ታላቁ ተስፋ

7/15

ሙታን ሊያነጋግሩን ይችላሉን?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው የቅዱሳን መላዕክቶች አገልግሎት ለእያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ የሚያጽናና እና የከበረ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያስተምረው እውነት በአንዳንድ የተሳሳተ የስነ-መለኮት አስተምህሮ ተበላሽቷል፡፡ የአለመሞት (Immortality) ትምህርት በመጀመሪያ በአረማዊያን ፍልስፍና፣ ቀጥሎም በታላቁ የቤተክርስቲያን የጨለማ ዘመን ወደ ክርስትና ሃይማኖት ሰርጎ የገባ ሲሆን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ «ሙታን አንዳች አያውቁም» የሚለውን እውነት መርዟል፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙዎች «የሙታን መናፍስት የድነት ወራሽ ለሆኑት የተላኩ አገልጋይ መልዕክተኞች ናቸው» ወደሚል እምነት መጥተዋል፡፡ ይህም ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስ ስለ የሰማይ መላዕክት እና ከሰዎች ጋር ስላላቸው አይነት ግንኙነት ከሚያስተምረው አስተምህሮ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ታተ 31.1

«ሰው ከሞተ በኋላ በምድር ስለሚሆነው ነገር ሁሉ ያውቃል፣ በተለይም ደግሞ የሙታን መናፍስት ተመልሰው በሕይወት ያሉትን ማገልገል ይችላሉ» የሚለው እምነት ለዘመናዊው መናፍስታዊነት (Spiritualism = ከመናፍስት ጋር መገናኘት ይቻላል የሚል ትምህርት) መንገድን ጠርጓል፡፡ ሙታን በእግዚአብሔርና በቅዱሳን መላዕክት ፊት መቅረብ ከቻሉ፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት ከነበራቸው እውቀት የበለጠ የታደሉ ከሆኑ፣ ለምንድን ነው ወደ ምድር ተመልሰው በሕይወት ላሉቱ እውቀትና ትምህርት የማይሰጡት? የታወቁ የስነ መለኮት አስተማሪዎች እንደሚያስተምሩት የሞቱት መናፍስት በምድር ላይ ከሚገኙት ወዳጆቻቸው በላይ መንሳፈፍ ከቻሉ ለምን ከእነርሱ ጋር መነጋገርና ከክፋት እንዲጠበቁ ማስጠንቀቅ ወይም በሃዘናቸው እነርሱን ማጽናናት እንዲችሉ አልተፈቀደላቸውም? «ሰው ከሞተ በኋላ በምድር ስለሚከሰቱት ነገሮች ሁሉ ያውቃል» ብለው የሚያምኑ ሰዎች እንዴት በተከበሩ መናፍስት ወደ እነርሱ የሚመጣውን መለኮታዊ ብርሃን ሊቃወሙ ቻሉ? ይህ እንደ ቅዱስ መስሎ የሚታይ ነገር ሰይጣን ተልዕኮውን ለመፈጸም የሚጠቀምበት መንገድ ነው፡፡ ከሰማይ የተባረሩት መላዕክት ከመናፍስት ዓለም አንደመጡ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ «ሕያዋንን ከሙታን ጋር እናገናኛለን» በሚሉበት ጊዜ የክፋት ልዑል የሆነው ሰይጣን በአዕምሮአቸው ውስጥ የጥንቆላ ተጽዕኖውን ያካሂዳል፡፡ ታተ 31.2

እርሱ የሞቱትን ወዳጆቻቸውን ምስል በፊታቸው የማምጣት ሃይል አለው፡፡ የማስመሰል ሃይሉ ፍጹም ነው፡- ተመሳሳይ መልክ፣ ተመሳሳይ ቃላቶች፣ ተመሳሳይ ድምጽ፣ እነዚህን ሁሉ ከእውነተኛው ጋር እጅግ ተመሳሳይ አድርጎ ያቀርባቸዋል፡፡ ብዙዎችም ወዳጆቻቸው የሰማይን ደስታ እያጣጣሙ እንደሆነ ሲመለከቱ ይጽናናሉ፡፡ ይህ ምንም አይነት አደገኛነት እንደሌለው ባለመጠራጠር ጆሮአቸውን «ለሚያስቱ መናፍስት እና ለዲያብሎስ ትምህርት» ይሰጣሉ፡፡ ታተ 31.3

ሙታን ከእነርሱ ጋር ለመነጋገር ወደ እነርሱ እንደሚመለሱ ካመኑ በኋላ፣ ሰይጣን ሳይዘጋጁ የሞቱትን (በመቃብር ውስጥ ያሉትን) እንዲገለጡ በማድረግ በሰማይ ደስተኞች እንደሆኑና በዚያም ከፍ ያሉ ቦታዎች እንደያዙ ሲመሰክሩ እንዲያደምጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ «በጻድቃንና በኃጢአተኞች መካከል ምንም ልዩነት የለም» የሚለውን የስህተት ትምህርት ያስተምራል፡፡ ከመናፍስት ዓለም የመጡ እነዚህ አስመሳይ እንግዶች አንዳንድ ጊዜ እውነተኛ የሆኑ ማስጠንቀቂያዎችን ይናገራሉ፡፡ ይህንን በማድረግ አመኔታን ካገኙ በኋላ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን አመኔታ የሚቀንሱ ትምህርቶችን ያቀርባሉ፡፡ በምድር ላይ ላሉት ለወዳጆቻቸው ደህንነት በጣም እንደሚጨነቁ በማስመሰል በጣም አደገኛ ስህተቶችን በእጅ አዙር (ቀጥታ ባልሆነ መንገድ) ያስተጋባሉ፡፡ የሚናገሩት ነገር አንዳንዱ እውነትነት ስላለው እንዲሁም ወደፊት ስለሚከሰቱት ክስተቶች መፈፀም አልፎ አልፎ አስቀድመው መናገር ስለሚችሉ፣ ለሚናገሩት ዓርፍተ ነገር አመኔታ ይሰጣቸዋል፡፡ ሐሰተኛ ትምህርቶቻቸውም በብዙዎች ልክ እንደተቀደሰ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ ወደ ጎን ይደረጋል፣ የጸጋም መንፈስ ይናቃል (ይረክሳል)፣ የኪዳኑም ደም እንደ ርኩስ ነገር ይቆጠራል፡፡ መናፍስት የክርስቶስን መለኮትነት ይክዳሉ፣ ራሳቸውን ከፈጣሪ ጋር በአንድ ደረጃ ላይ ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህም አይነት ታላቁ አመጸኛ በአዲስ ድብቅ መልክ በእግዚአብሔር ላይ ጦርነቱን ማኪያሄድ ይቀጥላል፡፡ ይህም ጦርነት በሰማይ የተጀመረና በምድር ላይ ወደ ስድስት ሺህ ዓመታት የሚጠጋ ጊዜን ያስቆጠረ ነው፡፡ ታተ 31.4

«መናፍስታዊ መገለጦች ሙሉ በሙሉ ውሸት እና በመናፍስት ጠሪዎች ጥበብ የተሞሉ የማጭበርበር ውጤቶች ብቻ ናቸው» በማለት ብዙዎች ይህንን ጉዳይ እንደ ቀላል ነገር ያዩታል፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ ተራ ማስመሰሎች እንደ እውነተኛ መገለጥ ተደርገው የቀረቡ ቢሆንም ቅሉ በሌላ በኩል ደግሞ በእርግጥ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆኑ ኃይላትም ሲገለጡ ይታያሉ፡፡ ዘመናዊው መናፍስታዊነት የጀመረባቸው ሚስጥራዊ ዘዴዎች እንዲሁ ተራ ሰብዓዊ ማታለሎች ወይም ሰብዓዊ ጥበቦች ሳይሆኑ፤ እጅግ በተሳካ መልኩ ነፍስ-አጥፊ ክፋትን የሚያሰራጩ የርኩሳን መላእክት ሥራ ናቸው፡፡ ብዙዎች «መናፍስታዊነት ተራ የሰዎች ማስመሰል ነው» በሚል እምነት ይጠመዳሉ፤ ከዚያም ያለ ምንም ጥያቄ ከሰብዓዊ ጥበብ በላይ ከሆኑ ለመካድ ከማይቻሉ መገለጦች ጋር ፊት ለፊት ሲጋፈጡ ያኔ ይታለላሉ፤ እነዚያንም መገለጦች እንደ ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል አድርገው ወደ መቀበል ይደርሳሉ፡፡ ታተ 32.1

እነኚህ ሰዎች በሰይጣንና በግብረአበሮቹ የሚፈፀሙትን ተዓምራቶች በተመለከተ በመፅሐፍ ቅዱስ በግልፅ የተፃፈውን ማየት ይሳናቸዋል፡፡ የፈርዖን አስማተኞች የእግዚአብሔርን ሥራ አስመስለው መሥራት ችለው የነበረው በሰይጣን ድጋፍ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ዳግም ምፃት በፊት በሰይጣናዊ ኃይላት ተመሳሳይ ነገሮች እንደሚገለጡ ጳውሎስ መስክሯል፡፡ ከክርስቶስ ዳግም ምፃት በፊት «በተዓምራት ሁሉና በምልክቶች፣ በሃሰተኞች ድንቆችም፣ በአመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሰራር» (2 ተሰ 2፡9-10) ያለው ሊገለጥ ግድ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚመጣውን ተዓምር ሰሪ ኃይል ሲገልጥ እንዲህ ይላል፡- «እሳትንም እንኳን ከሰማይ ወደ ምድር እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል፡፡ በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሳ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፡” (ራዕ. 13፡13-14)፡፡ እዚህ ላይ የተነገሩት በምንም ዓይነት መልክ ተራ ማስመሰሎች አይደሉም፡፡ የሰይጣን ተላላኪዎች እንዳደረጉት በሚያስመስሏቸው ተአምራት ሳይሆን በእርግጥም በሚያደርጓቸው (በሚያሳዩዋቸው) ተአምራት ሰዎች ይታለላሉ፡፡ ታተ 32.2

እጅግ ጠቢብ የሆነውን አዕምሮውን የማታለል ተግባራትን ብቻ ለማድረግ ያሰለጠነው የጨለማው ልዑል ፈተናዎቹን በሁሉም ጎራ እና ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሰዎች ገጣሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ሰዎች መናፍስታዊነትን እንዲሁ በጥበብ እና በምሁራዊ አቀራረብ በማቅረብ ብዙዎችን ለማጥመድ ይሳካለታል፡፡ መናፍስታዊነት የሚሰጠው ጥበብ ሐዋሪያው ያዕቆብ፡- «ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም ነገር ግን የምድር ነው፣ የሥጋም ነው፣ የአጋንትም ነው» በማለት ያስቀመጠው ጥበብ ነው (ያዕ. 3፡15)፡፡ ይህንን መሸፋፈን ዓላማውን የበለጠ የሚያሳካለት ሆኖ ካገኘው ታላቁ አታላይ ይሸፋፍነዋል፡፡ በምድረ በዳ ሲፈትነው ሳለ በክርስቶስ ፊት የሰማይን ሱራፌል መስሎ ብሩህ ሆኖ ቀርቦ የነበረው፤ ወደ ሰዎች ሲመጣ ደግሞ እጅግ በሚስብ መልኩ የብርሃን መልአክ መስሎ ነው የሚመጣው፡፡ የመጠቁ ርዕሶችን በማቅረብ አዕምሮን ይስባል፣ በሚማርኩ ስዕላዊ ገፅታዎች ምኞትን ያስደስታል፣ ፍቅርንና ቸርነትን አሽሞንሙኖ በማቅረብ ልብን ይማርካል፡፡ አስተሳሰብን በመጠቁ ከፍታዎች ላይ በማብረር ያነቃቃል፤ በዚህም፣ ሰዎች በራሳቸው ጥበብ በእጅጉ እንዲኮሩና ዘላለማዊ የሆነውን ግን እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል፡፡ የዓለም አዳኝን እጅግ ረጅም ወደ ሆነው ተራራ ላይ አውጥቶ የዓለምን መንግስታት ክብራቸውንም በፊቱ ያሳየው ኃያል ፍጡር ወደ ሰዎችም ፈተናውን ይዞ የሚቀርበው በመለኮታዊ ከለላ ያልተሸፈኑትን ሰዎች ሁሉ ስሜቶች በሚያዛባ መልኩ ነው፡፡ ታተ 32.3

ሰይጣን ልክ ያኔ በኤደን ገነት ሄዋንን እንዳማለለ ዛሬም ሰዎችን ያማልላል፣ የተከለከለ እውቀትን ለማግኘት እንዲቋምጡ ያነሳሳቸዋል፣ ራሳቸውን የማግነን (ከፍ የማድረግ) ውስጣዊ መሻትንም ይቀሰቅስባቸዋል፡፡ እነዚህ ክፉ ምኞቶች የራሱን ውድቀት ስላስከተሉ አሁን ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ ሰዎችን ለማጥፋት ተነስቶአል፡፡ «እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉውን የምታውቁ ትሆናላችሁ» በማለት ያውጃል (ዘፍ. 3፡5)፡፡ መናፍስታዊነት የሚያስተምረው ትምህርት፡- «ሰው የእድገት ፍጡር ነው፣ ፍጻሜውም ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ እያደገ እስከ ዘላለማዊነት፣ ራስ እስከሆነው እስከ እግዚአብሔር መድረስ ነው» የሚል ትምህርት ነው፡፡ በመቀጠልም «እያንዳንዱ አእምሮ በራሱ ላይ ይፈርዳል እንጂ ሌላው በእርሱ ላይ አይፈርድም» «ፍርዱም ትክክል ይሆናል ምክንያቱም ራስ-ፍርድ ስለሆነ…» «ዙፋኑ ያለው በውስጥህ ነው» በማለት ያስተምራል፡፡ አንድ መናፍስታዊ መምህር «መንፈሳዊ ህሊናው» በተነቃቃ ጊዜ እንዲህ በማለት አስተምሮ ነበር፡- «ከእኔ ጋር ያሉት ወዳጆቼ ሁሉ ሁላቸውም በኃጢአት ያልወደቁ ግማሽ አምላክ ናቸው፡፡» ሌላውም መምህር ቀጥሎ እንዲህ በማለት ተናገረ፡- «ማንኛውም ጻድቅ እና ፍጹም የሆነ ፍጡር ሁሉ ክርስቶስ ነው፡፡» ታተ 32.4

በመሆኑም አምልኮ በሚገባው በዘላለማዊው የእግዚአብሔር ጽድቅ እና ፍጽምና ምትክ፣ የሰዎች ተግባር ሁሉ መለኪያ በሆነው ጻድቅና ፍጹም ሕጉ ምትክ፤ ኃጢአተኛውንና አጥፊውን የሰው ተፈጥሮ መለኪያ ይሆን ዘንድ ሰይጣን ተክቶታል፡፡ መመለክ የሚገባው እራሱ ሰው እንደሆነ፣ የፍርድ እና የባህርይ መለኪያም (መመዘኛም) እርሱ ብቻ እንደሆነ ሰይጣን ሰውን አስተምሯል፡፡ በእርግጥ ይህ እድገት ወደላይ ሳይሆን ነገር ግን ቁልቁል እድገት ነው፡፡ ታተ 32.5

የአእምሮም ሆነ የመንፈሳዊ ሕግ የሚያስተምረው በመመልከት የምንለወጥ መሆኑን ነው፡፡ በሂደት እናብሰለስለው ዘንድ ራሳችን ለምንፈቅድለት ለዚያ ሀሳብ (ማንነት) አእምሮአችን በሂደት ራሱን ለዚያ ሃሳብ ያለማምዳል፡፡ ያፈቀርነውንና የተመሰጥንበትን፣ ልምዳችን የሆነውን ነገር አእምሮአችን ያንን እየመሰለ ይሄዳል፡፡ ሰው በራሱ መለኪያ ካስቀመጠው ንፅህና ወይም መልካምነት ወይም እውነት መለኪያው በላይ በፍፁም ከፍ ሊል አይችልም፡፡ እኔነት የእርሱ ታላቅ ዓላማ ከሆነ ከዚያ የከበረ ነገር ሊያገኝ ከቶውኑ አይችልም፡፡ ይልቁኑ ያለማቋረጥ እየዘቀጠ እየዘቀጠ ይሄዳል፡፡ ሰውን በእርግጥ ከፍ ሊያደርግ፣ ሊያገንን የሚችል ብቸኛው የእግዚአብሔር ፀጋ ነው፡፡ ራሱን በራሱ እንዲመራ የተተወ ሰው የሚሄደው ጉዞ ያለ አንዳች ጥርጥር ወደ ቁልቁል ነው፡፡ ታተ 33.1

በስሜታቸው ለሚመሩት፣ ተድላን ለሚወዱት፣ በሥጋቸው ለሚመሩት ሰዎች መናፍስታዊነት የሚገለጠው ለምሁራን እና ለጠቢባን በሚገለጥበት አይነት መልኩ አይደለም (ራሱን ለተማሩት ሲያቀርብ የሚያጠልቀውን አይነት ጭምብል አጥልቆ አይደለም የሚገለጠው)፤ ምክንያቱም መናፍስታዊነት ጠቅለል ባለ መልኩ ከዝንባሌያቸው ጋር የሚጣጣም ስለሆነ፡፡ ሰይጣን የእያንዳንዱን ሰብአዊ ተፈጥሮ ደካማ ጎን የሚጠቁመውን ምልክት በጥንቃቄ ያጠናል፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ሊፈፅማቸው የሚያስባቸውን ኃጢአቶች ለይቶ ይመዘግባቸዋል፤ ከዚያም ያ ግለሰብ በኃጢአት እንዲወድቅ በጥንቃቄ የተለያዩ ዕድሎችን (አጋጣሚዎችን) ይፈጥርለታል፡፡ ሰዎች መልካምና ትክክል የሆኑትን ነገሮች ከልክ በላይ እንዲያደርጉት በማባበል፣ መሻትን ባለመግዛት ምክንያት አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና ስነ-ምግባራዊ ኃይላቸው እንዲዳከም ያደርጋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሺህዎች የሚቆጠሩትን ሰዎች ሕይወት ያፈራረሰ ሲሆን ዛሬም ቢሆን በሥጋዊ መሻታቸው እንዲዘፈቁ በማድረግ ህይወታቸውን እያፈራረሰ በአጠቃላይ የሰውን ማንነት በዘግናኝ መልኩ እያወደመ ይገኛል፡፡ ይህን ሥራውን ለማጠናቀቅ ታዲያ በመናፍስቱ በኩል እንዲህ በማለት ያውጃል «እውነተኛ እውቀት ሰውን ከሁሉም ሕጎች በላይ ያስቀምጠዋል» «ሁሉም ነገር እርሱ ትክክል ነው» «እግዚአብሔር አይኮንንም» «ማንኛቸውም የተፈፀሙ ኃጢአቶች ባለማወቅ የተፈፀሙ ናቸው»፡፡ እንግዲህ በዚህ አማካኝነት ሰዎች «ምኞት ከፍተኛው ሕግ እንደሆነ» ወደ ማመን ከተነዱ፣ «ነፃነት የተፈለገውን ለማድረግ ፈቃድ ሰጪ ነው» ከተባለና «ሰው ተጠሪነቱ (ተጠያቂነቱ) ለራሱ ብቻ ነው» ከተባለ በሁሉም ቦታ የሞራል ውድቀትና ክፋት ቢስፋፋ ማን ይገረማል? በርካታ ሰዎች የሥጋዊ ልባቸውን መሻቶች እንዲታዘዙ ነፃነት የሚሰጧቸውን አስተምህሮዎች በጉጉት ይቀባሏቸዋል፡፡ ራስን የመግዛት ኃይል ምኞትን በማርካት ፍላጎት ይተካል፡፡ የህሊናና የነፍስ ኃይሎች ለእንስሳዊ ጋጠ-ወጥነት ይገዛሉ፤ በዚህም ሰይጣን በታላቅ ደስታ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸውን ከሚያውጁቱ በሺህዎች የሚቆጠሩትን ወደ መረቡ ይሰበስባል፡፡ ታተ 33.2

ነገር ግን ማንም በመናፍስታዊነት የሃሰት ትምህርት ሊታለል አይገባም፡፡ ወጥመዱን ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔር ለዓለም በቂ ብርሃን ሰጥቷል፡፡ አስቀድሞ እንደተገለፀው የመናፍስታዊነት ትምህርት የተገነባበት መሠረተ ፅንሰ ሀሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ግልፅ ትምህርት ጋር እጅግ የሚቃረን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «ሙታን አንዳች አያውቁም»፤«ሀሳባቸው ሁሉ ጠፍቷል»፤ «ከፀሐይ በታችም በሚደረገው አንዳች ነገር ውስጥ ዕድል ፈንታ የላቸውም»፤ «በምድር ላይ ያሉ እጅግ የሚቀርቧቸው ወዳጆቻቸው ያጋጠሟቸውን ደስታዎችም ሆነ ሀዘኖች በተመለከት አንዳች የሚያውቁት የለም» ነው የሚለው፡፡ ታተ 33.3

ከዚህ በተጨማሪም እግዚአብሔር ከሙታን መናፍስት ጋር የሚደረጉትን ማናቸውንም ግንኙነቶች በግልፅ አውግዟል፡፡ በዕብራዊያን ዘመን ልክ የዛሬዎቹ መናፍስት ጠሪዎች እንደሚሉት፣ «ከሙታን ጋር ግንኙነት አለን» የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነኚህ ከሌላው ዓለም የሚመጡት ጎብኚዎች «የመናፍስት ጠሪዎች» ተብለው ቢጠሩም ቅሉ መጽሐፍ ቅዱስ ግን «የሰይጣን መናፍስት» እንደሆኑ ይናገራል፡፡ (እነኚህን ጥቅሶች ያነፃፅሩ ዘሁ. 25፡1-3፣ መዝ. 106፡28፣ 1ቆሮ. 10፡20፣ ራዕ. 16፡14)፡፡ ከመናፍስት ጠሪዎች ጋር ግንኙነት የማድረግ ተግባር በግልፅ በእግዚአብሔር ላይ አመፅ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን በጥብቅ የተከለከለና በሞትም የሚያስቀጣ ወንጀል ነበር (ዘሌ. 19፡31፣ ዘሌ. 20፡27)፡፡ ዛሬ ዛሬ «አስማተኛ» የሚለው ቃል ራሱ የተጠላ ነው፡፡ «ሰዎች ከክፉ መናፍስት ጋር ግንኙነት ሊያደርጉ ይችላሉ» የሚለው ሀሳብ ከጨለማው ዘመን ተረቶች እንደ አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በመቶ ሺህዎች፣ እንዲያውም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት፣ ወደ ሳይንስ ቀጠና የዘለቀው፣ ቤተክርስትያናትን የወረረው እና በሕግ አውጭዎች ዘንድ፣ እንዲያውም በነገሥታት ዘንድ ሳይቀር ተቀባይነትን ያገኘው መናፍስታዊነት፤ ይህ ግዙፍ ማታለል ሌላ ምንም ሳይሆን አዲስ ጭምብል አጥልቆ የወጣ የቀድሞው የተወገዘ እና የተከለከለ አስማተኝነት መነቃቃት ነው፡፡ ታተ 33.4

ሌላ ምንም የመናፍስታዊነት ግልፅ መገለጫዎች እንኳ ባይኖሩም ለክርስቲያኑ እነዚህ መናፍስት በጽድቅ እና በኃጢአት፣ የከበሩና ንፁህ በሆኑት በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እና በሰይጣን አገልጋዮች መካከል ምንም አይነት ልዩነት አለማድረጋቸው ብቻውን ለአንድ ክርስቲያን በቂ ማስረጃ ሊሆን ይገባል፡፡ በምድር ህይወታቸው የላሸቀ ስነ ምግባር የነበራቸውን ሰዎች በሰማይ እንዳሉ እና በዚያም እጅግ የተከበሩ እንደሆኑ አድርጎ በማቅረብ ሰይጣን ለዓለም እንዲህ ይላል፡- «የፈለገውን ያህል ኃጢአተኛ ብትሆን፣ በእግዚአብሔርና በመጽሐፍ ቅዱስም አመንክ አላመንክ፣ ደስ እንዳሰኘህ ኑር! ሰማይ እንደሆን ቤትህ ነው!»፡፡ እነኚህ መንፈሳዊ መምህራን በአደባባይ እንዲህ በማለት ያውጃሉ፡- «ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፣ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል፤ ወይስ የፍርድ አምላክ ወዴት አለ?» (ሚል. 2፡17):: የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላል፡- «ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፣ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፣ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!»፡፡ (ኢሳ. 5፡20) ታተ 33.5

ሐዋርያት በሕይወት በነበሩበት ዘመን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጻፏቸውን መልእክቶች እነዚህ ሀሰተኛ መንፈሶች በሐዋሪያት ተመስለው በተቃራኒ መልኩ ያቀርቧቸዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ መለኮት መሆኑን በመካድ የክርስቲያን ተስፋን መሠረት ያስወግዳሉ፣ ወደ ሰማይ የሚወስደውን መንገድ የሚያሳየውን ብርሃንም ያጠፋሉ፡፡ ሰይጣን «መጽሐፍ ቅዱስ ተራ ልብ ወለድ ታሪክ ነው» ብላ ዓለማችን እንድታምን እያደረጋት ይገኛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን ይኖሩ ለነበሩት ገጣሚ የነበረ፣ ዛሬ ግን ቀለል ብሎ ሊታይ የሚገባው ወይም ዘመን ያለፈበት ስለሆነ ገሸሽ ሊደረግ የሚገባው እንደሆነ አድርጎ ሰይጣን ዓለምን ለማሳመን ይጣጣራል፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ፋንታ መናፍስታዊ መገለጦችና ተአምራትን በመተካት ሰዎች እንዲያምኑ ያደርጋል፡፡ በዚህ አማካኝነት ነው ዓለምን ሙሉ በሙሉ በእርሱ ቁጥጥር ስር የሚያደርገው፣ በዚህ አማካኝነት ነው ዓለማችን እርሱ የሚፈልገውን እንድታምን የሚያደርገው፡፡ እርሱንና ተከታዩቹን የሚኮንነውን መጽሐፍ እርሱ እንደሚፈልገው በጨለማ ያስቀምጠዋል፡፡ የዓለምን አዳኝ ከማንኛውም ሰው እኩል እንደሆነና እርሱ በምንም ከማንም የማይበልጥ እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ የክርስቶስን መቃብር ይጠብቅ የነበረው ሮማዊ ወታደር የኢየሱስን ትንሳኤ በተመለከተ የውሸት ዜናን እንደለፈፈ እና ካህናቱና ሽማግሌዎቹም ይህን ተቀብለው በማስተጋባት ትንሳኤውን እንዳስተባበሉ ሁሉ በመናፍስታዊ መገለጦችና ምልክቶች የሚያምኑ ሁሉ በአዳኛችን የምድር ሕይወት ክስቶች ውስጥም ምንም ተዓምራዊ ነገር የለበትም በማለት ተመሳሳይ ነገርን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መልኩ ክርስቶስን ከመጋረጃው በስተጀርባ እንዲቀመጥ ጥረት ካደረጉ በኋላ ትኩረትን ሁሉ ወደ ራሳቸው ተአምራት በመሳብ «እነኚህ ተአምራቶች ክርስቶስ ካደረጋቸው በእጅጉ ይበልጣሉ» በማለት ያውጃሉ፡፡ ታተ 34.1

እርግጥ ነው ዛሬ ዛሬ መናፍስታዊነት መልኩን እየለወጠ እንዲሁም ተቃውሞ የሚያስነሱበትን ገፅታዎች እየጋረደ የክርስትናን ጭንብል እያጠለቀ ይገኛል፡፡ በመድረክም ሆነ በህትመት ውጤቶች በኩል የሚያስተላልፉቸው መልእክቶች ለብዙ ዓመታት ያህል በህዝብ ፊት ቀርበዋል፡፡ እነኚህ አስተምህሮዎች ሊካዱ ወይም ሊደበቁ አይችሉም፡፡ ታተ 34.2

የአሁኑ ገፅታው ከቀድሞው ይልቅ በፍፁም ሊታገሱት የሚገባ አይደለም፡፡ ይልቁኑ በአሁኑ ዘመን እጅግ የረቀቀ በመሆኑ በእርግጥ አደገኛነቱ የከፋ ሆኗል፡፡ ከዚህ ቀደም ክርስቶስንና መጽሐፍ ቅዱስን ያወግዝ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ሁለቱንም እንደሚቀበል ይናገራል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልፅ እና ድርድር የማያስፈልጋቸው ቁልጭ ያሉ እውነቶች ላልተለወጠው ልብ በሚስማማበት መልኩ ይተረጎማሉ፡፡ ፍቅር የእግዚአብሔር ዋነኛው ባህሪ በመሆኑ ላይ እጅግ በማተኮር ፍቅር ወደ ተራ ስሜታዊነት ወርዶ በመልካምና በክፉው መካከል ያለውን ልዩነት አናሳ ያደርጋል፡፡ የእግዚአብሔር ፍትህ፣ በኃጢአት ላይ ያለው ውግዘት፣ የቅዱስ ሕጉ መጠይቆች፤ እነዚህ ሁሉ ትኩረት አይሰጣቸውም፡፡ ሰዎች አስርቱ ትእዛዛትን እንደሙት ደብዳቤ እንዲቆጥሯቸው ይማራሉ፡፡ አስደሳችና አማላይ ተረቶች ስሜትን ይማርኩና ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አንደ እምነታቸው መሠረት አድርገው እንዳይቀበሉ ያደርጓቸዋል፡፡ ክርስቶስ ልክ እንደ ቀድሞው በእርግጥ ይካዳል፡፡ ነገር ግን ማታለሉ እንዳይታወቅበት ሰይጣን የሰዎችን ዓይኖች ያሳውራል፡፡ ታተ 34.3

የመናፍስታዊነትን (ከመናፍስት ጠሪዎች ጋር ግንኙነትን የማድረግን) የማታለል ኃይል እና በተፅዕኖው ውስጥ የመውደቅን አደገኛነት በተመለከተ ትክክለኛው መረዳት ያላቸው ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ብዙዎች ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት ለማርካት ያህል ብቻ ከዚህ ጋር አጉል ዕቃቃ ይጫወታሉ፡፡ በነገሩ ላይ እውነተኛ የሆነ እምነት የላቸውም፡፡ እንዲያውም ራሳቸውን ለመንፈሱ ቁጥጥር አሳልፎ መስጠትን ሲያስቡ በሚዘገንን ስሜት ይሞላሉ፡፡ ነገር ግን በተከለከለው ቀጠና ውስጥ በመንቀሳቀስ ቁማር ይጫወታሉ፣ ከዚያም ታላቁ አጥፊ ከፈቃዳቸው በተቃራኒ ኃይሉን በእነርሱ ላይ ይጠቀማል፡፡ አንዴ ብቻ አዕምሯቸውን ለእርሱ አቅጣጫ ለማስገዛት ይጀምሩ እንጂ ምርኮኞች አድርጎ ይይዛቸዋል፡፡ ከዚህ ከሚያማልለውና ልብን ከሚሰርቀው ምርኮ በራሳቸው አቅም ለማምለጥ ፈፅሞ የማይቻል ነው፡፡ ለልባዊ የእምነት ፀሎት ምላሽ ሆኖ ከሚለገስ የእግዚአብሔር ኃይል ሌላ እነኚህን ወጥመድ ውስጥ የገቡ ነፍሳትን ሊታደግ የሚችል ሌላ ምንም የለም፡፡ ታተ 34.4

ከኃጢአት ባህሪ ጋር እቃ እቃ የሚጫወቱ ሁሉ ወይም ደግሞ ፈቅደው ግልፅ የሆነን ኃጢአት በውስጣቸው የሚንከባከቡ የሰይጣንን ፈተና እየጋበዙ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር እንዲሁም ከመላዕክቱ የጥበቃ ክብካቤ ራሳቸውን እየነጠሉ ሲሆን ክፉው ማሳሳቻዎቹን ይዞ ሲቀርብ ያለ መከላከያ በመሆናቸው በቀላሉ የእርሱ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በዚህ አማካኝነት (በዚህ መልኩ) ራሳቸውን በአጥፊው ኃይል መዳፍ ላይ የሚያስቀምጡ የህይወታቸው ፍፃሜ የት እንደሚሆን ያላቸው ግንዛቤ ጥቂት ነው፡፡ ፈታኙ እነዚህን ሰዎች በራሱ ቁጥጥር ስር ካደረገ በኋላ ሌሎችን ደግሞ ወደ ጥፋት እንዲሄዱ ያባብሉለት ዘንድ መጠቀሚያ ዕቃ ያደርጋቸዋል፡፡ ታተ 34.5

ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ይላል፡- «እነርሱም የሚጮሁትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሏችሁ ጊዜ ህዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለህያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን? ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም፡፡» (ኢሳ. 8፡19-20)፡፡ ሰዎች የሰውን ተፈጥሮና ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልፅ የተቀመጠውን እውነት ለመቀበል ፈቃደኛ ቢሆኑ ኖሮ በመናፍስታዊነት ትምህርቶችና ምልክቶች ውስጥ ሰይጣን በኃይል እና በምልክቶች በሀሰተኛም ተዓምራት እየሰራ እንዳለ ማየት በቻሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ሥጋዊ ለሆነው ልብ በእጅጉ የሚስማማውን ነፃነታቸውን ከማግኘት ይልቅ፣ የሚወዱትን ኃጢአት ከመተው ይልቅ ብዙዎች ለተገለጠላቸው ብርሃን ዓይናቸውን በመጨፈንና ማስጠንቀቂያዎችን ችላ በማለት ሰይጣን ወጥመዱን በዙሪያቸው ወደ ሚያንዣብብበት ወደ ፊት በመገስገስ ሰለባዎቹ ይሆናሉ፡፡ «ስለዚህም ምክንያት በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስህተትን አሰራር ይልክባቸዋል»፡፡ (2ተሰ. 2፡10-11) ታተ 35.1

የመናፍስታዊነትን ትምህርቶች የሚቃወሙ ሁሉ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን እየተገዳደሩና እየተዋጉ የሚገኙት ሰይጣንን እና መላእክቱንም ጭምር ነው፡፡ በከፍታዎች ላይ ካሉ ስልጣናት እና ኃይላት እንዲሁም ክፉ መናፍስት ጋር ትግል ገብተዋል፡፡ በሰማያዊ መልአክተኞች ወደ ኋላው ካልተገፋ በቀር ሰይጣን አንዲት ኢንች ያህል እንኳ ከይዞታው አያፈገፍግም፡፡ የእግዚአብሔር ህዝቦች ልክ ያኔ አዳኛችን ባደረገው መልኩ «ተብሎ ተፅፏል» እያሉ ያሉ ሰይጣንን መጋፈጥ መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ ሰይጣንም ልክ በክርስቶስ ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን እየጠቀሰ እና ትምህርታቸውን እያጣመመ ማደናበሪያዎቹን ለማስፋፋት ሊተጋ ይችላል፡፡ ይህንን እጅግ አደገኛ ጊዜ ተቋቁመው የሚያልፉ ሁሉ ታዲያ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስክርነት ለግላቸው የተረዱ ሊሆኑ ግድ ይላል፡፡ ታተ 35.2

በርካታ ሰዎችን የሰይጣን መናፍስት ከዚህ ቀደም የሞቱ ወዳጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ተመልሰው በመገለጥ እንዲሁም እጅግ አደገኛና ሀሰተኛ ትምህርቶችን እያወጁ ይገናኟቸዋል፡፡ እነኚህ ጎብኚዎች ውስጣዊ ስሜቶቻችንን ለመንካት (ለመማረክ) የሚማፀኑን ሲሆን ማስመሰሎቻቸው ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ተአምር ያደርጋሉ፡፡ «እነዚህ መናፍስት የሰይጣን መናፍስት ናቸው» «ሙታን ምንም አያውቁም» በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ለመጋፈጥ ዝግጁ ልንሆን ይገባል፡፡ «በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ዘንድ ያለው የፈተና ሰዓት ነው» የተባለው ጊዜ ደርሷል (ራእይ 3፡10)፡፡ እምነታቸው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስር ሰዶ ያልተመሠረተ ሁሉ ይታለላሉ፣ ይሸነፋሉ፡፡ ሰይጣን የሰዎችን ልጆች በቁጥጥሩ ስር ለማዋል የማታለል ሥራዎችን በሰፊው ይሠራል፣ ማታለያዎቹም ያለማቋረጥ እያደጉ (እየበዙ) ይሄዳሉ፡፡ ዓላማው የሚሳካለት ግን ሰዎች በፈቃዳቸው ለፈተናዎቹ ሲገዙ ብቻ ነው፡፡ እነኚህ የእውነትን እውቀት ለማግኘት ከልባቸው የሚፈልጉ ሁሉ፣ ነፍሳቸውን በታዛዥነት ለማንፃት በመጣጣር ለተጋድሎው ለመዘጋጀት አቅማቸው የሚችለውን የሚያደርጉ ሁሉ፤ እነርሱ የእውነት አምላክ በሆነው በእግዚአብሔር ውስጥ የታመነ መጠጊያ (ከለላ) ያገኛሉ፡፡ «የትዕግስቴን ቃል ስለጠበቅህ እኔ ደግሞ እጠብቅሃለሁ» (ራእይ 3፡10) የሚለው ቃል የአዳኙ የተስፋ ቃል ነው፡፡ በእርሱ የምትታመነውን አንዲትን ነፍስ ለሰይጣን እንድትሸነፍ ከሚተዋት ይልቅ በሰማይ ያሉ መላዕክትን ሁሉ ህዝቦችን ይጠብቁ ዘንድ ቢልካቸው ይመርጣል፡፡ ታተ 35.3

ከእግዚአብሔር ፍርድ የተከለሉ አድርገው ራሳቸውን እንዲቆጥሩ የሚያደርጋቸውን በኃጢአን ላይ የሚመጣውን አስፈሪ መታለል ነብዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ያቀርበዋል፡- «ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፣ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፣ ሀሰትን መሸሸጊያችን አድርገናል፣ በሀሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም» (ኢሳ. 28፡15)፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ የተካተቱት በትዕቢት አንገታቸውን አደንድነው «በኃጢአተኛ ላይ ምንም ቅጣት አይመጣም፣ ሁሉም ሰብአዊ ዘር የፈለገውን ያህል የዘቀጠ ስነ-ምግባር ቢኖረውም በሰማይ ልክ እንደ እግዚአብሔር መላዕክት ከብሮና ገንኖ ነው የሚኖረው» እያሉ ራሳቸውን የሚያፅናኑት ሁሉ ናቸው፡፡ ከዚያም በላይ ከሞት ጋር ቃልኪዳን በማድረግ እንዲሁም ከሲኦል ጋር በመማማል፤ ሰማይ በፈተና ጊዜ ለጻድቃን ከለላ ይሆን ዘንድ የሰጠውን እውነት በማውገዝ፣ በዚያ ፈንታ በሰይጣን የቀረበላቸውን ሀሰት (አታላዩን የመናፍስታዊነት ማስመሰል) መሸሸጊያቸው ያደርጋሉ፡፡ ታተ 35.4

የዚህ ትውልድ ሰዎች እውርነት በቃላት ሊገለፅ ከሚቻለው በላይ አስደናቂ ነው፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች «የእግዚአብሔር ቃል ሊያምኑት የማይገባ ነው!» በማለት በመቃወም የሰይጣንን ማታለያዎች ግን በልባዊ መተማመን ይቀበላሉ፡፡ ተጠራጣሪዎችና አሽሟጣጮች የነቢያትንና የሐዋርያትን እምነት ሰዎች ይቀበሉ ዘንድ የሚያደርጉትን ጥረት በማውገዝ፤ ክርስቶስን፣ የድነትን ዕቅድ፣ እንዲሁም እውነትን በሚቃወሙት ላይ የሚገለጠውን ፍትሃዊ ቅጣት በተመለከተ ቅዱሳን መጻሕፍት በአንክሮ በሚያውጁት እውነት ላይ በማፌዝ ያላግጣሉ፡፡ የእግዚአብሔርን መመሪያዎችና ትዕዛዛቱን የሚቀበሉ ሰዎች ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ደካሞች በመሆናቸው እንደሚያዝኑላቸው በማስመሰል ይናገራሉ፡፡ የሚያሳዩት እርግጠኝነት በእርግጥ ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ያደረጉ እና ከሲኦል ጋር የተማማሉ ያህል ነው፡፡ ልክ በራሳቸው እና በእግዚአብሔር የበቀል ቁጣ መካከል የማይታለፍና የማይጣስ ግድግዳ ያቆሙ ያህል ይመስላል፡፡ ፍርሃታቸውን ሊቀሰቅስ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ ራሳቸውን ለፈታኙ መቶ በመቶ ሰጥተዋል፣ ከእርሱም ጋር እጅግ በቅርበት ተቆራኝተዋል፣ በእርሱም መንፈስ እጅግ ተሞልተዋል፤ በመሆኑም ከወጥመዱ ሰብሮ ለማምለጥ አንዳች ኃይል ብቻ ሳይሆን ዝንባሌውም የላቸውም፡፡ ታተ 35.5

ሰይጣን ለረጅም ዘመናት ዓለምን ለማሳሳት የመጨረሻ ጥረቱን ለማድረግ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ የማታለል ሥራው መሠረት የተጣለው በኤደን ገነት ውስጥ ለሔዋን በሰጣት ማስተማመኛ ላይ ነበር፡፡ «ሞትን አትሞቱም» «ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ ይከፈታሉ እንደ እግዚአብሔርም ክፉንና መልካሙን ታውቃላችሁ» (ዘፍ. 3፡4-5)፡፡ መናፍስታዊነትን በማስፋፋት እቅዱ ውስጥ ቀስ በቀስ ያንን የማታለል ጥበቡን በመጠቀም መንገዱን አዘጋጀ፡፡ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ዕቅዱን ወደ ማከናወን አልደረሰም፡፡ ነገር ግን በዘመን ፍፃሜ (በዘመን ቅሬታ) እቅዱን ይፈፅማል፡፡ ነብዩ እንዲህ ይላል፡- «ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሶስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ፡፡» (ራዕይ 16፡13-14)፡፡ በእግዚአብሔር ኃይል፣ በቃሉ ላይ ባላቸው እምነት ከተጠበቁት ሰዎች በቀር መላው ዓለም በዚህ ማሳሳቻ ተጠርጎ ይወስዳል፡፡ ሰዎች በአደገኛ ደህንነት ውስጥ አሸልበዋል፤ ከዚያ የሚነቁትም የእግዚአብሔር ቁጣ ሲፈስባቸው ብቻ ነው፡፡ ታተ 36.1

እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል «ለገመድ ፍርድን ለቱምቢም ፅድቅን አደርጋለሁ፤ በረዶውም የሀሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፣ ውሆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ፡፡ ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃልኪዳን ይፈርሳል፡፡ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሀላ አይፀናም፣ የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ» (ኢሳ. 28፡17-18) ታተ 36.2