የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ አሥራ ስምንት—የትዳር መብትና ግዴታዎች
ክርስቶስ ብሕትውና ተግባራዊ እንዲሆን አላስገደደም፦ ጋብቻ በቅዱስ መመሪያው የተጠበቀ የእግዚአብሔር ቅዱስ ድንጋጌ እንደሆነ የሚቀበሉ በማመዛዘንና በማስተዋል ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው።1 AHAmh 78.1
ክርስቶስ ማንም ወንድ ባሕታዊ(ያላገባ) ይሆን ዘንድ አላስገደደም። ከፍ ከፍ ሊያደርገው ወደ ቀድሞው ቅድስናው ሊያድሰው እንጂ የተቀደሰውን የጋብቻን ግንኙነት ለመሻር አልመጣም። የተቀደሰና ራስ-ወዳድ ያልሆነ ፍቅር ተጽዕኖ የሚያሳድርበት ትዳር ጌታ በደስታ የሚመለከተው ነው።2 AHAmh 78.2
ጋብቻ ሕጋዊና ቅዱስ ነው፦ መብላትና መጠጣት ማግባትና መጋባት በራሱ ኃጢአት አይደለም። በኖህ ጊዜ ህጋዊ ነበረ፤ ከመጠን ያለፈና ወደ ኃጢአት የሚመራ ካልሆነና ህጋዊ የሆነው በትክክል ከተተገበረ ጋብቻ ዛሬም መልካም ነው። ነገር ግን በኖህ ዘመን ሰዎች እግዚአብሔርን ሳያማክሩ የእርሱን ምሪትና ምክር ሳይጠይቁ ይጋቡ ነበር.... AHAmh 78.3
ሁሉም የኑሮ ግንኙነታችን ጊዜያዊ ወይም ዘለዓለማዊ መሆናቸው በምንሠራውና በምንናገረው ላይ የለውጥ ተጽዕኖ ሊያመጡ ይገባል። በኖህ ጊዜም በአግባቡ ስላልተገበሩት ሕጋዊ የሆነው ሥርዓት ገደብ-የለሽና ከመጠን ያለፈ እንዲሆን ተደርጎ ስለነበረ ጋብቻ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት የሞላበት ሆነ። በዚህ ዘመን በጋብቻ ሐሳብ በመወስወስ፣ በትዳር ግንኙነት ዙሪያ ባለው ጠኔ በመናወዝ፣ ነፍሳቸውን የሚያጡ ብዙ አሉ።3 AHAmh 78.4
ትዳር ቅዱስ ነው፤ ሆኖም በዚህ በተበላሸ ዘመን ሁሉንም ዓይነት የረከሰ ነገር አካትቷል። ከውኃ ጥፋት በፊት ይሠራ እንደ ነበረው ኃጢአት ዓይነት ዛሬ ጋብቻ ያለ አግባብ በመተግበሩ የጥፋት መንስኤና ከመጨረሻው ዘመን ምልክቶች አንዱ ሆኗል…. AHAmh 78.5
የጋብቻን መብቶችና ቅዱስ ባህርይውን በአግባቡ ከተረዳን ዛሬም ሰማይ ሊያጸድቀው ይችላል፤ ውጤቱም ለሁለቱም ወገኖች ደስታና እግዚአብሔርም የሚከብርበት ይሆናል።4 AHAmh 78.6
የትዳር መብቶች፦ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ…. የትዳር መብታቸው* ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል በአንክሮ ማጤን ይገባቸዋል። የተቀደሰ መርህም የእያንዳንዱ ድርጊት መሠረት መሆን አለበት።5 AHAmh 78.7
ብዙ ጊዜ ወላጆች…. የትዳር መብቶቻቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመውባቸዋል፤ ለፍላጎቶቻቸውም በመገዛታቸው እንሰሣዊ ስሜቶቻቸውን አዳብረውባቸዋል።6 AHAmh 79.1
ከመጠን ማለፍን የማስወገድ ኃላፊነት፦ የተፈቀደው ነገር ከመጠን ያለፈ ሲሆን አሳዛኝ ኃጢአት ይሆናል።7 AHAmh 79.2
ብዙ ወላጆች በጋብቻ ሕይወት ማግኘት የሚገባቸውን ዕውቀት አያገኙ ይሆናል። በመሆኑም ሰይጣን በደካማ ጎናቸው ገብቶ አዕምሮአቸውንና ሕይወታቸውን እንዳይቆጣጠር የተጠበቁ አይደሉም። በትዳር ሕይወታቸው አላስፈላጊና በገፍ ከሚደረጉ ነገሮች እንዲቆጠቡ እግዚአብሔር እንደሚፈልግ አይታያቸውም። ፍላጎትን መቆጣጠር ኃይማኖታዊ ተግባር እንደሆነ የሚሰማቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው። ምርጫቸውን የማሟላት ዓላማ ይዘው የተጋቡ ሰዎች የረከሰ ፍላጎታቸውን ጭምር ለማርካት ጋብቻቸው እንደሚፈቅድ አደርገው ምክንያት ያቀርባሉ። በቅድስና የሚያምኑ ሴቶችና ወንዶች እንኳ ዝሙታዊ ፍላጎታቸውን ልቅ ያደረጉ ናቸው። አስፈላጊ የሆነውን ኃይላቸውን በማባከናቸው ለኑሮ አይበገሬ ይሆኑ ዘንድ የሚያስችላቸውን ብርታት ማዳከማቸውና በአጠቃላይ በሥረዓተ-ግንኙነታቸው ላይ የመቆጣጠር ወኔ ማጣታቸው በእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚያስጠይቃቸው ግንዛቤ የላቸውም።8 AHAmh 79.3
ራስን መካድና መሻትን መግዛት የይለፍ ቃል ይሁኑ፦ ኦ! ለፈጣሪያቸው እንከን-የለሽ አገልግሎት ለማቅረብ፣ አዕምሮአዊና አካላዊ ብቃታቸው ሙሉ መሆን እንዳለበትና ለእግዚአብሔር ያለባቸውን ግዴታ ሁሉ እንዲረዱ ማድረግ ብችል እንዴት መልካም ነበር! ሚስት የባልዋን እንስሣዊ ፍላጎት ከሚያነሳሱ ቃላት ወይም ድርጊቶች ትታቀብ። ገና ከልጅነታቸው አዕምሮአቸውን አድክመውታል፤ በእንስሣዊ ፍላጎት በመደሰትም የአደረጃጀት ቅርፁን ሸርሽረውታል። ራስን መካድና መጠንን ማወቅ የትዳር ሕይወታቸው የይለፍ ቃላት መሆን አለባቸው።9 AHAmh 79.4
ለሰው ዘር ሁሉ ጠቃሚ እንሆን ዘንድ፣ ለእግዚአብሔርም ፍጹም አገልግሎት ማቅረብ እንችል ዘንድ ንጹህ መንፈስና ጤናማ ሰውነት እንዲኖረን እግዚአብሔር ከባድ ኃላፊነት(ግዴታ) ጥሎብናል። ሐዋርያው እነዚህን የማስጠንቀቂያ ቃላት ይናገራል፡- “ስለዚህ የሚሞተውን ሥጋችሁን ለኃጢአት አታስገዙ፤ ፈቃዱንም በጅ[እሺ] አትበሉት።” እንዲህ በማለትም በተጨማሪ ያደፋፍረናል፡- “የሚጋደልም ሁሉ ነገርን ሁሉ ይተዋል።” ክርስቲያን ነን ብለው እራሳቸውን የሚጠሩትን ሁሉ ሰውነታቸውን ቀድሰው በጌታ ፊት እንዲያቀርቡ በጥብቅ ያሳስባቸዋል። “ህያውት[ህያው] መስዋዕት አድርጋችሁ የተቀደሰች እገዚአብሔርን ደስ የምታሰኝ።” ቀጥሎም እንዲህ ይላል፡- “ነገር ግን ሥጋዬን አጥብቄ እቀጣዋለሁ አስገዛውማለሁ ሌሎችንም አስተምሬ እኔ ለራሴ የተጣል ሁ እንዳልሆን።” 10 AHAmh 79.5
ሚስቱን የዝሙት መፈጸሚያ መሣሪያ ለማድረግ የሚያነሣሳ ወንድ ንጹህ ፍቅር በውስጡ የለም። ለከንቱ ፍላጎት የሚንጫጩት እንስሣዊ ፍላጎቶቹ ናቸው። ሐዋርያው ያስቀመጠውን አይነት ፍቅር የሚገልጹ ወንዶች እንዴት ጥቂቶች ናቸው፡- “ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያንን እንደ ወደደ ስለርስዋም ራሱን እንደሰጠ ያነፃት ዘንድ ይቀድሳትም ዘንድ…. ንጽሕት እንድትሆን እንጂ ያለ ነውርም።” እግዚአብሔር ይቀድሰው ዘንድ ዕውቅና የሚሰጠው የትዳር ፍቅር ዓይነት ይህ ነው። ፍቅር ንፁህና ቅዱስ መመሪያ ነው፤ በዝሙት የሚነሣሳ ፍላጎት ግን መታቀብን አሜን ብሎ አይቀበልም፤ በማገናዘብ አይመራም፤ አይገደብምም። ለሚያስከትለው መዘዝ እውር ነው፤ መንስኤውንና ውጤቱን አያመዛዝንም።11 AHAmh 80.1
ሰይጣን ራስ-መግዛትን የሚያዳክምበት ምክንያት፦ ሰይጣን ወደ ትዳር የሚገቡትን ራስ-መግዛታቸውን ለማዳከም፣ የንጽህና ደረጃቸውንም ዝቅ ለማድረግ ይጥራል፤ የረከሰው ፍላጎት እየጨመረ ሲሄድ የግብረ-ገብነት ኃይል በቀጣይነት እንደሚቀንስ ያውቃልና። እንዲህም ሲሆን መንፈሳዊ እድገታቸው ዲያብሎስን የሚያሳስበው አይሆንም። የራሱን የክፋት መልክ በልጆቻቸው ላይ ለማተም ከዚህ የተሻለ መንገድ እንደሌለም ጠንቅቆ ያውቃል። እንዲያውም ከወላጆቻቸው ጠባይ ይልቅ የልጆቻቸውን ባህርይ በቀላሉ እንደሚፈልገው መቅረጽ እንደሚችል ያውቃል።12 AHAmh 80.2
በመጠን ያለመኖር ውጤት፦ ወንዶችና ሴቶች ሆይ የዝሙትና የእርካታውን ውጤት አንድ ቀን ትደርሱበታላችሁ። የረከሰ ፍላጎት ጋብቻ ሳይፈፀም እንዳለ ሁሉ በትዳር ውስጥም ይገኛል።13 AHAmh 80.3
ርካሽ ለሆነ ፍላጎት ተገዥ መሆን ውጤቱ ምንድን ነው?.... የእግዚአብሔር መላእክት ሊቆጣጠሩት የሚገባው የመኝታ ክፍል በረከሰ ምግባር ቅድስናውን አጣ ማለት ነው። አሳፋሪ እንስሣዊ ባህርይ ስለሚገዛን ሰውነታችን ተበላሽቷል። ከጸያፊ አድራጎት ወደ ዘግናኝ በሽታ ይመራል፤ እግዚአብሔር ለበረከት የሰጠው ለእርግማን ይሆናል።14 AHAmh 80.4
ከመጠን ያለፈ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ለአምልኮ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ፍላጎት በእርግጠኝነት ይደመስሰዋል፤ አካል የሚያጎለብተውን ዋና ንጥረ-ነገር ከአዕምሮ ይወስዳል፤ ከምንም በላይ ደግሞ ጉልበታችን በማሟጠጥ በእጅጉ እንድንደክም ያደርጋል። በዚህ እራስን የማጥፋት ተግባር ሚስት ባልዋን ማገዝ የለባትም። በበሳልና በእውነተኛ ፍቅር የምትወደው ከሆነች አታደርገውም። እንስሣዊ ባህርያት እየተበረታቱ ከሔዱ ለእርካታ ያላቸው ጥሪ የአመጽ መልክ እየያዘ ይሄዳል። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሴቶችና ወንዶች ለኃላፊነቶቻቸው ይንቁ። በመጠን ባለመኖራቸው የተነሣ ብዙ የታወቁ ክርስቲያኖች በአዕምሮና በነርቭ መስለል በሽታ እየተሰቃዩ ናቸው።15 AHAmh 80.5
ባሎች አሳቢ ሁኑ፦ ባሎች ጆሮ የሚሰጡ፣ የማይቀየሩ፣ ጥንቁቅ፣ ታማኝና ሩኅሩኅ ይሁኑ። ርኅራኄንና ፍቅርን መግለጽ አለባቸው። የክርስቶስን ቃል የሚያከብሩ ከሆነ ፍቅራቸው በራሳቸው ሰውነት ላይ ጥፋትን፣ በሚስታቸው ላይ ደግሞ ዝለትንና በሽታን የሚያመጣ ስሜታዊ የሆነ ባህርይ ያለው ምድራዊና የረከሰ አይሆንም። በሁሉም ነገር እንዲታዘዙላቸው በሚስቶቻቸው ጆሮ እያንሾካሾኩ የወረደና ርካሽ ፍላጎታቸውን ለማርካት አይማስኑም። ባል ሁሉም ክርስቲያን ሊኖረው የሚገባ ጨዋ ባህርይ፣ የልብ ንጽህናና ከፍ ከፍ ያለ ሕሊና ያለው ከሆነ ይህ ጠባዩ በትዳር ሕይወቱ የሚገለጽ ይሆናል። የክርስቶስ ሐሳብ ያለው ከሆነ የሰውነቱ አጥፊ ሳይሆን በጌታ የቅድስና እርከን ከፍተኛውን ደረጃ ለመያዝ የሚጥር፣ በለሰለሰ ፍቅር የተሞላ ይሆናል።16 AHAmh 81.1
ጥርጣሬ እየዳኸ በሚገባበት ጊዜ፦ ነውረኛ የሆነውን ፍላጎቱን ለማገልገልና ባሪያው ለመሆን በትዕግሥት ፈቃደኛ የሆነችን ሚስት ማንም ወንድ በእውነተኛ ፍቅር ሊያፈቅራት አይችልም። ለእንደዚህ ዓይነት ፍላጎቱ ፈቃደኛ በመሆንዋ ምክንያት በተዘዋዋሪ በባልዋ ዕይታ የነበራትን ዋጋ ታጣዋለች። ከፍ ከፍ ከሚያደርገው ነገር ሁሉ እየተንሸራተተች ስትወርድ ያያታል። ለእርሱ እንዳደረገችው ሁሉ በሌላም ሰው ልትዋረድ፣ ያለ ማንገራገር ፈቃደኛ ልትሆን እንደምትችል ይሰማዋል። አቋምዋንና ንጽህናዋን ይጠራጠረዋል፤ ይሰለቻታል፤ ሰይጣናዊ ስሜቱን የሚያነሣሱና የሚያጋግሉት ሌላ አዳዲስ ነገሮችን መፈለግ ይጀምራል። የእግዚአብሔርን ሕግ አይጠብቅም። እነዚህ ወንዶች ደመ-ነፍስ ከሆኑት አውሬዎች የባሱ ናቸው፤ ሥጋ የለበሱና የሰው ምስል የያዙ ዲያብሎሶች ናቸው። ከፍ ከፍ የሚያደርገውንና የሚያስከብረውን የእውነተኛና የተቀደሰ ፍቅር መመሪያ የማያውቁ ናቸው። ሚስትም በበኩልዋ ባልዋን መጠርጠር ትጀምራለች፤ ዕድሉ ቢገጥመው ከእኔ ጋር የሚፈጽመውን ከሌላዋ ሴት ጋር ሳያንገራግር ያደርገዋል ብላ ትቀናለች። በሕሊናው ወይም በፍርሐተ-እግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር እንዳልሆነ ትመለከታለች። የተቀደሱት ግድቦች ሁሉ በዝሙት ፍላጎት ተሰብረዋል፤ በባል ውስጥ የነበረው እግዚአብሔርን የመምሰል ባህርይ የርካሽና አራዊታዊ ዝሙት አገልጋይ ሆኗል።17 AHAmh 81.2
ቅጥ ያጡ መጠይቆች(ፍላጎቶች) የሚያስከትሉት ችግር፦ አሁን እልባት ማግኘት ያለበት ነገር:- አካልዋን እንድትቀድሰውና እንድታከብረው፣ ለእግዚአብሔርም ሕያው መስዋዕት አድርጋ እንድታቀርበው ጌታ ኃላፊነት ጥሎባት ሳለ፤ የረከሰ ፍላጎት የተቆጣጠረው ባልዋ የጠየቃትን ብትፈጽም ለሰውነትዋ ጉዳት እንደሚያስከትል በምክንያት አስደግፋ ያረጋገጠችው ነገር ቢሆንም፣ የባልዋን ቃል ማክበር ስላለባት ብቻ ልትፈጽመው ፈቃደኛ መሆን አለባት? AHAmh 81.3
በጤናና በሕይወት ላይ ጉዳት የሚያስከትለውን የባልዋን እንስሣዊ ባህርይ ለማርካት የሚገፋፋት ለእርሱ ያላት ንጹህና ቅዱስ ፍቅር አይደለም። በዕውነት የምታፈቅረውና ብልሃተኛ ሴት ከሆነች አግባብነት የሌለው የዝሙታዊ ፍላጎት ስሜቱን እንዲቀይር መንፈሳዊ ርዕሶችን በማንሳትና አስደሳች የሆኑ የመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር አዕምሮውን በሌላ ነገር ትጠምደዋለች። የሚቀየማትም እንኳ ቢሆን በትህትናና በፍቅር ለእንደዚህ ዓይነት ሰውነትዋን ለሚያረክስ ከመጠን ላለፈ ወሲብ፣ እጅ እንደማትሰጥ ማስረዳት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። በሰውነትዋ ሁሉ ላይ ለእግዚአብሔር ያላት ተጠያቂነት ተቀዳሚ እንደሆነ ገርና ቸር በሆነ አነጋገር ልታስረዳው ያስፈልጋል። በታላቁ በእግዚአብሔር ቀን ከተጠያቂነት ስለማታመልጥ የጌታን ነገር ቸል ትል ዘንድ እንደማይቻላት ልትነግረው ይገባታል…. AHAmh 82.1
ፍላጎቶችዋ ከፍ ከፍ ያሉ እንዲሆኑ ማድረግ ከቻለች፤ በቅድስናና በክብር የነጠረውን የሴትነት ማዕረጓን ማስጠበቅ ከቻለች፤ ብልሃተኛ የሆነውን ተፈጥሮዋን ተጠቅማ የመቀደስ ተጽዕኖዋን በባልዋ ላይ ማሳደርና የሰማዩን ተልዕኮዋንም ማሳካት ትችላለች። እንዲህም በማድረጓ ራስዋንና ባልዋን በማዳን እጥፍ ሥራ ትሠራለች። ይህ እጅግ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አስቸጋሪ ጉዳይ፣ ብዙ ጥበብንና ትዕግሥትን እንዲሁም የግብረ-ገብነት ብርታትንና ጽናትን የሚጠይቅ ነው። ብርታትና ፀጋ በፀሎት ሊገኙ ይችላሉ። ሐቀኛ ፍቅር የልብ ገዢ መርህ ይሁን። ለድርጊትሽ ብቸኛውና ትክክለኛው መቆሚያ ለእግዚአብሔርና ለባልሽ ያለሽ ፍቅር ይሁን…. AHAmh 82.2
ሚስት ህሊናዋን፣ ክብርዋንና ማንነትዋን ሁሉ ሰውታ አካልዋንና አዕምሮዋን እንዲቆጣጠር በሁሉ ነገር የእርሱ ፈቃድ ብቻ እንዲፈፀም እራስዋን ለባልዋ አሳልፋ ስትሰጥ፣ ለመልካም ነገር የምትጠቀምበትን ባልዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ የሚያስችላትን ያን ታላቅ ተጽዕኖ የማሳደር ዕድልዋን ታጣለች። ሁለቱም የመለኮታዊ ተፈጥሮአቸው ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ፣ ለመንፈሳዊ ነገር የበለጠ ትኩረት በመስጠት በዝሙት ምክንያት ዓለምን ከሞላው ብልሽት ያመልጥ ዘንድ፣ ግትር ተፈጥሮውን ልታለዝበው፤ በሚቀድሰው ተጽዕኖዋም ልታጠራውና ልታነፃው፤ ፍላጎቱን ሊቆጣጠር ወደሚችልበት መንገድ ልትመራው ትችላለች። በፀጋ ዕጦት ያረጀው ልብ ከረከሰ ስሜትን የማርካት ፍላጎት ተላቆ፣ የሚሻውን ከፍ ያለና የከበረ መልዕክት ያገኝ ዘንድ ተጽዕኖዋ ከፍተኛ ሚና የመጫወት ኃይል አለው። የፍቅሩ ዋነኛ መሠረት እንስሳዊ ፍላጎት ሆኖ፣ እንቅስቃሴውን ሁሉ ተቆጣጥሮ እያለ ባልዋን ለማስደሰት ስትል በእርሱ ደረጃ ልክ ዝቅ ማለት እንዳለባት የሚሰማት ሴት፣ ሊቀድሰው የሚችለውን ተጽዕኖዋን በባልዋ ላይ ማሳረፍ አልቻለችምና እግዚአብሔርን በእጅጉ ታሳዝናለች። ሚስቱ ስለሆነች ያለ አንዳች የተቃውሞ ቃል ለእንስሣዊ ፍላጎቱ እጅ መስጠት የተገባት እንደሆነች የምታምን ከሆነ ለባልዋም ሆነ ለእግዚአብሔር ያሉባትን ግዴታዎች አታውቅም።18 AHAmh 82.3
ሰውነታችን የተገዛ ንብረት ነው፦ የወረዱ ፍላጎቶች በሰውነታችን ላይ ተቀምጠው ሥራቸውን በውስጡ ይሠራሉ። “ሥጋ” ወይም “የሥጋ” ወይም “የሥጋ ምኞት” የሚሉት ቃላት ዝቅ ያለውንና የተበላሸውን ተፈጥሮ ያቀፉ ናቸው፤ ሥጋ ብቻውን በራሱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይፃረር ዘንድ አይቻለውም። ከፍላጎቱና ከምኞቱ ጋር ሥጋን እንድንሰቅለው ታዘናል። የምንተገብረው እንዴት ነው? ሰውነታችንን በማቁሰል? አይደለም፤ ኃጢአት እንድንሠራ የሚፈታተነንን ፍላጎት በመግደል እንጂ። የተበላሸ አስተሳሰባችንን ከራሳችን ላይ አሽቀንጥረን ልናባርረው ይገባናል። ሐሳብና ምኞት ሁሉ በየሱስ ክርስቶስ ምርኮ ሥር ይሁኑ። ሁሉም እንስሣዊ ዝንባሌአችን ለበለጠው የነፍስ ኃይል መገዛት አለበት፤ የእግዚአብሔር ፍቅር በልዕልና መግዛት አለበት። ክርስቶስ ያልተከፋፈለ ዙፋን ላይ ይቀመጥ፤ አካሎቻችን በርሱ የተገዙ ንብረቶች እንደሆኑ ይታወቅ፤ የአካላችን ብልቶች የጽድቅ መሣሪያዎች መሆን ይገባቸዋል።19 AHAmh 83.1