የተሟላ ኑሮ
ሕይወት የቀልድ ጦርነት (ዘመቻ) አይደለም
በሕይወት ጦርነት ድልን ለማግኘት የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ የተሰለፍንበት ጦርነት ቀልድ አይደለም፡፡ ዘላለማዊ ጥቅም ወይም ጉዳት ሊያስከትል በሚችል ጦርነት ተሰልፈናል፡፡ ጤናን የሚያጓድል ነገር ሁሉ የአካልን ኃይል መቀነስ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮንና የሞራልንም ኃይል ጭምር ይቀንሳል፤ ያዳክማል፡፡ ጤናን ሊያጓድል የሚችል ልምድ ሁሉ በውነትና በሐሰት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ከማዳገቱም በላይ ኃጢአትን ለማሸነፍ አቅመቢስ ያደርጋል፡፡ የመሸነፍንም አስጊነት ያበዛል፡፡ CLAmh 6.2
“በሩጫ ውድድር ብዙ ሰዎች ይሮጣሉ፤ ሽልማቱን የሚያገኝ ግን አንድ ብቻ ነው” 1ቆሮ 9፡24፡፡ እኛ በተሰለፍንበት ጦርነት ግን ራሳቸውን የሚገቱና ትክክለኛዎቹን ደንቦች የሚከተሉ ሁሉ ሊያሸንፉ ይችላሉ፡፡ በየቀኑ ሕይወት እነዚህን ደንቦች የመጠበቅ ነገር በጣም ችላ ተብሏል፡፡ የጤናን ዋናነት ስንመለከት የምናደርገው ነገር ሁሉ ሊናቅ አይገባም፡፡ እያንዳንዱ የምናደርገው ነገር የሕይወትን ድል ነሺነት ወይም ተጠቂነት የሚወስነውን ሚዛን ወደ አንድ ጐን እንዲያጋድል ያደርገዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተ ሩጡ ሽልማቱን እንድታገኙ” ይላል፡፡ CLAmh 6.3
የጥንት ግሪክ ጨዋታ ተወዳዳሪዎቹ የሚያደርጉትን ራስን የመቆጣጠር ልምምድ በመጥቀስ ሐዋርያው ጳውሎስ “የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፤ እኛ ግን የማይጠፋውን፡፡ ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” ይላል፡፡ 1ቆሮ 9፡25-26 CLAmh 6.4
ለማንኛውም ቋሚ መታደስ መሰረቱ የእግዚአብሔር ሕግ ነው፡፡ ይህን ሕግ የመጠበቅን አስፈላጊነት ግልጽ በሆነ አኳኋን ማስረዳት አለብን፡፡ ይህም ሕግ በሕዝብ ፊት መደቀን አለበት፡፡ ሕጉም እንደ እግዚአብሄር ነዋሪና የማይለወጥ ነው፡፡ CLAmh 7.1
አሰቃቂ ከሆኑት ከመጀመሪያው የኃጢአት ውጤቶች አንዱ ሰው ራሱን የመግታት ኃይሉን ማጣቱ ነው፡፡ እውነተኛ መሻሻል የሚገኘው ይህ ኃይል ሲመለስ ብቻ ነው፡፡ CLAmh 7.2
ጠባይን ለማሻሻል አዕምሮና ነፍስ ሊዳብሩ የሚችሉት በአካል አማካይነት በቻ ነው፡፡ የነፍሳት ጠላት (ሰይጣን) የአካልን ኃይል ለማኮሰስ ፈተናውን የሚያነጣጥረው ለዚህም ምክንያት ነው፡፡ በዚህም ሥራው የተከናወነለት እንደሆነ መላው አካል ለክፉው ተገዢ ሆነ ማለት ነው፡፡ በበለጠ ኃይል ካልተገታ በስተቀር የሥጋዊ ተፈጥሯችን ዝንባሌ ጥፋትንና ሞትን እንደሚያስከትል የተረጋገጠ ነው፡፡ CLAmh 7.3
ሥጋችን መገታት አለበት፡፡ ከሰውነታችን የተሻለው ክፍል የገዢነት ሥልጣን ሊኖረው ይገባል፡፡ ስሜታችን ለፈቃድ ኃይላችን፤ ፈቃዳችንም ለእግዚአብሄር መገዛት አለበት፡፡ በመለኮታዊ ጸጋ የተቀደሰ የማሰብ ኃይል የሕይወታችን መሪ መሆን አለበት፡፡ CLAmh 7.4
እግዚአብሔር ከኛ ምን እንደሚፈለግ ለሕሊናችን ሊገለጥ ይገባዋል፡፡ ከመጥፎ ልማድና አጥፊ ከሆነ የምግብ ፍላጎት ገና ለመውጣት፤ ንጹሕ የመሆን ፍላጎት እንዲዚሁም ራስን የማሸነፍ ተግባር እንዲሰማው እያንዳንዱ ሰው መጐሳጐስ አለበት፡፡ የአዕምሯቸውና የአካላቸው ኃይል የእግዚአብሄር ስጦታ መሆኑንና ይህም ኃይል ለእግዚአብሔር አገልግሎት በተሻለ አኳኋን መጠበቅ እንዳለበት ሊገባቸው ይገባል፡፡ CLAmh 7.5
በጥንቱ የመስዋዕት አገልግሎት ነውር ያለበት መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር መሰዊያ አይቀርብም ነበር፡፡ የክርስቶስ ምሳሌ የነበረው መሥዋዕት እንከን የሌለው መሆን ነበረበት፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው፤ ልጆቹ ሊሆኑት የሚገባው ምሳሌ ነው፤ ይህም ማለት “ቅዱስና ያለነውር!” “ሕያው መሥዋዕት” “እግዚአብሔርን የሚያስደስቱ” እንዲሆኑ ነው፡፡ CLAmh 7.6
ያለ መለኮታዊ ኃይል ምንም ዓይነት ዘላቂ መታደስ ሊከናወን አይችልም፡፡ በተፈጥሮና በልምድ የሚመጣውን መጥፎ ዝንባሌ ለማገድ የሚደረግ ሰብአዊ መከላከያ ሁሉ በባሕር ዳር በማዕበል እንደሚታጠብ አሸዋ ነው፡፡ በውጭም ሆነ በውስጥም የሚያስቸግሩንን ፈተናዎች ለመከላከል የምንችለው የክርስቶስ ሕይወት በሕይወታችን የኃይል ምንጭ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ CLAmh 7.7
ነፍስን የሚያረክሱትን የተፈጥሮ መጥፎ ዝንባሌዎች ሰው በሙሉ ለማሸነፍ እንዲችል በማለት የሱስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የእግዚአብሔርን ሕግ ጠበቀ፡፡ የነፍስና የአካል ሐኪም የሆነው የሱስ በፍትወት ላይ ድልን አስገኘ፡፡ ሰው የጠባይን ፍጽምና እንዲያገኝ የሚያስፈልገውን መሣሪያ ሁሉ አደለ፡፡ CLAmh 8.1
ሰው ሕይወቱን ለክርሰቶስ ባስገዛ ጊዜ አዕምሮው በሕግ ይተዳደራል፤ ለምርኮኛስ ሁሉ ነጻነትን የሚያስገኝ የአርነት ሕግ (የእግዚአብሔር) ነው፡፡ ሰው ከክርስቶስ ጋር በመዋሐድ ነጻ ይሆናል፡፡ ለክርስቶስ መገዛት ማለት ፍጹም ሰው ለመሆን መታደስ ማለት ነው፡፡ CLAmh 8.2