መልዕክት ለወጣቶች
በይቅርታ የተሞላ የእግዚአብሔር ግብዣ
የእግዚአብሔር ግብዣ ለእያንዳንዱ ወጣት “ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ! በንፅህና •እጠብቃለሁ! ምኞቱንም ሁሉ በእውነተኛ ደስታ አጠግበዋለሁ::” በማለት ይቀርብለታል። እግዚአብሔር ወጣቶችን ማስደሰት ይፈልጋል። ለዚህም ነው እግዚአብሔር የሰጣቸው የአካል ክፍሎች በሙሉ በብርታትና በጤናማ ሁኔታ እንዲጠበቁ ልባቸውን ለእርሱ ጥበቃ አሳልፈው እንዲሰጡ የሚጠይቀው። የእግዚአብሔርን የህይወት ሥጦታ ይዘዋል። ልብ እንዲመታ የሚያደርግ እርሱ ነው! ለእያንዳንዱ የአካል ክፍል ብርታት የሚሰጥ እርሱ ነው። ንፁህ ደስታ ከእግዚአብሔር ሥጦታዎች አንዱንም አያበላሽም። ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር የሚለየንን ደስታ ስንፈልግ በራሳችን አካል ላይና በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት እንፈጽማለን። ወጣቶች ፈተና ባለበት ዓለም ውስጥ እንዲቀመጡ የተደረጉበት ምክንያት ከመላእክት ጋር ለመኖር ገጣሚ የሆነ ባሕርይ እንዳላቸው ለመፈተን እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል። MYPAmh 260.5
ጓደኞቻችሁ በክፋትና በከንቱነት መንገድ እንድትሄዱ በሚገፋፉአችሁ ጊዜ፣ በዙሪያችሁ ያሉ ሁሉ እግዚአብሔርን እንድትረሱ ሲፈትኑአችሁ፣ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ችሎታዎቻችሁን እንድታበላሹና በተፈጥሮአችሁ ውስጥ ያለውን ክቡር ነገር እንድታዋርዱ ሲፈትኑአችሁ ተቃወሙአቸው። የጌታ ንብረት መሆናችሁን፣ በእግዚአብሔር ልጅ ስቃይና መከራ በዋጋ የተገዛችሁ መሆናችሁን አስታውሱ…። MYPAmh 261.1
ጌታ ኢየሱስ አገልግሎታችሁን ይፈልጋል። ይወዳችኋል። ፍቅሩን ከተጠራጠራችሁ ቀራንዮን ተመልከቱ። ከመስቀሉ የተንፀባረቀው ብርሃን ማንኛውም ምላስ ሊገልፅ የማይችለውን የፍቅር ታላቅነት ይገልጽላችኋል። “ትዕዛዛቴን የሚጠብቅ የሚወደኝ እርሱ ነው።” ተግተን በማጥናት ከትእዛዛቱ ጋር መተዋወቅ አለብን:: በዚህም የእርሱ ታዘዥ ወንድና ሴት ልጆች መሆናችንን ማሳየት አለብን። MYPAmh 261.2