አእምሮ፣ባሕርይና ማንነት፣ክፍል 1
ምዕራፍ 26—የወንድማማች ፍቅር
ለሌሎች ያለን ፍቅር ደስታን ያመጣል።--በሁሉም ቦታ ላሉት ወንድሞች እንዲህ እላለሁ፡- የክርስቶስን ፍቅር አሳድጉ! ከክርስቲያን ነፍስ በምድረ በዳ እየፈሰሰ እንደሚያድስና እንደሚያሳምር፣ በራሱና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ደስታን፣ ሰላምንና ፍስሀን እንደሚያመጣ ምንጭ መፍለቅ አለበት። --5T 565 (1889). {1MCP 240.1} 1MCPAmh 198.1
ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር የሚያሳየው ምሳሌ መቋቋም የማይቻል ነው።--በባህርያችን አብልጠን አዳኛችንን ስንመስል እርሱ ለሞተላቸው ሰዎች ያለን ፍቅርም ትልቅ ይሆናል። ለእርስ በርሳቸው ራስ ወዳድነት የሌለበትን የፍቅር መንፈስ የሚያሳዩ ክርስቲያኖች የማያምኑ ሰዎች ሊቃወሙት ወይም ሊቋቋሙት የማይችሉትን ምስክርነት ለክርስቶስ እየሰጡ ናቸው። የዚህን ዓይነት ምሳሌነት ኃይል መገመት አይቻልም። በቤተ ክርስቲያን አባላት ውስጥ እንደ ተገለጠ የክርስቶስ ፍቅር የሰይጣንንና የመልእክተኞቹን መሳሪያዎች በተሳካ ሁኔታ ሊያሸንፍ የሚችልና የአዳኙን መንግስት መገንባት የሚችል ምንም ነገር የለም።--5T 167, 168 (1882). {1MCP 240.2} 1MCPAmh 198.2
ራስ ፍቅርን ሊደብቅ ይችላል።--ፍቅር እንቅስቃሴ የሚያሳይ መርህ ነው፤ ነፍሳትን ወደ ክርስቶስ የማምጣት ዓላማችን እንዳይጨናገፍ ከቸልተኝነት ተግባሮቻችን እየገታን ሁል ጊዜ የሌሎችን መልካምነት በፊታችን ያስቀምጣል። ፍቅር የራሱን አይሻም። ሰዎች የራሳቸውን ምቾት እንዲፈልጉና ራስን እንዲያሞላቅቁ አያነሳሳም። ብዙ ጊዜ ፍቅር እንዳያድግ የሚከለክለው ለራስ የምንሰጠው አክብሮት ነው። --5T 124 (1882). {1MCP 240.3} 1MCPAmh 198.3
ትህትና/ራስን ዝቅ ማድረግ የፍቅር ተቀጽላ ነው።-- ፍቅር በትዕቢት አይነፋም። ፍቅር ትሁት ነው፤ ሰው እንዲኩራራ፣ ራሱን ከፍ ከፍ እንዲያደርግ በፍጹም አያነሳሳውም። ለእግዚአብሔርና ለጎረቤቶቻችን ያለን ፍቅር በችኮላ ተግባራት አይገለጥም ወይም የሌሎችን ሀሳብ በመናቅ ልናዛቸው የምንፈልግ፣ ስህተት ፈላጊዎች፣ ወይም አምባ ገነኖች ወደ መሆን አይመራንም። ፍቅር አይነፋም። ሰዎች ከእኛ ፍላጎት ጋር ገጣሚ ቢሆኑም ባይሆኑም፣ ቢያከብሩንም ባያከብሩንም፣ ፍቅር የነገሰበት ልብ ከሌሎች ጋር ካለው ግንኙነት አንጻር ጨዋ፣ ገርና ርኅሩኅ የሆነ ባሕርይን ያሳያል።--5T 123, 124 (1882). {1MCP 241.1} 1MCPAmh 198.4
እውነተኛ ፍቅር ራስን የሚደብቅ ነው።--እግዚአብሔር የሚፈልግብን ፍቅር ራሱን የሚገልጠው ክርስቶስ ለሞተላቸው ነፍሳት ባለን ማስመሰል በሌለበት ፍቅር ነው። በልብ ውስጥ ክርስቶስ ማደሩ የሚገለጠው ደቀ መዛሙርቱ እንዲፈጽሙት ትዕዛዝ በሰጣቸው ፍቅር ነው። የእርሱ እውነተኛ ልጆች ሌሎችን ከራሳቸው ያስበልጣሉ። መክሊቶቻቸው ከወንድሞቻቸው መክሊት እንደሚበልጥ አድርገው ስለማይመለከቱ በማንኛውም ጊዜ ወይም ቦታ ለራሳቸው የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ አይፈልጉም። በርግጥ ይህ ሲሆን ክርስቶስ ለሰዎች ነፍሳት ያሳየውን ፍቅር በመግለጥ ሂደት ምልክት ይሰጣል፤ ክርስቶስ ለነፍሳት ያሳየው ፍቅር ራስ ወዳድነት የሌለው፣ የማያስመስል፣ ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ደህንነት የሚያስቀድም ፍቅር ነበር። --MS 121, 1899. {1MCP 241.2} 1MCPAmh 199.1
ፍቅር ባህርይን ይለውጣል።--እውነትን ለማያውቁ ሰዎች የኢየሱስ ፍቅር ይቅረብላቸው፣ ይህ ሲሆን ባህርይን ለመለወጥ እንደ እርሾ ይሰራል። -- 8T 60 (1904). {1MCP 241.3} 1MCPAmh 199.2
ራስ ወዳድ የሆነ ፍቅር።--እግዚአብሔር ልጆቹ እንዲገነዘቡለት የሚፈልገው ነገር ቢኖር እርሱን ለማክበር ፍቅራቸውን እጅግ ለሚፈልጉ ሰዎች እንዲሰጡ ነው…። ከእነዚያ ጋር በሚሰራበት ጊዜ ከፍተኛ ቢሆኑ ወይም ዝቅተኛ፣ ሀብታም ቢሆኑ ወይም ድሃ፣ በእይታ፣ በቃል ወይም በተግባር ምንም ዓይነት ራስ ወዳድነት መገለጥ የለበትም። ለሌሎች ቅዝቃዜንና ግድ የለሽነትን እያሳየ ለጥቂት ሰዎች ብቻ የደግነትን ቃላት የሚናገር ፍቅር፣ ፍቅር ሳይሆን ራስ ወዳድነት ነው። ይህ በምንም መንገድ ለነፍሳት ደህንነትም ሆነ ለእግዚአብሔር ክብር አይሰራም። ፍቅራችን ሌሎችን ችላ በማለት ልዩ ለሆኑት ብቻ ታሽጎ የሚቀመጥ መሆን የለበትም። ብልቃጡን ስበሩት፣ ቤቱ በመልካም ሽታ ይሞላል። --MS 17, 1899. (HC 231.) {1MCP 241.4} 1MCPAmh 199.3
ችሎታ ፍቅርን አይተካም።--ንግግር፣ ፈሪሳዊነት፣ እና ራስን ማመስገን በብዛት አለ፣ ነገር ግን እነዚህ በፍጹም ነፍስን ለክርስቶስ አይማርኩም። በክርስቶስ የሕይወት ሥራ የተገለጠው ዓይነት ንጹህና የተቀደሰ ፍቅር እንደ ቅዱስ ሽቶ ነው። ማርያም እንደሰበረችው የሽቶ ብልቃጥ ቤቱን በሙሉ በመልካም መዓዛ ይሞላዋል። አንደበተ ርቱእነት፣ እውነትን ማወቅ፣ በብዙዎች ዘንድ የማይታዩ ልዩ መክሊቶች፣ ከፍቅር ጋር ከተቀላቀሉ ሁሉም ውድ ተስጦኦዎች ናቸው። ነገር ግን ችሎታ ብቻውን፣ ምርጥ መክሊቶች ብቻቸውን፣ የፍቅርን ቦታ መውሰድ አይችሉም። --6T 84 (1900). {1MCP 242.1} 1MCPAmh 199.4
ልግስና የፍቅር ማረጋገጫ።--የፍቅራችን ማረጋገጫ የሚሰጠው ክርስቶስን በሚመስል መንፈስ፣ እግዚአብሔር የሰጠንን መልካም ነገሮች ለሌሎች ለማጋራት ፈቃደኛ በመሆን፣ የእግዚአብሔር ሥራ ወደ ፊት እንዲቀጥልና የሰብአዊ ዘር ስቃይ እንዲያበቃ ራስን መካድንና መስዋዕት ማድረግን ለመለማመድ ዝግጁ በመሆን ነው። የእኛን ልግስና የሚጠይቀውን ሰው እያየን በፍጹም ማለፍ የለብንም። የእግዚአብሔር ጸጋ ታማኝ መጋቢዎች ሆነን ስንሰራ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናሳያለን። እግዚአብሔር ንብረት ሰጥቶናል፤ በመጋቢነታችን ታማኞች ከሆንን በሰማይ የማይጠፋ ሀብት እንደምንሰበስብ መሃላ ያለበትን ቃል ሰጥቶናል። --RH, May 15, 1900. {1MCP 242.2} 1MCPAmh 200.1
ትክክለኛ የሆነ ፍቅር መስጠት የደቀ መዝሙርነት ምልክት።--የሙያ ብቃቱ ምንም ያህል ከፍ ያለ ቢሆን ልቡ ለእግዚአብሔርና ለመሰሎቹ ባለ ፍቅር ያልተሞላ ሰው እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር አይደለም። ትልቅ እምነት ቢኖረውና ተአምራቶችን ለመስራት ኃይል ቢኖረውም ያለ ፍቅር እምነቱ ከንቱ ነው። በጣም ለጋስ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ለልግስና ያነሳሳው እውነተኛ ፍቅር ሳይሆን የሆነ ምክንያት ከሆነ፣ ሀብቱን በሙሉ ድሆችን ለመመገብ ቢሰጥ፣ ድርጊቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አያስገኝለትም። ባለው ቅናት የሰማዕትነትን ሞት እንኳን ሊሞት ይችል ይሆናል፣ ሆኖም ይህ ድርጊቱ በፍቅር ካልተነሳሳ እግዚአብሔር የሚመለከተው ጽኑ ግለት እንዳለው የተታለለ ሰው ወይም አንድን ነገር ለማድረግ ጉጉት እንዳለው ግብዝ አድርጎ ነው።--AA 318, 319 (1911). {1MCP 242.3} 1MCPAmh 200.2
ፍቅር የሚገዛው ልብ።--ፍቅር የሚገዛው ልብ በስሜት ወይም በበቀል፣ ኩራትና የራስ ፍቅር ሊታገሱት የማይቻል ባደረጉት ቁስለቶች አይሞላም። ፍቅር ሌሎች ሰዎች አንድን ነገር ለማድረግ ስላነሳሳቸው ነገርና ስለ ተግባራቸው እጅግ ጥሩ የሆነ ትርጉም ስለሚሰጥ አይጠራጠርም።--5T 168, 169 (1882). {1MCP 243.1} 1MCPAmh 200.3
የሰይጣን ሰራዊት እንቅስቃሴ፣ ሰብአዊ ነፍስን የሚከበው አደጋ፣ የእያንዳንዱ ሰራተኛ ጉልበት ሥራ ላይ እንዲውል ይጠይቃል። ነገር ግን ምንም ዓይነት ግዳጅ ሊደረግ አይችልም። የሰውን ህገ ወጥነት በፍቅር፣ በትዕግስትና እግዚአብሔር በሚሰጠው መቻል መጋፈጥ ያስፈልጋል። --6T 237 (1900). {1MCP 243.2} 1MCPAmh 200.4
ልዩ ባህርያትን ያስተካክላል።--ሰው የመለኮታዊው ባህርይ ተካፋይ ሲሆን የክርስቶስ ፍቅር በነፍስ ውስጥ የሚኖር መርህ ይሆንና ራስና ልዩ ባህርያቱ ሳይታዩ ይቀራሉ። --6T 52 (1900). {1MCP 243.3} 1MCPAmh 201.1
የክርስቶስ ፍቅር ብቻ መፈወስ ይችላል።--ከክርስቶስ ልብ የሚፈልቅ ፍቅር ብቻ መፈወስ ይችላል። በዛፍ ውስጥ እንደሚፈስ ፈሳሽ ወይም በሰውነት ውስጥ እንደሚፈስ ደም ያ በውስጡ የሚፈስ ፍቅር ብቻ የቆሰለችውን ነፍስ መመለስ ይችላል። --Ed 114 (1903). {1MCP 243.4} 1MCPAmh 201.2
ሊሆን ለሚችል ለእያንዳንዱ መጥፎ ውጤት ያዘጋጃል።--እግዚአብሔርን በእውነት የሚወድ እያንዳንዱ ሰው የክርስቶስ መንፈስ እና የጋለ ፍቅር ለወንድሞቹ ሊኖረው ይገባል። የሰው ልብ ከእግዚአብሔር ጋር የበለጠ ግንኙነት ሲኖረው እና ያለው ፍቅር ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ሲሆን፣ በሕይወቱ በሚገጥሙት ውሽንፍሮችና ችግሮች የመረበሽ ሁኔታው እየቀነሰ ይሄዳል። --5T 483, 484 (1889). {1MCP 243.5} 1MCPAmh 201.3
ወንድማማችነት በፍጹም በድርድር አይገኝም።--ኢየሱስንና እርሱ የሞተላቸውን ነፍሳት የሚወዱ ሰዎች ሰላምን የሚፈጥሩ ነገሮችን ይከተላሉ። ነገር ግን አለመስማማትን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት እውነትን አሳልፈው እንዳይሰጡ፣ መከፋፈልን እየተከላከሉ መርህን መስዋዕት እንዳያደርጉ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በመርህ ላይ በመደራደር እውነተኛ የሆነ ወንድማማችነትን በፍጹም ጠብቆ ማቆየት አይቻልም። ክርስቲያኖች ክርስቶስን ወደ መምሰል እየቀረቡ ሲሄዱና በመንፈስና በተግባር ንጹህ ሲሆኑ የእባብ መርዝ ይሰማቸዋል። መንፈሳዊ የሆነ ክርስትና የማይታዘዙ ልጆችን ተቃውሞ ይቀሰቅሳል....። የአመለካከት ልዩነቶችን ሁሉ ለማስቀረት ሲባል በጋራ በመደራደር የተፈጠሩት ሰላምና መጣጣም ዋጋ ቢስ ናቸው። በሰውና ሰው መካከል ባሉ ስሜቶች አንዳንድ ጊዜ ስምምነቶች መፈጠር አለባቸው፤ ነገር ግን መጣጣምን ለመፍጠር ሲባል የመርህ አንዲት ነጥብ እንኳን መስዋዕት መደረግ የለባትም። --RH, Jan 16, 1900. {1MCP 244.1} 1MCPAmh 201.4
መለኮታዊ ፍቅር አድልዎ የሌለበት ነው።--ክርስቶስ ወደዚህች ምድር የመጣው የምህረትና የይቅርታ መልእክት ይዞ ነው። አይሁድና አህዛብ፣ ጥቁርና ነጭ፣ ባሪያና ጨዋ በአንድ የጋራ ወንድማማችነት የተገናኙበትን፣ በእግዚአብሔር ፊት እኩል ሆነው የሚታዩበትን ኃይማኖት መሰረት ጣለ። አዳኙ ለእያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር ገደብ የለሽ ፍቅር አለው። በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የመሻሻል ችሎታ መኖሩን ይመለከታል። ሕይወቱን የሰጠላቸውን በመለኮታዊ ጉልበትና ተስፋ ሰላም ይላቸዋል። 7T 225 (1902). {1MCP 244.2} 1MCPAmh 201.5
ሰብአዊ ወንድማማችነትን በእግዚአብሔር እቅፍ ያስቀምጣል።--ለእርስ በርስ ያለው የተባረከ ፍቅር ቅዱስ ነው። በዚህ ታላቅ ሥራ ውስጥ ለእርስ በርስ ያለ ክርስቲያናዊ ፍቅር--ከዚህ በፊት ታይቶ ከሚታወቀው በላይ እጅግ ከፍ ያለ፣ የማይለዋወጥ፣ ገርነት ያለው፣ ራስ ወዳድ ያልሆነ--ክርስቲያናዊ ገርነትን፣ ለጋስነትንና ትህትናን ጠብቆ ያቆይና እግዚአብሔር ለሰው መብቶች የሰጠውን ክብር በመቀበል ሰብአዊ ወንድማማችነትን በእግዚአብሔር እቅፍ ያስቀምጣል። ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ሲሉ ይህን ክብር ሁል ጊዜ ማሳደግ አለባቸው። --Lt 10, 1897. (5BC 1140, 1141.) {1MCP 244.3} 1MCPAmh 202.1
ለነፍሳት ያለህ ፍቅር ለእግዚአብሔር ላለህ ፍቅር መለኪያ ነው። በክርስቶስ ራስን የመካድና መስዋዕት የማድረግ ሕይወት የተገለጸው ፍቅር በተከታዮቹ ሕይወት መታየት አለበት። ‹‹እርሱ እንደተመላለሰ እንድንመላለስ›› ተጠርተናል።…በላያችን ባለው የሰማይ ብርሐን መቆም ለእኛ ልዩ ዕድል ነው። ሔኖክ ከእግዚአብሔር ጋር አካሄዱን ያደረገው በእንደዚህ መልኩ ነበር። ለሄኖክ የጽድቅ ሕይወት መኖር በአሁኑ ጊዜ ላለን ለእኛ ከሆነው የበለጠ ቀላል አልነበረም። በእርሱ ጊዜ የነበረው ዓለም በጸጋና በቅድስና ለማደግ ከአሁኑ ጊዜ የበለጠ ምቹ አልነበረም።…በመጨረሻዎቹ ቀናት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ስለምንኖር ብርታታችንን ከዚያው ምንጭ መቀበል አለብን። ከእግዚአብሔር ጋር መራመድ አለብን።. . . {1MCP 245.1} 1MCPAmh 202.2
ብርታታችሁን በሙሉ በሥራው ላይ እንድታደርጉ እግዚአብሔር ይጠራችኋል። በትክክለኛ ቦታ ቁማችሁ ቢሆን ኖሮ ልታደርጉ ትችሉት ለነበረው መልካም ነገር መልስ ትሰጣላችሁ። ከክርስቶስና ከሰማይ መላእክት ጋር አብራችሁ ሰራተኞች ለመሆን ጊዜው አሁን ነው። ልትነቁ ፈቃደኛ ናችሁን? የእናንተን እርዳታ የሚፈልጉ ነፍሳት በመካከላችሁ ናቸው። እነርሱን ወደ መስቀሉ የማምጣት ሸክም ተሰምቶአችሁ ያውቃልን? ለእግዚአብሔር ያላችሁ የፍቅር ደረጃ ለወንድሞቻችሁ፣ ለጠፉትና ላልተሳከላቸው፣ ከክርስቶስ ውጭ ላሉ ያላችሁን የፍቅር ደረጃ እንደሚያሳይ ልብ በሉ። -- RH, Jan 9, 1900. {1MCP 245.2} 1MCPAmh 202.3
የክርስቶስ ዓላማ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፍጹም ፍቅር እንዲኖር ነው።--ኢየሱስ እጅግ ጨለማ በሆኑ የሳይንስ ምስጢሮች ላይ ብሩህ የሆኑ የብርሃን ጮራዎችን ማብራት ይችል ነበር፣ ነገር ግን የድነት ሳይንስን እውቀት ከማስተማር ሥራው አንዲት ደቂቃ እንኳን አባክኖ አያውቅም ነበር። ጊዜው፣ እውቀቱ፣ የአካል ኃይሎቹ፣ እና ራሱ ሕይወቱ የተደነቁት የሰዎችን ሕይወት ለማዳን የሚሰራበት መንገድ በመሆናቸው ብቻ ነበር። ኦ፣ እንዴት ያለ ፍቅር፣ እንዴት ያለ ተወዳዳሪ የሌለው ፍቅር ነው! {1MCP 245.3} 1MCPAmh 202.4
የእኛን ደካማ፣ ሕይወት የለሽ፣ በከፊል ሽባ የሆኑ ጥረቶችን ከጌታ ኢየሱስ ሥራ ጋር አነጻጽሩአቸው። ቃላቶቹን፣ ‹‹እኔንም የወደድህበት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፣ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ›› (ዮ. 16፡ 26) በማለት ወደ አባቱ የጸለየውን ጸሎት አስቡ። እንዴት ያለ ቋንቋ ነው! እንዴት ጥልቅ፣ እንዴት ሰፊ፣ እንዴት ሙሉ ነው! ኢየሱስ የአካሉ ክፍል በሆነው በእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል አማካይነት ፍቅሩን ለሌሎች ለማድረስ ይሻል፣ ይህን ማድረግ የሚፈልገው የዚያ ፍቅር ከፍተኛ ብርታት በእያንዳንዱ የአካል ክፍል መዘዋወር እንዲችልና በእርሱ እንዳደረ በእኛም እንዲያድር ነው። ያኔ እግዚአብሔር ልጁን እንደሚወድ ሁሉ የወደቀውን ሰው ሊወደው ይችላል፤ እኛን በተመለከተ ከዚህ ውጭ የሚያረካው ምንም ነገር እንደሌለ ያውጃል። --MS 11, 1892. {1MCP 245.4} 1MCPAmh 203.1