የቤተ ፡ ክርስቲያን፡ ምክሮች፡፡
ማውጫ፡፡
ምዕራፍ ፩—ታማኙ ስለሚያገኘው ዋጋ የታየው ራእይ፡፡ (የመጀመሪ ራእዬ)
በቤተሰብ መሠውያ (መጸለያ) ስጸልይ ሳለሁ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደብኝ፣ ከጨለማው ዓለም በላይ እሩቅ ከፍ ከፍ እያልሁ የምነሳ መሰለኝ፡፡ በዓለም ያለውን የአድቬንት (ዳግመኛ መምጫ ተጠባባቂ) ሕዝብ እመለከት ዘንድ ዘወር አልሁ ግን ‹‹እንደገና ተመልከቺ፣ ትንሽም ከፍ አድርገሽ ተመልከቺ፣ ትንሽም ከፍ አድርገሽ ተመልከቺ›› የሚል ድምጽ በነገረኝ ጊዜ፤ ላገኛቸው አልቻልሁም፡፡ወደዚሁ ዓይኖቼን አንስቼ ቀጥ ያለና ጠባብ ጎዳና በዓለም በላይ ለጥ ብሎ አየሁ፡፡ በዚሁ ጎዳና የአድቬንት ሕዝብ እሩቅ በጎዳናው መጨረሻ ላይ ወዳለው ከተማ ይጓዙ ነበር፡፡ በጎዳናው መጀመሪያ ላይ በስተኋላቸው የበራ መብራት (ብርሃን) ይህንኑ መልአኩ የእኩለ ሌሊት ጩኸት ነው ሲል የነገረኝ ነበራቸው፡፡ ይህ መብራት በጎናው ላይ በራና እንዳይደናቀፉ ለእግሮቻቸው ብርሃን ሰጣቸው፡፡ በፊታቸው ሁኖ ወደ ከተማው ይመራቸው ወደ ነበረው ወደ የሱስ ዓይኖቻቸውን እንዳተኮሩ ቢቆዩ ደህናዎች ይሆኑ ነበር፡፡ ግን ወዲያው አንዳንዶች ደከሙ፤ አሉም፤ ከተማው እጅግ የራቀ ነው፤ ከዚያ በፊትም ሊገቡበት ተስፋ አደረጉ (ፈለጉ)፡፡ ከዚያም በኋላ፤ የሱስ የተከበረውን ቀኝ እጁን በማንሳት አደፋፈራቸው፣ ከክንዱም በአድቬንት ጭፍራ ላይ የተውለበለበ ብርሃን መጣ፤ እነሱም ‹‹ሃሌሉያ››! እያሉ ጮኹ ሌሎችም በስተ ኋላቸው ያለውን ብርሃን ከነአካቴው ካዱና እስከዚህ የመራቸው አምላክ እንዳልሆነ ተናገሩ፡፡ በስተ ኋላቸው የነበረው ብርሃን ጠፋ፣ እግሮቻቸውንም ፍጹም ጨለማ ውስጥ ተዋቸው እነሱም ተደናቅፈው ምልክቱና የሱስም ጠፍቶባቸው ከጎዳናው እታች ወዳለው ወደ ጨለማውና ኃጢአተኛ ዓለም ወደቁ፡፡ ወዲያው እንደ ብዙዎች ውኃዎች ያለውን የእግዚአብሔር ድምጽ የየሱስን መምጫ ሰዓት፤ ቀኑና ሰዓቱን ሰጠንን ሰማን፡፡ ኃጢአተኞች ነጎድጓድና የምድር መናወጥ መስሎዋቸው ሳለ ሕያዋን ቅዱሳን ቁጥራቸው ፩፻፵፬ሺህ የሆነ ድምፁን አወቁና አስተዋሉ፡፡ እግዚአብሔር ጊዜውን በተናገረ ጊዜ በላያችን መንፈስ ቅዱስን አፈሰሰብን፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ እንደ ሆነበት ፊቶቻችንም በእግዚአብሔር ክብር ያበሩና ያንፀባርቁ ጀመር፡፡ CCh 33.1
፩፻፵፬ሺህ ሁላቸው ታተሙ፤ በፍጹምም ተባበሩ፡፡ እግዚአብሔር፣ አዲሲቱ የሩሳሌም፤ የየሱስም አዲስ ስም ያለበት የተከበረ ኮከብ በግምባሮቻቸው ተጽፎ ነበር፡፡ ደስ ባለን የተቀደሰ ሁናቴያችን ኃጢአተኞች ተቆጡ፣ ወደ እሥርም ቤት ይጨምሩን ዘንድ እጆቻቸውን ሊጭኑብን በኃይል ገሠገሡብን፤ እኛም በዚኑ ጊዜ በእግዚአብሔር ስም እጃችንን ዘረጋን፤ እነሱም ረዳተቢስ ሆነው ወደ ምድር ወደቁ፡፡ የሰይጣን መስጊድ፤ (ሰይጣንን ይከተሉ ዘንድ የመረጡ) እግዚአብሔር የእርስበርሳቸውን እግሮች ሊያጥቡ የቻሉትንና በተቀደሰው መሳሳም ለወንድሞች ሰላምታ ሊሰጡ የቻሉትን እንደ ወደድን ያወቁ በዚያን ጊዜ ነበር፣ በእግሮቻችንም ወድቀው ሰገዱ፡፡ CCh 33.2
ወዲያው፣ ዓይኖቻችን ወደ ምሥራቅ አመሩ፤ አንድ ጥቁር ደመና አተላለቁ የሰው እጅ ግማሽ የሚያህል፣ ሁላችንም የሰው ልጅ ምልክት መሆኑን ያወቅነው ተገለጸ፡፡ አያቀረበ ሲመጣና እየበራ፣ የተከበረና ደግሞ በጣም የተከበረ ሁኖ ታላቅ ነጭ ደመና እስኪሆን ደመናውን በታላቅ ጸጥታ ሁላችንም አተኩረን ተመለከትን፡፡ ታቹ እንደ እሳት ይመስል ነበር፣ በደመናውም ላይ ቀስተ ደመና ነበር፣ በዙሪያውም አዕላፋት መላእክት እጅግ ተወዳጅ የሆነ መዝሙር እየዘመሩ፤ በላዩም የሰው ልጅ ተቀምጦ ነበር፡፡ ጸጉሩም የተንዥረገገ ነበር፤ በትከሻዎቹም ላይ ዘርፍ ነበር፤ በራሱም ላይ ብዙዎች አክሊሎች ነበሩ፡፡ እግሮቹም የእሳት አምሳልነት ነበረው፤ በቀኝ እጁም ስለታም ማጭድ ነበር፤ በግራውም የብር መለከት ነበር፡፡ ዓይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል ልጆቹን አጥብቀው የሚመረምሩ ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ ፊቶችን ሁሉ መገርጣት ከለበሳቸው እግዚአብሔርም ችላ ያላቸው ጥቁረት አጠለማቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ሁላችን ‹‹ማን ሊቆም ይችላል፤ ልብሴ ነውር የሌለበት ነውን››፤ እያልን ጮኸን፡፡ ከዚያም በኋላ መላእክት መዘመርን አቋረጡ፤ የሱስም ‹‹እነዚያ ንጹሆች እጆችና ንጹሆች ልቦች ያላቸው ሊቆሙ ይችላሉ፤ ጸጋዬ ይበቃችኋል›› ሲል በተናገረ ጊዜ ለጥቂት ጊዜ ታላቅ ጸጥታ ሆነ፡፡ በዚሁ ዓይኖቻችን በሩ፤ ደስታም በየልብ መላ፡፡ ደመናው ወደ ምድር እየቀረበና እየታቀረበ ሲመጣ ሳለ መላእክትም ቅኝቱን (ኖቱን) ከፍ አድርገው ቃኝተው እንደገና ዘመሩ፡፡ CCh 34.1
ከዚያ በኋላ በእሳት ነበልባሎች ተሸፍኖ በደመናው ሲወርድ የየሱስ የብር መለከት ተነፋ፡፡ ያንቀላፉትን የጻድቃንን መቃብሮች አተኩሮ ተመለከተ፤ ከዚያም በኋላ፤ አይኖቹንና እጆቹን ወደ ሰማይ አንስቶ ‹‹ንቁ ! ንቁ ! ንቁ! እናንተ በአዋራ ውስጥ የምትገኙ ተነሱ›› ሲል ጮኾ ተናገረ፡፡ በዚያን ጊዜ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፡፡ መቃብሮች ተከፈቱ ሙታንም የማይሞተውን ሰውነት ለብሰው ተነሱ ፩፻፵፬ሺህ በሞት ከነሱ ተለይተው የነበሩትን ባወቁ ጊዜ ‹‹ሃሌሉያ››! እያሉ እልልታ አቀረቡ፡፡ በዚያኑ ጊዜም እኛም ተለወጥን ጌታንም በአየር እንገናኘው ዘንድ ከነሱ ጋር ተነጠቅን፡፡ CCh 34.2
ሁላችንም ባንድነት በደመናው ውስጥ ገባን ወደ ብርጭቆ ባሕር ስንወጣም ሰባት ቀን ሆነን፣ በያኑ ጊዜም የሱስ አክሊሎችን አምጥቶ በገዛ ራሱ ቀኝ እጅ በራሶቻችን ላይ ጫነ፡፡ የወርቅ በገናዎች የድል መንሻ ሰሌኖች ሰጠን፡፡ እዚሁ በብር ጭቆ ባሕር ላይ ፩፻፵፬ሺህ ፍጹም በሆነው አራት ማዕዘን ቆሙ፡፡ አንዳንዶቻቸው እጅግ የሚያበሩ አክሎሎች ነበሩዋቸው ሌሎችም እንዲህ የበሩ አልነበሩም፡፡ አንዳንዶች አክሊሎች በኮከቦች የከበዱ ሆነው ይታዩ ነበር፡፡ ሌሎችም ጥቂቶች ብቻ ነበሩዋቸው፡፡ ሁላቸውም በአክሊሎቻቸው በፍጹም የተደሰቱ ነበር፡፡ ሁላቸውም ከትከሻዎቻቸው እስከእግሮቻቸው የተከበረ ነጭ ልብስ ለብሰው ነበር፡፡ ወደ ከተማው ደጅ በብርጭቆ ባህር ላይ ስንጓዝ መላእክት ሁላቸው በዙርያችን ነበሩ፡፡ የሱስ ኃያሉን የተከበረውን ክንዱን አንስቶ፤ ሉላዊውን ደጅ ይዞ በሚያንፀበርቁት ማጠፊያዎቹ ላይ ወለል አድርጎ ከፍቶት፣ ‹ልብሶቻችሁን በደሜ አጥባችኋል፣ ለእውነቴ ጸንታችሁ ቁማችኋላ ወደ ውስጥ ግቡ›› አለን፡፡ ሁላችንም ወደ ውስጥ ፍጹም ተሰልፈን ገባን በከተማውም ውስጥ ፍጹም የሆነ መብት አንዳለን ተሰማን፡፡ CCh 34.3
እዚህ የሕይወትን ዛፍና የእግዚአብሔርን ዙፋን አየን፡፡ ከዙፋኑም ንጹህ የሆነ የውኃ ወንዝ ይወጣ ነበር፡፡ በወንዙም ሁለቱ ወገን የሕይወት ዛፍ ነበረ፡፡ በወንዙ አንደኛው ወገን አንድ የዛፍ ጉንድ፣ በወንዙም ሌላው ወገን አንድ ጉንድ፣ ሁለቱም ንጹህ ከሆነው ከሚያብለጨልጭ ወርቅ የሆኑ ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ዛፎች ያየሁ መስሎኝ ነበር፡፡ እንደገና ተመለከትሁና እጫፍ ላይ ባንድ ዛፍ ሆነው የተገናኙ (የተጋጠሙ) መሆናቸውን አየሁ፡፡ በሕይወት ወንዝ በሁለቱ ወገን ያለው የሕይወት ዛፍ እንደዚህ ነበር፡፡ ቅርንጫፎቹ ወደ ቆምንበት ሥፍራ ተጎንብሰው ነበር ፍሬውም የተከበረ ብር የተቀላቀለበት ወርቅ ይመስል ነበር፡፡ CCh 34.4
ሁላችንም እዛፉ ሥር ሔድንና የሥፍራውን ክብር ለመመልከት ተቀመጥን በዚያኑ ጊዜም ወንድሞቻችን ፍችና ስቶክማን የመንግሥትን ወንጌል የሰበኩና እግዚአብሄር ሊያድናቸው እመቃብር ውስጥ ያኖራቸው ወደኛ መጡና እነሱ አንቀላፍተው (ተኝተው) ሳሉ፣ ምን ውስጥ አልፈን እንደነበርን ጠየቁን፡፡ ትላልቅ ፈተናዎቻችንን ልናስብባቸው ሞከርን ግን እጅግ ታላቅና ዘለዓለማዊ ከሆነው ከከበበን የክብር ክብደት (ሚዛን) ጋር ስናመዛዝን በጣም ትንሽ ሆነው ስለ ታዩን ልንናገራቸው አልተቻለንም፡፡ ሁላችንም፣ ‹‹ሀሌሉያ፣ ሰማይ እጅግ ርካሽ ነው›› እያልን ጩኸን ተናገርን፤ የተከበሩትንም በገናዎቻችንን መታንና የሰማይ ቅስቶች እንዲያስተጋቡ አደረግን፡፡ CCh 35.1
አለቃችን ከሆነው የሱስ ጋር ሁነን ሁላችን ከከተማው ወደዚህ ምድር፣ የሱስን ሊሸከመው ባልቻለው ታላቅና ኃይለኛ ተራራ ላይ ወረድን፣ ተራራውም ተከፋፍሎ ኃይለኛ ሜዳ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ላይ ተመለከትንና ትልቅዋን ከተማ አስራ ሁለት መሠረቶች፣ አሥራ ሁለት ደጆች ያሉዋትን፤ ሶስት በእያንዳንዱ ወገን፤ በእያንዳንዱ ደጅ አንድ መልአክ ሁኖበት አየን፡፡ ሁላችንም ‹‹ከተማው፣ ትልቅዋ ከተማ መውረድዋ ነው፣ ከእግዚአብሔር ከሰማይ ወደ ታች መውረድዋ ነው›› እያልን ጩኸን ተናገርን፡፡ ወረደችና በቆምንበት ሥፍራ ላይ ቆመች፡፡ ከዚያ በኋላ ከከተማዋ ውጭ ያሉትን የተከበሩ ነገሮች መመከት ጀመርን፡፡ እዚያም ለመመልከት እጅግ የደመቁ፣ እጅግም ባጌጡት ሌሎች በሸበረቁት አራት አምዶች የተደገፉትን እጅግ የደመቁ ቤቶች የብር መልክ የነበራቸውን አየሁ፡፡ እነዚህ ጻድቃን የሚኖሩባቸው ናቸው፡፡ በእያንዳንዳቸውም ውስጥ የወርቅ የዕቃ መደርደሪያ (ሼልፍ) ነበረባቸው፡፡ ብዙዎቹ ጻድቃን ወደ ቤቶቹ ሔደው የሚያንፀባርቁትን አክሊሎቻቸውን ከራሳቸው አንስተው፣ በእቃው መደርደሪያ ላይ አድርገዋቸው ከዚያ በኋላ ስለ መሬት ጉዳይ አንዳች ነገር ያደርጉ ዘንድ፣ በቤቶቹ አጠገብ ወዳለው መስክ ሲሔዱ አየሁ፡፡ እዚህ በምድር እንደምናደርገው ያለ አይደለም፣ የለም፣ የለም፡፡ እጅግ የሚያበራ ብርሃን በራሶቻቸው ሁሉ ላይ ይበራ ነበር፡፡ እነሱም ዘወትር ዕልልታ ሲያቀርቡና ለእግዚአበሔር ምሥጋና ሲያቀርቡ ነበር፡፡ CCh 35.2
በሁሉ ዓይነት አበቦች የተሞላውን ሌላ መስክ አየሁ፣ ስለቅማቸውም፣ ‹‹ከቶ አይጸወልጉም›› እያልሁ ጩኼ ተናገርሁ፡፡ ቀጥሎም ረዣዥም ሳር ያለበትን መስክ ለመለክትም እጅግ የደመቀውን አየሁ፣ ሕያው ልምላሜ ነበረው፣ ወደ ንጉሡ የየሱስ ክብር በእርጋታ ሲወዛወዝ የብርና የወርቅ ብልጭልጭታ ነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ሁሉ ዓይነት እንስሶች ወደ መሉበት መስክ ገባን፣ አንበሳ፣ በግ፣ ነብርና ተኩላ፣ ሁላቸውም ፍጹም በሆነው ኅብረት ባንድነት ነበሩ፡፡ በመኻከላቸውም አለፍን፣ በኋላችንም በሰላም ተከተሉን፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ ጫካ ውስጥ ገባን፡፡ እዚህ እንዳለን ጨለማ ጫካዎች የመሰለ አይደለም፣ የለም እረ የለም፣ ግን ብርሃን በሁሉ ላይ እጅግ ያሸበረቀ ሁኖ የዛፎቹም ቅርንጫፎች ወዲህና ወዲያ ይወዛወዙ ነበር፡፡ ሁላችንም፣ ‹‹በምድር በዳ በደህና እንኖራለን፣ በጫካዎችም ውስጥ እንተኛለን›› እያልን ጩኸን ተናገርን፡፡ በጫካማዎች ውስጥ አለፍን ወደ የጽዮን ተራራ ለመሔድ መንገዳችን ላይ ነበርንና፡፡ CCh 35.3
ስንጓዝ ሳለን የሥፍራውን ክብሮች ደግሞ አተኩረው ሲመለከቱ የነበሩትን ሰዎች ተገናኘን፡፡ የልብሶቻቸው ዘርፍ ቀይ ሁኖ አየሁ፡፡ አክሊሎቻቸውም የሚያበሩ ነበሩ፣ ልብሶቻቸው ጥርት ያሉ ነጭ ነበሩ፡፡ ሰላምታ ስንሰጣቸው እንማን እንደሆኑ የሱስን ጠየቅሁ፡፡ ለርሱ የተገደሉ ሰማዕታት እንደሆኑ ነገረኝ፡፡ ከነሱ ጋር ቁጥር የሌላቸው ትናንሾች ሰዎች ነበሩ፡፡ እነሱም ደግሞ በልብሶቸው ዘርፍ ላይ ቀይ ዝምዝማት ነበሩዋቸው፡፡ የጽዮን ተራራ እፊታችን ነበር፣ በተራራውም ላይ እጅግ የደመቀ (የተከበረ) መቅደስ ነበረ፣ በዙሪያውም ሌሎች ሰባት ተራራዎች፣ ጽጌረዳዎችና ሊሊ የሚያድጉባቸው ነበሩ፡፡ ትንንሾቹ ሲወጡ ወይም ከፈለጉ ትንንሾቹን ክንፎቻቸውን ተጠቅመውባቸው ወደ ተራሮቹ ጫፍ በርረው ከቶ የማይጠወልጉትን አበቦች ሲለቅሙ አየሁ፡፡ ሥፍራውንም የሚያሳምሩ ቦክስ (Box) ዝግባ፣ ጥድ፣ የወይራ ዛፍ፣ መርትል (ቀጋ ዓይነት)፣ ሩማን፣ የበለስም ዛፍ በደረሰው የበለስ ፍሬዎች ክብደት ጎበጠ፣ እነዚህ ሥፍራውን ሁሉ እጅግ ያሸበረቀ አደረጉት፡፡ ወደ ተቀደሰው መቅደስ ልንገባ ስንል፣ የሱስ የተወደደው ድምፁን አንስቶ ‹‹፩፻፵፬ ሺህ ብር ብቻ ይህን ሥፍር ይገቡበታል›› አለ እኛም ‹‹ሃሌሉያ›› እያልን እልልታ አቀረብን፡፡ CCh 36.1
ይህ መቅደስ በሰባት አምዶች ተደግፎ ነበር፡፡ ሁላቸውም ከሚያንፀባርቅ ወርቅ የሆኑ እጆች በሚያሸበርቁ ሉሎች ያጌጡ ናቸው፡፡ እዚያ ያየኋቸውን አስገራሚዎች ነገሮች ልናገር አልችልም፡፡ ከንዓን ቋንቋ ምነው ለመናገር በቻልሁ ኑሮ፣ በዚያን ጊዜ ስለ ጥሩው ዓለም ክብር ትንሽ ለመናገር በቻልሁ ነበር፡፡ እዚያም የ፩፻፵፬ሺህ ስሞች በወርቅ ፊደሎች የተቀረጹባቸውን የደንጊያ ጽላቶች አየሁ፡፡ የመቅደሱን ክብር ካየን በኋላ ወጣን፣ የሱስ ተወንና ወደ ከተማው ሔደ፡፡ ወዲያው የተወደደው ድምጹን አንደገና እንዲህ ሲል ሰማን ‹‹ሕዝቦቼ ከታላቅ መከራ ወጥታችኋል፣ ፈቃዴንም አድርጋችኋል፣ ለኔም ተሳቀያችሁ፣ ወደ ምሳም ኑ፣ እኔው ራሴ ታጥቄ አገልግላችኋለሁ››፡፡ ‹‹ሃሌሉያ!፣ ምሥጋና ይሁን!›› እያልን እልልታ አቀረብን፡፡ ወደ ከተማውም ገባን ከንጹህ ብር የሆነ ጠረጴዛ (ገበታ) አየሁ፡፡ በርዝመት ብዙ ማይል የሆነ ሆኖም ዓይኖቻችን ይደርሱበት ነበር፡፡ የሕይወት ዛፍ ፍሬ፣ መና፣ ሩማኞች፣ በለሶች፣ ፖምግኔት፣ ወይምኖች፣ ብዙዎችም ሌሎች ዓይነት ፍሬዎች አየሁ፡፡ ከፍሬው እንድበላ ይፈቀድልኝ ዘንድ የሱስን ጠየቅሁ፡፡ እርሱም ‹‹አሁን አይደለም፣ የዚህን አገር ፍሬ የሚበሉ እንደገና ወደ ምድር አይመለሱም፣ ነገር ግን ታማኝ ከሆንሽ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሕይወትን ዛፍ ፍሬ ትበያለሽ፣ የምንጩንም ውኃ ትጠጪያለሽ›› አለኝ፡፡ አለኝም፣ ‹‹እንደገና ወደ ምድር ተመልሰሽ የገለጥሁልሽን ለሌሎቸ መንገር አለብሽ››፡፡ ከዚያም በኋላ፣ መልአኩ ወደዚህ ጨለማ አለም በቀስታ ይዞኝ ወረደ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እዚህ ከእንግዲህ ልቆይ የማልችል ይመስለኛል፡፡ የምድሩ ነገሮች ሁሉ አሰቃቂዎች ሆነው ይታዩኛል፡፡ እዚህ ብቸኝነት እጅግ ይሰማኛል፣ ጥሩውን ምድር አይቻለሁና፡፡ ምነው እንደ ርግብ ክንፎች በኖሩኝና ከዚያ በኋላ በርሬ ዕረፍት አገኝ ነበር፡፡ CCh 36.2