የአድቬንቲስት ቤት

47/88

ምዕራፍ አርባ ስድስት—የእንጀራ እናት

ምክር ለእንጀራ እናት፦ ልጆች ያሉትን አባት ማግባትሽ በረከት እንደሚሆንልሽ እርግጥ ነው…. እራስሽን ማዕከል ከማድረግ የአስተሳሰብ አደጋ ተርፈሻል። እስካሁን ያልተጠቀምሽበት ሊነቃቃና ተግባር ላይ ሊውል የሚያስፈልገው ወርቃማ ባህርይ አለሽ…. በአዲሱ ግንኙነትሽ ልምድ በማካበት ከሚመጡት ልጆች የተለየ አስተሳሰብ ጋር እንዴት መግባባት እንደምትችይ ትማሪያለሽ። ልጆቹን ስትንከባከቢ በእግረመንገድሽ ሀዘኔታን ፍቅርንና ርኅራኄን ታጎለብቻለሽ። የተጣሉብሽ ኃላፊነቶች ለታላቅ በረከት ምክንያት ሊሆኑልሽ ይችላሉ። እነዚህ ልጆች ዋጋ የማይገኝላቸው የመማሪያ መጽሐፍ ይሆኑልሻል። በትክክል ልታነቢያቸው ካልቻልሽ ብዙ በረከቶች ሊያመጡልሽ ይችላሉ። እነርሱን ለመንከባከብ የተቀሰቀሰው የሐሳብ ባቡር ልስላሴ ፍቅርና ርኅራኄን ለሥራ ይጠራቸዋል። እነዚህ ልጆች የደምና የሥጋሽ ክፋይ ባይሆኑም ባገባሽው አባታቸው በኩል የአንቺ ሆነዋል፤ ልትወጃቸው፣ ልትንከባከቢያቸው፣ ልታሰለጥኛቸውና ከፍ ያለ ዋጋ ልትሰጫቸው ይገባሻል። ከእነርሱ ጋር በመቆራኘትሽ የምታሰላስያቸውና የምታቅጃቸው ሁሉ እውነተኛ ጥቅም ይሆኑልሻል…. ከቤትሽ በምታገኝው ልምድ ራስሽን ብቻ ማዕከል በማድረግ ስራሽን ሊያበላሹ ከነበሩት ሐሳቦች ተገላግለሽ፣ አዲስ ፈር በመቀየስ መስተካከል የሚያስፈልጋቸው የድሮዎቹ እቅዶችሽ እንዲሞረዱ፣ እንዲስተካከሉና በቁጥጥርሽ ሥር እንዲሆኑ ታደርጊያቸዋለሽ…. AHAmh 190.1

ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በርኅራኄ የተሞሉ የለሆሳስ ቃላት ይዘሽ ትቀርቢ ዘንድ የላቀ ገራምነትና ሰፊ ሰብአዊነት ማጎልበት ያስፈልግሽ ነበር። ልጆችሽ እነዚህ ባህርያት ከውስጥሽ እንዲመነጩ በመርዳት የማመዛዘን ችሎታሽንና የአስተሳሰብ ዳርቻሽን ያሰፉታል። ከእነርሱ ጋር ያለሽ የፍቅር ግንኙነትሽ በስቃይ ውስጥ ላለው የሰው ዘር አገልግሎትሽ የበለጠ የዋህና ሩኅሩኅ እንድትሆኚ ያስተምርሻል። 1 AHAmh 190.2

ወቀሳ ፍቅር ለጎደላት እናት፦ ባልሽን ወደሽው አግብተሽዋል። ስታገቢው የልጆቹ እናት ለመሆን ቃል ገብተሽ መሆኑን ታውቂያለሽ፤ በዚህ ጉዳይ እጥረት እንዳለብሽ አይቻለሁ። በአሳዛኝ ሁኔታ ጉድለት አለብሽ። የባልሽን ልጆች አትወጃቸውም፤ ሥር-ነቀል ለውጥ ካላደረግሽ፤ በራስሽና በአስተዳደርሽ ላይ ተሐድሶ ካላመጣሽ፤ እነዚህ የከበሩ ዕንቁዎች [ልጆች] ይጠፋሉ። የርህራሄ መገለጫ የሆነው ፍቅር የመመሪያሽ አካል አይደለም። AHAmh 190.3

የእነዚያን ልጆች ሕይወት በተለይም የሴትዋን መራራ እያደረግሽው ነው። ፍቅርሽ እንክብካቤሽና ታጋሽነትሽ የታለ? ከማበረታታትና ከማመስገን ይልቅ ተግሳጽ ከከንፈርሽ ይፈልቃል። ጠባይሽ የጭካኔ አካሄድሽና ርኅራኄ-አልባ ተፈጥሮሽ ለሰቀቅተኛዋ የእንጀራ ልጅሽ በለጋ ተክል ላይ እንደሚወርድ በረዶ ነው፤ ሕይወትዋ ተንኮታኩቶ የተሰባበረና የበለዘ እስኪሆን ድረስ እያንዳንዱ [ከአፍሽ የሚወጣው] ድንፋታ ያጎብጣታል። AHAmh 191.1

አስተዳደርሽ የልጆችሽን የፍቅር ተስፈኝነትና የደስታ መንገድ የሚያደርቅ ነው። የማይለወጥ ሐዘን በሕፃንዋ ልጃገረድ ፊት ይታያል፤ ሆኖም ይህ በውስጥሽ ርኅራኄና ልስላሴን በመቀስቀስ ፈንታ ትዕግሥተ-ቢስነትንና ሥር የሰደደ ጥላቻን ያነሣሳል። ብትወጅስ ይህን ሁኔታሽን ደስተኛና ሕይወት ሰጪ ወደ ሆነ ባህርይ ልትቀይሪው ትችያለሽ…. AHAmh 191.2

ልጆች የእናታቸውን ልብ በሚገባ ማንበብ ይችላሉ፤ እየተንፀባረቀ ያለው ፍቅር ወይስ ጥላቻ እንደሆነ ይገባቸዋል፤ አንቺ ግን የምትሠሪውን አታውቂም። በሐዘን የተዋጠው ትንሽ ፊት፤ ፍቅርን ተርቦ ከሚጣራው ከተጨቆነ ልብ የሚወጣው ወደ ላይ የሚገነፍለው ቁና ቁና አተነፋፈስ ሐዘኔታ አይጭርብሽምን? 2 AHAmh 191.3

አግባብነት የሌለው ጭቆና ውጤት፦ ከጥቂት ጊዜ በፊት የጄ(J) ሁኔታ ታይቶኝ ነበር፤ ጥፋቶችዋና ስህተቶችዋ ሁሉ አንድም ሳይቀር በፊትዋ ተስለውላት ነበር። በተሰጠኝ በኋለኛው ራዕይ ላይ ግን ስህተቶችዋ ሳይወገዱ ለባልዋ ልጆች ቀዝቃዛና ርኅራኄ የሌላት ነበረች። ተግሳጽና ወቀሳ የምትሠነዝረው ከባድ ለሚባሉ ጥፋቶች ብቻ ሳይሆን ተራና እንዳላየች ሆና ልታልፋቸው የምትችላቸው ጥቃቅን ስህተቶችም ጭምር ነበር። ተደጋጋሚ ጥፋትን የመፈለግ ዝንባሌ ስህተት ነው። ይህንን ባዘለ ልብ ውስጥ የክርስቶስ መንፈስ ሊኖር አይችልም። ልጆቹ ጥሩ ሲያደርጉ ቅጭጭ ሳይላት፣ አንድም የምሥጋና ቃል ጠብ ሳታደርግ አንዲት ትንሽ ስህተት ስታገኝ ግን ለማውገዝ በተጠንቀቅ የቆመች ናት። ይህ ምን ጊዜም የልጆችን ቅስም በመስበር ወደ ሥርዓተ-አልበኝነት የሚመራቸው ነው። ክፋትን በልባቸው በማማሰል ጭቃና እድፍ ያስተፋቸዋል [ፀያፍ ቃላት እንዲናገሩ ያደርጋቸዋል]። እንደ ልማድ ሆኖ ሁልጊዜ የሚገሰጹ ልጆች “አያገባኝም፤የራሱ ጉዳይ” የሚል መንፈስ ያላቸው ሲሆን ለሚመጣው መዘዝ ቁብ ሳይሰጡ ርኩስ ፍላጎትን የሚያንፀባርቁ ይሆናሉ…. AHAmh 191.4

እህት ጄ ርኅራኄና ፍቅር ማጎልበት ይገባታል፤ በስርዋ ላሉ እናት አልባ ልጆች መልካም ፍቅር ማሳየት ይጠበቅባታል። ይህም ልጆች በእግዚአብሔር ፍቅር እንዲባረኩና ፍቅሩም በእርስዋ ላይ እንዲንፀባረቅ ያደርገዋል። 3 AHAmh 191.5

እጥፍ [እን]ክብካቤ በሚያስፈልገበት ጊዜ፦ እናታዊ ፍቅር በጡትዋ ይፈስላቸው የነበረችውን እናታቸውን ያጡ ልጆች መቸም የማይተካውን ፍቅር አጥተዋል። የዚህን የተጎዳ ትንሽ መንጋ የእናትነት ቦታ ለመተካት የምትገባ ሴት እጥፍ ሐሳብና ሸክም ይወድቅባታል። በመሆኑም ከተቻለ እናታቸው ልትሆንላቸው ከምትችላቸው በላይ አፍቃሪ፤ ተግሳጽንና ምክርን በታጋሽነት የምትፈጽም መሆን አለባት። እንዲህም ሲሆን ትንሹ መንጋ የደረሰበት ጉዳት ይካካስለታል። 4 AHAmh 192.1