም። የእግዚአብሔርን ቃል እንዳለ በንፅህናው የሚሰብኩ ሁሉ ካለፈው የተሻለ ተቀባይነት አይኖራቸውም። ለእውነት ያለው የተቃውሞ መልክ (ስልት) ሊቀየር ይችል ይሆናል፤ የተሻለ ብልጠት የተላበሰ በመሆኑ ጠላትነቱ በገሃድ አይታይ ይሆናል፤ ነገር ግን ያ ተመሳሳይ ተቃውሞ አሁንም አለ፤ እስከ ዘመን መቋጫም የሚንፀባረቅ ይሆናል። GCAmh 108.3