የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሰባ ሰባት—ገና
ገና እንደ ዓመት-በዓል፡- ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ በዓለም ዙሪያ የምንሰማው “ገና ተቃርቧል” የሚለውን ማስታወሻ ነው። ለወጣቶች ለጎልማሶችና በዕድሜ ለገፉ ጭምር ታላቅ የሐሴትና የተድላ ጊዜ ነው። ግን ይህንን ያህል ትኩረት ይስብ ዘንድ ገና ምንድን ነው?.... AHAmh 350.1
የታህሳስ 25ኛ ቀን [ታህሳስ 29 በኢትዮጵያ የቀናት አቆጣጠር] የሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል፤ ይህ ቀን የተለመደና ሕዝባዊ ሆኖ ቀጥሏል። ነገር ግን ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን እያከበርን እንደሆነ የሚያረጋግጥልን ነገር የለም። ታሪክ ለዚህ የማያወላውል ማስረጃ አይሰጠንም። መጽሐፍ ቅዱስም ትክክለኛውን ጊዜ አይጠቅስም። ይህን ቀን ማወቅ ለመዳናችን አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ የሚያስፈልገንን ሁሉ እግዚአብሔር በነብያቱና በሐዋርያቱ በኩል ይነግረን ነበር። ነገር ግን በዚህ ነጥብ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ማለቱ ከእኛ የተሠወረው ለመልካም ዓላማ እንደሆነ ያሳየናል። AHAmh 350.2
ጌታ በጥበቡ ሙሴ የተቀበረበትን ቦታ ደበቀው፤ እግዚአብሔር ቀበረው፤ እርሱ አስነሳው፤ ወደ ሰማይም ወሰደው። ይህም ምሥጢራዊነት ጣዖት አምላኪነትን ለመገደብ የተደረገ ነበር። በሕይወት እያለ ያመጹበት፤ ሰው መሸከም ከሚችለው በላይ ያሰቃዩት እርሱ በሞት ከተለያቸው በኋላ ልክ እንደ እግዚአብሔር ሊመለክ ምንም አልቀረውም ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ለዓለም መድሃኒት፣ ለክርስቶስ ለራሱ የተገባው ክብር፣ ለተወለደበት ቀን እንዳይሰጥ በማሰብ የዕለቱ ትክክለኛ ጊዜ እውቀት ከዓለም የተሰወረ ሆነ። ልንቀበለውና ልናምነው፣ ከምንም በላይ ደግሞ ይደገፉበት ዘንድ ወደርሱ የሚመጡትን ፈጽሞ እንደሚያድነው እንደ ጌታ ገናን እንዳናየው ነው። የነፍስ አምልኮ የዘለዓለማዊ አባት ልጅ ለሆነው ለየሱስ መሰጠት ይገባዋል።1 AHAmh 350.3
ቀኑ ቸል ሊባል አይገባውም፡- ታህሳስ 25 [ታህሳስ 29 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር] የክርስቶስ መወለድ ታስቦ የሚውልበት ስለሆነ ልጆችም በተግባራዊ ተምሣሌት ይህ ቀን የተድላና የደስታ እንደሆነ ስለተማሩ የተወሰነ ትኩረት ሳትሰጡት ማለፍ ይከብዳችኋል። መልካም ተግባራት እንዲከናወኑበት መሆን ይችላል። በወጣቶች ዙሪያ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ከንቱ ጨዋታንና ደስታን በመፈለግ የመንፈሳዊነታቸው ገዳይ የሆኑ መዝናኛዎችን እራሳቸው እንዲመርጡ መለቀቅ የለባቸውም። የልጆቻቸውን ሐሳብና ሥጦታ ወደ እግዚአብሔር ወደ ሥራውና ነፍሳትን ወደ ማዳን በማዞር ወላጆች ሁኔታውን ሊቆጣጠሩ ይችላሉ። የመዝናናት ፍላጎታቸው እንዲሟላ በመልቀቅ ወይም በዘፈቀደ እምቢ በማለት ሳይሆን ትጉህ በሆነ ጥረት ወላጆች ነገሩን መምራት አለባቸው። ሥጦታዎችን የመስጠት ፍላጎታቸው ወደ ጠራና የተቀደሰ መንገድ ሊመራ፣ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ለመጣበት ታላቅና ግዙፍ ሥራ ይውል ዘንድ ጎተራውን በመሙላት ለሰዎች መልካም እንዲሆንላቸው ሊውል ይችላል። እራስን-መካድና እራስን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ የጌታ ሥራ መገለጫዎች ነበሩ። የዘለዓለማዊ ሕይወት ተስፋችን ምሰሶ የቆመው በእርሱ ላይ ነውና የሱስን እንወደዋለን ብለን የምንናገር ሁሉ የተግባራችን መገለጫ እርሱ እንዳደረገው ይሁን።2 AHAmh 350.4
የሥጦታ ልውውጥ እንደ ፍቅር መግለጫ፡- የበዓል ወቅት የሥጦታ ልውውጡን አንግቦ በፍጥነት እየደረሰ ነው። ወጣትና አዛውንቱ ሁሉ ለፍቅራቸው ማስታወሻነት ለጓደኞቻቸው ምን መስጠት እንዳለባቸው በአንክሮ እያጠኑ ነው። ምንም ትንሽ ቢሆን እንኳ ከምንወዳቸው ሥጦታ መቀበል የሚያስደስት ነው። እንዳልተረሳን ማረጋገጫችን ሲሆን የነበረንን ቅርበት በጥ ቂቱ ይጨምረዋል…. AHAmh 351.1
በዚህ ሁሉ ወደር የሌለውን ጓደኛችንን እግዚአብሔርን የማንረሳው ከሆነ ለማስታወሻነትና ለፍቅር መግለጫ ሥጦታ ብንለዋወጥ ትክክል ነው። ለተቀባዩ ትክክለኛ ጥቅም ሊሆኑ የሚችሉ ስጦታዎችን እናዘጋጅ። ምክሩን የበለጠ እንድንወደው የሚመሩ ወይም የእግዚአብሔርን ቃል የበለጠ እንድንረዳው የሚያደርጉ መጻሕፍትን በሥጦታ እንድንሰጥ እመክራለሁ። በረዣዥሞቹ የክረምት ምሽቶች ሊነበቡ የሚችሉ ሥጦታዎችን አዘጋጁ።3 AHAmh 351.2
ተመራጭ መጻሕፍት ለልጆች፡- ስለ ወቅታዊ እውነት የሚናገሩ መጻሕፍትና ሕትመቶች የሌሏቸው ብዙዎች ናቸው። ገንዘባችሁ የአደጋ መንስኤ ሳይሆን ጥቅም ላይ የሚውልበት መስክ ይኸውላችሁ። የሚያነብቡት የሚያስፈልጋቸው ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ ሕፃናት አሉ። The Sunshine Series, Golden Grain Series, Poems, Sabbath Readings* የመሳሰሉት ሁሉም ወርቃማ መጻሕፍት ናቸው። በእያንዳንዱ ቤት ሊገቡ የሚችሉ ናቸው። ለከረሜላዎችና እርባና-ቢስ የሕፃን አሻንጉሊቶች የሚወጡት ሳንቲሞች ተጠራቅመው እንዲህ ዓይነቶቹን መጻሕፍት መግዛት ይችላሉ…. ለልጆቻቸው፣ ለልጅ ልጆቻቸው፣ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ሴቶችና ወንዶች ልጆች ዋጋ ያለው ሥጦታ ማበርከት የሚፈልጉ ሁሉ ከላይ የተጠቀሱትን መጻሕፍት ይግዙላቸው። ለወጣቶች ደግሞ The Life of Joseph Bates ጥሩ ቅርስ ነው። ሦስቱ የThe Sprit of Prophecy** መጻሕፍት (volumes) በምድሪቱ ባለ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቤት ውስጥ ይኑሩ። እግዚአብሔር ከሰማይ ብርሃን እየሰጠ ነው፤ አንድም ቤተሰብ ያለዚህ ብርሃን አይሁን። የምታዘጋጇቸው ስጦታዎች ወደ ሰማይ በሚወስደው መንገድ ላይ የብርሃን ጮራ የሚፈነጥቁ ይሁኑ።4 AHAmh 351.3
የሱስ ሊረሳ አይገባውም፡- ወንድሞችና እህቶች ሆይ ለእርስ በእርሳችሁ ለምትሰጣጧቸው ስጦታዎች እየተዘጋጃችሁ ሳለ ሰማያዊ ጓደኛችን እንዳትረሱ፤ የእርሱን መጠይቅ እንዳትዘነጉ አሳስባችኋለሁ። እንዳልረሳነው ብናሳየው ክርስቶስ ደስ የማይለው ይመስላችኋል? የሱስ የሕይወት ልዑል የሆነው ጌታ ወደ ድነት መድረስ እንችል ዘንድ ሁሉን ነገሩን ሰጠን…. እስከሞቱ እንኳ ቢሆን የዘለዓለም ሕይወት ይሆንልን ዘንድ ለእኛ ተሰቃየ። AHAmh 352.1
እያንዳንዱን በረከት የምንቀበለው በክርስቶስ በኩል ነው…. ሰማያዊ ለጋሻችን የፍቅርና የምሥጋና መግለጫችን ተካፋይ መሆን አይገባውም? ኑ! ወንድሞችና እህቶች ሆይ ከልጆቻችሁ ጋር ኑ፤ በክንዳችሁ ላይ ያሉ ሕፃናትም ቢሆኑ ይዛችኋቸው ኑ፤ እንደ አቅማችሁ መጠን ለእግዚአብሔር ሥጦታዎቻችሁን አምጡ። በልባችሁ ጥዑመ-ዜማ ተቀኙለት፤ ምሥጋናውም በከንፈራችሁ ላይ ይሁ ን።5 AHAmh 352.2
ገና - እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ የምናደርግበት ጊዜ፡- ዓለም በዓላትን የሚያከብራቸው በእርባና-ቢስ በብክነት በቁንጣንና በታይታ ነው…. በሚመጡት የገናና የዘመን መለወጫ በዓላት በማያስፈልጉ ነገሮች የሚወጣው ገንዘብ፣ የጉዳቱ መጠን ብሩ ዝም ብሎ ሜዳ ላይ ቢበተን ከሚያመጣው ኪሳራ ይብሳል። ከዚህ የቆረቆዘ ዘመን፣ ባህልና ልማዶችን እንለይ ዘንድ እድሉ ተሰጥቶናል። ስለዚህ ሆዳችንን ለመሙላት ወይም አላስፈላጊ ምኞትን ለማርካት የማይጠቅሙ ጌጣጌጦችን ወይም አልባሳትን ለመግዛት ገንዘባችንን ከማውጣት ይልቅ በፊታችን ያሉትን በዓላት እግዚአብሔርን ለማክበርና ከፍ ከፍ ለማድረግ ልንጠቀምባቸው እንችላለን። AHAmh 352.3
ከሁሉም የበለጠው ዓላማችን ክርስቶስ ይሁን። ገና አሁን እየተከበረ ባለበት ሁኔታ ግን ለጌታ የተገባው ክብር ተወስዶ፣ በኃጢአት ለተሞላውና የጎደፈ ባህርይ በመላበሱ ምክንያት ክርስቶስ ወደ ዓለማችን ይመጣ ዘንድ ላስገደደው ሟች ሰው ተሰጥቷል።6 AHAmh 352.4
የሰማይ ግርማዊ ንጉሥና ሞገስ የሱስ የግብረ-ገብነት ጉልበቱ ለላሸቀው በኃጢአት ለተበላሸው የወደቀ ሰው መለኮታዊ እርዳታ ይመጣ ዘንድ ንጉሣዊነቱን ወደ ጎን ትቶ የክብር ዙፋኑንና የአዛዥነት የበላይነቱን ለቅቆ ወደ ዓለማችን መጣ…. AHAmh 352.5
ወላጆች እነዚህን ነገሮች በልጆቻቸው ፊት በማስቀመጥ ለእርስ በእርሳቸው ያሉባቸውን ግዴታዎች በማሳየት ሥጦታዎችን በማዘጋጀት እርስ በእርስ እንዲሞጋገሱና እንዲሞካሹ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ያለባቸውን ግዴታ ቃል በቃልና በመመሪያ ላይ መመሪያ በማውሳት ሊያስ ተምሯቸው ይገባል።7 AHAmh 352.6
የልጆችን አስተሳሰብ ወደ አዲስ መስመር ቀይሩት፡- ብዙ ጊዜ ለልጆቻችንና ለዘመዶቻችን ከሚበረከቱ አላስፈላጊ ከሆኑ ሥጦታዎች ይልቅ ደግነታችንን የሚያንፀባርቁና ደስታ ወደ ቤታችን የሚያመጡ በምርጫ የተሻሉና በዋጋም እጅግ ያነሱ ስጦታዎችን በብዙ መንገድ ማዘጋጀት ይቻላል። AHAmh 353.1
ስጦታቸው በዋጋ ያነሰበትን ምክንያት እየነገራችኋቸው በእግረ-መንገዳችሁን መልካም ትምህርት አስተምሯቸው። ከአሁን በፊት ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ ለእነርሱ ደስታ ቦታ ትሰጡ እንደነበር አሳዩአቸው። ስለ ራሳችሁ ደስታና ስለ እነርሱ ፍላጎት የበለጠ ታስቡ እንደ ነበር፤ ሥጦታ ለማያስፈልጋቸው በማበርከት የእግዚአብሔርን ሥራ ወደ ፊት ከማራመድ ይልቅ የዓለምን ባህልና አኗኗር ስትከተሉ እንደነበር ንገሯቸው። ልክ የቀድሞዎቹ ብልህ አባቶች ያደርጉት እንደነበረ ከሁሉ የበለጠውንና የተሻለውን ሥጦታ ለእግዚአብሔር በማበርከት ለኃጢአተኛው ዓለም የሰጠውን ግሩም ሥጦታ እንደምታደንቁ አሳዩት። አንድያ ልጁን ሳይሣሳ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ስጦታ እንዲያበረክቱለት በማነሳሳት የልጆቻችሁ አስተሳሰብ በአዲስና ራስ-ወዳድነት በሌለበት መንገድ እንዲቀየስ አድርጉ።8 AHAmh 353.2
የገና ዛፍ ይኑረን?፡- ለቤተ ክርስቲያን የሚበረከቱ ትንንሽም ሆኑ ትልልቅ ሥጦታዎች ሊንጠለጠሉባቸው የሚችሉ የገና ዛፎች በእያንዳንዱ ቤተ-ክርስቲያን ቢኖሩ እግዚአብሔር በጣም ደስ ይለዋል።* የገና ዛፍ ይኑረን ወይ? የሚሉ የጥያቄ ደብዳቤዎች ደርሰውናል። የገና ዛፍ ማኖራችን ዓለም እንደሚያደርገው መሆን አይሆንብንም? የሚሉም ጥያቄዎች ተነስተዋል። የእኛ መልስ እንደ ዓለም እንዲሆን የሚፈልግ ጠባይ ካላችሁ እንደ ዓለም ልታደርጉት ትችላላችሁ፤ እንደ ዓለም እንዳይሆን ከፈለጋችሁም ደግሞ ትችላላችሁ የሚል ነው። አረንጓዴ ዛፍ መምረጥና በቤተ-ክርስቲያኖቻችን ማስቀመጥ ኃጢአት የሚሆንበት የተለየ ምክንያት የለም። ወደዚህ ተግባር የሚገፋፋው ከጀርባ ያለው ሐሳብና በዛፉ የተቀመጡት ሥጦታዎች የሚውሉበት ጥቅም ግን ኃጢአት ሊያደርገው ይችላል። AHAmh 353.3
ዛፉ ለበዓሉ እንደሚስማማ ረዥምና ቅርንጫፎቹም ሰፋፊ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ጠንካራዎቹ ቅርንጫፎች በወርቃማና ብራማ ስጦታዎቻችሁ የተንዠረገጉ ይሁኑ፤ ይህንን የገና ስጦታችሁን ለጌታ አበርክቱ። የለገሳችኋቸው ስጦታዎች በፀሎት ይቀደሱ።9 AHAmh 353.4
የገናና የአዲስ ዓመት በዓላት ረዳት ለሌላቸው ሲባል ይከበሩ። ብዙ አባላት ያላቸውን ቤተሰቦች ለመርዳት ስንሰጥ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይላል።10 AHAmh 353.5
በሥጦታ የተሞላ ዛፍ ኃጢአት አይደለም፡- ለሰንበት ትምህርት ተማሪዎች መዝናኛ ይሆን ዘንድ በሁሉም ወቅት አረንጓዴ የሆነ ዛፍ መኖሩ ኃጢአት ነው የሚለውን አቋም ወላጆች መውሰድ የለባቸውም፤ ለታላቅ በረከት ሊውል ይችላልና። የቸርነት እሳቤዎችን በአዕምሮአቸው አስቀምጡ። የእንደዚህ ዓይነቶቹ ስብስባዎች ዓላማ እንዲያው ለመዝናናት ብቻ ፈጽሞ መሆን የለበትም። እነዚህ በዓላት ለአንዳንዶች የማይረባና የዘፈቀደ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት፣ አዕምሮአቸው መለኮታዊ መነካትን የማያገኝበት ቢሆኑም ለሌሎች ነፍሳትና ገፀ-ባህርያት ግን እጅግ ጠቃሚ ወቅቶች ናቸው። ብዙ ግብረ-ገብነትን የሚገድሉ ስብሰባዎች በመልካሞቹ ይተኩ ዘንድ መንገድ መቀየስ ስለሚቻል ሙሉ በሙሉ ረክቻለሁ።11 AHAmh 354.1
ያልጎደፈ ደስታ ለዕለቱ አቅርቡ፡- ክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ሆይ እራሳችሁን ለሥራ በማስታጠቅ በእግዚአብሔር ፍርሐት ይህ ጉዳይ በሥነ-ሥርዓት ይካሄድ ዘንድ፤ ደረቅና የማይስብ ሳይሆን የሰማይን የአዎንታ ማህተም የያዘ ከግድፈት የራቀና ደስታ የሞላበት ይሆን ዘንድ ቆርጣችሁ አትነሱም? ለነዚህ አስተያየቶች በመልካም የሚመልሱት ድኆች እንደሚሆኑ አውቃለሁ። ሆኖም ሀብታሞቹም ቢሆኑ ፍላጎት ማሳየትና እግዚአብሔር በአደራ ከሰጣቸው ገቢያቸው ጋር የሚመጣጠን ሥጦታና መሥዋዕት ሊያቀርቡ ይገባቸዋል። የእግዚአብሔር ሥራ በቋሚነት ይቀጥል ዘንድ መንግሥቱም ይቋቋም ዘንድ በልግስና በመስጠት እስካሁን ታይቶ የማያውቅ የገና በዓል በሰማያዊ መጻሕፍት ይመዝገብ።12 AHAmh 354.2