መልዕክት ለወጣቶች
በችግር ጊዜ ድፍረት
በመጨረሻ አሸናፊዎች የሚሆኑ በክርስትና ሕይወታቸው አሰቃቂ የሆኑ የግራ መጋባትና የፈተና ወቅቶች ያጋጥሙአቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ፈተና በክርስቶስ ት/ቤት ከሚገጥማቸው የባሕርይ ማረሚያ አንዱ ስለ ሆነና ሰሙን ከወርቁ ለማስወገድና ለማጥራት አስፈላጊ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን መታመን መጣል የለባቸውም፡፡ የእግዚአብሔር ባሪያ የጠላትን ጥቃቶችና አሰቃቂ ስድቦች በድፍረት በመታገስ ሰይጣን በመንገዱ ላይ የሚያስቀምጣቸውን እንቅፋቶች ማሸነፍ አለበት፡፡ MYPAmh 48.1
ሰይጣን የክርስቶስ ተከታዮች እንዳይፀልዩና ቃሉን እንዳያጠኑ ተስፋ ለማስቆረጥ ይሻል፡፡ ኢየሱስን ከእይታ ለመደበቅ አስጠሊታ ጥላውን በመንገዳቸው ላይ ይጥላል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች በማያቋርጥ ጥርጣሬ ስር ሆነው እየተሰቀቁ፣ እየተንቀጠቀጡ፣ እየተጨነቁ እንዲጓዙ ማድረግ ለእርሱ ደስታው ነው፡፡ መንገዳቸውን በተቻለው መጠን በሃዘን የተሞላ ለማድረግ ይሻል፡፡ ነገር ግን ምድራዊ ችግሮቻችሁን ከማየት ይልቅ ወደ ላይ መመልከታችሁን ብትቀጥሉ በመንገድ ላይ አትደክሙም፤ ኢየሱስ ሲረዳችሁና እጁን ሲዘረጋላችሁ ታያላችሁ፡፡ ከእናንተ የሚጠበቀው በእርሱ በመታመን እጃችሁን መስጠትና እንዲመራችሁ መፍቀድ ነው፡፡ በእርሱ እየታመንክ በሄድክ ቁጥር በተስፋ የተሞላህ ትሆናለህ፡፡ MYPAmh 48.2