የቤተ ፡ ክርስቲያን፡ ምክሮች፡፡

14/126

ምዕራፍ ፪—የፍፃሜ ጊዜ፡፡

የምንኖረው በፍጻሜ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ እየተፋጠኑ የሚፈጸሙት የጊዜያቱ ምልክቶች የክርስቶስ መምጫ እጅግ የቀረበ እንደሆነ የሚናገሩ ናቸው፡፡ የምንኖርበት ቀናት ጥብቅና ዋና ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥቂት በጥቂት ፤ እንደያውም በእርግጥ ከምድር እየራቀ ነው፡፡ መቅሰፍቶችና ፍርዶች ያምላክን ጸጋ በሚንቁት ላይ ፈጽመው በመውረድ ላይ ናቸው፡፡ በምድርና በባሕር ያሉት መዓቶች ያልተረጋጋው የማኅበር ሁናቴ ፤ የጦርነት ውካታዎች የሚያሠጉ ናቸው፡፡ የተቃረቡትን እጅግ ታላላቅ ሁኔታዎች አስቀድመው የሚያበስሩ (የሚናገሩ) ናቸው፡፡ CCh 37.1

የክፉው ወኪሎች ኃይሎቻቸውን እያስተባበሩና እያጸኑ ናቸው፡፡ ለመጨረሻው ታላቁ መከራ በመበርታት ላይ ናቸው፡፡ በዓለማችን ታላቅ መለወጥ በቶሎ ሊሆን ነው ፤ የመጨረሻዎቹም እንቅስቃሴዎች የሚፋጠኑ ይሆናሉ፡፡ በዓለም የነገሮች ሁኔታ ልክ አስቸጋሪ ጊዜያት በላያችን እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ዕለታዊ ጋዜጣዎች በቅርቡ ወደፊት ስለሚሆነው የሚያስፈራ ተጋድሎ በሚያመለክቱ ማመልከቻዎች የተመሉ ናቸው፡፡ በድፍረት የሚደረገው ቅሚያ ዘወትር የሚሆን ነው፡፡ የሠራተኞች መዶለት የተለመደ ነው፡፡ ሌብነትና ነፍስ መግደል በየሥፍራው ይደረጋል፡፡ ሰዎች ጋኔሎች አድረውባቸው የወንዶችን ፤ የሴቶችንና የትንንሽ ልጆች ሕይወትን ያጠፋሉ፡፡ ሰዎች በክፋት ተጨማልቀዋል፤ ልዩ ልዩ ዓይነት ክፋት ሁሉ አይሎአል፡፡ CCh 37.2

ጠላት ፍርድን በማጣመምና ራስን በመውደድ ትርፍ የማግኛ ምኞት በሰዎች ልቦች በመሙላት ተከናውኖለታል፡፡ «ፍርድም ወደ ኋላ ተመለሰ ጽድቅም በሩቅ ቆመ፡፡ እውነት ባደባባይ ወድቅዋልና ቅን ነገርም መግባት አልቻለም»፡፡ (ኢሳያስ ፶፱ ፡፲፬)፡፡ በታላላቅ ከተሞች በድህነትና በጉስቁልና የሚኖሩ በቂ ምግብ መጠጊያና ልብስ የሌላቸው አሉ፡፡ በዚያው ከተሞች ልብ ሊመኝ ከሚችለው በላይ ያላቸው ደግሞ በመሽሞንሞን (በመቀማጠል) የሚኖሩ ገንዘባቸውን ሉክስ በሆኑት ሙሉ ዕቃዎች ባሉበት ቤቶች ላይ ራስንም በማጌጥ ወይንም የባሰውን ለሥጋዊ ፍትወቶች መደሰቻ ለሚያሰክር መጠጥ ፤ ለሲጋራ እንዲሁም ለሌሎች ነገሮች የአንጎልን ኃይሎች ለሚያጠፉና አእምሮን ለሚያናውጥ ፤ ነፍስንም ለሚያዋርድ ሲያባክኑ ይገኛሉ፡፡ ሰዎች በልዩ ልዩ ጭቆናና ግፍ ከልክ ያለፈ ሐብት ሲቆልሉ ሳለ የራብተኞች ሰዎች ጩኸት በእግዚአብሔር ፊት እየወጣ ነው፡፡ CCh 37.3

ቤቶች ፎቅ በፎቅ ላይ ወደ ሰማይ ብድግ ሲሉ እመለከት ዘንድ በሌሊት ጊዜ ተጠርቼ ነበር፡፡ እነዚህ ቤቶች ለእሳት መድኅን የወጣላቸው እንደሆኑ ተመስክሮላቸው ነበር፤ ባለቤቶቻቸውንና ገንቢዎቻቸውን ለማስመስገን የተሠሩ ነበሩ፡፡ እነዚህ ቤቶች ከፍ እያሉና እጅግ ከፍ እያሉ ብድግ አሉ፤ በውስጣቸውም እጅግ ውድ ነገር (ዕቃ) ተሠርቶባቸዋል፡፡ የእኒህ ቤቶች ባለቤቶች የሆኑ ፤ «እግዚአብሔርን አብልጠን ልናመሰግነው እንዴት እንችላለን”? ብለው ራሳቸውን አልጠየቁም፡፡ እግዚአብሔርም በሐሳባቸው ውስጥ አልነበረም፡፡ CCh 37.4

እነዚህ ከፍ ያሉ ቤቶች ወደ ላይ እንደ ወጡ መጠን ባለቤቶቹ ራስን በማስደሰትና ጐረቤቶቻቸውን ቅናት ያስነሡባቸው ዘንድ የሚጠቀሙበት ገንዘብ ስለ ነበራቸው በመታበይና በትዕቢታቸው ተደሰቱ፡፡ አብዛኛው ገንዘብ ተቀማጭ ያደረጉት በግፍ ድሆችን በመጨቆን የተገኘ ነው፡፡ በሰማይ የንግድ ሥራ ሁሉ ሂሣብ የሚጠበቅ መሆኑን ረሱ፤ የግፍ አድራጎት ሁሉ የማታለል ሥራ ሁሉ እዚያ ይመዘገባል፡፡ CCh 38.1

ቀጥሎ እፊቴ የቀረበው ትርዕይት የዕሳት አደጋ ምልክት ነው፡፡ ሰዎች ከፍ ወዳለው እንደያውም ለእሳት መድኅን ወደ ወጣላቸው ቤቶች ተመልክተው ፤ «በፍጹም ደህና ናቸው” ብለው ነበር፡፡ ዳሩ ግን እነዚህ ቤቶች ከሬንጅ (ከቅጥራን) እንደ ተበጁት ተበሉ (ተቃጠሉ)፡፡ የእሳት አደጋ መኪናዎች ከጥፋት ሊያድኑ ምንም ሊያደርጉ አልተቻላቸውም፡፡ CCh 38.2

የጌታ ጊዜ ሲመጣ ፤ ትዕቢተኞች ፤ ኩሩዎቹ ሰብዓዊ ፍጥረቶች በልባቸው ምንም መለወጥ ባይሆንባቸው ለማዳን ጠንካራ የሆነው እጅ ለማጥፋትም ጠንካራ መሆኑን ሰዎች ያገኙታል፡፡ ማንም ምድራዊ ኃይል (ባለሥልጣን) ያምላክን እጅ ሊያግድ የሚችል የለም፡፡ ሕጉን ችላ ስለማለታቸውና ራስን ስለመውደድ ምኞታቸው በሰዎች ላይ ፍዳ ሊያመጣባቸው እግዚአብሔር የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ከመጥፋት የሚጠብቃቸው ፤ ቤቶችን በመሥራት ረገድ ምንም አርማቱራ (ጠንካራ ብረቶች) ሊጠቀሙባቸው አይቻልም፡፡ CCh 38.3

በአሁኑ የማኅበር ሁናቴ ስር ያሉትን ምክንያቶች የሚያስተውሉ በአዋቆችና በመኰንኖች መኻኸል እንኳ ብዙዎች አይደሉም፡፡ የመንግሥትን የኃላፊነት ሥራ የያዙ የሞራል እርኩሰት ድኅነት ፤ ጉስቁልናና እየተጨማመረ የሚሔደውን የወንጀል ሥራ ችግሩን ሊፈቱ አይቻላቸውም፡፡ በከንቱ የንግድን ሥራ በበለጠው ደህና መሠረት ላይ ሊያውሉ ይታገላሉ (ይጣጣራሉ)፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ትምህርቱን የልቁን ተቀብለው ቢሆን ለሚያስቸግሩዋቸው ችግሮች መፍትሔ ባገኙ ነበር፡፡ CCh 38.4

ቅዱሣት መጻሕፍት ክርስቶስ ዳግመኛ ከመምጣቱ በፊት ስለሚሆነው ስለ ዓለም ሁኔታ ይናገራሉ፡፡ በቅድሚያና በግፍ ትልቅ ሐብት ስለሚያከማቹት ሰዎች እንዲህ ተጽፎአል ፤ «ለኋለኛው ቀን መዝገብ አከማቻችሁት፡፡ እነሆ የሰራተኞች ምድራችሁን ያጨዱት ዋጋ እላንት የቀማችኋቸው ይጮኻል፡፡ ያጫጆችም ድምፅ ወደ ፀባዖት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደረሰ፡፡ በምድር ላይ ደስ አላችሁ በሴሰኝነት ተቀመጣችሁ፡፡ ልባችሁን አደነደናችሁ በበዓል ቀን እንደሆነ፡፡ በጻድቁም ፈረዳችሁ ገደላችሁትም አልተጠናወታችሁምም” ፡፡ ያዕቆብ ፭ ፫-፮ ፡፡ CCh 38.5

ፈጥነው በሚፈጸሙት የጊዜያቱ ምልክቶች የተሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች ማን ያነባል? ዓለማውያን ምን ይታሰባቸዋል? በጠባያቸው ምን መለወጥ ይታያል? በኖህ ዓለም ይኖሩ ከነበሩት ነዋሪዎች በጠባያቸው ይታይባቸው በነበረው በቀር ሌላ የለም፡፡ በዓለማዊ ሥራና ተድላ ተመስጠው ከጥፋት ውኃ በፊት የነበሩ ሰዎች «አላወቁምም የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን እስኪያጠፋ ድረስ»፤ ማቴዎስ ፳፬፡፴፱ ፡፡ ከሰማይ የተላከላቸው ማስጠንቀቂያዎች ደርሶአቸዋል፤ ግን መስማት አልፈቀዱም ፡፡ ዛሬም ዓለም የእግዚአብሐር ድምፅ ማስጠንቀቂያ ፈጽሞ ችላ ብሎ ወደ ዘላለማዊ ጥፋት እየገሰገሠ ነው፡፡ CCh 38.6

ዓለም በጦርነት መንፈስ ተነሳስቷል (ታውኳል)፡፡ የዳንኤል ፲፩ኛው ምዕራፍ ትንቢት ፤ መደምደሚያ ወደሆነው ፍጻሜው ለመድረስ ተቃርቧል፡፡ በትንቢቶቹ ውስጥ የተነገሩት የመከራ ሁኔታዎች በተሎ የሚሆኑ ናቸው፡፡ CCh 39.1

«እነሆ እግዚአብሔር ምድርን ባዶ ያደርጋል፤ ያጠፋትማል፤ ፊትዋንም ይገለብጣል፤ በርስዋም የተቀመጡትን ይበትናል፡፡ … ከሕግ ተላልፈዋልና የተሰራውንም ሥርዓት ለወጡ የዘላለሙንም ኪዳን አጠፉ፡፡ ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች በርስዋም የተቀመጡ ይቀጣሉ፡፡ … ከበሮ የሚመቱ ደስታ አለፈ፤ የደስተኞች ድምፅ ዝም አለ፤ የመሰንቆ ደስታ ቀረ»፡፡ ኢሳይያስ ፳፬፡ ፭-፰፡፡ CCh 39.2

«ወዮ ለቀን የእግዚአበሔር ቀን ቅርብ ነውና፡፡ እርሱም ሁሉን ከሚችል አምላክ እንደ ጥፋት ይመጣል» ፡፡ ዮኤል ፩፡፲፭ ፡፡ CCh 39.3

«ወደ ምድር አየሁ፡፡ እነሆ እርስዋ ባዶ ናት ምንም የለባትም ወደ ሰማዮችም አየሁ ብርሃንም የለባቸውም፡፡ ተራሮችን አየሁ እነሆ እርሳቸው ተንቀጠቀጡ ኮረፍቶችም ሁሉ ተናወጡ፡፡ አየሁ ሰውም የለም የሰማይም ዖፍ ሁሉ ርቆ በረረ፡፡ ተመለከትሁ እነሆ የሚያፈራ እርሻ እንደ ምድረ በዳ ሆነ ፤ ከተሞቹም ሁሉ ፈረሱ»፡፡ ኤርሚያስ ፬ ፤ ፳፫-፳፮፡፡ CCh 39.4

«ወዮ ያ ቀን ታላቅ ቀን ነውና ለርሱም ምሳሌ የለውም፡፡ የመከራ ዘመን እርሱ ለያዕቆብ ነው ከርሱ ግን ይድናል ኤርሚያስ ፴፤፯ ፡፡ CCh 39.5

በዚህ ዓለም እግዚአብሔርን በመቃወም የጠላት ወገን የሆኑ ሁሉ አይደሉም፡፡ ታማኞች (ታዛዦች) ያልሆኑ ሁሉ አይደለም፡፡ ለእግዚአብሔር እውነተኞች የሆኑ ጥቂቶች የታመኑ አሉ ፤ ዮሐንስ «ከዚህ ነው የቅዱሳን ትዕግሥት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጠብቁ የየሱስንም ሃይማኖት” ሲል ይጽፋልና፡፡ ራእይ ፬፡፲፪፡፡ እግዚአብሔርን በሚያገለግሉና በማያገለግሉት መኻኸል ጦርነቱ በቶሎ በኃይል የሚፋፋም ነው፡፡ ሊነቃነቁ የማይቻላቸው ነገሮች ይቆዩ ዘንድ፤ ሊነቃነቅ የሚቻል ሁሉ ይነቃነቃል፡፡ CCh 39.6

ሰይጣን ትጉ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ነው፡፡ ጊዜው ቅርብ እንደሆነ ናየውቃል፤ በዚህ ምድር ያለውን የእግዚአብሔርን ሥራ ይቃወም ዘንድ በማንኛውም ሐሳብ ሆነ ይሻል፡፡ ሰማያዊ ክብርና ያለፉት ስደቶች ደጋግመው በሚቀላቀሉበት ጊዜ በምድር ላይ ስለሚኖሩት (ሕያዋን የሆኑትን) የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁኔታ ማናቸውንም ሐሳብ ለመስጠት የማይቻል ነው፡፡ እነሱ ከእግዚአብሔር ዙፋን በሚወጣው ብርሃን ውስጥ ይሔዳሉ፡፡ በመላእክት አማካይነት ፤ በሰማይና በምድር መኻከል ዘወትር መገናኚያ ይሆንላቸዋል፡፡ ሰይጣንም በክፎች መላእክት ተከብቦ አምላክም እንደሆነ በመናገር ቢዠለው የተመረጡትን እንኳ ለማሳት ሁሉ ዓይነት ተዓምራት ያደርጋል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተዓምራት በመሥራት ደኅንነታቸውን የሚያገኙ አይደለም ፤ ሰይጣን የሚደረጉትን ተዓምራቶች አስመስሎ ይሠራልና፡፡ የተፈተኑትና የተሞከሩት የእግዚአብሔር ሕዝብ በዘፀዓት ፴፩፡፲፪-፲፰ በተነገረው ምልክት ኃይላቸውን ያገኛሉ፡፡ «ተጽፍዋል» በሚል ሕያው ቃል ጸንቶ አለባቸው፡፡ በደኅና የቆሙ ዘንድ የሚችሉበት መሠረቱ ይኸው ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ቃል ኪዳናቸውን የጣሱ በዚያን ቀን ያለ አምላክና ያለ ተስፋ ይሆናሉ፡፡ CCh 39.7

አምላክን የሚያመልኩ አራተኛውን ትእዛዝ በመጠበቃቸው በተለይ የሚታወቁ ይሆናሉ፤ ይህ የእግዚአብሔር የፈጣሪቱ ኃይል ምልክትና ሰው የሚያከብርበትና የሚሰግድለት የፍላጎቱ ምሥክር ነውና፡፡ ኃጢአተኞች የፈጣሪን መታሰቢያ ለማፍረስና የሮምን ድንጋጌ ከፍ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት ይታወቃሉ፡፡ CCh 40.1

በተጋድሎው ውጤት ክርስቲያኖች ሁሉ በሁለት ትላልቅ ክፍሎች ይከፈላሉ፤ የእግዚአብሐርን ትእዛዛትና የየሱስን ኃይማኖት የሚጠብቁ የአርዌውና ለምሳሌው የሚሰግዱ፤ ምልክቱንም የሚወስዱ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የአርዌውን መልክ ይወስዱ ዘንድ፤ «ታላቁን ታናሹንም ባለጠጎችንም ድሆችንም የሰው ልጆችንም ባሮችንም” ሁሉ ለማስገደድ ኃይላቸውን የሚያስተባብሩ ቢሆንም እንኳ ፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ግን አይቀበሉትም፡፡ ራዕይ ፲፫፡፲፮ ፡፡ CCh 40.2

የጳጥሞ ነቢይ፤ «አርዌውንም ድል የነሱ ምሳሌውንም፣ መልኩንም፣ የስሙንም ቁጥር በብርጭቆ ባሕር ቁመው፡፡ ከርሳቸውም ጋራ የእግዚአብሔር መሰንቆች” ፤ የሙሴንና የበጉን መዝሙር ሲዘምሩ ይመለከታቸዋል፡፡ ራእይ ፲፭፣፪ ፡፡ CCh 40.3

አስፈሪ የሆኑ ፈተናዎችና ሙከራዎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ ይቆያቸዋል (ይጠባበቃቸዋል)፡፡ የጦርነት መንፈስ ካንዱ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላይኛው ሕዝቦችን እያነሣሳ ነው፡፡ ግን ከሚመጣው መከራ ጊዜ መኻከል ፤ ይኸውም መከራ ፤ ሕዝብ ከሆነ ጀምሮ እንደርሱ ያለ ያልሆነ ፤ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ሳይነቃነቅ ይቆማል፡፡ ሰይጣንና ጭፍራው ሊያጠፋቸው አይችልም ፤ መላእክት በኃይል የሚበልጡ ይጠብቋቸዋልና፡፡ CCh 40.4