የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
እንደገና ለመቀደስ የቀረበ ጥሪ
አሁን የጠራ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሥር-ነቀል ተሃድሶን ለማምጣት የሚሰራውን ሥራ ለመምራት መንፈስ ቅዱስ እንዲቆጣጠራቸው ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን እግዚአብሔር ይጠራል፡፡ ከፊታችን ችግር እንዳለ አያለሁ፣ እግዚአብሔርም ሠራተኞቹ በሥራ መስመራቸው ላይ እንዲሆኑ ይጠራቸዋል፡፡ አሁን እያንዳንዱ ነፍስ ባለፉት አመታት ከነበረው ይበልጥ በጠለቀ ሁኔታ እና ለእግዚአብሔር እውነተኛ የሆነ መቀደስን በሚያሳይ ቦታ መቆም አለበት፡፡ Amh2SM 400.3
በ1909 ዓ.ም የጀኔራል ኮንፍራንስ ስብሰባ ወቅት በስብሰባው ላይ በተገኙት አባላት ልብ ውስጥ ከዚህ በፊት ያልተሰራ ሥራ መሰራት አለበት፡፡ በስብሰባው ውስጥ በተገኙ ሰዎች ልብ ውስጥ የነበረውን ጠፍ መሬት ለማረስ እንዲቻል ልብን ለመመርመር ጊዜ መስጠት ይቻል ነበር፡፡ ይህ በንስሃና በኑዛዜ አማካይነት በእነርሱ የሚሰራውን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሥራ እንዲያስተውሉ ግንዛቤ ሊሰጣቸው ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ኃጢአትን ለመናዘዝ፣ ልባዊ ለሆነ ንስሃ፣ እና አዎንታዊ ለሆነ ተሃድሶ ዕድሎች ቢሰጡም ሥር-ነቀል የሆነ ሥራ አልተሰራም ነበር፡፡ አንዳንዶች የመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ ተሰምቷቸው መልስ ሰጥተዋል፤ ነገር ግን ለዚህ ተጽእኖ ሁሉም አልተሸነፉም ነበር፡፡ የአንዳንዶች አእምሮዎች ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ይሮጡ ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ የነበሩት ሁሉ በበኩላቸው ልባቸውን አዋርደው ቢሆን ኖሮ አስደናቂ የሆኑ በረከቶች ይገለጡ ነበር፡፡ Amh2SM 400.4
ያ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ ለበርካታ ወራት ከባድ ሸክም ተሸክሜ እግዚአብሔር በፊታቸው በግልጽ እንዳቀርብ ያስተማረኝን ነገሮች በኃጢአት ውስጥ ወደነበሩ ወንድሞች ትኩረት ለማምጣት ግፊት አደርግ ነበር፡፡ በመጨረሻ ከብዙ ጸሎት እና የተሰጡት መልእክቶች በጥንቃቄ ከተጠኑ በኋላ ከአጠቃላይ ሥራው ጋር በተገናኘ ሁኔታ ታማኝነት በሚሹ ቦታዎች ላይ ከተቀመጡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ባያስተውሉትም እንዲሰሩ የተጠሩበትን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ሆኑ፤ እግዚአብሔርን በመፍራት ወደ ፊት ሲቀጥሉ ብዙ በረከት ተቀበሉ፡፡ Amh2SM 401.1
ራሳቸው በመረጡት መንገድ ከመሄድ ይልቅ በእግዚአብሔር መንገድ ለመሄድ በእምነት በመረጡት በእነዚያ ጥቂት ሰዎች ሕይወት ውስጥ አስደናቂ የሆኑ ለውጦችን ማየቴ በልቤ ውስጥ ታላቅ ደስታን አመጣ፡፡ እነዚያ በኃላፊነት ላይ የነበሩ ወንድሞች ነገሮችን በተሳሳተ ብርሃን ማየታቸውን ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ሥራውን በሚያሳዝን ሁኔታ የሚያበላሹ ሁኔታዎችን ይፈጥሩ ነበር፤ ነገር ግን ተልኮ የነበረውን መመሪያ በመስማት ጌታን በመፈለጋቸው እግዚአብሔር ወደ ሙሉ ብርሃን አመጣቸውና ተቀባይነት ያለውን አገልግሎት እንዲያቀርቡና መንፈሳዊ ተሃድሶዎችን እንዲያመጡ አስቻላቸው፡፡ Amh2SM 401.2
እግዚአብሔር ከአገልጋዮቹ ፊት መንገድ ለማዘጋጀት እጁን ሲዘረጋ እርሱ ወደሚመራቸው ቦታ መከተል የእነርሱ ተግባር ነው፡፡ በልባቸው ሙሉ አላማ በመያዝ የእርሱን ምሪት የሚከተሉትን ሰዎች አጠራጣሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አይተዋቸውም፣ አይጥላቸውምም፡፡ Amh2SM 401.3