ታላቁ ተስፋ

6/15

የመጀመሪያው ታላቅ የማታለል ሥራ

ሰይጣን ሰብአዊ ዘርን ማሳሳት የጀመረው ከጥንት የሰው ልጅ ታሪክ ጀምሮ ነው። በሰማይ አመጽን ያነሳሳው እርሱ ሲሆን በእግዚአብሔር መንግስት ላይ ባወጀው ጦርነት በምድር ያሉ ነዋሪዎችም ከእርሱ ጋር እንዲያብሩ ፈለገ። አዳምና ሔዋን ለእግዚአብሔር ሕግ የመታዘዝን ሕይወት እየመሩ ፍጹም የሆነ ደስታ ነበራቸው። ይህ ደግሞ በሰማይ የእግዚአብሔር ሕግ ጨቋኝና ለፍጥረታቱም መልካም ያልሆነ እንደሆነ አድርጎ ሰይጣን ላቀረበው ነጥብ በቋሚነት አፍራሽ ምስክርነት የሚሰጥ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፣ ለእነዚህ ኃጢአት አልባ ጥንዶች የተዘጋጀውን ውብ የሆነ ቤት በሚመለከትበት ጊዜ የቅናት ስሜቱ ተነሳሳ። ምድርን የራሱ ንብረት በማድረግ ልዑልን የሚፃረር መንግስት ለመመስረት ከመፈለጉ የተነሳ፤ እነርሱን ከእግዚአብሔር ለመለየትና በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ በኃጢአት ሊጥላቸው ቆርጦ ተነሳ። ታተ 22.1

ሰይጣን በእውነተኛ ማንነቱ ተገልጦ ቢሆን ኖሮ ወዲያውኑ ተቃውሞ በገጠመው ነበር፤ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን ይህንን አደገኛ ጠላት አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው ነበርና። ነገር ግን በጨለማ ውስጥ ራሱን በመደበቅ፣ እቅዱንም በመሰወር፣ ዓላማውን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈጸም ሰራ። በዚያን ጊዜ እጅግ አስደናቂ ፍጥረት የነበረውን እባብን እንደ መሳሪያው አድርጎ በመጠቀም፣ ሔዋንን እንዲህ አላት፡- «በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?።» (ዘፍ. 3፡1)። ከፈታኙ ጋር የንግግር ልውውጥ ከማድረግ ሔዋን ተቆጥባ ቢሆን ኖሮ፣ ከአደጋ ተጠብቃ በቆየች ነበር። ነገር ግን ከእርሱ ጋር ለመጫወት በፈለገች ጊዜ የእርሱ ማታለያ ሰለባ ሆነች። ብዙዎች ዛሬም ቢሆን የሚሸነፉት በዚሁ መንገድ ነው። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በተመለከተ ይጠራጠራሉ እንደዚሁም ይከራከራሉ። እነዚህን መለኮታዊ ትእዛዛት ከመታዘዝ ይልቅ፣ ሰብአዊ ፅንሰ-ሐሳቦችን (Theory) ይቀበላሉ፤ እነዚህም ፅንሰ-ሐሳቦች የሰይጣንን መሳሪያ በውስጣቸው የታጠቁ ናቸው። ታተ 22.2

«ሴቲቱም ለእባቡ አለችው። በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፡- እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። እባብም ለሴቲቱ አላት። ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።» (ቁጥር 2-5)። እንደ እግዚአብሔር እንደሚሆኑ አወጀ፤ ከዚህ ቀደም ከነበራቸው የበለጠ ጥበብ እንደሚኖራቸውና ላቅ ያለ ሕይወት ለመኖር አቅም እንደሚኖራቸው ነገራቸው። ሔዋን በዚህ ፈተና ተዘረረች፤ በእርሷም ተጽእኖ አዳም እጅ ሰጠ። የእባቡን ቃላት ተቀበሉ፤ እግዚአብሔር የተናገረው በእርግጥ እንደማይሆን አመኑ። ፈጣሪያቸውን ተጠራጠሩ፤ ነጻነታቸውን እየገደበባቸው እንዳለ ተሰማቸው፤ ሕጉን በመጣስ ታላቅ ጥበብና ክብር እንደሚያገኙ አሰቡ። ታተ 22.3

ነገር ግን አዳም፣ ኃጢአት ከሰራ በኋላ፣ «ከዚህ ፍሬ በበላህ ጊዜ በእርግጥ ትሞታለህ” የሚሉትን ቃላት ትርጉም በተመለከተ ምን ነበር የተረዳው? ሰይጣን እንዳሳመነው ወደ በለጠ ሁኔታ ነበር የተሸጋገረው? ሕግን በመተላለፍ ታላቅ መልካም ነገር እንደሚገኝ እና ሰይጣንም የሰብዓዊ ዘር ጠቃሚ (ረዳት) መሆኑ እንደሚረጋገጥ አሳምኖአቸው ነበር። ነገር ግን አዳም መለኮት አስቀድሞ የተናገረው ነገር ከዚህ ጋር ተቃራኒ መሆኑን ተረዳ። የኃጢአቱ መቀጮ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሰው ወደ ተገኘበት ወደ አፈር እንዲመለስ አወጀ፡- «ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ» (ቁጥር 19)። «አይናችሁ ይከፈታል” በማለት ሰይጣን የተናገረው እውነት የሆነው በዚህ መልኩ ብቻ በከፊል ነበር። አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ካመጹ በኋላ፣ የወሰዱትን ጥበብ የጎደለው ሥራ ውጤት አይናቸው ተከፍቶ ተመለከቱ። ክፋትን አወቁ፤ የመተላለፍን መራራ ፍሬ ቀመሱ። ታተ 22.4

በኤደን መካከል ላይ የሕይወት ዛፍ በቅላ ነበር። ፍሬዋም ሕይወት ዘላለማዊ ሆና እድትቆይ የማድረግ ኃይል አለው። አዳም ታዛዥ ሆኖ ለመቆየት መርጦ ቢሆን ነሮ፣ ከዚህች ፍሬ ለመብላት ነጻ እድል ይኖረው ነበር፤ ለዘላለምም ይኖር ነበር። ኃጢአት በሰራ ጊዜ ግን ከሕይወት ዛፍ እንዳይበላ ተከለከለ። በውጤቱም የሞት ሰለባ ሆነ። «ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ» የሚለው መለኮታዊ ቃል ሕይወት ለዘላለም እንደምትጠፋ የሚያመለክት ነው። ታተ 22.5

ለሰው በመታዘዝ ሕይወት ከጸና ብቻ ይቀበለው ዘንድ ቃል የተገባለት ኢሟቲነት (ዘላለማዊነት)፣ ሕግን በመተላለፉ ምክንያት ከእርሱ ተወሰደ። አዳም ደግሞ እርሱ ለራሱ የሌለውን ነገር ለዘሮቹ ማውረስ አልቻለም። ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር ልጁን መስዋዕት በማድረግ ኢሟቲነትን ባያቀርብልን ኖሮ በኃጢአት ለወደቀው ሰብአዊ ዘር ምንም አይነት ተስፋ ባልኖረ ነበር። «እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤» ነገር ግን ክርስቶስ «በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።” (ሮሜ. 5፡12፤ 2 ጢሞ. 1፡10)። አለመጥፋት (ኢሟቲነት) የሚገኘው በክርስቶስ ብቻ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡- «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3፡36)። እያንዳንዱ ሰው ይህንን እጅግ የከበረ በረከት ከቀረቡት መስፈርቶች ጋር ከተስማማ የራሱ ሊያደርገው ይችላል። «በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤” (ሮሜ. 2፡7)። ታተ 22.6

ባለመታዘዝ ሕይወት እንደሚሆንለት ለአዳም ቃል የገባለት ታላቁ አታላይ ብቻ ነው። በኤደን ገነት እባቡ «አትሞቱም» በማለት ለሔዋን የተናገረው ንግግርም፣ «ነፍስ አትሞትም» በተሰኘው ትምህርት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበ ስብከት ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው በሰይጣን ስልጣን ላይ ብቻ የተመሰረተ ስብከት ከክርስትና መድረኮች እያተስተጋባ ሲሆን በብዙ ሰብአዊ ፍጡራንም ዘንድ ልክ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በተቀበሉበት ፍጥነት ተቀባይነትን እያገኘ ይስተዋላል። «ኃጢአት የሰራች ነፍስ ትሞታለች” (ሕዝ. 18፡20) የሚለው መለኮታዊ ቃል ተለውጦ «ኃጢአት የሰራች ነፍስ አትሞትም፤ ነገር ግን ለዘላለም ትኖራለች» እንዲል ተደርጓል። የእግዚአብሔርን ቃላት ባለማመን የሰይጣንን ቃላት ለማመን እንዲህ የሙጥኝ ማለታቸው እጅግ ይገርመናል። ታተ 23.1

ለሰው ልጅ በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚደርስበት ነጻ ጎዳና ተትቶለት ቢሆን ኖሮ፣ ለዘላለም በኖረ ነበር፤ በዚህም ኃጢአትም ዘላለማዊ በሆነ ነበር። ነገር ግን ኪሩቤልና የሚንበለበለው ሰይፍ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚያደርሰውን መንገድ አጠረው (ዘፍ. 3፡24) ፤ ማንም የአዳም ዘር ከዚያ ገደብ አልፎ የሕይወትን ዛፍ እንዲበላ የሚፈቀድለት የለም። ከዚህም የተነሣ ዘላለም መኖር የሚችል ኃጢአተኛ ፈጽሞ የለም። ታተ 23.2

ነገር ግን ከውድቀት በኋላ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮው የማይሞት እንደሆነ ሁሉ ሰው እንዲያምን ለማድረግ ሰይጣን ለመላእክቱ ሥራ ሰጣቸው። ሰዎች ይህንን ስህተት እንዲቀበሉ ካደረጓቸው በኋላ፣ «ኃጢአተኞች ለዘላለም እየተሰቃዩ ይኖራሉ» ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ መሯቸው። የጨለማው ንጉስ፣ በወኪሎቹ በኩል፣ እግዚአብሔርን እንደ ተበቃይ አምባገነን መሪ፣ አድርጎ በማቅረብ እርሱን የማያስደስቱትን ሁሉ ወደ ገሃነም በማስገባት ለዘላለም ቁጣውን እንዲቀምሱ እንደሚያደርጋቸው አድርጎ ይስለዋል። በዘላለማዊ እሳት ሲሰቃዩ ሲመለከትም ፈጣሪያቸው ከላይ ሆኖ ወደ እነርሱ በማየት እንደሚረካ በማስመሰል እግዚአብሔርን ያቀርበዋል፡፡ በዚህም የውሸት አባት በራሱ ባሕርያት የሰው ልጆች ፈጣሪና መጋቢ የሆነውን አምላክ ሊያከናንበው ነው የሚፈልገው። ጭካኔ ሰይጣናዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ፍቅር ነው፤ እርሱም የፈጠረው ኃጢአት እስከገባባት ጊዜ ሁሉ ንጹሕ፣ ቅዱስ፣ እና ተወዳጅ ነበር። ኃጢአትን ያደርግ ዘንድ ሰውን ያታለለው ሰይጣን ራሱ ሲሆን፣ ከዚያም አቅሙ ቢኖረው ሊያጠፋው ይፈልጋል፤ ካጠፋውም በኋላ ባደረሰው ጥፋት ይኩራራል። ቢፈቀድለት መላውን ሰብአዊ ዘር በወጥመዱ ውስጥ ማስገባት ይፈልጋል፤ ስለ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ባይሆን ኖሮ፣ አንድም የአዳም ወንድ ወይም ሴት ልጅ ማምለጥ ባልቻለ ነበር። ታተ 23.3

ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን፣ በፈጣሪ ላይ ያላቸውን መተማመን በመናድና የእርሱንም አገዛዝ ጥበብ እንደዚሁም የሕጉን ፍትሐዊነት እንዲጠራጠሩ በማድረግ እንዳሸነፋቸው ሁሉ፣ ዛሬም ሰዎችን በተመሳሳይ መንገድ ማሸነፍ ይፈልጋል። ሰይጣንና መልእክተኞቹ እግዚአብሔርን የሚስሉት ከእነርሱ እጅግ የባሰ አድርገው ሲሆን፣ ይህንንም የሚያደርጉት ያመጹበትን ምክንያት አሳማኝ አድርገው ለማቅረብ ነው። ታላቁ አታላይ የራሱን ዘግኛኝ የሆነ ጨካኝ ባሕርይ ወደ ሰማዩ አባታችን ሊያሳልፍ ፤ በዚህም ከሰማይ በመባረሩ ምክንያት ትልቅ በደል እንደተሰራበት፣ ይህም የሆነው ፍትሃዊ ላልሆነ ገዢ ላለመገዛት በመምረጡ ምክንያት እንደሆነ ለማሳየት ይፈልጋል ። በዓለም ፊት በእርሱ ቢሆኑ ሊያገኙ ስለሚችሉት ነጻነት፣ በይሖዋ ጥብቅ ሕጎች ባሪያ ከመሆን እንደሚሻሉ እያነጻጸረ ያቀርባል። በዚህም ነፍሳትን ከእግዚአብሔር ጋር ካላቸው ሕብረት ቀስ በቀስ በማራቅ እየተሳካለት ይታያል። ታተ 23.4

ኃጢአተኛ ሙታን ለዘላለም በሚቃጠል የገሃነም እሳት ውስጥ እየተሰቃዩ እንደሆነ የሚያስተምረው አስተምህሮ ፍቅርና ምህረት እንደዚሁም የፍትሕ ልብ ላለው ሁሉ እንዴት አጸያፊ ነው!። ይህም በምድር ላይ ለቆዩበት አጭር የኃጢአት ሕይወት፣ ለዘላለም እንዲሰቃዩ የሚያደርግ አካሄድ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አስተምህሮ አሁንም በሰፊው የሚስተማርና በብዙ የክርስትና እምነት የእምነት አቋሞችም ላይ የሰፈረ ነው። አንድ የስነ-መለኮት ዶክተር የሆነ የተማረ ሰው እንዲህ ሲል ተናገረ፦ «የገሃነም እሳትን ስቃይ መመልከት የቅዱሳንን ደስታ ለዘላለም እየጨመረው ይሄዳል። በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥረው የነበሩ እንደነርሱ ያሉ ፍጥረታት እንደዚያ ባለ ሰቆቃ ውስጥ ሲዘፈቁ፣ በአንጻሩ ደግሞ እነርሱ ተለይተው ሲቆሙ ማየት ምን ያህል ደስተኛ ሰዎች እንደሆኑ ያስገነዝባቸዋል።» ሌላው ደግሞ እነዚህን ቃላት ነበር የተጠቀመው፦ «በቁጣ እቃዎች ላይ ቅጣቱ ለዘላለም በሚፈጸምበት ጊዜ፣ የምህረት እቃዎች እያዩት የስቃይ ጢሳቸው ወደ ሰማይ ይወጣል፤ ቅዱሳንም ከእነዚህ አሳዛኝ ፍጥረቶች ጋር ከመተባበር ይልቅ፣ አሜን፣ ሃሌሉያ! ጌታ ይመስገን!» ይላሉ። ታተ 23.5

ለመሆኑ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እንዲህ ያለው ትምህርት የሚገኘው የት ላይ ነው? በሰማይ የሚገኙት የዳኑ ቅዱሳን የርህራሄና የሃዘኔታ ስሜታቸው ሌላው ቢቀር ሰብአዊነት እንኳ ከእነርሱ ይገፈፋልን? እነዚህ ሁሉ ስሜቶች ወደ ጭካኔ ይለወጣሉን? በፍጹም! እንዲህ አይደለም!። የእግዚአብሔር መጽሐፍ እንደዚህ አያስተምርም። ከላይ የቀረቡት ሃሳቦች የተወሰዱት ከተማሩና እንደዚሁም ሃቀኛ ከሆኑ ሰዎች ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በሰይጣን ማታለያ የተቀመሙ ናቸው። ሰይጣን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ጠንከር ያሉ አባባሎችን በተሳሳተ መልኩ እንዲያስተውሉ በማድረግ፣ የፈጣሪያችን ሳይሆን የራሱን ባሕሪይ የሚያንጸባርቁ መራራ ቋንቋዎችን ሰጥቶአቸዋል። «እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?” (ሕዝ. 33፡11)። ታተ 24.1

ማብቂያ የሌለውን የኃጢአተኞች ስቃይ እግዚአብሔር በመመልከት እንደሚደሰት ብናስብ፣ በእርግጥ እርሱ በገሃነም እሳት ውስጥ በያዛቸው ፍጥረታቱ የስቃይ ሲቃ ድምጽ እንደሚደሰት ብናስብ ስለ እግዚአብሔር ምን አይነት ስእል ነው የሚኖረን? እነዚህ የሰቆቃ ድምጾች ጥልቅ ፍቅር ባለው አምላክ ጆሮ ውስጥ ሲገቡ ሙዚቃ ሊሆኑ ይችሉ ይሆን? በኃጢአተኞች ላይ ማብቂያ የሌለው ስቃይ መድረሱ በዩንቨርስ ሰላምና ሥርአት ላይ ቀውስ ባመጣው በኃጢአት ላይ እግዚአብሔር ያለውን ጥላቻ የሚያሳይ እንደሆነ ይነገራል። ይህ ግን አስፈሪ የሆነ በእግዚአብሔር ላይ ሊነገር የሚችል የስድብ ቃል ነው፡፡ ልክ የእሳቱ ሳይጠፋ መቆየት እግዚአብሔር ለኃጢአት ያለውን ጥላቻ ለማሳየት እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ። በእነዚህ የስነ-መለኮት ሊቃውንቶች አስተምህሮ መሰረት፣ ምህረት አልባ በሆነ መልኩ የሚቀጥለው የማሰቃየት ሥራ፣ ኃጢአተኞችን ቁጣቸውን በመራገምና እግዚአብሔርን በመሳደብ እንዲገልጹ በማድረግ ያሳብዳቸዋል፤ በዚህ መልኩ ለዘላለም የበደለኝነት ሸክማቸውን ተሸክመው ይኖራሉ። ማብቂያ ለሌለው ጊዜ ኃጢአትን እየጨመረ እንዲሄድ በማድረግ የእግዚአብሔር ክብር አይጨምርም። ለዘላላም እየተሰቃዩ መኖርን በሚያስተምረው የስህተት ትምህርት ምክንያት የመጣውን የክፋትን ኃይል ማስተዋል ከሰው አእምሮ በላይ ነው። በፍቅርና በመልካምነት የተሞላው፣ በርህራኄ የተትረፈረፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይማኖት በብዙ ተረታተረቶች ጨለመ፤ በስህተትም ተሸፈነ። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የቀባበትን የውሸት ቀለሞች ስናስብ፣ መሐሪውን ፈጣሪያችንን ሰዎች ፈርተው መሸሻቸው ምን ይገርማል? ከቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ስለ እግዚአብሔር የሚስተማሩት ትምህርቶች በሺዎች፣ አዎ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሃዲዎችና ተጠራጣሪዎች እንዲሆኑ አድርጓል። ታተ 24.2

የዘለዓለማዊ ሥቃይ ጽንሰ ሃሳብ «ባቢሎን የዝሙቷን ቁጣ አሕዛብን ሁሉ አጠጥታለች» በሚለው ውስጥ ከሚካተቱት የስህተት ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ (ራእይ 14፡8 ፤ ራእይ 17፡2)፡፡ የክርስቶስ ካህናት ይህን ኑፋቄ ተቀብለው ከተቀደሰው ገበታ መስበካቸው በእርግጥ ምሥጢር ነው፡፡ እነርሱ የተሳሳተውን ሰንበት እንደተቀበሉ ሁሉ ይህንንም የተቀበሉት ከሮም ነው፡፡ እውነት ነው፣ ይህንን ታላላቅና መልካም የሆኑ ሰዎች አስተምረውታል፡፡ ሆኖም በዚህ ርዕስ ላይ ለእኛ የተገለጸው የእውነት ብርሃን ለእነርሱ አልመጣላቸውም፡፡ እነርሱ የሚጠየቁበት በዘመናቸው፣ ስለተገለጠላቸው ብርሃን ነው፤ እኛ ደግሞ በዚህ ጊዜ ስለታየው ብርሃን ኃላፊነት አለብን፡፡ ከቃለ እግዚአብሔር ምስክር ፊታችንን አዙረን አባቶቻችን በማስተማራቸው ብቻ የተሳሳተ ትምህርት ብንቀበል በባቢሎን ላይ በተሰጠው ፍርድ ውስጥ እንወድቃለን የዝሙቷን ቁጣ ጠጅም እንጠጣለን፡፡ ታተ 24.3

ዘላለማዊ ስቃይን በተመለከተ የሚሰጠው ትምህርት ልባቸውን ያሸፈተው አያሌ ወገኖች ወደ ተቃራኒ ስህተት ተመርተዋል፡፡ እነርሱ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔርን እንደ ፍቅርና ሩህሩህ ማቅረባቸውን ያያሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ እርሱ «ፍጡራኑን ዘላለም ለማይጠፋ የሲኦል ነበልባል ይዳርጋቸዋል» ብለው ለማመን ያዳግታቸዋል፡፡ ሆኖም «ነፍስ በተፈጥሮዋ ኢሟቲ (የማትሞት) ናት» የሚለውን በመያዝ የሰው ዘር ሁሉ በመጨረሻ ጊዜ እንደሚድን በማሰብ ከዚህ መደምደሚያ መድረስን ብቻ እንጂ ሌላ አማራጭን አይመለከቱም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ማስጠንቀቂያዎች በተግባር እንዲፈጸሙ ሳይሆን የታቀዱት ይልቁንም ስዎችን ለማስፈራራትና ታዛዥ ለማድረግ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚህ አኳኋንም ኃጢአተኛው ከእግዚአብሔር የሚፈለግበትን ከቁም ነገር ባለመቁጠር፤ ያም ሆነ ይህ፣ በመጨረሻ ጊዜ እግዚአብሔር በፍቅር እንደሚቀበለው ተስፋ በማድረግ በራስ ወዳድነት ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ይሞክራል፡፡ የእግዚአብሔርን ምሕረት በማሰብና የእርሱን ዳኝነት ግን በመናቅ ሥጋዊ ልብን ደስ ለማሰኘት ይፈልጋል፤ ኃጢአተኛውም በአመጹ የልብ ልብ ተሰምቶት ይቀጥላል። ታተ 24.4

«ሁሉም ሰው ይድናል» ብለው የሚያምኑት ነፍስን ወደ ጥፋት ለሚመራው ትምህርታቸው ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዴት አዛብተው እንደሚተረጉሟቸው ለማመልከት የራሳቸውን ንግግር መጥቀሱ ብቻ አሰፈላጊ ነው፡፡ በድንገተኛ አደጋ ሳቢያ የሞተ የአንድ ኃይማኖት የለሽ ወጣት ሥርዓተ ቀብር በተከናወነበት ወቅት አንድ «ሁሉ ሰው ይድናል» በማለት የሚያምን አገልጋይ (ፓስተር) ለማንበብ የመረጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ዳዊትን በተመለከተ የተጻፈውን ነበር፡፡ እንዲህም ይነበባል፡- «ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።» (2ኛ ሳሙ 13፡39)፡፡ ታተ 24.5

ያው አገልጋይ ቀጥሎም እንዲህ ብሏል፣ «በኃጢአት እንዳሉ ዓለምን ትተዋት የሚሄዱ፣ ምናልባት በሰካራምነት እንደፀኑ የሚሞቱ፣ ከወንጀል ተግባራቸው ሳይነፁ አሻራው እንዳለ የሚሞቱ፣ ወይም ደግሞ እንደዚህ ወጣት ሥርዓተ ኃይማኖትን ሳይከተሉ የሞቱ ሰዎች ዕድል ፈንታ ምን እንደሚሆን በተደጋጋሚ ተጠይቄአለሁ፡፡ እኛ መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው እናምናለን፤ የመጻሕፍቱ መልስ ችግሩን ይፈታል፡፡ አምኖን ሲበዛ ኃጢአተኛ ነበር፤ የማይፀፀት ነበር፣ እንዲሰክር ተደረገ፣ እንደሰከረም ተገደለ፡፡ ዳዊት የእግዚአብሔር ነቢይ ነበረ፤ አምኖን በሚመጣው ዓለም ይከፋ ወይም ይደሰት ዳዊት ነቢይ እንደመሆኑ ማወቅ ነበረበት። እንግዲህ ዳዊት በልቡ የተሰማውን እንዴት ነበር የገለጸው? ‹ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።› (ቁ 39)» ታተ 25.1

«እናስ፣ ከእንደዚህ አይነቱ ቋንቋ ምን አይነት ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል? ዘለዓለማዊ ሥቃይ የዳዊት እምነት አካል እንዳልሆነ ከዚህ ንግግሩ መረዳት አይቻልምን? ስለዚህም በመጨረሻ ላይ ለሁሉ ሰው የሚሆን ሰላምና ንጽሕና እንዳለ ከዚህ እንረዳለን፡፡ ልጁ መሞቱን ሲያይ ተፅናንቶ ነበርና፡፡ ‹ለምን እንዲህ ሆነ?› ካልን፣ ምክንያቱም ዳዊት በዓይነ-ትንቢት ሲቃኝ፣ ክብር ያለውን ተስፋ መመልከት ችሎ ነበር፡፡ ልጁ ከመሳሳት፣ ከኃጢአት ባርነትና ምግባረ ብልሹነት ተላቆ በቂ በሆነ መጠን ቅዱስ ሆኖ ወደ ላይ ወዳረጉትና በደስታ ወደ ተሞሉት የመናፍስት ጉባዔ ሲቀላቀል ተመለከተ፡፡ የእርሱ ብቸኛ መፅናናት ተወዳጅ ልጁ ካለበት የኃጢአትና የሥቃይ ኑሮ ተገላግሎ እጅግ ድንቅ የሆነው የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በፅልመት በተጋረደው ነፍሱ ላይ ብርሃን ወደሚያበራበት፣ አእምሮውም የመንግሥተ ሰማያትን ጥበብና ሕያው ፍቅር ይቀበል ዘንድ ብሩኀ ወደሚሆንበት በመሄዱና፣ እንዲህ ሲሆንም ሰማያዊውን መንግሥት ከቀሩት ቅዱሳን ጋር ለመውረስ በቅድስና በመዘጋጀቱ ነው፡፡» ታተ 25.2

«በዚህ ሐሳብ መሠረት የሰማይ ቤት ወራሾች መሆናችን በዚህ ሕይወታችን ልንሠራው በምንችለው ነገር ላይ እንደማይመሠረት እናስተውላለን፡፡ ወይም ደግሞ መዳናችን አሁን በምንለማመደው የልብ ለውጥም ሆነ አሁን በምናምነው እምነት እንዲሁም በሃይማኖታዊነታችን ላይ የተመሠረተ አይደለም ብለን እንድናምን ያደርገናል፡፡» ታተ 25.3

በመሆኑም፤ ይህ «የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ» የሚለው ሰው፡- «በእውነት አትሞቱም» «ከእርሷ በበላችሁ ቀን ዓይናችሁ ትከፈታለች፣ እንደ አምላክም ትሆናላችሁ» በማለት የኤደኑ እባብ በሐሰት የተናገረውን በድጋሚ ያስተጋባል፡፡ እጅግ ኃጢአተኛ የሆኑት፡- ነፍሰ ገዳዮች፣ ሌቦችና አመንዛሪዎችም ጭምር ከሞቱ በኋላ ወደ ዘላለማዊ የደስተኝነት ኑሮ እንደሚገቡ ይገልጻል፡፡ ታተ 25.4

ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲህ አዛብቶ የተናገረው ይህ ሰው ከየት ተነስቶ ይሆን ከእንዲህ ያለ መደምደሚያ የደረሰው? «ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።» ከሚለው ዐረፍተ ነገር ነበር፡፡ እንደ ፓስተሩ አባባል የዳዊት ልጅ ወደ ሕያው ልጅ ተሻግሮ ተስተውሏል፡፡ ዝሙተኛውና ሰካራሙም አምኖን በሞተ ጊዜ ወዲያውኑ ንፅሕናን አግኝቶ ኃጢአት ከሌላባቸው ከመላእክት ጋር ይሆን ዘንድ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ አባባል ሥጋዊ ልብን ደስ ለማሰኘት የሚበቃ መልካም ተረት ነው፡፡ ይህ የራሱ የዲያብሎስ ትምህርት ሲሆን ሥራውም በሚገባ ይከናወንለታል፡፡ ይህን በመሰለ ትምህርትስ ኃጢአተኝነት የበዛ ቢሆን ሊገርመን ይገባልን? ታተ 25.5

በዚህ ዓይነቱ ሐሰተኛ መምህር የተሰጠው ትምህርት የብዙ ሌሎች መምህራንን ሥዕለ ገፅታ ያንፀባርቃል፡፡ ጥቂት ቃላትን ከዋናው ሐሳብ ይገነጥሉና ያነባሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ራሳቸው ጥቅሶቹ የተሰጣቸውን ትርጓሜ በትክክል መቃረናቸውን ያመለክታሉ፡፡ በዚህ አኳኋን ተገንጥለው የሚታዩ ዐረፍተ ነገሮች ትርጓሜያቸው ተዛብቶ በቃለ እግዚአብሔር ውስጥ መሠረት ለሌለው ትምህርት ማስረጃ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ሰካራሙ አምኖን ወደ መንግስተ ሰማያት የገባ መሆኑን በመጥቀስ የተሰጠው ምስክር ሰካራሞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ የሠፈረውን በቀጥታ የሚቃረን ነው፡፡ (1ኛ ቆሮ. 6፡18)። ተጠራጣሪዎችና እምነት የሌላቸው ሰዎች እውነትን ወደ ሐሰት የሚለውጡት በዚህ ሁናቴ ነው፡፡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎችም በአሳሳች አስተሳሰባቸው ተሸንግለው በሥጋዊ ደህንነት ቆጥ ላይ እየዋዠቁ ተኝተዋል፡፡ ታተ 25.6

የሁሉም ሰው ነፍስ በሰዓተ ሕልፈት በቀጥታ ወደ መንግስተ ሰማያት የምትሄድ መሆኑ እውነት ቢሆን ኖሮ ከሕይወት ይልቅ ለሞት ልንጓጓ እንችል ነበር፡፡ መከራ፣ ግራ መጋባትና ኃዘን በሚበረታበት ጊዜ የሕይወትን ገመድ በጥሶ ሐሴት ወደ ሚደረግባት ዘለዓለማዊ ዓለም መክነፍ ቀላል ነገር ይመስላል፡፡ ታተ 25.7

እግዚአብሔር ሕጉን የሚተላለፉትን እንደሚቀጣ በቃሉ ወሳኝ ምስክር ሰጥቷል፡፡ «እግዚአብሔር እጅግ ሲበዛ መሐሪ ስለሆነ በኃጢአተኛ ላይ አይፈርድም» ብለው ራሳቸውን የሚሸነግሉ ሰዎች የቀራንዮን መስቀል መመልከት ብቻ ይኖርባቸዋል፡፡ የንፁሁ የእግዚአብሔር ልጅ ሞት የኃጢአት ዋጋ ሞት መሆኑን፤ ለእያንዳንዱም የሕገ-እግዚአብሔር መተላለፍ ተገቢው ቅጣት እንደሚፈጸም ይመሰክራል፡፡ ኃጢአት የሌለበት ክርስቶስ ስለ ሰው ኃጢአት ሆነ፡፡ እርሱ የሕግን መተላለፍ ኃጢአት ተሸከመ፡፡ ይህንንም ያደረገው ልቡ እስኪደቅ ሕይወቱም እስኪጠፋ ድረስ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ መሥዋዕት የተደረገው ኃጥአን ይድኑ ዘንድ ነበር፡፡ የሰው ልጅ በምንም ሌላ ዓይነት መንገድ ከሚደርስበት የኃጢአተኝነት ቅጣት ነፃ መሆን አይችልም ነበር፡፡ ይህን መሰሉን በከባድ መሥዋዕት የተበረከተውን ስርየት ለመቀበል የማትፈቅድ ማንኛይቱም ነፍስ ሕግን በመተላለፍ የሚደርስባትን ቅጣት ራስዋ መሸከም ግድ ይሆንባታል፡፡ ታተ 26.1

«ሁሉም ሰው ይድናል» በማለት የሚያስተምሩ ሰዎች በሰማይ ከቅዱሳንና ደስተኛ ከሆኑ መላእክቶች ጋር እንደሚሆኑ ስለሚናገሩላቸው፣ እግዚአብሔርን ስለማይፈሩት ንስሃም ስላልገቡት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር እናንብ፡- «እኔ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ በከንቱ እሰጣለሁ» (ራእይ 21፡6)፡፡ ይህ የተስፋ ቃል የተሰጠው ለተጠሙ ብቻ ነው፡፡ ይህን የሚያገኙ የሕይወት ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው የሚገነዘቡ ሌላውን ነገር ሁሉ ትተው እሱን ብቻ የሚሹ ናቸው፡፡ «ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል» (ቁጥር 7)። ሁሉንም ነገር ለመውረስ ኃጢአትን መቋቋምና ድል መንሳት ይኖርብናል፡፡ ታተ 26.2

እግዚአብሔር አምላክ በነብዩ በኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ሲል ይገልጻል፡- «የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና፤ ጻድቁን፦ መልካም ይሆንልሃል በሉት። እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል።» (ኢሳ. 3፡10-11)። ጠቢቡም እንዲህ ይላል፡- «እኔ ጥበብ በብልሃት ተቀምጫለሁ፥ እውቀትንም ጥንቃቄንም አግኝቻለሁ። እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን ይጠላል፣ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ።» (መክ 8፡12-13) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ እንዲህ ሲል ምስክሩን ይሰጣል፡- «ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል» (ሮሜ 2፡ 5፣6፣9)፡፡ ታተ 26.3

«ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም።» (ኤፌ. 5፡5)፡፡ «ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።» (ዕብ. 12፡14)። «ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሻዎችና አስማተኞች፣ ሴሰኛዎችም፣ ነፍሰ ገዳዮችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩት፣ ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።» (ራእይ 22፡14-15)፡፡ ታተ 26.4

እግዚአብሔር ስለ ባሕርይውና ኃጢአትንም በተመለከተ ምን እንደሚያደርግ ለሰዎች ገልጾአል፡፡ «እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ፡- እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ።» (ዘፀ. 34፡6-7)። «እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል።» «በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ። የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል።» (መዝ 145፡20፣ መዝ 37፡38)። የመለኮታዊው መንግሥት ኃይልና ሥልጣን አመፅን ለማጥፋት ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ፍርዱ ከእግዚአብሔር ጋር የተስማማ ይሆናል፡፡ ታተ 26.5

እግዚአብሔር የማንንም ሰው ፈቃድ ወይም ፍርድ በማስገደድ አይቆጣጠርም። በባርነት ቀንበር ሥር ሆኖ የሚቀርብ የመታዘዝ ነገር አያስደስተውም። እርሱ በእጁ የፈጠራቸው ሰዎች መወደድ ስለሚገባው ያፈቅሩት ዘንድ ፅኑ ፍላጎቱ ነው፡፡ ፍጡራኑ ለእሱ እንዲታዘዙ የሚያደርጋቸው ጥበቡን፣ ፍትሑንና ርኀራኄውን የሚገነዘቡ በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህን የእርሱን ባሕርያት በትክክል የተረዱ ሁሉ የተግባሩን ፍሬ በማድነቅ ወደ እርሱ ስለቀረቡ ያፈቅሩታል፡፡ ታተ 26.6

በመድኃኒታችን አማካኝነት በትምህርትነት የተሰጡትና በምሳሌያት የተገለጹት የደግነት፣ የምሕረትና የፍቅር መርሖዎች የእግዚአብሔር ፈቃድና ባሕርይ ቅጂዎች ናቸው፡፡ ክርስቶስ ከአባቱ ከተቀበለው በቀር አንዳችም ሌላ ነገር እንዳላስተማረ ተናግሯል፡፡ የመለኮታዊ መንግስት መሠረተ አቋም ‹ጠላቶቻችሁን ውደዱ› ከሚለው ከመድኃኒታችን ትምህርት ጋር ፍጹም የተስማማ ነው፡፡ እግዚአብሔር በኃጢአን ላይ የሚፈርደው ለዓለማት በጎነት እንደዚሁም ፍርድ ለተሰጣቸውም ጭምር መልካምነት በማሰብ ነው፡፡ በመንግስቱ ሕግጋትና ፍትሕን በተላበሰው ባሕርይው መሠረት ይህን ለማድረግ ከቻለ እነርሱን ደስ ያሰኛቸዋል፡፡ በእርሱ የፍቅር ምልክቶች ዙሪያቸው እንዲከበብ ያደርጋል፣ የእርሱን ሕግ እውቀት ይሰጣቸዋል፣ በበረከትና ምህረቱም ይከተላቸዋል፡፡ እነርሱ ግን ፍቅሩን ዋጋ ያሳጡታል፣ ሕጉን ያፈርሱታል፣ ምህረቱንም ለመቀበል አይፈቅዱም፡፡ ባለማሰለስ የእርሱን ስጦታ እየተቀበሉ ሰጭውን ግን ክብሩን ይነፍጉታል፡፡ እነርሱ እግዚአብሔርን ይጠላሉ፣ ምክንያቱም እርሱ የእነርሱን ኃጢአት መጥላቱን ያውቃሉና፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ጥፋታቸውን ለረዠም ጊዜ ይታገሣል፣ ነገር ግን የእነርሱ መጨረሻ የሚወሰንበት ጊዜ በኋላ ይመጣል፡፡ ያን ጊዜስ እነዚህን አማፅያን በእርሱ በኩል ይሆኑ ዘንድ ያሥራቸዋልን? ፈቃዱንስ ያደርጉ ዘንድ ያሰገድዳቸዋልን? ታተ 26.7

ዲያብሎስን አለቃቸው እንዲሆን መርጠው የእርሱ ሥልጣን ተገዥ የሆኑት እግዚአብሔር ወዳለበት ለመግባት የተዘጋጁ አይደሉም፡፡ ትዕቢት፣ ሽንገላ፣ ዝሙት፣ ጭካኔ ከባሕርያቸው ጋር ተቆራኝተዋል፡፡ ታዲያ በምድር ላይ ከናቋቸውና ከጠሏቸው ጋር ለዘለዓለም ለመኖር ወደ መንግስተ ሰማይ ለመግባት ይችላሉን? እውነት ለሐሰተኛ ፈጽሞ የሚስማማ አይሆንም፡፡ ትዕግስተኝነት ራሱን ከፍ ከፍ ለሚያደርግና ለትዕቢተኛ አያረካም፡፡ ንፅሕና በምግባረ ብልሹነት ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ በጥቅም ላይ ያልተመሰረተ ፍቅር ለራስ ወዳዶች መልካም መስሎ አይታይም፡፡ እናስ፣ ፍጹም በምድራዊና በራስ ወዳድነት ስሜት ለተዋጡ ሰዎች መንግሰተ ሰማያት ምን የደስታ ምንጭ ሊያፈልቅላቸው ይችላል? ታተ 27.1

የሕይወታቸውን ዘመን በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ያሳለፉ ሰዎች ወዲያውኑ ወደ መንግስተ ሰማያት ተወስደው እያንዳንዲቱ ነፍስ በፍቅር የተመላችበትን ብሩህ ጸዳል፣ እያንዳንዱም ነፍስ የሚያንጸባርቀውን የደስታ ብርሃን፣ ለእግዚአብሔርና ለበጉ የሚቀርበውን የደስታ ዜማ፣ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠውም ፊት ላይ የሚፈነጥቀውንና በዳኑት ላይ የሚያርፈውን የማያቋርጥ የብርሃን ጨረር ቢመለከቱስ? ልባቸው በእግዚአብሔር፣ በቅድስናውና በእውነቱ ላይ ባደረባቸው ጥላቻ የተሞላው እነዚያ ሰዎች በሰማይ ካሉት ጋር ቢቀላቀሉና በምስጋና ዜማቸውም ቢተባበሩስ? የእግዚአብሔርንና የበጉን ክብርና ግርማ ይችሉታልን? በፍጹም አይችሉትም! በጭራሽ!፡፡ እነርሱ ለመንግሥተ ሰማያት የተገባውን የባሕርይ መልክ ለመያዝ እንዲችሉ አያሌ ዓመታት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ልባቸው ንፅሕናን ይወድ ዘንድ አላደረጉም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን ቋንቋ ፈጽሞ አልተማሩም፡፡ አሁን ግን ጊዜው አለፈባቸው፡፡ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ያሳለፉት ሕይወት ለመንግሥተ ሰማያት ብቁ ሳያደርጋቸው ቀርቷል፡፡ የመንግስተ ሰማያት ንፅሕና፣ ቅድስናና ሰላም ለእነርሱ ስቃይ ነው የሚሆንባቸው፡፡ የእግዚአብሔር ክብር ለእነርሱ እንደሚፋጅ እሳት ነው የሚሆንባቸው፡፡ በመሆኑም ከእዚህ ቅዱስ ስፍራ ለመሸሸ ይመኛሉ፡፡ እነርሱን ለማዳን ሲል ከሞተው ከጌታ ፊት ለመሰወር ሲሉ፣ ውድመትን ወደራሳቸው ይጠራሉ፡፡ የኃጥአን መጨረሻ የሚወሰነው በራሳቸው ምርጫ ነው፡፡ ከመንግስተ ሰማያት የሚገለሉት ራሳቸው ፈልገው ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ምንግዜም ቢሆን ጻድቅ እና መሐሪ ነው፡፡ ታተ 27.2

በኖህ ዘመን የነበረው የጥፋት ውሃ እንዳደረገው ሁሉ የታላቁም ቀን እሳት ኃጥአን እንደማይድኑ ፍርዱን ይገልጻል፡፡ ኃጢአን ለመለኮታዊ ስልጣን አይገዙም፡፡ የእነርሱ ፈቃድ የሆነው ዐመፅ ነበር በህይወታቸው ተግባራዊ ሲሆን የኖረው፡፡ የሕይወታቸው ፍጻሜ በሚደርስበት ጊዜ የአስተሳሰባቸውን አቅጣጫ ለመለወጥ፤ ከሕግ ተላላፊነት ወደ ታዛዥነት፣ ከጥላቻ ወደ ፍቅር ለመለወጥ ይረፍድባቸዋል፡፡ ታተ 27.3

እግዚአብሔር የነፍሰ ገዳዩን የቃየልን ሕይወት ወዲያውኑ ባለማጥፋት፣ ኃጢአተኛ ለእግዚአብሔር ተገዥነት ሳይኖረው በኃጢአት ተግባሩ ይቀጥል ዘንድ መፍቀድ የሚያስከትለውን ውጤት እግዚአብሔር ለዓለም በምሳሌነት አሳይቷል፡፡ በቃየል ትምህርትና ምሳሌ አማካይነት የሰው ክፋት በምድር ላይ የበዛ እስኪሆን ድረስ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የቃየል ዝርያዎች ወደ ኃጢአት ተመርተው ነበር፡፡ «የልብም ሃሳብና መመኘት ፈጽሞ ክፉ ሆነ፤ ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሽታ ነበረች፡፡ ምድርም ግፍ ሞላበት» (ዘፍ 6፡5፣11)፡፡ ታተ 27.4

በዘመነ ኖህ፣ እግዚአብሔር በቸርነቱ ኃጢአኑን የምድር ነዋሪዎች አጥፍቷቸዋል፡፡ በእርሱ ቸርነት ምግባረ ብልሹዎቹን የሰዶም ሰዎች አጥፍቷል፡፡ ነገር ግን በዲያብሎስ የሸንጋይነት ኃይል አማካይነት ክፋት ሠሪዎች መወደድንና መደነቅን ያገኛሉ፡፡ እንዲህም ሲሆን ሌሎችን ባለማሰለስ ወደ አመፅ ይመራሉ፡፡ በዘመነ ቃየልና በዘመነ ኖህ፣ በዘመነ አብርሃምና በዘመነ ሎጥ የሆነው ይኸው ነበር፡፡ በእኛም ዘመን ያለው እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመጨረሻ ጊዜ የእርሱን ፀጋ የማይቀበሉትን የሚያጠፋው ለዩኒቨርስ ምህረትን ለማድረግ ሲል ነው፡፡ ታተ 27.5

«የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።» (ሮሜ 6፡23)። ሕይወት የጻድቃን ውርስ ሲሆን፣ ሞት የኃጢአን ድርሻ ነው፡፡ ሙሴ ለእስራኤል እንዲህ አለ፡- «ተመልከት ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ።» (ዘዳ. 30፡15)። በእነዚህ መጻሕፍት የተጠቀሰው ሞት በአዳም ላይ የተነገረው ሞት አይደለም፡፡ የዘለዓለማዊ ሕይወት ተቃራኒ የሆነው ሁለተኛው ሞት ነው፡፡ ታተ 27.6

በአዳም ኃጢአት ምክንያት ሞት ወደ ሰው ዘር ሁሉ ተላለፈ፡፡ መሰል ፍጡራን ሁሉ ወደ መቃብር ይወርዳሉ፡፡ በድነት ዕቅድ በተዘጋጀው መመሪያ መሠረትም ሁሉም ከመቃበር የሚወጡ ይሆናል፡፡ የሞቱት ፃድቃንም ሆኑ ኃጢአን ከመቃብር ይነሣሉ፡፡ ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁም ሁሉም በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና (ሐዋ. 24፡15 ፣ 1ኛ ቆሮ 15፡22)፡፡ ሆኖም ከሞት በትንሣኤ በሚነሱት መካከል ልዩነት አለ፡- «በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።» (ዮሐ. 5፡28-29):: «በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም» (ራዕይ 20፡6)። ንስሃ በመግባትና በእምነት ምህረት ያላገኙ ግን የበደለኝነታቸውን ቅጣት ይኼውም የኃጢአትን ዋጋ መቀበል አለባቸው። እንደበደላቸው መጠን፣ በርዝመቱም ሆነ በክብደቱ የተለያየን ቅጣት ይቀበላሉ፡፡ መጨረሻቸው ግን ሁለተኛው ሞት ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በዳኝነቱና በምሕረቱ ኃጢአተኛን በኃጢአቱ እንዳለ ለማዳን ስለማይቻለው በበደሉ ምክንያት ሕይወቱን ያጣል። በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የጻፈው ነቢይ እንዲህ ይላል፡- «ገና ጥቂት፥ ኃጢአተኛም አይኖርም ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።» ሌላውም እንዲህ ይላል፡- «እንዳልሆኑም ይሆናሉ።» (መዝ. 37፡16 ፤ አብድዩ 16)። በኃጢአት እንደተሸፈኑ ተስፋ ወደ ሌለው ዘለዓለማዊ መረሳት ይወርዳሉ፡፡ ታተ 28.1

በዚህ አኳኋን ኃጢአት የእርሱ ፍሬ ከሆነው መከራና ጥፋት ጋር መጨረሻው ይሆናል፡፡ ዘማሪው እንዲህ ይላል፡- «አሕዛብን ገሠጽህ፥ ዝንጉዎችንም አጠፋህ፥ ስማቸውንም ለዘላለም ደመሰስህ። ጠላቶች በጦር ለዘላለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውም በአንድነት ጠፋ።» (መዝ. 9፡5-6) ፡፡ ዮሐንስ በራዕይ ዘለዓለማዊውን መንግስት ሲጠባበቅ በምንም ያልተረበሸ ሁሉን ያቀፈ የምስጋና ዝማሬን ሰምቶ ነበር፡፡ በሰማይም ሆነ በምድር ፍጥረት ሁሉ ክብርን ለእግዚአብሔር ሲሰጥ ይደመጣል፡፡ (ራዕይ 5፡13)፡፡ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ የሚጠሩ በኃጢአት የወደቁ ነፍሳት አይኖሩም፡፡ በገሃነም ያሉ ኃጢአተኞች የመከራ ሲቃቸው ከቅዱሳን መዝሙር ጋር አይደባለቅም፡፡ ታተ 28.2

«ሰው በተፈጥሮው የማይሞት ነው (ኢሟቲ ነው)» በማለት በሚያስተምረው አስተምህሮ ውስጥ ሰው ከሞተ በኋላ የሚደረገውን እንደሚያውቅ ተደርጎ የሚሰጠው ትምህርት ይገኛል፡፡ ይህ ትምህርት እንደ ዘለዓለማዊው ሰቆቃ ሁሉ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምክንያታዊነትንና የእኛንም የሰብዓዊነት ስሜት የሚቃረን ነው፡፡ ብዙዎች የሚያምኑት፣ ከሞቱ በኋላ ወደ ሰማይ የተወሰዱ ነፍሳት በምድር ላይ የሚደረገውን ሁሉ በተለይ ደግሞ በምድር የቀሩትን ወዳጆቻቸውን የኑሮ ሁኔታ እንደሚያውቁ ነው፡፡ ነገር ግን በምድር የሚኖሩትን ሰዎች መከራ ማወቅ፣ ወዳጆቻቸው ኃጢአት ሲሠሩ ማየት፣ የመጣባቸውን ኃዘን፣ ቅሬታና ጭንቀት መመልከት እንዴት ባለ አኳኃን በመንግስተ ሰማያት ሐሤት ያደርጉ ዘንድ ምክንያት ሊሆናቸው ይችላል? በምድር ላይ ባሉ ወዳጆቻቸው ጉዳይ ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ በመንግስተ ሰማይ ያሉ ነፍሳት እንዴት በሰማይ ያለውን ደስታ ሊያጣጥሙ ይችላሉ? ‹የኃጢአተኛው ነፍስ ልክ ከሥጋው እንደተለየች ወደ ገሃነም እሳት ወዲያውኑ ትገባለች› ብሎ ማሰብስ እንዴት የማያስደስት አሳብ ይሆናል! ሳይዘጋጁ ወደ መቃብር የሚወርዱትን ወደ ዘላለማዊ ዋይታ የሚገቡትን ወዳጆቻቸውንስ ማየት ምንኛ ጥልቅ ወደ ሆነ ኃዘን ውስጥ ይጨምራቸዋል! በዚህ በጣም አሳዛኝ የሆነ አሰተሳሰብ ብዙዎች ወደ እብደት ተመርተዋል፡፡ ታተ 28.3

እነዚህ ነገሮች በተመለከተ መጻሕፍት ምን ይላሉ? ዳዊት ሰው በሞተ ጊዜ ምንም እንደማያውቅ ይነግረናል፡፡ «መንፈሱ ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል።» (መዝ. 146፡4)፡፡ ሰለሞንም ተመሳሳይ ምስክርነትን እንዲህ በማለት ይሰጣል፡- «ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና ሙታን ግን አንዳች አያውቁም መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው፣ ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።… አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።» (መክ. 9፡5፣6፣10)፡፡ ታተ 28.4

ሕዝቅያስ ያደረገው ጸሎት ተሰምቶለት በዘመኑ ላይ አስራ አምስት ዓመት በተጨመረለት ጊዜ ይኸው ንጉሥ ሕዝቅያስ ለተደረገለት ምህረት ለእግዚአብሔር ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል፡፡ በምስጋና መዝሙሩ ለምን እንዲያ ያለ ሐሤት እንዳደረገ ምክንያቱን ይነግራል፡፡ «ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና ወደ ጕድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም። እኔ ዛሬ አንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል አባት ለልጆች እውነትህን ያስታውቃል።» (ኢሳ 38፡18-19)፡፡ ብዙዎች የሚቀበሉት ነገረ መለኮታዊ መረዳት በሰማይ ያሉ የጸደቁ ሙታን ሐሤት እንደሚያደርጉ፣ ባልደረቀች ምላስም እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑ ያመለክታል፡፡ ሕዝቅያስ ግን ይህን መሰል ታላቅ ነገር በሞት ውስጥ ሊያይ አልቻለም፡፡ የሕዝቅያስ ቃል ከዘማሪው ምስክር ጋር ይስማማል፡- «በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?» «አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ» (መዝ. 6፡5፤ መዝ 115፡17)፡፡ ታተ 28.5

ጴጥሮስ በዕለተ ጴንጤቆስጤ ዳዊት የአባቶቹ አለቃ እንደሞተና እንደተቀበረም መቃብሩም እስከ ዛሬ ከእኛ ዘንድ እንደሆነ ወደ ሰማይም እንዳልወጣ በግልጽ ተናግሯል (ሐዋ 2፡29-34)፡፡ ዳዊት እስከ ትንሣኤ ሙታን ጊዜ ድረስ በተቀበረበት መቆየቱ ፃድቃን በሞታቸው ጊዜ ወደ ሰማይ እንደማይወጡ ያረጋግጣል፤ ዳዊት በመጨረሻ ጊዜ በእግዚአብሔር ቀኝ ለመቀመጥ የሚችለው በትንሣኤ፣ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳቱ ብቻ ነው፡፡ ታተ 28.6

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ «ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ።» (1ኛ ቆሮ 15፡16-18)፡፡ ለአራት ሺህ ዓመታት ፃድቃን እንደሞቱ ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ወጥተው ከሆነ ጳውሎስ ትንሣኤ ሙታን ከሌለ በክርስቶስ የተኙ ደግሞ ፈጽመው ጠፉ ለማለት እንዴት ተቻለው? በዚህ አኳኃን ትንሣኤ ሙታን አያስፈልግም ነበር፡፡ ታተ 29.1

ሰማዕቱ ዊሊያም ቲይንዴል የሙታንን ሁናቴ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ «እነርሱ (ሙታን) አሁን ክርስቶስ በክብሩ ባለበት ቦታ ወይም የተመረጡት የእግዚአብሔር መላእክት ባሉበት የክብር ቦታ ውስጥ መኖራችውን ለማመን እንደማልችል በግልጽ እናገራለሁ፡፡ ይህ የእኔ እምነትም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ቢሆን ኖሮ የሰዎችን በሥጋ መነሣት በተመለከተ ያለው ስብከት ከንቱ ይሆናልና፡፡» (William Tyndale, Preface to New Testament (ed. 1534). Reprinted in British Reformers--Tindal, Frith, Barnes, page 349) ታተ 29.2

በሞት ጊዜ ይሆናል የሚባለው የሕያው ብፅዕና ተስፋ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ ሙታን የሚያስተምረውን ሰዎች ችላ እንዲሉ ማድረጉ የማይታበል እውነት ነው፡፡ ይህን በተመለከተ በዶ/ር አዳም የቀረበው ሐተታ እንዲህ ይነበባል፡- «ትምህርተ ትንሣኤ ከዛሬው ዘመን ይልቅ እጅግ በበለጠ አኳኋን በጥንት ይኖሩ በነበሩት ‹ያልተማሩ ክርስቲያናት› ዘንድ የተሰጠ ይመስላል፡፡ ይህ እንዴት ሆነ? ሐዋርያቱ ይህንን ትምህርት ደጋግመው ያስተማሩ ሲሆን፣ የእግዚአብሔርንም ተከታዮች በዚህ ትምህርት እንዲተጉ፣ እዲታዘዙና ደስተኞች እንዲሆኑ አነቃቅተዋቸዋል፡፡ በዘመናችን ያሉ የእነርሱ ተተኪዎች ግን እምብዛም ሲናገሩት አይደመጥም፡፡ ሐዋርያት ሰበኩት፤ የጥንት ክርስቲያኖችም አመኑት፡፡ እኛም ዛሬ እንሰብከዋለን፤ አድማጮቻችንም ያምኑታል፡፡ እንደ ትንሳኤ ሙታን ያለ በወንጌል ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ትምህርት አናገኝም፤ በዚያው ልክ ደግሞ በዘመናችን እንደ ትንሳኤ ሙታን ቸል የተባለም ትምህርት የለም!» (Commentary, remarks on 1 Corinthians 15, paragraph 3). ታተ 29.3

ይህም የከበረ የትንሳኤ እውነት ሙሉ በሙሉ እስኪሰወርና ከክርስትናው ዓለም እይታ እስኪጠፋ ድረስ ደረሰ፡፡ ከዚህ የተነሳ አንድ የታወቀ የኃይማኖት ጸሐፊ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18 በሚገኘው የጳውሎስ ቃል ላይ ሃሳብ ሲሰጥ እንዲህ አለ፡- «ይበልጥ ተጨባጭ የሆነ መጽናናትን ለማግኘት ሲባል የጻድቃን ነፍስ የማትሞት መሆኗን የሚያስተምረው የተባረከው ትምህርት ማንኛውንም አጠራጣሪ የሆነውን የጌታን ዳግም ምጻት ትምህርት ተክቶአል፡፡ በምንሞትበት ጊዜ ጌታ ይመጣልናል፡፡ ያንን ነው ልንጠባበቅ የሚገባን፡፡ የሞቱት ወደ ክብር ገብተዋል፡፡ ፍርድ እንዲሰጣቸው ወይም ደግሞ በረከትን እንዲያገኙ መለከት እስኪነፋ ድረስ አይጠብቁም፡፡» ታተ 29.4

ነገር ግን ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ሲለያቸው፣ ‹በቅርብ ጊዜ ወደ እኔ ትመጣላችሁ› አላላቸውም፡፡ እርሱ ያላቸው፡- «በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።» (ዮሐ. 14፡2-3)፡፡ ከዚያም ጳውሎስ ጨምሮ እንዲህ ይለናል፡- «ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።» (1ተሰ. 4፡16-18)፡፡ በእነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትና ቀደም ብሎ በተጠቀሰው ‹ሁሉም ሰዎች ይድናሉ› የሚለውን ሐሳብ በሚያራምደው አገልጋይ ቃላት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ አገልጋዩ ቤተዘመዱን ያጽናናው፥ ‹ግለሰቡ በምድር ላይ የፈለገውን ያህል ኃጢአተኛ ቢሆንም፤ ልክ የመጨረሻ ትንፋሹን ተንፍሶ በሞተ ጊዜ በመላእክት አቀባበል ተደርጎለታል› በማለት ነበር፡፡ ጳውሎስ ደግሞ አማኞችን ያጽናናው ወደ ጌታ ምጻት በማመልከት ነበር፤ የመቃብር ማሰሪያዎች በሚበጠሱበት ጊዜና በክርስቶስ የሞቱት ለዘላለም ሕይወት በሚነሱበት ጊዜ የሚሆነውን ተናገረ፡፡ ታተ 29.5

ማናቸውም ሰዎች ለብጹአን ወደ ተዘጋጀው ቤት ከመግባታቸው በፊት፣ ጉዳያቸው መመርመር፣ ባሕርያቸውና ሥራቸውም በእግዚአብሔር መመዘን አለበት፡፡ ሁሉም በመጽሐፍቱ በተጻፈው መሠረት ሊመዘኑና እንደ ሥራቸውም መጠን ሊከፈላቸው ወደ ፍርድ ዙፋን ሊቀርቡ ይገባል፡፡ ይህ ፍርድ ደግሞ ግለሰቡ በሚሞትበት ጊዜ አይከናወንም፡፡ የጳውሎስን ቃላት ልብ በሉ፡- «ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።» (ሐዋ. 17፡31)፡፡ ሐዋርያው በግልጽ እንዳስቀመጠው የፍርድ ቀን ተቀጥሮአል፡፡ ታተ 29.6

ይሁዳም ስለ ተመሳሳይ ጊዜ እንዲህ በማለት ይጠቁማል፡- «መኖሪያቸውንም የተውትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።» ከዚያም የሄኖክን ቃላት ይጠቅሳል፡- «ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።» (ይሁዳ 6,14-15)፡፡ ዮሐንስም እንዲህ በማለት ያውጃል፡- «ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።» (ራዕይ 20፡12)፡፡ ታተ 30.1

ነገር ግን ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ የሰማይን ደስታ እያጣጣሙ ወይም በገሃነም እየተቃጠሉ ከሆነ ለወደፊት ሊመጣ ያለው ፍርድ ለምን ያስፈልጋል? ይህንን በተመለከተ ግን የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት የሚያሻማና እርስ በርሱ የሚጋጭ አይደለም፡፡ በማንም ዘንድ መስተዋል ይችላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ተቃራኒ በሆነው ትምህርት ውስጥ ከቶ ምን አይነት ጥበብና ፍትህ ማየት ይቻል ይሆን? ጻድቃን ለረዥም ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ከቆዩ በኋላ በፍርድ ጊዜ ጉዳያቸው ታይቶ፡- «መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ» ይባላሉን?፡፡ ደግሞስ ኃጢአተኞች ይቃጠሉበት ከነበረው ስፍራ ተጠርተው በዓለም ላይ የተሰጠውን ፍርድ፡- «እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።» የሚለውን ፍርድ እንዲሰሙ ይደረግ ይሆን? (ማቴ. 25፡21፣41)፡፡ ይህ ማፌዝ ነው! በእግዚአብሔር ጥበብና ፍትህ ላይ መቀለድ ነው! ታተ 30.2

«ነፍስ የማትሞት ናት» የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ሮም ከአረማዊ ሃይማኖት ከተዋሰቻቸውና ወደ ክርስትና አስተምህሮ ከተበረዙ የስህተት ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው። እንዲህ ያለውን ትምህርት ማርቲን ሉተር «የሮም የስህተት ትምህርትን ከገነቡ አጸያፊ ተረቶች መካከል» የሚመደብ እንደሆነ ይገልጻል። (E. Petavel, The Problem of Immortality, page 255)፡፡ በመጽሐፈ መክብብ ሰለሞን ሙታን ምንም እንደማያውቁ በተናገረው ላይ ሃሳብ ሲሰጥ ይህ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አርበኛ እንዲህ ብሏል፡- «ሙታን ምንም አይነት ስሜት እንደሌላቸው የሚያረጋግጥልን ሌላ ክፍል ይህ ነው። ጠቢቡ እንደሚለው፤ በዚያ ሳይንስ፣ እውቀት፣ ጥበብ የለም። ሰለሞን ሙታን የሞቱ መሆናቸውን ይመሰክራል፤ ምንም ነገርም አይሰማቸውም። ሙታን በመቃብራቸው ቀናትንም ሆነ ዓመታትን መቁጠር በማይችሉበት እንቅልፍ ውስጥ ያሉ ሲሆን፣ በሚቀሰቀሱበትም ጊዜ፣ አንድ ደቂቃ ላልሞላ ጊዜ ብቻ የተኙ ይመስላቸዋል።» (Martin Luther, Exposition of Solomon’s Book Called Ecclesiastes, page 152)። ታተ 30.3

በመጽሐፍ ቅዱስ አንድም ቦታ ጻድቃን ሲሞቱ ወደ ሽልማታቸው እንደሚሄዱ፣ ኃጥአን ደግሞ ወደ ቅጣታቸው እንደሚሄዱ የሚናገር ክፍል የለም። ርዕሰ አበውና ነብያት እንዲህ ያለ ዋስትና አልሰጡንም። ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ስላለው ነገር ምንም አይነት ፍንጭ አልሰጡም። መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ወዲያው ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ በግልጽ ነው የሚያስተምረው። እስከ ትንሳኤ ድረስ በእንቅልፍ እንደተኛ ሰው ሆነው እንደሚቆዩ ነው የተነገረው (1 ተሰ. 4፡14፤ ኢዮብ 14፡10-12)። «የብር ድሪው ሲበጠስ፣ የወርቅ ኩስኩሰት ሲሰበር» (መክ. 12፡6) የሰው ሃሳብ ይጠፋል። ወደ መቃብር የሚወርዱ ሁሉ በዝምታው ዓለም ውስጥ ይገኛሉ። ከጸሐይ በታች ስላለው ነገር ከእንግዲህ ወዲህ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም (ኢዮብ 14፡21)። በትጋት ሰርቶ የደከመው ጻድቅ የተባረከ የእረፍት ጊዜ ያገኛል። በዚያ መቃብር ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜ አጭርም ይሁን ረዥም ለእነርሱ አይታወቃቸውም። ይተኛሉ፤ ከዚያም በእግዚአብሔር መለከት ለዘላለማዊነት ክብር ይነሳሉ። «መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ፣ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል።» (1 ቆሮ. 15፡52-54)። ከጥልቅ እንቅልፋቸው በሚቀሰቀሱበት ጊዜ፣ መቼ ወደ እንዲህ ያለ እንቅልፍ ውስጥ እንደገቡ ለማሰብ ይጀምራሉ። ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስታውሱት ነገር ግን በሞት ማሸለባቸውን ብቻ ይሆናል። ለመጨረሻ ጊዜ ያሰቡት ከመቃብር ኃይል በታች እየወደቁ መሆኑን ነበር። ከመቃብር ሲወጡ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያስቡት የደስታ አሳብ በመለከት ድምጽ እንዲህ ይስተጋባል፡- «ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” (ቁ.55) ታተ 30.4