ታላቁ ተስፋ

13/15

የእግዚአብሔር ሕዝብ ነጻ መውጣት

የእግዚአብሔርን ሕግ በማክበር ታማኝ ከሆኑት ላይ መንግስታት የደነገጓቸው የሕግ ከለላዎች በሚነሱበት ጊዜ፣ በተለያዩ አገሮች በተመሳሳይ ሁኔታ እነርሱን የማጥፋት እንቅስቃሴ ይጀመራል። በአዋጁ የተደነገገው የጊዜ ገደብ ሲቃረብ አሕዛብ እነዚህን ጥቂት ታማኝ ቅሬታዎች ለመግደል ይወስናሉ። ለየት ያለ አቋም የያዙትን ሰዎች ድምጽ በአንድ ሌሊት ጸጥ ለማሰኘትና እነርሱን ለዘላለም ለማስወገድ ይወሰናል። ታተ 71.1

የእግዚአብሔር ህዝቦች፣ ግማሾቹ በወህኒ ቤት፣ ሌሎቹም በዋሻ፣ በተራሮች እና በጫካ ውስጥ በስደት ላይ ሆነው፤ ደግመው ደጋግመው የመለኮት ጥበቃ እንዲላክላቸው ሲማጸኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች በክፉ የመላዕክት ሠራዊት ተመርተው የሞትን አዋጅ ለማስፈጸም ይዘጋጃሉ። በዚህ እጅግ በጣም አደገኛ በሆነበት ሰዓት፣የእስራኤል አምላክ ለእርሱ የተመረጡትን ለመታደግ ጣልቃ ይገባል። ጌታ እንዲህ ይላል፥- «ዝማሬ በተቀደሰች የዐውደ ዓመት ሌሊት እንደሚሆን ዝማሬ ይሆንላችኋል፤ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ እስራኤል አምባ ይመጣ ዘንድ እንቢልታ ይዞ እንደሚሄድ ሰው የልብ ደስታ ይሆንላችኋል። እግዚአብሔርም ክቡር ድምፁን ያሰማል፥ የክንዱንም መውረድ በሚነድድ ቍጣውና በምትበላ እሳት ነበልባል በዐውሎ ነፋስም በወጨፎም በበረዶ ጠጠርም ይገልጣል»። (ኢሳ. 30፡29 እና 30) ታተ 71.2

በዚያን ጊዜ ከድቅድቅ ጨለማ የባሰ ጽልመት ምድርን ይከባታል፡፡ ክፉ ሰዎች የድል ነሽነት ጩኸት፣ የማላገጥ እና የመራገም መዓት እያወረዱ በሰለባዎቻቸው ላይ ለመውደቅ ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ፣ ከእግዚአብሔር ዙፋን ክብር የሚመነጭ የቀስተ ዳመና ብርሃን ከሰማይ ጀምሮ የሚፀልዩትን ሰዎች ዙሪያ ይከባቸዋል። በዚያን ጊዜ በቁጣ የተሞሉት አህዛብ በቅፅበት ፀጥ አሉ። የማላገጥ ጩኸታቸው በአንዴ ሞተ። ለመግደል የነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ተረሳ። በፍርኃት ተውጠው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ምልክት እያዩ በሚያንጸባርቀው ልዩ ብርሃን ለመከለል ይመኛሉ። ታተ 71.3

«ወደ ላይ ተመልከቱ!» የሚል በዝማሬ የተሞላ ግልጽ ድምጽ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጆሮ ተሰማ፡፡ ወደ ሰማይ ቀና ብለው ሲመለከቱ የቃል ኪዳኑን ቀስተ ዳመና አዩ ። ያ ሰማይን የጋረደው ጽልመት የተሞላው ጥቁር የቁጣ ዳመና ተወገደ፥ ከዚያም ልክ እንደ እስጢፋኖስ በጽናት ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሲመለከቱ፣ የእግዚአብሔር ክብር እና የሰው ልጅ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አዩት። በመለኮታዊነቱ ውስጥ የእርሱን ትህትና ተመለከቱ፥ ከአፉም ከወጣው ቃል በአባቱ እና በቅዱሳን መላዕክቱ ፊት ያቀረበውን ጥያቄ ያዳምጣሉ፥ እንዲህ ሲል፡- «የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ፣ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱም ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ ጻድቅ አባት ሆይ» (ዮሐንስ 17፡24):: በድጋሚ በሚያምር ሙዚቃ እና ድል ነሺነት ዜማ ሌላ ድምጽ ተሰማ፣ እንዲህ የሚል፡- «እነሆ ቅዱስ እና ትሁታን እንዲሁም ያለ ነቀፋ ሆነው መጡ፣ የትዕግስቴን ቃል ጠብቀዋል እና ከመላዕክት ጋር ይራመዳሉ፡፡» በእምነታቸው ሳይናወጡ ሲጠብቁ የነበሩት ፃድቃን ከድንጋጤ የተነሳ የቀላው ከንፈራቸው እየተነቀጠቀጠ ድልን ከፍ አድርገው አወጁ። ታተ 71.4

እግዚአብሔር ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት ኃይሉን የሚገልጸው በእኩለ ሌሊት ላይ ነው። ከዚያ በመቀጠልም ጸሐይ በሙሉ ኃይሏ ለመብራት ብቅ ትላለች። ድንቅ ምልክቶች እና ተዓምራት ተከታትለው ይታያሉ። ጻድቃን ነጻ በመውጣታቸው እውነታ ምክንያት ደስታ እና ተድላ ሲያገኙ፤ ኃጢአተኞች በድንጋጤ እና በመደነቅ ተሞልተው ክስተቱን ይመለከታሉ። ተፈጥሮ ሁሉ ከተለመደው ሥርዓት ውጪ የሆነ ይመስላል። ወንዞች መፍሰስ አቆሙ፥ ጥቁር እና ከባድ ዳመናዎች እርስ በርሳቸው ተጋጩ፣ በዚህ በተቆጣ ሰማይ መካከል አንድ መግለጽ በሚያዳግት ሞገስ የተሞላ ብርሃን ታየ፣ ከዚያም ልክ እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ድምጽ የሚመስለው የእግዚአብሔር ድምጽ «ተፈጸመ» ሲል ተሰማ። (ራዕ. 16፡17) ታተ 71.5

ይህም ድምጽ ሰማይንና ምድርን አንቀጠቀጠ። ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ «ትልቅም የመሬት መናወጥ ሆነ ሰውም በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናወጥ ከቶ አልነበረም፣ ከሁሉ በለጠ» (ራዕ. 17 እና 18):: ሰማያት አንዴ የሚከፈቱ አንዴ ደግሞ የሚዘጉ ይመስላሉ። ከእግዚአብሔር ዙፋን የሚመነጨው ክብር ሰማዩን ሰንጥቆ ብልጭ አለ። ልክ በንፋስ እንደሚወዛወዝ ዛፍ ተራሮች ተንቀጠቀጡ፣ የተሰነጣጠቁ አለቶች በየአቅጣጫው ተፈናጠሩ። የሚያጓራ ሃይለኛ የነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ። ባህር በታላቅ ቁጣ ተተራመሰ። ሃይለኛ የአውሎ ንፋስ ድምጽ ልክ ለጥፋት ተልዕኮ እንደተሰማሩ የርኩሳን መናፍስት ጩኸቱን አሰማ። ምድር እንደ ባህር ሞገድ ወዲያና ወዲህ፣ ወደላይና ወደታች አለች። ምድርም ተፈረካከሰች። የምድር መሰረት የተናጋ እና ቦታውን የለቀቀ ይመስላል። ተራሮች ሰጠሙ። መኖሪያ የነበሩ ደሴቶች ተሰወሩ። የሶዶምን ፈለግ የተከተሉ ወደቦች ሁሉ በተቆጣው ውኃ ተዋጡ። ታላቂቱ ባቢሎን «የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ታሰበች» «በሚዛን አንድ ታላንት በሚያክል ታላላቅ በረዶዎች» የማጥፋት ሥራቸውን ይሰራሉ። (ራዕ. 19 እና 21) በትዕቢት ተሞልተው የነበሩ ከተሞች ተደመሰሱ። የምድር ታላላቅ ሰዎች ለራሳቸው ክብር ብለው ሃብታቸውን ያፈሰሱባቸው የሚያማምሩ የነግስታት ቤተ መንግሥቶች አይኖቻቸው እያዩ ፈራረሱ። የእስር ቤቶች ግንቦች ፈራረሱ፥ በእምነታቸው ምክንያት በዚያ ታስረው የነበሩት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ነጻ ወጡ። ታተ 71.6

መቃብሮች ተከፍተው፣ «በምድር ትብያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፥ እኩሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኩሌቶቹም ወደ እፍረት እና ወደ ዘላለም ጉስቁልና ይሄዳሉ» (ዳን 12፡2) የሶስተኛውን መልአክ መልእክት አምነው ተቀብለው የሞቱት በታላቅ ክብር ከመቃብራቸው ተነስተው የእግዚአብሔርን ሕግ ያከብሩ ከነበሩ ሌሎች ፃድቃን ጋር የእግዚአብሔርን የሰላም ቃል ኪዳን ሰሙ። «የወጉትም ሁሉ» (ራዕ 1፡7)፣ በክርስቶስ የስቃይ ሞት ላይም የተሳለቁት፣ክርስቶስ ያስተማረውን እውነትና የእርሱን ሕዝብ የተቃወሙት ሁሉ የእርሱን የክብር ግርማ ሞገስ ለማየት እንዲሁም ለታማኞቹ እና ለታዘዙት የሚሰጠውን ሽልማት ለማየት ተነሱ፡፡ ታተ 72.1

ከበድ ያለ ደመና ሰማይን ቢጋርዳትም፥ ልክ በበቀል ዓይን እንደሚመለከት የአምላክ ዓይን ሆና ፀሐይ ብልጭ ድርግም አለች። ሃይለኛ መብረቆች ከሰማይ ብልጭ በማለት ምድርን በነበልባል ወላፈን ዋጧት። በሚያስፈራው የነጎድጓድ ጩኸት ውስጥ የኃጥአንን እጣ ፋንታ የሚገልጽ ምስጢራዊ እና የሚያስፈራ ድምጽ አስተጋባ። የተሰማው ድምጽ ለብዙዎቹ ግልጽ አልነበረም፣ ነገር ግን ሃሰተኛ አስተማሪዎች በግልጽ አስተውለውታል። ከጥቂት ጊዜ በፊት ግድ የለሽ፣ ትዕቢተኛ፣ እምቢተኛ የነበሩት እና የእግዚአብሔርን ሕግ በሚጠብቁት ላይ የከፋ ጭካኔ ያሳዩ የነበሩት ሰዎች ሁሉ አሁን ተደናግጠውና ተሸብረው በፍርሃት ተዋጡ። የእነርሱ ለቅሶ ከሁሉ ድምጽ በልጦ ተደመጠ። ሰዎች በታላቅ ፍርኃት ተውጠው ምህረትን ከክርስቶስ ሲማጸኑ፣ እርኩሳን መናፍስት ግን የክርስቶስን መለኮትነት በመገንዘብ በእርሱ ስልጣን ፊት ተንቀጠቀጡ።. ታተ 72.2

የብሉይ ኪዳን ነብያት የእግዚአብሔርን ቀን አስቀድመው በራዕይ ከተመለከቱ በኋላ እንዲህ ብለዋል፡- «የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና አልቅሱ፥ ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ እንደሚመጣ ጥፋት ይመጣል» (ኢሳ. 13፡6)፡፡ «ከእግዚአብሔር ማስደንገጥና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻ ግባ፥ በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ። ከፍ ያለችውም የሰው ዓይን ትዋረዳለች፥ የሰዎችም ኵራት ትወድቃለች፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኵራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፥ እርሱም ይዋረዳል፤ … በዚያን ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል። እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ከማስደንገጡና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ይገባሉ።» (ኢሳ. 2፡10-12፣ 20፣ 21) ታተ 72.3

በደመናው ስንጥቅ መካከል፣ ከጨለማው ጋር ሲነፃፀር ጨለማውን በአራት እጅ የሚያጥፍ ብሩህ የሆነ የኮከብ ወጋገን ፍንጥቅ አለ። ይህ ብርሃን ለታማኞች ተስፋን እና ደስታን ሲያበስር፥ የእግዚአብሔርን ሕግ ለማይታዘዙት ግን ጭካኔንና ቁጣን ይናገራል። ለክርስቶስ ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉ ሁሉ አሁን በጌታ አምባ ውስጥ እንደተሸሸጉ ያህል ሙሉ ደህንነት አላቸው። በዓለም ፈተና እና እውነትን በናቁት ሰዎች ተፈትነው ለሞተላቸው ጌታ ታዛዥነታቸውን አረጋግጠዋል። ታማኝነታቸውን እሰከሞት ድረስ ጸንተው ለያዙት፣ አሁን አስገራሚ ለውጥ መጣላቸው። ወደ እርኩሳን መናፍስትነት ከተለወጡት ከአስፈሪ ጨለማና ጨካኝ ሰዎች እጅ በቅጽበት ነጻ ወጡ። በፍርሃት፣ በድንጋጤ እና በድካም ገርጥቶ የነበረው ፊታቸው አሁን በአድናቆት በእምነት እና በፍቅር በርቷል። ድምፃቸውን በድል መዝሙር ከፍ አድርገው፥ «አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትናወጥ ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም። ውኆች ጮኹ ተናወጡም፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሳ ተናወጡ» (መዝ 46፡1-3) ታተ 72.4

እነኝህ የተቀደሱ የእምነት ቃሎች ወደ እግዚአብሔር በሚያስተጋቡበት ጊዜ ደመናዎች ተከፈቱ፡፡ ከአስፈሪውና ጨለማው ሰማይ ጋር ሲነፃፀር፣ በቃላት ለመግለፅ የሚያዳግት ክብር ያላቸው የሰማይ ከዋክብት ጎልተው ታዩ፡፡ ከሰማይ የምትመጣዋ ከተማ ክብር በተከፈቱት የሰማይ በሮች ሰንጥቆ አንፀባረቀ። ከዚያም ሁለት የተደራረቡ የድንጋይ ፅላቶችን የያዘ እጅ በሰማይ ላይ ታየ። ነብዩ እንዲህ ብሏል፡- «ሰማያት ጽድቁን ይናገራሉ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና…» (መዝ 50፡6) ያ ቅዱስ ሕግ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ በሲና ተራራ ላይ የሕይወት መመሪያ ይሆን ዘንድ በነጎድጓድ እና በእሳት መካከል ታውጆ የነበረው ሕግ፥ አሁን ፍርድ የሚሰጥበት መስፈርት ሆኖ ለሰዎች ተገለጠ። እጁ ጽላቱን ሲከፍት በዚያ ላይ የተፃፉት ሕጎች በእሳት እንደተነቀሱ መስለው ታዩ። ቃላቶቹ ግልጽ በመሆናቸው ማንም ሰው ሊያስተውላቸው ይችላል። ያን ጊዜ ትውስታ ተቀሰቀሰ፣ ጽልመት እና አፈ ታሪክ ከሰዎች አእምሮ ተወገደ፥ ዕጥር ምጥን፣ ግልፅ እና ሙሉ ስልጣን ያላቸው አስርቱ የእግዚአብሔር ትዕዛዛት በምድር ለሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ ታዩ። ታተ 72.5

የእግዚአብሔርን ቅዱስ ሕግ በእግራቸው በረገጡት ላይ የመጣውን ሽብር እና ተስፋ መቁረጥ ለመግለጽ ያዳግታል። በሕይወት ዘመናቸው እግዚአብሔር ሕጉን ሲሰጣቸው፥ የንስሃ እና የመለወጥ ዕድል በነበራቸው በዚያን ጊዜ፤ ባህሪያቸውን በርሱ መዝነው ከስህተታቸው መታረም ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን የዓለምን ደስታና ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ትዕዛዙን ወደ ጎን በመተው ሌሎችም እንዲተላለፉ አስተማሯቸው። እንዲሁም የእግዚአብሔር ህዝቦች የእግዚአብሔርን ሰንበት [ቅዳሜ] እንዲያረክሱ ለማስገደድ ሙከራ አደረጉ። አሁን ግን በዚያ በናቁት ሕግ ተፈረደባቸው። በሚያስደነግጥ እርግጠኝነት ሊያቀርቡ የሚችሉት በቂ ምክንያት እንደሌላቸው አዩ። ማንን እንደሚያገለግሉ እና ማንን እንደሚያመልኩ በምርጫቸው ወስነዋልና፡- «ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጥያተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ» (ሚል. 3፡18) ታተ 73.1

ከአገልጋዮች ጀምሮ ከበታቻቸው እስካሉት አባሎቻቸው ድረስ ያሉት የእግዚአብሔር ሕግ ጠላቶች በሙሉ አሁን ስለ እውነት እና ስለነበረባቸው ግዴታ አዲስ አመለካከት ኖራቸው። ጊዜው ካለፈ በኋላ የአራተኛው ትዕዛዝ ሰንበት [ቅዳሜ] የሕያው እግዚአብሔር ምልክት መሆኑን ተረዱ። ጊዜ ካለፈ በኋላ የሃሰተኛውን ሰንበት [እሁድ] ሐቅ እና ሲገነቡበት የነበረውን አሸዋማ መሰረት ተገነዘቡ። ከእግዚአብሔር ጋር ይዋጉ እንደ ነበር አሁን ተገነዘቡ። የኃይማኖት መሪዎች ነፍሳትን ወደ ገነት የመሩ ቢመስላቸውም፣ ነገር ግን ወደ ሲኦል ዕርግማን እየመሯቸው ነበር። በተቀደሱ የሥልጣን ወንበሮች ላይ ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች ኃላፊነት እና የእነርሱ አለመታመን ያስከተለው ውጤት በመጨረሻው የፍርድ ሰዓት ግልጽ ይሆናል። የአንዲትን ነፍስ መጥፋት አስከፊነት በትክክል የምናስተውለው በዘላለማዊው ዘመን ውስጥ መኖር ስንጀምር ነው። እግዚአብሔር «ከእኔ ራቅ አንተ ክፉ ባሪያ» የሚለው ሰው እድል ምንኛ ያስፈራል! ታተ 73.2

የክርስቶስን የመምጫ ቀንና ሰዓት እያወጀ ዘላለማዊውን ኪዳን ለሕዝቡ የሚያስተጋባ የእግዚአብሔር ድምጽ ከሰማይ ተሰማ። ልክ እንደ ታላቅ የነጎድጓድ ድምጽ ቃሉ በመላው ዓለም አስተጋባ። የአምላክ ልጆች ፊታቸውን ወደላይ ቀና አድርገው አዳመጡ፡፡ ልክ ሙሴ ከሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ እንደበራ የእነርሱም ፊት ከግርማው የተነሳ ያበራል። ኃጥአኖች ሊመለከቷቸው አይችሉም። ሰንበትን በቅድስና በመጠበቅ እግዚአብሔርን ላከበሩት የበረከት ቃላት ሲነገርላቸው ታላቅ የድል ጩኸት ተሰማ። ታተ 73.3

ከዚያም በምሥራቅ አቅጣጫ የሰው እጅ መዳፍ ግማሽ የሚያህል ትንሽ ጥቁር ደመና ታየ። ይህ ከሩቅ ሲታይ በጨለማ የተጋረደ የሚመስል ደመና አዳኛችንን የሚጋርድ ደመና ነው። የእግዚአብሔር ህዝቦች ይህ ምልክት የሰው ልጅ ምልክት እንደሆነ ያውቃሉ። ወደ ምድር በሚቃረብበት ጊዜ ደመናው እየደመቀ፣ ብሩህ ባለ ግርማ ሲሆን እና እንደሚፋጅ እሳት ሲመስል እንዲሁም ከበላዩ ያለው የቃል ኪዳኑ ቀስተ ዳመና ሲታይ ፃድቃን ተመስጠው በጸጥታ ይመለከቱታል። ኢየሱስ እንደ ታላቅ ድል አድራጊ ጀግና ሆኖ ሲመጣ ይታያል። እንደ ቀድሞው «የሕማም ሰው» ሆኖ የሐዘንና የውርደት መራር ጽዋ ለመጠጣት አይደለም የሚመጣው፤ በሰማይና በምድር ድል ነሺ ሆኖ በህያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ነው የሚመጣው፡፡ እርሱ «የታመነና እውነተኛ ይባላል፣ በፅድቅም ይፈርዳል፣ ይዋጋልም» «በሰማይ ያሉት ጭፍራዎች… ይከተሉታል» (ራዕ. 19፡11,14) እልፍ አእላፍ የቅዱሳን መላዕክት ሠራዊት የሚያምር ሰማያዊ መዝሙር እየዘመሩ ያጅቡታል፡፡ ሰማይ በሚያብለጨልጩ «ሺህ ጊዜ ሺህ፣ እልፍ ግዜ እልፍም» በሆኑ ነገሮች ተሞልቷል። የሚታየውን ትዕይንት ምንም አይነት ሰብአዊ ቀለም ሊስለው አይችልም፣ ሟች የሆነውም አእምሮ የጸዳሉን ብርሃን ሊያስተውል አይችልም። «ክብሩ ሰማያትን ከድኗል ምስጋናውም ምድርን ሞልቷል፥ ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው» (ዕንባ. 3፡3-4) ያ ሕያው ዳመና እየቀረበ ሲመጣ ሁሉም ዓይን የሕይወትን ልዑል ይመለከታል። በተቀደሰው ራስ ላይ የእሾህ አክሊል ሳይሆን የተቀመጠው የክብር ፀዳል ነው ቅዱስ ግምባሩን የከበበው። ፊቱም ከማለዳ ጸሐይ የበለጠ ያበራል። «በልብሱና በጭኑ ላይ የነገሥታት ንጉሥ እና የጌቶች ጌታ የሚል ስም ተጽፏል» (ራዕ. 19፡16) ታተ 73.4

በእርሱ ፊት የቆሙት ሰዎች ገፅታ ገረጣ። የእግዚአብሔርን ምህረት በናቁት ላይ የዘላለም ተስፋ መቁረጥ ወደቀባቸው። «ልባቸው በፍርሃት ቀለጠ፣ ጉልበታቸውም ተብረክርኳል የሰዎች ሁሉ ፊት ጠቁሯል» (ኤር. 30፡6, ናሆም 2፡10) ጻድቃን በመንቀጥቀጥ በታላቅ ድምፅ «ማን ሊቆም ይችላል?» ይላሉ። የመላዕክት ዝማሬ ሲቋረጥ፥ አስፈሪ ጸጥታ ሆነ። ከዚያም የኢየሱስ ድምጽ «ጸጋዬ ይበቃችኋል» ሲል ተሰማ። የፃድቃን ፊት በራ፣ ልባቸውም በደስታ ተሞላ። መላዕክትም መዝሙራቸውን በመቀጠል ወደ ምድር እየቀረቡ መጡ። ታተ 73.5

የነገሥታት ንጉሥ በእሳት ነበልባል ተከቦ በደመና ላይ ሆኖ መጣ። ሰማያት እንደ ወረቀት ተጠቀለሉ፥ ምድርም በፊቱ ተንቀጠቀጠች፥ ተራሮች እና ደሴቶች ሸሹ። «አምላካችን ይመጣል፣ ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ አውሎ ነፋስ አለ። በላይ ያለውን ሰማይን ምድርንም በህዝቡ ለመፍረድ ይጠራል።» (መዝ 50፡3ና4) ታተ 73.6

«የምድር ነገሥታትና፣ መኳንንት፣ ሺህ አለቃዎችም ባለጠጋዎችም፥ ኃይለኛዎችም፣ ባሪያዎችም፥ ጌቶችም፥ ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥ ተራሮችንና ዓለቶችንም ... በላያችን ውደቁ፥ በዙፋኑም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቁጣ ሰውሩን፥ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቷልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሏቸው።» (ራዕ. 6፡15-17) ታተ 74.1

አሁን ፌዝ አብቅቷል። ሃሰተኛ ምላሶች ጸጥ ብለዋል። የጦር መሳሪያ ካካታም፣ «ለጦርነት የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፥ በደም የተለወሰ ልብስ» ጸጥ ብለዋል (ኢሳ. 9፡5)፡፡ አሁን ከጸሎት፣ ከልቅሶና ዋይታ ድምፅ በቀር የሚሰማ ሌላ ድምፅ የለም። ከዚህ በፊት ሲያሾፉ ከነበሩት ከንፈር አሁን «ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቷልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል?» የሚል ጩኸት ተሰማ። ኃጥያተኞች አንዴ ንቀውት እና እምቢ ብለውት ከነበረው ፊት ከመቆም ይልቅ በተራሮችና ዋሻዎች ስር ለመቀበር ለመኑ። ታተ 74.2

የሙታንን ጆሮ ሳይቀር ዘልቆ የሚገባውን ድምጽ ያውቁታል። ይህ ድምፅ በርካታ ጊዜ በግልጽና በትህትና ቃል ንስኃ እንዲገቡ ለምኗቸው ነበር። ለበርካታ ጊዜ እንደ ጥሩ ወዳጅ ድምፅ፣ እንደ ጥሩ ወንድም ድምፅ፣ እንደ አዳኝ ድምፅ ሆኖ ተማጽኗቸዋል። «ክፉ ሥራችሁን ተው፣ መሞት ለምን ትፈልጋላችሁ?» (ሕዝ 33፡11) በማለት ይማፀን ከነበረው ድምፅ በስተቀር እነኚህን ፀጋውን የናቁ ሰዎች ሊወቅሳቸው የሚችል ሌላ ድምፅ የለም፡፡ «ኦ! ምነው ያ ድምፅ የባዕድ ድምፅ በሆነ!» ይላሉ፡፡ ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፡- «ወደ እኔ እንድትመጡ እጄን ዘርግቼ ጠራኋችሁ፣ እናንት ግን ጥሪዬን ቸል አላችሁ፣ ምክሬን ናቃችሁ፣ ተግሳጼንም አልተቀበላችሁም» (ምሳሌ 1፡24ና25)፡፡ ይህ ድምጽ ከዚህ በፊት የናቋቸውን ማስጠንቀቂያዎች፣ አምቢ ያሉትን ግብዣ፣ ያልተጠቀሙበትን ዕድል አስታወሳቸው። ታተ 74.3

ክርስቶስ ሲዋረድ ያፌዙበት የነበሩ ከእነርሱ መካከል ነበሩ። በሊቀ ካህኑ ትዕዛዝ በተፈረደበት ጊዜ በታላቅ ድምፅ «ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይሉ የእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታዩታላችሁ እንዲሁም በሰማይ ደመና ሆኖ ሲመጣ ታዩታላችሁ» በማለት የተናገረው የጌታ ቃል በሚያስፈራ ኃይል ትዝታው ወደ አእምሮአቸው መጣ። (ማቴ 26፡64)፡፡ አሁን በግርማው ክብር ሆኖ አዩት፣ በኃይሉም በእግዚአብሔር ቀኝ ሲቀመጥም ያዩታል። ታተ 74.4

«የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ» በማለቱ ምክንያት ያፌዙበት የነበሩ ሁሉ አሁን ዝም አሉ። ስለ ንጉሥነቱ ሲሰማ ያሾፈበት እና ሲቀልዱበት ለነበሩት ወታደሮቹ አክሊል እንዲጭኑለት ያዘዛቸው ትዕቢተኛው ሄሮደስ ከዚያ ቆሟል። በኃጢአተኛ እጃቸው ወይን ጸጅ ካባ የደረቡለት፣ በቅዱስ ራሱም ላይ የእሾህ አክሊል የደፉለት፥ በዛለው እጁ ውስጥም የውርደት በትር ያኖሩለት ሰዎች፥ በፊቱም ተደፍተው በትዕቢት እያሾፉ የሰገዱለት ሰዎች እዚያው ነበሩ። የሕይወት ምንጭ ልዑልን ይመቱ እና ይተፉበት የነበሩት ሰዎች አሁን ከሚዋጋው ዓይኑ ፊት ዞር በማለት ከታላቅ ግርማ ሞገሱ ፊት ለመሰወር ይሞክራሉ። ምስማሮችን በእጁ እና በእግሩ የቸነከሩት ወታደሮች እንዲሁም ጎኑን በጦር የወጋው ወታደር፤ አሁን እነኝያን ጠባሳዎች በፍርሃት እና በህሊና ወቀሳ ተመለከቷቸው። ታተ 74.5

ካህናት እና መሪዎች የቀራንዮን ክስተት በግልፅ ሁኔታ አስታወሱ፡፡ ራሳቸውን እየነቀነቁ «ሌሎችን አዳነ ራሱን ግን ማዳን አይችልም፤ እርሱ የእሥራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፣ እኛም እንመንበት» (ማቴ 27፡42ና43) በማለት ሰይጣናዊ ደስታ በተሞላበት መንፈስ በጩኸት ሲናገሩ የነበሩትን ቃላት በፍርሃት እና በመንቀጥቀጥ አስታወሱ። ታተ 74.6

የወይን እርሻ ቦታውን ፍሬ ለጌታቸው ለመስጠት አሻፈረኝ ስላሉት እና በኋላም አሽከሮቹን ስለደበደቧቸው፣ ከዚያም ልጁን ሲልክ ስለ ገደሉት የተናገረውን የኢየሱስን ምሳሌዎች በግልጽ አስታወሱ። እነርሱ ራሳቸው «ጌታ ራሱ እነኝያን ክፉዎች ይቀጣቸዋል» በማለት የተናገሩትን አረፍተ ነገር አስታወሱ። በእነኝያ ታማኝ ያልነበሩ ሰዎች ኃጥያት እና ቅጣት ውስጥ እነዚህ ካህናት እና ሽማግሌዎች የራሳቸውን ባህርይ፣ ፍርድና እጣ ፋንታ ተመለከቱ። አሁን የሞት ሲቃ ድምፅ አሰሙ። በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ «ስቀለው ስቀለው!» ብለው ከጮሁት ድምፅ በላይ ከፍ አድርገው «እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው! እርሱ እውነትም መሲህ ነው!» የሚል የተስፋ መቁረጥ ወዮ ድምፅ አሰሙ፡፡ ከነግሥታት ንጉሥ ፊት ለመሰወር ሞከሩ። በምድር መናወጥ ምክንያት በተሰነጠቁት ዓለቶች እና ዋሻዎች ውስጥ በከንቱ ራሳቸውን ለመሸሸግ ሞከሩ። ታተ 74.7

እውነትን ላለመቀበል «እምቢ» ባሉት ሰዎች የምድራዊ ሕይወት ውስጥ ሲኖሩ የነበረውን የአስመሳይነት ሕይወት እና ይናገሯቸው የነበሩትን አስመሳይ ቃላትን የሚያታውሱበትና ነፍሳቸውም በህሊና ወቀሳ በፀፀት የሚሰቃይበት ጊዜ ነበር። ነገር ግን ይህ የህሊና ወቀሳ፣ «ስጋት እንደጥፋት» «ጥፋትም እንደ አውሎ ነፋስ» በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ ከመጣው የህሊና ወቀሳ ጋር ሲነፃፀር ወደር የለውም (ምሳሌ 1፡27)፡፡ ክርስቶስንና ታማኝ ሕዝቦቹን ለማጥፋት የተመኙት ሁሉ አሁን በእርሱ ላይ ያረፈውን ክብር በዓይኖቻቸው ተመለከቱ። በዚህ በሚያስደንቅ ሁኔታ ውስጥ ሆነው፥ «እነሆ ተስፋ ያደረግነው አምላካችን፣ የጠበቅነው፣ እርሱም ያድነናል» (ኢሳ 25፡9) የሚለውን የፃድቃንን የደስታ ድምፅ ይሰማሉ። ታተ 74.8

ምድር በምትንቀጠቀጥበት ጊዜ፥ የመብረቅ ብርሃን ብልጭ ሲል ጊዜ እንዲሁም የነጎድጓድ ድምጽ ሲሰማ የእግዚአብሔር ልጅ ድምፅ በምድር ያንቀላፉትን ጻድቃን ይጠራቸዋል። ወደ ጻድቃን መቃብር በመመልከት፣ እጁን ወደ ሰማይ አንስቶ፡- «እናንት በምድር ትብያ ያንቀላፋችሁ ንቁ፥ ንቁ፥ ንቁ! ተነሱ!» በማለት ይናገራል። በምድር ሥፋት እና ርዝመት ሁሉ ያሉ ሙታን በሙሉ ድምጹን ይሰማሉ፣ ድምፁን የሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። ከየጎሳው፣ ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡ በተውጣጣ ሠራዊት ምድር ተሞላች። ከሞት እስር ቤቶች ነፃ ወጥተው የማይሞት ክብር ተላብሰው፥ «ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህስ የት አለ?» እያሉ ይጮሃሉ (1ኛ ቆሮ. 15፡55)፡፡ በሕይወት ያሉት ጻድቃን እና ከሞት የተነሱት ጻድቃን ድምጻቸውን አስተባብረው ረጅም የደስታና የድል ጩኸት አስተጋቡ። ታተ 75.1

ከሞት የሚነሱት ሁሉ ያኔ ወደ መቃብር ሲሄዱ የነበራቸውን ቁመና ይዘው ነው ከመቃብር የሚወጡት፡፡ ከሞት ከተነሱት መካከል የነበረው አዳም ቁመቱ ረጅም፣ እና ግዙፍ ሲሆን፤ ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር ሲነፃፀር ቁመቱ በትንሽ ብቻ ያጥራል። ከመጨረሻው ትውልድ ጋር ሲነፃፀር ግን ልዩነቱ ጉልህ ሆኖ ይታይ ነበር። በዚህ በአንድ ምሳሌ የሰው ዘር ምን ያህል እንደቆረቆዘ መመልከት ይቻላል። ነገር ግን ሁሉም ፃድቃን ዘላለማዊ የወጣትነት ኃይል የተላበሰውን አካል ይዘው ይነሳሉ። በፍጥረት መጀመሪያ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ነበር የተፈጠረው፥ በባህሪይ ብቻ ሳይሆን በመልክ እና በቅርጽም እንዲሁ። ኃጥያት የመለኮትን መልክ አበላሸው፣ ቀየረው፤ ክርስቶስ ግን ያ የጠፋውን መልክ መልሶ ለመፍጠር መጣ። እርሱ የተበላሸውን አካላችንን ይለውጣል፣ በራሱም የክብር አካል አምሳያ ይቀርጸዋል። ይህ ሟች፣ የበሰበሰ፣ ቅርጹን ያጣ እና በኃጥያት የተበላሸው አካል፥ አሁን ፍጹም፣ ውብ እና የማይሞት ይሆናል። ነቀፋ የነበረው እና ጉድለት የነበረው የአካል ክፍል በሙሉ በመቃብር ውስጥ ይቀራል። በኤደን ገነት ያጡትን ያንን የሕይወት ዛፍ ቅዱሳን አሁን ያገኛሉ፡፡ ይህንንም በማግኘታቸው ቀድሞ ለሰው ዘር ተሰጥቶ ወደነበረው ቁመና ድረስ እስኪደርሱ ድረስ «ያድጋሉ» (ሚል. 4፡2)። የመጨረሻዋ የኃጥያት ጠባሳ ሳትቀር ትወገዳለች፥ የክርስቶስ ታማኞችም በአእምሮ፣ በመንፈስ እና በአካል የአምላካቸውን ፍፁም ምሳሌ ይዘው የአምላካችንንና የጌታችንን ውበት ያንፀባርቃሉ። ኦ! ምን አይነት አስደናቂ ድነት ነው! ለዘመናት የተወራለት፣ ተስፋ የተደረገለት፣ በጉጉት እንናፍቅ የነበረው ነገር ግን በፍጹም ልናስተውለው ያዳገተን! ታተ 75.2

ቀጥሎም በሕይወት ያሉት ጻድቃን «በቅጸበት ዓይን» ተለወጡ። የእግዚአብሔርን ድምጽ በሰሙ ጊዜ ወደ ክብር ተለውጠው የማይሞተውን ሥጋ ለብሰው ከመቃብር ከተነሱት ቅዱሳን ጋር ሆነው በአየር ላይ ጌታቸውን ሊቀበሉ ተነጠቁ። «መላዕክትን ይልካል፣ ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል» (ማር. 13፡27)፡፡ ሕፃናቶች በቅዱሳን መላዕክት ታቅፈው ወደ እናታቸው እቅፍ ተወሰዱ። በሞት ተለያይተው የነበሩ ወዳጆች ዳግም ላይለያዩ ተገናኝተው የደስታን መዝሙር እየዘመሩ ወደ እግዚአብሔር ከተማ አረጉ። ታተ 75.3

እያንዳንዱ የደመና ሰረገላ ክንፎች አሉት፥ ከስሩም ሕይወት ያለው ተሽከርካሪ አለው፡፡ ሰረገላው ወደላይ ሲያቀና ተሽከርካሪዎቹ «ቅዱስ» እያሉ ይጮሃሉ፡፡ ክንፎቹም መንቀሳቀስ ሲጀምሩ «ቅዱስ» እያሉ ያስተጋባሉ። የሚከተሏቸው መላዕክቶችም «ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ኃያል አምላክ እግዚአብሔር» ይላሉ። የዳኑትም ፃድቃን በታላቅ ድምፅ «ሃሌሉያ!» ሲሉ ሰረገላው ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ጉዞውን ቀጠለ። ታተ 75.4

ወደ እግዚአብሔር ከተማ ከመግባታቸው በፊት መድኃኒታችን ለተከታዮቹ የድል ሽልማት ይሰጣቸዋል፣ የንጉሣዊ ክብር ልብስም ያጎናፅፋቸዋል። የሚያንጸባርቁ ማዕረግ ያላቸው ሁሉ ከቅዱሳንና ከመላዕክት ሁሉ በላይ ከፍ ብሎ እና ፊቱ በልዩ ፍቅር በሚያበራው ንጉሣቸው አራት መአዘን ዙሪያ ቆመዋል። የእነዚህ ቁጥራቸው እንደ አሸዋ የሚሆን ፃድቃን ዓይን ሁሉ በእርሱ ላይ ተተከለ፥ የእያንዳንዱ ዓይን «ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ መልኩም ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ተጎሳቁሏል» (ኢሳ. 52፡14) የተባለለትን የእርሱን ክብር ይመለከታል። በእያንዳንዱ ድል ነሺ ራስ ላይ ኢየሱስ በቀኝ እጁ የክብር አክሊል ይጭናል። ለእያንዳንዱ ድል የነሳ ፃድቅ የእርሱን «አዲስ ስም» «ለአምላክ የተቀደሰ» የሚል ፅሁፍ የተፃፈበት አክሊል ተዘጋጅቷል (ራዕ 2፡17)፡፡ ለእያንዳንዱ እጅ የድል ዘንባባ እና የሚያንፀባርቅ በገና ይሰጣል፡፡ ከዚያም መሪዎቹ መላዕክት የመጀመሪያውን የበገና ክር ሲመቱ የፃድቃን እጆች የያዙትን የበገና ክሮች መምታት ይጀምራሉ፣ ጣፋጭ የሆነ፣ ልብን የሚማርክ ዜማ ይደመጣል፡፡ በቃላት የማይገለጽ ተድላ የፃድቃንን ልብ ይሞላል፣ ከእያንዳንዱ አንደበት የሚወጣውም ድምጽ በምስጋና የተሞላ ውዳሴን እንዲህ በማለት ያሰማል፡- «ለወደደን ከኃጥያታችንም በደሙ ላጠበን፥ መንግስትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን አሜን።» (ራዕ. 1፡5-6) ታተ 75.5

ቅድስቲቷ ከተማ ከተዋጁት ሠራዊት ፊት ተዘጋጅታ ታየች። ኢየሱስ የእንቁ ደጆቿን ከፈተ፣ እውነትን የጠበቁ ፃድቃንም በበሮቿ ገቡ። ከዚያም ሆነው አዳም በኃጢአት ከመውደቁ በፊት ይኖርባት የነበረውን የእግዚአብሔርን ገነት ተመለከቱ። ከዚያም በሟች ጆሮ ውስጥ ገብቶ ከሚያውቅ የሙዚቃ ዜማ ሁሉ የሚበልጥ ድምጽ እንዲህ ሲል ተሰማ፡- «ተጋድሎአችሁ አበቃ፣ ኑ እናንት የአባቴ ብሩካን፥ ዓለም ሳይፈጠር ወደ ተዘጋጀላችሁ መንግስት ግቡ»። « ታተ 76.1

«በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላቸው አድርጎ እንዲያቆማቸው» (ይሁዳ 24) የሚለው ቃል እና አዳኛችን «አንተ የሰጠህኝ እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እመኛለሁ» በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ወደ አባቱ የጸለየው ጸሎት ፍጻሜን አገኘ፡፡ ክርስቶስ በደሙ የዋጃቸውን በአባቱ ፊት እንዲህ በማለት ያቀርባቸዋል፡- «እነሆ አንተ የሰጠኸኝን ልጆች ይዤ እኔ ቀርቤአለሁ … አንተ የሰጠኸኝን ሁሉ ጠብቄአለሁ» (ኢሳ. 8፡18፤ ዮሐ. 17፡12)። ኦ! ምን አይነት አሰደናቂ የሚዋጅ ፍቅር ነው! ዘላለማዊው አባት የኃጢአት ጉስቁልና እና የእርግማን ጫና የተወገደላቸውን የእርሱን አምሳል የሚያንፀባርቁትን ፃድቃን የሚመለከትበት፣ ሰብዓዊነት ከአምላካዊነት ጋር የሚስማማበት ያ ሰዓት ኦ ምንኛ የከበረ ነው! ታተ 76.2

በቃላት ለመግለጽ በሚያዳግት ፍቅር ኢየሱስ ታማኞቹን «ወደ አምላካችሁ ደስታ እንኳን ደህና መጣችሁ» ይላቸዋል። የመድህን ደስታ በእርሱ ውርደትና ስቃይ አማካኝነት የተዋጁት ወደ ክብረ-መንግሥቱ ሲገቡ ማየት ነው። የተዋጁትም በጸሎታቸው፣ በትጋታቸው እና በፍቅር አገልግሎታቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ለክርስቶስ የሰጡትን ሰዎች በዚያ መኖራቸውን ሲመለከቱ የጌታ ደስታ ተካፋይ ይሆናሉ። በዚያ በታላቁ ነጭ ዙፋን ዙሪያ ከበው ሳለ ወደ ክርስቶስ ያመጧቸውን ነፍሳት ሲመለከቱ፣ እነርሱም ደግሞ ሌሎችን፣ ሌሎቹም እንዲሁ ሌሎችን ወደ ክርስቶስ ያመጧቸው ነፍሳት ወደ ሰማያዊ እረፍት እንደገቡ ሲመለከቱ፣ ሁሉም አክሊላቸውን በክርስቶስ እግር ስር ሲያኖሩ እና ማለቂያ ለሌለው ዘመን ሲያመሰግኑ ሲመለከቱ፤ ልባቸውን በቃላት ለመግለፅ የማይቻል ደስታ ሞላው። ታተ 76.3

የተዋጁት ወደ አምላክ ከተማ በሚገቡበት ጊዜ ከባቢውን አየር ሁሉ የሚያደስት የውዳሴ ድምፅ ሞላው። ሁለቱ አዳሞች ሊገናኙ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ እርሱ ራሱ የፈጠረውን፣ ፈጣሪውን በድሎ የነበረውን፣ የመስቀል ሞት ምልክቶችን የያዘው በእርሱ ኃጢአት ምክንያት የሆነውን፥ የሰብዓዊ ዘር አባት የሆነውን አዳምን ለመቀበል እጁን ዘርግቶ ቆሟል፡፡ አዳም አሰቃቂውን የምስማር ጠባሳ ሲመለከት በክርስቶስ እቅፍ ላይ ሳይሆን የወደቀው፤ በእግሩ ስር ተደፍቶ ራሱን አዋርዶ እንዲህ አለ፡- «ይገባዋል፣ ይገባዋል የታረደው በግ ይገባዋል!»። መድህንም አዳምን በርህራሄ ከፍ አድርጎ በአንድ ወቅት መኖሪያው የነበረችውን፣ ከእርሷ ተባሮ ለረጅም ዘመናት ያላያትን ኤድንን እንዲመለከት ለመነው። ታተ 76.4

ከኤደን ከተባረረ በኋላ የአዳም የምድር ኑሮ በኃዘን የተሞላ ነበር። እያንዳንዱ የሚረግፈው ቅጠል፣ እያንዳንዱ የመስዋዕት ጠቦት፣ በፍጥረት ላይ የሚታየው እያንዳንዱ እርግማን፣ በሰው ንጽህና ላይ የሚታየው የኃጢአት እድፈት፥ አዳም የሰራውን ኃጢአት እንደ አዲስ ያስታውሱት ነበር። የኃጢአትን መስፋፋት ሲመለከት የተሰማው ጸጸት እጅግ የከፋ ነበር፡፡ የኃጢአት ሁሉ መንስኤ እርሱ ራሱ እንደሆነ ሰዎች በሚናገሩ ጊዜ ራሱን ይኮንን ነበር። ሆኖም ግን ራሱን ዝቅ በማድረግ ወደ ሺህ ዓመት ለሚጠጋ ዘመን ያህል በትዕግስት የኃጢአትን ውጤት ተሸክሞ ኖረ። በታማኝነትም ስለ ኃጢአቱ ንሥሃ ገብቶ፣ የአዳኙን የድነት ነጻ ስጦታ አምኖ፥ የትንሳኤን ተስፋ ጨብጦ ነበር የሞተው። የእግዚአብሔር ልጅ የሰውን ድካም እና ውድቀት ዋጀ፥ በዚህ የማስታረቅ ሥራም፥ አዳም ወደ ቀድሞው ሥፍራ ወደ ርስቱ መመለስ ቻለ። ታተ 76.5

አዳም በታላቅ ደስታ ተሞልቶ በአንድ ወቅት እጅግ በጣም ይወዳቸው የነበሩትን፥ ያኔ ፍፁም እና ደስተኛ በነበረ ጊዜ ፍሬአቸውን ይቀጥፍ የነበሩትን እነኛን ዛፎች ተመለከተ። እርሱ ራሱ ያሳድጋት የነበረችውን የወይን ፍሬ እንዲሁም አንድ ወቅት ይንከባከባት የነበረችውን አበባ ተመለከተ። እየተመለከተ ያለው ነገር ሁሉ እውነት እንደሆነ በአእምሮው አስተዋለ፡፡ አሁን የሚመለከታት አዲሲቷ ኤደን ገነት ቀድሞ ከተባረረባት ይልቅ እጅግ የተዋበች እንደሆነች ተገነዘበ። መድህን አዳምን ወደ ሕይወት ዛፍ ከወሰደው በኋላ ውብ ፍሬዋን ቆርጦ እንዲበላ ሰጠው። በርሱ ዙሪያም፤ የተዋጁትን የእርሱን ቤተሰብ አባላት ሁሉ በእግዚአብሔር ገነት ውስጥ ተመለከታቸው። በዚን ጊዜ የሚያንጸባርቀውን አክሊሉን በኢየሱስ እግር ስር አስቀምጦ፥ በደረቱ ላይ ተጠምጥሞ አዳኙን አቀፈው። ወርቃማውን በገና አንስቶ በሚሞዝቅበት ጊዜ ሰማይ የድል ነሺውን ዜማ በማስተጋባት እንዲህ አሉ፡- «ታርዶ የነበረው በግ፣ አሁን የሚኖረው ይገባዋል፣ ይገባዋል፣ ይገባዋል!»። የአዳም ቤተሰቦች በሙሉ አብረው እየዘመሩ ሳለ ሁሉም አክሊላቸውን በየተራ በአክብሮት በአዳኙ እግር ስር አኑረው ሰገዱለት። ታተ 76.6

ይህንን የቤተሰብ ቅልቅል ከዚህ ቀደም አዳም በኃጢአት በወደቀበት ጊዜ አልቅሰው የነበሩት፣ ኢየሱስ ደግሞ ከትንሳኤ በኋላ በእርሱ ስም የሚያምኑትን የጻድቃንን መቃብር ከፍቶ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ደስ የተሰኙት መላዕክት ተመለከቱት። አሁን የድነት ሥራ እንደተፈጸመ በመመልከት በምስጋና መዝሙር ሌሎቹን ተቀላቀሏቸው። ታተ 76.7

«አውሬውን እና ምልክቱን እንዲሁም ምስሉን እና የስሙን ቁጥር ድል የነሱት» (ራዕ. 15፡2) ቅዱሳን ሠራዊት፣ በዙፋኑ ዙሪያ በእሳት የተቀላቀለ በሚመስለው፥ በዚያ በእግዚአብሔር ግርማ ባሸበረቀው የብርጭቆ ባህር ላይ ቆመው ነበር፡፡ ከበጉ ጋር ከነገድ ሁሉ የተዋጁት መቶ አርባ አራት ሺ ሰዎች በጽዮን ተራራ ላይ የእግዚአብሔርን በገና ይዘው ይታያሉ፡፡ ከዚያም ልክ እንደ ብዙ ውኃ ድምጽ፣ እንደ ታላቅ ነጎድጓድም ድምጽ በገናን የሚጫወቱ በዙፋኑ ፊት ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህዎች በቀር ማንም የማያውቀውን አዲስ ቅኔ ሲቀኙና ሲዘምሩ ተሰማ። ይህ የሙሴ መዝሙር እና የበጉ መዝሙር ነው፥ የነጻነት መዝሙር። ከእነኝያ ከመቶ አርባ አራት ሺህዎች በቀር ማንም ሊያውቀው አይችልም፥ ምክንያቱም እንደርሱ ያለ ልምምድ ማንም ተለማምዶት የማያውቅ፣ የራሳቸው ብቻ የልምምዳቸው መዝሙር ነውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነኝህ ናቸው፡፡ እነርሱ በምድር ይኖሩ ከነበሩት ሁሉ ተለይተው ወደ ሰማይ የተነጠቁ ስለሆኑ ለእግዚአብሔር እና ለበጉ የበኩር ፍሬዎች ይባላሉ። (ራዕ. 14፡1-5 እና ራዕ. 15፡2-3)፡፡ «እነኝህ ከታላቅ መከራ የመጡት ናቸው» (ራዕ. 7፡14) «እነርሱ ፍጥረት ከሆነ ወዲህ ሆኖ ከማያውቅ ከታላቅ የመከራ ጊዜ ውስጥ አልፈዋል፥ የያዕቆብን የመከራ ጊዜ ስቃዩን ታግሰዋል፥ እነርሱ የእግዚአብሔር የቁጣ ጽዋ በፈሰሰ ጊዜ ያለ አማላጅ ቁመዋል፤ ሆኖም ግን በበጉ ደም ልብሳቸውን አጥበው ስላነጹ ነፃ ወጥተዋል። «በአፋቸውም ውሸት አልተገኘበትም፥ በእግዚአብሔር ፊትም ነውር የለባቸውም» «ቀንና ሌሊትም በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት በመቅደሱ ያገለግሉት ነበር፥ በዙፋኑ ያለውም ከነርሱ መካከል ይኖራል» (ራዕ. 14፡5, ራዕ. 7፡15) ምድር በረሃብ እና በበሽታ ምድረ በዳ ስትሆን አይተዋል፥ ጸሐይም በታላቅ ትኩሳት ስትፋጅ እነርሱ ራሳቸው ስቃዩን፣ ረሃቡንና ጥማቱን ታግሰዋል። አሁን ግን ዳግም አይራቡም፥ ዳግምም አይጠሙም፥ ጸሐይም ትኩሳቷ ከቶ አይጎዳቸውም፥ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፥ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከአይናቸው ያብሳል (ራዕ. 7፡16-17) ታተ 77.1

በዘመናት ሁሉ የአዳኙ ምርጦች የሆኑት ፃድቃን በፈተና ትምህርት ቤት ውስጥ በማለፍ ሰልጥነዋል። በምድርም ላይ ሲኖሩ በጠባቡ መንገድ ተጉዘዋል። በስቃይም ወላፈን ነጽተዋል። ስለ ኢየሱስ ብለው ተቃውሞን፣ ጥላቻን፣ የሥም ማጥፋትንም ታግሠዋል። በስቃይ መንገድ ቢሄዱም እርሱን ይከተሉ ነበር። ራስን በመካድ መራራ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን ተጋፍጠዋል። በራሳቸው መራራነት በተሞላበት ልምምድ ውስጥ በማለፍ የኃጢአትን ክፋት፣ የኃጢአትን ኃይል፣ የበደለኝነት ስሜት እና የኃጢአትን ዋጋ ተምረዋል፥ ኃጢአትን መጸየፍንም እንዲሁ፡፡ ለእነርሱ ድነት ሲባል የተከፈለውን ታላቅ መስዋዕትነት ሲያስተውሉ፣ በትህትና በመሞላት ከልባቸው ለአምላካቸው ምስጋና እና ክብር አቀረቡ። የዳኑት ፃድቃን የተሰማቸውን ስሜት እና አክብሮት በኃጢአት ያልወደቁት ፍጡራን ሊያተውሉት አይችሉም፡፡ ብዙ ይቅር ስለተባሉ ብዙ ያፈቅሩታል፡፡ የክርስቶስ ስቃይ ተካፋይ ስለነበሩ አሁን የክብሩ ግርማ ተካፋይ ለመሆን ችለዋል፡፡ ታተ 77.2

የእግዚአብሔር መንግስት ወራሾች፥ በጣሪያ ሥር ካሉ መኖሪያዎች፣ ከደሳሳ ጎጆዎች፣ ከየእሥር ቤቱ፣ ከየድንኳኑ፣ ከተራሮች፣ ከየምድረበዳው፣ ከዋሻዎች እና ከባህር ሰርጦች ነው የመጡት። በምድር ላይ ሲኖሩ ድሆች፣ የተሰቃዩና ግፍ የደረሰባቸው ነበሩ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታማኝ ክርስቲያኖች የሰይጣንን የሐሰት ትምህርቶች ላለመቀበል በጽናት በመቆማቸው ምክንያት የመናቅ ሸክም እንደከበዳቸው ወደ መቃብር ወርደዋል። በሰብዓዊ ፍርድ ቤቶች እንደ ክፉ ወንጀለኞች ተወንጅለው ተፈርዶባቸዋል። አሁን ግን «እግዚአብሔር ራሱ ፈራጅ ነው» (መዝ. 50፡6) አሁን የምድር ውሳኔዎች ሁሉ ተቀልብሰዋል። «የህዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ አስወግዷል» (ኢሳ. 25፡8) «እግዚአብሔር የተቤዣቸው የተቀደሰ ሕዝብ ብለው ይጠሯቸዋል» «በአመድ ፋንታ አክሊልን፣ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፣ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጎናጸፊያ እሳጣቸው ዘንድ ልኮኛል» (ኢሳ. 62፡12 ፣ 61፡3) እነርሱ ካሁን ወዲያ ደካሞች፣ የተሰቃዩ፣ የተበተኑና የተጨቆኑ አይሆኑም። ካሁን ወዲያ ለዘላለም ከአምላካቸው ጋር ይሆናሉ። በምድር ላይ ተከብሮ ይኖር የነበረ ሰው ለብሶት ከሚያውቀው እጅግ የሚበልጥ የክብር ልብስ ተጎናጽፈው በዙፋኑ ፊት ይቆማሉ። በምድራዊ ንጉሥ ራስ ላይ ተጭነው ከነበሩት የሚበልጥ እጅግ የተዋበ አክሊል በየራሶቻቸው ላይ ተጭኖላቸዋል። እነኝያ የስቃይና የለቅሶ ቀናት ለዘላለም አለፉ። የክብር ንጉሥ እንባቸውን ከዓይናቸው አበሰ፥ የኀዘን ምንጮች ሁሉ ተወገዱ። የዘነባባን ዝንጣፊ እያወዛወዙ ግልጽ፣ ጣፋጭ እና በህብር የተሞላውን ውዳሴአቸውን አቀረቡ። በሰማይ ዳርቻ ሁሉ እስኪሰማ ድረስ ሁሉም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እየተቀባበሉ፡- «በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችን፥ ለበጉ ማዳን ሆኗል» ሲሉ፤ በሰማይ የሚኖሩ ፍጥረታት ደግሞ፡- «አሜን በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን አሜን» እያሉ በመዝሙር መልስ ይሰጣሉ። (ራዕ. 7፡10,12) ታተ 77.3

በምድራዊ ሕይወታችን የመዳንን ድንቅ ዓላማ ማስተዋል እንጀምራለን። በዚህ ውስን በሆነው አእምሮአችን በመስቀል ላይ የተገናኙትን ሃፍረትንና ክብርን፣ ሕይወትንና ሞትን፣ ፍርድንና ምህረትን፥ በጥልቀት ልናስተውለው እንሞክር ይሆናል። ነገር ግን የአእምሮ ብቃታችን እጅግ የላቀ ቢሆንም እንኳ ጥልቅ ትርጉማቸውን ፈጽሞ ማስተዋል አንችልም። የማዳን ፍቅር ስፋትና ርዝመት፣ ጥልቀትና ከፍታ በደብዛዛ መልኩ ነው የምናስተውላቸው። የተዋጁት እግዚአብሔር እንደሚያያቸው ቢያዩ እንኳ፣ አሁን እንደታወቁት ቢያውቁም እንኳ፤ የድነትን እቅድ ፈጽመው ሊያስተውሉት አይችሉም፡፡ ነገር ግን በየእለቱ ለሚገረመው እና በደስታ ለተሞላው አእምሮአቸው ለዘላለም ያለማቋረጥ አዲስ እውነት ይገለጥለታል። የምድር ኀዘን፣ ስቃይ እና ፈተና ቢያበቁም፣ መንስኤዎቻቸውም ቢወገዱም ቅሉ፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ለደህንነታቸው የተከፈለውን ዋጋ ፈጽመው አይረሱትም፣ ሁልጊዜ ያስታውሱታል። ታተ 77.4

የክርስቶስ መስቀል ለዳኑት ፃድቃን የዘላለም ሳይንሳቸው እና መዝሙራቸው ይሆናል። ግርማ በተጎናፀፈው ክርስቶስ ውስጥ የተሰቀለውን ክርስቶስን ይመለከታሉ። ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ዓለማትን እጅግ ሰፊ በሆነው በሕዋ ውስጥ የፈጠረውና ያለ ምሶሶ ደግፎ የያዛቸው፣ በእግዚአብሔር የተወደደው፣ የሰማይ ንጉሥ፣ ኪሩቤል እና የሚያበራው ሱራፌል ሊሰግዱለት ደስ የሚላቸው፣ የወደቀውን የሰው ዘር ከፍ ለማድረግ ራሱን ያዋረደው፣ የኃጢአትን በደል እና ኀፍረት የተሸከመው፣ የምትጠፋው ዓለም ዋይታ ልቡን እስኪሰብር እና በቀራንዮ መስቀል ላይ ሕይወቱ እስኪያልፍ ድረስ የአባቱ ፊት ከእርሱ ሲሰወር በትእግስት የቻለውን መድህን መቼም ቢሆን አይረሳም፡፡ የዓለም ሁሉ ፈጣሪ የሆነውና የሁሉን መጨረሻ የሚወስነው፣ ሰዎችን ከማፍቀሩ የተነሳ ክብሩን ሁሉ ትቶ ራሱን ያዋረደውን፣ መላው ዩኒቨርስ ለዘላለም ሲያደንቀው እና ሲያመልከው ይኖራል። የዳኑት ፃድቃን መድህናቸውንና ዘላለማዊው የአባቱ ክብር በፊቱ ላይ ሲያበራ ሲመለከቱት፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ፀንቶ የሚኖረውን፣ ዙፋኑን ሲመለከቱ፣ ክብረ-መንግሥቱም ፍፃሜ እንደሌለው ሲያስተውሉ፤ በታላቅ ደስታ ተሞልተው፡- «ይገባዋል፣ ይገባዋል፣ይገባዋል! በውድ ደሙ ከእግዚአብሔር ጋር ላስታረቀን ለታረደው በግ» እያሉ ይዘምሩለታል። ታተ 78.1

የመስቀሉ ምስጢር ሌሎች ምስጢሮችን ያብራራል። ከዚህ ቀደም እኛን ያስፈራን እና ያስደነግጠን የነበረው የእግዚአብሔር ባህርይ አሁን ውብ እና ማራኪ ሆኖ ከቀራንዮ በሚፈልቀው ብርሃን ውስጥ ታየ። ምህረት፣ ርህራሄ እና የወላጅነት ፍቅር፣ ከቅድስና፣ ከፍትህ እና ከኃይል ጋር ተዋህደው ተገለጹ። የዙፋኑን ግርማ ልቆ እና ከፍ ብሎ ስንመለከት፤ ባህሪውን በጸጋ ተሞልቶ እናገኘዋለን፣ ከዚያም «አባታችን» የሚለውን የከበረ ስም ከዚህ ቀደም ባላስተዋልነው መልኩ እናስተውላለን። ታተ 78.2

በዘላለማዊው ጥበብ የተካነው አምላክ ለድነታችን መፍትሄ ልጁን መስዋዕት ከማድረግ ውጭ ሌላ መንገድ እንዳልነበረው ይስተዋላል። ይህ መስዋዕት ያስገኘው ውጤት፣ አዲሲቷን ምድር በዳኑት፣ በቅዱሳን፣ በደስተኞችና በማይሞቱ ሰዎች ስትሞላ በማየት መደሰት ነው፡፡ አዳኛችን ከጨለማው ኃያላን ጋር ያደረገው ተጋድሎ ውጤት ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእግዚአብሔር ክብር የሚያስተጋባው የፃድቃን ደስታ ነው፡፡ አብ የከፈለው ዋጋ አንዲት ነፍስ ያላትን ትልቅ ዋጋ ያሳያል፡፡ ክርስቶስም እራሱ የመስዋዕቱን ፍሬ ሲመለከት ደስ ይለዋል፣ ይረካል፡፡ ታተ 78.3