የአድቬንቲስት ቤት

79/88

ምዕራፍ ሰባ ስምንት—ቤተሰብ - የአገልግሎት ማዕከል

ወላጆች ለልጆች ትክክለኛ አቅጣጫ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡- እንደ ክርስቲያንነታችንና እንደ ወላጅነታችን ልጆቻችን ትክክለኛውን አቅጣጫ ይይዙ ዘንድ እንድናስተምራቸው ኃላፊነት ተጥሎብናል። በጥንቃቄ፣ በጥበብና በገርነት ወደ ክርስቶስ-መሰል አገልግሎት ልንመራቸው ይገባናል። ልጆቻችን ለእርሱ አገልግሎት እናሳድጋቸው ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ቅዱስ ቃል-ኪዳን ገብተናል። የአገልግሎት ሕይወት ይመርጡ ዘንድ በሚያስችላቸው ተጽዕኖ እንድንከባቸውና አስፈላጊውን ሥልጠና እንድንሰጣቸው ተቀዳሚ ኃላፊነት አለብን።1 AHAmh 355.1

ዛሬም ልጆች ዳንኤሎችና አስቴሮች መሆን ይችላሉ፡- በምድጃዎቻችን ዙሪያ ለሚያድጉት ልጆች የእኛ ውስን የማየት ችሎታ መረዳት ከሚችለው በላይ እግዚአብሔር ሰፊ ጥልቅና ከፍ ያለ እቅድ አለው። ከተራ ቤተሰብ የወጡ እርሱ ታማኝነቱን ያሳያቸው፤ ባለፉት ዘመናት ለእርሱ ምሥክር ይሆኑ ዘንድ በዓለም ከፍተኛ ሥፍራዎች ተጠርተዋል። በይሁዳዊ ቤቱ እንዳደገው ዳንኤል ዛሬም ብዙ የእግዚአብሔርን ቃልና ሥራዎቹን እያጠኑ የታማኝ አገልግሎትን ትምህርት እየተማሩ የሚያድጉ ወጣቶች ለነገስታት ንጉሥ ምሥክሮች ይሆኑ ዘንድ በሕግ አውጪዎች በፍርድ-ሸንጎዎችና በንጉሣዊ ፍርድ ቤቶች ፊት ይቆማሉ። ብዙዎች ለሰፊው አገልግሎቱ ይጠራሉ። ዓለም በሙሉ ለወንጌሉ እየተከፈተ ነው…. በኃጢአት የተመቱ ልቦች ጩኸት የፍቅር አምላክን ዕውቀት በመሻት ከእያንዳንዱ የዓለማችን ዳርቻ ይመጣል… ጩኸታቸውን የመመለስ ኃላፊነት እውነቱን በተቀበልነው በእኛና ይህንን ዕውቀት ልናካፍላቸው በተገባን ልጆቻችን ጫንቃ ላይ ነው። ለእያንዳንዱ ቤተሰብ፣ ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት፣ ለእያንዳንዱ ወላጅ፣ መምህርና ልጅ የወንጌሉ ብርሃን ለበራለት ሁሉ በእስራኤል ታሪክ እጅግ ከባድ ፈተና በነበረበት ጊዜ ለንግሥት አስቴር የቀረበላት ጥያቄ በዚህ ችግር ጊዜም ይቀርብለታል፡ “ደግሞስ እንዲህ ላለው ጊዜ አንቺ ወደ መንግሥት እንደደረስሽ ማን ያውቃል?” 2 AHAmh 355.2

ለክርስቶስ ለመመሥከር የሚያስችሉ ውጤታማ መንገዶች፡- ሁሉም ሰው አገልጋይ ሆኖ ወደ ሌላ አገር መሄድ አይችልም፤ ነገር ግን በቤተሰቡና በጎረቤቱ ሁሉም አገልጋይ መሆን ይችላል። የቤተ-ክርስቲያን አባላት በዙሪያቸው ላሉ ሁሉ መልእክቱን የሚያስተላልፉበት የተለያዩ መንገዶች አሉ። እጅግ ውጤታማ ከሆኑት መንገዶች አንዱ ሌሎችን አጋዥ የሆነ ራስ-ወዳድነት-የሌለበት ክርስቲያናዊ ሕይወት ነው። በከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ሆነው የሕይወትን ጦርነት የሚፋለሙ ሁሉ ምንም ወጪ በማያስወጣ ትንሽ ትኩረት ሊጠናከሩና ሊታደሱ ይችላሉ። እንዲሁ የሚነገሩ ደጋግ ቃላት የሚቸሩ ጥቃቅን ትኩረቶች የፈተናንና የጥርጥርን ደመና ከነፍስ ጠራርገው የሚወስዱ ናቸው። በቀናነት የሚቸር በእውነት ከልብ የሚገለጽ ርኅራኄ ቀላልና ለስላሳ የሆነውን የክርስቶስን መንፈስ ዳበሳ የሚሹትን ልቦች በር የመክፈት ኃይል አለው።3 AHAmh 355.3

ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች ሰፊ የሥራ መስክ አለ። የተዋጣለት ምግብ አብሳይዋ፣ የልብስ ሰፊዋ፣ የነርስዋ… የሁሉም እርዳታ ይፈለጋል። የድኃ ቤተሰቦች ምግብ እንዴት እንደሚዘጋጅ የራሳቸውን ልብስ እንዴት እንደሚሠሩና የተቀደደውን እንዴት እንደሚለፉ፣ የታመመን እንዴት እንደሚንከባከቡና ቤትን በሥነ-ሥርዓት እንዴት እንደሚያስተዳድሩ ይማሩ። ልጆች ሳይቀር የነርሱን ያህል እድለኞች ላልሆኑ ሲሉ ጥቂት የፍቅርና የምህረት እርምጃ ይራመዱ ዘንድ ሊመሩ ይገባቸዋል።4 AHAmh 356.1

ሌሎችን ለማገልገል ልጆችና ወጣቶች ይተባበሩ፡- አንዳንዶች ማስተባባያ በመፈለግ “የቤት ውስጥ ኃላፊነቶች ጊዜዬንና ገንዘቤን ሁሉ ወሰዱት” ይላሉ። ወላጆች ሆይ ለጌታ ለመሥራት ያላችሁን ጉልበትና ችሎታ ለመጨመር ልጆቻችሁ ሊረዷችሁ ይገባል። ልጆች የጌታ ቤተሰብ ወጣት አባላት ናቸው። በፍጥረትና እንደገና በማዳን የራሱ ንብረት ላደረጋቸው እግዚአብሔር እራሳቸውን እንዲቀድሱ ሊመሩ ይገባቸዋል። የአካላቸው፣ የአዕምሮአቸውና የነፍሳቸው ኃይላት ሁሉ የእርሱ እንደሆኑ ይማሩ። በተለያዩ መስኮች ራስ-ወዳድነት የሌለበት አገልግሎት መስጠት ይችሉ ዘንድ ይሠልጥኑ። ልጆቻችሁ እንቅፋት ይሆኑባችሁ ዘንድ አትፍቀዱ። ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር ሥጋዊና መንፈሳዊ ሸክሞችን ይጋሩ ዘንድ ይገባቸዋል። ሌሎችን በመርዳት የራሳ ቸውን ደስታና ጠቀሜታ ይጨምራሉ።5 AHAmh 356.2

እያንዳንዱ/ዷ ወጣት በእርግጥ እራሳቸውን ለእግዚአብሔር ቀድሰው ቢያቀርቡ፤ የደከሙትንና ችግር የበሳሰካቸውን እናቶቻቸውን ያሳርፉ ዘንድ በቤት ውስጥ ሕይወታቸው ራስን የመካድ ልምድ ቢያዳብሩ፤ በቤተ-ክርስቲያኖቻችን ምን ዓይነት ለውጥ በመጣ ነበር! እናትም ጎረቤቶችዋን ለመጎብኘት ጊዜ ባገኘች ነበር። አጋጣሚዎች ሲገኙ ሌሎችን ሊባርኩ የሚችሉ ጥቃቅን የቸርነትና የፍቅር የመላላክ ተግባራትን በማከናወን ልጆች ገና በሕፃንነታቸው እንኳ ሊያግዙ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ድኃና ችግረኛ የሆኑ የእኛን እምነት የማይጋሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ሊደረሱ ይችላሉ። ስለጤናና መጠንን ስለማወቅ የሚያወሱ መጻሕፍት ለብዙ ቤቶች ይዳረሳሉ። የእነዚህ መጻሕፍት ስርጭት አስፈላጊ ሥራ ነው። በሽታ እንዴት እንደሚታከም የሚያስተምሩ እነርሱ ወርቃማ እውቀት ተሸክመዋል። ይህ እውቀት ለሐኪም ገንዘብ ከፍለው መታከም ለማይችሉ ታላቅ በረከት ነው።6 AHAmh 356.3

እግዚአብሔር ለሥራው ልጆችን እንደ ትንንሽ ወንጌላዊያን ይፈልጋቸዋል፡- እግዚአብሔር እያንዳንዱን በለጋ እድሜ ያለ ልጅ የራሱ ልጅ ይሆን ዘንድ ወደርሱ ቤተሰብ እንዲቀላቀል ይፈልጋል። ልጅነት ቢኖራቸውም ወጣቶች የአማኞች ቤተሰብ አባል በመሆ ን እጅግ ዋጋ ያለ ው ልምድ መቅሰም ይችላሉ።7 AHAmh 357.1

በሕፃንነታቸው ልጆች ለእግዚአብሔር ሥራ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ… ትዕግሥተ-ቢስነትን፣ ነዝናዛነትንና ኃጢአትን ሁሉ ማሸነፍ ይችሉ ዘንድ ጌታ ፀጋውንና ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣቸዋል። የሱስ ልጆችን ይወዳል። ለእነርሱ ብዙ በረከቶች አሉት፤ ለወላጆቻቸው ታዛዦች ሆነው ማየትን ይወዳል። የራሳቸውን ዝንባሌ በመግታት እራስን ማዕከል ላደረገ ደስታ ከማደር እምቢ በማለት እርሱን ያገለግሉት ዘንድ ሕፃን ወንጌላውያን እንዲሆኑለት እግዚአብሔር ይፈልጋል። ይህ የሕፃናት አገልግሎት ልክ እንደ ጎለመሱ ልጆች በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነው።8 AHAmh 357.2

መመሪያዎችን በማስቀመጥና ምሣሌ በመሆን ልጆች ላልተለወጡ ነፍሳት ይሠሩ ዘንድ ወላጆች ያስተምሩ። ለተጎዱና በዕድሜ ለገፉ ርኅራኄ ያደርጉ ዘንድ የድሆችንና የተጨነቁትን ሁሉ ስቃይ ያስታግሱ ዘንድ ልጆች በአንክሮ መማር አለባቸው። በሚሲዮናዊ ሥራቸውም ታታሪ ይሆኑ ዘንድ ይማሩ። ከእግዚአብሔር ጋር የሥራ ባልደረቦች ይሆኑ ዘንድ ገና በጨቅላ ዕድሜአቸው እራስን መካድና እራስን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን በማስተማር ለሌሎች መልካምነትና ለክርስቶስ ዓላማ መሳካት ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው የመስጠት ትምህርት በውስጣቸው ሊሰርጽ ያስፈልጋል።9 AHAmh 357.3

ወላጆች በክርስቶስ ያለውን እውነት ሳይጨምሩ ሳይቀንሱ ሳይበርዙና ሳይከልሱ ለልጆቻቸው ይናገሩ። ልጆች ደግሞ በቀናነት ተፈጥሮአቸው የተማሩትን ለጓደኞቻቸው ይደግሙላቸዋል።10 AHAmh 357.4

ቤተ-ክርስቲያን ለወጣቶች ሥራ አላት፡- ወጣት ወንዶችና ሴቶች በአደራ የተሰጧቸውን መክሊቶች ጥቅም ላይ ማዋል ይችሉ ዘንድ እንዲሠለጥኑ የቤተ-ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች እቅዶችን መንደፍ ያስፈልጋቸዋል። በዕድሜ ገፋ ያሉ የቤተ-ክርስቲያን አባላት ልባዊና ርኅራኄ የተላበሰ ሥራ ለልጆችና ለወጣቶች ይሥሩ። አገልጋዮች ያላቸውን ዕውቀት ሁሉ በመጠቀም ወጣት የቤተ-ክርስቲያን አባላት በሚሲዮናዊ ሥራ አብረዋቸው መሥራት የሚችሉበትን መንገድ ያመቻቹ። ነገር ግን በአገልግሎት ሰብስባችሁ ረዥም ስብከት በመስበክ ፍላጎታቸውን እናነሣሳለን ብላችሁ እንዳታስቡ። ትኩስ ፍላጎት ሊገነፍል የሚችልበትን መንገድ አቅዱ። ሁሉም የሚጫወተው ሚና ይኑረው። የተሰጣቸውን ሥራ ማከናወን ይችሉ ዘንድ ወጣቶችን አሠልጥኑ፤ በየሣምንቱም ወደ ወንጌል ሥራው ስብሰባ ዘገባቸውን (ሪፖርታቸውን) ይዘው ይምጡ፤ ምን እንደገጠማቸው በክርስቶስ ፀጋም ምን ስኬት እንዳገኙ ይናገሩ። ዝርዝር መግለጫው በተቀደሱ ሠራተኞች ከቀረበ የአገልግሎት ስብሰባው ለዛ-ቢስና አሰልቺ አይሆንም። የሚስቡና የሚያስደስቱ ይሆናሉ፤ ተሳታፊዎቹም ከስብሰባው አይቀሩም።11 AHAmh 357.5

በአካባቢያችሁ ልትጠቀሙባቸው የምትችሏቸውን ዕድሎች ፈልጉ፡- በአካባቢያችን ያሉትን አጋጣሚዎች እያንዳንዱ ሰው የመድረስ ዕድል አለው። ኃላፊነት የተሰጣችሁን በአካባቢያችሁ ልትሠሩት የሚገባችሁን ሥራ ለመፈጸም ተነሱ።*ሥራውን ትሠሩ ዘንድ ሌሎች እስኪገፋፏችሁ አትጠብቁ። ግላዊ ኃላፊነታችሁ ሕይወቱን ለሰጣችሁ ለእርሱ እንደሆነ እያሰባችሁ ሳትዘገዩ ተንቀሳቀሱ። ልክ ክርስቶስ በአካል ሲጠራችሁ እንደሰማችሁ ከእንቅልፋችሁ ባንናችሁ በመነሣት እግዚአብሔር በሰጣችሁ እያንዳንዱ ክህሎት የተቻላችሁን ሁሉ ለአገልግሎቱ ልታደርጉ ተጣደፉ። ከሕያው እግዚአብሔር ቃል የተነሣ ሌላ ማን እንደተቀሰቀሰ ለማየት ዞር ዞር አትበሉ። ሙሉ ለሙሉ ከተቀደሳችሁ እናንተን እንደ መሣሪያው በመጠቀም እውነትን ወደ ሌሎች ያዳርሳል፤ እውነትም ያገኙትን ሰዎች በጨለማ ላሉ ብዙ ነፍሳት ብርሃን የሚያዳርሱ አገልጋዮች ያደርጋቸዋል።12 AHAmh 358.1

የክርስቲያን ቤተሰቦች ወደ ጨለማ ሀገራት ይግቡ፡- በስህተትና በጨለማ ውስጥ ወዳሉ ሕብረተሰቦች የክርስቲያን ቤተሰቦች እንዲሄዱና ሳይታክቱ በጥበብ ለጌታ እንዲሠሩ እግዚአብሔር ይጠራቸዋል። የዚህ ጥሪ መልስ እራስንመሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን ይጠይቃል። ብዙዎች እያንዳንዱ መሰናክል እስኪወገድ ድረስ እየጠበቁ ሳለ ነፍሳት ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እየሞቱ ናቸው። ብዙዎች እጅግ ብዙዎች ዓለማዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሮጡ፤ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ለመቅሰም ሲሉ ቸነፈር ወደበዛባቸው ቦታዎች በመሄድ በችግርና መከራ ይሰቃያሉ። ስለ አዳኙ ለሌሎች ይመሠክሩ ዘንድ ወደ እንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ለመሄድ ፈቃደኛ የሆኑት ሰዎች የት ናቸው? ወንጌሉ ወደሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች የሚዘምቱ በጨለማ ያሉትን ወደ ዓለም መድኃኒት የሚያመላክቱ ወንዶችና ሴቶች የት አሉ?13 AHAmh 358.2

ቤተሰቦች ጨለማ በሆኑ የምድር ክፍሎች፣ የመንፈስ ድግዝግዝ በዋጣቸው አካባቢዎች ቢሠፍሩ የክርስቶስ ሕይወት ብርሃን በእነርሱ በኩል ይፈነጥቅላቸው ዘንድ በጨለማ ወደ ተከበቡ አገራት ቢሄዱ ታላቅ ሥራ መከናወን ይችላል። ያለ አገልጋዮች እርዳታ ሥራው በጣም ሰፍቶ የማይችሉት ካልሆነ በስተቀር የቤተ-ክርስቲያንን ገንዘብ ሳይጠቀሙ እዩኝ እዩኝ በማይል ሁኔታ በፀጥታ ሥራቸውን ይጀምሩ።14 AHAmh 358.3

ሌሎች መሥራት በማይችሉበት ጊዜ ልጆች ሥራውን ይሠራሉ፡- እውነቱን ይናገሩ ዘንድ ጎልማሳ ሰዎች እንደማይፈቀድላቸው የሰማይ ኃይላት በሚመለከቱበት ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በልጆች ላይ ይወርዳል፤ መንገዳቸው በመታጠሩ ምክንያት ታላላቆች ሊሠሩት የማይችሉትን እውነትን የማወጅ ሥራ ልጆች ይፈጽሙታል።15 AHAmh 359.1

በዓለም ታሪክ መዝጊያ የመጨረሻ ትዕይንቶች ሰዓት እነዚህ ልጆችና ወጣቶች በእውነት ምስክርነታቸውና በቀናነታቸው ሆኖም በመንፈስና በኃይል በሚከናወን ተግባራቸው ሕዝብን ያስደንቃሉ። እግዚአብሔርን መፍራት ተምረዋል፤ በጥንቃቄና ፀሎት በተሞላበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልባቸው ለስልሷል። በቅርብ ጊዜ ልጆች በእግዚአብሔር መንፈስ ተሞልተው እውነትን ለዓለም በማወጅ በሰዓቱ በታላላቅ የቤተ-ክርስቲያን አባላት ሊሠሩ የማይችሉትን ሥራዎች በብቃት ያከናውናሉ።16 AHAmh 359.2

የቤተ-ክርስቲያን ትምህርት-ቤቶቻችን ልጆችን ለዚህ ታላቅ ሥራ ያዘጋጁ ዘንድ በእግዚአብሔር ተቀብተዋል። በዚህ ቦታ ተግባራዊ ለሚሆን ሚሲዮናዊ ሥራና ለዚህ ጊዜ በሚያስፈልግ እውነት እንዲሠለጥኑ አስፈላጊ ነው። የታመሙትንና የሚሰቃዩትን ይረዱ ዘንድ ስማቸውን በሠራተኛ ወታደሮች ዝርዝር ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። ልጆች በህክምና ሚሲዮናዊ ሥራ ላይ በመሳተፍ በጥቃቅን አስተዋጾአቸው ሥራው ወደፊት እንዲገፋ ሊረዱ ይችላሉ…. በእነርሱ የእግዚአብሔር መልዕክት እንዲታወቅ የሚፈውሰውም መድኃኒቱ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲደርስ ይሆናል። ስለዚህ ቤተ-ክርስቲያን ለመንጋው ጠቦቶች ስትል ሸክምን ትሸከም፤ ልጆች ለእግዚአብሔር አገልግሎት ይማሩ፤ ይሠልጥኑ።17 AHAmh 359.3

ማድረግን በማድረግ ተማሩ፡- ለክርስቶስ ያለው ፍቅርና ታማኝነት የእውነተኛ አገልግሎት ሁሉ ምንጭ ነው። በጌታ ከተነካ ልብ ውስጥ ለእርሱ የመሥራት ፍላጎት ይፈልቃል። ይህ ፍላጎት ይበረታታ፤ በትክክለኛው አቅጣጫ ይመራ። በቤት፣ በጎረቤት ወይም በትምህርት ቤትም ቢሆን ችግረኞች፣ ተጎጂዎች፣ ማስተዋል የጎደላቸው፣ ወይም ዕድለ-ቢሶች ቢኖሩ እንደ መጥፎ አጋጣሚ ሳይሆን የተሰጡንን የማገልገል ሥጦታዎቻችን ተግባራዊ ማድረግ እንችል ዘንድ ያገኘናቸው ወርቃማ ዕድሎች እንደሆኑ ነው መቁጠር ያለብን። በማንኛውም ሥራ እንደሚታየው ሁሉ በዚህ ተግባርም የሙያ ልምድ የበለጠ ይዳብራል። ውጤታማነታችን የሚረጋገጠው በተለመዱ የኑሮ ተግባራት ተሳትፎ በምናገኘው ሥልጠና እንዲሁም ለተቸገሩና ለሚሰቃዩ በምናደርገው አገልግሎት ነው። ያለዚህ ልምምድ ላቂያ የሌላቸው ጥረቶች እንኳ ዋጋ-ቢስ እንዲያውም ጎጂዎች ይሆናሉ። ሰዎች ዋና የሚማሩት በውኃ ውስጥ እንጂ በየብስ ላይ አይደለም።18 AHAmh 359.4