የተሟላ ኑሮ

2/201

1—የተሻለ ሕይወት

የጤና አጠባበቅ ደንብ ማወቅ ከአሁኑ የበለጠ አስፈልጎ አያውቅም፡፡ ብዙ ሰዎች ባለማወቅ የጤናን ሕግ ስለሚተላለፉ መማር አለባቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ግን አውቆ አጥፊ ስለሆኑ እውቀታቸውን የሕይወታቸው መመሪያ የማድረግ ዋናነት ሊገለጽላቸው ይገባል፡፡ CLAmh 5.1

አብዛኛውን ጊዜ ስለጤና ጥበቃ በቂ ጥረት አይደረግም፡፡ ከታመሙ በኋላ እንዴት እንደሚታከም ከማወቅ ይልቅ መከላከል በጣም የተሻለ ነው፡፡ CLAmh 5.2

ለራሱና ለመላው ሰብአዊ ፍጡር ሲል እያንዳንዱ ሰው የሕይወትን ሕግ ማወቅና በሙሉ ሕሊናውም መታዘዝ አለበት፡፡ ማንኛውም ሰው ከፍጥረት ሁሉ ብልጫ ስላለው አስገራሚ ስለሚሆነው ስለሰው አካል ማወቅ አለበት፡፡ የልዩ ልዩ ብልቶችን ሥራና መላው አካል ጤነኛ ይሆን ዘንድ እንዴት እንደሚተባበሩም እያዳንዱ ሰው ማወቅ ይገባዋል፡፡ እንደዚሁም በአንጎልና በአካል ክፍሎች መካከል ያለውን ግንኙነትና በምን ሕግም እንደሚተዳደሩ ማጥናት አለበት፡፡ CLAmh 5.3

ሕመም ማለት የጤናን ሕግ በመተላለፍ ከሚመጣው ጉድለት አካልን ነጻ ለማውጣት ሥነ ፍጥረት የምታደርገው ጥረት ነው፡፡ የሕመም መነሻው መታወቅ አለበት፡፡ ጤናን የሚያጓድል ሁናቴ ሁሉ መለወጥና መጥፎ የኑሮ ልምድም መታረም አለበት፡፡ በዚህም አኳኋን ከአካል ቆሻሻውን ለማስወጣትና ትክክለኛውን ሁናቴ ለመመለስ ሥነ ፍጥረት መረዳት አለበት፡፡ እውነተኛዎቹ መድኃኒቶች ንጹሕ አየር፣ የጸሐይ ብርሃን፣ ጥሩ ምግብ መመገብ፣ እረፍት፣ የሰውነት ማጠንከሪያ ልምምድ ማድረግ፣ በውኃ መጠቀምና በመለኮታዊ ኃይል ማመን ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የሥነ ፍጥረት መድኃኒቶች ምን እንደሆኑና እንዴትም ሊጠቀምባቸው እንደሚገባው ማወቅ አለበት፡፡ የታመመ ሰው በሚታከምበት ጊዜ ምን ሕግ መከተል እንደሚገባ ማወቅና ይህንንም ሕግ በትክክል ሊጠቀሙበት መቻል እንደሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ CLAmh 5.4

በተፈጥሮ (በሥነ ፍጥረት) በመድኃኒቶች መጠቀም ብዙ ሰዎች ሊሞክሩ ከሚፈቅዱት ጥረትና ጥንቃቄ የበለጠ ይጠይቃል፡፡ የሥነ ፍጥረት የመጠገንና የማከም ሥራ ቀስ በቀስ ስለሚካሄድ ትዕግስት ለሌላቸው ዳተኛ ይመስላቸዋል፡፡ የማይጠቅምን ልምድ መተው መሥዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ እንቅፋት ካላጋጠማት ግን ሥነ ፍጥረት ሥራዋን በጥበብና በጥሩ መንገድ ታከናውናለች፡፡ የሥነ ፍጥረትንም ሕግ በመከተል የሚጸኑ ሁሉ ዋጋቸው የአካልና የአዕምሮ ጤንነት ይሆናል፡፡ CLAmh 5.5

ጤንነት በዕድል የሚመጣ ለመሆኑ ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ጤንነት ሕግን የመታዘዝ ውጤት ነው፡፡ ይህም በስፖርት ተወዳዳሪዎች ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ስፖርት ተወዳዳሪዎች በጣም ተጠንቅቀው ይዘጋጃሉ፡፡ ደህና አድርገው ይለማመዳሉ፤ ጥብቅ ሕግም ይከተላሉ፡፡ እያንዳንዱ የአካል ሕግ ይጠበቃል፡፡ የአካልን ብልት የሚያዳክም ቸልተኝነት ወይም መጠን አለማወቅ እንደሚያስጠቃቸው ያውቃሉ፡፡ CLAmh 6.1