የአድቬንቲስት ቤት

46/88

ምዕራፍ አርባ አምስት—የእናት ተቀዳሚ ተግባር ልጆችዋን ማሠልጠን ነው

በሥርዓት የሠለጠነ ልጅ መሆን የሚችላቸው ነገሮች፦ እርባና-ቢስ የመሰለው ሰብአዊ ዘር፣ ሁሉን ነገር ማድረግ የሚቻለው እንደሆነ እግዚአብሔር ያውቃል። ሰው በጥሩ ሥልጠና ለመልካም ነገር መሣሪያ መሆን እንደሚችልም ጌታ ያያል። አግባብነት በሌለው ቸርነት እግዚአብሔር ለሕጻኑ ያለውን እቅድ በመሰረዝ፣ ባደራ የሰጣቸውን ልጅ ከአሁኑና ከዘለዓለማዊው ፋንታው ያጠፉት ወይስ ዓላማውን ያሳኩት እንደሆነ አምላክ ወላጆችን በጭንቀትና በጥልቅ ፍላጎት ይመለከታቸዋል። ይህንን ራሱን መርዳት የማይችል ፍጡር ለዓለም በረከት ለእግዚአብሔር ክብር ወደሚይሆንበት ደረጃ ማሳደግ ታላቅና ከባድ ሥራ ነው። ወላጆች በእነርሱና ለልጆቻቸው ባለባቸው ግዴታ መካከል ምንም ዓይነት ነገር ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ የለባቸውም። 1 AHAmh 185.1

ለእግዚአብሔርና ለሀገር ሥራ፦ በፊታቸው ባለው ታላቅ ፍልሚያ ምን ዓይነት ሚና ይጫወቱ ይሆን በማለት የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚጠብቁ ወላጆች ሊገለጽ በማይችል ተስፋና ፍርሃት ልጆቻቸውን ይመለከቷቸዋል። ተጨናቂዋ እናት ትጠይቃለች “ምን ዓይነት አቋም ይወስዱ ይሆን? ዘለዓለማዊ ክብር ይቀበሉ ዘንድ ድርሻቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እንዴት ላዘጋጃቸው እችላለሁ?” እናቶች ሆይ በእናንተ ላይ ከባድ ኃላፊነት ተጥሏል፤ የብሔራዊ ምክር-ቤት አባል ባትሆኑም….ለእግዚአብሔርና ለሀገራችሁ ታላቅ ሥራ ልትሠሩ ትችላላችሁ። ልጆቻችሁን ልታስተምሩ ትችላላችሁ፤ ክፋት እንዲሠሩ የሚወዘውዛቸውን ወይም ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸውን ሳይሆን ሌሎች መልካም እንዲያደርጉ የሚጎተጉትና ተጽዕኖ የሚያደርግ ባህርይ እንዲያጎለብቱ ልታደርጓቸው ትችላላችሁ። በእምነት በምትፀልዩት ልባዊ ፀሎት ዓለምን የሚያሽከረክር ክንድ ታጎለብታላችሁ። 2 AHAmh 185.2

መመሪያዎች መሰጠት ያለባቸው ገና በልጅነትና በወጣትነት ዕድሜ ነው። ልጆች ጠቃሚ እንዲሆኑ ሊሠለጥኑ ይገባል። በቤት ውስጥ ሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንዲሠሩ መሠልጠን አለባቸው። የርኅራኄ ቃላትና አድናቆት በተላበሱ ትዕዛዛት ወላጆች በተቻላቸው መጠን እነዚህ ሥራዎች አስደሳች ይሆኑ ዘንድ ይጣሩ። 3 AHAmh 185.3

የቤት ውስጥ ሥልጠና በብዙዎች ችላ የሚባል ነው፦ በትምህርት አሰጣጥ ዘዴዎች የሚያኮሩ እመርታዎች ታይተዋል ቢባልም እንኳ፣ የልጆች ሥልጠና ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አሁንም ድረስ እንከን ያለበት ነው። የተረሳው ደግሞ የቤት ውስጥ ሥልጠናው ነው። ወላጆች በተለይም ደግሞ እናቶች ኃላፊነታቸውን አያውቁም። እንዲጠብቋቸው በአደራ የተሰጧቸውን ትንንሽ ፍጡራን ሊቆጣጠሩአቸውና በጥበብ ሊያሠለጥኑአቸው ትዕግሥት የላቸውም። 4 AHAmh 185.4

እናቶች ለእናትነታቸው ታማኝ ሆነው በሥራ ገበታቸው አይገኙም የሚለው አባባል በጣም ትክክል ነው። በእርሱ ብርታት ታግዘን ልንሠራው የማንችለውን፣ ለራሳችንም ሆነ ለልጆቻችን መልካም ያልሆነን ምንም ነገር እግዚአብሔር እንድንሠራ አይጠብቅብንም። 5 AHAmh 186.1

እናቶች መለኮታዊ እርዳታ ይጠይቁ፦ እናቶች የተልዕኮአቸውን አስፈላጊነት በሚገባ ቢያስተውሉት ኖሮ፣ እንዲባርካቸው በተማጽኖ ልጆቻቸውን ወደ ጌታ በማቅረብ፤ የተቀደሰውን ኃላፊነታቸውን በትክክል መተግበር ይችሉ ዘንድ ጥበብ እንዲሰጣቸው በምሥጢራዊ ፀሎት በተጠመዱ ነበር። እናት ጠባያቸውንናልማዳቸውን ለመቅረጽና ለማበጀት ያገኘችውን እድል ሁሉ ትጠቀምበት። ከሚገባው በላይ የገዘፉትን ባህርያት ጨቆን፤ የጫጩትን ደግሞ እንዲጎለብቱ ደገፍ በማድረግ የተመጣጠነ የባህርይ አድገት እንዲኖራቸው በአፅንኦት ትከታተል። ለዚህ ወርቃማ ኃላፊነት እራስዋን ንጹህና የከበረ ተምሣሌት አድርጋ ታቅርብ። 6 AHAmh 186.2

እናት በጥረቶችዋ ሁሉ በመለኮታዊ እርዳታ ሁልጊዜ በመደገፍ በወኔና በብርታት ሥራዋን ትሥራ። ቀስ በቀስ የባህርያቸውን ከፍ ከፍ ማለት፤ የራሳቸውን ደስታ ከማሳደድ በዘለለ ለሕይወታቸው ታላቅ ዓላማ አንግበው እስክታያቸው ድረስ እናት በቃኝ ብላ ማረፍ የለባትም። የምትፀልይን እናት የተጽዕኖ ኃይል መገመት ፈጽሞ የሚቻል አይደለም። ይባርካቸው ዘንድ እየለመነች ልጆችዋን በፀጋው ዙፋን ፊት ለክርስቶስ ታቀርባቸዋለች። የፀሎትዋ ተጽዕኖ ለእነዚህ ልጆች እንደ “ሕይወት ምንጭ” ነው። በእምነት የተፀለዩት እነዚህ ፀሎቶች የክርስቲያን እናት ኃይልና ምርኩዝ ናቸው። ከልጆቻችን ጋር የመፀለይን ተግባር ችላ አልን ማለት ልናገኛቸው ከምንችላቸው ታላላቅ በረከቶች እና በሕይወት በምናልፍባቸው ግራ መጋባቶች ችግሮችና ሸክሞች ሊያግዙን ከሚችሉ ከታላላቅ እርዳታዎች አንዱን አጣን ማለት ነው። 7 AHAmh 186.3

የእናት የፀሎት ኃይል ምንም ያህል ቢበረታ ከሚገባው በላይ ተጋነነ ሊባል አይችልም። በሕፃንነት ውጣውረዶች እንዲሁም በወጣትነት አደጋዎች ውስጥ ከሴቶችና ወንዶች ልጆችዋ ጎን የምትንበረከክ እናት ፀሎትዋ በልጆችዋ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምን ያህል እንደሆነ ከፍርድ ቀን በፊት እርስዋም ራስዋ እንኳ ፈጽማ በውል አታውቀውም። እናት ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር በእምነት ከተቆራኘች፣ የእናትነት እጇ ወንድ ልጅዋን ከሚፈትን ነገር እንዲያፈገፍግ፤ ሴት ልጅዋ በኃጢአት ውስጥ ሐሴት እንዳታደርግና እንድትቆጠብ ሊያደርግ ይችላል። የሥጋ ስሜት ሊሠለጥንና የበላይ ደረጃ ለመያዝ በሚዋጋበት ጊዜ፣ የፍቅር ኃይል የሚደግፈው ልባዊና ቆራጥ የሆነው የእናት ተጽዕኖ የነፍስ ሚዛን ወደ መልካሙ እንዲያጋድል ያደርገዋል። 8 AHAmh 186.4

ጎብኝዎች ጣልቃ በሚገቡበት ጊዜ፦ ከእነዚህ ሕፃናቶቻችሁ ጋር ለመጫወትና ለመፀለይ ጊዜ ውሰዱ፤ ከልጆቻችሁና ከእግዚአብሔር ያላችሁን የአንድነት ጊዜ የሚያቋርጥ ምንም ነገር እንዲኖር አትፍቀዱ። ለእንግዶቻችሁ “እግዚአብሔር እንድሠራ የሰጠኝ ሥራ አለ፤ ለሀሜት ጊዜ የለኝም” በሏቸው። ለዘመንና ለዘለዓለም የሚሆን የምትሠሩት ሥራ እንዳለባችሁ ይሰማችሁ። ተቀዳሚው ግዴታችሁ ለልጆቻችሁ ነው። 9 AHAmh 187.1

ከእንግዶች በፊት፤ ስለ ሌላ ምንም ነገር ከማሰባችሁ አስቀድሞ ልጆቻችሁ መጀመሪያ ይምጡ…. በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ለልጆቻችሁ ያለባችሁ የሥራ ኃላፊነት ግድየለሽነትን በፀጋ የሚቀበል አይደለም። በሕይወቱ/ትዋ መርህ ሊዘነጋበት የሚችልበት አንድም ደቂቃ የለም። 10 AHAmh 187.2

እንግዶቻችሁን በነፃነት ለማጫወት ብላችሁ ልጆቻችሁን ከቤት አስወጥታችሁ አትስደዷቸው፤ ነገር ግን እንግዶች በሚኖሩበት ጊዜ በአክብሮትና በፀጥታ እራሳቸውን እንዲቆጣጠሩ አስተምሯቸው። 11 AHAmh 187.3

እናቶች የመልካምነትና የጨዋነት ምሣሌ ይሁኑ፦ እናቶች ሆይ ወርቃማ ጊዜያችሁን ልብ በሉ። ልጆቻችሁ ከእናንተ ትምህርትና ሥልጠና ውጪ ወደሚሆኑበት ጊዜ እየገሰገሱ ነው። መልካም ንጹህና የላቀ ለሆነው ነገር ሁሉ ምሣሌ ልትሆኑላቸው ትችላላችሁ። ፍላጎታችሁን ከልጆቻችሁ ጋር አመሳስሉት። 12 AHAmh 187.4

በሌላው ነገር ሁሉ ባይሳካላችሁ እንኳ በዚህ ጉዳይ የተጠናቀቃችሁ፣ ብቁና እንከንየለሽ ሁኑ። ልጆች በቤት ስልጠናቸው ንጹህና መልካም ባህርይ ያላቸው ሆነው ከወጡ፤ እግዚአብሔር ለዓለም ባለው መልካምና ታላቅ እቅድ ውስጥ [በሰው ማስተዋል] ዝቅተኛና የተዋረዱ ናቸው የተባሉትን ቦታዎች እንኳ የሚሽፍኑ ከሆነ፤ ሕይወታችሁ በውድቀት ሊጠራና በቁጭት ሊታወስ የሚችልበት አጋጣሚ አይኖርም። 13 AHAmh 187.5

ሕጻናት የራስዋ ልማዶችና ባህርያት ተንጸባርቀው የምታይበት የእናት መስታወቶች ናቸው። ታዲያ ለቋንቋዋና ለፀባይዋ በእነዚህ ትናንሽ ተማሪዎች ፊት እንዴት ልትጠነቀቅ ይገባት ይሆን! በልጆችዋ ተስፋፍተው ልታያቸው የምትፈልጋቸውን ባህርያት መጀመሪያ እራስዋ ውስጥ ማሳደግ አለባት። 14 AHAmh 188.1

ዓለም ከሚያስቀምጠው ደረጃ የላቀ ግብ ይኑራችሁ፦ እናት ዓለም በሚሰነዝረው ሐሳብ ወይም በሚያስቀምጠው ደረጃ መተዳደር አይገባትም። ታላቁ ዓላማና የሕይወት ዕቅድ ምን እንደሆነ ወስና፣ ያንን ዓላማም ጥግ ለማድረስ ያላትን ኃይል ሁሉ ማፍሰስ ይኖርባታል። ከጊዜ እጦት የተነሣ በቤትዋ ውስጥ ሳይከናወኑ የምትተዋቸው ግን ብዙም መጥፎ ሁኔታዎችን የማያስከትሉ ነገሮች ይኖራሉ፤ የልጆችዋን የመልካም ሥነ-ሥርዓት ሥልጠና ቸል ብትል ግን ሳትቀጣ አትቀርም። ጎደሎ ያለበት ባህርያቸው እምነት-የለሽነትዋን ገሐድ ያወጣዋል። ሳይስተካከሉ የታለፉት ክፋቶች፤ እነዚያ ሸካራና ጎርባጣ ባህርያት፤ ማዋረዱና አመጸኛ መሆኑ፤ የሥንፍናና የትኩረት-የለሽነት ልማዶች ሁሉ ራስዋን ውርደት በማከናነብ ሕይወትዋን መራራ ያደርጉታል። እናቶች ሆይ የልጆቻችሁ ዕጣ ፈንታ በእጃችሁ ውስጥ ነው። በዚህ ሥራችሁ ከወደቃችሁ ልጆቻችሁ ነፍሳትን ለጥፋት የሚያጠምዱ የሰይጣን ሹማምንት ይሆኑ ዘንድ ታስቀምጧቸዋላችሁ። ወይም በተቃራኒው ታማኝ ሥርዓታችሁና እግዚአብሔራዊ ምሣሌነታችሁ ወደ ክርስቶስ ይመራቸዋል። እነርሱም የመልካም ተጽዕኖ ይሆኑ ዘንድ ሌሎችን በመለወጥ በእናንተ መሣሪያነት ብዙ ነፍሳት ወደ ደህንነት ይመጣሉ። 15 AHAmh 188.2

መልካሙን አጎልብቱ ክፉውን ግቱ፦ በእርሱ ፍርሃትና ፍቅር ሥር ልጆቻቸውን ያሳድጉ ዘንድ ወላጆች ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት እንዲሠሩ ይጠበቅባቸዋል። ልጆቻቸውን በትክክለኛው መንገድ ከማሠልጠን ፈቀቅ ከማለታቸው የበለጠ፣ አምላክን ሊያሳዝኑት የሚችሉበት ሌላ ነገር የለም። ጠላት በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ምንም እድል እንዳያገኝ የልጆቻቸውን ንግግርና እንቅስቃሴ በጥንቃቄ እንዲከታተሉ ያስፈልጋል። ዲያብሎስ የእግዚአብሔርን ዓላማ የሚፃረርና የሚያዳክም ሥራ ለመሥራት በጋለ ስሜትና ጥልቅ ፍላጎት ለመተግበር ይሻል። ወላጆች በታናናሽ ፍጡሮቻቸው ከሚታዩት ባህርያት መካከል መልካሙን እያበረታቱ መጥፎውን ሁሉ ደግሞ እየቀጩ በቸርነት በሙሉ ፍላጎትና በትህትና ለልጆቻቸው ይሥሩ። 16 AHAmh 188.3

በጥሞና የተሠራ ሥራ የሚያፈልቀው ደስታ፦ ልጆች የእግዚአብሔር ቅርሶች ናቸው፤ በአደራ የተሰጠንን ንብረቱን እንዴት እንዳስተዳደርንለት አንድ ቀን መልስ የምንሰጥበት ጉዳይ ይሆናል። ልጆች ክርስቲያን እንዲሆኑ ማስተማርና ማሠልጠን፣ ወላጆች ለእግዚአብሔር ሊሰጡት ከሚችሉት አገልግሎት ሁሉ እጅግ የላቀና ተወዳዳሪ የሌለው ተግባር ነው። ትዕግሥት የሚጠይቅ ሥራ ነው - የዕድሜ ልክ ፈታኝና ጽኑ ትግል። ለዚህ አደራ ግድ-የለሽ በመሆን እምነት-አልባ መጋቢዎች መሆናችንን እራሳችን እናረጋግጠዋለን…. በደስታ ወደ እግዚአብሔር ቀርበው “እነሆኝ እኔ እግዚአብሔርም የሰጠኝ ልጆች” ማለት እስኪችሉ ድረስ ወላጆች በፍቅር፣ በእምነትና በፀሎት ለቤተሰቦቻቸው ይሥሩ። 17 AHAmh 188.4