የተሟላ ኑሮ
ለእርዳታ የተዘረጋ እጅ
ቤቶቻችን ፈተና ለደረሰባቸው ወጣቶች ሁሉ መከለያ ምሽግ መሆን አለባቸው፡፡ ብዙ ወጣቶች በመንታ መንገድ ላይ ቆመዋል፡፡ የሚደረግላቸው ወይም የሚነገራቸው ነገር ሁሉ በያዝነውም ሆነ በሚቀጥለው ሕይወት የት እንደሚደርሱ ይወስናል፡፡ ሰይጣን ያድማቸዋል፡፡ የሚያታልልባቸውን ነገሮች የሚያጭበረብሩና የሚያጓጉ ናቸው፡፡ በነዚህ ፈተናዎች የሚታለለውን ሁሉ እንኳን ደህና መጣህ ብሎ ይቀበለዋል፡፡ ቤተሰብ በማጣት ወይም በማይረባ ቤተሰብ ምክንያት ባካባቢያችን ወጣቶች ይበላሻሉ፡፡ በበራችን አጠገብ ወደ ጥፋት ይሄዳሉ፡፡ CLAmh 11.4
እነዚህ ወጣቶች ለእርዳታ የርኅራኄ እጅ ሊዘረጋላቸው ይገባል፡፡ ጥቂት የርኅራኄ ቃላት ቢነገራቸውና ትንሽ የእርዳታ መንፈስ ቢያሳዩአቸው የከበባቸው የፈተና ደመና በተነሳላቸው ነበር፡፡ የክርስቶስ ጣፋጭ ቃላትና የፍቅር መንፈስ የሚያሻቸውን ልቦች ከሰማይ በወረደ ሰራጭ ኃይል ለመክፈት ይቻላል፡፡ ወጣቶችን ብናፈቅራቸው፣ ወደ ቤታችን ብናድማቸውና የረዳትነትና የደስታ መንፈስ ብናሳያቸው ብዙዎች በደስታ ወደ ላይ ወደሚወስደው መንገድ በተመለሱ ነበር፡፡ CLAmh 12.1
እዚህ የምንኖረው ሕይወት አጭር ነው፡፡ በዚህ አለም የምናልፈው አንድ ጊዜ ብቻ ስለሆነ በሙሉው እንጠቀምበት፤ የሕይወት መመሪያ ለሆኑት መለኮታዊ ደንቦች ቤታችንና ልባችንን ብንከፍት ሕይወት ሰጪ ለሆነ ኃይል መተላለፊያ እንሆን ነበር፡፡ ድርቅ ለመታውም ሕይወት ሁሉ የፈውስና የውበት ምንጭ ከቤታችን ይፈልቅ ነበር፡፡ CLAmh 12.2