የተሟላ ኑሮ
“ማን ነካኝ”
ያች ደስ ያላት ሴት ታላቁን ፈዋሽ ማመስገን ፈልጋ ነበር፤ ግን ፈራች፤ አስራ ሁለት ዓመት ሙሉ ባለመድኃኒቶች ካደረጉላት የበለጠ በነፃ ፈጸመላት፡፡ ደስ ተሰኝታ በልቧ እያመሰገነች ከጉባዔው ወጥታ ልትሄድ አሰበች፡፡ የሱስ ድንገት ቆም አለና “ማን ነካኝ” አለ፡፡ ጴጥሮስ በመገረም “አቤቱ ሕዝቡ ያጨናንቁሃል ያጋፉህማል የዳሰሰኝ ማነው ትላለህ? አለ፡፡ (ሉቃስ 8፡45) ፡፡ የሱስም “አንድሰው ዳስሶኛል ኃይል ከእኔ እንደወጣ እኔ አውቃሉና” አለ፡፡ (ቁ. 46)፡፡ የሃይማኖትን መዳሰስ በግዴለሽነት ከተፈጸመ ድንገተኛ ግፊ ለይቶ ማወቅ ቻለ፡፡ ሆነ ተብሎ አንድ ሰው ስለዳሰሰው በመንካቱ የፈለገው ተፈጽሞለታል፡፡ ክርስቶስ ያን ጥያቄ የጠየቀ ለራሱ መልስ ፈልጎ አልነበረም፡፡ CLAmh 146.1
ሕዝቡን፤ ደቀመዛሙርቱንና ሴትዮዋን በዚህ አጋጣሚ ሊያስተምራቸው ፈለገ፡፡ የተጨነቁትን በተስፋ ሊያበረታታቸው ፈለገ፡፡ ፈውስን የሚያስገኝ የዕምነት ኃይል መሆኑን ሊያስረዳቸው ተነሣ፡፡ የሴትዮዋ ሃይማኖት እንዲሁ ሳይታወቅ ማለፍ እንደሌለበት አወቀ፡፡ በሴትዮዋ የምስጋና ንግግር እግዚአብሔር መከበር አለበት፡፡ ክርስቶስ ዕምነቷን እንደተቀበለላት ሊያስታውቃት ፈለገ፡፡ በግማሽ ብቻ ተባርካ እንድትመለስ አልፈቀደም፡፡ ችግሯን እንዳወቀላት፣ እንዳዘነላትና እምነቷን እንደደገፈላት ማወቅ ያስፈልጋታል፡፡ CLAmh 146.2
የሱስ ወደ ሴትዮዋ እየተመለከተ ማን እንደዳሰሰው ለማወቅ መፈለጉን ቀጠለ፡፡ ነገሩን መደበቋ እንዳላዋጣት አይታ እየተንቀጠቀጠች መጣችና ከእግሩ ሥር ወደቀች፡፡ የደስታ ልቅሶ እያለቀሰች እንዴት በእምነት የልብሱን ዘርፍ እንደነካችና እንደተፈወሰች በሕዝብ ፊት መሰከረች፡፡ ልብሱን መንካቷ ከድፍረት እንዳይቆጠርባት ሰግታ ነበር፡፡ ግን ክርስቶስ በአድራጎቷ አልነቀፋትም፤ የድጋፍ ቃሉን ሰነዘረላት፡፡ የሰውን ችግር ሰለሚያስተውል ከፍቅር ልብ በመነጨ ገር ንግግር አነጋገራት፡፡ “ልጄ ሆይ ዕምነትሽ አድኖሻል በሰላም ሂጂ” አላት (ቁ. 48)፡፡ ይህ አነጋገር በጣም አስደስቷት በልቧ አድሮ የነበረው የፍርሃት መንፈስ ስለተወገደላት ደስታዋ ሙሉ ሆነ፡፡ CLAmh 146.3