የአድቬንቲስት ቤት

18/88

ምዕራፍ አሥራ ሰባት—የጋራ ግዴታዎች

እያንዳንዱ የራሱ ኃላፊነት አለው፦ እነዚህ ፍላጎታቸውን ያጣመሩ ሁለት ሰዎች የየግል ባህርያትና የየራሳቸው ኃላፊነቶች አሉባቸው፤ እርሱም ሥራ አለው፤ እርስዋም ሥራ አላት። ነገር ግን ሴቶች ልክ አንደ ጭነት እንሰሳ መሥራት በሚችሉት ሥራ መጠን መገምገም(መለካት) የለባቸውም። ሚስት በሚስትነትዋ በቤተሰቡ ዙሪያ ሞገስ፤ ለብልህ ባልዋም ጓደኛ መሆን አለባት። በምትወስደው በእያንዳንዱ እርምጃ እንዲህ ብላ ትጠይቅ:- “የእውነተኛ ሴትነት ደረጃ ይህ ነው?” “ተጽዕኖዬ ክርስቶስመሰል የሚሆነው እንዴት ነው?” ባልም ሥራዋን እንደሚያደንቅላት ለሚስቱ ሊያሳውቃት ይገባል።1 AHAmh 73.1

ሚስት ባልዋን ታክብር፤ ባል ደግሞ ሚስቱን ይውደድ፤ ይንከባከባትም። የጋብቻ ቃል-ኪዳናቸው አንድ እንዳደረጋቸው በክርስቶስ ያላቸው እምነት ደግሞ የበለጠ ሊያዋህዳቸው ይገባል። ወደ ትዳር ኑሮ የሚገቡ በአንድነት ከየሱስ ለመማር ብሎም በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት የሚያደርጉትን ጥረት ከማየት የበለጠ እግዚአብሔርን ምን የሚያስደስተው ነገር አለ?2 AHAmh 73.2

ከመጋባታችሁ በፊት ያልነበሩ አሁን ልታከናውኗቸው የሚገባችሁ ኃላፊነቶች አሉባችሁ። “ስለዚህ ቸርነትንም ትህትናውንም ገርነትንም ትዕግሥትንም…. ልበሱ” “ክርስቶስ እንደ ወደደን በፍቅር ተራመዱ።” የሚቀጥለውን መመሪያ በጥንቃቄ አጥኑ፡ - “እላንት ሴቶች ለባሎቻችሁ ተገዙ ለጌታ እንደምትገዙ። ወንድ የሴት ራስ ነውና ክርስቶስ የቤተ-ክርስቲያን ራስ እንዳለ…. ቤተ-ክርስቲያንም ለክርስቶስ እንድትገዛ እንዴሁም ሴቶች ለባሎቻቸው ይገዙ በሁሉ። እላንት ወንዶች ምሽቶቻችሁን [ሚስቶቻችሁን] ውደዱ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያኒቱን እንደ ወደደ ስለ እርስዋም ራሱን እንደ ለወጠ።” AHAmh 73.3

የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ለሔዋን፦ ሔዋን እጣ ፈንታዋ የሚሆነው ሐዘንና ስቃይ ተነግሮአት ነበር፤ ጌታም አለ:- “ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ትሆናለች እርሱም ይገዛሻል።” በፍጥረት ጊዜ እግዚአብሔር ከአዳም እኩል አድርጎ ሠራት። ለእግዚአብሔር ታዛዥ ቢሆኑ ኖሮ - ግሩም ለሆነው የፍቅር ሕጉ ቢገዙ ኖሮ - ለዘለዓለም ተስማምተው መኖር በቻሉ ነበር። ኃጢአት ግን ጥልን አመጣ፤ በመሆኑም ጥምረታቸው ሊቀጥል፣ መግባባታቸው ሊጠበቅ የሚችለው አንዳቸው ለሌላው ሲረቱ ብቻ ሆነ። በመተላለፍ ሔዋን የመጀመሪያ ነበረች፤ ከመለኮታዊ ምሪት ተቃራኒ በሆነ መልኩ ከባልዋ በመነጠልዋ በፈተና ወደቀች። በእርስዋ ማባበል ምክንያት አዳም ኃጢአት ሠራ፤ በእርሱም እዝ ሥር እንድትሆን ተደረገች። ከጥፋትም በኋላ የእግዚአብሔር ሕግና መመሪያዎች ጥቅም፣ በወደቀው ዘር ዋጋ ተሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ በኃጢአት ምክንያት የመጡ ቢሆንም ለበረከት ይሆኑላቸው ነበር። ነገር ግን ለወንድ የተሰጠው የበላይነት ያለ አግባብ እየተተገበረ የሴትን ዕጣ ፈንታ መራራና ሸክምዋ የከበደ አድርጎታል። AHAmh 73.4

በኤደን በነበረው ቤታቸው ሔዋን ከባልዋ ጎን ሆና ፍጹም ደስተኛ ነበረች። ነገር ግን እንደ ቁንጥንጦቹ ዘመናዊ ሔዋኖች እግዚአብሔር ከወሰነላት የበለጠ ከፍ ወዳለ ሥፍራ መግባት አሰበች። ከነበራት ደረጃ በላይ መዝለቅ ስትሞክር ወደ ታች ርቃ ወደቀች። እንደ እግዚአብሔር እቅድ የሕይወታቸውን ሸክም በፀጋ ለመቀበል እምቢ የሚሉ ሁሉ ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥማቸዋል።4 AHAmh 74.1

ሚስቶች ተገዙ፤ ባሎች ውደዱ፦ ብዙ ጊዜ ይህ ጥያቄ ይጠየቃል፡-“ሚስት የራስዋ ፈቃድ ሊኖራት አይገባም?” ባል የቤተሰብ እራስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምጦታል። “እላንት ሴቶች ለባሎቻችሁ ተገዙ።” ትዕዛዙ እዚህ ላይ ቢያልቅ ኖሮ ሚስት ፈጽሞ መሆን የማትመኘው ደረጃ ስለተሰጣት፣ ኃላፊነትዋም በብዙ ነገር አስቸጋሪና ፈታኝ በመሆኑ ብዙ ጋብቻዎች ባይፈጸሙ ይሻላል AHAmh 74.2

ማለት እንችል ነበር። ብዙ ባሎች “ሚስቶች ተገዙ” የሚሉት ቃላት ላይ ያቆማሉ። የዚህን ትዕዛዝ ማጠቃለያ ስናነብ ግን “በጌታ እንደሚገባ” ይላል። ሚስት አምላክዋን መፍራትና ማክበር ሁልጊዜ በፊትዋ ትጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር ይጠይቃታል። ሙሉ በሙሉ መታዘዝ የሚገባት የራሱ ልጅ አድርጎ ዋጋ በማይገኝለት ሕይወቱ ለገዛት ለጌታ የሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ብትጥሰውና ብታረክሰው ሳትቀጣ የማትቀርበትን ምክንያት የሚያመዛዝን ሕሊና እግዚአብሔር ሰጥቷታል። ማንነትዋ ከባልዋ ጋር ሊዋሃድ አይችልም፤ እርስዋ በክርስቶስ የተገዛች የእርሱ ንብረት ናትና። ከሰይጣን ባርነት ነፃ ለማውጣት ዋጋ ለተከፈለበት(ክርስቶስ ቤዛ ለሆነለት) ሰውነትዋ ሳትጠነቀቅ እንዲህ በማድረጓ አካልዋንና መንፈስዋን እንደምትጎዳ እርግጠኛ ብትሆንም በጭፍን ታማኝነት ባሌ ያዘዘኝን ሁሉ ልክ እርሱ እንዳለው መፈፀም አለብኝ ብላ ማሰብዋ ስህተት ነው። ከባልዋ የበለጠ ከፍ ከፍ ያለ አለ፤ እርሱም የዋጃት የሱስ ነው። ለባልዋ መገዛትዋም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ይሁን - “በጌታ እንደሚገባ።” AHAmh 74.3

ሴቶች በቤት ውስጥ ተሰሚነት ሊኖራቸው እንደማይችል፣ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ መታዘዝ እንዳለባቸው ሲገልጹና ለባሎቻቸው በፍጹም መገዛት እንዲገዙ ሲጠየቁ ሳለ፣ ባሎች ግን ለሚስቶቻቸው የሚሰጡት ቦታ ከቃሉ የሚፃረር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በዚህ ሁኔታ በመተርጎማቸው በጋብቻ ተቋም ዕቅድ ላይ ተቃውሞ ያነሣሉ። ይህ አተረጓጎማቸው ለእነርሱ ያልተሰጠውን መብት አጣምመው በመውሰድ የራሳቸውን የፍርደ-ገምድልነት ፈቃድ ለማሳካት ሲሉ የሚተገብሩት ነው። ማንበባችንን እንቀጥል፡ - “እላንት ወንዶች ሴቶቻችሁን ውደዱ በእርሳቸውም አትቆጡ” ባል ለሚስቱ መራር የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው? የምታበሳጭና ብዙ ስህተት ያለባት ሆና አግኝቷት ቢሆን እንኳ መንፈሰ-መራራነቱ ለጥፋትዋ መድኃኒት አይሆንም።5 AHAmh 74.4

ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት ያለባቸው ልክ ባሎች ለክርስቶስ መገዛት እንዳለባቸው ነው፦ ከሚስቶቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ብዙ ባሎች የጌታን መንገድ ካለመጠበቃቸው የተነሣ የሱስ ክርስቶስ ከቤተ-ክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነቱ በትክክል አልተወከለም። ሚስቶቻቸው በሁሉም ነገር ለእነርሱ ታዛዥ መሆን እንዳለባቸው ያውጃሉ። እራሱን ለክርስቶስ ሳያስገዛ ባል እንደ ቤት እራስነቱ ቁጥጥር እንዲያደርግ የእግዚአብሔር እቅድ አልነበረም። ክርስቶስ ከቤተ-ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት ይወክል ዘንድ ገዥነቱን፣ እንዲሁም ሚስቱ በሁሉም ነገር ልትታዘዝለት እንደሚገባት ያለውን ሐሳብ ፈጽሞ መናገርም ሆነ ማንፀባረቅ የለበትም። እርሱ እግዚአብሔር አይደለም። እንዲህ የሚያደርግ ወንድ በትክክለኛ ትርጉሙ ባል ተብሎ ሊጠራ አይገባውም…. AHAmh 75.1

ባሎች በኤፌሶን መልዕክት እንደተቀመጠው ዓይነት የሚወክሉት ምሣሌነት ምን ዓይነት ባህርይ እንዳለው ሊያውቁ ይገባቸዋል። ክርስቶስ ከቤተ-ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት ዓይነት ባል ለቤተሰቡ እንደ መሲህ መሆን እንደሚጠበቅበት፣ ባለቤቱንና ልጆቹን ከፍ ከፍ ለማድረግ እግዚአብሔር በሰጠው ጨዋ ወንድነቱ ፀንቶ ይቆማል? ንጹህና ጣፋጭ አየር የሚተነፍስ ነው? የቤተሰብ የመሪነት እርካብ ላይ ሲቆናጠጥ የበላይነቱን ለማረጋገጥ እንደሚለፋ ሁሉ የየሱስን ፍቅር የቤቱ ቋሚ መርህ አድርጎ ለማሳደግ በትጋት ይሠራል? AHAmh 75.2

እያንዳንዱ ባልና አባት የክርስቶስን ቃል በሁሉም አቅጣጫ ለመረዳት ያጥና። ሚስት ለባልዋ ትገዛ በሚለው ሐሳብ ውስጥ በመኖር የቃሉን አንድ ጎን ብቻ ማየት አይገባውም። ነገር ግን የራሱ ደረጃ በቤተሰቡ ዙሪያ ምን እንደሆነ ከቀራንዮ መስቀል በሚወጣው ብርሃን ፈልጎ ማግኘት አለበት። “እላንት ወንዶች ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያኒቱን እንደ ወደደ ለእርስዋም ራሱን እንደሰጠ። በውኃ ማጸብያ በቃሉም ያነጻት ዘንድ ይቀድሳትም ዘንድ።” በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሊያነጻን፣ ከኃጢአትና ከብክለት ሊጠብቀን በመስቀል ላይ ሊሞት ራሱን አሳልፎ ሰጠ።6 AHAmh 75.3

ይቅር መባባል አስፈላጊ ነው፦ በቤታችን ስምምነት እንዲሰፍን ከፈለግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ላይ ሊኖር ግድ ነው። ሚስት የክርስቶስ መንፈስ ካላት ለምትናገረው ትጠነቀቃለች፤ የተሰጠችም ትሆናለች፤ ሆኖም የባልዋ አጋር እንጂ ያለ ደሞዝ የምትሠራ ባሪያ እንደሆነች አይሰማትም። ባል የእግዚአብሔር አገልጋይ ከሆነ በሚስቱ ላይ ፈላጭ-ቆራጭነቱን የሚጭንባት አይሆንም። ከመጠን ባለፈ ጥንቃቄ የቤትን ፍቅር መጠበቅ አንችልም፤ የጌታ መንፈስ የሚኖርበት ከሆነ ግን የሰማይ አምሳል ይሆናል…. አንዱ ሲያጠፋ ሌላኛው የክርስቶስን ዓይነት ይቅር-ባይነት ያሳያል እንጂ በቀዝቃዛ መንፈስ አይርቅም።7 AHAmh 75.4

ሚስትም ሆነች ባል የፈላጭ-ቆራጭነት ቁጥጥር በሌላኛው ላይ ለማስፈን መሞከር የለባቸውም። ለራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ትኩረት በመስጠት የራሳችሁ ሐሳብ የአጋራችሁን ስሜት እንዲያንበረክክ አታስገድዱ። በእንዲህ ዓይነት ስሜት ፍቅራችሁን እንደነበረ ማቆየት አትችሉም። ቸር፣ ትዕግስተኛና ይቅር-ባይ፣ አሳቢና ሩኅሩኅ ሁኑ። በጋብቻ መሐላችሁ ለመፈጸም ቃል እንደገባችሁ ብትተጉ በክርስቶስ ፀጋ ለእርስ በእርሳችሁ ደስታ በመፍጠር ውጤታማ ትሆናላችሁ።8 AHAmh 76.1

እያንዳንዱ ትህትና በተሞላበት መረታት ይረታ፦ በትዳር ሕይወት ወንዶችና ሴቶች አንዳንድ ጊዜ እንዳልተቀጡ ብልሹ ልጆች ይሆናሉ። ባል እርሱ የሚለው እንዲሆን ይፈልጋል፤ ሚስት በበኩልዋ እኔ ያልኩት ካልሆነ ትላለች፤ ሁለቱም መሸነፍ አይፈልጉም። እንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታቸው የሚያመጣው ትርፍ ጥልቅ የሆነ ሐዘንን ብቻ ነው። ሁለቱም የየራሳቸውን መንገድ ወይም ሐሳብ ለመተው ዝግጁ መሆን አለባቸው። ሁለቱም የሚፈልጉትን ነገር ካላደረግን ብለው ድርቅ ማለታቸው ደስተኞች የመሆናቸውን ዕድል የሚያጠብ ነው።9 AHAmh 76.2

ሴቶችና ወንዶች የዋህነትንና ራስን ዝቅ ማድረግን ከክርስቶስ ካልተማሩ በስተቀር ሁልጊዜ በልጆች የሚታየውን ችኩልና ምክንያት-አልባ መንፈስ ያንፀባርቃሉ። ኃይለኛውና ያልተገራው ፍላጎት ሊሠለጥንባቸው ይፈልጋል። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የሐዋርያው ጳውሎስን ቃል ያጥኑ:- “ህፃን በነበርሁ ጊዜ እንደ ህፃን እናገር ነበርሁ፤ እንደ ህፃን አውቅ ነበርሁ፤ እንደ ህፃንም አስብ ነበርሁ። ጎልማሳ ግን በሆንሁ ጊዜ የህፃኑን ፀባይ ተውሁ።” 10 AHAmh 76.3

የቤተሰብ ችግሮች፦ ባልና ሚስት ያሉባቸውን ብዙ ኃላፊነቶች ሚዛናዊና ተገቢ በሆነ መልኩ ለመከፋፈል ቢጥሩም እንኳ ልባቸውን ለእግዚአብሔር ማስረከብ ከተሳናቸው የቤተሰባቸውን ችግሮች መቅረፍ በጣም ከባድ ይሆንባቸዋል። ባልና ሚስት የትዳር ሕይወታቸውን ፍላጎቶች ከፋፍለው በምን ዓይነት መንገድ የሞቀ ፍቅራቸውንና ጠንካራ ጥምረታቸውን መጠበቅ ይችላሉ? ለትዳራቸው በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ የጋርዮሽ ፍላጎት ማሳየት አለባቸው፤ ሚስት ክርስቲያን ከሆነች ከባልዋ ጋር ፍላጎትዋን ታስማማለች፤ እርሱ የቤተሰቡ ራስ ነውና።11 AHAmh 76.4

ምክር ለሚጋጩ ቤተሰቦች፦ መንፈስህ ልክ አይደለም። አቋም ስትወስድ በጥንቃቄ ሳታመዛዝን፣ አስተያየትህ ምን ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል በደንብ ሳታጤን፣ ሚስትህ ተመሳሳይ አቋም እንደሌላት እያወቅህ የራስህን ኃሳብ ከፀሎታችሁና ከንግግራችሁ ትደበልቀዋለህ። እንደ ጨዋ ወንድ የምትለያዩባቸውን ነጥቦች በየዋህነት እንደመሸሽ፣ ለባለቤትህ ስሜት አክብሮት እንደመስጠት፣ በሚያጨቃጭቋችሁ ነጥቦች ላይ ነገርህን ቀጥለሃል። በዙሪያህ ላሉት ደንታ ሳትሰጥ የራስህን ሐሳብ በመግለጽ ግትርነት አሳይተሃል። ሌሎች ሰዎች በነገሮች ላይ ከአንተ የተለየ ሐሳብና ዕይታ ሊኖራቸው መብታቸው እንዳልሆነ ይሰማሃል፤ እነዚህ ፍሬዎች በክርስቲያን ዛፍ ላይ አያድጉም።12 AHAmh 76.5

ወንድሜና እህቴ ሆይ፣ የሱስን ለመቀበል የልባችሁን በር ክፈቱ። ወደ ነፍሳችሁ መቅደስ ጋብዙት። የጓዳ ሕይወታችሁን መሰናክል ሁሉ ለማሸነፍ ተረዳዱ። ከባለንጋራችሁ ከሰይጣን ጋር የከረረ ግጭት ይጠብቃችኋል፤ በዚህ ጦርነት እግዚአብሔር እንዲረዳችሁ ከፈለጋችሁ ለማሸነፍ በምትወስኑት ውሳኔ አንድ መሆን አለባችሁ። ክፉ ነገርን ከመናገር ምላሳችሁን ልትሰበስቡ፣ አፋችሁን ልትለጉሙ፣ በጉልበታችሁ በመውደቅና በመጮኽ “ጌታ ሆይ የነፍሴን ባላንጣ ቅሰፍ” ልትሉ ይ ገባችኋል።13 AHAmh 77.1

ክርስቶስ በእያንዳንዳችሁ ልብ ሕብረትን ያመጣል፦ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽሙ ከሆነ ባልና ሚስት ይከባበራሉ፤ ፍቅርና ልበ-ሙሉነትን ያዳብራሉ። የቤተሰቡን ሠላምና አንድነት የሚያውክ ማንኛውም ነገር ሁሉ በእርግጥ ሊቀጭ ይገባዋል፤ በአንፃሩ ቸርነትና ፍቅር ሊበረታቱ ይገባቸዋል። የገራምነትን፣ የይቅር-ባይነትንና የፍቅርን መንፈስ የሚያንፀባርቅ እርሱ ተመሳሳይ መንፈስ ይንፀባረቅለታል። የእግዚአብሔር መንፈስ የነገሠበት ቤት ያለመመቻቸት ወሬ የሚወራበት አይደለም። የክብር ተስፋው ክርስቶስ በእርግጥ በውስጣቸው ካለ ሕብረትና ፍቅር በቤታቸው ውስጥ ይበዛል። በሚስት ልብ ውስጥ የሚኖረው ክርስቶስ በባል ልብ ውስጥም ያለው እራሱ ክርስቶስ ስለሆነ ሁሉም ነገራቸው ስምሙ ይሆናል። ክርስቶስ ለሚወዱት ያዘጋጀላቸውን እልፍኝ ለመውረስ በሕብረት የሚጥሩ ይሆናሉ።14 AHAmh 77.2