የተሟላ ኑሮ

25/201

የሕፃንነት ትምህርት ጠቃሚነት

ሕፃናትን የማስተማር ዋናነት በቀላሉ ሊገመት አይገባም፡፡ ቆይተው ከሚያገኙት ትምህርት ይልቅ በሕፃንነታቸው ጊዜ የሚማሩት ትምህርትና የሚመሠርቱት ልምድ በበለጠ አኳኋን ጥሩ ጠባይን ለመገንባትና የሕይወትንም ትክክለኛ መስመር ለመያዝ ይረዳቸዋል፡፡ CLAmh 27.2

ወላጆች ይህንን ሊያስቡበት ይገባቸዋል፡፡ የሕፃናትን ጥንቃቄና ትምህርት ደንቦች ማስተዋል አለባቸው፡፡ ልጆቻቸው የአካል፣ የአእምሮና የሞራል ጤንነት እንዲኖራቸው አድርገው የማሳደግ ችሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ወላጆች የሥና ፍጥረትን ሕግ ማጥናት አለባቸው፡፡ የሰውንም አካል ብልቶች ማወቅ አለባቸው፡፡ የእያዳንዱ ብልት ሥራ የብልቶቹንም ግንኙነትና አንዱ ያለ ሌላ ሊሠራ እንደማይችል መረዳት አለባቸው፡፡ አካልና አእምሮ ያላቸውን ግንኙነትና በትክክልም ሊሠሪ የሚችሉበትን ሁናቴ ማጥናት ይገባቸዋል፡፡ የዚህን ዓይነት ዝግጅት ሳያደርጉ የወላጅነት ኃላፊነት መሸከም ኃጢአት ነው፡፡ CLAmh 27.3

በሰብአዊ ዘር ላይ ሥቃይንና ጥፋትን ከሚያመጡት መጥፎ ነገሮች አብዛኛዎቹን ለማስወገድ ይቻላል፤ ይህንም የማድረግ ኃይል ያለው በወላጆች እጅ ነው፡፡ የሕፃናትን ሕይወት የሚያጠፋ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እሱስ የነሱን ሞት አይመኝም፡፡ ልጆችን ለወላጆች መስጠቱ በዚህም ዓለም ሆነ በሚቀጥለው ጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ትምህርት እንዲሰጧቸው ነው፡፡ CLAmh 27.4

የልጁ ሕይወት በእርጋታና በመጠኑ እንደተያዘ መጠን ለአካሉና ለአእምሮው እድገት የተመቸ ይሆናል፡፡ እናቲቱ ሁልጊዜ ረጋ ያለችና ራስዋን የገታች መሆን አለባት፡፡ አንዳንድ ሕፃናት የበርጋጋነት ዝንባሌ ስላለባቸው የእናቲቱ የርጋታ መንፈስ ጥቅሙ ሊገመት የማይቻል የሚያረጋጋ ስሜት ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ CLAmh 27.5

ሕፃናት ሙቀት ይፈልጋሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ሙቀቱ ከመብዛቱ የተነሳ ንጹህ አየር በሌለበት ክፍል በማኖር ትልቅ ስህተት ይሠራል፡፡ የሕፃናትን ፊት የመሸፈን ልምድ ጎጂ ነው፤ ምክንያቱም በደንብ እንዳይተነፍሱ ስለሚያደርጋቸው ነው፡፡ CLAmh 27.6

ሕፃን ሰውነቱን ከሚያዳክም ወይም ከሚመርዝ ነገር ሁሉ መጠበቅ አለበት፡፡ አካባቢውን ንጹሕና የሚያስደስት ለማድረግ ማንኛውም ዓይነት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ድንገተኛ ወይም ብዙ የሙቀት መለዋወጥ እንዳይደርስባቸው በመጠንቀቅ ሕጻናት ተኝተው ወይም ነቅተው ሳል ቀንም ሆነ ማታ ንጹሕ አየር እዲያገኙ ማድረግ ይገባል፡፡ CLAmh 28.1

የሕፃኑ ልብሶች በሚዘጋጁበት ጊዜ ያለባበስን ፈሊጥ ለመከተል ወይም የሚያስደንቁ ለማድረግ ከመሞከር ይቅ ምቾትና ጤንነት የሚሰጡ ለማድረግ መጣር ይገባል፡፡ CLAmh 28.2