ታላቁ ተስፋ

12/15

የመከራ ዘመን

በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል ህዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተፅፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል» (ዳንኤል 12፡1)፡፡ ታተ 61.1

የሦስቱ መላእክት መልእክት ተሰራጭቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ኃጢአተኛ ለሆኑት ለምድር ነዋሪዎች የክርስቶስ ፀጋ ያበቃል የእግዚአብሔር ሕዝብ ተልዕኮአቸውን (ሥራቸውን) አሟልተው ፈፅመዋል የእግዚአብሔር ሕዝብ «ኋለኛውን ዝናብ» እና «ከጌታ ፊት መጽናናትን» ተቀብለዋል፣ ለሚጠብቃቸው የፈተና ጊዜ ተዘጋጅተዋል፡፡ መላእክትም በሰማይ ወዲህ እና ወዲያ እያሉ ይሯሯጣሉ፡፡ ከምድር የተመለሰው አንዱ መልአክ ሥራውን እንደፈፀመ፣ የመጨረሻውም ፈተና በዓለም ላይ እንደጀመረና ለመለኮታዊ ትዕዛዛት ታማኝ የነበሩ ሁሉ «የሕያው አምላክን ማህተም» እንደተቀበሉ አስታወቀ (አወጀ)፡፡ ከዚያም ኢየሱስ በሰማዩ ቤተመቅደስ ያከናውን የነበረውን የማማለድ ሥራ ያቆማል፡፡ እጆቹንም ወደላይ ከፍ አድርጎ በታላቅ ጩኸት «ተፈጸመ!» ሲል ይናገራል፡፡ «አመጸኛው ወደፊት ያምጽ፣ እርኩሱም ወደፊት ይርከስ፣ ጻድቁም ወደፊት ጽድቅ ያድርግ፣ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ» (ራእ. 22፡11) ብሎ ሲያውጅ የመላእክት ሠራዊት ሁሉ ዘውዶቻቸውን አንስተው ያስቀምጣሉ፡፡ ታተ 61.2

የእያንዳንዱ ሰው ጉዳይ ወይ ለሕይወት ወይም ደግሞ ለሞት ተወስኗል፡፡ ክርስቶስ ለህዝቡ የሚያደርገውን የእርቅ ሥራ ፈጽሟል፡፡ ኃጢአቶቻቸውንም ደምስሷል፡፡ የተገዢዎቹ ቁጥርም ተወስኗል፡፡ «መንግስት፣ ኃይልና ከሰማያት ያለው ሥልጣን ሁሉ ለዳኑት ይሰጣል ኢየሱስም የነገሥታት ንጉሥ እና የጌቶች ጌታ ሆኖ ይነግሳል፡፡ ኃጢአተኞች የምህረት ገደባቸውን አሳልፈዋል፡፡ ወደ ንስሃ ሲመራቸው ባለማቋረጥ ሲቃወሙት የነበረው የእግዚአብሔር መንፈስ በመጨረሻ ከእነርሱ ይወሰዳል፡፡ በመለኮታዊ ፀጋ ስላልተጋደሉ ለክፉው የተጋለጡ ይሆናሉ፡፡ ከዚያም ሰይጣን በምድር የሚኖሩትን ወደ መጨረሻው ታላቅ የመከራ ዘመን ይመራቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር መላእክት አግደው ይዘው የነበሩትን ኃይለኛ ነፋሳት በሚለቁበት ጊዜ የሁከትና የብጥብጥ ኃይላት (ሥልጣናት) ይፈታሉ፡፡ ይህች ዓለም በጥንቲቱ ኢየሩሳሌም ከደረሰው ጥፋት ወደ ሚበልጥ አሰቃቂ ጥፋት ትገባለች፡፡ አንድ መልአክ ብቻውን የግብፃዊያንን በኩር ልጆች ሁሉ አጠፋ፣ ምድሪቱንም በሃዘን አጥለቀለቃት፡፡ ንጉሥ ዳዊትም ሕዝቡን በመቁጠሩ ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት በበደለ ጊዜ ኃጢአቱ የሚቀጣበትን አሰቃቂ ጥፋት አንድ መልአክ ብቻውን ሊያመጣ ቻለ፡፡ ያ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ መሠረት ቅዱሳን መላእክት ይሰሩበት የነበረው የማጥፋት ኃይል ጌታ እራሱ በሚፈቅድበት ጊዜ ደግሞ በክፉ መላእክት ይከናወናል፡፡ በየቦታው ታላቅ ጥፋትን ለማስከተል የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብቻ በመጠባበቅ የተዘጋጁ ኃይሎች ዛሬም አሉ፡፡ ታተ 61.3

የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያከብሩት ሰዎች «በዓለም ላይ ፍርድን ያመጣችሁት እናንተ ናችሁ!» በመባል ይከሰሳሉ፡፡ «ብጥብጥ፣ ደም መፋሰስ ያመጣችሁት እናንተ ናችሁ!» ተብለው በሀሰት ይወነጀላሉ፡፡ የመጨረሻውን ማስጠንቀቂያ አጅቦ የነበረው ኃይል ኃጢአተኞችን አስቆጣቸው፣ ቁጣቸውም መልዕክቱን በተቀበሉት ሁሉ ላይ ነድዷል፡፡ ሰይጣንም በበለጠ የጥላቻ እና የስደት መንፈስን በማጋጋል ሥራውን ይቀጥላል፡፡ ታተ 61.4

ያኔ እግዚአብሔር ከአይሁድ ሕዝቦች በመጨረሻ እራሱን ባገለለበት ወቅት ካህናትም ሆነ ሕዝቡ ይህንን አላስተዋሉም ነበር፡፡ በሰይጣን ቁጥጥር ስር ቢሆኑም፣ በጣም መጥፎና አሰቀቂ በሆነው ንዴታቸው ቢነዱም ቅሉ ራሳቸውን «እኛ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ነን» እያሉ ይሸነግሉ ነበር፡፡ በቤተመቅደስ ያደርጉት የነበረውንም አገልግሎት ይቀጥሉ፣ መስዋዕቶቻቸውንም በረከሱት መሰዊያዎቻቸው ላይ ይሰው፣ በየቀኑም የእግዚአብሔር ልጅ ክቡር ደም በፈሰሰውና የእርሱን አገልጋዮችና ሐዋሪያት ለመግደል በሚሻው ህዝብ ላይ መለኮታዊ በረከት እንዲፈሰስ ይለምኑ ነበር፡፡ እንዲሁም ዛሬም በሰማይ ቤተ መቅደስ ውስጥ የማይሻረው ውሳኔ በሚተላለፍበትና የዓለም የመጨረሻ ዕጣ ለዘላለም በሚወሰንበት ጊዜም የምድር ነዋሪዎች ይህን ሳያስተውሉ ይቀራሉ፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ የራቃቸው ሰዎች የአምልኮ መልክ (ሃይማኖታዊነት) ይታይባቸዋል፡፡ በጥላቻ የተሞላው፣ ዓላማው ይከናወን ዘንድ እርሱን ለሚከተሉት ሰዎች የሚሰጣቸው ሰይጣናዊ ቅናት እንደ እግዚአብሔር ቅናት መስሎ ይቀርባል፡፡ ታተ 61.5

ሰንበት በመላው የክርስቲያን ዓለም አጨቃጫቂ ነጥብ ስለሆነ ሃይማኖታዊና ዓለማዊ ባለስልጣናት እሁድ ቀን እንዲከበር ሲተባበሩ በቁጥር እጅግ ጥቂት የሆኑት ይህንን ግዳጅ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ይህ ውሳኔአቸው ለጥላቻ የተዳረጉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ የቤተክርስቲያንን ስርዓትና የመንግስትን ሕግ የሚቃወሙት ጥቂት ሰዎች በትዕግስት ሊታለፉ እንደማይገባቸው ጥብቅ ማሳሰቢያ ይወጣል፡፡ ይህም «መላው ሕዝብ ተሳስቶ ሕገ-ወጥ ከሚሆን ጥቂቶች ቢሰቃዩ ይመረጣል» በሚል መንፈስ ነው የሚፈፀመው፡፡ ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ ዓመታት በፊትም የእስራኤል ሕዝብ ባለስልጣናት በክርስቶስ ላይ ተመሳሳይ ምክንያት ሰጥተው ነበር፡፡ ቀያፋ እንዲህ ነበር ያለው «ህዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ህዝቡ አንድ ሰው ቢሞት የሚሻል መሆኑን አታስተውሉም? (ዮሐ. 11፡50)፡፡ ታተ 62.1

ይህ አስተሳሰብ እንደ አንድ ወሳኝ አስተሳሰብ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ በመጨረሻም አራተኛይቱ ትዕዛዝ ሰንበትን ቀድሰው የሚጠብቁ ሰዎች ብርቱ ቅጣት እንደሚገባቸው፣ እነርሱን የሚያወግዝና ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ለሞት እንዲዳርጓቸው ለሕዝቡ ነፃነትን የሚሰጥ ድንጋጌ ይወጣል፡፡ በጥንቷ ዓለም የነበረው ካቶሊካዊነትና በአዲስ ዓለም ያለው ከሃዲ ፕሮቴስታንትነት የመለኮትን ሕግ (ትዕዛዛት) በሚያከብሩት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ሕዝቦች (ወገኖች) ነብዩ ኤርሚያስ «የያእቆብ የመከራና የስቃይ ዘመን» ብሎ ወደ ተነበየው ጊዜ ይገባሉ፡፡ «የሚያስፈራ ድምጽ ሰምተናል የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም፡፡ ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፣ እርሱንም የሚመስል የለምና፣ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፣ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል» (ኤር. 30፡5-7)፡፡ ታተ 62.2

የያዕቆብ የጭንቀት ሌሊት (ያኔ ከወንድሙ ከኤሳው እጅ ይድን ዘንድ በፀሎት የታገለው ትግል) የእግዚአብሔር ሕዝብ በመከራ ዘመን ከሚጋፈጡት ስደትና ስቃይ ጋር ይመሳሰላል (ዘፍ. 32፡24-30)፡፡ ያዕቆብ ለወንድሙ ለኤሳው የታሰበውን በረከት ለራሱ ለማድረግ አባቱን በማታለሉ ኤሳው እንዳይገድለው ሕይወቱን ለማዳን ሸሽቶ ነበር፡፡ ለአያሌ አመታት በስደት ከቆየ በኋላ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ሚስቶቹንና መንጎቹንም ይዞ ወደ ትውልድ ሃገሩ ለመመለስ ተነሳ፡፡ በሃገሩም ድንበር አጠገብ በደረሰ ጊዜ ኤሳው ወታደሮቹን ይዞ ሊቀበለው መምጣቱን ሲሰማ ተሸበረ፡፡ ከያዕቆብ ጋር ያሉት ያልታጠቁና መከላከል የማይችሉት ተከታዮቹ የጭከናና የግድያ ሰለባዎች የሚሆኑ ይመስላል፡፡ በድንጋጤውና በፍርሃቱም ላይ «ይህንን አደጋ በራሴ ላይ ያመጣሁት በኃጢአቴ ምክንያት ነው» የሚለው ራስን የመውቀስ ስሜት ተጨመረበት፡፡ የእርሱ ብቸኛ ተስፋ የእግዚአብሔር ምህረት፣ መከላከያው ደግሞ ፀሎት ብቻ መሆን ነበረበት፡፡ ሆኖም ወንድሙንም በመበደሉና በዚያን ሳቢያ የመጣበትን መከራ ለመግታት ያላደረገው ጥረት አልነበረውም፡፡ የክርስቶስ ተከታዮችም እንዲሁ ወደ መከራ ዘመን ሲቃረቡ በሕዝብ ፊት እራሳቸውን በእውነት ብርሃን ለማሳየት፣ የሃሰት ክስን ለማክሸፍ፣ እንዲሁም የህሊና ነፃነት የሚገፈፍበትን አደጋ ለማገድ እጅግ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ታተ 62.3

የነበረውን ጭንቀትና ሃዘን እንዳይመለከቱ በማሰብ ያዕቆብ ቤተሰቡን ወደ ሌላ ስፍራ ከሰደዳቸው በኋላ እግዚአብሔር እንዲማልደው ለመጠየቅ ብቻውን ቀረ፡፡ ራሱን እጅግ ዝቅ በማድረግ እግዚአብሔር ከአባቶቹ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን፣ ለእርሱም በቤቴልና በስደት አገር የተሰጠው የተስፋ ቃል እውን ይሆን ዘንድ እየተማጸነ ኃጥአቱን ተናዘዘ፣ በእግዚአብሔር ምህረትም ታመነ፡፡ በዚያ በጨለማና በብቸኝነት ጊዜ ራሱን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ማድረጉን ቀጠለ፣ ጸሎቱንም አላቋረጠም፡፡ በዚያም ጊዜ በድንገት አንዲት እጅ በትከሻው ላይ አረፈች፡፡ ሕይወቱን ሊያጠፋ የመጣ ጠላት መስሎት ባለው በሌለው ኃይሉ ከእርሱ ጋር መታገል ጀመረ፡፡ ጎህ መቅደድ ሲጀምርም ይህ እንግዳ ሰው መለኮታዊ ኃይሉን ተጠቀመ የጭኑን ሹልዳም ሲነካው በዚያን ጊዜ ያ ጉልበተኛ ሰው እንደ ሽባ ተዝለፍልፎ በእንግዳው ሰውዬ አንገት ላይ ረዳተ-ቢስና ደካማ መስሎ ወደቀ፡፡ በዚያን ጊዜ ያዕቆብ ሲታገል የነበረው ከቃል ኪዳኑ መልአክ ጋር እንደነበረ አስተዋለ፡፡ ምንም እንኳን አቅመ ቢስና ከፍተኛ ህመም የተሰማው ቢሆንም ዓላማውን አልተወም፡፡ በኃጢአቱም ምክንያት ለረዥም ጊዜ መከራ፣ ጸጸትና ችግርን ታግሶ ነበር አሁን ግን ለኃጢአቱ ምህረትን እንዳገኘ ማረጋገጫን ይፈልግ ነበር፡፡ መለኮታዊው እንግዳ ትቶት ሊሄድ ሲል ያዕቆብ አጥብቆ ያዘውና ይባርከው ዘንድ ጠየቀው፡፡ መልአኩም «ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ ልሂድ አለው!» ያዕቆብም «ካልባረከኝ አልለቅህም!» ብሎ መለሰ፡፡ እንዴት ያለ መታመን፣ እንዴት ያለ ፅኑነትና እንዴት ያለ ትዕግስት ነው እዚህ ላይ የተገለፀው?!፡፡ ይህ ልመና የኩራትና የትዕቢት ቢሆን ኖሮ ያዕቆብ ከመቅጽፈት ይጠፋ ነበር፡፡ ያዕቆብ ግን ቃልኪዳኑን በሚጠብቀው በእግዚአብሔር ምህረት በመታመን ደካማነቱንና ዋጋቢስነቱን በማወቅ ነበር ልመናውን ያቀረበው፡፡ ታተ 62.4

«ከአምላክ ጋር ታገለ፣ አሸነፈውም» (ሆሴዕ 12፡5) ፡፡ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ በትህትና፣ በንስሃና ራስን በማስረከብ ይህ ኃጢአተኛ፣ ተሳሳችና ሟች ሰው ከእግዚአብሔር ክብር ጋር ድልን ተጎናፀፈ፡፡ በሚንቀጠቀጡ እጆቹ የእግዚአብሔርን ተስፋ አጥብቆ ያዘ፡፡ የዘላለማዊው ፍቅር ልብም የኃጢአተኛውን ተማፅኖ አልናቀም፡፡ ለድል ነሺነቱ ማስረጃ እንዲሆንና ሌሎችም የእርሱን ምሳሌ ይከተሉ ዘንድ ለማበረታት ኃጢአትን ያስታውስ የነበረው ስሙ አሸናፊነትን ወደሚያዘክረው አዲስ ስም ተለወጠ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎ ማሸነፉ ሰውንም እንደሚያሸንፍ ማረጋገጫ ሆነለት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር መከታው ስለነበር የወንድሙን ቁጣ ለመጋፈጥ ፍፁም አልፈራም፡፡ ታተ 62.5

ሰይጣን «ያዕቆብን በኃጢአቱ ምክንያት ለማጥፋት መብት አለኝ» በማለት በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ወንጅሎት ነበር፡፡ ኤሳውንም በያእቆብ ላይ እንዲነሳ አነሳስቶት ነበር፡፡ ከመልአኩ ጋር በታገለበት በዚያች ሌሊትም የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማው ሊያስገድደው ሞከረ፡፡ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት እርሱን ተስፋ አስቆርጦ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን አንድነት እንዲያቋርጥ ነበር፡፡ ያዕቆብ በዚያ ወቅት ተስፋ ሊቆርጥ ምንም ያህል አልቀረውም ነበር፣ ከሰማይ እርዳታ ካልደረሰለት በስተቀር መጥፋት እንዳለበት ያውቅ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ስለ ታላቅ ኃጢአቱ በቅን ልቦና ንስሃ ገባ፡፡ የእግዚአብሔርንም ምህረት ለመነ፡፡ ከዓላማው ፈቀቅ አላለም፣ ይበልጡንም መልአኩን አጥብቆ ያዘ፣ እስከሚያሸንፍ ድረስም ከልብ በመቃተትና በማልቀስ ልመናውን አቀረበ፡፡ ታተ 63.1

ኤሳው በያዕቆብ ላይ እንዲዘምትበት ሰይጣን ተፅእኖ እንዳደረገ ሁሉ በመከራ ዘመንም ክፉዎች የእግዚአብሔርን ልጆች እንዲያጠፉ ያነሳሳቸዋል፡፡ ያዕቆብን እንደከሰሰ የእግዚአብሔርን ልጆችም እንዲሁ ይወነጅላል፡፡ ዓለምን እንደ ግዛቱ አድርጎ ይቆጥራል፣ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጠብቀው ትንሹ መንጋ ግን የእርሱን የበላይነት ይቃወማል፡፡ ሰይጣን እነዚህን ምዕመናን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ከቻለ ድሉ ፍጹም እንደሚሆንለት ያውቃል፡፡ እነርሱን ቅዱሳን መላእክት እንደሚጠብቋቸው ይመለከታል፣ ለኃጢአቶቻቸውም ምህረትን እንደተቀበሉ ያውቃል ሆኖም ግን የእነርሱ ጉዳይ በሰማይ ቤተመቅደስ እንደተወሰነ አያውቅም፡፡ በእርግጥ በእርሱ የማታለል ፈተና የሠሩትን ኃጢአቶች ያውቃል፡፡ ኃጢአቶቻቸውን ከመጠን በላይ በማጋነን እንደ እርሱ እራሱ «እነዚህም ሰዎች ከእግዚአብሔር ፍቅር (ፀጋ) ሊለዩ ይገባል» በማለት ይናገራል፡፡ «እግዚአብሔር በቅን ፍትህ እነዚህን ሰዎች ይቅር ብሎ እኔንና መላእክቴን ሊያጠፋ አይገባውም» በማለት ይናገራል፡፡ እነዚህ ኃጠአተኞች በሙሉ የእኔ ናቸው በማለት ያጠፋቸው ዘንድ ፈቃድ እንዲሰጠው እግዚአብሔርን ይጠይቃል፡፡ ታተ 63.2

ሰይጣን የእግዚአብሔርን ወገኖች (ልጆች) ስለ ኃጢአታቸው በሚወነጅልበት ወቅት እነርሱን እስከሚቻለው ድረስ እንዲፈትናቸው ጌታ ራሱ ይፈቅድለታል፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው ታማኝነት፣ እምነትና ጽኑእነት በብርቱ ይፈተናል፡፡ ያለፈውን ሕይወታቸውን ሲያስታውሱ ተስፋቸው ይመነምናል ምክንያቱም በቀድሞ ህይወታቸው ብዙ መልካም ነገር እንዳላደረጉ ይመለከታሉና፡፡ ደካማነታቸውና ዋጋቢስነታቸው ሙሉ በሙሉ ይስተዋላቸዋል፡፡ ሰይጣን የኃጢአት እድፈታቸው የማይነጻና ተስፋ የሌላቸው መሆናቸውን በመግለጽ ሊያስደነግጣቸው ይጥራል፡፡ በዚህ አኳኋን እምነታቸውን አጥፍቶ ለእርሱ ፈተና እንዲሸነፉለትና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን ታማኝነት ይተው ዘንድ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ታተ 63.3

ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ልጆች ሊያጠፏቸው በተዘጋጁ ጠላቶቻቸው ቢከበቡም የሚያሳስባቸውና የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ «ያለተናዘዝነው ኃጢአት ይኖር ይሆን? በሕይወታችን ያላስተካከልነው ነገር፣ እንደ ጌታ ቃል ያልሄድንበት ጊዜ ይኖርን? ለዚህ ይሆን እንዴ ጌታ ‹የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ› ብሎ የገባልንን ቃል ኪዳን የማይፈጽመው?» የሚለው ሃሳብ እንጂ ስለ እውነት በመቆማቸው ምክንያት ስለደረሰባቸው ስደት አይደለም፡፡ ታተ 63.4

ኃጢአታቸው ሁሉ እንደተሰረየላቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ቢሆኑ ኖሮ በደረሰባቸው ስቃይም ሆነ የሞት ፍርድ አይደነግጡም ነበር፡፡ ነገር ግን በራሳቸው የባህርይ ጉድለት ምክንያት ዋጋቢስ ሆነው ሕይወታቸውን መስዋእት ቢያደርጉ የእግዚአብሔር ቅዱሰ ስም ይዘለፋል፡፡ እነርሱ በሁሉ ቦታ የአመጻ ሴራ ሲካሄድ ይሰማሉ፣ የአመጽ ተግባርም በሁሉ ቦታ ሲካሄድ ያያሉ፡፡ ይህ ታላቅ ክህደት በቶሎ እንዲያበቃና የኃጢአተኞችም ክፋት ይፈጸም ዘንድ ነፍሳቸው ትመኛለች፡፡ በአንድ በኩል ይህ የአመጽ ሥራ እንዲገታ እግዚአብሔርን ሲማጸኑ በሌላ በኩል ግን ኃያሉን የክፋት ሞገድ በራሰችው ኃይል ለመቋቋምና ለመመለስ ባለመቻላቸው በራሳቸው ያዝናሉ፡፡ «ያለንን ችሎታ በሙሉ ክርስቶስን በማገልገል ሥራ ላይ ብናውለው እና ይበልጥም ከብርታት ወደ ብርታት እየጠነከርን ከሄድን ሰይጣን እኛን ለማሸነፍ ያለው የኃይል ብቃት ያነሰ ይሆናል» የሚል ሃሳብ ይሰማቸዋል፡፡ ታተ 63.5

ቀድሞ ላደረጉት ኃጢአቶቻቸው ንስሃ እንዲገቡ በመጠቆምና አዳኛቸውን «ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ» በማለት የሰጣቸውን የተስፋ ቃል እንዲፈጽምላቸው በመማፀን ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ያስጨንቃሉ፡፡ ፀሎታቸው ወዲያውኑ ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት እምነታቸው አይናወጥም፡፡ ምንም እንኳን ከባድ ጭነት፣ መሸበርና ሃዘን ቢደርስባቸውም ልመናቸውን ለእግዚአብሔር ከማቅረብ ወደኋላ አይሉም፡፡ ያዕቆብ መልአኩን አጥብቆ እንደያዘ እነርሱም የእግዚአብሔርን ብርታት የሙጥኝ ብለው ይይዛሉ፡፡ ልሳነ ነፍሳቸውም «ካልባረከኝ በቀር አልለቅህም» የሚለው ነው፡፡ ታተ 63.6

ያዕቆብ ብኩርናውን በማታለል በመውሰድ ያደረገውን ኃጢአት አስቀድሞ ባይናዘዝ ኖሮ እግዚአብሔር ጸሎቱን ባልሰማና ሕይወቱንም በምህረቱ ባላዳነለት ነበር፡፡ እንዲሁም የእግዚአብሔር ሕዝብ በፍርሃትና በጭንቀት በሚሰቃዩበት በዚያ የመከራ ጊዜ ትዝ የሚሏቸው ከዚህ ቀደም ያልተናዘዟቸው ኃጢአቶች ቢኖሯቸው በጠላት ይሸነፋሉ፡፡ ተስፋ መቁረጣቸውም እምነታቸውን ያጠፋል ይድኑም ዘንድ እግዚአብሔርን ለመማጸን ልበ ሙሉነት (ሙሉ እምነት) ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ነገር ግን እነርሱ የዋጋቢስነት ስሜት ከልብ ከተሰማቸው የሚገለጹ እና፣ የተደበቁ ስህተቶች (በደል) የላቸውም፡፡ ኃጢአቶቻቸው አስቀድሞ ለፍርድ ቀርቦ ተፍቋል ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይታሰቡም፡፡ ታተ 63.7

«በእለት ሕይወታችን የምንሠራቸውን ጥቃቅን ስህተቶች እግዚአብሔር አይቶ እንዳላየ ይሆናል» በማለት ሰይጣን ብዙዎችን ያሳምናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ግን ክፉን ዝም ብሎ እንደማያልፍ በያዕቆብ ላይ ባደረገው ድርጊት ያሳያል፡፡ ኃጢአቶቻቸውን ቸል ለማለትና ለመሸፈን የሚጥሩ፣ ሳይናዘዟቸውና ምህረት ሳያገኙባቸው፣ ኃጢአቶቻቸው ከሰማይ መጻሕፍት ሳይሰረዝ ሰፍረው እንዲቆዩ የሚፈቅዱ ሁሉ በሰይጣን ይሸነፋሉ፡፡ ዝግጅትን እስከ እግዚአብሔር ቀን ድረስ የሚያዘገይ ማንም ሰው በመከራ ዘመንም ሆነ ከዚያም በኋላ ባለው ጊዜ የመዘጋጀት እድልን አያገኝም፡፡ የዚህ አይነት ሰው ሁኔታ ተስፋ ቢስ ነው፡፡ ታተ 64.1

ወደ መጨረሻው አስፈሪ ተጋድሎ ሳይዘጋጁ የሚደርሱ የይስሙላ ክርስቲያኖች፣ በጭንቀት ውስጥ ሆነው በምሬት እየተቃጠሉ ኃጢአታቸውን ይናዘዛሉ፤ ሌሎች ኃጢአተኞችም የእነርሱን ጭንቀት በማየት ያፌዙባቸዋል። እነዚህ ኑዛዜዎች ከኤሳው ወይም ከይሁዳ ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እንዲህ ያሉ ኑዛዜዎችን የሚናዘዙ ሁሉ የሚያለቅሱት ከበደላቸው የተነሳ ሳይሆን መተላለፋቸው የሚያመጣባቸውን ቅጣት በመፍራት ነው። ምንም አይነት እውነተኛ የልብ መሰበር ወይም ኃጢአትን መጸየፍ አይሰማቸውም። ኃጢአታቸውን አምነው የሚቀበሉት ቅጣትን በመፍራት ነው። ነገር ግን፣ ልክ እንደ ጥንቱ ፈርኦን፣ ፍርዱ ሲነሳላቸው በሰማይ ላይ ወደ ማመጻቸው ይመለሳሉ። ታተ 64.2

የያዕቆብ ታሪክ እግዚአብሔር ተታለውና ተፈትነው እንደዚሁም ራሳቸውን ለኃጢአት አሳልፈው ሰጥተው ነገር ግን በእውነተኛ ንስሓ ወደ እርሱ የተመለሱትን ወደ ውጪ አውጥቶ እንደማይሰዳቸው ያረጋግጥልናል። እንዲህ ያሉትን ሰይጣን ሊያጠፋቸው የሚፈልግም እንኳን ቢሆን፣ እግዚአብሔር ግን ሊያጽናናቸውና ሊጠብቃቸው በጭንቅ ጊዜ መላእክቱን ይልክላቸዋል። የሰይጣን ጥቃቶች ብርቱና ጠንካራ ቢሆኑም፣ ማታለያዎቹም አስከፊ ቢሆኑ፣ ነገር ግን የጌታ አይኖች በልጆቹ ላይ ናቸው፤ ጆሮዎቹም ጩኸታቸውን ይሰማሉ። መከራቸው ታላቅ ነው፤ የእቶኑ እሳትም ሊበላቸው የተቃረበ ይመስላል፤ ነገር ግን አንጥረኛው ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ብቻ ነው ወደ እሳቱ የሚያቀርባቸው። እግዚአብሔር በከባድ መከራ ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ ለልጆቹ ያለው ፍቅር እጅግ ደማቅ በሆነው በስኬታቸው ቀን እንዳለው ጠንካራና በገርነት የተሞላ ነው። ነገር ግን በመከራው እሳት ውስጥ መግባታቸው አስፈላጊ ነው፤ ምድራዊነታቸው ሊወገድ ይገባል፤ በዚህም የክርስቶስ ምስል ይበልጥ ፍጹም ሆኖ ይንጸባረቃል። ታተ 64.3

በፊት ለፊታችን ያሉት የጭንቀትና የኃዘን ወራት ድካምን፣ መዘግየትን፣ ርሃብን መቋቋም የሚችል እምነትን ይጠይቃሉ። እንዲህ ያለው እምነት የፈለገ በከባድ ሁኔታ ቢፈተን አይጠፋም። የምህረት በር ከመዘጋቱ በፊት ያለው ጊዜ የተሰጠው ለዚያ ጊዜ ዝግጅት ለማድረግ ነው። ያዕቆብ ያሸነፈው ጽኑና ትእግሰተኛ ስለነበረ ነው። የተቀዳጀው ድል የጸሎት ሕይወት ኃይል ማስረጃ ነው። ልክ እንደ እርሱ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የተጠማጠሙ፣ ልክ እንደ እርሱ በጽናት የታገሱ፣ እርሱ ድል እንደነሳው እነርሱም ድል ይነሳሉ። እኔነትን ለመካድ እምቢተኛ የሆኑ፣ በእርሱም ፊት ለመቃተት፣ ለእርሱም በረከት ከልባቸው ዘለግ አድርገው የማይጸልዩ አያገኙትም። ከእግዚአብሔር ጋር መታገልን፣ ምን ያህል ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው የሚያውቁት? የምን ያህሎች ልብ ነው ኃይልን ሁሉ በመጠቀም በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት የሚቆየው? የሀዘን ሞገድ ሲያጥለቀልቀን፣ ጥቂቶች ብቻ ነን ለእግዚአብሔር ተስፋ ቃል በሙሉ እምነት ራሳችንን የምንሰጥ። ታተ 64.4

አሁን ትንሽ እምነትን ብቻ የሚለማመዱ ሰዎች፣ በሰይጣን የማታለያዎች ኃይልና ሕሊናንም ለማስገደድ በሚያወጣው አዋጅ ውስጥ የመውደቅ እድላቸው ከፍተኛ ነው። ፈተናውን በጽናት ለመቋቋም የሚችሉም ቢሆን በመከራው ጊዜ ጥልቅ በሆነ ጭንቀትና ምሬት ውስጥ ይወድቃሉ። ምክንያቱም እግዚአብሔርን መታመንን ልማዳቸው አድርገውት አያውቁም ነበርና። ችላ ብለውት የነበረውን የእምነት ትምህርት አሁን በአስቸጋሪ የሐዘን ጫና ውስጥ ሆነው ሊማሩት ይገደዳሉ። ታተ 64.5

የተስፋ ቃሎቹን በመፈተሽ ራሳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማስተዋወቅ ያለብን አሁን ነው። እውነተኛ ከልብ የምትመነጨውን እያንዳንዷን ጸሎት መላእክት ይመዘግባሉ። ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ችላ ከማለት ይልቅ እኔነትን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት ልንተወው ይገባል። በእርሱ ፈቃድ የሚመጣ ጥልቅ የሆነ ድህነትና ራስን መካድ ከሀብት፣ ከክብርና ከመሳሰሉት ሁሉ ይበልጣል። ለመጸለይ ጊዜ ልንወስድ ይገባል። አእምሮአችንን በምድራዊ ነገሮች እንዲወሰድ ከፈቀድን፣ የወርቅ፣ የቤቶች ወይም የለመለመ መሬት ጣዖቶቻችንን ከእኛ በማስወገድ እግዚአብሔር ጊዜ ሊሰጠን ይችላል። ታተ 64.6

የእግዚአብሔር በረከት እንዲከተላቸው ሊጠይቁ ከሚችሉበት መንገድ ውጪ በሌላ በማንኛውም መንገድ ውስጥ ላለመግባት ቢወስኑ ወጣቶች ለኃጢአት እጃቸውን አይሰጡም ነበር። ለምድራችን የተሰጠውን የመጨረሻውን ቅዱስ የማስጠንቀቂያ መልእክት የተሸከሙ መልአክተኞች ቀዝቃዛና ስንፍና በተሞላበት መንገድ ሳይሆን፣ ነገር ግን በግለትና በእምነት ልክ እንደ ያዕቆብ ቢጸልዩ፣ «እግዚአብሔርን አየሁት፤ ሕይወቴም ድና ቀረች” በማለት የሚናገሩበት ብዙ ስፍራዎች ባገኙ ነበር (ዘፍ. 32፡30)። በሰማይም ከሰውም ሆነ ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎ ለማሸነፍ ኃይል እንዳላቸው ይቆጠራሉ። ታተ 65.1

«ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ የመከራ ጊዜ» ከፊት ለፊታችን በቅርብ ይከሰታል፤ ብዙዎች በስንፍና ምክንያት የሌላቸውን፣ እኛም ብንሆን አሁን የሌለንን ልምምድ ማግኘት ይፈለግብናል። ብዙ ጊዜ መከራ ይደርሳል ተብሎ ሲጠበቅ የሚያስፈራውን ያህል በሚደርስበት ጊዜ እንደዚያው አይሆንም። ከፊት ለፊታችን በሚጠብቀን መከራ ላይ ግን ነገሩ እንደዚህ አይደለም። የፈለገ ግልጽ የተባለው መግለጫ የመከራውን መጠን ሊገልጸው አይችልም። በዚያ የመከራ ጊዜ እያንዳንዱ ነፍስ ስለ ራሱ በእግዚአብሔር ፊት ሊቀርብ ይገባዋል። «ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦» (ሕዝ. 14፡20) ታተ 65.2

አሁን ሊቀ ካህናችን ለእኛ ለማስተስረይ እያማለደ ባለበት ጊዜ በክርስቶስ ፍጹም ለመሆን መመኘት ይኖርብናል። በሃሳብ እንኳ አዳኛችን ለፈተና ኃይል እጁን አልሰጠም። ሰይጣን መቆናጠጫ አግኝቶ ምሽጉን የሚሰራባቸውን ነገሮች በሰው ሕይወት ውስጥ ያገኛል። አንዳንድ የኃጢአት ልምምዶች በእኛ ዘንድ ትኩረት ያገኛሉ፤ ነገር ግን ክርስቶስ ራሱ እንዲህ በማለት ተናግሯል፡- «ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤” (ዮሐ. 14፡30)። ሰይጣን በእርሱ ላይ ድልን ለመቀዳጀት ያስችለው ዘንድ ምንም አይነት ክፋት በሰው ልጅ ላይ ሊያገኝበት አልቻለም። የአባቱን ትዕዛዛት ጠበቀ፤ ሰይጣንም ለራሱ ጥቅም ሊጠቀምበት የሚችል አንድም ኃጢአት በእርሱ ዘንድ አልነበረም። በመከራ ጊዜ የሚያልፉ ሰዎችም ሊገኙበት የሚገባ ሁኔታ ይህ አይነት መሆን አለበት። ታተ 65.3

ኃጢአትን ከሕይወታችን መለየት ያለብን በዚህኛው ሕይወት ነው። ይህንንም የምናደርገው በክርስቶስ የሚያስተሰርይ ደም በኩል ባለን እምነት ነው። ውዱ አዳኛችን ራሳችንን ከእርሱ ጋር እንድናጣብቅ ይጠራናል። የእኛን ድካሞች ከእርሱ ብርታት ጋር እንድናያይዛቸው፣ አለማወቃችንን ከእርሱ እውቀት ጋር፣ የእኛን አለመብቃት ከእርሱ ጽድቅ ጋር ማቆራኘት አለብን። የእግዚአብሔር እንክብካቤ ትምህርት ቤት የኢየሱስን ትህትናና ዝቅ ማለትን የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው። እግዚአብሔር በፊታችን ዘወትር የሚያስቀምጠው ለእኛ መልካምና ቀላል መስሎ ታይቶን በቀላሉ የምንመርጠውን አይነት ሳይሆን፣ እውነተኛ የሕይወት ጭብጥ ያለውን ነው። ባሕሪያችን የመለኮትን አምሳል እንዲመስል ለማድረግ ከሚሰሩት መላእክቶች ጋር በመተባበር መሥራት የእኛ ድርሻ ነው። ማንም ሰው ነፍሱን በጣም ከባድ አደጋ ላይ ለመተው ካልሆነ በስተቀር እንዲህ አይነቱን ነገር ችላ ሊል አይገባም። ታተ 65.4

ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕይ ከሰማይ እንዲህ የሚል ከፍ ያለ ድምጽ ሰማ፡- «ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (ራዕ. 12፡12)። ከሰማይ እንዲህ ያለ ድምጽ እንዲሰማ ያደረገው ትዕይንት በእርግጥም አስፈሪ ነው። ጊዜው እንዳለቀ መጠን የሰይጣን ቁጣ እየጨመረ ይሄዳል፤ የእርሱም የማታለልና የማጥፋት ሥራ ጫፍ ላይ የሚደርሰው በመከራው ጊዜ ነው። ታተ 65.5

በቅርብ በሰማያት ላይ ተፈጥሮአዊ ከሆነው ነገር ውጪ የሆኑ አስፈሪ ክስተቶች መታየት ይጀምራሉ፤ እነዚህም የተአምር አድራጊ አጋንንቶችን ኃይል የሚያሳዩ ናቸው። የአጋንንት መናፍስት ወደ ምድር ነገስታትና ወደ መላው ዓለም በመውጣት፣ በማታለል ሥራቸው እንዲተባበሩና፣ ከሰይጣንም ጋር በማበር በሰማይ መንግስት ላይ እንዲነሱ ያደርጓቸዋል። በእነዚህ ኃይላትም፣ ገዢዎችና ሕዝቦቻቸው ሁሉ ይታለላሉ። ራሱ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያስመስሉ ሰዎች ይነሳሉ፤ ለዓለም አዳኝ የሚገባውን ማዕረግና አምልኮንም ለራሳቸው ለማድረግ ይሰራሉ። አስደናቂ የሆኑ የፈውስ ሥራዎችን ይሰራሉ። ከተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ምስክርነት ጋር የሚቃረን መገለጥ እንዳላቸውም ይናገራሉ። ታተ 65.6

በዚህ ታላቅ የማታለል ድራማ ውስጥ የመጨረሻ ድርጊት ሆኖ የሚመጣውም፣ ሰይጣን ራሱን ክርስቶስ በአካል እንደመጣ አስመስሎ በማቅረብ ነው። ቤተክርስቲያን የተስፋዋ የመጨረሻ ፍጻሜ በመሆን ‹አዳኙ ዳግም ይመጣል› በማለት በመናገር ስትጠባበቅ ኖራለች። አሁን ደግሞ ታላቁ አታላይ ልክ ክርስቶስ እንደመጣ ለማስመሰል ይጥራል። በዓለማችን የተለያዩ ቦታዎች፣ ሰይጣን ራሱን በሰዎች መካከል እጅግ አንጸባራቂ የሆነ ባለግርማ ፍጡር አድርጎ ይገልጻል። በዚህም በራዕ. 1፡13-15 ላይ የሚገኘውን ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን መግለጫ ይኮርጃል። በእርሱ ዙሪያ የሚከበውም ክብር ከዚህ በፊት ሟች የሆነው የሰው አይን አይቶት የማያውቀው ይሆናል። «ክርስቶስ መጣ! ክርስቶስ መጣ!” የሚል የድል ጩኸት አየሩን ይሞላዋል፡፡ ሕዝቡም በፊቱ ምስጋናን በመስጠት ሲደፉ፣ እርሱ ደግሞ እጁን በማንሳት በእነርሱም ላይ የባርኮት ቃላትን ይናገራል። ይህም ልክ ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለ ደቀመዛሙርቱን የባረከበትን አይነት የሚመስል ነው። ድምጹ ለስለስ ያለና፣ ዜማ ያለው ነው። ገርነትና ርህራሄ በተሞላ ድምጽ አዳኙ አስቀድሞ የተናገራቸውን ተመሳሳይ በጸጋ የተሞሉ ሰማያዊ ቃላት ይናገራል። የሰዎችን ደዌ ይፈውሳል። የክርስቶስን ገጸ ባሕርይ በመላበስም ሰንበትን ከቅዳሜ ወደ እሁድ እንደቀየረው ይናገራል። ከዚያም እርሱ የባረከውን ቀን ሰው ሁሉ ቅዱስ አድርጎ እንዲጠብቀው ይናገራል። ሰባተኛውን ቀን ቅዱስ አድርገው በመጠበቅ የሚጸኑ ሰዎች ብርሃንና እውነትን አስይዞ የላካቸውን የእርሱን መላአክት ባለመስማት የእርሱን ስም እንደሚሳደቡ ይናገራል። ይህ በጣም ጠንካራና፣ ሁሉን ሊያሸንፍ የሚችል ማታለያ ነው። በስምኦን ተታለው እንደነበሩት ሰማርያውያን፣ ከትንሽ እስከ ትልቁ ድረስ፣ ለእነዚህ የጥንቆላ ድምጾች ጆሮ በመስጠት እንዲህ ይላሉ፡- ይህ «ታላቅ የእግዚአብሔር ኃይል” ነው። (የሐዋ. 8፡10) ታተ 65.7

ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝቦች አይታለሉም። የዚህ ሐሰተኛ ክርስቶስ አስተምህሮዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተስማሙ አይደሉም። የእርሱ ባርኮት የሚፈሰው አውሬውንና ምስሉን በሚያመልኩት ላይ ነው፤ በእነዚህም ላይ መጽሐፍ ቅዱስ «ያልተቀላቀለው የእግዚአብሔር ቁጣ» እንደሚፈስባቸው አውጆአል። ታተ 66.1

እንደዚሁም፣ ሰይጣን የክርስቶስን አመጣጥ ሙሉ በሙሉ በማስመሰል ይሰራው ዘንድ አልተፈቀደለትም። አዳኙ ሕዝቡን እንዲህ ካለው ማታለያ እንዲጠበቁ አስጠንቅቋቸው ነበር፤ ይህንንም ያደረገው የእርሱ አመጣጥ እንዴት እንደሚሆን በመናገር ነበር። «ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።… እንግዲህ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤» (ማቴ. 24፡24-27፣31፤ 25፡31፤ ራዕ. 1፡7፣ 1ተሰ. 4፡16-17)። በዚህ አይነት አመጣጥ ምንም አይነት የማስመሰል ሥራ ሊሰራበት አይችልም። ይህ ዓለም አቀፋዊ፣ ሁሉም ዓለም የሚያየው ክስተት ነው። ታተ 66.2

የመጽሐፍ ቅዱስ ትጉ ተማሪ የሆኑትና እውነትን የሚወድ ልብ ያላቸው ብቻ ዓለምን ሁሉ በቁጥጥር ስር ከሚያውለው ከእንዲህ አይነቱ ማታለያ ይጠበቃሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት እነዚህ ሰዎች የአታላዩን ጭምብል ለይተው ያውቃሉ። ለሁሉም ሰው ፈታኙ ጊዜ ይመጣል። በፈተና ማበጠሪያም የእውነተኛ ክርስቲያኖች ማንነት ይገለጣል። የእግዚአብሔር ሕዝቦች የስሜት ሕዋሳቶቻቸው የሚያቀርቡላቸውን መረጃዎች ባለመቀበል የእግዚአብሔር ቃል ብቻ የሚለውን ለመቀበል በሚችሉበት ሁኔታ ተመስርተዋል? እንዲህ ባለ የቀውስ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ለመጠማጠም ይችላሉ? ሰይጣን ከተቻለው በዚያ ቀን ለመቆም እንዳይችሉ ዝግጅት እንዳያደርጉ ለማድረግ ይፈልጋል። ነገሮችን ጥሩ አድርጎ በማቀናጀት በምድራዊ ነገር እንዲቆላለፉ በማድረግ፣ እጅግ አድካሚ የሚወጥር ሸክም እንዲሸከሙ በማድረግ፣ ልባቸው በዚህ ዓለም ነገር ብቻ እንዲሞላ በማድረግ የመከራው ጊዜ ልክ እንደሌባ እንዲደርስባቸው ያደርጋል። ታተ 66.3

ትዕዛዛቱን በሚጠብቁት ላይ በተለያዩ የክርስትና መሪዎች አማካኝነት አዋጅ በሚወጣበት ጊዜ የመንግስት ከለላ ከእነርሱ ላይ ስለሚነሳ፤ የእነርሱን ጥፋት ለሚፈልጉት ተላልፈው እንዲሰጡ ይሆናል። የእግዚአብሔር ሕዝቦችም ከከተማዎችና ከመንደሮች ይሸሻሉ። በተለያዩ ማሕበሮችም ራሳቸውን በማደራጀት፣ በጣም በራቁ የብቸኝነት ስፍራዎች ይቀመጣሉ። ብዙዎች በተራሮች መካከል ምሽግ ያገኛሉ። በፔይዴሞንት ሸለቆ እንደነበሩት ክርስቲያኖች፣ የምድርን ከፍታ ቦታዎች መቅደሶቻቸው በማድረግ ስለ «ጠንካራ አምባዎች” እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ (ኢሳ. 33፡16)። ነገር ግን ከትልቅና ከትንሽ፣ ከሃብታምና ከድሃ፣ ከጥቁርና ከነጭ መካከል ብዙዎች በጣም ፍትህ በጎደለውና ጭካኔ በተሞላ እስር ውስጥ ይወድቃሉ። የተወደዱት የእግዚአብሔር ሕዝቦች የድካም ቀኖችን ያልፋሉ፤ በሰንሰለት ይታሰራሉ፤ በእስር ቤት ይጣላሉ፤ ለመታረድ ይፈረድባቸዋል፤ አንዳንዶችም በረሀብ እንዲያልቁ በጨለማ እስር ቤት ውስጥ ይተዋሉ። የእነርሱን ሲቃ ለመስማት የሚያዘነብል ምንም አይነት ሰብአዊ ጆሮ አይኖርም፤ ሊረዳቸውም የሚዘረጋ እጅ አይኖርም። ታተ 66.4

እግዚአብሔር እንዲህ ባለው ፈታኝ ጊዜ ሕዝቡን ይተዋቸዋልን? ከውሃ ጥፋት በፊት በነበረው ሕዝብ ላይ የፍርድ ቅጣት በወረደ ጊዜ ታማኙን ኖህን እግዚአብሔር ትቶታልን? ከተሞቹን ለመብላት ከሰማይ እሳት በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ሎጥን ረስቶታልን? በጣኦት አምላኪ ግብጻውያን በተከበበ ጊዜ ዮሴፍንስ ረስቶት ነበርን? ለበአል ነብያት በገጠማቸው ነገር እርሱንም እንደምትጎበኘው ኤልዛቤል በቁጣ በማለች ጊዜ ኤልያስን ትቶታልን? በጨለማ የእስር ቤት ጉድጓድ ውስጥ ኤርሚያስን ትቶታልን? ሦስቱን ታማኞች በእሳቱ እቶን ለብቻቸው ተዋቸውን? ወይስ ዳንኤልን በአንበሳ ጉድጓድ? ታተ 66.5

«ጽዮን ግን፦ እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ መዳፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ።” (ኢሳ. 49፡14-16)። «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፡- ከክብሩ በኋላ ወደ በዘበዙአችሁ አሕዛብ ልኮኛል፣ የሚነካችሁ የዓይኑን ብሌን የሚነካ ነውና።» (ዘካ. 2፡12) ታተ 66.6

ምንም እንኳን ጠላቶቻቸው ወደ እስር ቤት ቢወረውሯቸውም፣ የእስርቤቱ ግድግዳዎች በነፍሳቸውና በክርስቶስ መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያቋርጡ አይችሉም። እያንዳንዱን ድካማቸውን ያየ እርሱ፣ ደግሞም መከራቸውን ራሱ ቀምሶ የሚያውቅ እርሱ፣ ከምድራዊ ኃይሎች ሁሉ ይበልጣል። መላእክቶችም ለብቻቸው በተቀመጡባቸው እስር ቤቶች የሰማይን ሰላምና ብርሃን ይዘው ይመጡላቸዋል። እስር ቤቱም እንደ ቤተመንግስት ይሆንላቸዋል። በእምነት ባለጸጋ የሆኑት በዚያ ይኖራሉና። ጨለማ የዋጣቸው የእስር ቤቱ ግድግዳዎች ላይ የሰማይ ብርሃን ይበራባቸዋል። ልክ ጳውሎስና ሲላስ በፊልጲስዮስ እስር ቤት በእኩለ ሌሊት ሲጸልዩና የምስጋና መዝሙር ሲዘምሩ እንደሆነው ይሆናል። ታተ 67.1

የእግዚአብሔር ፍርዶች የእርሱን ሕዝብ ሊጨቁኑና ሊያጠፉ በሚፈልጉ ሁሉ ላይ ይመጣሉ። ክፋትን መታገሱ ክፉዎችን በክፋታቸው ደፋሮች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ነገር ግን ቅጣታቸው ረዥም ጊዜ ዘግይቶ እንደመምጣቱ የተረጋገጠና አሰቃቂ ነው የሚሆነው። «እግዚአብሔርም ሥራውን፣ ማለትም እንግዳ ሥራውን ይሠራ ዘንድ፥ አድራጎቱንም፣ ማለትም ያልታወቀውን አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ በፐራሲም ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፥ በገባዖንም ሸለቆ እንደ ነበረ ይቈጣል።” (ኢሳ. 28፡21)። ለመሐሪው አምላካችን የቅጣቱ ድርጊት እንግዳ ድርጊት ነው። «እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።” (ሕዝ. 33:11)። እግዚአብሔር «መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥» ነገር ግን «በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥» አምላክ ነው። «እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም ‹ንጹሕ ነህ› አይልም፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።” (ናሆም 1:3)። በጽድቁ የተረገጠውን የእርሱን ሕግ ስልጣን ለማሳየት አሰቃቂ ነገሮችን ያደርጋል። አመጸኞች የሚጠብቃቸው ቅጣት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እግዚአብሔር ይህንን ቅጣት ለማውረድ ምን ያህል እየታገሰ እንዳለ በመመልከት መረዳት ይቻላል። ለረዥም ጊዜ የሚታገሳቸው ሕዝቦች፣ ጽዋቸውም እስከሚሞላ ድረስ የማይነካቸው፣ በመጨረሻ ከምህረት ጋር ያልተቀላቀለውን የቁጣውን ጽዋ ይጠጣሉ። ታተ 67.2

ክርስቶስ በሰማያዊ መቅደስ ማማለዱን ሲያቆም፣ «ለአውሬውና ለምስሉ በሚሰግዱት እንደዚሁም ምልክቱን በሚቀበሉ ላይ ይወርዳል» የተባለው ያልተቀላቀለው ጽዋ ይመጣል (ራዕ. 14፡9-10)። እስራኤልን ከግብጽ ነጻ ከማውጣቱ በፊት እግዚአብሔር እንዳወረደው አይነት መቅሰፍት ሆኖ ነገር ግን የበለጠ አሰቃቂና መጠነ ሰፊ የሆነ መቅሰፍት የእግዚአብሔር ሕዝብ ለመጨረሻ ጊዜ ነጻ ከመውጣታቸው በፊት ይመጣል። እነዚህን አሰቃቂ መቅሰፍቶች በተመለከተ ሲገልጽ ባለራዕዩ እንዲህ ብሏል፡- «ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቍስል ሆነባቸው። ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፥ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ። ሦስተኛውም መልአክ ጽዋውን በወንዞችና በውኃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ።» እነዚህ መቅሰፍቶች ከባድ ቢሆኑም፣ የእግዚአብሔር ፍትሐዊነት በግልጽ ይታይባቸዋል። የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ ይላል፡- «ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፥ ቅዱስ ሆይ፥ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።» (ራዕ. 16፡2-6) የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት በሰጡት ፍርድ፣ ራሳቸውም ደም በራሳቸው ለማፍሰስ የሞከሩ ያህል ነበር የሆኑት። በተመሳሳዩ ክርስቶስም በዘመኑ የነበሩትን አይሁዶች ከአቤል ጀምሮ የፈሰሱትን የንጹሕ ሰዎችን ደም በተመለከተ ተጠያቂዎች መሆናቸውን ተናገረ። ምክንያቱም መንፈሳቸው ተመሳሳይ ሲሆን ነብያቱን ከገደሉት ሰዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነን ነገር ማድረግ ስለሚፈልጉ ነው። ታተ 67.3

ቀጥሎ በሚመጣው መቅሰፍት ለጸሐይ «ሰዎችን በታላቅ ትኩሳት ለማቃጠል” ኃይል ተሰጣት። «ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፥” (ራዕ. 16፡8-9)። በዚህ አስፈሪ ጊዜ የምድር ሁኔታ ምን እንደሚመስል ሲገልጽ ነብዩ እንዲህ ይላል፡- «እህሉ ጠፍቶአልና፥ ወይኑም ደርቆአልና፥ ዘይቱም ጐድሎአልና እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአል፥ ምድሪቱም አልቅሳለች። መከሩ ከእርሻቸው ጠፍቶአልና ገበሬዎች ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ አፈሩ፣ የወይን አትክልተኞችም አለቀሱ። ወይኑ ደርቆአል፣ በለሱም ጠውልጎአል፣ ሮማኑና ተምሩ እንኰዩም የምድርም ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፣ ደስታም ከሰው ልጆች ዘንድ ርቆአል። … አቤቱ፥ እሳት የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና፥ ነበልባሉም የዱሩን ዛፍ ሁሉ አቃጥሎአልና ወደ አንተ እጮኻለሁ። ፈሳሹ ውኃ ደርቆአልና፥ እሳቱም የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና የምድር አራዊት ወደ አንተ አለኸለኩ።» «የመቅደሱ ዝማሬ በዚያ ቀን ዋይታ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፥ በስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል።” (ኢዮኤል 1:10-12, 17-20፤ አሞጽ 8:3) ታተ 67.4

እነዚህ መቅሰፍቶች በሁሉም ላይ የሚወርዱ አይደሉም። ባይሆን ኖሮ የምድር ነዋሪዎች በሙሉ በጠፉ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ሥጋ ለባሽ አይቶት የማያውቀው እጅግ አሰቃቂ ቅጣቶች ናቸው። በሰዎች ላይ ከምህረት መዘጋት በፊት የሚወርድ ፍርድ ሁሉ ከምህረት ጋር የተቀላቀለ ነው። የሚማልደው የክርስቶስ ደም የበደላቸውን ሙሉ ቅጣት እንዳያገኙ ሸፍኖአቸዋል። ነገር ግን በመጨረሻው ፍርድ ጊዜ ቁጣው ምንም አይነት ምህረት ሳይቀላቀልበት ይወርዳል። ታተ 68.1

በዚያ ቀን፣ ለረዥም ጊዜ ሲያፌዙበት የነበረውን የእግዚአብሔርን ከለላ ለማግኘት ብዙዎች ይመኛሉ። «እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይሯሯጣሉ፥ አያገኙትምም።» (አሞጽ 8፡11-12) ታተ 68.2

የእግዚአብሔር ሕዝብ ከስቃይ ነጻ አይሆንም፤ ነገር ግን ስደትና መከራ ሲደርስባቸው፣ በችግር ውስጥ በጽናት ሲያልፉና ምግብ በማጣት ሲሰቃዩ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ያጠፏቸው ዘንድ ለብቻቸው አይተዋቸውም። ለኤልያስ የተጠነቀቀ አምላክ ራሱን ለእርሱ መስዋዕት በሚያደርግ ልጁ አጠገብ እንዲሁ አያልፍም። የጸጉራቸውን ልክ እንኳን ቆጥሮ የሚያውቅ አምላክ ለእነርሱ ጥንቃቄ ያደርጋል፤ በረሐብ ጊዜም እነርሱ ይጠግባሉ። ክፉዎች ከረሃብና ከቸነፈር የተነሳ ሲያልቁ፣ መላእክት ጻድቃንን ይጋርዱአቸዋል፤ የሚያስፈልጋቸውንም ነገሮች ያሟሉላቸዋል። «በጽድቅ ለሚሄድ» የሚከተለው የተስፋ ቃል ተገብቶለታል፡- «እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች።» «ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም።» (ኢሳ. 33፡15፣16፤ 41፡17) ታተ 68.3

«ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥” ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚፈራ እርሱ እንዲህ ይላል፡- «በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” (ዕንባ.3፡17-18) ታተ 68.4

«እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል። ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት።” «እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥአንንም ብድራት ታያለህ። አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም።» (መዝ. 121፡5-7፤ 91፡3-10) ታተ 68.5

ይሁን እንጂ ከሰብአዊ እይታ አኳያ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት ሰማዕታት በደማቸው ምስክርነታቸውን በቅርብ እንደሚያትሙ ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል። እነርሱ ራሳቸውም ጌታ በጠላቶቻቸው እጅ ውስጥ እንዲወድቁ ትቶአቸው እንደሄደ በማሰብ መፍራት ይጀምራሉ። ጊዜው በፍርሃት የተሞላ ሲቃ የሚደመጥበት ነው የሚሆነው። በቀንና በማታ ይታደጋቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጮሃሉ። ክፉዎችም ይጓደዳሉ፤ በማፌዝም እንዲህ ያላሉ፡- «እምነታችሁ አሁን የት ሄደ? በእርግጥ እናንተ የእርሱ ሕዝብ ከሆናችሁ እግዚአብሔር ለምን ከእጃችን አይታደጋችሁም?” ነገር ግን በመከራ እየታገሱ የሚጠበቁቱ ኢየሱስ በቀራኒዮ መስቀል ላይ በሚሞትበት ጊዜ የካህናት አለቆችና ገዥዎች በማፌዝ እንዲህ በማለት የተናገሩትን ያስታውሳሉ፡- «ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን።” (ማቴ. 27፡42)። ልክ እንደ ያዕቆብ፣ ሁሉም ከእግዚአብሔር ጋር ትግል ይገጥማሉ። የፊት ገጽታቸው የውስጥ ትግላቸውን ይገልጻል። በሁሉም የፊት ገጽ ላይ መገርጣት ይታያል። ይህም ሆኖ ግን ከልብ የሚፈልቀው ምልጃቸው አይቋረጥም። ታተ 68.6

ሰዎች በሰማያዊ መገለጥ ማየት ቢችሉ ኖሮ፣ የክርስቶስን የትዕግስት ቃል በሚጠብቁት ዙሪያ የሰፈሩትን እጅግ በኃይል የበረቱ መላእክትን ስብስብ ማየት በቻሉ ነበር። ርህራኄ በተሞላ ገርነታቸው፣ መላእክቶች በመከራ ውስጥ የሚያልፉትን ቅዱሳን ጭንቀት ያያሉ፤ ጸሎታቸውንም ሰምተዋል። እነርሱንም ካሉበት ሁኔታ ነጥቀው ለማውጣት የአዛዣቸውን ትዕዛዝ ብቻ ነው የሚጠባበቁት። ነገር ግን ይህንን ከማድረጋቸው በፊት ለጥቂት ጊዜ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከጽዋው መጠጣት አለባቸው፤ ጥምቀቱንም መጠመቅ አለባቸው። ምንም እንኳን መዘግየቱ እጅግ የሚያም ቢሆንም፣ ላቀረቡት ልመና ግን ምርጥ የሆነው መልስ እርሱ ነው። እግዚአብሔር እንደሚሰራ በእርሱ በመታመን ለመቆየት ሲታገሉ እምነትን፣ ተስፋንና ትእግስትን ወደ መለማመድ ይመራሉ። ከዚህ ቀደም በነበራቸው ኃይማኖታዊ ልምምድ ውስጥ እነዚህን የተለማመዱት በጣም በጥቂቱ ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ፣ ለተመረጡት ሲባል የመከራው ጊዜያት ያጥራሉ። «እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል።” (ሉቃ. 18፡7፣8)። መጨረሻው ሰዎች ከሚጠባበቁት በላይ በፍጥነት ይመጣል። ስንዴው ይሰበሰብና ነዶው ታስሮ በእግዚአብሔር እንዲሰበሰብ ይቀመጣል፤ እንክርዳዶች ደግሞ በእሳት ለመቃጠል ይሰበሰባሉ። ታተ 68.7

ለተሰጣቸው ኃላፊነት ታማኝ የሆኑ የሰማይ ጠባቂዎች አሁንም መጠበቃቸውን ይቀጥላሉ። ትዕዛዛቱን ጠባቂዎች መቼ እንደሚገደሉ ጊዜውን የወሰነ አጠቃላይ አዋጅ ቢታወጅም፣ ጠላቶቻቸው ግን ይህንን አዋጅ ጊዜው ሳይደርስ ለመተግበርና የእግዚአብሔርን ልጆች ሕይወት ለማጥፋት ይሞክራሉ። ነገር ግን በእያንዳንዱ ታማኝ ነፍስ ዙሪያ የሰፈሩትን ኃያል ጠባቂዎች ማንም አልፎ ሊነካቸው አይችልም። አንዳንዶች ከከተማዎችና ከመንደሮች ይባረራሉ፤ ነገር ግን በእነርሱ ላይ የሚመዘዙት ሰይፎች ይሰበራሉ፣ እንደ ሳር ኃይል የለሽ ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ የጦር ሰዎች የሚመስሉ መላእክቶች ይከላከሉላቸዋል። ታተ 69.1

በዘመናት መካከል፣ ሕዝቡን ለማዳንና ለመታደግ በቅዱሳን መላእክቱ በኩል ሰርቶአል። የሰማይ አካላት በሰዎች ጉዳይ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ አላቸው። ልብሳቸው እንደ መብረቅ እያብረቀረቀ የተገለጹበት ጊዜ ነበር፤ እንደ አልፎ ሂያጅ መንገደኛም መስለው የቀረቡበት ጊዜ ነበር። መላእክት ለእግዚአብሔር ሰዎች በሰው አምሳልም የተገለጡበት ጊዜ ነበር። ልክ እንደ ደከማቸው በመሆን በቀትር ከዛፍ ስር አርፈው ነበር። ሰዎች ላቀረቡላቸው ጥሪ ምላሽ በመስጠት በቤታቸው ተስተናግደዋል። ግራ ለተጋቡ ተጓዦች እንደ መሪ በመሆን አገልግለዋል። በራሳቸው እጅ የመሰዊያውን እሳት አንድደዋል። የእስር ቤት በሮችን በመክፈት የጌታን ባሪያዎች ነጻ አውጥተዋል። የሰማይን ልብስ ለብሰው ከአዳኙ መቃብር ላይ ድንጋዩን ለማንከባለል ተገልጠው ነበር። ታተ 69.2

መላእክት በቅዱሳን ጉባዔ በሰው አምሳል ሆነው ብዙ ጊዜ ይገኛሉ፡፡ ተግባራቸውን ለመዘገብና የእግዚአብሔርን የትዕግስት ወሰን ማለፋቸውንና አለማለፋቸውን ለመወሰን ወደ ሰዶም እንደሄዱ ዛሬም በክፉዎች ጉባዔ መካከል ይገኛሉ፡፡ እግዚአብሔር ምህረት በማድረግ ደስ ይለዋል፡፡ ከልባቸው ለሚያመልኩት ለጥቂቶቹ ሲል መዓትን ከማምጣት የሚቆጠብና የብዙዎችንም ሰላም የሚያራዝም አምላክ ነው፡፡ ኃጢአተኞች በሕይወት ለመኖራቸው ባለውለታዎቻቸው የሚፌዙባቸውና የሚጨቁኗቸው ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑት ጥቂት ሰዎች መሆናቸውን አያስተውሉም፡፡ ታተ 69.3

የዚህ ዓለም ገዢዎች ባያውቁትም እንኳን፣ በየስብሰባዎቻቸው መላእክት ንግግሮቻቸውን ሲመሩ ኖረዋል፡፡ ሰብአዊ አይኖች አይተዋቸዋል፤ ጆሮዎቻቸውም ተማጽኖዎቻቸውን ሰምተዋቸዋል፡፡ ሰብአዊ አንደበቶች የእነርሱን ሃሳብ ተቃውመዋል፤ በምክሮቻቸውም ላይ አፊዘዋል፡፡ ሰብአዊ እጆች ጉዳት ሊያደርሱባቸው ሞክረዋል፡፡ በምክር ቤቶችና በፍርድ ቤት አደባባዮች እነዚህ ሰማያዊ መልእክተኞች ስለ ሰብአዊ ዘር ጠንቅቀው እንደሚያውቁ አሳይተዋል፡፡ ለተጠቁት ጥብቅናን በመቆም ብቃት ካላቸውና አንደበተ-ርቱዕ ከሆኑ ሌሎች ጠበቃዎች ይልቅ የተሻሉ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ ሊያደናቅፍና በሕዝቡም ላይ ታላቅ ስቃይ ሊያመጡ የሚችሉ አጀንዳዎችን አክሽፈዋል፤ የክፋት ሥራዎችንም ተቆጣጥረዋል፡፡ በአደጋና በጭንቅ ጊዜ «የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።» (መዝ. 34፡7)፡፡ ታተ 69.4

ከልብ በሆነ ናፍቆት የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚመጣውን ጌታቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ በማማው ላይ ያለው ጠባቂ «ሊነጋ ምን ያህል ቀረው?» ተብሎ ሲጠየቅ ያለ አንዳች ጥርጥር እንዲህ በማለት መለሰ፡- «ይነጋል፣ ግን ተመልሶ ይመሻል፤ መጠየቅ ከፈለጋችሁ፣ ጠይቁ፤ ነገር ግን ተመልሳችሁ ኑ» (ኢሳ. 21፡11-12)፡፡ በተራራ ጫፎች ላይ ባረፉ ደመናዎች ብርሃን ያንጸባርቃል፡፡ ብዙም ሳይቆይ የጌታ ክብር ይገለጣል፡፡ የጽድቅ ጸሐይ ልትወጣ ነው፡፡ ንጋትና ሌሊት በደጅ ናቸው፡፡ ለጻድቃን የዘላለማዊ ማለዳ የንጋት ብርሃን፣ ለኃጢአን ደግሞ ዘላለማዊው ሌሊት የሚጀምርበት፡፡ ታተ 69.5

በትግል ውስጥ ያሉት ጻድቃን ልመናቸውን ወደ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ፣ ከማይታየው መንፈሳዊ ዓለም የለያቸው መጋረጃ የተነሳ ይመስላል፡፡ ሰማያት በዘላለማዊ ቀን ንጋት ብርሃን ያበራሉ፡፡ እንደ መላእክት መዝሙር ባለ ጣፋጭ ዜማም የሚከተሉት ቃላት በጆሮዎች ይደመጣሉ፡- «በታማኝነታችሁ ጽኑ፡፡ እርዳታ እየመጣ ነው»፡፡ ሁሉን ቻዩ ድል አድራጊ ክርስቶስ ለዛሉት ወታደሮቹ የማይጠፋን የክብር አክሊል በእጆቹ ይዞአል፡፡ ከተከፈተው በር ድምጹ እንዲህ ሲል ይደመጣል፡- «እነሆ እኔ ከእናንተ ጋራ ነኝ፡፡ አትፍሩ፡፡ ሰቆቃችሁን አውቃለሁ፤ ጥልቅ ሃዘናችሁንም ተሸክሜአለሁ፡፡ ውጊያችሁ ከዚህ በፊት ከማላውቃቸው ጠላቶች ጋር አይደለም፡፡ ጦርነቱን በእናንተ ፈንታ ቀድሜያችሁ ተዋግቼዋለሁ፤ በስሜም ከአሸናፊዎች ትበልጣላችሁ፡፡» ታተ 69.6

ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ውዱ አዳኝ እርዳታ ይልክልናል። ወደ ሰማይ የሚወስደው መንገድ በእርሱ ዱካ ተቀድሶአል። የእኛን እግር ሊያቆስል የሚችል እሾህ ሁሉ የእርሱን እግር አቁስሎታል። እኛ እንድንሸከመው የተጠራነውን መስቀል ሁሉ እርሱ አስቀድሞ ተሸክሞታል። ጌታ ነፍሳችንን ለሰላም ለማዘጋጀት ግጭቶች እንዲከሰቱ ይፈቅዳል። የመከራው ጊዜ ለእግዚአብሔር ሕዝብ አስፈሪ የሆነ ጊዜ ነው። ነገር ግን ለእያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ ደግሞ ወደ ሰማይ የሚያመለክትና፣ በእምነትም የተስፋው ቀስተደመና እርሱን ከቦት የሚመለከትበት ጊዜ ነው። ታተ 69.7

«እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ የዘላለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል። የማጽናናችሁ እኔ ነኝ! የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ? ሰማያትንም የዘረጋው ምድርንም የመሠረተውን ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ረስተሃል፡፡ ያጠፋ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቍጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሃል፤ የአስጨናቂው ቍጣ የት አለ? ምርኮኛ ፈጥኖ ይፈታል አይሞትም ወደ ጕድጓድም አይወርድም፥ እንጀራም አይጐድልበትም። ሞገዱም እንዲተምም ባሕርን የማናውጥ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ሰማያትን እዘረጋ ዘንድ ምድርንም እመሠርት ዘንድ፥ ጽዮንንም። አንቺ ሕዝቤ ነሽ እል ዘንድ ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፥ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ።” (ኢሳ. 51፡11-16) ታተ 70.1

«ስለዚህም ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፥ ይህን ስሚ፤ ስለ ወገኑ የሚምዋገት አምላክሽ ጌታሽ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የሚያንገደግድን ጽዋ የቍጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። ‹ነፍስሽንም እንሻገር ዘንድ ዝቅ በዪ› በሚሉአት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ ጀርባሽንም ለሚሻገሩት እንደ መሬትና እንደ መንገድ አደረግሽላቸው።” (ኢሳ. 51፡21-23) ታተ 70.2

በዘመናት መካከል ወደ ታች ሲመለከቱ የኖሩት የእግዚአብሔር አይኖች፤ ምድራዊ ኃይላት በህዝቡ ላይ በሚነሱበት ጊዜ በሚፈጠሩት ችግሮች ላይ ያነጣጥራሉ። በምርኮ ተወስደው እንደነበሩት ግዞተኞች በረሃብና በሚደርስባቸው ጥቃት እንሞታለን የሚል ስጋት ሊገባቸው ይችላል። ነገር ግን በእስራኤል ፊት ቀይ ባህርን የከፈለው ቅዱስ ታላቅ ኃይሉን በመግለጽ ምርኮኝነታቸውንም ይገለብጣል «እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ።» (ሚል. 3፡17)። በዚህን ጊዜ የክርስቶስ ታማኝ ምስክሮች ደማቸው ቢፈስ እንደ ቀድሞ ሰማዕታት ደም ለእግዚአብሔር መከር ፍሬን ለመስጠት የሚዘራ ዘር አይሆንም። ለእምነት መቆማቸው ሌሎች እውነት ለመቀበል እንዲችሉ የሚያደርግ ምስክርነት አይሆንም። ምክንያቱም አመጸኛ ልቦች የምህረትን ሞገድ ባለማቋረጥ ተቋቁመው፣ መመለስ የማይችሉበት ነጥብ ላይ ደርሰው ነበርና። ጻድቃን በጠላቶቻቸው እጅ ተላልፈው ቢሰጡ፣ ለጨለማውም ገዢ ድል ይሆንለት ነበር። መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፡- «በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና።» (መዝ. 27፡5) ክርስቶስም እንዲህ ብሏል፡- «ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቍጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፣ እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፥ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።” (ኢሳ. 26፡20-21) የእርሱን ምጻት በትእግስት የተጠባበቁትና ስማቸውም በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉትን ሁሉ የሚገጥማቸው እጅግ የከበረ ነጻ መውጣት ይሆናል። ታተ 70.3