የተሟላ ኑሮ
27—የሃይማኖት ጀብዱ
በልቧ “ልብሱን የዳሰስሁ እንደሆነ እድናለሁ” ትል ነበረችና (ማቴዎስ 9፡21) ይህን የተናገረች ለ12 ዓመታት በአሰቃቂ በሽታ ተይዛ የኖረች አንዲት ቀን የጎደለባት ምስኪን ሴት ነበረች፡፡ ያላትን ሀብትና ንብረት ሁሉ ለባለመድኃኒቶች አንጠፍጥፋ ከፍላ አትድኝም በማለት ተስፋ አስቆርጠዋት ነበር፡፡ ግን፤ ስለአስገራሚው ፈዋሽ ስትሰማ ተስፋ በልቧ አደረባት፡፡ CLAmh 145.1
ቀርቤ ባነጋግረው እድን ይሆናል የሚል አሳብ አደረባት፡፡ የሱስ ኢሮስ የተባለ የምኩራብ አለቃ ልጁን እንዲፈውስለት ስለለመነው ወደ ሰውየው ቤት በመጓዝ ላይ ነበር፡፡ CLAmh 145.2
“ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” የሚለው የኢሮስ ልመና የየሱስን ልብ ስለነካው ሳያመነታ ተነሥቶ ጉዞውን ጀመረ፡፡ CLAmh 145.3
ሕዝቡ ስለበዛ ጉዞአቸው የጉንዳን ጉዞ ነበር፡፡ የሱስ በሕዝቡ መካከል ሲጓዝ በሽተኛ ሴት ወዳለችበት ቦታ ደረሰ፡፡ ወደርሱ ለመቅረብ ደጋግማ ብትሞክር ሳይሳካላት ቀረ፡፡ ልታነጋግረው አለመቻሏ ገባት፡፡ ጉዞውን ልታዘገይበት አልፈለገችም ነበር፡፡ ግን ልብሱን በመንካት ብቻ ሊያድን መቻሉን ሰምታ ነበር፡፡ ስለዚህ ያ ያገኘችው መልካም አጋጣሚ እንዳያመልጣት ብላ ለራሷ “የልበሱን ጫፍ ብነካ እድናለሁ” በማለት ወደፊት ገሠገሰች፡፡ CLAmh 145.4
ክርስቶስ አሳቧ ስለገባው ወደ ቈመችበት ሄደላት፡፡ ችግሯን ስላወቀላት ዕምነቷን ከሥራ ላይ እንድታውለው ፈቀደላት፡፡ CLAmh 145.5
ባጠገቧ ሲያልፍ የልብሱን ዘርፍ ልትነካ ቻለች፡፡ ያን ጊዜ መዳኗን አወቀች፡፡ ልብሱን ብትነካ መዳኗን ከልብ ስላመነች ስቃዩዋና ደካምነቷ ተወገደ፡፡ ድንገት ደስታ እንደ ኮረንቲ ኃይል በአካላቷ ሲሰራጭ ተሰማት፡፡ የጤንነት ስሜት ተሰማት፡፡ “ከሥቃይም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች፡፡” (ማርቆስ 5፡29) ፡፡ CLAmh 145.6