መልዕክት ለወጣቶች

424/511

መዝናናትና ራስን ማስደሰት

በትምህርት ላይ ያሉ ሰዎች መዝናናት ያስፈልጋቸዋል። በቀላሉ ሊጎዳ የሚችል የአእምሮ ማሽን እንዳይደክም አእምሮ ሁል ጊዜ በሀሰብ ውስጥ መሆን የለበትም። አካልም ሆነ አእምሮ እንቅስቃሴ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን ልክ እንደ ሌሎች መከተል እንደምንፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ የራስ መደሰቻን በመፈለግ ረገድም መሻትን የመግዛት ታላቅ አስፈላጊነት አለ። የመደሰቻዎቹ ባሕርይ በጥንቃቄና በጥልቀት መታየት አለበት። እያንዳንዱ ወጣት ራሱን እነዚህ መደሰቻዎች በአካል፣ በአእምሮና በግብረገብ ጤንነት ላይ ምን ተፅእኖ ያሳድራሉ? ብሎ መጠየቅ አለበት። አእምሮዬ እግዚአብሔርን እስከሚረሳ ድረስ በደስታ ይጠመድ ይሆን? የእርሱን ክብር ከፊቴ ማድረግን እተው ይሆን? ብሎ መጠየቅ አለበት። MYPAmh 244.2

ካርታን መጫወት መከልከል አለበት። በዚህ ምክንያት የሚፈጠሩ ጎደኝነቶችና ዝንባሌዎች አደገኛ ናቸው። በእንደዚህ ዓይነት መደሰቻዎች ለነፍስም ሆነ ለአካል የሚጠቅም ምንም ነገር የለም። የአእምሮ ችሎታን የሚያጠነክርና ለወደፊት ጥቅም የሚውል ጠቃሚ ሀሳብን ለማጠራቀም የሚረዳ ምንም ነገር የለውም። የሚደረገው ንግግር ብዙ ጊዜ ተራና አዋራጅ በሆኑ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው…። MYPAmh 244.3

እነዚህን ካርታዎች በመጫወት ኤክስፐርት (የተዋጠለት) መሆን ብዙ ጊዜ ይህንን እውቀትና ብልሃት ለግል ጥቅም ወደ ማዋል ይመራል። በመጀመሪያ ጥቂት ገንዘብ ይገኛል፣ ቀጥሎም ወደማይቀረው ጥፋት የሚመራ የቁማር ጥማት እስከሚፈጠር በዛ ያለ ገንዘብ ይገኛል። ይህ አደገኛ የሆነ መደሰቻ ስንቶችን ነው ወደ ኃጢአት ልምምድ፣ ወደ ድህነት ፣ ወደ ወህኒ ቤት፣ ወደ ነፍስ ግድያና ወደ ስቅላት የመራቸው። MYPAmh 244.4

ደስታን ለማግኘት ተብሎ ከሚኬድባቸው እጅግ አደገኛ ቦታዎች አንዱ ሲኒማ ነው። ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የግብረ ገብና የመልካም ባሕርያት መማሪያ ት/ቤት በመሆን ፋንታ የእርኩሰት መፈልፈያ ነው። በእነዚህ መዝናኛዎች መጥፎ ልምዶችና የኃጢአት ዝንባሌዎች ይጠናከራሉ፣ ይፀናሉም። ደረጃቸው የወረዱ መዝሙሮች፣ ፍትወትን የሚያነሳሱ የአካል እንቅስቃሴዎች፣ የሀሳብ መገለጫዎችና አመለካከቶች አስተሳሰብን ያዛቡና የግብረ ገብ ውድቀትን ያመጣሉ። የዚህን ዓይነት የሚታዩ ነገሮችን መከታተል ልምዱ ያደረገ ወጣት የመርህ ብልሽት ያጋጥመዋል። በሲኒማ አማካኝነት ከሚደረግ መደሰቻ የበለጠ አስተሳሰብን የሚመርዝ፣ የእምነት አሻራዎችን የሚያጠፋና ለትክክለኛ ደስታና ትክክለኛ ለሆኑ የህይወት እውነታዎች ያለውን ፍላጎት የሚያደነዝዝ ነገር የለም። MYPAmh 244.5

አስካሪ መጠጥ ሲጠቀሙት ሱሰኛ እንደሚያደርግ ሁሉ እያንዳንዱ ወደ እነዚህ የመደሰቻ ቦታዎች የሚደረግ ጉብኝት ወደዚያ ቦታ የመሄድን ፍቅር እየጨመረ ይሄዳል። ብቸኛ የሆነው ከአደጋ የመጠበቂያ እርምጃ ከቲያትር ቤቶች፣ ከሰርከስ ቦታዎችና ከእያንዳንዱ ጥያቄ ከሚያሳድር የመዝናኛ ቦታ መራቅ ነው። MYPAmh 244.6

ለአካልም ሆነ ለአእምሮ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም የሚሰጡ የመዝናኛ አይነቶች አሉ። ብሩህና ነገሮችን የመለየት ችሎታ ያለው አእምሮ ከተለመደው ሥራ የሚለይና የሚያዝናናን ነገር ቀለል ካሉ ነገሮች ብቻ ሳይሆን አስተማሪ ከሆኑ ነገሮችም ማግኘት ይችላል። ወጣ ብሎ ነፃ በሆነ ቦታ መዝናናትና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ የእግዚአብሔር ሥራዎችን ማሰላሰል እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ ይኖረዋል። Testimonies for the Church, Vol. 4, P. 651 -653. MYPAmh 244.7