የተሟላ ኑሮ
በኤደን የአትክልት ቤት
ሰው በተጨነቀ የከተማ ዓይነት ኑሮ እንዲኖር የእግዚአብሄር ፈቃድ አይደለም፡፡ የመጀመሪ ወላጆቻችንን ለዓይንና ለጆሮ በነገሮች መካከል አስቀመጣቸው፤ አሁንም እኛ በእንደዚህ ያሉ ነገሮች እንድንደሰት ምኞቱ ነው፡፡ ወደ መጀመሪያው የእግዚአብሄር እቅድ እደተጠጋን መጠን የአካል፣ የአዕምሮና የነፍስ ጤንነት ለማግኘት ያለን ዕድል ከፍ ያለ ነው፡፡ CLAmh 18.5
ውድ በሆነ ቤት መኖር፤ ብዙና ውድ የሆኑ የቤት ዕቃዎች፣ እንደዚሁ ማንኛውም ዓይነት ምቾትና ድሎት ደስተኛና ጠቃሚ ለሆነ ሕይወት የሚያስፈልገውን ሁናቴ አያስገኝም፡፡ የሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ሰው ከሠራው ሁሉ የበለጠውን ለመስራት ነው፡፡ የተሻለ ሕይወት እንዴት ልንኖር እንደሚገባ ለማሳየት የእግዚአብሔር አምባሳደር (መልዕክተኛ) ሆኖ መጣ፡፡ ኃያል የሆነው አባቱ ለልጁ እንዴት ያለ ሁናቴ መረጠለት? ለኢየሱስ የወጣትነት ሕይወት የተመረጡት ዕድሎች ወይም ሁናቴዎች በገሊላ ተራራዎች ላይ ብቻዋን የምትገኝ ቤት፣ ራስን በሚያስከብር ሞያ የሚተዳደር ቤተሰብ፣ የተራ ሰው ኑሮ፣ በየዕለቱ ከችግር ጋር መጋፈጥ፣ ለራስ ይቅርብኝ ማለት፣ ቁጠባ፣ ትዕግስት፣ የፈቃድ አገልግሎት፣ በእናቱ አጠገብ ሆኖ በተወሰነ ሰዓት በብራና ላይ የተጻፉትን የጥንት መጻሕፍት ማንበብ፣ በበልግ በተሸፈኑት ሸለቆዎች የሚያስደስት የፀሐይ ግብ ወይም ጎህ፣ የተቀደሰ የሥነ ፍጥረት አገልግሎት፣ የፍጥረትና የእግዚአብሔር ጥንቃቄ ጥናትና ከእግዚአብሔር ጋር የመንፈስ ግንኙነት ነበሩ፡፡ CLAmh 18.6
በታሪክ የታወቁ ታላላቅ ሰዎችም በእንደዚህ ያለ ሁናቴ ነበር የኖሩት፡፡ የአብርሃምን፣ የያዕቆብን፣ የዮሴፍን፣ የሙሴን፣ የዳዊትንና የኤልሳዕን ታሪክ አንብብ፡፡ ከነዚህም በኋላ ታማኝነትን የሚጠይቅ የኃላፊነት ሥራ በሚገባ ያከናወኑትንና ዓለምንም ለማሻሻል ትልቅ ርዳታ ያደረጉትን ሰዎች ታሪክ አጥና፡፡ CLAmh 19.1
ከነዚህስ መካከል ስንቱ ናቸው በገጠር ያደጉ፡፡ ስለምቾት ኑሮ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ወጣትነታቸውን ጨዋታ በማሳደድ አላሳለፉትም፡፡ ብዙዎች ከድህነትና ከችግር ጋር የመታገል ግዴታ ነበረባቸው፡፡ ከወጣትነታቸው ጀምረው ከሥራ ጋር ተለማመዱ፡ ንጹህ አየር በብዛት በሚገኝበት ቦታ የኖሩት ንቁ ሕይወት አካላቸውን አጠነከረው፡፡ በራሳቸው የተፈጥሩ ችሎታ ላይ የመተማመን ግዴታ ችግርን ለማሸነፍና እንቅፋትን ለመዝለል አስቻላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ድፍረትንና ተስፋ አለመቁረጥን አተረፉ፡፡ በራስ የመተማመንና ራስን የመግታት ትምህርት ተማሩ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከመጥፎ ጓደኝነት በመጠበቃቸው የሥነ ፍጥረት አስደሳች ነገሮችና ንጹሕ ጓደኝነት ይበቃቸው ነበር፡፡ የኑሮ ልምዳቸው መጠነኛ ነበር፡፡ የሕይወትን ደንቦች ስለተከተሉ ንጹሕ፣ ብርቱና እውነተኛ ሆነው አደሩ፡፡ ለሕይወት ሥራቸው በተጠሩ ጊዜ በሙሉ አካል፣ አዕምሮና መንፈስ በመሥራታቸው መጥፎ ጠባይን አሸንፈው በዓለም ውስጥ ለጥሩው ነገር ኃይለኛ ድጋፍ ሆኑ፡፡ CLAmh 19.2