ታላቁ ተስፋ
መጠበቂያው የእግዚአብሔር ቃል
ወደ ሕጉና ወደ ምስክር ቃሉ ሂዱ! እነርሱም እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም» (ኢሳ. 8፡20)፡፡ የእግዚአብሔር ህዝቦች በሃሰት መምህራን ትምህርትና በጭለማ መናፍስት አታላይ ሃይል እንዳይሳቡ (እንዳይታለሉ) ጠባቂያቸው ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር ቃል ይመራሉ፡፡ ሰዎች የመጽሐፍ ቀዱስን እውቀት እንዳያገኙ ለመከላከል ሰይጣን በተቻለው ብልሃት ሁሉ ይጠቀማል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ የርሱን የማታለል ሥራ ስለሚያጋልጥበት ነው፡፡ በማንኛቸውም የእግዚአብሔር ሥራ በተሃድሶ ወቅት የክፋት ልዑል ደግሞ በእንቅስቃሴው ይበልጥ የተጋ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰይጣን ክርስቶስንና ተከታዮቹን በመቃወም የሚያደረገውን የመጨረሻ ትግል ለማካሄድ የሚቻለውን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ታላቁና የመጨረሻው የማታለል ሥራው በቅርቡ በፊታችን ሊገለጥ (ሊታይ) ነው፡፡ የክርስቶስ ተቃዋሚ በአይናችን ፊት ድንቅ ሥራውን ሊያከናውን ነው፡፡ በእውነትና በአስመሳይ እውነት መካከል ያለው ልዩነት በጣም ከመመሳሰላቸው የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ካልሆነ በስተቀር መለየት አይቻልም፡፡ ማንኛውም ምስክርነትና ማንኛውም ተአምር በቅዱስ ቃል መለካት (መፈተን) ይኖርበታል፡፡ ታተ 51.1
የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመፈፀም የሚሞክሩ ሁሉ ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል፤ ሰዎችም ይሳለቁባቸዋል፡፡ እነርሱ መቆም የሚችሉት በእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የሚጠብቃቸውንም ፈተና ለመቋቋም እንዲችሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ አለባቸው፡፡ እርሱን ሊያከብሩና ፈቃዱን ለማድረግ የሚችሉት ስለ ባህርዩ፣ ስለ መንግስቱና ስለ ዓላማው ትክክለኛ ግንዛቤ ሲኖራቸው ብቻ ነው፡፡ በመጨረሻው ታላቁ ተጋድሎ ወቅት ሊቆሙ የሚችሉት ልባቸውን በእግዚአብሔር ቃል እውነት የሞሉ ብቻ ናቸው፡፡ እያንዳንዷ ነፍስ የምርመራ ፈተና ይመጣባታል፡- ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን ልታዘዝን? ወሳኙ ሰአት እነሆ ቀርቦአል! እግሮቻችን በማይለወጠውና እንደ አለትም በጠነከረው በእግዚአብሔር ቃል ቆመዋልን? ለእግዚአብሔር ትእዛዛት እና ለኢየሱስ እምነት በፅኑ ተሟጋችነት ለመቆም ተዘጋጅተናልን? ታተ 51.2
መድኃኒታችን ከመሰቀሉ በፊት እርሱ እንደሚሞትና ከመቃብርም እንደሚነሳ አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሮአቸው ነበር፡፡ መላእክትም የእርሱን ቃል በእነርሱ ልብና አእምሮ ለመቅረጽ በአካባቢያቸው ተገኝተው ነበር፡፡ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ ከሮማውያን ቀንበር ጊዜያዊ ነፃነትን ያገኙ ዘንድ ይጠብቁ ስለነበር ተስፋቸውን ሁሉ የጣሉበት ጌታ የውርደት ሞትን ይሞታል የሚለው ሃሳብ ራሱ እነርሱ ሊቀበሉት የማይችሉት ሃሳብ ሆነባቸው፡፡ ሊታወሳቸው ይገባ የነበረው ቃል ከአእምሯቸው ጠፍቶ ስለነበር የፈተና ጊዜ በመጣበት ወቅት ሳይዘጋጁ ቀሩ፡፡ የክርስቶስ ሞት ቀደም ብሎ ተነግሯቸው እንዳልነበረ ተስፋቸው ሙሉ በሙሉ ጠፋባቸው፡፡ ስለዚህ ያኔ በክርስቶስ ቃል አማካኝነት ለደቀ መዛሙርቱ ቀድሞ ተገልፆላቸው እንደነበር ዛሬም ለእኛ በትንቢት የወደፊት ነገር ሁሉ ተገልፆልናል፡፡ ከምህረት ደጅ መዘጋትና ለመከራ ጊዜ ከመዘጋጀት ሥራ ጋር የተያያዘው የዓለም ሁኔታ በግልፅ ይታየናል፡፡ ሰይጣን ሰዎች ስለ ድነት እውቀቱ እንዳይኖራቸው የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፤ ያም የመከራ ጊዜ ሳይዘጋጁ ያገኛቸዋል፡፡ ታተ 51.3
እግዚአብሔር ወደ ሰዎች ጠቃሚ ማስጠንቀቂያ በሚልክበት ጊዜ ማንኛውም የማመዛዘን ችሎታ ያለው ሰው መልእክቱን እንዲያስተውል ይፈልጋል፡፡ ለአውሬውም ሆነ ለምስሉ በሚሰግዱት ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፍርድ (ራእይ 14፡9-11) ሰዎች ሁሉ የአውሬው ምልክት ምን እንደሆነ እርሱንም ላለመቀበል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለማወቅ (ለመረዳት) ትንቢቱን ተግተው ያጠኑ ዘንድ ሊያነሳሳቸው ይገባል፡፡ ብዙ ሰዎች ግን እውነትን ላለመስማት ጆሮአቸውን እየደፈኑ ወደ ተረት ያተኩራሉ፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ መጨረሻዎቹ ቀኖች እየተመለከተ እንዲህ ሲል ገልፆአል፡- «ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጣል…» (2ኛ ጢሞ 4፡3)፡፡ ይህ ጊዜ ዛሬ መጥቶአል፡፡ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን አይፈልጉም፣ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ኃጢያተኛና ዓለም ወዳጅ የሆነው የልባቸውን ምኞት ይነካባቸዋልና፡፡ ሰይጣንም እነዚህ ሰዎች የሚመኙትን በማቅረብ ያታልላቸዋል፡፡ ታተ 51.4
እግዚአብሔር ግን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ የትምህርትና ተሃድሶ ሁሉ መሰረት አድርገው የሚይዙ ሰዎች በዚህ ምድር ይኖሩታል፡፡ የምሁራን አስተያየት፣ የሳይንስ ውጤቶች፣ የካህናት አብያተ መማክርት እምነትም ሆነ ውሳኔዎች፣ የብዙሃኑ ድምፅ ሁሉ ቢሰበሰብ ከእነዚህ ውስጥ እንዱ እንኳን ለሃይማኖት እምነት ማስረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ ማንኛውንም ትምህርት ወይም ትእዛዝ ከመቀበላችን በፊት «እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ብሎአልን?» ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ሰይጣን ሰዎች በእግዚአብሔር ፈንታ በሰዎች ላይ እንዲያተኩሩ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን መርምረው ያለባቸውን ግዴታ በማወቅ ፈንታ ጳጳሳትን፣ ቀሳውስትንና የሥነ-መለኮት ሊቃውንትን እንደመሪዎቻቸው አድርገው እንዲመለከቷቸው ይመራል፡፡ ከዚያም የእነዚህን መሪዎች አእምሮ በመቆጣጠር ብዙሃኑ በሱ ፈቃድ እንዲመሩ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ታተ 51.5
ክርስቶሰ የሕይወትን ቃል ለመናገር በመጣ ጊዜ ተራው ህዝብ በደስታ ያዳምጠው ነበር፡፡ ካህናትና መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ በእርሱ አመኑ፡፡ ነገር ግን የካህናት አለቆችና የህዝቡ መሪዎች የእርሱን ትምህርት ለማውገዝና ላለመቀበል ወሰኑ፡፡ ምንም እንኳን ላያገኙበት ወንጀል ከርሱ ለማግኘት ቢጥሩም፣ ምንም እንኳን የሚናገረው ቃል በጥበብና በመለኮታዊ ኃይል የተሞላ መሆኑን ቢያውቁም ቅሉ፤ በርሱ ላይ የነበራቸው የጥላቻ መንፈስ እየባሰባቸው ሄደ፡፡ የመሢህነቱንም ግልጽ ማስረጃ ላለመቀበል ወሰኑ፡፡ ቢቀበሉማ ኖሮ ደቀመዛሙርቱ ይሆኑ ዘንድ እውነት ባስገደዳቸው ነበር፡፡ እነዚህን የኢየሱስ ተቃዋሚዎች ሕዝቡ ገና ከሕጻንነት ዘመኑ ጀምሮ እንዲያከብራቸውና እንዲገዛላቸው ተምሮ ነበር፡፡ ሕዝቡም እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል «ገዢዎቻችንና ምሁራን ጸሐፊዎቻችን በኢየሱስ የማያምኑት እንዴት ነው? እርሱ ክርስቶስ ቢሆን ኖሮ እነዚህ አዋቂዎች በተቀበሉት ነበር!»፡፡ የእነዚህ የህዝብ መምህራን ተጽእኖ ነበር የአይሁድ ህዝብ ክርስቶስን እንዳይቀበሉ ያደረገው፡፡ ታተ 52.1
እነዚያን ካህናትና መሪዎች ያነሳሳ መንፈስ ዛሬም በብዙዎች «ሃይማኖተኞች ነን» ባዮች እየተገለጸ ነው፡፡ እነርሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ልዩ ወቅታዊ እውነቶች ለመመርመር አይፈልጉም፡፡ የአባላቶቻቸውን የቁጥር ብዛት፣ ያላቸውን ሃብትና ዝና ብቻ በማስመልከት ትክክለኛውን እውነት የሚሰብኩትን እነርሱ «በቁጥር ያነሱ፣ ድሆችና ዝና የሌላቸው እንዲሁም ከዓለም ጋር የሚለያይ ትምህርት ያላቸው ናቸው» በማለት እጅግ ዝቅ አድርገው በማየት ይንቋቸዋል፡፡ ታተ 52.2
ክርስቶስ የእነዚህ የፈሪሳዊያንና የሕግ መምህራን ስልጣን ተጽእኖ በአይሁዶች መበታተን ብቻ እንደማያበቃ ቀደም አድርጎ ተመልክቷል፡፡ በዘመናት ሁሉ ለቤተክርስትያን እርግማን የሆነውን፤ ህሊናን ለመግዛት ሲባል የሰውን ስልጣን ከፍ የማድረግን ሥራ አስቀድሞ በትንቢት አይቶአል፡፡ ክርስቶስ ፈሪሳውያንንና የሕግ መምህራንን በጥብቅ ያወገዘውና ህዝቡ እነዚህን እውር አለቆች እንዳይከተል የሰጠው ማስጠንቀቂያ ለመጪው ትውልድ እንደ ተግሳጽ (ምክር) ይሆን ዘንድ ተጽፎ ይገኛል፡፡ የሮማ ቤተ ክርስቲያን «መጸሐፍ ቅዱስን የመተርጎም (የማስረዳትና የማስተማር) መብት ለካህናት ብቻ ተሰጥቷል፤ በመሆኑም የእግዚአብሔርን ቃል ለማስረዳት ብቃት ያላቸው ካህናት ብቻ ናቸው» በማለት ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስ በእጁ እንዳይገባ አድርጋለች፡፡ ምንም እንኳን የተሃድሶ እንቅስቃሴ (ሪፎርሜሽን) በወቅቱ መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ሰው እንዲዳረስ ቢያደርግም፣ የሮማ ቤተ ክርስቲን ይዛ የነበረችው ተመሳሳይ መሠረተ አቋም በፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ያሉትን ብዙ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስን ራሳቸው በግል እንዳይመረምሩ አግዷቸዋል (አሰናክሏቸዋል)፡፡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ቤተክርስቲያን እንደተረጎመችው መቀበል እንዳለባቸው ይማራሉ፡፡ ምንም እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተጻፈ ትምህርት ቢሆንም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ከመምህራኑ እምነትም ሆነ ከቤተክርስትያናቸው መሰረታዊ ትምህርት ጋር የሚቃረን ሆኖ ካገኙት በጭራሽ አይቀበሉትም፡፡ ታተ 52.3
የሃሰት መምህራንን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ማስጠንቀቂያዎችን የያዘ ቢሆንም የነፍሳቸውን ድነት ለካህናት ለማስረከብ የተዘጋጁ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዛሬው ዘመን ስለሚያምኑት እምነት ምክንያት እንዲሰጡ ቢጠየቁ ከሃይማኖት መሪዎቻቸው ቀድሞ ከተቀበሉት በቀር ሌላ ምክንያት የማያቀርቡ በብዙ ሺህ የሚቀጠሩ ክርስትያኖች አሉ፡፡ የመድኃኒዓለምን ትምህርት እጅግም ሳያስተውሉት ያልፉታል፡፡ ካህናት የተናገሩት ቃላት ግን ሙሉ በሙሉ ይታመናሉ፡፡ ለመሆኑ ካህናት የማይሳሳቱ፣ እንከን የሌላቸው ናቸውን? ነፍሶቻችንን እንዲምሩ እንዴት አምነን ለነሱ አደራ እንሰጣለን? ከብልሹ አለማዊ መንገድ ለመውጣት የሚያስችል የሞራል ድፍረት እጦት ብዙዎች አካሄዳቸውን ከምሁራን ጋር እንዲያደርጉ ይመራቸዋል፡፡ እውነትን ራሳቸው በግል መመርመርን ስላልፈለጉ ተስፋ በሚያስቆርጥ መንገድ በሃሰት ሰንሰለት ይታሰራሉ፡፡ እነርሱ የወቅቱ እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ እንደተጻፈ ያያሉ፣ የመንፈስ ቅዱስ ኃይልም በመልእክቱ ውስጥ እንዳለ ይመለከታሉ፤ ቢሆንም የካህናቱ ተቃውሞ ከተገለጠላቸው ብርሀን እንዲያሸሻቸው ይፈቅዱለታል፡፡ ምንም እንኳን አእምሮአቸውና ህሊናቸው ቢቀበልም እነዚህ የተታለሉ ነፍሳት ካህናት አገልጋዮቻቸው ከሚያምኑት እምነት የተለየ ለማመን አይደፍሩም፡፡ በመሆኑም የግል ውሳኔያቸውና ዘላለማዊ ፍላጎታቸው በሌላ ሰው ቁጥጥር ስር ሆኖአል፡፡ ታተ 52.4
ሰይጣን የእርሱ ምርኮኞች የሆኑትን አጥብቆ ለመያዝ በሰብአዊ ተፅዕኖ አማካኝነት የሚሰራባቸው ዘዴዎች በርካታ ናቸው፡፡ የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ከሆኑት ጋር በፍቅር የሃር ክር በማያያዝ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች የራሱ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ወዳጅነት በማንኛውም መልኩ ቢሆን (የወላጅና ተወላጅ ዝምድና፣ የትዳርም ሆነ የማህበራዊ ወዳጅነት) ውጤቱ ያው ነው፡፡ የእውነት ተቃዋሚዎች ህሊናን ለመግዛት (በቁጥጥር ስር ለማዋል) ኃይላቸውን ይጠቀማሉ፡፡ በእነርሱ ተፅዕኖ ስር የወደቁትም ነፍሳት ያመኑበትን ተቀብለው ግዴታቸውን በሥራ ላይ ለማዋል በቂ ድፍረት ወይም ነፃነት የላቸውም፡፡ ታተ 52.5
እውነትና የእግዚአብሔር ክብር የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችን እያለ በተሳሳቱ አስተያየቶች እግዚአብሔርን ማክበር የማይቻል ነው፡፡ ብዙ ሰዎች «የአንድ ሰው ሕይወት ቅንነት ካለው የፈለገውን ቢያምን ምንም የለበትም» ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሕይወት መልክ የሚያገኝው በእምነት ነው፡፡ መንፈሳዊ ብርሃንና እውነትን ለማግኘት እየቻልን እውነትን የማዳመጥና የማስተዋል ፍላጎታችንን ለማሻሻል ካልፈለግን፤ ፈቅደን አንቀበልም በማለታችን ከብርሃን ይልቅ ጨለማን እየመረጥን ነን ማለት ነው፡፡ «ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፣ መጨረሻዋ ግን ሞት ነው» (ምሳሌ 16፡25)፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ እየቻልን አለማወቅ ለምንሰራቸው ኃጢያቶችና ስህተቶች ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ ሰው ጉዞ በሚጓዝበት ጊዜ መንታ መንገድ አጋጠመው እንበል፤ በዚያም ቦታ መንገዶቹ ወደየት እንደሚያመሩ የሚያሳዩ በሁለቱም መንገዶች ላይ የተተከሉ ምልክቶች አሉ፡፡ ይህ ሰው ገሸሽ ብሎ በራሱ ግምት ልክ መስሎ የሚታየውን መንገድ ቢወስድ ራሱን በተሳሳተ መንገድ ላይ ያገኛል፡፡ ታተ 53.1
ከእርሱ ትምህርት ጋር እንድንተዋወቅ እና እርሱ ከእኛ ምን እንደሚጠይቅ እንድናውቅ ሲል እግዚአብሔር ቃሉን ሰጥቶናል፡፡ ከሙሴ ሕግ መምህሮች አንዱ ወደ ኢየሱስ መጥቶ «ዘላለማዊ ሕይወትን ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?» ብሎ በጠየቀበት ጊዜ መድሃኒታችን «በሕግ የተፃፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነበዋለህ?» በማለት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ አመላከተው፡፡ አለማወቅ ታናናሾችንም ሆነ ታላላቆችን ይቅር አያሰኝም፤ ወይም ደግሞ የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ ሳቢያ ከሚመጣ ቅጣት አያድናቸውም ምክንያቱም ህጉ፣ የህጉ መርህ እና ህጉ የሚጠይቀው ነገር ሁሉ በግልፅ ቀርቦላቸው በእጃቸው አለና፡፡ መልካም ሃሳብ ብቻ መያዝ በቂ አይደለም፡፡ ሰው ራሱ መልካም ነው ብሎ የሚያስበውን ወይም ቄሱ መልካም ነው ብሎ የሚያስተምረውን ማድረግ በቂ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለራሱ መመርመር አለበት አለበለዚያ የዚህ ሰው መዳን በአደጋ ላይ ይገኛል ማለት ነው፡፡ እውነቱ የቱንም ያህል ጠንካራ ቢሆን፣ በቄሱ እውነትን የማወቅ ችሎታ የፈለገውን ያህል ቢተማመንም የአንድ ሰው መሰረት ይህ ሊሆን አይገባም፡፡ ወደ ሰማይ ቤት ለመጓዝ የሚረዳው ካርታ ስላለው ምንም ነገር በግምት ማድረግ የለበትም፡፡ ታተ 53.2
የማመዛዘን ችሎታ ያለው ፍጡር ሁሉ እውነት ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ መማር፣ በተገለጠለት ብርሃን መመላለስና ሌሎችም የእርሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ማበረታታት የመጀመሪያውና እጅግ ከፍተኛ ተግባሩ መሆን አለበት፡፡ በየቀኑ እያንዳንዱን ሃሳብ በማመዛዘንና ጥቅስን ከጥቅስ ጋር እያነፃፀርን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት አለብን፡፡ ታተ 53.3
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልፅ የተፃፉት እውነቶች «ታላቅ ጥበብ አለን» በሚሉ ምሁራን «መጽሐፍ ቅዱስ አሁን በምንገለገልበት ቋንቋ ግልፅ ያልሆነ፣ ድብቅና ሚስጥራዊ ትርጉም (ትምህርት) አለው» እያሉ በማስተማር መጽሐፍ ቅዱስ በጥርጣሬ እና በጨለማ እንዲከበብ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ሃሳዊያን መምህራን ናቸው፡፡ «መጽሐፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁም ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን?» (ማር 12፡24) ብሎ የተናገረው እነዚህን ለመሰሉ ሰዎች ነው፡፡ በምሳሌ ወይም በስእላዊ አነጋገር ካልተፃፈ በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስ መብራራት ያለበት ግልፅ ሆኖ በተፃፈው ትርጉም መሰረት ነው፡፡ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተስፋ ሰጥቶናል፡- «ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ቢሆን ያውቃል፡፡» (ዮሐ. 7፡17)፡፡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚነበበው ብቻ ቢወስዱ ኖሮ፣ የሚያሳስቱና ግራ የሚያጋቡ የሃሰት መምህራን ባይገኙ ኖሮ መላእክትን ደስ የሚያሰኝና በስህተት ተዘፍቀው የሚንከራተቱትን እልፍ አእላፍ ሰዎች ወደ ክርሰቶስ በረት እንዲገቡ የሚያደርግ ተግባር በተከናወነ ነበር፡፡ ታተ 53.4
የተቻለንን ያህል ማስተዋል እንችል ዘንድ በአእምሮ የማሰብ ሃይላችንን ከፍ በማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እናጥና፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች ለማስተዋል እንድንችል በቀላሉ ሊያስተምሩትና ታዛዥ ባህርይ እንዳለው ህፃን ሆነን መቅረብ እንዳለብን እንወቅ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አስቸጋሪ ጥቅሶችን ለመረዳት ልክ የፍልስፍና ሚስጥሮችን ለመግለፅ በምንጠቀምባቸው መንገዶች አንጠቀም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና አስቀድመን ፀሎት በማድረግ፣ በእግዚአብሔር በመመካትና የእርሱንም ፈቃድ ለማወቅ በቅንነት በመሻት እንጂ ብዙ ሰዎች ሳይንስን ለማስተዋል ሲሉ እንደሚያደርጉት በራሳችን መተማመን የለብንም፡፡ በትህትናና ለመማር ፈቃደኛ በሆነ መንፈስ «እኔ ነኝ» ወዳለውና ታላቅ ወደሆነው ጌታ እንቅረብ፡፡ አለበለዚያ ክፉ መላእክት የእውነት ብርሃን በልባችን እንዳይቀረፅ አእምሮአችንን ይደፍናሉ፣ ልባችንንም ያደነድናሉ፡፡ ታተ 53.5
ብዙ ምሁራን «ሚስጥር ናቸው» ወይም «አይጠቅሙም» ብለው ያለፏቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በክርስቶስ ትምህርት ቤት ለተማረው ሰው ሙሉ መፅናኛና ጠቃሚ መመሪያዎች ናቸው፡፡ አያሌ የስነ መለኮት ሊቃውንት የእግዚአብሔርን ቃል በግልፅ የማይረዱበት አንዱ ምክንያት ተግባራዊ ለማድረግ ለማይፈልጉት እውነት አይናቸውን ስለሚጨፍኑ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተዋል የሚቻለው ጽድቅን ከልብ በመሻትና በመናፈቅ ላይ የተመረኮዘ ዓላማን ይዞ በመምጣት እንጅ በተፈጥሮ ብልህነት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ፀሎት በጭራሽ መጠናት የለበትም፡፡ በቀላሉ ሊስተዋሉ የሚችሉ ጥቅሶችን ጠቃሚነት እንድናስተውል የሚደረግ ወይም ደግሞ ለመረዳት የሚያስቸግሩትን ጥቅሶች እንዲስተዋሉን የሚያደርግና የተሳሳተ ትርጉም እንዳንሰጥ የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል እንድናስተውልና በቃሉ ውበት እንድንማረክ፣ በማስጠንቀቂያዎቹም እንድንገሰጽ፣ ወይም ደግሞ በተስፋ ቃሎቹ ሕይወት እንድናገኝና እንድንጠነክር ልቦቻችንን የሚያዘጋጁት የሰማይ መላእክት ናቸው፡፡ የዘማሪውን ተማጽኖ (ፀሎት) የራሳችን ማድረግ አለብን፡- «በሕግህ ውስጥ ያለውን አስደናቂ እውነት ማየት እንድችል አይኖቼን ክፈትልኝ» (መዝ 119፡18)፡፡ ታተ 53.6
ብዙውን ጊዜ ፈተና የማይቋቋሙት የሚሆነው፣ ፀሎትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ችላ በማለትና፣ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃላት ወዲያውኑ ለማስታወስ ባለመቻልና ተፈታኙ መጽሐፍ ቅዱስን መሳሪያው አድርጎ ሰይጣንን ስለማይጋፈጠው ነው፡፡ የእግዚአብሔር መላዕክት ግን ስነ መለኮትን ለመማር በሚፈቅዱ ሰዎች ዙሪያ ናቸው፡፡ እጅግ አስፈላጊ ወቅት በሚያጋጥምበት ጊዜም ለወቅቱ ጠቃሚ የሆነውን እውነት ሰዎች እንዲያስታውሱ ያደርጋሉ፡፡ በመሆኑም ጠላት እንደ ጎርፍ ፈሳሽ ቢመጣም የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ አርማውን ያነሳበታል (ኢሳ 59፡19)፡፡ ታተ 54.1
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ተስፋ ሰጥቶአል፡ «አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፣ የነገርኳችሁንም ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል» (ዮሐ 14፡26)፡፡ ነገር ግን በመከራ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንዲያሳስበን የምንፈልግ ከሆነ የክርስቶስ ትምህርት አስቀድሞ በአእምሮአችን የተቀመጠ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም ባለመዝሙሩ ዳዊት እንዲህ አለ፡- «አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርሁ» (መዝ 119፡11) ፡፡ ታተ 54.2
ለዘላለማዊ ሕይወታቸው ዋጋ የሚሰጡ ሁሉ ጥርጥር እንዳያሸንፋቸው ጥንቁቃን መሆን አለባቸው፡፡ የእውነት ምሶሶዎች (መሠረቶች) ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ፌዝ፣ ሽንገላ፣ ደባና አለማመን ካለበት ከዘመኑ የሐሰት ትምህርት ለመራቅ አይቻልም፡፡ ሰይጣን ለሁሉም መደቦች እንዲመች አድርጎ ፈተናውን ያቀርባል፡፡ መሃይሙን (ያልተማረውን) በዋዛ ፈዛዛ በቀላሉ በማታለል ያጠቃዋል የተማረውን ወገን ደግሞ ሳይንሳዊ ቅራኔዎች፣ የፍልስፍና ምክንያቶችን ይዞ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲጠራጠሩ ወይም ደግሞ ዋጋ እንዳይሰጡት በማድረግ ያጠቃቸዋል፡፡ እምብዛም የሕይወት ልምድ የሌላቸው ወጣቶች እንኳን ሳይቀሩ የክርስትናን መሠረታዊ አቋም በተመለከተ ጥርጣሬያቸውን በተዘዋዋሪ መንገድ ለመግለጽ ይነሳሉ፡፡ ይህም የወጣቶች አለማመን ጥራዝ ነጠቅ ቢሆንም ተጽእኖ አለው፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹ «የጸጋን መንፈስ እየናቁ» በአባቶቻቸው እምነት ላይ ያፌዛሉ (እብ 10፡29)፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ክብር ለዓለምም በረከት ይኖሩ ዘንድ ተስፋ የነበራቸው ብዙ ሕይወቶች በአለማመን መርዝ ተመርዘው ጠውልገው ይገኛሉ፡፡ ትምክህት በተሞላበት ሰብአዊ ሚዛን ውሳኔ የሚታመኑ መለኮታዊ ምስጢርን ለመግለጽ እንደሚችሉ በማሰብ የእግዚአብሔር ጥበብ ረድኤት ሳይኖርበት ወደ እውነት እንደርሳለን የሚሉ ሁሉ በሰይጣን ወጥመድ የተያዙ ናቸው፡፡ ታተ 54.3
እኛ አሁን የምንኖረው በዚህ ዓለም ታሪክ እጅግ አስፈሪ በሆነው ወቅት ነው፡፡ በምድር ላይ የሰፈሩት እልፍ አእላፍ ሰዎች ዕጣ ሊወሰን ተቃርቦአል፡፡ እኛ የራሳችን የወደፊት ድነት የተመረኮዘው በአሁኑ አካሄዳችን ላይ ነው፡፡ በእውነት መንፈስ መመራት ያስፈልገናል፡፡ እያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ ከልቡ «ጌታ ሆይ ምን እንዳደርግ ትፈቅዳለህ?» ብሎ መጠየቅ ይገባዋል፡፡ በጾምና በፀሎት ራሳችንን በጌታ ፊት ዝቅ ማድረግ፣ የእግዚአብሔር ቃልን በተለይ ደግሞ የፍርዱን ትእይንት ከልብ ማሰላሰል ያስፈልገናል፡፡ በስነ መለኮት የጠለቀና ሕያው የሆነ ልምምድ ይኖረን ዘንድ መሻት አለብን፡፡ አንድ አፍታ እንኳን እንዲሁ መባከን የለበትም፡፡ አበይት ሁኔታዎች በዙሪያችን እየተፈጸሙ ነው፡፡ እኛ ያለነው ዲያብሎስ በሚፈነድቅባት መሬት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጠባቆች አትተኙ! ባላጋራው አድፍጦ እየተቃረበ ነው፡፡ ዳተኞችና ያንቀላፋችሁ ስትሆኑም በእናንተ ላይ በመውደቅ ታድኖ እንደሚበላ እንስሳ ሊያደርጋችሁ በማናቸውም ወቅት ዝግጁ ነው፡፡ ታተ 54.4
ብዙዎች በእግዚአብሔር ፊት ስላላቸው ትክክለኛ ሁኔታ የተሳሳተ አመለካከት አላቸው፡፡ መጥፎ ነገሮችን ባለመሥራታቸው ይደሰታሉ ቢሆንም እግዚአብሔር ከእነርሱ የሚፈልገውን እነርሱ ግን ለመፈጸም ችላ ያሉትን መልካምና የተከበረ ተግባር መፈጸምን ይዘነጋሉ፡፡ እነርሱ የአፀደ እግዚአብሔር ዛፎች መሆናቸው ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ፍሬ በማፍራት እርሱ ከእነርሱ ለሚጠብቀው መልስ መስጠት የሚኖርባቸው ናቸው፡፡ የእርሱ ጸጋ በበዛላቸው ያህል ሊያከናውኗቸው የሚችሉአቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ ባለመፈጸማቸው እርሱ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች በሰማይ መጽሐፍት የተመዘገቡት እንደምድር ሸክም ነው፡፡ ሆኖም የእነዚህ ወገኖች ጉዳይም ቢሆን ፍጹም ተስፋ ቢስ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርን ምህረት ላቀለሉትና የእርሱንም ጸጋ ላረከሱት ሰዎች በትዕግስትና በፍቅር የተመላው የእግዚአብሔር ልብ ይማጸንላቸዋል፡፡ ስለዚህም ይላል፡- «አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሳ ክርስቶስም ያበራልሃል፣ . . . እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ» (ኤፌ. 5፡14-16) ታተ 54.5
ያ የፈተና ጊዜ ሲመጣ የእግዚአብሔርን ቃል የሕይወታቸው መመሪያ ያደረጉቱ ይገለጻሉ፡፡ በበጋ ወራት ወቅት ሁሌም ለምለም በሆኑትና በሌሎች ዛፎች መካከል ጎልቶ የሚታይ ልዩነት የለም፡፡ የክረምት ሃይለኛ ነፋስ ሲመጣ ግን ሁሌም ለምለም አትክልት መልካቸውን ሳይለውጡ ይቀራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ቅጠላቸው ይረግፍባቸዋል፡፡ ስለዚህ አስመሳይ ክርስቲያን አሁን ከእውነተኛ ክርስቲያን ተለይቶ ላይታወቅ ይችላል፡፡ ልዩነቱ የሚታይበት ጊዜ ግን ቀርቦአል፡፡ ተቃውሞ ይነሳ፣ ስደት መከራም ይምጣ፣ ሽብርም ይፋፋም ያን ጊዜ ግብዝና ገሚስ ልብ ያላቸው ሁሉ ግን ያወላውላሉ እምነታቸውንም ይተዋሉ፡፡ ሐቀኛው ክርስቲያን ግን በደህናው ጊዜ ካደረገው የበለጠ ተስፋው ይበልጥ ብሩህ ሆኖ፣ እምነቱ ጠንክሮ እንደ አለት ጸንቶ ይቆማል፡፡ ታተ 55.1
ባለ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፡- «ሕግህን ዘወትር አሰላስላለሁ» «ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ» (መዝ 119፡99,104)፡፡ «ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው» «በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሰጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል» (ምሳሌ 3፡13 እና ኤር 17፡8)፡፡ ታተ 55.2