መልዕክት ለወጣቶች
የሥነ-ፅሁፍ ማህበራት
ብዙ ጊዜ የሥነ-ፅሁፍ ማህበራት ለወጣቶቻችን ጠቃሚ ናቸውን? ተብሎ ይጠየቃል። ይህንን ጥያቄ በትክክል ለመመለስ እነዚህ ማህበራት ይሰጣሉ ተብሎ የተገባውን ቃል ብቻ ሳይሆን ከልምድ እንደተረጋገጠው ያሳደሩትን ተፅዕኖ መመልከት ያስፈልገናል። ለራሳችን፣ ለህብረተሰባችንና ለእግዚአብሔር አእምሮአችንን የማሻሻል ሀላፊነት አለብን። ነገር ግን አእምሮን ለማሳደግ በማለት ግብረገብንና መንፈሳዊነትን የሚጎዳ መንገድን መቀየስ የለብንም፡፡ የአእምሮም ሆነ የግብረ ገብ ከፍ ያለው የፍፅምና ደረጃ ሊደረስ የሚችለው ሁለቱም አብረው ሲያድጉ ብቻ ነው። ታድያ እነዚህ ውጤቶች በአጠቃላይ እንደሚደረጉት ከሥነ-ፅሁፍ ማህበራት ይገኛሉን? MYPAmh 253.1
የሥነ-ፅሁፍ ማህበራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው ከሚገልፀው ተቃራኒ የሆነ ተፅእኖ እያሳደሩ ናቸው። በአጠቃላይ ሂደታቸው ለወጣቶች ጎጂ ናቸው። በእነዚህ ማህበራት ተግባራት ላይ ሰይጣን የራሱን ማህተም ለማሳረፍ ይመጣል። ወንዶችን ወንድ የሚያደርግና ሴቶችን ሴት የሚያደርግ ነገር ሁሉ ከክርስቶስ ባሕርይ ተንፀባርቋል። በእነዚህ ማህበራት ለኢየሱስ አነስተኛ ቦታ በሰጠን ቁጥር መታየት የሚገባው ከፍ የሚያደርግ፣ የሚሞርድና የከበረ የሚያደርግ ነገር ይቀንስብናል። ዓለማውያን ምኞታቸውን ለማሟላት እነዚህን ስብሰባዎች ሲያካሄዱ የክርስቶስ መንፈስ ቦታ አይሰጠውም። አእምሮ ትክክለኛ በሆነ ነገር፣ በእግዚአብሔር፣ እርግጠኛና አስፈላጊ በሆነ ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደ ግምታዊና ጥልቀት ወደሌለው ነገር ይወሰዳል። ምነው የሥነ-ፅሁፍ ማህበራት ስማቸው እውነተኛ ባህርያቸውን በገለፀ! ገለባ ለስንዴ ምን ይጠቅማል? MYPAmh 253.2
የሥነ-ፅሁፍ ማህበራትን ለመመስረት የሚመራው ዓላማና ምክንያት ጥሩ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ጥበብ እነዚህን ድርጅቶች ካልተቆጣጠረ በስተቀር ክፉ ኃይል ይሆናሉ። ብዙ ጊዜ ሃይማኖተኞች ያልሆኑና በልባቸውና በህይወታቸው ያልተቀደሱ ሰዎች የማህበሩ አባል በመሆን በአብዛኛው በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ይቀመጣሉ። እያንዳንዱ አእምሮን ወይም አካልን የሚጎዳ ተፅእኖን ለመከላከል ብቁ ናቸው ተብለው የታሰቡ ህጎችና ደንቦች ተቀባይነት ሊያገኙ ይችላሉ። ነገር ግን ተንኮለኛ ጄኔራል የሆነ ሰይጣን ህብረተሰቡ ከእርሱ እቅዶች ጋር እንዲስማማ ለማድረግ ሥራ ላይ ነው። በሂደትም ይሳካለታል። ታላቁ ጠላት ከዚህ በፊት በቁጥጥር ሥር ያደረጋቸውን የሚቀርብበትን መንገድ በቀላሉ ያገኝና በእነርሱ አማካኝነት አላማውን ይፈጽማል። ስብሰባዎች ለዓለማውያን የሚስቡ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ የማዝናኛ ነገሮች እንዲገቡበት ይደረጋሉ። ከዚህም የተነሣ የሥነ-ፅሁፍ ማህበራት ተግባራት ተብለው የተጠቀሱ ነገሮች አዋራጅ ወደሆነው የቲያትር ሥራና ርካሽ ነገር ደረጃ ዝቅ ይላሉ። እነዚህ ነገሮች ከእግዚአብሔር ጋር ጠላትነት ያለውን የሥጋን አእምሮ ያስደስታሉ። ነገር ግን አእምሮን አያበረቱም፣ ወይም ግብረ ገብን አያንጹም። MYPAmh 253.3
በእነዚህ ማህበራት አማካኝነት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ከማያምኑት ጋር የሚፈጥሩት ህብረት ኃጢአተኞችን ፃድቃን አያደርጋቸውም። የእግዚአብሔር ህዝብ በፈቀዳቸው ከዓለማውያንና ካልተቀደሱ ጋር አንድነት ሲፈጥሩና የበላይነት ሲሰጡአቸው ራሳቸውን ባስገዙአቸው በእነዚህ ሰዎች ያልተቀደሰ ተፅዕኖ ከእግዚአበሔር እንዲርቁ ይመራሉ። ለአጭር ጊዜ ይህንን ያህል እጅግ የሚያስጠላ ነገር ላይኖር ይችላል፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር መንፈስ ቁጥጥር ሥር ያልዋሉ አእምሮዎች የእውነትና የጽድቅ ሽታ ያላቸውን ነገሮች በቀላሉ አይቀበሉም። ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ ራሳቸውን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያሰልፉ ነበር። ሁለቱንም ክፍሎች የሚቆጣጠሩአቸው ሁለት የተለያዩ ጌቶች ስለሆኑ በአለማቸው፣ በተስፋቸው፣ በፍላጎታቸውና ለነገሮች ካላቸው ፍቅር አንፃር ተቃራኒ ናቸው። የኢየሱስ ተከታዮች የተረጋጋ፣ትርጉም ያለውና ከፍ ያለ ነገር ሲያስደስታቸው ለቅዱስ ነገር ፍቅር የሌላቸው ደግሞ በሚደረጉ ነገሮች ውስጥ ጥልቀት የሌላቸውና እውነተኛ ያልሆኑ ነገሮች ከሌሉበት በስተቀር በእነዚህ ስብሰባዎች ደስ አይሰኙም። ጥቂት በጥቂት መንፈሳዊው ነገር መንፈሳዊ ባልሆነ ነገር እየተሸፈነ ይሄድና በባሕርያቸው ተፃራሪ የሆኑ መርሆዎችን ለማጣጣም የተደረገው ጥረት ከንቱ ልፋት መሆኑ ይረጋገጣል። MYPAmh 253.4
ግንኙነት ላላቸው ሁሉ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል የሥነ-ፅሁፍ ማህበር የሚመሠረትበትን እቅድ ለማዘጋጀት ጥረቶች ተደርገው ነበር። ያውም የማህበሩ አባላት በሙሉ ማህበሩ መሆን የሚገባውን ሆኖ እንዲገኝ የሞራል ሃላፊነት እንዳለባቸው እንዲሰማቸውና እነዚህን ህብረቶች ብዙ ጊዜ ለመንፈሳዊ መርሆዎች አደገኛ እንዲሆኑ ከሚያደርጉ ክፉ ነገሮች ለመታደግ ነበር። ሚዛናዊ የሆነ አእምሮ ያላቸው፣ ከሰማይ ጋር ሕያው ግንኙነት ያላቸው፣ ክፉ ዝንባሌዎችን ማየት የሚችሉና በሰይጣን ያልተታለሉ ሰዎች ሁልጊዜ የክርስቶስን ባንዲራ ከፍ አድርገው በመያዝ በታማኝነት መንገድ ቀጥ ብለው ወደ ፊት ይጓዛሉ። በእነዚህ ማህበራት ውስጥ ለመቆጣጠር የዚህ ዓይነት ሰዎች ያስፈልጋሉ። የዚህ ዓይነት ተፅዕኖ ክብር የሚገባው በመሆኑ እነዚህን ስብሰባዎች እርግማን ከመሆን ይልቅ በረከት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። MYPAmh 254.1
የዚህን ዓይነት የሥነ-ፅሁፍ ማህበር ለማደራጀትና ለመንቀሳቀስ በእድሜ የበሰሉ ወንዶችና ሴቶች ከወጣቶች ጋር አንድነት ቢፈጥሩ ኖሮ ጠቃሚና ተወዳጅ ይሆን ነበር። ነገር ግን እነዚህ ስብሰባዎች የቀልድና የፈንጠዚያ ስብሰባዎች ሲሆኑ ጥቅም የለሽ ይሆናሉ። አእምሮንና ግብረ ገብን የሚያዋርዱ ይሆናሉ። MYPAmh 254.2
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በጥልቅ መመርመር፣ አእምሮን የሚያሻሽሉና እውቀትን የሚሰጡ ፅሁፎችን ማንበብ፣ ትንቢቶችን ወይም የክርስቶስን ውድ ትምህርቶች ማጥናት የአእምሮ ኃይሎችን የማጠንከርና መንፈሳዊነትን የመጨመር ተፅዕኖ ይኖራቸዋል። ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በደንብ መተዋወቅ ነገሮችን ለይቶ የማወቅ ኃይሎችን ይሞርዳል፣ ነፍስንም ከሰይጣን ጥቃት ይሸሽጋል። MYPAmh 254.3
ሐሳብንና ግምትን መቆጣጠር ሃላፊነታቸው እንደሆነ የሚገነዘቡ ጥቂቶች ናቸው። ያልተገራን አእምሮ ትርፋማ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ከባድ ነው። ነገር ግን አስተሳሰቦች በተገቢው ሁኔታ ሥራ ላይ ካልዋሉ በስተቀር ሃይማኖት በነፍስ ውስጥ ማደግ አይችልም። በቅድሚያ አእምሮ በቅዱስና ዘላለማዊ ነገሮች መያዝ አለበት። ካልሆነ ግን ከንቱና ጥልቀት የሌላቸውን ሐሳቦች ያስተናግዳል። የአእምሮም ሆነ የግብረ ገብ ኃይሎች መገራት አለባቸው! ከዚያ በኋላ ሥራ ላይ ሲውሉ እየጠነከሩና እየተሻሻሉ ይሄዳሉ። MYPAmh 254.4
አእምሮም ሆነ ልብ ለእግዚአብሔር አገልግሎት መቀደስ አለበት። ለእኛ ያለው ነገር ሁሉ የእርሱ ነው። የክርስቶስ ተከታይ የሆነ ሰው በማንኛውም የራስን ፍላጎት የማሟላት ተግባር ላይ፣ ወይም የፈለገውን ያህል ክፋት የሌለውና ተቀባይነት ያለው ቢመስልም ከእግዚአብሔር የተማረ ህሊና ለእውነት ያለውን ቅናት የሚቀንስና መንፈሳዊነትን ዝቅ የሚያደርግ መሆኑን የሚነገረውን ነገር መፈፀም የለበትም። እያንዳንዱ ክርስቲያን የክፋትን ኃይል ወደ ኋላ ለመመለስና ወጣቶቻችንን ወደ ጥፋት ጠራርጎ ከሚወስድ ተፅዕኖ ለመታደግ መሥራት አለበት። ማዕበሉን በመቋቋም መንገዳችንን መቀጠል እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን። Counsels to Teachers, Parents and Students, P. 541-544. MYPAmh 254.5