መልዕክት ለወጣቶች
ዝቅ ባለ ደረጃ ላይ የመሆን ምክንያት
ወጣቶቻችንም ሆኑ በእድሜ የበሰሉት በቃላሉ ወደ ፈተናና ወደ ኃጢአት የሚመሩበት ምክንያት ምንድነው? ለዚህ ምክንያቱ የእግዚአብሔር ቃል መጠናት የሚገባውን ያህል ባለመጠናቱና አእምሮ እንዲያሰላስል እድል ባለመሰጠቱ ነው። ቃሉ አድናቆት ተችሮት ቢሆን ኖሮ ውስጣዊ ቀናነትና ክፉን ለማድረግ የሚገፋፋውን የሰይጣንን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል የመንፈስ ጥንካሬ ይኖር ነበር። የተቀደሰው የእግዚአብሔር ቃል ስላልተጠናና የማሰላሰል አርእስት ካለመሆኑ የተነሣ ፅኑና አቋም ያለው የፈቃድ ኃይል በሕይወትና በባሕርይ ውስጥ የለም። አእምሮን ከንፁህና ከተቀደሱ ሀሳቦች ጋር ለማገናኘትና ንፅህና ከጎደላቸውና እውነተኛ ካልሆኑ ሐሳቦች ለመመለስ የተደረገ ጥረት የለም:: የተሻለውን የመምረጥ፣ ማሪያም እንዳደረገችው በኢየሱስ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ከመለኮታዊ መምህር እጅግ የተቀደሱ ትምህርቶችን በመማር በልብ ውስጥ እንዲመሠረቱና በእለታዊ ሕይወት ሥራ ላይ እንዲውሉ የማድረግ ምርጫ አልተደረገም። የተቀደሱ ነገሮችን ማሰላሰል ከፍ ያለና ንፁህ አእምሮን በመፍጠር ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች እንድንሆን ያደርጋል። MYPAmh 270.3
እግዚአብሔር በሥጋ ፍትወት፣ ምድራዊ እርኩሰቶች፣ በሐሳብ ወይም በቃል ወይም በድርጊት የእርሱን ኃይል የሚያቃልሉትን (ዝቅ የሚያደርጉትን) ሰዎች አይቀበላቸውም። ሰማይ ራሳቸውን ካላነጹ፣ መንፈሳዊ ካልሆኑ፣ ካልተስተካከሉና ካልጠሩ በስተቀር ማንም መግባት የማይችልበት ንፁህና ቅዱስ ቦታ ነው። ለራሳችን መሥራት ያለብን ሥራ አለ! ያንን ሥራ መሥራት የምንችለው ከኢየሱስ ብርታት ስናገኝ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን መውደድና እንደ እግዚአብሔር ድምፅ መታዘዝ አለብን። እርሱ የሚያስቀምጣቸውን ገደቦችና የሚጠይቅብንን ነገሮች ማየትና ማስተዋል አለብን። “አድርግ”፣ “አታድርግ” የሚለንን ነገሮች ማስተዋልና የእግዚአብሔርን ቃል ትክክለኛ ትርጉም መገንዘብ አለብን። MYPAmh 270.4