የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

299/349

ጸሎት፣ እምነት፣ በእግዚአብሔር መደገፍ

በዚህ አደጋ በሞላበት ዘመናችን ውስጥ ሰይጣን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ጥላውን በሚያጠላበት ጊዜ የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር ልባዊ ከሆነ እምነት ጋር የተቀላቀለ ግለት ያለው ጸሎትና በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሕዝቡን ተማጽኖ መስማት እንደሚያስደስተው እያንዳንዱ ሰው ልብ ይበል፤ የኃጢአት መብዛት የበለጠውን ልባዊ ጸሎት እንዲደረግ ይጋብዛል፡፡ እግዚአብሔር ምንም እንኳን ቢዘገይ ቀንና ማታ ወደ እርሱ ለሚጮሁት ምርጦቹ እንደሚበቀልላቸው ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ Amh2SM 372.2

ሰዎች የእግዚአብሔርን ትዕግሥት ያለ አግባብ ወደ መጠቀምና ይቅር ባይነቱን ወደ መዳፈር ያዘነብላሉ፡፡ ነገር ግን በሰዎች ኃጢአት ውስጥ እግዚአብሔር ጣልቃ የሚገባበት ጊዜ አለ፤ ውጤቶቹም አስከፊ ናቸው፡፡ «እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ፣ ኃይሉም ታላቅ ነው፤ በደለኛውንም ንጹህ ነህ አይልም» (ናሆም 1፡3)፡፡ የእግዚአብሔር ትዕግሥት አስደናቂ ነው፣ ይህ የሆነበት ምክንያት እርሱ በራሱ ባሕርይ ላይ ግዴታ ስለሚያስቀምጥ ነው፡፡ ነገር ግን ቅጣት የማይቀር ነው፡፡ በየምዕተ ዓመቱ የተፈጸመው ስድ ተግባር ለፍርድ ቀን ቁጣን አስቀምጧል፤ ያ ቀን ሲመጣና የበደል ጽዋ ሲሞላ እግዚአብሔር እንግዳ (ያልተለመደ) ሥራውን ይሰራል፡፡ የእግዚአብሔር ትዕግሥት ማለቅ አሰቃቂ ነገር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ ከምህረት ጋር ያልተቀላቀለ ተብሎ የተገለጸበት ምክንያት በአስደናቂ ሁኔታና በኃይል ስለሚወርድ እና ምድር ባድማ ስለምትሆን ነው፡፡ የበደል ስፍር የሚሞላው ብሔራዊ ክህደት ሲፈጸም፣ የአገሪቱ መሪዎች የሰይጣንን መርህ በመተግበር ራሳቸውን ከኃጢአት ሰው ጋር ሲያሰልፉ ነው፤ ብሔራዊ ክህደት የብሔራዊ ውድቀት ምልክት ነው፡፡ Amh2SM 372.3

እግዚአብሔር የብዙ ትውልድን መሠረት ለማንሳትና በዙሪያቸው አጥር ለማጠር ሕዝቡን ባዘጋጀላቸው ክፍት ቦታ ውስጥ ጨምሯአቸዋል፡፡ ሰማያዊ ኃይሎች፣ በብርቱነታቸው የላቁ መላእክት፣ ከሰብአዊ ወኪሎች ጋር ለመተባበር ለእግዚአብሔር ትዕዛዝ ታዛዥ በመሆን እየተጠባበቁ ስለሆኑ ሁኔታዎች ከመለኮታዊ ኃይል በስተቀር ምንም ነገር የሰይጣን ወኪሎችን መመከት እስከማይችልበት ደረጃ ድረስ ሲደርሱ ጌታ ጣልቃ ይገባል፡፡ ሕዝቡ የሰይጣን ኃይልን መቃወም የማይችሉ እስኪመስል ድረስ እጅግ ከፍተኛ በሆነ አደጋ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ይሰራል፡፡ ነገሮች ከሰው አቅም በላይ መሆናቸው እግዚአብሔር ሥራውን እንዲሰራ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ Amh2SM 373.1

የእግዚአብሔር ክብር በላያቸው ስለወጣ አሁን ታማኞችና እውነተኞች ተነስተው የሚያበሩበት ጊዜ ነው፡፡ አሁን መልካችንን ለመደበቅ ጊዜ የለም፣ ጦርነቱ እያየለ እየመጣ ሳለ ከዳተኞች ለመሆን ጊዜ የለም፡፡ የጦር መሣሪያዎችን ለማስቀመጥ ጊዜ የለም፡፡ በጽዮን ግንብ ላይ ያሉ ጠባቂዎች መንቃት አለባቸው፡፡ Amh2SM 373.2

በዚህ ሰዓት እግዚአብሔርን እጅግ የማመሰግነው ዙሪያችንን ከሚከቡ ችግሮች እና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከሚመጣው ጭቆና አእምሮአችንን ማራቅ እና ብርሃንና ኃይል ወዳለው ሰማይ መመልከት ስለምንችል ነው፡፡ ራሳችንን በእግዚአብሔር አጠገብ፣ በክርስቶስና በሰማያዊ ኃይሎች አጠገብ ካስቀመጥን ሁሉን የሚችለው አምላክ ሰፊ ከለላ በላያችን ነው፣ ብርቱ የሆነው የእሥራኤል አምላክ ረዳታችን ነው፤ ስለዚህ መፍራት የለብንም፡፡ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚነኩ ሰዎች የእርሱን የዓይን ብሌን ይነካሉ…፡፡ Amh2SM 373.3

ወንድሞች ሆይ! ወደ ቤቶቻችሁ እና ወደ ቤተ ክርስቲያኖቻችሁ ስትመለሱ የክርስቶስን መንፈስ ይዛችሁ ትሄዳላችሁን? አለማመንን እና ነቀፌታን ታስወግዳላችሁን? ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አብረን ወደ ፊት መግፋት እና አብረን መሥራት ወዳለብን ጊዜ እየደረስን ነን፡፡ በአንድነት ብርታት አለ፡፡ በአለመስማማትና በመለያየት ውስጥ ያለው ድካም ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ወይም አራት ሰዎች ወይም ሃያ ሰዎች በሥራው ውስጥ ያሉትን ሌሎች ሰዎች ሳያካትቱ ወሳኝ የሆነውን ሥራ በእጃቸው ይዘው እነርሱ ብቻ እንዲያከናውኑ በፍጹም የእግዚአብሔር እቅድ አይደለም፡፡ Amh2SM 373.4

እግዚአብሔር የሚፈልገው ሕዝቡ አብሮ እንዲመክር፣ የተባበረች ቤተ ክርስቲያን እንዲሆንና በክርስቶስ ፍጹም አካል እንዲሆን ነው፡፡ ከአደጋ የምንጠበቅበት ብቸኛው ደህንነታችን ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ በመሻት ከእርሱ ጋር አብሮ ለመስራት በሰማይ ምክሮች ውስጥ መግባት ነው፡፡ ማንኛውም ቡድን ሕብረት በመፍጠር «ይህን ሥራ ተረክበን በራሳችን መንገድ ልናከናውነው ነው፤ ሥራው እኛ እንደምንፈልገው ካልሄደልን ወደ ፊት እንዲቀጥል ተጽእኖአችንን አናሳርፍም» ማለት የለበትም፡፡ ይህ የሰይጣን ድምጽ እንጂ የእግዚአብሔር ድምፅ አይደለም፡፡ ይህን ለመሰለ አስተያየት ታዛዦች አትሁኑ፡፡ Amh2SM 373.5

እኛ የምንፈልገው የኢየሱስን መንፈስ ነው፡፡ የእሱ መንፈስ ሲኖረን እርስ በርሳችን እንዋደዳለን፡፡ ተሸክመን መሄድ ያለብን መረጃዎች እነዚህ ናቸው፡- «እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች በዚህ ያውቃሉ» (ዮሐ. 13፡ 35)፡፡ Amh2SM 374.1