የአድቬንቲስት ቤት
ክፍል ፮—አዲሱ ቤት
ምዕራፍ አሥራ ዘጠኝ—ቤት የት መሆን አለበት?
ቦታን ለመምረጥ የሚረዱ መርሆች፦ ቤተ-ቦታ በምንመርጥበት ጊዜ ከሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔር እንድናስብበት የሚፈልገው በቤተሰባችን ዙሪያ ያለው የግብረ-ገብነትና የኃይማኖት ተጽዕኖ ነው።1 AHAmh 85.1
ለመንፈሳዊ ዕድገታችን አመቺ የሆነ ህብረተሰብ መምረጥ አለብን፤ ማግኘት የምንችለው እርዳታ መድረስ የምንችልበት ይሁን። ሰይጣን ብዙ መሰናክሎችን በማስቀመጥ በተቻለው መጠን ወደ ሰማይ የምናደርገው እርምጃ አስቸጋሪ እንዲሆንብን ይጥራል። ብዙዎቹ የሚፈልጉት ዓይነት አካባቢ ማግኘት ስለማይችሉ ይህ ፈታኝ ሁኔታ ሊሆንብን ይችላል። ሆኖም በፈቃደኝነት፣ የክርስቲያን ባህርይ ለመመሥረት ተስማሚ ባልሆነ ተጽዕኖ ተከበን ራሳችንን ማጋለጥ የለብንም። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ግድ ከሆነ በክርስቶስ ፀጋ ተከልለን ሳንበከል እንቀር ዘንድ ተንበርክከን በዕጥፍ መፀለይና መትጋት ይኖርብናል።2 AHAmh 85.2
ወንጌሉ…. ነገሮችን በትክክለኛ ዋጋቸው እንድንገምታቸው፣ ጥረታችንም ብልጫ ዋጋ ላላቸው - በጽናት ለሚቆዩ ነገሮች - እንዲሆን ያስተምረናል። ይህ ትምህርት መኖሪያ ቤት የመምረጥ ኃላፊነት ለተጣለባቸው ሰዎች አስፈላጊ ነው። ከከፍተኛው ዓላማቸው እንዲደናቀፉ መፍቀድ የለባቸውም…. AHAmh 85.3
የቤቱ መቀመጫ ሲመረጥ ይህ መርህ ምርጫውን የሚመራ ይሁን። የሀብት ፍላጎት፣ የፋሽን ጥማት ወይም የህብረተሰቡ ልማድ አይቆጣጠራችሁ። አካባቢው ቀለል ያለ ኑሮ መኖርን፣ ንጽህናን፣ ጤናንና ትክክለኛ ጥቅምን መጠበቅ የሚችል መሆኑን አረጋግጡ…. AHAmh 85.4
የሰዎች ሥራ ብቻ የሚታይበት፣ በድምጹና በትዕይንቱ የርኩሰት ሐሳብ የሚደጋገምበት፣ ግርግሩና ትርምሱ የሚያደክምና ዕረፍት በሚነሣ አካባቢ ከመኖር፣ የእግዚአብሔርን ሥራዎች ልትመለከቱበት ወደምትችሉበት ቦታ ሂዱ። በተፈጥሮ ፀጥታ፣ ሠላምና ውበት የነፍስ ዕረፍት አግኙ። ዐይናችሁ በአረንጓዴው መስክ፣ በጫካውና በኮረብታው ላይ ይረፍ። በከተማው አቧራና ጭስ ያልተሸፈነ ብሩህሰማይ ተመልከቱ፤ ኃይል የሚሰጠውን ሰማያዊ አየር ተንፍሱ።3 AHAmh 85.5
የመጀመሪያው ቤት ተምሣሌነት፦ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ቤት፣ ምድርን ለሚሞሉት ልጆቻቸው ሠርቶ-ማሳያ ነበር። በእግዚአብሔር በራሱ የተዋበው ያ ቤት፣ የከበረ ቤተ-መንግሥት አልነበረም። ሰዎች ለጉራቸው እጹብ ድንቅና ውድ ህንጻ ገንብተው በራሳቸው እጅ ሥራዎች ሃሴት ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔር ግን አዳምን በአትክልት ቦታ አስቀመጠው። ይህ የእርሱ ቤት ነበረ። ሰማይ ጣራው ነበረ፤ መሬት በውብ አበባዎችዋና በህያው አረንጓዴ ምንጣፏ ወለሉ ነበረች፤ ችፍግ ያለ ቅጠል ያላቸው ግዙፍ ዛፎች አጎበሩ ነበሩ። የታላቁ ጥበበኛ (አርቲስት) የእጅ ሥራዎች በሆኑት፣ እጹብ ድንቅ ማስጌጫዎች ግድግዳው ተጊጦ ነበር። በቅዱሳኑ ጥንዶች ዙሪያ ለሁልጊዜ የሚሆን ትምህርት ነበር፤ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው የኩራትና የድሎትን ፍላጎት በማርካት ሳይሆን በእጅ ሥራዎቹ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት በመፍጠር ነው። ህዝቦች የሰው ሠራሽ ነገርን ቀንሰው ቀላልና ተፈጥሮአዊ በሆነ ነገር ላይ ቢያተኩሩ፣ በእጆቹ ሥራዎች አማካይነት የእግዚአብሔርን ዓላማ ወደ ማሳካት የበለጠ በተጠጉ ነበር። ትምክህትና ምኞት መቼም ቢሆን አይረኩም፤ በእውነት ብልህ የሆኑ ሁሉ ግን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ደስታ ሁሉም ፍጡር ይደርሰው ዘንድ እግዚአብሔር ካስቀመጣቸው የደስታ ምንጮች በገፍ ያገኛሉ።4 AHAmh 85.6
እግዚአብሔር ለልጁ የመረጠው ምድራዊ ቤት፦ በሰዎች መካከል ከተፈጸመው ሥራ ሁሉ የሚበልጠውን ለማከናወን የሱስ ወደ ምድር መጣ። እንዴት መኖርና የሕይወትን አብላጫ ጥቅም እንዴት እንደምናገኝ ሊያሳየን የእግዚአብሔር እንደራሴ ሆኖ መጣ። በዘለዓለማዊው አባቱ ለክርስቶስ የተመረጡት ሁኔታዎች ምን ዓይነት ነበሩ? መኖሪያው በገሊላ ኮረብታዎች ወጣ ያለና ገለልተኛ ነበር፤ ታማኝና ለራሱ ክብር በሚሰጥ ልፋትና ጥረት የቆመ ቤት ውስጥ ይኖር ነበር፤ ቀላል የሆነ ሕይወት ይመራ ነበር፤ ከየዕለቱ ችግርና መከራ ጋር ትንቅንቅ ያለበት የራስ መስዋዕትነት፤ ቆጣቢነት፣ ታጋሽነትና ደስታ አምጪ አገልግሎት የሚጠይቅ ኑሮ ነበረው፤ የቃሉን ጥቅልል ወረቀት ገልጦ በእናቱ አጠገብ ሆኖ ለማጥናት ጊዜ ይወስድ ነበር። የንጋት ፀጥታ ወይም የፀሐይ ግባት ጮራ በአረንጓዴው ሸለቆ በሚያርፍበት ጊዜ ስለ ተቀደሱት ተፈጥሮአዊ መግለጫዎች፣ ስለ ተፈጥሮ ጥናትና አቅርቦት እንዲሁም ነፍስ ከእግዚአብሔር ጋር ስላላት ትሥስር ጥናት ያደርግ ነበር - የክርስቶስ የልጅነት ሁኔታዎችና ገጠመኞች ይህን ይመስሉ ነበር።5 AHAmh 86.1
የገጠር ቤቶች በተስፋይቱ ምድር፦ እስራኤሎች በምድረ በዳ ሲጓዙ ሳለ በበረሃ የተጀመረው መመሪያ ትክክለኛ ልማድ መመሥረት እንዲያስችል ተደርጎ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላም ቀጥሎ ነበር። ህዝቡ በከተማ ተጨፋፍቀው አንድ ላይ እንዲኖሩ አልተደረጉም፤ ነገር ግን ጤና ሰጪ የሆነውን ተፈጥሮአዊና ያልተበላሸ የሕይወት በረከት ማግኘት ይችል ዘንድ እያንዳንዱ ቤተሰብ መሬት ተሰጥቶት ነበረ።6 AHAmh 86.2
አካባቢው በመጥምቁ ዮሐንስ ላይ የነበረው ተጽዕኖ፦ የክርስቶስን መምጣት ያወጀው መጥምቁ ዮሐንስ የልጅነት ሥልጠናውን ከወላጆቹ አገኘ። የሕይወቱ አብላጫው ጊዜ በበረሃ ነበር ያለቀው…. በጥብቅ የበረሃ መመሪያ የከተማን ኑሮ ደስታና ድሎት ሊተው የዮሐንስ ፈቃድ ነበር። ይህ የበረሃ አካባቢ ቀለል ያለ ኑሮ ለመኖርና ራስን ለመካድ አመቺ ነበር። በዓለም ጫጫታ ሳይቋረጥ እዚህ የተፈጥሮን፣ የራእይንና የእግዚአብሔርን ጥበቃ ትምህርት ማጥናት ችሎ ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ ተልዕኮው በፊቱ ተቀምጦለት ነበር፤ የቅዱሱን ጥበቃም በእምነት ተቀበለ። ጥርጣሬ፣ እምነት-አልባነትና እድፍ ከሞላውና ርኩሰት ከከበበው ህብረተሰብ በረሃ ጥሩ ማምለጫ ሆኖት ነበር። ፈተናን መቋቋም በራሱ እንደማይችል ገብቶት እራሱን ስላላመነው፣ ከበዛውም ኃጢአት የተነሳ ርኩሰትን ቀስ በቀስ ተለማምዶ ኃጢአትነቱ እንዳይረሳው በመስጋት ክፋትን በየዕለቱ ከመገናኘት ተቆጠበ።7 AHAmh 86.3
በገጠር ያደጉ በምሣሌነታቸው ሊጠቀሱ የሚገባቸው ሌሎች ሰዎች፦ እንደ አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ሙሴ፣ ዳዊትና ኤልያስ ያሉ በተለያየ የዕድሜ ክልል የነበሩ እጅግ ከፍ ከፍ ያሉና የተከበሩ ሰዎችን ታሪክ አንብቡ። በቅርብ ጊዜም የነበሩ የታማኝነትንና የኃላፊነትን ቦታ ይዘው የነበሩ፣ እጅግ ዋጋ የነበራቸው ሰዎችን ሕይወት አጥኑ። ከነዚህ ውስጥ ስንቶቹ ነበሩ በገጠር ያደጉ? ድሎትን አያውቁትም ነበር። የወጣትነት ጊዜያቸውን በጨዋታ አላሳለፉትም፤ ብዙዎቹ በችግርና በድህነት ትግል ውስጥ እንዲያልፉ ተገድደው ነበር። ገና በልጅነታቸው ሥራ ተማሩ፤ ክፍት በሆነ አየር ያደገው ንቁ ሕይወታቸው ለሚሠሯቸው ሥራዎች ወኔ፣ ብርታትና ብቃት ለገሷቸው። በራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲተዳደሩ ተገድደው ችግርን መቋቋም፣ እንቅፋትን ማለፍ፣ ተምረው ብርታትና ጽናትን አተረፉ። እራሳቸውን ችለው መተዳደርንና እራስ-መግዛትን ለመዱ፤ በብዙ መንገድ ከከንቱ አብሮነት ተከልክለው በተፈጥሮ ደስታ መርካትንና ጤናማ ጓደኝነትን መመሥረት ቻሉ። ምርጫቸው ቀላል ልማዳቸውም ቁጥብ ነበር። በመመሪያም የሚተዳደሩ ንጹህ፣ ጠንካራና እውነተኛ ሆነው ያደጉ ነበሩ። ወደ ሥራም በተጠሩ ጊዜ አካላዊና አዕምሮአዊ ጉልበት፣ የደስታ መንፈስ፣ የማቀድና የመተግበር ችሎታ፣ ክፋትንም በመቋቋም ቆራጥና ለመልካምነት አጋዥ የሆነ ኃይል ይዘው ወጡ።8 AHAmh 87.1