ታላቁ ተስፋ
የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ
ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ ከብርሃኑም የተነሳ ምድር በራች፡፡ በብርቱም ድምጽ፡- ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፣ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኩሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች . . . ከሰማይም ሌላ ድምጽ ሰማሁ እንዲህም ሲል፡- ሕዝቤ ሆይ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ» (ራዕይ 18፡1,2,4)፡፡ ታተ 56.1
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ልክ በራዕይ 14፡8 ላይ ሁለተኛው መልአክ እንደተናገረው የባቢሎን የውድቀት ጊዜ መድረሱን በድጋሚ የሚጠቁም ሲሆን መልእክቱ መሰበክ ከተጀመረበት ከ1844 ዓ.ም. የበጋ ወራት ጀምሮ የባቢሎን አካል ወደ ሆኑት ልዩ ልዩ ድርጅቶች ያሉትን ብልሽቶች (እርኩሰቶች) በተጨማሪ ይጠቅሳል፡፡ የሃይማኖቱ ዓለም አሰቃቂ ሁኔታ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ተገልጾአል፡፡ በእያንዳንዱ እውነት ለመቀበል አለመፈለግ (እውነትን የመናቅ) እርምጃ የሰዎች አእምሮ እየጨለመ ልቦቻቸውም በበለጠ እየደነደነ ይሄድና በመጨረሻ ካለማመን አለት ጋር ይጣበቃሉ፡፡ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ መናቅና ከአስርቱ ትዕዛዛት ውስጥ በአንዱ ላይ መሳለቅ ብቻ ሳይሆን ቀድሰው የሚጠብቁትን ሰዎች እስከ ማሳደድ ይደርሳሉ፡፡ በቃሉና በሕዝቡ ላይ በሚደረገው ፌዝና ቅሌት አማካይነት ክርስቶስ ይናቃል፡፡ የሙታን መናፍስት ህያውነት እምነትና ትምህርት በአብያተ-ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ሲያገኝ በሥጋዊው ልብ ላይ የተጣለው ማእቀብ ይነሳል በመሆኑም ሃይማኖተኝነት የኃጢአት መሸፈኛ ካባ ይሆናል፡፡ ታተ 56.2
«የሙታን መናፍስት ይገለጹልናል» የሚለው እምነት ለአታላይ መናፍስትና ለሰይጣን ትምህርት በር ይከፍታል፡፡ በዚህም አማካይነት የክፉ መላዕክት ተጽእኖ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ይታያል፡፡ በትንቢት ስለ ባቢሎን ሲገለጽ እንዲህ ተብሏል፡- «ኃጢአትዋ እስከሰማይ ድረስ ደርሶዋልና እግዚአብሔርም አመጻዋን አሰበ» (ራዕይ 18፡5)፡፡ ባቢሎን የበደሏን ሚዛን ስለሞላች ጥፋትም በእርሷ ላይ ሊደርስ ተቃርቧል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በባቢሎን ሰዎች አሉት፣ ከፍርዱ በፊትም እነዚህ ታማኞች የኃጢአትዋ ተካፋይ እንዳይሆኑና ከመቅሰፍትዋም እንዳይካፈሉ ከእርሷ ይወጡ ዘንድ መጠራት አለባቸው፡፡ ስለዚህም ከሰማይ በሚወርደው ከብርሃኑም የተነሳ ምድር የምታበራው የባቢሎንንም ኃጢአት በማሳወቅ በታላቅ ድምጽ የሚጮኸው መልአክ የዚህ ንቅናቄ (Movement) ምሳሌ ነው፡፡ ከመልእክቱም ጋር በማያያዝ እንዲህ የሚል ጥሪ ይሰማል፡ «ሕዝቤ ሆይ ከእርሷ ውጡ!» እነዚህ ጥሪዎች ከሶስተኛው መላእክት መልእክት ጋር አንድ ላይ በመሆን እንደ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መልእክት ሆነው በመሬት ለሚኖሩ ሁሉ ይሰጣሉ፡፡ ታተ 56.3
ዓለም በመጨረሻ የሚደርስበት ሁኔታ በጣም አስፈሪ ነው፡፡ በምድር ያሉ ስልጣናት የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመዋጋት ሕብረት ፈጥረው «ታላላቆችም፣ ታናናሾችም፣ ባለጸጎችም፣ ጌታዎችም፣ ድሆችም» (ራዕይ 18፡5) ሐሰተኛውን ሰንበት በማክበር የቤተክርስቲያኒቱን ባህልና ወግ መከተል እንዳለባቸው ይደነግጋሉ፡፡ ይህንን ድንጋጌ የማያከብሩ ሁሉ በሕግ ይቀጣሉ፡፡ በመጨረሻም «እነርሱ ሞት ይገባቸዋል» ተብሎ ይወሰናል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የፈጣሪ የእረፍት ቀን ሰንበት መከበር እንዳለበት የሚገልጸው የእግዚአብሔር ሕግ፣ ትእዛዙ እንዲከበር በመጠየቅ ትዕዛዙን በሚተላለፍ ሁሉ ላይ ቁጣ እንደሚወርድ ያስጠነቅቃል፡፡ በዚህም አኳኋን የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ የተቀመጠለትና ያም ሆኖ ግን የሰዎችን ትእዛዝ ለማክበር ሲል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በእግሩ የሚረግጥ ማንኛውም ሰው የአውሬውን ምልክት ይቀበላል፡- በእግዚአብሔር ፈንታ ይገዛለት ዘንድ ለመረጠው ስልጣን የታማኝነትን ምልክት ይቀበላል፡፡ ከሰማይ የመጣው ማስጠንቀቂያ እንዲህ ይላል፡- «ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩ ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ደግሞ በቁጣው ጽዋ ሳይቀላቀል ከተዘጋጀው የእግዚአብሔር ቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል» (ራዕይ 14፡9,10)፡፡ የእውነት ብርሃን ወደ አእምሮውና ወደ ህሊናው በር መጥቶ ለመግባት በሚማጸንበት ጊዜ አንድ ሰው እምቢ ብሎ ይህንን የተገለጠለትን እውነት ውድቅ እስካላደረገ ድረስ ማንም ሰው የእግዚአብሔር ቁጣ አይወርድበትም፡፡ ታተ 56.4
በጊዜው ወቅታዊ የሆነውን የተለየ የእውነት ብርሃን ለመስማት ፈጽሞ እድል አግኝተው የማያውቁ ብዙዎች አሉ፡፡ የአራተኛውን ትዕዛዝ መጠበቅ አስፈላጊነት በትክክለኛው ብርሃን ተገልፆላቸው አያውቅም፡፡ እያንዳንዱን ልብ የሚያነበውና የእያንዳንዱን ሰው አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሳበትን ምክንያት (Motivation) መመርመር የሚችለው አምላክ የእውነትን እውቀት ለማወቅ ፍላጎት እና ምኞት ያለውን ሰው በተጋድሎው ፍጻሜ ጊዜ ይታለል ዘንድ አይተወውም፡፡ ታተ 56.5
በምድር ባለስልጣናት የሚወጣው ድንጋጌ በሰዎች ላይ የደፈና ተጽእኖ በማድረግ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው አውቆ በማስተዋል ራሱ መወሰን እንዲችል በቂ ብርሃን ያገኛል፡፡ ሰንበት የታማኝነት መፈተኛ አብይ ሚዛን ይሆናል ምክንያቱም በተለየ መንገድ የተካደው እውነት እርሱ ነውና፡፡ በሰዎች ላይ የመጨረሻው መመዘኛ (ፈተና) በሚመጣበት ጊዜ እግዚአብሔርን በሚያገለግሉትና በማያገለግሉት መካከል መለያ መስመር ይደረጋል፡፡ ሐሰተኛውን ሰንበት ማክበር አራተኛውን የእግዚአብሔር ትዕዛዝ መቃረን ከመሆኑም በላይ እግዚአብሔርን ለሚቃወም ኃይል ታማኝነትን መግለጽና መገዛት ሲሆን የእግዚአብሔርን ሕግ በማክበር እውነተኛውን ሰንበት (ቅዳሜ) መጠበቅ ደግሞ ለፈጣሪ ታማኝ የመሆን ማስረጃ ነው፡፡ አንዱ ወገን ለምድራዊ ባለስልጣናት የመገዛቱን ምልክት በመቀበል የአውሬውን ምልክት ሲቀበል ሌላው ወገን ደግሞ ለመለኮታዊው ስልጣን የታማኝነትን ምልክት በመምረጥ የእግዚአብሔርን ማህተም ይቀበላል፡፡ ታተ 57.1
ከዚህ ቀደም የሦስተኛውን መልአክ መልእክት እውነት ለሕዝብ ያስተምሩ የነበሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እንደ አስደንጋጮች ተቆጥረዋል፡፡ «በአሜሪካ የሃይማኖት ጥላቻ እንደሚስፋፋ፣ ቤተክርስቲያንና መንግስት የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠበቁትን ለማሳደድ ሕብረት እንደሚፈጥሩ አስቀድመው የተናገሩትን ትንቢት እንደ ምክንያተ-ቢስና መሳለቂያ አድርገው ይወስዱባቸዋል፡፡ «ይህች ምድር (አሜሪካ) አሁን ከያዘቸው አቋም ፈቀቅ አትልም፡፡ ማለትም ምንም ጊዜ ቢሆን የሃይማኖት ነጻነት አስጠባቂ ናት፣ ትሆናለችም» ብለው በድፍረት እስከመናገር ደርሰዋል፡፡ ነገር ግን እሁድን የማክበር (የመጠበቅ) ግዴታ ጥያቄ በሰፊው ቅስቀሳ ሲደረግ ለረጅም ጊዜ አጠራጣሪና የማይታመን ሆኖ የቆየው ሁኔታ እየቀረበ ሲመጣ ይታያል፡፡ የሦስተኛው መልአክ መልእክትም ከዚህ ቀደም ሊኖረው ያልቻለውን ውጤት ያመጣል፡፡ ታተ 57.2
በእያንዳንዱ ትውልድ፤ በዓለምም ሆነ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን ኃጢአት ይገልጽ ዘንድ እግዚአብሔር አገልጋዮች ልኳል፡፡ ሰዎች ግን የለሰለሱ ቃላትን ብቻ ሊሰሙ ይፈልጋሉ በመሆኑም ያልተኳኳለውና ያልደበዘዘው እውነት ተቀባይነት የለውም፡፡ አያሌ የሃይማኖት ማሻሻል ንቅናቄ አድራጊዎች (የተሃድሶ እንቅስቃሴ ሰዎች) አገልግሎታቸውን ሲጀምሩ የቤተክርስቲያንንና የሕዝቡን ኃጢአት ለማረም በታላቅ ጥንቃቄና ለስለስ ባለ መልኩ ነበር የሚናገሩት፡፡ በንፁህ የክርስትና ሕይወት ምሳሌ በመሆን ሰዎችን ወደ እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመመለስ ተስፋ አድርገው ነበር ነገር ግን በነብዩ ኤልያስ እንደሆነው ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በመውረድ የክፉውን ንጉሥና የከሃዲውን ህዝብ ኃጢአት እንዲገልጽ እንዳነቃነቀው የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱ ላይ መጣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግልፅ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትንና ከዚህ በፊት ለማቅረብ ሲያንገራግሩ የቆዩትን ትምህርት ከማስተማር ሊቆጠቡ አልቻሉም፡፡ እውነትን በድፍረት በመስበክ ለአደጋ የተጋለጡትን ነፍሳት ማስጠንቀቅ ጀመሩ፡፡ ሊደርስባቸው የሚችለውን መዘዝ ሳይፈሩ ጌታ የሰጣቸውን ቃላት ተናገሩ ሕዝቡም ማስጠንቀቂያውን ይሰሙ ዘንድ ተገደዱ፡፡ ታተ 57.3
በዚህ መንገድም እንዲሁ የሦስተኛው መልአክ መልእክት ይታወጃል፡፡ መልዕክቱ በታላቅ ኃይል የሚሰራጭበት ቀን በሚደርስበት ጊዜ ጌታ በትሁታን መሳሪያዎቹ እራሳቸውን ለአገልግሎት ቀድሰው በሚሰጡ ሰዎች አእምሮ ይሰራል፡፡ አገልጋዮቹ ለሥራ ብቁ የሚሆኑት በሳይንሳዊ ተቋሞች ትምህርት ሳይሆን ይበልጡን በእግዚአብሔር መንፈስ በመቀባታቸው ነው፡፡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች በመንፈስ ቅዱስ ቅባት እንጂ በከፍተኛ ትምህርት ቤት ተቋማት በሚያገኙት ስልጠና አይደለም ለአገልግሎት ብቁ የሚሆኑት፡፡ የእምነትና የፀሎት ሰዎች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ቃላት ለማሰራጨት በተቀደሰ ልባዊ ስሜት (ቅናት) ይነሳሳሉ፡፡ በዚያን ጊዜ የባቢሎን ኃጢአት ይገለጣል በመንግስት ባለስልጣናት በኩል የሚደረገው የቤተክርስቲያን ባህልን የመከተል የሕግ አስገዳጅነት ውጤት፣ የሙታን መናፍስት ሕያውነት እምነት ድፍረታዊ ትምህርት፣ በስውርና በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው ጳጳሳዊ ኃይል እነዚህ ሁሉ በገሃድ ይጋለጣሉ፡፡ በእነዚህ አስፈላጊ ማስጠንቀቂያዎች አማካኝነት ሰዎች ይቀሰቀሳሉ፡፡ እንደዚህ ያሉትን ቃላት ሰምተው የማያውቁ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ያዳምጣሉ፡፡ በስህተቷና በኃጢአትዋ ምክንያት ከሰማይ የተላከላትን እውነት ባለመቀበሏ የወደቀችው ባቢሎን ያቺው ቤተክርስቲያን መሆኗን የሚያመላክተውን ቃላት በመገረም ያዳምጣሉ፡፡ ሰዎቹም ወደ ቀድሞዎቹ መምህራኖቻቸው በመሄድ «እነዚህ ነገሮች ልክ ናቸውን?» ብለው ከልብ ሲጠይቁ መምህራኖቻቸው የሰዎቹን ፍርሃት ለማስታገስና የነቃውን ህሊና ዝም ለማሰኘት ተረትንና ለሥጋ ደስ የሚል ትንቢት ይነግሯቸዋል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ በሰብአዊ ስልጣናት መርካትን ስላልወደዱና «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» የሚለውን ለማወቅ አጥብቀው ሲጠይቁና ልክ ከዚህ ቀደም ፈሪሳውያን ስልጣናቸው ጥርጣሬ ውስጥ በመግባቱ ምክንያት በቁጣ ገንፍለው እንደነበር እነዚህ ወግ አጥባቂ ካህናትም «እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችና መልእክቶች ከሰይጣን የመጡ ናቸው» በማለት ይመልሳሉ፡፡ ከዚያም የኃጢአት ወዳጆች የሆኑትን ብዙሃን ይህንን መልእክት የሚያሰራጩትን ምእመናን እንዲያወግዟቸውና እንዲያሳድዷቸው ይቀሰቅሷቸዋል፡፡ ተጋድሎው ወደ አዳዲስ መስኮች እየተስፋፋ ሲሄድና የሰዎችም ልብ (ሃሳብ) በእግር ወደ ተረገጠው የእግዚአብሔር ሕግ ሲያመራ ሰይጣን ይቆጣል (ይሸበራል)፡፡ በመልእክቱ ውስጥ ያለው ኃይል መልእክቱን የሚቃወሙትን ብቻ ያስቆጣል፡፡ መንፈሳዊ መሪዎች (ካህናቶች) በመንገዶቻቸው ላይ ብርሃን እንዳይበራ ለማድረግ እጅግ ከሰው አቅም በላይ በሆነ ኃይል ይጥራሉ፡፡ በተቻላቸው መንገድ የዚህን ጠቃሚ ጥያቄ ውይይት በትእዛዛቸው ለማጥፋት ይጥራሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ጠንካራ የሆነውን የመንግስት ኃይል ጉዳይዋን እንዲያስፈጽምላት ትጠይቃለች (ጥሪ ታቀርባለች)፣ በዚህ ሥራም የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን (ሉተራንስ) ይተባበራሉ፡፡ እሁድ ይከበር ዘንድ ግዳጅ እንዲወጣ በመጣር ላይ የሚገኘው እንቅስቃሴ ይበልጥ ጉልህና ድፍረታዊ እየሆነ ሲመጣ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በሚጠብቁት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ጥሪ ይተላለፋል፡፡ ታተ 57.4
የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጠብቁት በገንዘብ ወይም በእስር እንደሚቀጡ በማስጠንቀቅ ያስፈራሯቸዋል፡፡ ለአንዳንዶቹ ደግሞ እምነታቸውን ከተው ስልጣንን፣ ስጦታና ጥቅምን እንደሚያገኙ ቃል ይገቡላቸዋል፡፡ የእነዚህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች የማይለወጥ መልስ ግን «ስህተታችንን በእግዚአብሔር ቃል ተደግፋችሁ አሳዩን» የሚል ይሆናል፡፡ ይህ አባባል ማርቲን ሉተር በተመሳሳይ ሁኔታ በነበረ ጊዜ ካቀረበው ጥያቄ ጋር አንድ ነው፡፡ ተወንጅለው በፍርድ ቤት የቀረቡት ሰዎች ስለ እውነት የማያወላውል ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ እነርሱን የሚያደምጡ አንዳንዶችም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሙሉ ለመጠበቅ አቋም ይወስዳሉ፡፡ በመሆኑም እውነትን በሌላ መንገድ ለማወቅ የማይችሉቱ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች የእውነት ብርሃን ይበራላቸዋል፡፡ ታተ 58.1
በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል በቅን መታዘዝ እንደ አመጽ ይታያል፡፡ ልባቸው በሰይጣን ስለታወረ ወላጆች በጌታ ቃል በሚያምነው በገዛ ልጃቸው ላይ የጭከና ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ ጌቶች የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚጠብቁትን አገልጋዮቻቸውን ይጨቁናሉ|፣ ፍቅርም ትቀዘቅዛለች፡፡ ልጆች የወራሽነት መብታቸውን ተገፈው ከቤታቸው ይባረራሉ፡፡ የጳውሎስ ትንቢት ቃል በቃል ይፈጸማል «በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ» (2ኛ ጢሞ. 3፡12)፡፡ ስለ እውነት የቆሙት ክርስትያኖች እሁድን በሰንበትነት ለማክበር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሲገልጹ አንዳንዶቹ ወደ ወህኒ ቤት ይከተታሉ፣ ሌሎች ደግሞ እንደ ባሪያዎች ይቆጠራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ይፈጸማል ብሎ ለማመን ያስቸግር ይሆናል ነገር ግን ይህ ሁሉ እንዳይሆን ለጊዜው የሚያግደው የእግዚአብሔር መንፈስ ከሰው ሁሉ በሚወሰድበትና ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ በሚጠላው በሰይጣን ቁጥጥር ስር ሲሆን እንግዳ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ፍቅር ከሰዎች ልብ ሲርቁ የሰው ልብ ጨካኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ማእበሉ እየተቃረበ ሲመጣ «በሶስቱ መላእክት መልእክት እናምናለን» ብለው የተናገሩት፣ ነገር ግን ለእውነት በመታዘዝ ያልተቀደሱት ክርስትያኖች አቋማቸውን ትተው ከተቃራኒው (በተቃዋሚው) ወገን ይሰለፋሉ ከዓለም ጋር አንድ በመሆንና ከአለማዊ መንፈስ ጋር በመተባበር ነገሮችን በተመሳሳይ ብርሃን ይመለከታሉ፡፡ ፈተናም ሲመጣባቸው ቀላሉንና በሰዎች ሁሉ የተወደደውን ጎን ይመርጣሉ፡፡ ታተ 58.2
መልካም ስምና ተውህቦ ያላቸው በአንድ ወቅት በእውነት ሐሴት ያደርጉ የነበሩ ሰዎች ኃይላቸውን ነፍሳትን በማታለልና በተሳሳተ ጎዳና በመምራት ሥራ ላይ ያውሉታል፡፡ የቀድሞ ወንድሞቻቸውም ብርቱ ጠላቶች ይሆናሉ፡፡ ሰንበትን የሚጠብቁ ምእመናን በእምነታቸው ምክንያት በፍርድ ፊት መልስ ለመስጠት በሚቀርቡበት ጊዜ የእነርሱን ጉዳይ በተመለከተ አሳሳች ነገር በማቅረብ እና በመወንጀል፣ የሀሰት ዘገባና ትክክለኛ ያልሆነ ሪፖርት በማቅረብ ገዢዎች እንዲቃወሟቸው የሚያደርጉ የሰይጣን ወኪሎች እነዚሁ ከሃዲያን ናቸው፡፡ ታተ 58.3
በዚህ የስደት ጊዜ የጌታ አገልጋዮች እምነት ይፈተናል፡፡ እግዚአብሔርንና ቃሉን በመመልከት ብቻ ማስጠንቀቂያውን በታማኝነት አስተላልፈዋል (አሰራጭተዋል)፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ልባቸውን በማነሳሳት እንዲመሰክሩ አደፋፍሮአቸዋል፡፡ በተደቀደሰ ቅንአት ተነሳስተውና የእግዚአብሔር መንፈስ በሰጣቸው ጠንካራ ኃይል ተደግፈው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ቃል ለሕዝብ በመናገራቸው የሚከተለውን መዘዝ ሳያስቡ ግዴታቸውን ተወጡ፡፡ እነርሱ ስለምድራዊ ጥቅማቸው ዝናቸውም ሆነ ሕይወታቸው አደጋ ይደርስበታል ብለው አላሰቡም፡፡ ይሁንና የተቃውሞና የዘለፋ ማዕበል በእነርሱ ላይ በሚነሳበት ጊዜ አንዳንዶቹ ከድንጋጤ የተነሳ «የቃላችን ውጤት ይህ መሆኑን አስቀድመን ብናውቅ ኖሮ ባንናገር ይሻለን ነበር» ብለው ለመናገር የተዘጋጁ ይሆናሉ፡፡ እነርሱም በችግር ይከበባሉ፡፡ ሰይጣንም በብርቱ ፈተና ያስጨንቃቸዋል፡፡ የጀመሩትን ሥራ መፈፀም ከአቅማቸው በላይ የሆነና ለመፈጸም የሚያቸግርም ይመስላቸዋል፡፡ የግድያ ማስጠንቀቂያም ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት አነሳስቷቸው የነበረው ጽኑዕ የፍላጎት ስሜትም ይርቃቸዋል፡፡ ቢሆንም ወደኋላ አይመለሱም፡፡ ከዚያም ያለ አንዳች አጋዥ ብቻቸውን መሆናቸው ሲሰማቸው ኃያሉ አምላክ ብርታቱን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እርሱ ይሸሻሉ፡፡ የተናገሯቸው ቃላት ሁሉ ማስጠንቀቂያውን እንዲያስተላልፉ ያዘዛቸው የእግዚአብሔር እንጂ የእነርሱ ቃላት አለመሆናቸውን ያስታውሳሉ፡፡ እግዚአብሔር በልባቸው እውነትን ዘርቶአልና ይህንን እውነት በግልጽ ከማሰራጨት (ከመናገር) ሊቆጠቡ አልቻሉም፡፡ ታተ 58.4
ባለፉት ዘመናትም ሁሉ ተመሳሳይ ፈተናዎች በእግዚአብሔር ሰዎች ላይ ደርሶባቸው ነበር፡፡ ዋይክሊፍ፣ ሃስ፣ ሉተር፣ ሊነደል፣ ባክስተር፣ ዌይስሊ እነዚህ ሁሉ እያንዳንዱ የሃይማኖት ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ መመዘንና መፈተን እንዳለበት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሚኮንነውን ነገር ሁሉ እንደማያደርጉ አጥብቀው ተናግረዋል (አሳስበዋል)፡፡ በእነዚህ ሰዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ስደት ደርሶባቸዋል፡፡ ሆኖም እነርሱ እውነትን ከመናገር አላረፉም፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ የተለያዩ ክፍለ ጊዜያት ወቅት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልዩ እውነቶች ጎልተው በገሃድ ይገለጡ ነበር፡፡ እነዚህም እውነቶች በዚያን ጊዜ ለነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ጠቃሚ የነበሩ ናቸው፡፡ በዘመኑም ይገለጥ የነበረው እያንዳንዱ አዲስ የእውነት ብርሃን በጥላቻ እና በቅራኔ መንገድ ነበር ያለፈው፡፡ በዚህ አዲስ የእውነት ብርሃን የተባረኩ ሁሉ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት ጌታ ለሕዝቡ ከቃሉ ልዩነት እውነትን ይገልጣል፡፡ ማነው ደፍሮ ይህንን እውነት አላውጅም የሚል? ለዓለም የመጨረሻውን የምህረት ግብዣ እንዲያሰራጩ እግዚአብሔር አገልጋዮችን ያዛል፡፡ አገልጋዮቹም ከዚህ ዓለም በሞት እስካልተለዩ ድረስ በዝምታ ለመቆየት አይችሉም፡፡ የክርስቶስ አምባሳደሮች ሁኔታው ስለሚያስከትለው ውጤት ምንም አያገባቸውም፡፡ እነርሱ ግዴታቸውን መፈጸምና ውጤቱን ለእግዚአብሔር መተው ብቻ ነው ያለባቸው፡፡ ታተ 59.1
ፈተናውና ተቃውሞው እየበረታ በሚመጣበት ጊዜ ህውከቱን ያመጡት እነርሱ እንደሆኑ መስሎ ስለታያቸው የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንደገና ይታወካሉ፡፡ ነገር ግን ሕሊናቸውና የእግዚአብሔር ቃል እነርሱ የወሰዱት እርምጃ ትክክለኛ መሆኑን ያረጋግጥላቸዋል፡፡ ፈተናው ቢቀጥልም መከራውን ለመሸከም የበረቱ ይሆናሉ፡፡ ውጊያውም እየተባባሰና እየጠነከረ ቢሄድም የእግዚአብሔር አገልጋዮች እምነት ግን የበለጠ እያየለ ይሄዳል፡፡ የምስክርነታቸውም ቃል የሚከተለው ነው፡- «ዓለም እንድትወድደን ብለን ‹ይህ አስፈላጊ ነው ይህ ደግሞ አያስፈልግም› እያልን ሕጉን በመከፋፈል የእግዚአብሔርን ቃል ለመለወጥ አንደፍርም፡፡ የምናገለግለው አምላክ ሊያድነን ይችላል፡፡ ክርስቶስ ምድራዊ ኃይላትን ድል ነስቷል፣ ታዲያ እኛ ይህችን የተሸነፈችውን ዓለም እንፈራታለን?»፡፡ ታተ 59.2
ሰይጣን በሕይወት እስካለና ክርስትና አብይ ኃይል እስካለው ድረስ ስደት በተለያየ መልኩ መገለጹ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ማንም ሰው ቢሆን በእርሱ ላይ ተሰልፈው የተነሱት የጨለማ ሰራዊት ተቋውሞ ሳይገጥመው እግዚአብሔርን ማገልገል አይችልም፡፡ ክፉ መላዕክት ምርኮኞቻቸው እንዳይነጠቁ በመስጋት የእግዚአብሔርን አገልጋይ ያስጨንቁታል፡፡ ክፉ ሰዎችም ከክፉ መላዕክት ጋር በመተባበር የእግዚአብሔር አገልጋይ ከጌታው ይለያይ ዘንድ እያባበሉ መፈተን ይሻሉ፡፡ ይህም ጥረታቸው ፍሬያማ ሳሆን በሚቀርበት ጊዜ ሕሊናን በሚያስገድድ ኃይል ይጠቀማሉ፡፡ ታተ 59.3
ነገር ግን ኢየሱስ በሰማይ ቤተ መቅደስ ሆኖ ሰዎችን በማማለድ ሥራው ላይ እስካለ ድረስ የፈለጉትን እንዳያደርጉ የሚከለክላቸው የመንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ በገዢዎችና በሰዎች ላይ ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ አሁንም ቢሆን የአገርን ሕግ እስከተወሰነ ደረጃ ይቆጣጠራል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ የዓለም ሁኔታ ከአሁን እጅግ የባሰ ይሆን ነበር፡፡ ብዙዎቹ መሪዎቻችን (ገዢዎቻችን) የሰይጣን ጽኑ ወኪል ቢሆኑም እግዚአብሔር ከመንግስታት መሪዎች ውስጥ የራሱ የሆኑ መሳሪያዎች አሉት፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ በብርቱ የሚያደናቅፉ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ ጠላት ባሮቹን ያነሳሳል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ የመንግስት ባለ ሥልጣናት በቅዱሳን መላዕክት ድጋፍ አማካኝነት የጠላት አገልጋዮች መልስ መስጠት እሰኪሳናቸው ድረስ ሃሳባቸውን ይቃወማሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ ጥቂት ሰዎች የክፉውን «የኮረንቲ ኃይል» ይገታሉ፡፡ ታተ 59.4
የሶስቱ መላእክት መልእክት ሥራውን ያከናውን ዘንድ የእነዚህ የእውነት ጠላቶች ተቃውሞ ይታገዳል፡፡ የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ በሚሰራጭበት ጊዜ እግዚአብሔር የእርሱ መሳሪያዎች የሆኑት እነዚህ ባለስልጣናት መልእክቱን እንዲያስተውሉት ያደርጋል፡፡ አንዳንዶቹም ማስጠንቀቂያውን ተቀብለው በመከራ ጊዜም ከእግዚአብሔር ወገኖች ጎን ይቆማሉ፡፡ ታተ 59.5
የሶስተኛውን መልእክት የሚያስተላልፈውን መልአክ የሚከተለው ሌላው መልአክ መላዋን ምድር በክብሩ ብርሃን ያበራል (ራዕይ 18)፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ከጽንፍ እስከ አጽናፍ የሚዳረስ ዓለምአቀፍ ሥራና፣ ታይቶም ያልታወቀ ኃይል ተተንብዮአል፡፡ እ.አ.አ. ከ1840-1844 የነበረው (የተካሄደው) የምጽአት እንቅስቃሴ (አደቬንት ሙቭመንት) የእግዚአብሔርን ኃይልና ስልጣን ክብር በተሞላበት ሁኔታ የገለጸ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ የመጀመሪያው መልአክ መልእክት በዓለም ላይ ባሉት የሚሽነሪ ማእከላት ሁሉ ደርሶ ነበር፡፡ በአንዳንድ አገሮች እንዲውም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የሃይማኖት ተሃድሶ ንቅናቄ በየትኛውም ሃገር ታይቶ ከነበረው ሃይማኖታዊ ፍላጎት እጅግ የበለጠ ፍላጎት ታይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በሦስተኛው መልአክ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ጊዜ የሚነሳሳው ኃያል እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ሁሉ የሚበልጥ ይሆናል፡፡ ታተ 59.6
ይህ እንቅስቃሴ በጴንጤ ቆስጤ ከነበረው ጋር ይመሳሰላል፡፡ ዘሩ ይበቅል ዘንድ ያኔ በሐዋሪያት ዘመን «የፊተኛው ዝናብ» በመንፈስ ቅዱስ መልክ እንደተሰጠ እንዲሁም ደግሞ መከሩ ለአጨዳ ይደርስ ዘንድ «የኋለኛው ዝናብ» በመጨረሻው ዘመን ይሰጣል፡፡ «እንወቅ፣ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን እንደ ዝናብም ምድርን እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል» (ሆሴዕ 6፡3) «አምላካችሁ እግዚአብሔር የፊተኛውን ዝናብ በጽድቅ ሰጥቶአችኋልና እንደ ቀድሞውም የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦላችኋልና በእርሱ ደስ ይበላችሁ» (ኢዩኤል 2፡23) «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሀሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ ጎበዞቻችሁም ህልም ያልማሉ. . . የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል፡፡ (ሐዋ 2፡17,21) ታተ 59.7
የእግዚአብሔር ኃይል የሚገለጽበት የመጨረሻው ታላቅ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ ከነበረው በጥቂትም ቢሆን አያንስም፡፡ በሐዋሪያት ዘመን በዘነበው «ፊተኛው ዝናብ» ወቅት የተፈጸሙት ትንቢቶች በመደምደሚያው ጊዜ በሚዘንበው «በኋለኛው ዝናብ» ወቅትም ይፈጸማሉ፡፡ ሐዋሪያው ጴጥሮስ «እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሃ ግቡ፣ ተመለሱም» ብሎ በተናገረበት ጊዜ በሃሳብ ህሊናው አርቆ ይመለከተው የነበረው «የመፅናናት ዘመን» ይህ ነው (ሐዋ 3፡19-20)፡፡ ታተ 60.1
የእግዚአብሔር አገልጋዮች ፊቶቻቸው ብሩክ በሆነ ቅድስና እያንፀባረቁ ከሰማይ የመጣውን መልዕክት ለማዳረስ ከስፍራ ስፍራ ይጣደፋሉ፡፡ በሺህ በሚቆጠሩ አንደበቶች አማካኝነት ማስጠንቀቂያው በመላው ዓለም ይሰራጫል፡፡ ተአምራቶች ይታያሉ፣ በሽተኞች ይድናሉ፣ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮችም ምእመናንን ይከተሏቸዋል፡፡ ሰይጣንም እንዲሁ የሃሰት ተአምራትን ያደርጋል፡፡ እንዲያውም «በሰዎች ፊት ከሰማይ ወደ ምድር እሳት እስከሚያወርድ ድረስ» ተአምር ይሰራል፡፡ (ራዕይ 13፡13)፡፡ በዚህም አማካኝነት በምድር የሚኖሩ ሁሉ አቋም እንዲወስዱ ይገደዳሉ፡፡ ታተ 60.2
መልእክቱ የሚሰራጨው በክርክር ሳይሆን ጥልቅ በሆነው የመንፈስ ቅዱስ የማሳመን ሥራ ነው፡፡ እነሆ ዘሩ ተዘርቷል፣ አሁን በቅሎ ፍሬ መስጠት ይኖርበታል፡፡ በወንጌል መልእክተኞች የተሰራጩት የጽሁፍ ሥራዎች በአንባቢዎቻቸው ላይ ተፅእኖ አሳድረዋል፡፡ ቢሆንም በሰሙት መልእክቶች ልባቸው ተነክቶ የነበረ ብዙዎች እውነትን ሙሉ በሙሉ እንዳያስተውሉ ወይም ደግሞ የመታዘዘን ፍሬ እንዳያፈሩ ተሰናከሉ፡፡ አሁን ግን ጨረሮች በየቦታው ሰንጥቀው ይገባሉ እውነት ንፁህ ሆና ትታያለች ታማኞች የእግዚአብሔር ልጆችም አስረዋቸው ከነበሩት ነገሮች ሁሉ ይላቀቃሉ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ የቤተሰብ ግንኙነቶችም ሆነ የቤተክርስቲያን ዝምድናዎች በእነርሱ ላይ ማዕቀብ ለማድረግ ኃይል የላቸውም፡፡ እውነት ከሁሉም ይበልጥ የላቀ ዋጋ ያላት ነች፡፡ እውነትን ለመቃወም የተባበሩትን ኃያላን ቅንጅት ቢመለከቱም ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ሰዎች ከእግዚአብሔር አምላክ ጎን ይቆማሉ፡፡ ታተ 60.3