የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሃያ—ቤተሰብና ከተማ
የከተማ ሕይወት አደገኛነት፦ የከተማ ሕይወት ሰው ሠራሽና የውሸት ሕይወት ነው። ገንዘብ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት፤ የደስታና የሐሴት ፍለጋ አዙሪት፤ የእዩኝ እዩኝ ጥማት፤ ድሎትና ብክነት በቁጥር እጅግ ከበዛው የሰው ዘር ጋር ተዳምረው ከትክክለኛው የሕይወት ዓላማው አዕምሮን ፈቀቅ የሚያደርጉ ናቸው። ለሺህ ርኩሰት በር የሚከፍቱ ናቸው። በወጣቶች ላይ መቋቋም የማይችሉት ኃይል እየሆነባቸው ነው። በከተማ የሚኖሩ ልጆችንና ወጣቶችን የሚያሸንፍ አሳሳችና አደገኛ የሆነ ፈታኝ ነገር ቢኖር ተድላን(pleasure) የማፍቀር ዝንባሌ ነው። የበዓል ቀናት ብዙ ናቸው፤ ለተለያዩ ጨዋታዎች(games)ና ለፈረስ ግልቢያ ብዙ ሰዎች ይወጣሉ፤ የደስታና የፍስሐ ጉጉት ከተገቢው የሕይወት ኃላፊነት ጎትቶ ይወስዳቸዋል። ለጠቃሚ ነገር መቆጠብ ያለበት ገንዘብ ለጨዋታ ይበተናል።1 AHAmh 88.1
የጤናን አቋም አጢኑት፦ ከተማዎችን የከበበው ቁሳዊ ነገር ለጤና አጥፊ ነው። ከበሽታ ጋር ሁልጊዜ የመነካካት ዕዳ፤ የተበከለ አየርና ንጹህ ያልሆነ ውኃ፤ የተበከለ ምግብ፤ የተጨናነቁና ብርሃን የማይደርስባቸው ለጤና የማይስማሙ መኖሪያ ቤቶች፣ ከተማ ውስጥ በመኖር ከምናገኛቸው መቅሰፍቶች ጥቂቶቹ ናቸው። ሰዎች ከተማ ውስጥ ተጨናንቀው በበረንዳ ተኮራምተውና በኪራይ ቤቶች ታጭቀው እንዲኖሩ የእግዚአብሔር ዕቅድ አልነበረም። ዛሬ የደስታ ምንጭ ይሆኑን ዘንድ በሚመኝልን፣ ለዓይን የሚማርኩ ዕይታዎችና መረዋ ድምፆች በሞሉበት ሥፍራ፣ እግዚአብሔር የመጀመሪያ ወላጆቻችንን አስቀመጠ። በመስማማትም ወደ እግዚአብሔር የመጀመሪያ እቅድ እየቀረብን ስንሄድ የአካል፣ የአዕምሮና የነፍሳችንን ጤንነት ለመጠበቅ አቀማመጣችን የተመቸ እየሆነ ይሄዳል።2 AHAmh 88.2
የኃጢአት ቋቶች፦ ከተሞች በፈተና የተሞሉ ናቸው። የሥራችንን እቅድ ስናወጣ በተቻለን መጠን ታዳጊዎቻችንን ከዚህ ብክለት ለመጠበቅ በማሰብ መሆን አለበት።3 AHAmh 88.3
ልጆችና ወጣቶች በጥንቃቄ መያዝ አለባቸው። በከተሞቻችን ከሚገኙት የኃጢአት ምንጭ ከሆኑ ነገሮች ሁሉ ልናርቃቸው ይገባል።4 AHAmh 88.4
ትርምስምስና ድንግርግር፦ ሁልጊዜ ትርምስምስና ግርግር ባለባቸው ከተሞች ውስጥ ሕዝቦቹ ይኖሩ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። ልጆቻቸው ከዚህ መትረፍ አለባቸው፤ ሁሉም ነገር በችኮላ፣ በጥድፊያና በጫጫታ ግብረ-ገብነቱ የተበላሸ ነውና።5 AHAmh 88.5
የሥራ ችግሮች፦ በድርጅቶች አሠራር፣ በሠራተኛ ማህበራትና በሠላማዊ AHAmh 89.1
ሰልፎች ምክንያት የከተማ ኑሮ ችግር እየተባባሰ መጥቷል። ከባድ ችግሮች በፊታችን ናቸው፤ ለብዙዎች ቤተሰቦች ከተማን መልቀቅ ግዴታ ይሆንባቸዋል።6 AHAmh 89.2
እየመጣ ያለው ውድመት፦ ሰፋፊ ከተሞች ተጠራርገው የሚወሰዱበት ጊዜው ቅርብ ነው፤ እየመጣ ያለውን ፍርድ ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል።7 AHAmh 89.3
ኦ! ለዝሙት በተሰጡት በሽዎች በሚቆጠሩ ከተሞች ላይ ሊመጣ ያለውን ውድመት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ቢረዱት ምን አለበት!8 AHAmh 89.4
የምድራዊ ምኞትና የትርፍ ፍቅር፦ ብዙ ጊዜ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በመልካም ተጽዕኖ የመታጠራቸውን ጉዳይ ቸል ሲሉት ይታያሉ። ብዙ ጊዜ መኖሪያ ቤት ሲመርጡ ምድራዊ ፍላጎታቸውን ከግብረ-ገብነትና ማህበራዊ ሁኔታዎች አስበልጠው ይመለከታሉ። በዚህም ምክንያት ልጆቻቸው ቅድስናን ለማጎልበትና ትክክለኛ ባህርይ ለመመሥረት የማያስችሏቸውን ጉድኝቶች ይመሠርታሉ…. AHAmh 89.5
ከነዓናውያን ልጆቻቸውን ለሞሎክ መሰዋታቸውን ያወገዛችሁ ወላጆች ሆይ! ምን እያደረጋችሁ ነው? እጅግ ውድ የሆኑትን ይዞታዎቻችሁን [ልጆቻችሁን] ለገንዘብ ጣዖታችሁ እያበረከታችኋቸሁ ነው። ልጆቻችሁ ያለ ፍቅር አስነዋሪ ባህርይ ይዘው ሲያድጉ፤ የርኩሰታቸውንና የእምነት-ጎዶሎነታቸውን ዝንባሌ ስታዩ፤ ከጥፋት አላዳናቸውምና የምትመሰክሩትን እምነታችሁን ትኮንኑታላችሁ። በፀጋ ሀብት ፈንታ ራስ-ወዳድ የሆነ የዓለም ፍቅር ምርጫችሁ ውጤት ነውና የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ። ቤተሰቦቻችሁን ፈተና ወደበዛባቸው ሥፍራዎች ወሰዳችኋቸው፤ ክብራችሁና መጠለያችሁ ሊሆን የተገባው የእግዚአብሔር ታቦት አስፈላጊ ሆኖ አላገኛችሁትም። በመሆኑም ልጆቻችሁ ከፈተና ይጠበቁ ዘንድ ጌታ ተዓምር አይሠራም።9 AHAmh 89.6
ከተሞች እውነተኛ ጠቀሜታ የላቸውም፦ በከተማ በመኖሩ ምክንያት በአካል፣ በአዕምሮ ወይም በመንፈሳዊ ነገር የሚሻሻል ከመቶ አንድ ቤተሰብ አይገኝም። እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅርና ደስታ ወጣ ባሉ ሜዳዎች ኮረብታዎችና ዛፎች ባሉበት፣ በገለልተኛ ሥፍራ በተሻለ ሙላት ይገኛሉ። ከከተማው እይታ፣ ከሚንቀጫቀጩና ከሚንጋጉ መኪኖችና ጋሪዎች ድምፅ ልጆቻችሁን አርቋቸው፤ አዕምሮአቸውም ጤናማ ይሆናል። የእግዚአብሔርን የዕውነት ቃል ወደ ቤትም ሆነ ወደ ልባቸው ለማምጣት ቀላል ይሆናል።10 AHAmh 89.7
ምክር ከገጠር ወደ ከተማ ለሚፈልሱ፦ ትርፋማነቱንና አስፈላጊነቱን በማመን ብዙ ወላጆች የገጠር ቤታቸውን ለቅቀው ወደ ከተማ ይገባሉ። ይህን በማድረጋቸው ግን ልጆቻቸውን ለብዙ ከባድ ፈተናዎች ያጋልጧቸዋል። ወንዶች ልጆች ሥራ ይፈታሉ፤ የጎዳና ትምህርትም ይማራሉ። መልካም፣ ንጹህና ቅዱስ የሆነው ፍላጎታቸው ሁሉ ከውስጣቸው እስኪጠፋ ድረስ ከአንዱ ብልሹነት ወደ ሌላው ይንሸራተታሉ። ቤተሰቡ ተጽዕኖው ለአካላዊና ለአዕምሮአዊ ጥንካሬ እጅግ አመቺ በሆነበት በገጠር እንደነበር ቢቀር ኖሮ እንዴት መልካም ነበር። ንጽህናቸውን እንደያዙ የድካም ጣፋጭ እንቅልፍ ይተኙ ዘንድ ወጣቶች መሬት ማረስን(መቆፈርን) መማር አለባቸው። AHAmh 89.8
በወላጆች እንዝህላልነት ምክንያት በከተማችን ያሉ ወጣቶች በእግዚአብሔር ፊት መንገዳቸውን እያበላሹና ነፍሳቸውን እየበከሉ ነው። ይህ ምንጊዜም ብዙ የመቀመጥና የሥራ መፍታት ውጤት ነው። የድኃ መርጃ አዳራሾች፣ እስር ቤቶችና የሰው መስቀያ እንጨቶች፣ በወላጆች ቸል የተባሉትን ኃላፊነቶች በገሐድ የሚተርኩ አሳዛኝ ትዕይንቶች ናቸው።11 AHAmh 90.1
ትጠነቀቁላቸው ዘንድ በአደራ የተሰጧችሁን ብርቅዬ ነፍሳት አደጋ ላይ ከመጣል፣ ሁሉንም ዓለማዊ ሐሳብና እቅድ ብትሰዉ ይሻላል። በፈተና ተጠቂ ይሆናሉ፤ እንዴት መቋቋም እንዳለባቸው መማር ይኖርባቸዋል። በግልጽና በነፃነት ራሳችሁንና ቤተሰባችሁን ለእግዚአብሔር ከመገበር የሚከለክላችሁን እያንዳንዱን መጥፎ ልማድ የመስበር፤ እያንዳንዱን እስር የመፍታት፤ እያንዳንዱን ተጽዕኖ የመቁረጥ ኃላፊነት በራሳችሁ ላይ ነው። AHAmh 90.2
በተጨናነቀ ከተማ ከምትኖሩ ይልቅ፣ በምትችሉት ሁሉ ልጆቻችሁ ከፈተና የሚከለሉበትን ወጣ ያለ ቦታ ምረጡ። በዚያም ሥፍራ ጠቃሚ ሆነው ያድጉ ዘንድ አስተምሯቸው፤ አሰልጥኗቸውም። ነቢዩ ሕዝቅኤል ሰዶምን ወደ ኃጢአትና ጥፋት የመሩትን ነገሮች ሲዘረዝር:- “ትዕቢት፣ እንጀራን መጥገብ፣ ድንዳኔም፣ ተግባር መፍታትም በርስዋ ነበረች፤ በልጆችዋም። የችጋረኛውንም እጅ የድሃውንም አላጸናችም።” የሰዶምን ጥፋት ለማምለጥ የሚፈልጉ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ በዚያች ርኩስ ከተማ እንዲፈጸም ካደረገው አካሄድ የመቆጠብ ግዴታ እንዳለባቸው ተናግሯል።12 AHAmh 90.3
ሎጥ ወደ ሰዶም ሲገባ ከርኩሰት ነፃ ሊሆንና ቤተሰቡም እርሱን ይመስሉ ዘንድ ጽኑ ፍላጎት ነበረው። ግን ጎልቶ በሚታይ አወዳደቅ ወደቀ። በዙሪያው የነበረው ተጽዕኖ በራሱ እምነት ላይ ጉዳት ነበረው፤ ከሰዶም ጋር የነበራቸው የልጆቹ ትስስር ፍላጎቱን ከሰዶማውያን ጋር አቆራኘው። ውጤቱን የምናውቀው ነው። አሁንም ብዙዎች [ከዚህ ታሪክ ሳይማሩ] ተመሳሳይ ጥፋት አየሠሩ ነው።13 AHAmh 90.4
በምትችሉት መጠን ቤታችሁ ከሰዶምና ጎሞራ ይርቅ ዘንድ በጥንቃቄ የመምረጥ ጥናት አድርጉ። ከትልልቅ ከተሞች ራቁ። እንደዚያ በማድረጋችሁ ሀብታም መሆን የሚቀርባችሁ ቢሆን እንኳ፣ የምትችሉ ከሆነ ቤታችሁን ወጣ ባለና ፀጥታ በሰፈነበት ሥፍራ አድርጉት። መልካም ተጽዕኖ ባለበት ቦታ ተቀመጡ።14 AHAmh 91.1
ለቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ፍለጋ ህዝባችን ወደ ከተማ እንዳይጎርፍ ማስጠንቀቂያ እንድሰጥ እግዚአብሔር አዞኛል። ለአባቶቻችንና ለእናቶቻችን እንዲህ እንድል ታዝዣለሁ:- “ልጆቻችሁን በራሳችሁ አጥር ግቢ ውስጥ ለማስቀረት የተሳናችሁ አትሁኑ”። 15 AHAmh 91.2
ከከተሞች የመውጣት ጊዜው አሁን ነው፦ የእኔ መልእክት ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁ ከከተማ ውጡ ነው።16 AHAmh 91.3
እግዚአብሔር መንገዱን ከፍቶ እያለ ቤተሰቦች ከከተሞች የሚወጡበት ጊዜ መጥቷል። ልጆች ወደ ገጠር ይወሰዱ። ወላጆች አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን የሚስማማ መኖሪያ ይምረጡ። መኖሪያ ቤቱ ጠባብ ቢሆንም በዙሪያው የሚታረስ መሬት ይኑረው።17 AHAmh 91.4
ሞልቶ የሚፈስሰው መቅሰፍት በምድር ነዋሪዎች ላይ ከመውረዱ በፊት፣ ለዚያ ቀን ይዘጋጁ ዘንድ እውነተኛ እስራኤላውያን የሆኑቱን ሁሉ እግዚአብሔር አሁን ይጠራቸዋል። ለወላጆች የማስጠንቀቂያ ጩኸቱን እያሰማ ነው፤ ልጆቻችሁን ወደ እራሳችሁ ቤት ሰብስቡ። የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ከሚንቁ፣ ርኩሰትን ከሚያስተምሩና ከሚያደርጉ ከነዚያ ነጥሏቸው። በተቻላችሁ ፍጥነት ከትላልቅ ከተሞች ውጡ።18 AHAmh 91.5
እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ያግዛል፦ በደም ቧንቧዎቻችን የሚዘዋወረውን የሕይወት ደም የሚያበላሸውን ሥጋ ሊተኩ የሚችሉ አትክልትና ፍራፍሬ የሚያሳድጉ ቦታዎችን እንዲሁም የሚታረስ እርሻ ያለው ትንሽ ቤት ወላጆች በገጠር ማግኘት(መግዛት) ይችላሉ። በእንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ልጆችን በሚያበላሸው የከተማ ተጽዕኖ አይከበቡም። ከከተሞች ወጣ ያሉ የመኖሪያ ቦታዎች እንዲያገኙ እግዚአብሔር ህዝቦቹን ያግዛል።19 AHAmh 91.6