የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
ክርስቶስ ምሳሌያችን
ክርስቶስ ወደ ዓለም የተላከው ለአባቱ ፍላጎቶች እንዲጠነቀቅ ነበር፡፡ እርሱ በሁሉም ነገር ምሳሌያችን ነው፡፡ ትምህርቱ የተለያየ ዓይነት መሆኑ እኛም ማጥናት የሚያስፈልገን ትምህርት ነው፡፡ {2SM 155.3} Amh2SM 155.3
ሁሉም ሰዎች በማስተዋላቸውና በልምምዳቸው ወይም ቃሉን በሚያስተላልፉበት መንገድ ተመሳሳይ አይደሉም፡፡ አንዳንዶች ያለማቋረጥ የክርስቶስን ሥጋና ደም ይወስዳሉ፡፡ የሕይወት ዛፍ ቅጠሎችን ይበላሉ፡፡ በክርስቶስ ትምህርት ቤት የማያቋርጡ ተማሪዎች ናቸው፡፡ በየቀኑ በመልካምነት ለውጥ ያሳያሉ፣ ለጌታ እንዲሰሩ ገጣሚ የሚያደርጋቸውን ልምድም ያገኛሉ፡፡ ተጽእኖአቸው የሕይወት ሽታ ለሕይወት ነው፡፡ መንፈሳዊ አእምሮ ስላላቸው መንፈሳዊ ነገሮችን በቀላሉ ለይተው ያውቃሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ነው፡፡ ምንም ዓይነት ሰማያዊ ወይም መለኮታዊ የሆነ ነገርን የማይገልጹ መጽሔቶች፣ ጋዜጣዎች እና መጻሕፍት አይስቧቸውም፡፡ ነገር ግን ለእነርሱ የእግዚአብሔር ቃል ሁል ጊዜ የከበረ እየሆነላቸው ይሄዳል፡፡ እግዚአብሔር ይቀርባቸውና ለመረዳት በማይከብዳቸው ቋንቋ ይናገራቸዋል፡፡ {2SM 155.4} Amh2SM 155.4
በየቀኑ አዲስ የጸጋ አቅርቦት በሚያገኙባቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ አእምሮአቸውን ማተኮርን ያልተማሩ ሌሎች አሉ፡፡ {2SM 155.5} Amh2SM 155.5
አንዳንድ ሰዎች ከሰማይ የተለየ መልእክት አላቸው፡፡ እነርሱ ለራሳቸው ጉዳት በቤተ ክርስቲያናት ላይ ለማንዣበብና ለእግዚአብሔር ሥራ እንቅፋት ለመሆን ሳይሆን ሕዝብን ለማንቃት መላክ አለባቸው፡፡ አንድን ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ሁለት ወይም ሶሰት አገልጋዮች መኖር ለቤተ ክርስቲያኗ ምንም አይጠቅምም፡፡ እነዚህ አገልጋዮች በጨለማ ውስጥ ላሉት ለማገልገል ከሄዱ ሥራቸው አንዳንድ ውጤቶችን ያሳያል፡፡ ልምድ ያላቸው ሰዎች ለአገልግሎት እየተዘጋጁ ያሉትን ወጣቶች ይውሰዷቸውና የማስጠንቀቂያ መልእክትን ለማስተላለፍ ወደ አዲስ የስራ መስክ ይሂዱ፡፡ {2SM 156.1} Amh2SM 156.1
እውነትን የሚያምኑ ሰዎች ብርሃናቸው በመልካም ሥራ ተገልጦ እንዲበራ በመፍቀድ እግዚአብሔር የሰጣቸውን በረከቶች ለሌሎች ሲያጋሩ ሳለ በከፍተኛ ደረጃ ይባረካሉ፡፡ በሁሉም ተግባሮቻቸው ትክክለኛ የሆኑ መርሆዎችን በማሳየት በግል ቅድስና ብርሃናቸው እንዲበራ ሲፈቅዱ የእግዚአብሔርን ሕግ መርሆዎች ያጎላሉ፡፡ እግዚአብሔር ሰራተኞቹ አዲስ ክልል እንዲጨምሩለት ይጠራቸዋል፡፡ በዓለም ውስጥ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር ላሉት ልባዊ በሆነ ቅንነት መስራት አለብን፡፡ ታማኝ የሆኑ ሰራተኞችን እየጠበቁ ያሉ ፍሬ ማፍራት የሚችሉ የሥራ መስኮች አሉ፡፡ {2SM 156.2} Amh2SM 156.2
በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ ተሰማርተው ያሉ ሰዎች ትሁትና ልባዊ በሆነ ጸሎት በፊቱ ከሰገዱ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በእጃቸው ይዘው በቃሉ ውስጥ ከመተላለፋቸውና ከኃጢአታቸው የተነሳ ሙታን እንደሆኑ የተገለጹትን ሰዎች የደነዘዙ ስሜቶቻቸውን ለመቀስቀስ መሄድ አለባቸው፡፡ ይህን ሥራ የሚሰሩ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ይባረካሉ፡፡ እውነትን የሚያውቁ ሰዎች ለአገልጋዮች «በእግዚአብሔር ስም ወደ መከሩ መስክ ሂዱ፣ ጸሎታችን እንደ ስለታም ማጭድ ከእናንተ ጋር ይሄዳል» በማለት እርስ በርሳቸው መበረታታት አለባቸው፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኖቻችን ለእግዚአብሔር ከልባቸው ወስነው ምስክርነትን ማስተላለፍ አለባቸው፣ ደግሞም ለነፍሳት ለመስራት ወደ ሥራ መስኩ የሚሄዱ አገልጋዮች እንዲጠቀሙ አስራታቸውንና ስጦታቸውን ለእርሱ ማምጣት አለባቸው፡፡ {2SM 156.3} Amh2SM 156.3
የዓለማችን ክፋት እንደ ሶዶምና ጎሞራ ክፋት በሆነበት በዚህ ዘመን ለጌታ በታማኝነት እየሰራ ያለ ሰው ማን ነው? በዙሪያው ያሉት የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኙ እየሰራ ያለ ሰው ማን ነው? ጌታ እንዲጠቀምብን እንደ ክብር ዕቃዎች ገጣሚ ለመሆን ነጽተን ተቀድሰናል ወይ? አሁን እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ቅርጸ-ቢስነት ከእግዚአብሔር አለመሆኑን ያስታውሳልን? መለኮት በግርማና በኃይል እጅግ በጣም የላቀ ስለሆነ በውበትና በቅድስና መመለክ አለበት፡፡. . . {2SM 156.4} Amh2SM 156.4
እግዚአብሔር ክርስትና በዓለማዊነት ላይ ያለውን ብልጫ ሕዝቡ በሕይወታቸው እንዲያሳዩ ይመኛል፡፡ እኛ መኖር ያለብን እግዚአብሔር ወንዶችንና ሴቶችን በመለወጥና የባሕርይ ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም ነጭ ወደማድረግ በመምራት ሥራው ውስጥ ሊጠቀምብን እንዲችል ነው፡፡ እኛ «በክርስቶስ ኢየሱስ ለመልካም ሥራ የተፈጠርን» (ኤፌ. 2፡10) የእርሱ ሰራተኞች ነን፡፡ በእኛ አማካይነት እግዚአብሔር ዘርፈ ብዙ ጥበቡን መግለጥ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ብርሃናችን በመልካም ሥራ በርቶ እንዲታይ ይጠራናል፡፡ --Manuscript 73a, 1900. {2SM 157.1} Amh2SM 157.1