ታላቁ ተስፋ
ከፊታችን የሚጠብቀን ተጋድሎ
ታላቁ ተጋድሎ በሰማይ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የእግዚአብሔርን ሕግ ገልብጦ መጣል የሰይጣን ዓላማ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በፈጣሪ ላይ ያመጸውም ይህንን ዓላማውን ለመፈጸም ነበር፡፡ እርሱ ከሰማይ ቤት እንዲወጣ ቢደረግም ያንኑ በሰማይ የጀመረውን ተጋድሎ በምድር ላይ ማካሄዱን ቀጠለበት፡፡ ሰዎችን ማሳሳት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲተላለፉ ማድረግ የእርሱ አቢይ ዓላማ ነው፡፡ ሕጉን በሙሉ ማፍረስም ሆነ ወይም ከትእዛዛቱ አንዱን እንዲጥሉ ማድረግ ውጤቱ ተመሳሳይ ስለሆነ ዓላማው ተከናወነለት ማለት ነው፡፡ «ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ቢኖር» ለሕግጋቱ በሙሉ አለመታዘዙን ይገልጻል፡፡ «በሁሉም በደለኛ ይሆናልና» (ያዕ 2:10)፡፡ ታተ 46.1
ሰዎች መለኮታዊውን ሕግ እንዲንቁት በመሻት ሰይጣን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲወላገድ አድርጎአል፡፡ ብዙ ስህተቶችም «የእግዚአብሔርን ቃል እናምናለን» ከሚሉ ከብዙዎች ሰዎች እምነት ጋር ሳይቀር ተዋህደዋል፡፡ በእውነትና በሐሰት መሃከል ያለው የመጨረሻው ታላቅ ተቃርኖ የእግዚአብሔርን ሕግ በተመለከተ የረዥም ጊዜ ትግል ነው፡፡ ወደዚህም ተጋድሎ በመግባት ላይ ነን ይህም ተጋድሎ በሰዎች ሕግጋትና በእግዚአብሔር አምላክ ትዕዛዛት መካከል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖትና በባሕላዊና በልማድ ላይ በተመሠረተ ሃይማኖት መሃከል የሚካሄደው ተጋድሎ ነው፡፡ ታተ 46.2
እውነትንና ጽድቅን ለመቃወም ሕብረት ፈጥረው የሚነሱ ወኪሎች አሁን በታታሪነት ሥራቸውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በስቃይ እና በደም መስዋእትነት የተሰጠን የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ፋይዳ እንደሌለው ዋጋቢስ ነገር ተቆጥሮአል፡፡ ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስን ማንም ሊያገኘውና ሊቀበለው ይችላል፡፡ ነገር ግን የሕይወት መመሪያ አድርገው በልባቸው የሚቀበሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በዓለማዊያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ እምነት-አልባነት በሚያስደነግጥ ሁኔታ ነግሦአል፡፡ ብዙዎች የክርስትና ሃይማኖት ምሶሶ የሆኑትን ትምህርቶች ክደዋል፡፡ በእግዚአብሔር መንፈስ የተመሩ ጸሐፊያን ያቀረቡት የፍጥረትን፣ የሰው አወዳደቅ፣ የመስቀሉ እርቅና የእግዚአብሔር ሕግ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር መሆኑን የሚመሰክሩ እውነቶች ሙሉ በሙሉ ወይም ግማሽ በግማሽ በብዙዎች «ክርስቲያኖች ነን» ባዮች ተቀባይነትን አጥተዋል፡፡ በጥበባቸውና በነጻነታቸው የሚኮሩ በብዙ ሺ የሚገመቱ አስመሳይ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ መታመንን የደካምነት ማስረጃ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ በቃለ እግዚአብሔር ላይ ማሾፍና የራሳቸውን ጥራዝ ነጠቅ ሐቅ መንፈሳዊ አስመስሎ ማቅረብና መግለጽ ብልጫ ያለው ማስረጃ ትምህርት የመያዝ ማስረጃ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ አያሌ ካህናት መንጎቻቸውን፣ ሊቃውንትና መምህራንም ተማሪዎቻቸውን «የእግዚአብሔር ሕግ ተለውጧል፣ ተሽሯል” እያሉ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የእግዚአብሔር ትእዛዝ አሁንም ያልተሻሩ መሆናቸውን፣ መከበርም እንደሚገባቸው የሚያስቡ ሰዎች ደግሞ ፌዝና ውርደት የሚገባቸው ናቸው ተብለው ይታሰባሉ፡፡ ታተ 46.3
ሰዎች እውነትን ውድቅ በሚያደርጉበት ጊዜ የእውነትን ደራሲ እግዚአብሔርን ውድቅ ያደርጋሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ በሚረግጡበት ወቅት የሕግ አውጭውን ስልጣን ይክዳሉ፡፡ ከእንጨትና ከድንጋይ ጣዖትን ቀርጾ ለማውጣት እንደሚቀል፣ የሐሰት ትምህርቶችንና ቲዮሪዎችን ጣዖት ለማድረግም እንደዚሁ የቀለለ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሃሰት በማንቋሸሽ ሰይጣን ሰዎችን ጌታ መጥፎ ጸባይ ያለው አስመስለው እንዲያስቡና የፈጣሪያቸውን እውነተኛ ባህርይ እንዳይገነዘቡ ይረዳቸዋል፡፡ በእግዚአብሔር ፈንታ የፍልስፍና ጣኦቶች ሞልተዋል፡፡ በቃሉ የተገለጸው፤ በክርስቶስ ያታየውና በፍጥረታቱ ሃያልነቱ የተገለጸው ህያው የሆነው እግዚአብሔር ግን በጥቂቶቹ ብቻ ሲመለክ ይታያል፡፡ ሰዎች ፍጥረትን እንደ እግዚአብሔር ሲያመልኩ የፍጥረት ሁሉ አምላክ የሆነውን ግን ይክዳሉ፡፡ ምንም እንኳ የተለየ መልክ ቢኖረውም በዘመነ ኤልያስ በጥንታዊቱ እስራኤል የነበረው የጣኦት አምልኮ አይነት በዛሬው የክርስትና ሃይማኖት ውስጥም ይታያል፡፡ የብዙዎች ጠቢባን ፈላስፎች ባለቅኔዎች ፖለቲከኞች ጋዜጠኞች አምላክ የብዙ ኮሌጆች ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም አንዳንድ መንፈሳዊ ተቋማት አምላክ የፎኒሽያ (Phoenicia) የጸሐይ አምላክ ከሆነው በኣል የሚሻለው ጥቂት ብቻ ነው፡፡ ታተ 46.4
በክርስቲያኑ ዓለም ውስጥ ተቀባይነት ያገኘ ማንኛውም ሃሰት መለኮታዊ ስልጣንን ሊቃወም አይችልም፡፡ «የእግዚአብሔር ሕግ በሰዎች ላይ አይጸናም” ከሚለው ዘመናዊ ትምህርት ሌላ ግልጽ በግልጽ ተቃውሞ የሚያጋጥመውና ውጤቱ የከፋ የሆነ ነገር የለም፡፡ እያንዳንዱ አገር የሚያከብረውና እንዲታዘዝለትም ያወጣው ሕግ አለ፡፡ ያለ ሕግ መኖር የሚችል መንግስትም የለም፡፡ እንዲህስ ከሆነ ሰማይና ምድርን የፈጠረ አምላክ የፈጠራቸውን ሰዎች የሚያስተዳድርበት ደንብ የለውም ተብሎ ሊታሰብ ይችላልን? ለምሳሌ ያህል ታላላቅ አገልጋዮች አገራቸውን ለማስተዳደር እና የዜጎቻቸውን መብት ለመጠበቅ ያወጡት ሕግጋት የሰዎችን የማክበር ግዴታ እንደማይጠይቁ፤ ሕግጋቱ የህዝቡን ነጻነት የሚነፍጉ በመሆናቸው መከበር እንደማይገባቸው በግልጽ ሲሰብኩ እንዲህ አይነቶቹ መምህራን ለምን ያህል ጊዜ ነው በመድረክ ላይ እንዲያስተምሩ በትእግስት የሚታለፉት? ታዲያ የአገራትን ሕግ መናቅ የመንግስታትን ሁሉ መሰረት የሆነውን መለኮታዊ ሕግን ከመርገጥ የበለጠ ያሳዝናልን? ታተ 47.1
የዓለማት ሁሉ ንጉሥ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ ህጉን ሽሮ ጥፋተኛውን የሚኮነንበትን ወይም ትእዛዝ አክባሪውን የሚያጸድቅበትን የፍርድ ሚዛን ከሚያስወግድ መንግስታት ሕግጋታቸውን ሽረው ህዝባቸው የፈቀደውን እንዲያደርግ ቢተውት ይመረጣል፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ መሻር የሚያስከትለውን ውጤት እናውቃለን? ከዚህ በፊት ተሞክሮ ነበር፡፡ ክህደተ እግዚአብሔር ፈረንሳይን በቁጥጥሩ ስር ባደረገ ጊዜ የተፈጸመው ሁኔታ አሰቃቂ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያስቀመጠውን መቆጣጠሪያ ማፍረስ (ማስወገድ) የጨካኞችን ገዢነት መቀበል መሆኑን በዚያን ጊዜ ለዓለም ታይቷል፡፡ የጽድቅ ሚዛን በሚሻርበት ጊዜ የክፋት ልዑል ዲያቢሎስ ስልጣኑን በምድር ላይ ይመሰርት ዘንድ መንገዱ ክፍት ይሆንለታል፡፡ ታተ 47.2
መለኮታዊው ሕግ በሚናቅበት ጊዜ ኃጥያት ኃጥያት መስሎ አይታይም፤ ጽድቅም ተፈላጊነት አይኖረውም፡፡ ለእግዚአብሔር መንግስት የማይገቡ ሰዎች ራሳቸውን ለመግዛት ፈጽሞ የማይቻላቸው ናቸው፡፡ በእነርሱ ጠንቀኛ ትምህርት አማካኝነትም በልጆቻቸውና በወጣቶቻቸው ልብ ያለመታዘዝ መንፈስ ይተካል፡፡ በዚህ አማካኝነት ሕገ-ቢስና ስርዓት አልባ ህብረተሰብ ይፈጠራል፡፡ ታተ 47.3
የእግዚአብሔርን ሕግ በማክበር በእምነታቸው ጽኑ በሆኑት ላይ በማፌዝ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች የዲያቢሎስን ሽንገላ በጉጉት ይቀበላሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ አቅልለው እንዲመለከቱ ህዝቡን የሚያስተምሩ ሰዎች ያለመታዘዝን ፍሬ ለመልቀም ያለመታዘዝን ዘር የበተኑ ናቸው፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲንቁ የሚያስተምር ሰው አመጻን ዘርቶ አመጻን ያጭዳል፡፡ በመለኮታዊ ህጎች ውስጥ የተደነገጉት ገደቦች በሙሉ ሲሻሩ ጥቂት ቆይቶ በሰው የተሰጡትን ሕግጋት የሚያከብር አይኖርም፡፡ ታማኝነት የሌላቸውን ድርጊቶች የሰውን ሀብት መመኘትን ሀሰትንና ማታለልን እግዚአብሔር ስለሚከለክል፤ ሰዎች ለምድራዊ ብልጽግናቸው መሰናክል የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ ይረግጣሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት ከመጣስ የሚገኘው ውጤት እነርሱ ያልጠበቁትን ነገር ያመጣባቸዋል፡፡ ሕግ በሰዎች ላይ የሚጸና ባይሆን ኖሮ ለምን አንድ ሰው ለመተላለፍ ይፈራል? የእግዚአብሔር ሕግ በሚረገጥበት ጊዜ ንብረት ዋስትና አይኖረውም፡፡ ሰዎች የጎረቤቶቻቸውን ንብረት በጉልበት ይነጥቃሉ፡፡ በኃይል የበረታውም ሰው ከሌሎቹ ሁሉ የበለጠ ባለጸጋ ይሆናል፡፡ ሕይወት ራስዋ የተከበረች አትሆንም፡፡ የጋብቻ ቃልኪዳን ቤተሰብን በሚገባ የሚጠብቅ ቅዱስ ደንብ ሆኖ አይቆይም፡፡ ኃይልና ስልጣን ያለው ከፈለገ የጎረቤቱን ሚስት አስገድዶ ሊወስድ ይችላል፡፡ አምስተኛው ትዕዛዝ ከአራተኛው ትዕዛዝ ጋር አብሮ ይሻራል፡፡ ልጆች በምግባረ-ብልሹነት የደነደነውን የልባቸውን ምኞት ለማሳካት ከቻሉ፤ የወላጆቻቸውን ሕይወት ከማጥፋት አይመለሱም፡፡ የሰለጠኑት አለማት የቀማኞችና የነፍሰ ገዳዮች መንጋ ይሆናሉ፡፡ ሰላም፤ደስታና እረፍት ከዚህ ምድር ይጠፋሉ፡፡ ታተ 47.4
«ሰዎች የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ከመታዘዝ ነጻ ወጥተዋል» የሚለው ትምህርት የግብረ-ገብነትን ግዴታ አድክሟል፡፡ በዓለም ላይም አመጻ እንዲበዛ በርን ከፍቷል፡፡ ስርዓተ-አልባነት፤ ብኩንነትና የአመጽ ሥራ እንደሚያስፈራራ የማዕበል ጎርፍ አጥለቅልቀውናል፡፡ በቤተሰብ ውስጥም ሰይጣን በሥራ ላይ ነው፡፡ «ክርስትያን ነን» በሚሉ ቤቶችም እንኳን ሳይቀር ሰንደቅ ዓላማውን ያውለበልባል፡፡ በእነዚህ አይነት ቤተሰብ ውስጥ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ሁከት፣ ግብዝነት፣ አለመጣጣም፣ ፉክክር፣ መካካድ፣ ስግብግብነትና ከመጠን ያለፈ ምኞት ይታያል፡፡ ታተ 47.5
ወንጀል በመሥራታቸው ምክንያት በእስር ቤት የሚገኙት ከባድ ወንጀለኞች አብዛኛውን ጊዜ ትልቅ ጀብዱ እንደሰራ ጀግና ስጦታና ምስጋና ሲሰጣቸው ይታያል፡፡ በሰሩት ወንጀልና ባሳዩት መጥፎ ጸባይ በህዝብ ፊት ሞገስ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ጋዜጠኞች አንድ ወንጀለኛ የሰራውን ወንጀል በዝርዝሩ በመጻፍ ሌሎችም እንደዚሁ የማታለል፤ የንጥቂያና የነፍስ ግድያ ሥራ እንዲሠሩ መንገድ ይከፍታሉ፡፡ ሰይጣን ይህ ሲኦላዊ መርሀ ግብሩ ስለተከናወነለት ይደሰታል፡፡ ወንጀልን የመሥራት ፍቅር፣ ግድያን የመፈጸም የጋለ ፍላጎት፣ ራስን ያለመግዛትና የአመጽ መብዛት የእግዚአብሔር ሰዎች «ይህንን የክፋት ማዕበል ለመቋቋም ምን ማድረግ ይቻላል?» የሚለውን ጥያቄ እንዲጠይቁና እንዲመረምሩ ሊያነሳሳቸው ይገባል፡፡ ታተ 47.6
ፍርድ ቤቶች ተበላሽተዋል (ተበክለዋል)፡፡ መሪዎች በሥጋዊ ደስታና በማካበት ፍላጎት ተይዘዋል፡፡ ራስን ያለመግዛት የብዙዎችን አእምሮ አበላሸ፣ ከዚህም የተነሳ ሰይጣን ሰዎችን ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠራቸው ትንሽ ቀርቶታል፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ከትክክለኛው መንገድ ርቀዋል፡፡ ጉበኞችና የሚሸነግሉም ሆነዋል፡፡ ሰካራምነትና ጸብ፣ ስሜታዊ ምኞትና ምቀኝነት እንዲሁም ሃቀቢስነትና ክፉ ሥራዎች ሕግን በሚፈጽሙ ግለሰቦች መካከል ይገኛሉ፡፡ ነብዩ ኢሳያስ እንዲህ ብሎ ነበር፡- «ፍትህ ከኛ ርቋል፣ ጽድቅም በሩቁ ቆሟል፣ እውነት በመንገድ ላይ ተሰናክሏል፣ ቅንነትም መግባት አልቻለም» (ኢሳ 59፡14)፡፡ ታተ 48.1
በታላቋ ሮም ቤ/ክ ጊዜ እያደገ የመጣው አመጻና መንፈሳዊ ጽልመት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መጨቆን አይቀሬ ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን በሃይማኖት ነጻነት ዘመን፣ የወንጌል ብርሃን እያበራ ባለበት ጊዜ፣ አለማቀፋዊ የሆነ እምነተ ቢስነት፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አለመቀበልና በዛም ምክንያት የመጣው ምግባረ ብልሹነት መንስኤ ምን ይሆን? ዛሬ ሰይጣን ሰዎች መጸሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡ በመከልከል ዓለምን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ስለማይችል፤ ያንኑ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ሌላ ብልሀት ይፈልጋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለውን ዕምነት ማጥፋት ራሱን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥፋት ስለሆነ ይህንን ግቡን ለመምታት ይጥራል፡፡ ታተ 48.2
«የእግዚአብሔር ሕግ በሰዎች ላይ አይጸናም» የሚለውን በማስተማር ሰዎች ትዕዛዙን ፈጽሞ ሰምተው እንዳላወቁ ያህል እንዲተላለፉት ይመራቸዋል፡፡ በድሮ ጊዜ እንዳደረገው አሁንም ዓላማውን ለመፈጸም ቤተ ክርስቲያኒቱን መሳሪያ በማድረግ ይጠቀማል፡፡ የዘመኑ የሃይማኖት ድርጅቶች በመጸሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጽ ሆነው የተቀመጡትንና በብዙ ሰዎች ታዋቂነት የሌላቸውን እውነቶች ላለመቀበል ወሰኑ፡፡ በአንጻሩም የራሳቸውን ትርጉም በማበጀት የጥርጣሬ ዘር የሚዘራባቸውን አቋሞች ያዙ፡፡ «ሰው ሲሞት ነፍሱ ህያው ነች» «ሰው ከሞተ በኋላ የሚያደርገውን ያውቃል» የሚለውን ጳጳሳዊ የሃሰት ትምህርት አጥብቆ በመያዝ እነርሱን ከ «ስፒሪቲዝም» (spiritism) የማታለል ሥራ ሊጠብቃቸው (ሊከላከላቸው) ይችል የነበረውን እውነት ካዱ (ጣሉ)፡፡ ስለ ዘላለማዊ ስቃይ የሚሰበከው ትምህርት ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጠራጠሩ መርቷቸዋል (አድርጎአቸዋል)፡፡ ታተ 48.3
የአራተኛው ትዕዛዝ ትርጉም ለሰዎች ግልጽ በሚደረግላቸው ጊዜ እና ሰዎች ሰባተኛውን ቀን ሰንበትን (ቅዳሜን) የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ግልጽ በሚሆንበት ጊዜ ያኔ ብዙ ታዋቂና ዝነኛ መምህራን ትዕዛዙን መጠበቅ ስለማይፈልጉ «የእግዚአብሔርን ሕግ የመጠበቅ ግዴታ የለብንም፣ የእግዚአብሔር ሕግ ተሽሯል፣ መጠበቅም አያስፈልግም» በማለት ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ይሞክራሉ፡፡ በዚህም አኳኋን ሕግንና ሰንበትን አንድ ላይ ውድቅ ያደርጋሉ፡፡ ሰንበትን መልሶ የማቆም (የማደሰ) እንቅስቃሴ እየተስፋፋ በሚመጣበት ጊዜ ይህንን አራተኛ ትዕዛዝ የሚለውን ላለማሟላት ብቻ ሲባል የመለኮታዊውን ሕግ ማጥላላትና መካድ የተለመደ ነገር ይሆናል፡፡ ታተ 48.4
ሃላፊነት ያላቸው የሃይማኖት መሪዎች የሚያስተምሩት ትምህርት ለዕምነተ ቢስነት ለ ስፒሪቲዝም እና የእግዘአብሔርን ቅዱስ ሕግ ለመናቅ በር ከፍቷል፡፡ በክርስቲያኑ ዓለም ለሚታየው አመጽ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ከባድ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ እንዲያውም እነዚህ መሪዎች «እንደዚህ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው ብልሹነት የመጣው የክርስቲያኖችን ሰንበት (እሁድን) የማርከስ ምክንያት ነው» ብለው ይናገራሉ፡፡ «እሁድን የመጠበቅ ግዴታም የህብረተሰቡን የሞራል ሁኔታ በብዙ ያሻሽለዋል» በማለት ይመክራሉ፡፡ ይህ አባባል በተለይ የዕውነተኛው የሰንበት ዕውነት ትምህርት በተሰበከባት በአሜሪካ አገር በይፋ ይነገራል፡፡ በዚሁ አገር ስነ-ምግባርን (ሞራልን) ለማሻሻል ጠቃሚ መሳሪያ የሆነውን የመሻትን መግዛት (ቴምፔራንስ) ትምህርት ብዙ ጊዜ ከእሁድ እንቅስቃሴ ጋር በማዋሀድ ይቀርባል፡፡ ታተ 48.5
አነዚህ የእሁድን እንቅስቃሴ የሚካያሂዱት ሰዎች «የህብረተሰቡን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላት እየሰራን ነን» ይላሉ፡፡ ከእነርሱ ጋር ለመተባበር ያልፈለጉቱ ደግሞ «የመሻትን መግዛትና የተሀድሶ ጠላቶች ናቸው» ተብለው ይወገዛሉ፡፡ ነገር ግን ሃሰትን ለማቋቋም (ለማስፋፋት) ሲባል መልካም ከሆነው ዓላማ ጋር አንድ የመደረጉ እውነት ሃሰቱን ለመደገፍ የሚረዳ ማስረጃ አይደለም፡፡ መርዝን ከደህና ምግብ ጋር በመደባለቅ ልንሸፍነውና ልንደብቅው እንችላለን፤ የመርዝነት ባህርይውን ግን ልንቀይረው አንችልም፡፡ እንዲያውም ያላወቁት እንዳለ ሊመገቡት ስለሚችሉ የበለጠ አደገኛ ነው፡፡ ሰዎችን ለማሳመን ብዙ ሃሰትን ከጥቂት እውነት ጋር መቀላቀል ሰይጣን ሰዎችን የሚያታልልበት መሳሪያው ነው፡፡ የእሁድ እንቅስቃሴ መሪዎች ህዝቡ የሚፈልገውን የተሀድሶ እንቅስቃሴ እና ከመጸሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማውን መሰረታዊ ትምህርት ሊያስተምሩ ይችላሉ፤ ቢሆንም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚቃወም መመሪያዎችን ስለሚያወጡ የጌታ ባሪያዎች ከእነርሱ ጋር መተባበር የለባቸውም፡፡ የሰዎችን ደንቦች (ወጎች) ለመቀበል ሲባል የእግዚአብሔር ትዕዛዝ የሚሻርበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ ታተ 48.6
በሁለቱ ታላላቅ የሃሰት ትምህርቶች ማለትም «ነፍስ ህያው ነች አትሞትም» በሚለውና «እሁድ ቅዱስ ሰንበት ናት» በሚለው ትምህርቱ ሰይጣን ሰዎችን ያስታል፡፡ «ነፍስ ህያው ነች አትሞትም» የሚለው ትምህርት መናፍስትን ለመሳብ (ስፒሪቲዝም) መሰረትን ሲጥል የእሁድ ቅዱስነት ደግሞ ከሮም ጋር የስምምነት መተሳሰሪያን ከፍቷል፡፡ የአሜሪካ ፕሮቴስታንቶች መናፍስትን የመሳብ ትምህርትን ለመቀበልና ከባህረ ሰላጤ ባሻገር እጃቸውን በመዘርጋት ከሮማዊው ስልጣን ጋር ይሆናሉ፡፡ በዚህም ሥሉስ ህብረት (ሮም አሜሪካ ስፒሪቲዝም) ተጽእኖ አማካኝነት አሜሪካ የህሊና ነጻነትን በመርገጥ የሮምን ዱካ ትከተላለች፡፡ ታተ 48.7
የመናፍስታዊነት (ስፒሪቲዝም) ትምህርት ከዘመኑ አስመሳይ የክርስትና ኑሮ ጋር በሚዋሃድበት ጊዜ ሰዎችን ለማሳሳትና ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት ታላቅ ኃይል ይኖረዋል፡፡ ሰይጣን ጊዜውን ለመምሰል ይለወጣል፡፡ በብርሃን መልአክ ተመስሎ ይቀርባል፡፡ በስፒሪቲዝም መሳሪያ አማካኝነት ተአምራት ይደረጋሉ፣ በሽተኞች ይፈወሳሉ፣ አያሌ ሊካዱ የማይችሉ ተአምራት ይሰራሉ፡፡ መናፍስቶቹም «መጸሐፍ ቅዱስን እናምናለን» ስለሚሉና ለቤተ ክርስትያን ስርዓትም ስለሚታዘዙ ሥራቸው በመለኮታዊ ስልጣን እንደተገለጸ ሆኖ ተቀባይነትን ያገኛል፡፡ በሐቀኛ ክርስትያኖችና በማያምኑት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ከባድ ይሆናል፡፡ አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስትያን አባላት ዓለም የሚወደውን ይወዳሉ፣ ከዓለማዊያን ጋር ለመተባበርም ዝግጁ ናቸው፡፡ ሰይጣንም ዓላማውን ለማጠናከር እነርሱን አንድ አካል በማድረግ ስፒሪቲዝምን ለማስፋፋት ቆርጦ ተነስቷል፡፡ «ተአምራት የእውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ምልክት ነው» የሚሉ ካቶሊኮች በእነዚህ የተአምር ሥራዎች ይታለላሉ፡፡ የእውነትን ጋሻ አሽቀንጥረው የጣሉት ፕሮቴስታንቶችም እንዲሁ ይታለላሉ፡፡ ካቶሊኮች፣ ፕሮቴስታንቶች እና ዓለማዊያን ኃይሉን ክደው የአምልኮትን መልክ (የሃይማኖተኝነትን መልክ) ይቀበላሉ፡፡ በዚህም ህብረት (አንድነት) አማካኝነት ዓለምን የሚለውጥና ለረጅም ጊዜ ሲጠባበቁት የነበረው ሺህ ዓመት የሚጀመርበት እንቅስቃሴ ዘመን እንደሆነ ይሰማቸዋል (ይገምታሉ)፡፡ በስፒሪቲዝም ትምህርት (ከርኩሳን መናፍስት ጋር የሚደረግ ግንኙነት) አማካኝነት ሰይጣን ሰዎችን የሚጠቅም መስሎ ይታያል (ይቀርባል)፡፡ የህዝቡን በሽታ ለመፈወስ የተሻለ ሃይማኖት ያመጣ በማስመሰል እንደ አጥፊ ሆኖ ይሰራል፡፡ በዚህ የማታለል ሥራው በብዙ የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ጥፋት ይመራል፡፡ ራስን መቆጣጠር አለመቻል የማመዛዘን ችሎታን ከማስወገዱ ባሻገር እርኩስነትን፣ ጸብና ደም መፋሰስን አስከትሏል፡፡ ሰይጣን በጦርነት ይደሰታል፤ አንዱ መንግስት በሌላው መንግስት ላይ ጦርነት እንዲያስነሳ ይቀሰቅሳል፡፡ በዚህም አማካኝነት የሰዎችን አስተሳሰብ በማዘናጋት ለእግዚአብሔር ፍርድ ቀን እንዳይዘጋጁ ያደርጋል፡፡ ታተ 49.1
ሰይጣን በወኪሎቹ አማካኝነት ያልተዘጋጁትን ነፍሳት እንደ ሰብል ለመሰብሰብ ይተጋል፡፡ እሱ የተፈጥሮን ሚስጥር ጠንቅቆ አጥንቷል፡፡ እግዚአብሔር እስከፈቀደለት ደረጃም ድረስ ማንኛውንም ነገር በቁጥጥሩ ስር ለማዋል ያለ የሌለውን ሃይል ይጠቀማል፡፡ እዮብን እንዲያሰቃይ በተፈቀደለት ጊዜ ከመቅጽበት አከታትሎ መንጋውን፣ አገልጋዮቹን፣ ቤቱን እና ልጆቹን አጠፋበት፡፡ ፍጥረታትን ሁሉ የሚጠብቅ ከአጥፊውም ኃይል የሚከላከል እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የክርስትያኑ ዓለም የእግዚአብሔርን ሕግ ቸል አሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እርሱ «አደርገዋለሁ» ያለውን ይፈጽማል፣ በረከቱን ከምድር ያነሳል፣ ህጉን በመቃወም በሚያምጹትና ሌሎችም የነርሱን ክፉ ሥራ እንዲሰሩ በሚያስገድዱት ላይ ያለውን የጥበቃ አጁን ያነሳል፡፡ በእግዚአብሔር ጥበቃ (ክልል) ስር ያልሆኑት ሁሉ በሰይጣን ቁጥጥር ስር ይውላሉ፡፡ ዓላማውን ለማካሄድ ሲል ሰይጣን ጥቂቶችን ይወዳል፣ ያበለጽጋልም፤ በሌሎች ላይ ደግሞ መከራን በማምጣት፤ ይህንን መከራ ያመጣባቸው እና የሚቀጣቸው እግዚአብሔር እንደሆነ እንዲያምኑ ያደርጋል፡፡ በአንድ በኩል በሽታውን ሁሉ የሚያድን ሐኪም መስሎ ለሰው ሲታይ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሽታንና መቅሰፍትን ያመጣል፡፡ ታላላቅ ከተሞች እንኳን እስኪደመሰሱና ምድረ በዳ እስኪሆኑ ድረስ ጥፋትን ያመጣል፡፡ አሁን እንኳን ሳይቀር በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ በባህርና በየብስ የአደጋ መቅሰፍት፣ በታላቅ የሰደድ እሳት፣ በሃይለኛ አውሎ ነፋስ እና ዝናም፣ ጎርፍ፣ ማዕበልና የመሬት መናወጥ በማስከተል ሃይሉን ይጠቀምበታል፡፡ የደረሰውን አዝመራ ጠራርጎ ይወስዳል፣ ረሃብንና ችግርን ያስከትላል፣ አየሩን በመጥፎ መርዝ በመበከል አእላፍ ፍጡራንን በወረርሽኝ ይጨርሳል፡፡ እነዚህ እና የመሳሰሉት መአቶች ተደጋጋሚና አስከፊ እየሆኑ ይመጣሉ፡፡ «ምድር አለቀሰች፣ ረገፈችም፣ ዓለም ደከመች፣ ረገፈችም የምድርም ህዝብ ታላላቆች ደከሙ፡፡ ምድርም ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች፣ ህጉን ተላልፈዋልና ስርአቱንም ለውጠዋልና የዘላለሙን ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና» (ኢሳ 24፡4-5) ታተ 49.2
በዚያን ጊዜ «ለዚህ ሁሉ ክፋት መንስኤ የሆኑት እግዚአብሔርን የሚያገለግሉት ሰዎች ናቸው» በማለት ታላቁ አታላይ ህዝቡን ያሳምናል፡፡ እግዚአብሔርን ያሳዘኑት ነፍሳት (ሰዎች) የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በሚያከብሩት ምዕመናን ላይ ያሳብባሉ፡፡ «ሰዎች የእሁድን ሰንበትነት ባለማክበራቸው እግዚአብሔርን በማሳዘን ላይ ናቸው» ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህም ኃጢአት መከራ ማስከተሉን እንደማያቋርጥና እሁድ እስካልተባረከችና እንድትከበር የሚያስገድደው ሕግ እስካልወጣ ድረስ እንደሚቀጥል ይነገራል፡፡ ከዚያም እነዚያ እሁድን አርክሰው እውነተኛውን ሰንበት የሚጠብቁ ሰዎች «በህዝቡ ላይ መከራ የሚያመጡና ምድር እንዳትበለጽግ እንቅፋት የሆኑ ናቸው» ይባላል፡፡ በዚህም አኳኋን ጥንት በእግዚአብሔር ባሪያዎች ላይ የተነሳው ክስ አሁን እንደገና በተመሳሳይ ሁኔታ ይደገማል፤ «አክአብም ኤልያስን ባየው ጊዜ እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን? አለው፡፡ ኤልያስም፡- እስራኤልን የምትገለባብጡ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ትታችሁ በኦሊምን የተከተላችሁ አንተ እና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጅ እኔ አይደለሁም» (1ኛ. ነገስት 18፡ 17-18)፡፡ በሃሰት ውንጀላ ቀስቃሽነት የህዝቡ ቁጣ ሲነሳሳ፤ ከሃዲዋ እስራኤል በኤልያስ ላይ እንደፈጸመችው ሁሉ እነርሱም በተመሳሳይ መልክ በእግዚአብሔር አገልጋዮች ላይ ያንኑ ያደርጋሉ፡፡ ታተ 49.3
በሲፒሪቲዝም አማካኝነት የሚደረገው ተአምራዊ ኃይል ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን በሚመርጡ ሰዎች ላይ ተጽእኖውን ያደርጋል፡፡ መናፍስቶች «እሁድን አናከብርም ብለው የተሳሳቱትን እንድናሳምን እግዚአብሔር ልኮናል፤ የመንግስት ትዕዛዞችም እንደ እግዚአብሔር ትዕዛዝ መቆጠር አለባቸው» ብለው ይናገራሉ፡፡ እነርሱም በዓለም ላይ ስላለው ታላቅ ክፋት በማዘን «ይህ እየዘቀጠ የመጣው የሞራል ብልሽት እሁድን ከማርከስ የተነሳ ነው» የሚለውን የሃይማኖት መሪዎች ምክር ይደግፋሉ፡፡ የእነርሱን ምስክርነት ለመቀበል በማይፈቅዱት ላይ ቁጣ ይነሳል፡፡ ታተ 50.1
ሰይጣን ከእግዚአብሔር ሰዎች ጋር በሚያደርገው ተጋድሎ የሚጠቀመው መርህ በታላቁ ተጋድሎ መክፈቻ ጊዜ ከነበረው መርህ ጋር የተመሳሰለ ነው፡፡ ሉሲፈር ያኔ መለኮታዊውን መንግስት ለመገልበጥ በስውር እየዶለተ ሳለ የመለኮታዊውን መንግስት ጽናት እንደሚሻ ይናገር ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ይፈጽመው የነበረውን ብርቱ ጥረት ታማኞች መላዕክት እንዲሰሩት አታለለ፡፡ ተመሳሳዩን የማሳሳት መርህ (ፖሊሲ) በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ እንደዋለ ታሪክ ይገልጻል፡፡ በሮም አገዛዝ ስር ወንጌልን በማመን በመጽናታቸው ምክንያት ሞት የተፈረደባቸው «ክፉ አድራጊዎች ናቸው» ተብለው ይወገዙ ነበር፡፡ «እነርሱ ከሰይጣን ጋር ህብረት አላቸው» በማለት በህዝብ አይንና ለራሳቸው እንኳን ሳይቀር እጅግ ከባድ ወንጀለኞች መስለው እንዲቀርቡ ለማድረግ ይቻል ዘንድ እነርሱን ለመዝለፍ ያልተሞከረ ዘዴ አልነበረም፡፡ አሁንም እንደዚያው ነው የሚሆነው፡፡ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያከብሩትን ሰዎች ለማጥፋት በሚጥርበት ጊዜ እነርሱን እንደ ሕግ አፍራሾች፤ እግዚአብሔርን እንደማያከብሩና በዓለም ላይ ጥፋት (መአት) እንዳመጡ ተቆጥረው እንዲከሰሱ ያደርጋል፡፡ ታተ 50.2
እግዚአብሔር ፈቃድን ወይም ህሊናን ፈጽሞ አያስገድድም፡፡ ነገር ግን ሰይጣንን ስንመለከት አታልሎ ሊያገኛቸው የማይችለውን በጭካኔ መንገድ ያስገድዳቸዋል፡፡ በፍርሃት ወይም በኃይል ህሊናን ተቆጣጥሮ ለራሱ ክብርን ለማግኘት ይጥራል፡፡ በመሆኑም የሃይማኖትን እና አለማዊ ባለስልጣናትን መሳሪያ በማድረግ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀው የሰውን ሕግ እንዲጠብቁ ያስገድዳል፡፡ የመጸሐፍ ቅዱስን ሰንበት የሚያከብሩ እንደ ሕግ ጠላቶችና ስርአተ አልባዎች፣ የሞራል ውድቀት እንደሚያመጡና «የእግዚአብሔር ፍርድ በምድር ላይ እንዲመጣ የሚያደርጉ ናቸው» ተብለው በሀሰት ይወነጀላሉ፡፡ የህሊናቸው ምርጫ (ውሳኔያቸው) ግትር ደንዳናነትና የባለስልጣናት ንቀት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ «የመንግስት ጠላቶች ናቸው» በመባል ይወነጀላሉ፡፡ የመለኮትን ሕግ የሚክዱ ካህናት የመንግስት ስልጣናት በእግዚአብሔር የተቀቡ መሆናቸውን በመግለጽ ለእነርሱ የመታዘዝ ግዴታ ተገቢ እንደሆነ በመድረክ ላይ ወጥተው ያስተምራሉ፡፡ በችሎትና ፍርድ ቤቶች የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚጠብቁት በሃሰት ተወንጅለው ይፈረድባቸዋል፡፡ ለሚናገሩት ቃላት የሃሰት ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ለሚያደርጉትም ተግባር (ሥራ) እጅግ የከፋ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ታተ 50.3
የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስትያናት በእግዚአብሔር ሕግ ትክክለኛነት የቆሙትን ግልጽ የመጸሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫዎች ውድቅ በሚያደርጉበት ጊዜ መጸሐፍ ቅዱስንና እምነታቸውን በቃሉ ላይ ያደረጉትን ሰዎች ዝም ለማሰኝት ይመኛሉ፡፡ ምንም እንኳን እውነትን ላለማየት አይናቸውን ቢጨፍኑም፤ ቀሪው የክርስትያን ዓለም የሚያደርገውን ላለማድረግ፣ የጳጳስንም ሰንበት ላለመቀበል የቆረጡትን ታማኞች ያሳድዱ ዘንድ መንገድን ሲያበጁ ይታያሉ፡፡ የቤተክርስቲያናትና የመንግስት ባለስልጣናት ሁሉም ወገን (ሰው ሁሉ) እሁድን ያከብር ዘንድ በጉቦ ለመደለል፣ ለማሳመን፣ ወይም ለማስገደድ ይተባበራሉ፡፡ የመለኮት ስልጣን በጨቋኝ ድንጋጌዎች ይተካል፡፡ የፖለቲካ ውድቀት (ብልሹነት) የፍትህን፣ ፍቅርና የእውነትን ክብር (ለእውነት መሰጠት የሚገባውን ክብር) እየደመሰሰ ነው፡፡ ነጻነት በሞላበት አሜሪካ እንኳን ሳይቀር መሪዎችና ሕግ አውጭዎች በህዝብ ለመወደድ ሲሉ እሁድ በሰንበትነት ይከበር ዘንድ በሕግ እንዲደነገግ የሚቀርበውን ጥያቄ ይቀበላሉ፡፡ ታላቅ መስዋዕትነት የተከፈለበት የህሊና ነጻነት ከእንግዲህ ወዲህ አይከበርም፡፡ በቅርብ ጊዜ በሚፈጸመው ተጋድሎ እንዲህ የሚለውን የነብዩን ትንቢት ጎልቶ በተግባር እናየዋለን፡- «ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን፣ ከዘርዋም የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ» (ራዕይ 12፡17)፡፡ ታተ 50.4