ታላቁ ተስፋ
የኅሊና ነፃነት ለአደጋ ሲጋለጥ
የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ከቀድሞው ይልቅ በአሁኑ ጊዜ የሮም ካቶሊክ ቤተክርስትያን ለምታስተምራቸው ትምህርቶች ልባቸው ተከፍቶአል። የካቶሊክ ሃይማኖት ባልተስፋፋባቸው እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አመራሮች ተጽእኖን ለማምጣት ከፕሮቴስታንቶች ጋር ለመስማማት ፍላጎት በሚያሳዩባቸው አገሮች ውስጥ ፕሮቴስታንቶችንና ካቶሊኮችን በሚለያዩት ትምህርቶች ላይ እየጨመረ የሚሄድ ግድየለሽነት ይታያል። ፕሮቴስታንቶች «ዋና ዋና በሆኑ ትምህርቶች ላይ ከካቶሊክ ሃይማኖት ጋር ብዙ ልዩነት የለንም፤ ዋና ዋና ያልሆኑትን ነጥቦች ወደጎን ብናደርግ ከሮም ካቶሊክ ቤ/ክ ጋር የተሻለ ግንኙነት ይኖረናል» ብለው ያስባሉ። ከዚህ ቀደም ፕሮቴስታንቶች ዋጋ ለከፈሉበት ለህሊና ነፃነት ትልቅ ዋጋ ይሰጡ ነበር። ከሮም ጳጳሳዊ ስርአት ጋር መስማማት ልክ እግዚአብሔርን እንደመካድ ስለሚቆጥሩት ልጆቻቸው የጳጳሳዊው ስርአትን እንዲጠሉ ያስተምሩዋቸው ነበር። ፕሮቴስታንቶች ዛሬ ያላቸው አቋም ከቀድሞው እንዴት በሰፊው ተለውጧል! ታተ 37.1
የሮም ጳጳሳዊ ስርአት ደጋፊዎች «ቤተክርስቲያናችን ተክዳለች» የሚለውን አባባል ፕሮቴስታንቶች ለመቀበል እያዘነበሉ መጥተዋል። ብዙዎች «በአሁኑ ጊዜ ያለችውን የሮም ካቶሊክ ቤ/ክ ከቀድሞዋ ለዘመናት ባለማወቅ ስትመራ ከነበረችው ጨካኝ የካቶሊክ ቤ/ክ ጋር ማመሳሰል ተገቢ አይደለም» በማለት ድምፃቸውን ያሰማሉ። ከዚህ ቀደም ያደርጉት የነበረውን አሰቃቂ የጭካኔ ተግባር «የዘመኑ ስልጣኔ የሮም ካቶሊክ አስተሳሰብን ቀይሮታል» በማለት ያድበሰብሱታል። ታተ 37.2
ለስምንት መቶ ዓመታት ይህ ራሱን ከፍ ሲያደርግ የነበረ ጳጳሳዊ ስልጣን ምንም እንከን እንደሌለበት እና በፍፁም ሊሳሳት እንደማይችል መግለፁን እነዚህ ሰዎች ረስተውት ነውን? ይህ አመለካከት ከመደብዘዝና ከመጥፋት ይልቅ እንደውም በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በአዎንታዊ ጎን እየተረጋገጠ እና እየተንፀባረቀ ነው። የሮም ቤተ ክርስቲያን አስረግጣ «ቤተ ክርስቲያን በፍፁም ተሳስታ አታውቅም፥ ወደ ፊትም አትሳሳትም፥ በመፃሕፍት መሰረት ፈጽሞ አልተሳሳተችም» ትላለች። (John L. Von Mosheim, Institutes of Ecclesiastical History, Book 3, Century II, Part 2, Chapter 2, Section 2, Note 17) ላለፉት በርካታ ዘመናት ትተዳደር የነበረበትን መርሆዎች እንዴት ልትተውና ልትክድ ትችላለች? ታተ 37.3
ጳጳሳዊቱ ቤተክርስቲያን መቼም ቢሆን «ምንግዜም ትክክል ነኝ፤ በፍፁም ልሳሳት አልችልም» የሚለውን አመለካከት አትተውም። እድሉ ቢሰጣት ከዚህ በፊት ቤተክርስቲያኗ ትክክል ነው ብላ የተቀበለችውን ዶግማ የተቃወሙትን እንዳሳደደች ዛሬም ይህንን ድርጊት አትደግምምን? መንግስታት የደነገጉት ሕግ ቢነሳና ሮም እንደቀድሞው በስልጣን ወንበሯ ላይ ብትቀመጥ፤ የጭቆና አገዛዟና የማሳደድ ተግባሯ በፍጥነት ተመልሶ ነፍስ ይዘራል። ታተ 37.4
እጅግ የታወቀ አንድ ፀሀፊ የህሊና ነፃነትን በተመለከተ የጳጳሱ ስርዓት የሚያንፀባርቀውን አመለካከት እና አሜሪካ ፖሊሲዋን እንዳትተገብር እንቅፋት ሊሆን ስለሚችለው አደጋ የሚከተለውን ይናገራሉ፦ «አሜሪካ ውስጥ የካቶሊክን መስፋፋት እና ተፅዕኖ መፍራት አክራሪነት እና አለመብሰል እንደሆነ የሚያስቡ በርካታ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በሮም ካቶሊክ ባህሪ እና አመለካከት ውስጥ ተቋሞቻችንን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ምንም አይነት አስፈሪ ነገር አለመኖሩን ያያሉ ወይም ደግሞ በእድገት ሂደቷ ላይ ምንም አይነት አደጋ አያገኙም። ስለዚህ በመጀመሪያ ዋና ዋና የመንግስታችንን መርሆዎች እና የካቶሊክን ቤተክርስቲያንን መርሆዎች እናወዳድር። ታተ 37.5
የአሜሪካ ሕገ መንግስት የህሊና ነፃነትን ያረጋግጣል። ከዚህም ሌላ ምንም አይነት ሌላ ወሳኝ እና መሠረታዊ ነገር የለም። ሊቀ ጳጳስ ፒዩስ ዘጠነኛ ነሐሴ 15 ቀን 1854 ዓ.ም. በፃፉት ጥብቅ ደብዳቤ «በብዥታ የተሞሉ እና ሐሰተኛ የሆኑትን፣ የህሊና ነፃነት እንዲኖር የሚያበረታቱን ሕጎች አንድ መንግስት ከምንም ነገር የበለጠ ሊጸየፋቸው ይገባል» ብለዋል። እኚሁ ሊቀ ጳጳስ ታህሳስ 8 ቀን 1864 ዓ.ም. በፃፉት ሌላ ጥብቅ ደብዳቤ «የህሊና ነፃነትን የሚያረጋግጡና የአምልኮ ነፃነትን የሚያከብሩ» እንዲሁም «በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኗ ኃይል መጠቀም የለባትም» የሚሉ ወገኖችን አውግዘዋል። ታተ 37.6
«አሜሪካ ውስጥ እየተንፀባረቀ የሚገኘው የሮም ድምፅ፤ ሮም የተለወጠ አስተሳሰብ (የተለወጠ ልብ) እንደሌላት ነው የሚጠቁመው። ቤተክርስቲያኗ መቻቻልን የምታንፀባርቀውና ተግባራዊ የምታደርገው ጉልበትና ኃይል ባልተላበሰችበት ስፍራ ብቻ ነው። ጳጳስ ኦከነር ‘የሃይማኖት ነፃነት ተረጋግጦ የሚቀጥለው በተቃራኒው ያለው ጽንፍ የካቶሊክ ዓለም ላይ ጉዳት ሊያስከትል በማይችልበት መንገድ እስኪተገበር ድረስ ብቻ ነው’ ብለዋል።’ . . . በአንድ ወቅት የቅዱስ ሉቃስ ጳጳስም የሚከተለውን ተናግረው ነበር፦ ‘መናፍቅነት እና አለማመን ወንጀል ናቸው። በክርስትያን ሃገሮች - ለአብነት ያህል ሁሉም ሰው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆነበት እንደነ ጣሊያን እና ስፔን - የካቶሊክ እምነት እንደ ወሳኙ የሀገሪቱ ሕግ በሚራመድበት ምድር መናፍቅነት እና ኢ-አማኝነት ልክ እንደሌሎች ወንጀሎች ያስቀጣል።’ «እያንዳንዱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካርዲናል፥ ቢሾፕ እና ሊቀ-ቢሾፕ በታማኝነት ለጳጳሱ ለመገዛት እና ለመታዘዝ በቃለ መሐላ የሚያረጋግጥ ሲሆን በዚህም ቃለ መሐላ ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦ «ጌታችንን [ጳጳሱን] ወይም የእርሱ ተተኪ የሆነውን የሚቃወሙትን መናፍቃንን፣ መከፋፈልን የሚያመጡትን አማጽያንን እና ኢ-አማንያንን በተቻለኝ ሁሉ አሳድዳለሁ፥ እቃወማለሁ።» (Josiah Strong, Our Country, Ch.5, Pars. 2-4.) ታተ 37.7
በሮማ ካቶሊክ ማህበረ ሃይማኖት ውስጥ እውነተኛ ክርስቲያኖች መኖራቸው እሙን ነው። በዚያች ቤተክርስቲያን ውስጥ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በተገለጠላቸው ብርሃን እግዚአብሔርን በቅንነት እና በታማኝነት ያገለግላሉ። ቃለ እግዚአብሔርን እንዲያውቁ አይደረግም ስለዚህም እውነቱን አያውቁም። ከልብ በመነጨ አገልግሎትና በወግና የድግግሞሽ ስርዓተ-አምልኮ መካከል ያለውን ልዩነት ፈጽሞ አላዩም። እርካታን በሚያጎናፅፉ እና አሳሳች በሆነ የእምነት ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ እነዚህን ነፍሶች እግዚአብሔር በርህራሄ ነው የሚመለከተው። የከበባቸውን ድቅድቅ ጨለማ ሰንጥቆ መውጫ መንገድ የሚያሳይ የብርሃን ጨረር ይፈጥርላቸዋል። በኢየሱስ ያለውን እውነት ይገልጽላቸዋል። ብዙዎችም የእርሱ ከሆኑት ጋር ይወግናሉ። ታተ 38.1
ነገር ግን የሮማ ካቶሊክነት በሥርአትነቱ ከቀድሞ ጊዜ በበለጠ አኳኋን ከክርስቶስ ወንጌል እና አስተምህሮ ጋር ያልተጣጣመበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስትያናት በታላቅ ጽልመት ውስጥ ናቸው የሚገኙት፤ ወይም የጊዜውን ምልክት መለየት ነበረባቸው። የሮማ ቤተክርስቲያን እቅዷንና የእንቅስቃሴ ዘዴዋን በስፋት ይዛዋለች። ተፅዕኖ የመፍጠር ጉልበቷን ለመመለስ፣ ያላትን ኃይል በመጨመር ያጣችውን ዓለም ለመቆጣጠር ስልጣን እንደገና ለማግኘት፣ የማሳደድ ተግባሯን እንደገና ለማደስ እንዲሁም የተሃድሶ ንቅናቄ (ፕሮቴስታንቲዝም) ስራን ለመቀልበስ ማንኛውንም መሳርያ ጥቅም ላይ እያዋለች ለጨካኝና ቆራጥ ተጋድሎ ትዘጋጃለች። በሁሉም አቅጣጫ የካቶሊክ እምነት መሰረት እየጣለ ነው። ፕሮቴስታንት በሆኑ አገሮች እየጨመረ የመጣውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና የፀሎት ቤት ብዛት እስቲ ተመልከቱ። በፕሮቲስታንቶችም በሰፊው ድጋፍ የሚደረግላቸው በአሜሪካ የሚገኙትን ኮሌጆች እና ትምህርት ማዕከሎች ዝና ተመልከቱ። በእንግሊዝ አገር እያደገ ያለውን ሃይማኖታዊ ወግ እና ከሌሎች ተቋማት ያለማቋረጥ ወደ ካቶሊክ ጎራ የሚጎርፉትን ሰዎች ብዛት ተመልከቱ። እነዚህ ነገሮች ለንጹህ የወንጌል መርሆዎች ዋጋ የሚሰጡትን ሰዎች ሁሉ መንፈሳዊ ቅንአት መቀስቀስ ይኖርባቸዋል። ታተ 38.2
ፕሮቲስታንቶች ጳጳሳዊውን ስርዓት ዝቅ አድርገው በመመልከት ድጋፍ አድርገዋል፤ እያንፀባረቁት የሚገኙት የአቋም ልሽቀት እና መለሳለስም የመንበረ ጳጳስ ሰዎች በመገረም የሚያዩትና የማይገባቸው ሆኗል። ሰዎች እውነተኛውን የሮማ ካቶሊክ ባህርይና የሮማ የበላይነት ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ እንዳያዩ የሚመለከቱበትን አይን እየከደኑ ነው። የሃይማኖትና ህዝባዊ (ሲቪል) ነፃነትን ለማጥፋት እያደገ የመጣውን አደገኛ ጠላት ለመቃወም፥ ይህ ህዝብ መነሳት አለበት። ታተ 38.3
በርካታ ፕሮቲስታንቶች የካቶሊክ ሃይማኖት ስርዓት የማይስብ፣ አምልኳቸውም የማያነቃ እና ትርጉም የለሽ ስርዓት እንደሆነ ያስባሉ። እዚህ ላይ ተሳስተዋል። ምንም እንኳን የሮም ሃይማኖት በሽንገላ ላይ የተገነባ ቢሆንም ስርዓታቸው እና አቀራረባቸው ተራ እና መስብ የሌለው አይደለም። የሮማ ቤተክርስቲያን አገልግሎት እና ሃይማኖታዊ ስርዓት እጅግ በጣም ማራኪ ነው። ድምቀት ያለው አቀራረብና ማራኪ ስርዓት የሕዝቡን ስሜት በመማረክ ምክንያታዊነትና ድምጸ ሕሊናን ዝም የሚያሰኝ ነው። በአንፃሩ አይን ይደሰታል። ዕጹብ ድንቅ የሆኑ አብያተ ክርስትያናት፣ ግርማ ያለው አቀራረባቸው እና ሰልፍ፣ ወርቃማ መሰዊያዎች፣ በልዩ ልዩ ጌጦች የተንቆጠቆጠ ቅዱስ ስፍራ፣ ምርጥ ስዕሎች እና ውብ ቅርፃ ቅርፆች በሙሉ የውበትን ፍቅር የሚቀሰቅሱ ናቸው። ጆሮም እንዲሁ ይማረካል። ሙዚቃው ፍፁም ወደር የለውም። ግዙፍ ከሆኑት ካቴድራሎችዋ በብዙ ኖታዎች በጥልቅ ከተቃኘው ኦርጋን፥ ከብዙ ድምጾች ጋር ተቀላቅሎ የሚያስተጋባው ዜማ አእምሮን በክብርና በሞገስ ለመማረክ አይሳነውም። ታተ 38.4
የሐሰት እርካታን ብቻ የሚሰጡት፥ በኃጢአት የታመመችው ነፍስ የምትናፍቃቸው፦ ውጫዊ ክብር፣ ታይታ እና ሃይማኖታዊ ወግ ለውስጣዊ ብልሹነት መረጃ ናቸው። የክርስቶስ ሃይማኖት ይህን መሰል ማራኪ ነገር መጠቀምን አያዝም። ከመስቀሉ ውስጥ በሚፈልቀው ብርሃን፤ እውነተኛ ክርስትና ንፁህ እና ተወዳጅ ሆኖ በማመልከት ምንም አይነት ውጭያዊ ማጋጌጫ ትክክለኛ እሴቱን ከፍ ሊያደርግ አይችልም። በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ያለው የቅድስና ውበት፥ የዋህ እና ትሁት መንፈስ ነው። ታተ 38.5
እጅግ በጣም አዋቂ መሆን የግድ የንጹህና የምጡቅ አስተሳሰብ መገለጫ አይደለም። ከፍተኛ የስነ ጥበባት ግንዛቤ፣ በሳልነት ብዙውን ጊዜ ምድራውያን በሆኑና ስሜታዊነት በሚያጠቃቸው ሰዎች አዕምሮ ውስጥ ይገኛል። እነዚህ መስህቦች ሰዎች ለነፍስ አስፈላጊ የሆነውን ነገር እንዲረሱ፣ ስለ መጪው ጊዜ ዘላለማዊ ሕይወት እይታ እንዳይኖራቸው፣ ከዘላለማዊ ረዳታቸው እንዲርቁ፣ ለዚህ ዓለም ሲሉ ብቻ እንዲኖሩ በሰይጣን ይመለመላሉ። ታተ 39.1
ውጫዊ ነገሮችን መሰረት ያደረገ ሃይማኖት ያልታደሰ እና አሮጌ ልብ ያላቸውን ሰዎች ይማርካል። ሃይማኖታዊ ድምቀትና ስርዓት የተላበሰ የካቶሊክ አምልኮ ብዙዎች የሚታለሉበት አማላይ ጉልበት አለው፤ የሮም ቤተክርስትያንን እንደ የመንግስተ ሰማያት የመግቢያ በር አድርገው ይመለከታሉ። ሆኖም በእውነት መሰረት ላይ እግሮቻቸውን የተከሉ እና በእግዚአብሔር መንፈስ ልባቸው የታደሰ በእርሷ ተጽዕኖ ሥር አይወድቁም። የክርስቶስ ማንነት በሚገባ ያላወቁ አእላፍ ሰዎች ታዲያ የአምልኮ መልክ ያላቸው ነገር ግን ኃይሉን የካዱትን የሮም ካቶሊክን ይቀበላሉ። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች የሚፈልጉት ይህን መሰሉን ሃይማኖት ነው። ታተ 39.2
ቤተክርስቲያኗ የምታስተጋባው ኃጢአትን የማስተሰረይ ስልጣን አማኞች ኃጢአት ለመስራት ነፃነት ያላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋል፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ኃጢአትን የምታስተሰርይበት የኃጢአት ኑዛዜ ስርዓት ሰዎች በቀላሉ ኃጢአትን እንዲሰሩ በርን ይከፍታል፡፡ ነገር ግን በኃጢአት በወደቀ ሰው ፊት ተንበርክኮ፣ ያሰበውን እና በልቡ የተመኘውን ሚስጥር ገልጦ የሚናዘዝ፥ ሰብአዊ ማንነቱ ዝቅ እያደረገና እያንዳንዱ ክቡር ነፍሱን ተፈጥሮ እያዋረደ ነው። ለአንድ ለሚሳሳት፣ኃጢያተኛም ሟችም ለሆነ፣ ብዙውን ጊዜ በወይን ጠጅና በምግባረ ብልሹነት የሚጨማለቅ ቄስ ፊት የዕድሜ ልኩን ኃጢአት መናዘዙ የባሕርዩን ደረጃ ዝቅ ያደርጋል በዚህ ምክንያትም ይረክሳል። በእግዚአብሔር ላይ ያለው አስተሳሰብም እርሱም በኃጢአት ከወደቀው ሰው ጋር በማመሳሰሉ ዝቅ ብሏል፤ ምክንያቱም ቄሱ የእግዚአብሔር እንደራሴ ሆኖ ቆሟልና። ይህ ኃጢአትን ለሰው የመናዘዝ እና ንሰሃ የመግባት ስርዓት ዓለምን ወደ መጨረሻ ጥፋት የሚወስድ፣ ታላቅ ክፋት የፈለቀበት ምስጢራዊ ምንጭ ነው። ሰው ልቡን ከፍቶ ኃጢአቱን ለእግዚአብሔር ከሚናዘዝ ይልቅ ለሰው መናዘዝ ይቀለዋል፡፡ ለሰብአዊው ተፈጥሮ ከኃጢአት ከመቆጠብ ይልቅ ራስን መቅጣት በጣም ይስማማዋል፤ ሥጋዊ ምኞትን ከመስቀል ይልቅ ስጋን በሰንሰለት መግረፍ፣ አካልን መጉዳትና ማጎሳቆል ይቀለዋል። ለክርስቶስ ቀንበር ከመንበርከክ ይልቅ ስጋዊ ልብ ለመሸከም የሚፈቅደው ቀንበር ከባድ ነው። ታተ 39.3
ክርስቶስ መጀመርያ በመጣበት ዘመን በሮም ቤተክርስትያን እና በአይሁድ ቤተመቅደስ መካከል የጎላ መመሳሰል አለ። አይሁዶች እያንዳንዱን የእግዚአብሔርን መርሕ በሚስጥር እየጣሱ በውጪ ግን ለህጉ ተፈፃሚነት ቀናተኛ መስለው እየቀረቡ፣ ባህል እና ፅኑ ስርአት በመቆለል መታዘዝን ከባድና አስጨናቂ አድርገውታል። አይሁዶች ሕግን እንደሚያከብሩ ቃል እንደገቡ ሁሉ፣ ሮማውያን ደግሞ መስቀልን እናከብራለን ይላሉ። ሆኖም ግን የክርስቶስን ህመም እና መከራ ምልክት ከፍ አድርገው እያወደሱ በእውነተኛ ሕይወታቸው ግን ምልክቱ የሚወክለውን አምላክ ይክዱታል። ታተ 39.4
ጳጳሳዊያን መስቀልን በቤተክርስቲያናቸው፣ መሰዊያቸው እና ልብሳቸው ላይ ያስቀምጣሉ። በሁሉም ስፍራ የመስቀሉ ምልክት ይታያል። በሁሉም ስፍራ ውጪያዊ ክብር እና ከፍታ ተሰጥቶታል። የክርስቶስ ትምህርቶች ግን በትርጉም የለሽ ልማዶች፣ በሐሰት ትርጓሜዎችና ለመጠበቅ አስቸጋሪ በሆኑ ሃይማኖታዊ መመርያዎች ውስጥ ተቀብረዋል። ሐሳበ-ጠባብ የሆኑትን አይሁዶችን በተመለከተ መድኃኒታችን የተናገረው ቃል ይበልጡን ኃይል ባለው አኳኋን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስትያን መሪዎች ይመለከቱታል፦ «ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።» (ማቴ. 23፡4) ትጉህ ነፍሶች የእግዚአብሔርን የቁጣ መዓት በመፍራት ዘወትር እንደተሸበሩ ይቆያሉ፤ ብዙ የቤተ ክርስትያን አለቆች ግን ስሜታቸውን በማርካትና በቅንጦት ይኖራሉ። ታተ 39.5
የምስል እና ቅርስ አምልኮ፣ ቅዱሳንን መማጸን እና ጳጳሱን ከፍ ከፍ ማድረግ የሰዎችን አዕምሮ ከእግዚአብሔርና ከልጁ ለመሳብ እና ለማራቅ ሰይጣን የሚጠቀምበት ስልት ነው። ዲያብሎስ የሰዎችን ጥፋት ለማከናወን ድነት ማግኘት ከሚችሉበት ከእግዚአብሔር እንዲርቁ ትኩረታቸውን ይስባል። «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።» (ማቴ11፡28) ሲል ለተናገረው ጌታ ምትክ ሊሆን ወደሚችል ወደ ማንኛውም ነገር ይመራቸዋል። ታተ 39.6
የእግዚአብሔርን ባህርይ፣ የኃጢአትን ተፈጥሮና የታላቁን ተጋድሎ እውነተኛና አቢይ ጉዳዮች በተሳሳተ መልክ ማቅረብ የሰይጣን የዘወትር ጥረቱ ነው። የእርሱ ሽንገላ የመለኮታዊውን ሕግ አስፈላጊነት በማሳነስ ሰዎች ኃጢአት እንዲሰሩ ማድረግ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ፣ እግዚአብሔርን በፍቅር ከመመልከት ይልቅ በፍርሃትና በጥላቻ እንዲመለከቱት ያደርጋል። በባህርዩ ያለው ተፈጥሮአዊ ጭካኔ ከፈጣሪ እንደመጣ አድርጎ ያመለክታል፤ይህም ባህርይ የስርዓተ ሃይማኖት አካል በመሆን በአምልኮት መልክ ይገለጻል። እንዲህም የሰዎችን አእምሮ አሳውሮ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ጋር ለመዋጋት የራሱ ወኪል በማድረግ ያሰልፋቸዋል። ጣኦት አምላኪ ህዝቦች በአምላክ ለመወደድ ሰብአዊ መስዋዕት የግድ አስፈላጊ እንደ ሆነ በማመን፥ መለኮታዊውን ባህርይ በስህተት በመገንዘብ ሲመሩ ቆይተዋል። በተለያየ የጣዖት አምልኮ ስርዓቶችም አሰቃቂ ጭካኔዎች ተፈጽመዋል። ታተ 40.1
የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አረማዊነትን እና ክርስትናን በመደባለቅ፣ ልክ እንደ አረማውያን የእግዚአብሔርን ባህርይ በተሳሳተ መልክ በማቅረብ፤ ከዚህ ያልተናነሰ ጭካኔና አመጽ በተግባር ፈጽማለች። ሮም ልዕለ ኃያል በነበረችበት ዘመን የእርሷን ትምህርት እንዲቀበሉ ለማስገደድ የምትጠቀምባቸው የማሰቃያ መሳርያዎች ነበሩ። ትምህርቶችዋን የማይቀበሉ ታስረዋል። በፍርድ ጊዜ ሲገለጥ ካልሆነ በቀር የማይታወቅ የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል። የቤተክርስቲያኗ አለቃ ከመሪያቸው ሰይጣን እግር ስር ቁጭ ብለው በእጃቸው የወደቀውን ሰው ሕይወቱን ሳይቀጥፉ ነገር ግን በተቻለ መጠን እጅግ ከባድ የሆነ ስቃይ የሚያደርስ ስልት ለመፍጠር ያጠኑ ነበር። ብዙ ጊዜ ይህ አሰቃቂ ድርጊት (ጭካኔ) ሰብዓዊነት ሊቋቋመው እስከማይቻለው ድረስ፣ ተፈጥሮ ትግልዋን እስክታቆምና የሚሰቃየው ሰው ሞትን እንደ ጣፋጭ ነፃነት እንኳን ደህና መጣህ እስኪለው ድረስ ተደጋግሟል። ታተ 40.2
ይህ ነበር የሮም ተቃዋሚዎች እጣ ፈንታ። ለደጋፊዎቿም ልብን በሚሰብር መልኩ የግርፋት፣ በረሃብ የመቅጣት፣ በተለያዩ መንገድ ስጋን የመጨቆን አካሄድ ነበራት። ገነት እንደሚገቡ ለማረጋገጥ ንስሃ የገቡ ሰዎች የተፈጥሮን ሕግ በመጣስ የእግዚአብሔርን ሕግንም ተላልፈዋል። ሰዎች በምድራዊ ቆይታቸው እንዲባረኩበትና እንዲደሰቱበት እግዚአብሔር አሳምሮ ከፈጠረው እንዲርቁ ተምረዋል። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ምድራዊ ኑሮ ለመባረክ እና አስደሳች ለማድረግ የፈጠራቸውን ነገሮች እንዲጠሉ ተደርገዋል። ቤተክርስቲያን በመቃብሮቿ ውስጥ፣ እግዚአብሔር በሚጠላው መንገድ፣ ተፈጥሯዊ የፍቅር ፍላጎታቸውን ለመቋቋም፣ ለባልንጀሮቻቸው ያላቸውን እያንዳንዱን የርህራሄ አስተሳሰብና ስሜት ለመግታት፣ ዘመናቸውን በሙሉ ከንቱ (ዋጋ ቢስ) ተግባሮች በማድረግ ያሳለፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዚህ ሰለባ የሆኑ ነፍሳትን ይዛለች። ታተ 40.3
ለብዙ ምዕተ ዓመታት የተገለጸውን የዲያብሎስን ቁርጥ ጭካኔ ለመረዳት ከፈለግን፤ የእግዚአብሔርን ስም ያልሰሙ በማያውቁት ሳይሆን ነገር ግን በክርስያኖች ልብ የሮማ ካቶሊክን ታሪክ ብቻ መመልከት አለብን። በዚህ ግዙፍ የሽንገላ ስርዓት የክፋት ልዑል (ዲያብሎስ) እግዚአብሔርን ለማዋረድ ለሰው ልጅም ፍዳን ለማምጣት ያለውን ዓላማ ያሳካል። ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን መሪዎች አማካይነት ስራውን ሲያከናውንና ራሱን ሲሰውር ስንመለከት ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳለው ይበልጥ ልንገነዘብ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ከተነበበ የእግዚአብሔር ምህረትና ፍቅር ይገለጣል፥ እግዚአብሔር በሰዎች ላይ እነዚህን ከባድ ሸክሞች እንዳልጫነ ይታያል። እግዚአብሔር የሚጠይቀው ሁሉ፦ የተሰበረና የተጸጸተ ልብ፥ ትሑትና ታዛዥ መንፈስን ነው። ታተ 40.4
ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ለመንግስተ ሰማያት ብቁ ይሆኑ ዘንድ በገዳም ተዘግተው እንዲኖሩ ክርስቶስ አንዳች ምሳሌ አልሰጠንም። ፍቅርንና ርህራሄን መደበቅ እንዳለባቸው ፈፅሞ አላስተማረም። የመድኃኒታችን ልብ በፍቅር ሞልቶ የፈሰሰ ነው። ሰው ወደ ግብረገባዊነት ፍጽምና ይበልጥ በቀረበ ቁጥር፥ ስሜቶቹ መንፈሳዊ ነገሮችን ለማስተዋል በጣም ንቁ ናቸው፣ ኃጢአትን የመገንዘብ ችሎታው ይበልጥ ይጨምራል፣ ለተጎዱት ያለው ኃዘኔታ ጥልቅ ነው። ጳጳሱ «የክርስቶስ ወኪል ነኝ» ይላል፤ ነገር ግን ጠባዩ እንዴት ብሎ ነው ከመድኃኒታችን ሊነፃፀር የሚችለው? እንደ የሰማይ ንጉሥ ክብር ስላልሰጡት ክርስቶስ ወደ እስር ቤት ወይም ወደ ስቃይ በመወርወር ይታወቃልን? ያልተቀበሉትንስ ለሞት ሲኮንናቸው ድምፁ ተሰምቷልን? የሰማሪያ ሰዎች ክርስቶስን ባልተቀበሉት ጊዜ ሐዋሪያው ዮሐንስ ተቆጥቶ የሚከተለውን ጠይቆ ነበር፦ «ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት።» እርሱ ግን ዘወር ብሎ ተመለከታቸውና ቁጡ መንፈሱን ገሰፀው። «የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ።» (ሉቃ 9፡54,56) በክርስቶስ የተገለጠው መንፈስ «ወኪል ነኝ» ከሚለው ጳጳስ መንፈስ ምን ያህል የተለየ ነው!። ታተ 40.5
የሮም ቤተክርስቲያን አሰቃቂ ጭካኔዋን በይቅርታ በመሸፈን መልካም ገፅታዋን አሁን ለዓለም እያቀረበች ነው። ራሷን ክርስቶስን በሚመስሉ አልባሳት አጎናጽፋለች። ነገር ግን አልተለወጠችም። ባለፉት ዘመናት የነበረ እያንዳንዱ የጳጳሱ መርህ ዛሬም አለ። በጨለማው ዘመን የተዘጋጁትን ትምህርቶች እስካሁን ይዘዋቸው ነው ያሉት። ማንም ራሱን አያታልል። ያኔ ዓለምን ሲመራ ሳለ የእግዚአብሔር ሰዎች ሕይወታቸውን ሳይሳሱ፣ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ዓመጽ ለማጋለጥ ፀንተው ሲቆሙ ለነበረው ጳጳሳዊ ስልጣን ነው ዛሬ ፕሮቴስታንቶች ክብርን ለመስጠት የሚፈልጉት፡፡ ዛሬም የጳጳሳዊው ስርዓት ራስን የበላይ አድርጎ የመቁጠርንና የትዕቢትን መንፈስ በመያዝ «በመሳፍንትና በነገስታት ላይ እንድገዛ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ልዩ ስልጣን አለኝ» ይላል። ዛሬም ያለው የጭካኔና የአምባገነንነት መንፈስ፥ የልዑሉን ቅዱሳን ሲያርድና የሰዎችን ነጻነት ሲገፍ ከነበረበት ጊዜ የሚያንስ አይደለም። ታተ 40.6
ጳጳሳዊው ስርዓት «በኋለኛው ዘመን እውነትን የሚቃወም ስልጣን ነው» ተብሎ በትንቢት የታወጀለት ነው። (2ተሰ2:3-4)። ዓላማውን ይበልጥ የሚያሳካለትን ባህርይ መላበስ የፓሊሲው ክፍል ነው፤ ነገር ግን በሚለዋወጠው የእስስት ገጽታው ስር የማይለዋወጥ የእባብ መርዝ ይደብቃል። «እምነት ከኑፋቄ ጋር ተቀላቅሎ መጠበቅ የለበትም፥ በመናፍቅነት ከሚጠረጠሩ ሰዎችም ጋር» ብሎ ያውጃል፡፡ (ሌንፋንት፣ መጽሐፍ 1፣ ገጽ 516)። ለእልፍ ዓመታት መዝገቡን በቅዱሳን ደም የጻፈው ይህ ኃይል፥ አሁን እንደ የክርስቶስ ቤተ ክርስትያን አካል ይቆጠራልን? ታተ 41.1
ያለ ምክንያት አይደለም «ካቶሊክ ከፕሮቴስታንት እምነት ከቀድሞ ዘመን ይልቅ ልዩነቱ እጅግ የጠበበ ነው» እየተባለ በፕሮቴስታንት አገሮች የሚነገረው። በርግጥ ለውጥ ነበር፤ ለውጡ ግን በ ጳጳሳዊው ስርዓት ላይ አይደለም። የካቶሊክ እምነት አሁን ካለው የፕሮቴስታንት እምነት ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ ምክንያቱም የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ከመጀመርያ የተሐድሶ ጊዜያት ወዲህ በደረጃው እያሽቆለቆለ መጥቷል። ታተ 41.2
የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያናት በዓለም ዘንድ መወደድን ሲሹ በመቆየታቸው የሐሰት ፍቅር አይናቸውን አሳውሮታል። የሚታያቸው ነገር በክፋት ሁሉ ውስጥ መልካምን ማመን ትክክል እንደ ሆነ ሲሆን በመጨረሻም የመልካምን ሁሉ ክፋት ወደ ማመን መሄዳቸው አይቀርም። ታተ 41.3
ከዚህ ቀደም ለቅዱሳን የተሰጠውን እምነት ለመከላከል በመቆም ፈንታ፥ ለሮም ቤተ ክርስትያን በነበራቸው አሉታዊ አስተሳሰብ በመጸጸት፥ እነሱ ቀድሞ እንዳደረጉት አሁንም ለሮም ቤተክርስትያን ይቅርታን ይጠይቃሉ። ታተ 41.4
ከእነርሱ መካከል ብዙዎች የሮም ሃይማኖታዊ ስርዓትን በበጎ ዓይን ባይመለከቱትም፤ ኃይሏና ተጽዕኖዋ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ አቅልለው ይመለከታሉ፡፡ ብዙዎች «በመካከለኛው ዘመን ሰፍኖ የነበረውን የእውቀትና የሞራል ጽልመት ትምህርት እምነቷን (ዶግማዋን)፣ የሐሰት ትምህርቷንና ጭቆናዋን ለማስፋፋት ረድቷታል» በማለት አጥብቀው ይናገራሉ፤ «የዘመናዊው ጊዜ አስተዋይነት፣ ባጠቃላይ የእውቀት ማደግ፣ እየጨመረ ያለው የሃይማኖት ነፃነት ጉዳይ፤ ጭቆናና አለመቻቻል ተመልሶ እንዲስፋፋ አይፈቅድም፡፡» ይህን የመሰለ ሁኔታ በዚህ በሰለጠነው ዓለም ይገኛል ብሎ ማሰብ እንደ ፌዝ ይቆጠራል። ለዚህ ትውልድ የእውቀት፣ የግብረ ገብነትና የሃይማኖት ትልቅ ብርሃን ማብራቱ እውነት ነው። ግልጽ በሆኑት ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃላት በዚህ ዓለም ላይ ብርሃን ከሰማይ ፈንጥቋል። ነገር ግን ይበልጥ ብርሃን በተሰጠ ቁጥር፥ ቃሉን በሚያጣምሙና በማይቀበሉት ዘንድ ይበልጡን ጨለማ እንደሚሆን ሊታወስ ይገባል። ታተ 41.5
ፕሮቴስታንቶች መጽሐፍ ቅዱስን በጸሎት ቢያጠኑ፣ የመንበረ ጳጳሱን እውነተኛ ባህሪ ስለሚያሳያቸው እንዲጠሉትና እንዲርቁት ያደርጋቸው ነበር፤ ነገር ግን ብዙዎች በራሳቸው አስተሳሰብ በጣም ልባሞች በመሆናቸው ወደ እውነት ለመመራት ዝቅ ብሎ እግዚአብሔርን መሻት እንደሚያስፈልጋቸው አይሰማቸውም። ምንም እንኳ በእውቀታቸው ቢኩራሩም ስለ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ስለ እግዚአብሔር ኃይል እውቀት የላቸውም። ኅሊናቸውን ለማሳረፍ የሆነ ነገር መጠቀም ስላለባቸው በጣም ትንሽ መንፈሳዊነትና ትህትና ያለበትን ነገር ይሻሉ። እነርሱ የሚፈልጉት እግዚአብሔርን የማስታወስ መልክ ያለው፤ እግዚአብሔርን የሚረሱበትን መንገድ ነው፡፡ መንበረ ጳጳሱ የእንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት በሚገባ የተመቻቸ ነው። ዓለምን በቁጥጥሩ ስር ለማዋል ለሁለት ዓይነት የሰው ጎራዎች ተዘጋጅቷል፥ በመልካም ስራቸው መዳን ለሚፈልጉና ከነኃጢያታቸው መዳን ለሚፈልጉ ሰዎች። የኃይሉ ምስጢር ይህ ነው። ታተ 41.6
ታላቁ የእውቀት ጨለማ ዘመን ለመንበረ ጳጳሱ መሳካት ምቹ እንደነበር ታይቷል። ታላቅ የእውቀት ብርሃንም በተመሳሳይ መልኩ ለስኬቱ ምቹ እንደሆነም ተረጋግጧል። ባለፉት ዘመናት ሰዎች ያለ እግዚአብሔር ቃል እና ያለ እውነት እውቀት ሲኖሩ ሳለ ዓይናቸው ታወረ፥ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችም በእግራቸው ስር የተጠመደውን ወጥመድ ባለማየታቸው ምክንያት ተጠመዱ። በዚህ ትውልድም «በሐሰት ሳይንስ ተብሎ በሚጠራው» ሰብአዊ ግምታዊ አስተሳሰብ ነጸብራቅ ዓይናቸው የታወረ ብዙዎች ናቸው፥ በመሆኑም የተዘረጋውን ወጥመድ ባለመለየታቸው በጭፍን እየተራመዱ ይገቡበታል። የሰው የማስተዋል ኃይል በጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባ የፈጣሪው ስጦታ ሲሆን እግዚአብሔር ያቀደው እውነትንና ጽድቅን ለማገልገል እንዲጠቀምበት ነው፤ ነገር ግን ትእቢትና ራስ ወዳድነት ሁልጊዜ በአእምሮ ሲስተናገዱ፥ ሰዎችም የራሳቸውን መላምት ከእግዚአብሔር ቃል በላይ ሲያስበልጡ፥ አለአዋቂነት ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ የሰው አስተዋይነት የበለጠ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ እምነትን የሚያጣጥለው የዘመኑ ሐሰተኛ ሳይንስ፤ ልክ በጨለማው ዘመን እውቀትን አፍኖ መያዝ የመንበረ ጳጳሱን ስልጣን የበለጠ እንዲጠናከር መንገድ ከፍቶለት እንደ ነበረው፤ መንበረ ጳጳሱ (ከሚማርኩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶቹ ጋር) ተቀባይነት እንዲያገኝ መንገዱን በተሳካ መልኩ የሚያዘጋጅ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡ ታተ 41.7
በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ባሉት፣ የቤተክርስቲያንን ተቋማትና ልማዶች በመንግስት ጥበቃ ሥር የማድረግ እንቅስቃሴዎች ፕሮቴስታንቶች የጳጳሳዊያኑን መንገዶች እየተከተሉ ነው። ይሕም ብቻ አይደለም፣ ይልቁንም በቀደመው ዓለም ጳጳሳዊው ስርዓት በፕሮቴስታንታዊው አሜሪካ ውስጥ ያጣውን የበላይነት እንዲቀዳጅ በር እየከፈተለት ነው። ለዚህም እንቅስቃሴ የበለጠ ክብደት የሚሰጠው ነገር በዋናነት የሚያጠነጥንበት ዓላማ ከሮማ የመነጨውና እንደ የስልጣኗ መገለጫ የምትቆጥረው ልማድ፣ የእሁድ መከበር መሆኑ ነው። ይህ የጳጳሳዊው ስርዓት መንፈስ፣ ከዓለማዊ ልማድና ወጎች ጋር የመመሳሰል መንፈስ፣ ከእግዚአብሔር ትዕዛዛት ይልቅ ለሰው ልማድ የመገዛት መንፈስ ወደ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን በመግባት ላይ ሲሆን ከእነርሱ በፊት ጳጳሳዊው ስርዓት ወደ አቋቋመው እሁድን ወደ ማክበር ስራ እየመራቸው ነው። ታተ 42.1
በቅርቡ በሚከሰቱት አለመግባባቶች መጠቀሚያ የሚሆኑትን መሳሪያዎች አንባቢው ማስተዋል ሲፈልግ በታሪክ ወደ ኋላ ሄዶ ኖሮ በቀደመው ዘመን ሮማ ለተመሳሳይ ዓላማ የተጠቀመችባቸውን መሳሪያዎች ማጥናት ይኖርበታል። ጳጳሳውያንና ፕሮቴስታንቶች የእነርሱን አስተምህሮዎች የሚቃወሙትን ምን እንደሚያደርጉባቸው ማወቅ ካስፈለገው በሰንበትና በሰንበት ጠባቂዎች ላይ ሮም የገለጠችውን መንፈስ ይመልከት። ታተ 42.2
በዓለማዊ ሥልጣናት የተደገፉ ንጉሳዊ አዋጆች፣ የመማክርት ጉባኤዎች እንዲሁም የቤተክርስቲያን ድንጋጌዎች ይህን የባእድ አምልኮ በዓል በክርስትያኑ ዓለም የክብር ቦታ ለመቀዳጀት መወጣጫ ነበሩ። የመጀመሪያው እሁድ እንዲከበር የተወሰደው መንግስታዊ እርምጃ በቆስጠንጢኖስ በ321 ዓ.ም. በወጣው ሕግ ነበር። ይህ ድንጋጌ የከተማ ሰዎች «በተቀደሰው የፀሐይ ቀን (Sunday)» እንዲያርፉ ይጠበቅባቸዋል፥ የገጠር ሰዎች ግን የእርሻ ስራቸውን መስራት እንዲቀጥሉ ፈቅዶላቸዋል። በዋናነት ዓለማዊ ሕግ የነበረ ቢሆንም፥ ንጉሱ ክርስትናውን ለይምሰል ከተቀበለ በኋላም ተፈፃሚነቱ ቀጥሏል። ታተ 42.3
«በአምላካዊው ስልጣን ተወክያለሁ» የሚለው ንጉሣዊው ስልጣን ለተተኪነት በቂ መረጃ ባይቀርብም፥ የመሳፍንትን ወዳጅነት ናፋቂ የነበረውንና የቆስጠንጢኖስ የተለየ ወዳጅና አምላክ የነበረው ኢዮሴቢየስ የተባለው ጳጳስ ክርስቶስ ሰንበትን ወደ እሁድ አሸጋግሮታል በማለት ነገሩ እንዲስፋፋ አድርጎታል። ለአዲሱ ትምህርት ማስረጃ እንዲሆን ከቅዱሳት መፃህፍት (መጽሐፍ ቅዱስ) አንድ ማረጋገጫም አልተጠቀሰም። ኢዮሴቢየስ ራሱ በማያወላውል ሁኔታ የትምህርቱን ሐሰተኛነትና የለውጡን እውነተኛ ምንጮች ማንነት ያምናል። «ሁሉም ነገር» ይላል «በሰንበት ቀን [ሰባተኛ ቀን/ቅዳሜ] መደረግ ያለበት ማንኛውም ነገር ወደ ጌታ ቀን (እሑድ) እንዲዛወር አድርገናል።» (Robert Cox, Sabbath Laws and Sabbath Duties, ገፅ 538)። የእሁድ ነገር ምንም አይነት መሠረት የሌለው እንደመሆኑ ሰዎች የጌታን ሰንበት በድፍረት እንዲያጣጥሉ ምክንያት ሆኖአል። በዓለም መከበርን የሚሹ ሁሉ በዝነኛ ክብረ በዓል ተቀብለውታል። ታተ 42.4
ጳጳሳዊው ስርዓት ተጠናክሮ ሲቋቋም እሁድን የማክበሩ ነገርም እየቀጠለ ሄደ። ለግዜው በእርሻ ስራ የተሰማሩ ሰዎች ቤተክርስቲያን አይሔዱም ነበር፥ ሰባተኛው ቀንም አሁንም እንደ ሰንበት ሲከበር ኖሯል። ቀስ በቀስ ግን ለውጥ መጣ። በፍትህ ቢሮዎች የሚሰሩ ሰዎች በእሁድ ቀን በማናቸውም አይነት የፍትሐብሔር ክርክር ፍርድ እንዳይሰጡ ተከለከሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማናቸውም አይነት ማዕረግ ያላቸው ሰዎች በእሁድ ቀን ስራ እንዳይሰሩ የሚከለክል ትእዛዝ ተሰጣቸው፤ይህን ትእዛዝ ለተላለፉ - ለነፃ ሰዎች የገንዘብ ቅጣት፣ ለባሮች ደግሞ የግርፋት ቅጣት እንዲሆን ተወሰነ። ወደ በኋላም ባለ ሐብቶች የንብረታቸውን እኩሌታ እስከማጣት ድረስ እንዲቀጡ በዚህም የማይታረሙ ከሆነ ባሮች እንዲሆኑ ተደነገገ። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የሕብረተሰቡ ክፍሎች እስከ መጨረሻው ከሃገር ይባረሩ ነበር። ታተ 42.5
የተለያዩ ተአምራትም ይነገሩ ነበር። ከሚነገሩትም ተአምራት መካከል፦ አንድ ሰው በእሁድ ቀን መሬቱን ለማረስ ማረሻውን በብረት በማፅዳት ላይ ሳለ ብረቱ በእጁ ላይ ተጣብቆ ለሁለት ዓመታት ያህል ተሸክሞት በ «ታላቅ ሕመምና ሐፍረት» ቆይቷል የሚለው ይገኝበታል። (Francis West, Historical and Practical Discourse on the Lord`s Day, ገፅ 174) ታተ 42.6
በኋላም ጳጳሱ የየአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን ቄሶች የእሁድን እረፍት የሚሽሩትን ሰዎች እንዲገስፁና ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው ፀሎታቸውን እንዲያቀርቡ እንዲያዙአቸው አለበለዚያ ግን በራሳቸውና በጎረቤታቸው ላይ መቅሰፍት ሊወርድ እንደሚችል በማሳሳብ ትዕዛዝ አስተላለፉ። የሃይማኖት መማክርትም በብዙሃኑ ዘንድ፤ በፕሮቴስታንቶችም ሳይቀር ተቀባይነት ያለው ከመሆኑም በላይ በእሁድ የሚሰሩ ሰዎች በመብረቅ እየተመቱ ስለሆነ የሰንበት ቀን ስለመሆኑ ማስረጃ ነው የሚል የማሳመኛ ሐሳብ አመጡ። «ይህንን ቀን መናቅ አምላካዊ ቁጣ እንደሚያነድ ግልፅ ነው» በማለት ካህናት አስረዱ። ቄሶች፣ ሚኒስትሮች፣ ነገስታት፣ ልኡካን፣እንዲሁም ታማኝ ሰዎች በሙሉ «በተቻላቸው መጠን ይህንን ቀን ወደ ቀድሞው ክብሩ ለመመለስና ለክርስትና እምነት መከበር፥ ለመጭው ግዜ በጥንቃቄ እንዲጠብቁት» ጥሪዎች አቀረቡ። (Thomas Morer, Discourse in Six Dialogues on the Name, Notion, and Observation of the Lord`s Day, ገፅ 271) ታተ 42.7
የመማክርቱ አዋጆች በቂ ሆነው ባለመገኘታቸው ዓለማዊ ባለስልጣናት ሕዝቡ በእሁድ መስራቱን እንዲያቆም ለማድረግ የሚያስችሉ አስደንጋጭ ትዕዛዞችን እንዲያውጁ ተደረገ። በሮም በተደረገ ጉባኤ የቀደሙት ትዕዛዛት በሙሉ እንዲታደሱና በበለጠ ኃይልና ሥነሥርዓት እንዲፈፀሙ ውሳኔ ተደረገ። እነዚህም በመላው ክርስቲያናዊ ዓለም የሃይማኖት ሕጎች እንዲሁም የፍትህ ማስከበሪያ ሕጎች ውስጥም ተካተቱ። (Heylyn, History of the Sabbath, pt 2, ch. 5, sec. 7.) ታተ 43.1
አሁንም ቢሆን እሁድን ለመጠበቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንም አይነት ድጋፍ አለመገኘቱ ትንሽ እንኳን አላስደነቃቸውም። የፀሐይን ቀን ለማክበር ተብሎ ግልፅ የሆነውን የይሖዋን «የሰባተኛው ቀን የአምላክህ የእግዚአብሔር ሰንበት ነው» የሚለውን አዋጅ ወደ ጎን ለማድረግ አስተማሪዎቹ ምን መብት እንዳላቸው ሕዝቡ ይጠይቅ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ የታጣውን ማስረጃ ለማካካስ ሌላ እርምጃዎች አስፈለጉ። በ12ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ የእንግሊዝን አቢያተ-ክርስቲያናት የጎበኘ አንድ ቀናተኛ የእሁድ ጠበቃ፥ ለእውነት ታማኝ የሆኑ ምስክሮች ተቃወሙት፤ ጥረቱ ሁሉ ከንቱ ሆኖበት ለተወሰነ ግዜ ሀገሩን ለቆ በመሔድ ትምህርቱን ተፈፃሚ ሊያደርግ የሚችልበትን ዘዴ ሲያጠና ከረመ። ተመልሶ ሲመጣ ክፍተቱ ተሞላ፥ ልፋቱም ታላቅ ስኬትን አመጣለት። ይህ የእሁድ ጠበቃ ከእግዜአብሔር ከራሱ እንደመጣ የሚነገርለትን እሁድን የማክበርን አስፈላጊነት ትእዛዝንና፥ ትዕዛዙን የማይቀበሉትን የሚያስበረግግ ከባድ ማስፈራሪያዎችን የያዘ ጥቅል ብራና ይዞ መጣ። መሰረቱና የሚደግፈውም ተቋም አስመሳይ የሆነው ይህ «ክቡር ጥቅል ጽሑፍ» በኢየሩሳሌም፥ በቅዱስ ስምኦን መሰዊያ ላይ በጎልጎታ ከሰማይ ወድቆ መገኘቱ ሲነገርለት ነበር። በእውነት የፈለቀበት ቦታ ግን የሮማው ጳጳስ በሚገኝበት ቤተ መንግስት ነበር። የቤተክርስቲያንን ኃይልና ብልጽግናን ለማስፋፋት ሲባል ተንኮልና የተጭበረበሩ ማስመሰያዎችን መጠቀም፥ በጳጳሳዊው የስልጣን ተዋረድ ለዘመናት እንደ ህጋዊ ተግባራት ሲታዩ ኖረዋል። ታተ 43.2
ይህ ጥቅል ከቅዳሜ ከከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት አንሥቶ እስከ ሰኞ ማለዳ ፀሐይ መውጫ ድረስ ስራ መስራትን ይከለክላል፤ የጽሑፉ እውነተኛነትም በብዙ ተዓምራት መረጋገጡ ይነገርለት ነበር። በተከለከለው የጊዜ ገደብ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች በሽባነት እንደተያዙ ተዘግቦ ነበር። እህሉን ሊፈጭ የሞከረ አንድ ባለወፍጮ በዱቄት ፈንታ የደም ጅረት ተመለከተ፤ የውሃው ግፊት ኃይለኛ ቢሆንም የወፍጮው ተሸከርካሪ ዘንግ ግን ቀጥ ብሎ ቆመ። የዳቦ ሊጥ በመጋገሪያው ውስጥ ያስገባች አንዲት ሴት መጋገሪያው በጣም የጋለ ቢሆንም እንኳ ስታወጣው ያልበሰለ ሊጥ ሆኖ አገኘችው። በሌላ በኩል ደግሞ ሊጧን ለመጋገር ካዘጋጀች በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ሆኖባት እስከ ሰኞ ድረስ ለማስቀመጥ የወሰነች አንዲት ሴት በሚቀጥለው ቀን በአምላካዊ ኃይል ተጋግረው የተዘጋጁ ዳቦዎችን አግኝታለች። በቅዳሜ ዘጠኝ ሰዓት ዳቦ የጋገረ ሰውዬ፥ ዳቦውን በነጋታው ጠዋት ሲቆርሰው ከዳቦ ውስጥ ደም ፈሰሰ። በእንደዚህ አይነት ግራ የተጋቡና አጓጉል የእምነት ታሪኮች ነበር የእሁድ ጠበቆች ቅድስናውን ለማስፋፋት የጣሩት። (Roger de Hoveden, Annals, መጽሐፍ 2, ገጽ 528-530) ታተ 43.3
ልክ በእንግሊዝ እንደሆነው በስኮትላንድም የጥንቱን ሰንበት በጥቂቱ በመቀላቀል ለእሁድ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጠው ተደርጎ ነበር። ሆኖም ግን በቅድስና የሚጠበቀው የሰዓት ገደብ የተለያየ ነበር። የስኮትላንዱ ንጉሥ ድንጋጌ «ቅዳሜ ከቀኑ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ የተቀደሰ ሊሆን ይገባል እናም ማንም ሰው ከዚያ ሰዓት ጀምሮ እስከ ሰኞ ጠዋት ድረስ በዓለማዊ ተግባራት ሊጠመድ አይገባውም» የሚል ነበር። (Morer, ገጽ 290, 291) ታተ 43.4
የእሁድ ቅድስናን ለማስጠበቅ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም፥ ሰንበት [ሰባተኛው ቀን/ቅዳሜ] በመለኮታዊው ስልጣን እንደተመሰረተ፥ የሰባተኛው ቀን በእሁድ መተካት ምንጩ ሰብዓዊ መሆኑን ጳጳሳውያን ራሳቸው በአደባባይ ተናዘዋል። በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጳጳሳዊው ምክር ቤት በግልጽ እንዲህ ሲል አውጇል «ሰባተኛው ቀን በእግዚአብሔር ዘንድ የተቀደሰ መሆኑን አይሁዶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሰዎችም ይቀበሉትና ያከብሩት እንደ ነበር ክርስትያኖች ሁሉ ሊያስታውሱት ይገባል፤ ምንም እንኳን እኛ ክርስትያኖች የእነርሱን ሰንበት (ሰባተኛውን ቀን) ወደ የጌታ ቀን (እሁድ) የቀየርነው ብንሆንም።» (Morer, ገጽ 281, 282) የመለኮታዊውን ሕግ ያጣምሙ የነበሩት የስራቸውን ባህርይ ሳያውቁ ቀርተው አልነበረም። ሆን ብለው ራሳቸውን ከአምላክ በላይ እያደረጉ ነው እንጂ። ታተ 43.5
የሮማ ፖሊሲ ከእርሷ ጋር በማይስማሙት ላይ የምትወስደውን አቋም በአስደናቂ ሁኔታ የሚገልጸው ከመካከላቸው ጥቂቶቹ የሰንበት ጠባቂዎች በነበሩበት ዋልደንሶች ላይ ያደረሰችው ረዥምና ደም ያፈሰሰ ክደት ነው። ሌሎችም እንዲሁ ለአራተኛው ትዕዛዝ ባሳዩት ታማኝነት ስቃይ ደርሶባቸዋል። የኢትዮጵያና አቢሲኒያ አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ በተለይ በዚህ ረገድ ጉልህ ሚና አለው። በዚያ በጨለማ ዘመን በመካከለኛው አፍሪካ የሚገኙ ክርስቲያኖች በዓለም አይን በማይገቡበትና በተረሱበት ዘመን ለመቶዎች ዓመታት የእምነት ነፃነታቸውን እያጣጣሙ ቆይተዋል። በስተመጨረሻ ግን ሮም እነዚህ ሃገሮች መኖራቸውን ተገነዘበች፤ የአቢሲኒያ ንጉሥም ጳጳሱ የክርስቶስ ተወካይ መሆኑን እንዲቀበል ተሸነገለ። ሌሎች መግባባቶችም ተከተሉ። ሰንበትን [ሰባተኛውን ቀን/ቅዳሜን] መጠበቅ ከባድ ቅጣት እንደሚያስከትል የሚገልፅ ድንጋጌም ታወጀ። (Michael Geddes, Church History of Ethiopia, ገጽ 311,312 ይመልከቱ)። ሆኖም ጳጳሳዊው አረመኔያዊ አገዛዝ በጣም የሚያስጨንቅ ቀንበር ስለሆነባቸው የአቢሲኒያ ሕዝቦች ይህንን ቀንበር ከአንገቶቻቸው ሊሰብሩት ቆረጡ። ከአሰቃቂ ትግል በኋላ የሮም የበላይነት ተወገደ፥ የጥንቱ እምነትም ወደነበረበት ተመለሰ። እነዚያ ቤተ ክርስትያኖችም ስለ ነፃነታቸው ሐሴትን አደረጉ፥ እናም የሮምን አታላይነት፣ አክራሪነትና አምባገነን ኃይል ፈፅሞ ላይረሱት ትምህርት አገኙ። በራሳቸው ገለልተኛ ክልል ውስጥ ሆነው በሌላው ክርስቲያናዊ ዓለም ሳይታወቁ መኖር ለእነርሱ በቂ ነበር። ታተ 44.1
የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት የጳጳሱ ቤተክርስቲያን ወደ ፍፁም ክህደት ከመምጣቷ በፊት ትጠብቀው በነበረ ሁኔታ ሰንበትን ይጠብቁ ነበር። የእግዚአብሔር ትዕዛዝ የሆነውን ሰባተኛውን ቀን በማክበር ሲጠብቁት ሳለ እንደ ቤተክርስቲያን ልማድ ደግሞ በእሁድ ሥራ ከመስራት ይቆጠቡ ነበር። ከፍተኛ ኃይል በተቀዳጀችበት ወቅት ሮም የራሷን ሰንበት [እሁድን] ለማግነን ስትል በእግዚአብሔር ሰንበት ላይ ተረማመደችበት፤ ሆኖም የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ወደ ሺህ ለሚጠጉ ዓመታት ተደብቀው ስለቆዩ በዚህ ክህደት ውስጥ አልተሳተፉም። በሮም ተፅዕኖ ስር በወደቁበት ጊዜ እውነተኛውን ትተው ሐሰተኛውን ሰንበት እንዲያከብሩ ተገደዱ፤ ሆኖም ወዲያውኑ ባይሆንም ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ አራተኛውን ትዕዛዝ ወደ መጠበቅ ተመልሰዋል። ታተ 44.2
እነኚህ የታሪክ መዛግብት ሮም ለእውነተኛው ሰንበትና ለጠባቂዎቹ ያላትን ጥላቻ እንዲሁም እርሷ የፈጠረችውን ተቋም ለማስከበር የምትጠቀምባቸውን መንገዶች በግልፅ ያሳያሉ። የሮም ካቶሊኮችና ፕሮቲስታንቶች እሁድን ለማክበር ህብረት በሚፈጥሩበት ጊዜ እነዚህ ትዕይንቶች እንደሚደገሙ የእግዚአብሔር ቃል ያስተምራል። ታተ 44.3
በራዕ 13 ላይ ያለው ትንቢት እንደሚለው፤ እንደ በግ ቀንዶች ባሉት አውሬ የተመሰለው ኃይል «በምድርና በውስጧ የሚኖሩት» «ልክ እንደ ነብር» የተመሰለውን አውሬ - ማለትም የጳጳሱን ስርዓት - እንዲያመልኩ ያደርጋል። ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬም «በምድር የሚኖሩት ለአውሬው ምስል እንዲያደርጉ» ፤ በተጨማሪም ሁሉንም «ታናናሾችንና ታላላቆችን፣ ባለጠጎችንና ድሆችን፣ ጌቶችንና ባሪያዎችን ሁሉ» የአውሬውን ምልክት እንዲቀበሉ እንደሚያዝ ይናገራል። (ራዕይ 13፥11-16)። የበግ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉት አውሬ የሚወክለው ኃይል የአሜሪካ መንግስት መሆኑ ቀደም ሲል ተገልፆአል፥ እናም ይህ ትንቢት የሚፈፀመው ሮም የልዕልናዋ መገለጫ አድርጋ የምትወስደውን የእሁድ መከበር አሜሪካ ተፈፃሚ ስታደርግ ነው። ለጳጳሳዊው ስርዓት በምታሳየው አክብሮት አሜሪካ ብቻዋን አትሆንም። ሮም ከዚህ ቀደም በግዛትዋ ስር በነበሩ ሃገሮች ያሳደረችው ተፅዕኖ ገና አልፈረሰም ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢትም ኃይሏ እንደሚታደስ ይነግረናል። «ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ» (ቁጥር 3)። ለሞት የሆነው ቁስል የሚያመለክተው በ1798 ዓ.ም የተከሰተውን የጳጳሳዊውን ስርዓት መውደቅ ነው። ከዚህ በኋላ ይላል ትንቢት ተናጋሪው፡- «ለሞቱ የሆነው ቁስል ተፈወሰ፣ ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ።» ጳውሎስ በግልጽ «የዓመፅ ሰው እስከ ምፅአት ድረስ ይቀጥላል» ብሎ ያስቀምጣል። (2ኛ ተሰ 2፡3-8)፡፡ እስመጨረሻው ሰዓት ድረስ የማሳሳት ሥራውን ይገፋበታል። ባለ ራዕዩም ጳጳሳዊውን ስርዓት እያመለከተ «ስሞቻቸው በሕይወት መፅሐፍ ያልተፃፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሠግዱለታል ይላል» (ራዕይ 13፡8)፡፡ በሮም ብቸኛ ስልጣን በተፈጠረው የእሁድ ተቋም መከበር አማካኝነት የጥንቱም ሆነ የአሁኑ ዘመን የጳጳሳዊው ስርዓት ተቀባይነትን ያገኛል። ታተ 44.4
ከ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ አንስቶ በአሜሪካ የሚገኙ የትንቢት ተማሪዎች ይህንን ምስክርነት ለዓለም አቅርበዋል። አሁን እየሆኑ ያሉት ክስተቶች ወደዚህ ትንቢት ፍጻሜ በፍጥነት የሚመሩ እርምጃዎችን ያሣያሉ። ልክ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለመተካት ተአምራትን የፈበረኩት ጳጳሳዊ መሪዎች፥ የፕሮቴስታንት አስተማሪዎችም ያለ ምንም መፅሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ እሑድን መጠበቅ መለኮታዊ መሠረት እንዳለው አድርገው ያስተምራሉ። «የእሁድን ሰንበት በማይጠብቁት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ ይፈረድባቸዋል» የሚለው አባባል ይፈፀማል። አሁን ራሱ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገ ይገኛል። እሁድን ለማስጠበቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ በፍጥነት ተቀባይነትን እያገኘ ነው። ታተ 44.5
የሮም ቤተክርስቲያን ተንኮልና ብልህነት ግሩም ድንቅ የሚባል ነው። ምን እንደሚሆን ቀድማ ማንበብን ትችላለች። የሮም ቤተክርስቲያን፥ የፕሮቴስታንት አብያተ-ክርስትያናት ሐሰተኛውን ሰንበት በመቀበል ለእርሷ ክብርን መስጠታቸውን ስትመለከት ባለፉት ጊዜያቶች (በቀድሞ ዘመን) የሰራችውን እንድትገፋበት እያዘጋጇት ነው፥ እርሷም ይህን የተመቻቸ አጋጣሚ ትጠብቃለች። የእውነትን ብርሃን የማይቀበሉት ሁሉ ይህን ከራሷ የመነጨውን ተቋም ከፍ ለማድረግ ሲሉ በራሷ ያቆመችውን የኃያሏን ስልጣን እርዳታ ይሻሉ። እርሷም በዚህ ረገድ ፕሮቴስታንቶችን ለመርዳት ምን ያህል ዝግጁ እንደምትሆን ለመገመት አያዳግትም። ደግሞም ቤተክርስቲያንን የማይታዘዙትን በተመለከተ ምን መደረግ እንዳለበት ከጳጳሳዊ መሪዎች በበለጠ ማን ሊረዳ ይችላል? ታተ 45.1
የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን፥ በመላው ዓለም ካሉ ተከታዮቿ ጋር አንድ ትልቅ የጳጳሳዊን ስርዓት የሚያስከብር በቁጥጥሩ ስር የሚኖር አንድ ትልቅ ተቋም ያቋቁማል። በመላው ዓለም በሚገኙ ሃገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መልዕክተኞች ራሳቸውን ለጳጳሱ ታማኝ አድርገው እንዲጠብቁ ይታዘዛሉ። የማናቸውም ዜጋ ወይም መንግስት ቢሆኑም የቤተክርስትያንን ስልጣን ከሁሉ በላይ አድርጎ መመልከት ይኖርባቸዋል። ምንም እንኳን ለመንግስት ታማኝ ለመሆን ቃለ መሃላ ቢገቡም፥ ማንኛውም ከእርሷ ጥቅም ጋር የሚፃረር ነገር ከሆነ ግን ይቅርታን የሚያሳጣቸው ሌላ ከሮም ጋር የተገነባ ቃለ መሃላ ከበስተጀርባው ይገኛል። ታተ 45.2
ሮም ጥበብ በተሞላበትና ባላሰለሰ ጥረት በመንግስታት ጉዳይ ውስጥ እንዴት መቆናጠጫ አግኝታ እንደምትገባና ሕዝብንና መሳፍንትን የሚያጠፋ እንኳን ቢሆን የራሷን ዓላማዎች ከማስፋፋት ወደኋላ እንደማትል ታሪክ ይመሰክራል፡፡ በ1204 ዓ.ም ሳልሳዊ ጳጳስ ኢኖሰንት ከአራጎን ንጉሥ ከዳግማዊ ጴጥሮስ የሚከተለውን አስገራሚ ቃለ መሃላ አግኝቶ ነበር፡፡ «እኔ ጴጥሮስ፣ የአራጎንያኖች ንጉሥ፣ ለጌታዬ ለጳጳስ ኢኖሰንት፣ ለካቶሊክ ተተኪዎቹ እንዲሁም ለሮማ ቤተክርስቲያን ታማኝና ታዛዥ ልሆን፣ መንግስቴንም በትዕዛዙ ስር በታማኝነት ላፀና፣ በክህደት የሚመላለሱትን ለማሳደድና ለማጥፋት፣ የካቶሊክን እምነት ልጠብቅ ቃል መግባቴን በአፌ እመሰክራለሁ፡፡» (John Dowling, The History of Romanism b.s ch.6 sec 55) ይሄም «የሮማ ቀሳውስት መንግስታትን ቃል ለማስገባትና ዜጎቻቸውንም በፅድቅ ለማይመራቸው መሪዎች ከሚኖርባቸው የዜግነት ግዴታ ነፃ ለማውጣት ስልጣን አለን» ከሚሉት መመሪያ ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ (Mosheim ,b.3, cent 11, pt 2, ch 2, sec. 9, Not 17) ታተ 45.3
ሮም ፈፅሞ አለመለወጧ የምትኮራበት መሆኑ ሊታወስ ይገባል። የጎርጎሪዎስ ሰባተኛና የሳልሳዊ ኢኖሰንት መርሖዎች ዛሬም የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መርሆዎች ናቸው። ዛሬ ስልጣኑ ቢኖራት ኖሮ ባለፉት ምዕተ-ዓመታት ካደረገችው በበለጠ ስልጣኗን ተግባራዊ ታደርገው ነበር። ፕሮቴስታንቶች እሁድን በማክበሩ ረገድ የሮምን እርዳታ ሲቀበሉ ምን እያደረጉ እንዳሉ በቅጡ አይረዱትም። እነርሱ የራሳቸውን ዓላማ በማሳካቱ ላይ ብቻ ሲያተኩሩ ሮም ግን ኃይሏን እንደገና ለማደራጀት፣ ያጣችውን የበላይነትም ለማስመለስ እያለመች ነው። በአሜሪካ ቤተክርስቲያን እንደገና በመንግስት ጉዳይ እጇን ማስገባት ወይም ቁጥጥር ማድረግ ከጀመረች ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በዓለማዊ ሕጎች መፈፀም ይጀምራሉ። በቅርብ ጊዜ የቤተክርስቲያን እና የመንግሥት ስልጣን ሕሊናን መቆጣጠር ይጀምራሉ፤ እናም የሮም ድል መንሳት በዚህች አገር የተረጋገጠ ይሆናል። ታተ 45.4
የእግዚአብሔር ቃልም ሊመጣ ስላለው አደጋ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፤ ይህ ካልታወሰ የፕሮቴስታንቱ ዓለም የሮምን ዓላማዎች በትክክል ምን እንደሆነ የሚረዳው ከወጥመዱ ለማምለጥ እጅግ ከዘገየ በኋላ ነው። የሮም ኃይል ቀስ በቀስ እያደገ ነው። ሃይማኖታዊ ትምህርቷ በሕግ አውጪ አካላት መሰብሰቢያዎች ውስጥ፣ በአብያተ ክርስቲያናትና በሰዎች ልብ ውስጥ ተፅኖአቸውን እያሳደሩ ይገኛሉ። ባለፈው ያደረገቻቸውን የማሳደድ ድርጊቶችን ለመድገም ታላላቅና ከባድ እቅዶቿን በፀጥታና በሚስጥር እያጠናከረች ትገኛለች። ድምጽዋን አጥፍታ በማይገመት ሁኔታ ጊዜዋ እስከሚደርስበት ድረስ እቅዶቿን የምታሳካበትን ኃይል እያጠናከረች ትገኛለች። የምትፈልገው ነገር ቢኖር የተመቻቸ እድል ብቻ ነው፥ ይህም ደግሞ እየተሰጣት ነው። የሮም እቅድ ምን እንደሆነ በቅርቡ እናያለን፥ እንረዳለንም። የእግዚአብሔርን ቃል የሚያምንና የሚታዘዝ ሁሉ ተቃውሞና ስደት ይደርስበታል። ታተ 45.5