የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ አርባ ሰባት—የክርስቶስ ማበረታቻ ለእናቶች
ክርስቶስ ልጆችን ባርኳል፦ እጆቹን በላያቸው ጭኖ ይባርካቸው ዘንድ ክርስቶስ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ እናቶች ልጆቻቸውን ወደርሱ ያመጡ ነበር። በዚህ ድርጊታቸው በክርስቶስ ያላቸውን እምነት እንዲሁም በጊዜውና ለወደፊቱ በአደራ የተሰጣቸው የልጆቻቸው ደህንነት ላይ የነበራቸውን ከባድ ጭንቀት ይገልጹ ነበር። ነገር ግን ልጆችን ያስተውል ዘንድ ጌታ ከተግባሩ እንዳይቋረጥ በማሰብ ደቀመዛሙርቱ እናቶችን ይመልሷቸው ጀመር፤ ክርስቶስም ደቀ-መዛሙርቱን ገስጾ ልጅ ለያዙ አማኝ እናቶች መንገድ እንዲከፍቱ ሕዝቡን ተናገራቸው። እንዲህ አለ:- “ሕፃናትን ተው አትከልክሏቸው ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ። መንግሥተ-ሰማያት እንደለዚህ ላሉት ናትና።” AHAmh 193.1
እናቶች አቧራ በሞላው መንገድ ሲራመዱና ወደ አዳኙ ሲቀርቡ፤ በዝምታ ለልጆቻቸው ሲጸልዩ፤ ሊቆጣጠሩት ያልቻሉት እንባቸው ሲፈስና ከንፈራቸው ሲንቀጠቀጥ ተመለከተ። የደቀ-መዛሙርቱን የተግሳጽ ቃላት ሲሰማ የእነርሱን ትዕዛዝ ውድቅ አድርጎ በተቃራኒው ተካው። ታላቁ የፍቅር ልቡ ልጆችን ለመቀበል ክፍት ነበረ። አንድ ሕፃን ደረቱን ተደግፎ በእንቅልፍ ጭልጥ ብሎ ሳለ ሌሎቹን አንድ በአንድ እያቀፈ ባረካቸው፤ ክርስቶስ በሥራቸው ዙሪያ ለእናቶች ብርታት የሚሰጥ ንግግር አደረገ፤ ኦ እንዴት ያለ ዕረፍት ወደ አዕምሮአቸው መጣ! ያንን የማይረሳ ጊዜ መለስ ብለው ሲያስታውሱት በክርስቶስ መልካምነትና ምህረት ምን ያህል በደስታ ይሞሉ ይሆን! ደርባባ ንግግሩ የልባቸውን ሸክም አራገፈላቸው፤ በአዲስ ተስፋና ብርታት አጠነከራቸው። የድካም መንፈስ ድራሹ ጠፋ። AHAmh 193.2
ይህ የእናቶች የሁልጊዜ የማበረታቻ ትምህርት ነው። ማድረግ የሚችሉትን መልካም ነገር ሁሉ ለልጆቻቸው ካደረጉ በኋላ ወደ የሱስ ያምጧቸው። በእናቶቻቸው እቅፍ ያሉት ትንንሽ ጨቅላዎች እንኳ በዓይኑ ፊት የከበሩ ናቸው። መስጠት እንደማትችል የምታውቀውን እርዳታ የእናት ልብ ሲናፍቅ፤ መለገስ የማትችለውን ፀጋ ስትሻ፤ እራስዋንና ልጆችዋን በመሐሪው የክርስቶስ ክንድ ትጣል፤ በደስታ ተቀብሎ ይባርካቸዋል። ለእናትና ለልጆችዋ ሠላም ተስፋና ደስታ ይሰጣቸዋል። ይህ ተስፋ የሱስ ለሁሉም እናቶች የሰጠው ወርቃማ እድል ነው። 1 AHAmh 193.3
ክርስቶስ አሁንም እናቶችን ይጋብዛል፦ የሰማይ ግርማ የሆነው ክርስቶስ “ሕፃናትን ተው አትከልክሏቸው ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ። መንግሥተ-ሰማያት እንደለዚህ ላሉት ናትና” አለ። የሱስ ልጆቹን ወደ መምህራን(ራባይ) አይሰዳቸውም፤ ወደ ፈሪሳዊያን አይልካቸውም፤ እነዚህ ሰዎች ወደር የሌለውን ጓደኛቸውን እንዲተዉ እንደሚያስተምሯቸው ያውቃልና። ልጆቻቸውን ወደ የሱስ ያመጡ እናቶች መልካም አደረጉ…. አሁንም እናቶች ልጆቻቸውን ወደ የሱስ ይምሯቸው። የወንጌል አገልጋዮች በእቅፋቸው ይዘው በየሱስ ስም ይባርኳቸው፤ ፍጹም ፍቅር በተሞላበት ንግግር ያነጋግሯቸው። ክርስቶስ የመንጋውን ጠቦቶች አቅፎ ባርኳቸዋል። 2 AHAmh 193.4
እናቶች ከነግራ-መጋባቶቻቸው ወደ የሱስ ይምጡ። ልጆቻቸውን ለማስተዳደር የሚያስችላቸው በቂ ፀጋ ያገኛሉ። ሸክምዋን በአዳኙ እግር ሥር ማራገፍ ለምትፈልግ ለእያንዳንዷ እናት በሩ ክፍት ነው…. ጌታ አሁንም ይባርካቸው ዘንድ፣ ታናናሾችን ወደርሱ ይመሯቸው ዘንድ እናቶችን ይጋብዛቸዋል። በእቅፍ ውስጥ ያለ ጨቅላ እንኳን በአማኝዋና በፀሎት በምትተጋው እናቱ ምክንያት በኃይሉ ጥላ ሥር ይኖራል። መጥምቁ ዮሐንስ ከተወለደ አንሥቶ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር በሕብረት ከኖርን እኛም መለኮታዊ መንፈስ ከመጀመሪያዋ ደቂቃ ጀምሮ ለልጆቻችን ቅርጽ ሲያበጅላቸው ልናይ እንችላለን። 3 AHAmh 194.1
የታዳጊዎች ልብ በቀላሉ የሚማረክ ነው፦ እርሱ [ክርስቶስ] እራሱን ከተዋረዱ፣ ከድሆችና ከተጠቁ ጋር አመሳሰለ። ሕፃናትን በእቅፉ ይዞ ወደ እነርሱ ደረጃ ዝቅ አለ። ሰፊ የፍቅር ልቡ የሚያስፈልጋቸው እንዲሁም ፈተናቸው የሚገባው ነበርና ደስ ሲላቸው ሲያይ ሀሴት አደረገ። በተጨናነቀው ከተማ ግርግርና ሽርጉድ መንፈሱ ዝሎ፤ ከተንኮለኞችና ከግብዞች ሕብረት የተነሣ ደክሞ ሳለ ከንፁህ ልጆች ጋር ከነበረው የአብሮነት ጊዜ ዕረፍትና ሠላም አገኘ። መገኘቱ ፈጽሞ አላራቃቸውም። የሰማይ ልዑል ራሱን ዝቅ አድርጎ ጥያቄአቸውን መመለስ ጀመረ፤ የሕፃንነት መረዳታቸውን እንዲስማማ አድርጎ አስፈላጊውን ትምህርቱን ቀለል አድርጎ አቀረበላቸው። በለጋና በሚፋፋው አዕምሮአቸው አድጎና አፍርቶ በጎልማሳነታቸው ዓመታት የተትረፈረፈ ምርት የሚያስገኝ የእውነት ዘር ዘራ። 4 AHAmh 194.2
እነዚህ ልጆች ምክሩን እንደሚያደምጡትና አዳኛቸው አድርገው እንደሚቀበሉት ያውቅ ነበር። በአንፃሩ በዓለም ጥበብ የበለጸጉ፣ ልባቸው የደነደነ፣ በዕድሜ የበሰሉ ሰዎች ሊያደምጡትና በአባቱ መንግሥት ቦታ ሊያገኙ የመቻላቸው ዕድል የጠበበ ነበር። እነዚህ ሕፃናት ወደ የሱስ መጥተው ምክሩንና ቡራኬውን ተቀበሉ። ፈጽሞ ሊፋቅ በማይችል ሁኔታ መልኩና የርኅራኄ ንግግሩ ቅርፅ ለማስያዝ ቀላል በሆነው አዕምሮአቸው ታተመ። ከዚህ ከክርስቶስ አድራጎት የምንማረው ነገር አለ፤ የክርስትናን ትምህርት ለመቀበል የታዳጊዎች ልብ የተዘጋጀ ነው፤ ወደ ደግነትና ቅድስና እንዲያዘነብሉ ለማድረግ ቀላል የሆኑ፤ የተቀበሉትን ጠብቆ የማቆየት ጥንካሬ ያላቸው ናቸው። 5 AHAmh 194.3
“ሕፃናትን ተው አትከልክሏቸው ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ። መንግሥተ-ሰማያት እንደለዚህ ላሉት ናትና።” እነዚህ ወርቃማ ቃላት በእናት ብቻ ሳይሆን በአባትም ጭምር ከፍተኛ ዋጋ ሊሰጣቸው ይገባል። እነዚህ ቃላት ልጆቻቸውን ልብ ይላቸው ዘንድ ወደ እርሱ እንዲያስጠጓቸው፤ በሁሉም የቤተሰባቸው አባላት ላይ የአባቱ በረከት እንዲያርፍ በክርስቶስ ስም ይለምኑ ዘንድ ብርታት ይሆናቸዋል። ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የተወደደና የማይጠገብ ዓይነት ባህርይ ያላቸው ልጆች ብቻ አይደለም፤ እንዲያውም ጥንቁቅ ሥልጠናና መልካም ምሪት የሚያሻቸው የሚቁነጠነጡና አስቸጋሪ ልጆች ናቸው። 6 AHAmh 195.1