የአድቬንቲስት ቤት

22/88

ምዕራፍ ሀያ አንድ—የገጠር ኑሮ ጥቅም

በቁራጭ መሬትና በሚመች መኖሪያ ቤት፦ ማድረግ የሚችሉ እስከሆኑ ድረስ ለልጆቻቸው በገጠር ቤት ይሠሩ ዘንድ የወላጆች ኃላፊነት ነው።1 AHAmh 93.1

ቁራጭ መሬትና ምቾት ያለው የመኖሪያ ቤት ያላቸው አባቶችና እናቶች ንጉሦችና ንግሥቶች ናቸው።2 AHAmh 93.2

ከከተሞች ወጥታችሁ ወደ ገጠር እንድትፈልሱ ስትጠሩ እንደ ችግር አትቁጠሩት፤ ካወቃችሁበት ለሚሰበስበው ሁሉ በረከት የሞላው በዚህ ሥፍራ ነው።3 AHAmh 93.3

ለምጣኔ ሀብት ዋስትና እገዛ፦ የራሳቸውን ስንቅ ማዘጋጀት ይችሉ ዘንድ እግዚአብሔር አሁንም አሁንም ደጋግሞ፣ ሕዝቦቹ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ከከተማ እንዲወጡና ወደ ገጠር እንዲሄዱ አዟል፤ መግዛትና መሸጥ እጅግ ከባድ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣልና። ደጋግሞ የተሰጠንን ትዕዛዝ ከአሁኑ መስማት መጀመር አለብን። ከጠላት ጣልቃ ገብነት ነፃ ወደምትሆኑበት ቤት፤ ተቀራርበውና ተጨፍቀው ወዳልተሠሩበት ሥፍራዎች፣ ከከተማ ውጡና ወደ ገጠር አውራጃዎች ሂዱ።4 (በዚህ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ምክር ለማግኘት Country Living (የአገር ቤት አኗኗር) የሚለውን መጽሐፍ ይመልከቱ።) AHAmh 93.4

ምክር ለከተማ ነዋሪ፦ የወጣቱን ግብረ-ገብነት የማበላሸት ያን ያህል ተጽዕኖ በሌለበት አካባቢ ብትኖሩ፣ ግራ የሚያጋቡ ችግሮቻችሁን አራግፋችሁ ማምለጫ ቤታችሁን በገጠር ብታደርጉ መልካም ይሆንላችኋል። እርግጥ ነው ከብስጭትና ከሚያደነጋግሩ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ነፃ አትሆኑም፤ የልጆቻችሁን ጭንቅላት ሊያሸንፍ ለተቃረበውና ለሚያሰጋው የፈተና ጎርፍ በራችሁን ልትዘጉና ብዙ ርኩሰት ልታስቀሩ ግን ትችላላችሁ። ልጆች ሥራ መሥራትና ለውጥ(variety) ማግኘት ይፈልጋሉ። ያለዚያ በዙሪያቸው ያለው ነገርና የቤቶች ተመሳሳይነት የማይመቻቸውና ዕረፍት የሚነሳቸው ይሆናል፤ በመሆኑም ከግብር-የለሽ (ክፉ) የከተማው ወጣቶች ጋር የመቀላቀል ልማድ ያዳብራሉ፤ የጎዳና ትምህርትም ያገኛሉ…. AHAmh 93.5

በገጠር መኖራቸው ለእነርሱ እጅግ ጠቃሚ ነው፤ ከቤት ውጭ የሆነ ሕይወት የአዕምሮና የአካል ንቃትንና ጤናማነትን ያጎለብታል። የሚኮተኩቱት የአትክልት ሥፍራ ይኑራቸው፤ እንዲጫወቱና ጠቃሚ ሥራ እንዲሠሩ ያደርጋል። የዕፅዋትና የአበባዎች እንክብካቤ ምርጫቸውና አመዛዛኝነታቸው እንዲሻሻል ያደርጋል። ከእግዚአብሔር ጠቃሚና ውብ ፍጥረቶች ጋር መለማመዳቸው(መተዋወቃቸው) በአዕምሮ ላይ ከፍ ከፍ የሚያደርግና ስብዕናን የሚያጎለብት ተጽዕኖ ያሳድራል፤ ወደ 94 የአድቬንቲስት ቤት ሁሉንም ፈጣሪና ገዥ ያመላክታቸዋል።5 AHAmh 93.6

ለገጠር ነዋሪዎች የተረጋገጠው የተትረፈረፈ በረከት፦ ሀብትዋን ለመሰብሰብ ጀግንነቱ፣ ፈቃዱና ጽናቱ ላላቸው ሰዎች ምድር በውስጧ ያመቀችው ብዙ በረከት አላት.... ዝቅ ያለ የሥራ መስክ እንደሆነ ስለሚቆጥሩት ብዙ ገበሬዎች ለሚበሉት እንኳ በቂ ምርት ማግኘት አቅቷቸዋል፤ መሬት በውስጧ ለእነርሱና ለቤተሰቦቻቸው የሚበቃ በረከት እንደያዘች አይታያቸውም።6 AHAmh 94.1

አዕምሮን የሚያነቃና ባህርይን የሚያነጥር ሥራ፦ አስተዋዩ ሠራተኛ መሬትን በማረስ ታልመው የማያውቁ፣ ተቆንጥረው የማያልቁ በረከቶችን መክፈት ይችላል። ለተፈጥሮአዊ ህጎችዋ ትኩረት ሳይሰጥ ማንም ገበሬ ወይም አትክልተኛ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። የእያንዳንዱ ዕፅ የተለየ ጠባይ በውል መጠናት አለበት። የተለያዩ ዝርያዎች የተለያየ አፈርና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። የውጤታማነት ምሥጢሩም ለነዚህ ህጎች ተገዢ መሆን ነው። ችግኝን ማዛወር የሚጠይቀው ትኩረት፤ አንድም እንኳ የሥር ዘለላ እንዳይጨፈቅ ወይም ያለቦታው እንዳይቀመጥ የሚያስፈልገው ጥንቃቄ፤ ለቡቃያ የሚያስፈልገው እንክብካቤ፤ መግረዝና ውኃ ማጠጣት፤ ከማታ ቅዝቃዜና ከቀን የፀሐይ ብርሃን ለመከላከል ዳስ መሥራት፤ አረም በሽታንና ትላትልን ማስወገድ፤ የማስተካከልና አቅጣጫ የማስያዝ ሥራ የሚረዳው ለባህርይ መሻሻል ብቻ ሳይሆን ሥራው እራሱ ትምህርት ነው። ጥንቁቅነት፣ ታጋሽነት፣ ለጥቃቅን ነገሮች ትኩረት መስጠትና ለህግ ታዛዥ መሆን የሚያካፍሉት እጅግ ጠቃሚ የሆነ ሥልጠና አላቸው። ከሕይወት ረቂቃዊነትና ከተፈጥሮ መልካምነት ጋር የሚያደርገው የማይቋረጥ ግንኙነት፣ እንዲሁም ውብ የሆኑትን የእግዚአብሔርን ፍጡራን ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ገርነት አዕምሮን ይስላል፤ ባህርይን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ያጠራዋልም።7 AHAmh 94.2

እግዚአብሔር ይመራል፤ ያስተምራልም፦ የኤደንን የአትክልት ሥፍራ እንዴት እንደሚንከባከቡት አዳምና ሔዋንን ያስተማረ እርሱ ዛሬም ሰዎችን ያስተምራል፤ ያሠለጥናል። እርፉን ወይም መቆፈሪያውን ለሚጨብጠው፣ ለሚተክለውና ለሚዘራው ለእርሱ ጥበብ አለ። ምድር የተደበቀ ሀብት አላት። እግዚአብሔር በእርሻ ላይ መሥራት የሚችሉ በሺዎችና፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ፣ በከተሞች ተጨናንቀው ፍርፋሪ ለማግኘት የሚርመሰመሱ ብዙ ሰዎች አሉት….ቤተሰቦቻቸውን ወደ ገጠር የሚወስዱ እነርሱ ከከተማ ነዋሪዎቹ ጋር ሲነፃፀር ጥቂት ፈተናዎች ብቻ ባሉበት ቦታ ያስቀምጧቸዋል። እግዚአብሔርን ከሚወዱና ከሚፈሩት ወላጆች ጋር የሚኖሩ ልጆች የጥበብ መፍለቂያና ምንጭ ከሆነው ከታላቁ መምህር ለመማር በተሻለ ሁኔታ ላይ ይሆናሉ። ለሰማያዊ መንግሥት ብቁ የሚያደርጋቸው እድል የተመቻቸላቸው ይሆናሉ።8 AHAmh 94.3

የእግዚአብሔር እቅድ ለምድረ-እስራኤል፦ ባለመታዘዛቸው ምክንያት አዳምና ሔዋን ኤደንን አጡ፤ በኃጢአት ምክንያት መላ ምድር ተረገመች። ሆኖም የእግዚአብሔር ሕዝቦች ትእዛዙን የሚከተሉ ቢሆን ኖሮ መሬታቸው ወደ ለምነትዋና ውበትዋ በተመለሰች ነበር። ስለ መሬቱ ባህርይ እግዚአብሔር ራሱ ያስተምራቸው ዘንድ ምድሪቱንም ወደ ቀድሞው ለማደስ ይቻል ዘንድ ከእርሱ ጋር ሊተባበሩ ይገባቸው ነበር። እንዲህም ሲሆን ምድር መላዋ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ሆና የመለኮታዊ እውነት ተግባራዊ ማስተማሪያ ምሣሌም ትሆን ነበር። የእግዚአብሔርን የተፈጥሮ ህግ በመታዘዝ መሬት ሀብትዋን እንደምትሰጥ ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን የግብረ-ገብነት ህግ በመታዘዝ የሰው ልብ የእርሱን ባህርይ መገለጫዎች ማንጸባረቅ በቻለ ነበር።9 AHAmh 95.1

በኑሯችሁ የዘወትር መንፈሳዊ ትምህርት ውሰዱ፦ የአዕምሮአችንን ትኩረት ለመሳብ እግዚአብሔር በውብ የተፈጥሮ ገጽታ ከብቦናል። የተፈጥሮን ውበት ከእርሱ ባህርይ ጋር እንድናዛምደው እቅዱ ነው። የተፈጥሮን መጽሐፍ በታማኝነት ብናጠና ወደር ስለሌለው ዘለዓለማዊ ፍቅሩና ኃይሉ በጥልቀት እንድናስብ ፍሬአማ ምንጫችን ሊሆን ይችላል።10 AHAmh 95.2

ክርስቶስ የሚያስተምረን በዕረፍት ቀን ብቻ አይደለም፤ በሥራ ቀናት ሁሉ እንጂ…. በማረስና በመዝራት፣ በመኮትኮትና በማጨድ ፀጋው በልባችን የሚሠራውን ምሳሌ በተግባር ያስተምረናል። ስለዚህ በእያንዳንዱ የሥራ መስክ፣ በሁሉም የሕይወት ህብረት የመለኮታዊ እውነት ትምህርት እንድናገኝ ይፈልግብናል። ይህም ሲሆን የዕለት ልፋታችን ሙሉ በሙሉ ትኩረታችንን ስቦ እግዚአብሔርን እንድንረሳ አያደርገንም፤ ፈጣሪያችንና አዳኛችንን በቋሚነት ያስታውሰናል እንጂ። የእግዚአብሔር ሐሳብ በቤታችን ባሉብን ኃላፊነቶችና ተግባሮቻችን ሁሉ ላይ በማለፍ እንደ ወርቅ ሀብል ይሆናል። የፊቱ ክብር ለእኛ እንደገና በተፈጥሮ ፊት ላይ ያርፋል። ሁሌም ስለሰማያዊ እውነት አዲስ ነገር እንማራለን፤ የእርሱ የንጽህናው አምሳል ወደ መሆንም እናድጋለን።11 AHAmh 95.3

ተፈጥሮንና የሰውን ዘር የሚያስተዳድረው ህግ አንድ ነው፦ በሁሉም ፍጥረታት የሚናገረውን ድምፅ ይሰሙ ዘንድ ታላቁ መምህር አዳማጮቹን ከተፈጥሮ ጋር አገናኛቸው። ልባቸው ሲለሰልስና አዕምሮአቸውም መቀበል ሲጀምር ዐይናቸው የሚያርፍበት ገጽታ የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ትምህርት ይተረጉምላቸው ነበር…. በትምህርቱም እያንዳንዱን አዕምሮ የሚስብ፣ እያንዳንዱን ልብ የሚያጓጓ ነገር ነበር። በመሆኑም የየቀኑ ተግባርና የልፋት ድግግሞሽ የበለፀገ አስተሳሰብ የሌለበት ሳይሆን የማይታየውንና መንፈሳዊ የሆነውን ነገር እንዲያስታውሱ በሚረዷቸው ነገሮች የፈካና የተነቃቃ ነበረ። ማስተማር ያለብን እንዲህ ነው። የእግዚአብሔርን ጥበብና የፍቅሩን አገላለጽ ልጆች ከተፈጥሮ ይማሩ፤ ለእርሱ ያላቸው ሐሳብ ከወፉ፣ ከአበባውና ከዛፉ ጋር ይዛመድ፤ የሚያዩት ነገር ሁሉ የማይታየውን ነገር የሚተረጉም ይሁንላቸው፤ እንዲህም ሲሆን እያንዳንዱ የሕይወት ገጠመኝ የመለኮታዊ ትምህርት መማሪያ ምክንያት ይሆንላቸዋል። AHAmh 95.4

በፍጡር ሁሉ ላይ እንዲሁም በኑሮ ተሞክሮ የሚገኘውን ትምህርት ማጥናትና መማር ሲጀምሩ፣ የተፈጥሮን ነገሮችና የሕይወትን ጉዳዮች የሚያስተዳድሩት ሕጎች እኛንም ሊቆጣጠሩን እንደሚገባ እንዲያውቁ፣ የተሰጡን ለራሳችን ጥቅም ሲባል እንደሆነና እውነተኛ ደስታና ስኬት የምናገኘው እነርሱን [ሕጎቹን] ስንታዘዝ ብቻ እንደሆነ ይገነዘቡ ዘንድ ልጆቻችሁን እርዷቸው።12 AHAmh 96.1

በግብርና ተግባራዊ ትምህርት አስተምሩ፦ ለመቁጠር ከሚያታክቱ፣ የተለያዩ የማሳደግ ሂደቶች ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መካከል ጥቂቶቹ በአዳኛችን የዘር ምሣሌ የተላለፉት መልእክቶች ናቸው። ለታላላቆችም ሆነ ለታናናሾች የሚሆኑና ትምህርት ያዘሉ ናቸው…. AHAmh 96.2

የዘሩ መብቀል የመንፈሳዊ ሕይወት ጅማሮን ይወክላል፤ የተክሉ አስተዳደግም የባህርይ መጎልመስ ምሣሌ ነው…. ወላጆችና መምህራን እነዚህን ትምህርቶች ሲያስተምሩ በተግባራዊ ትምህርት የተደገፈ መሆን ይገባዋል። ልጆች እራሳቸው አፈር አዘጋጅተው ዘር ይዝሩ። በሥራም ላይ እንዳሉ ወላጆች ወይም መምህራን የልብን የአትክልት ሥፍራ ይግለጹላቸው። ጥሩ ወይም መጥፎ ዘር ሊዘራ ይችላል። ሆኖም የአትክልት ቦታው ለተፈጥሮ ዘር መዘጋጀት እንዳለበት ሁሉ ልብም ለእውነት ዘር መስተካከል ይገባዋል…. ባልለሰለሰ መሬት ላይ ዘር ዘርቶ ማንም ምርት እሰበስባለሁ ብሎ የሚያስብ የለም። እርሻን ማዘጋጀት፣ ዘርን መዝራትና ሰብልን ማሳደግ ትጋትንና ጽናትን የሚጠይቅ ሥራ ነው፤ የመንፈስ ዘርም የሚዘራው በዚህ ሁኔታ ነው።13 AHAmh 96.3

መጥፎ ልማዶች እንደ አረም ይቆጠራሉ፦ ከተቻለ ልጆች የሚቆፍሩት መሬት ከከተማ ውጭ ቢሆን ይመረጣል። እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ቁራጭ መሬት ይኑራቸው፤ የአትክልት ሥፍራውን እንዴት እንደሚያዘጋጁ፣ አፈሩን ለዘር እንዴት እንደሚያለሰልሱ፣ ሁሉንም አረም ማስወገድ እንደሚገባቸው ስታስተምሯቸው ለዓይን አስቀያሚና ጎጂ የሆኑ ባህርያትንም ከሕይወታቸው ማራቅ እንዳለባቸው አስተምሯቸው። አረም ከአትክልት ቦታቸው ማጥፋት እንዳለባቸው ሁሉ መጥፎ ልማዶችንም እንዲሁ ማስወገድ እንዳለባቸው አሳውቁአቸው። እነዚህን ትምህርቶች ለማስተማር ጊዜ ይወስዳል፤ ሆኖም መልሶ የሚከፍል ተግባር ነው - በእጅጉ የሚከፍል።14 AHAmh 96.4

የቤታችን ዙሪያ የእምነታችን ነፀብራቅ ይሁን፦ አካባቢያቸው ከሚያምኑት እምነት ጋር የሚጣጣም እንዲሆን እግዚአብሔር ለወላጆች መተግበር ያለበት ኃላፊነት ሰጥቷል። እንዲህም ሲሆን ለልጆቻቸው ትክክለኛ ትምህርት መስጠት ይችላሉ፤ ልጆቻቸውም ምድራዊውን ቤት በላይ ካለው ጋር ማዛመድ ይችላሉ። ቤተሰቡ በሚችለው ሁሉ በሰማይ ያለው ቤተሰብ ምሳሌ ይሁን። እንዲህም ሲሆን የተዋረደውንና የረከሰውን ፍላጎት ለማርካት የሚፈጠሩ ፈተናዎች ኃይል ያጣሉ። ልጆች እዚህ ምድር ለሙከራ ብቻ እንዳሉና እርሱን ለሚወዱና ትዕዛዛቱንም ለሚጠብቁ ሁሉ ክርስቶስ በሰማይ እያዘጋጀላቸው ያለውን እልፍኝ በመውረስ የሰማይ ዘለዓለማዊ ነዋሪዎች እንዲሆኑ ሊማሩ ይገባቸዋል። ይህ ከሁሉም በላይ የሚበልጠው ወላጆች መተግበር ያለባቸው ሓላፊነት ነው።15 AHAmh 96.5

ወላጆች ሆይ በገጠር ቤት ሥሩ፦ እግዚአብሔር ለሕዝባችን የመናገር ኃይል እስከሰጠኝ ድረስ ቀላልና ንጹህ የሆነውን የአኗኗር ትምህርት ከተፈጥሮ መጽሐፍ እንዲማሩ መሬትን ማረስና ሰብልን ማምረት ወደሚችሉበት ወደ ገጠር ሄደው ቤት እንዲሠሩ፣ ከከተሞችም ለቅቀው እንዲወጡ የማደርገውን ጥሪዬን እቀጥልበታለሁ። ተፈጥሮአዊ ነገሮች መንፈሳዊ እውነት ያስተምሩን ዘንድ ከጌታ የተሰጡን የማይናገሩ አገልጋዮች ናቸው። የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚነግሩንና የታላቁን የኪነ-ጥበብ ሊቅ እውቀት የሚመሰክሩልን ናቸው። AHAmh 97.1

የሚያማምሩትን አበቦች እወዳቸዋለሁ፤ እምነት ካለን በቅርቡ ወደምንገባበት የተባረከ ሀገር የሚያመላክቱ፣ የኤደንን ትዝታ(ትውስታ) ያዘሉ ናቸው። ጤና የሚሰጥ ተፈጥሮ ወዳላቸው ዛፎችና አበቦች እግዚአብሔር ህሊናዬን እየመራው ነው።16 AHAmh 97.2