የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
የእሁድ ሕግ ችግር
ሌሊት በአእምሮዬ እምነታችንን የሚያጠናክሩ መረጃዎችን እየዘረዘርኩ ያለሁ ይመስለኝ ነበር፡፡ አሳሳቾች እየከፉ እንደሆኑ እናያለን፡፡ ዓለም ሀሰተኛ ሰንበትን በሕግ እስከ መመስረትና ለሁሉም መፈተኛ እስከ ማድረግ ድረስ እየሠራ እንደሆነ እናያለን፡፡ ጥያቄው በቅርቡ ከፊታችን ይቀርባል፡፡ የእግዚአብሔር ሰንበት ተረግጦ ሀሰተኛው ሰንበት ከፍ ከፍ ይላል፡፡ በእሁድ ሕግ ውስጥ ሰባተኛውን ቀን በሚጠብቁ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ሥቃይ የማድረስ ሁኔታ አለ፡፡ የሰይጣን እቅዶች አሰራር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ስደትን ያመጣል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋዮች ተጋድሎው የሚያስከትለውን ውጤት መፍራት የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ የተቀመጠላቸውን ምሰሌ የሚከተሉ ከሆነ፣ እግዚአብሔር እንዲያደርጉ ለሚፈልግባቸው ነገሮች ታማኞች ከሆኑ፣ ሽልማታቸው ዘላለማዊ ሕይወት፣ በእግዚአብሔር ሕይወት የሚለካ ሕይወት ነው፡፡ Amh2SM 375.1
በዚህ ወቅት በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ቁርጠኝነት ያለበትን ባሕርይ የመገንባት ሥራ መካሄድ አለበት፡፡ በዓለም ፊት የአዳኙን ባሕርይ ማጎልበት አለብን፡፡ እውነተኛና የሚቀድስ እምነትን ሳይለማመዱ እግዚአብሔርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ ለእምነታችን እያንዳንዳችን በግላችን ሀላፊነት አለብን፡፡ እውነተኛ እምነት ፈተናና ችግር ሲገጥመው የሚሸነፍ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር ለሕዝቡ የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ The Review and Herald, Sept. 30, 1909. Amh2SM 375.2
ቸርነትንና እውነተኛ ትህትናን ማሳየት ያለብን ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ ህሊናችን በሚያዘን መንገድ እግዚአብሔርን የማምለክ መብት እንዲከበርልን በሕግ መማክርት ፊት ልባዊ የሆነ ተማዕጽኖ ማቅረብ ሊኖርብን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር በፈቃዱ የሕጉ ጥያቄዎች በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ በተቀመጡ ሰዎች ፊት እንዲቀርቡ አቅዷል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ፊት ስንቆም የስሜት መራርነት ማሳየት የለብንም፡፡ ያለማቋረጥ ለመለኮታዊ እርዳታ መጸለይ አለብን፡፡ ባሪያዎቹ በግንባራቸው ላይ ማህተም እስኪደረግላቸው ድረስ አራቱን ነፋሳት የሚይዝ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ The Review and Herald, Feb. 11, 1904 Amh2SM 375.3