የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
ከአመጽ ምስጢር ጋር ስምምነት የለም
በኢየሱስ የነበረው አይነት እምነት ያላቸው ሰዎች በዝምታ እንኳን ለአመጽ ምስጢር እውቅና አይስጡ፡፡ የማስጠንቀቂያ ድምጽ ማሰማትን በፍጹም አያቋርጡ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ትምህርትና ሥልጠና በመካከላችን ያሉት ልጆችና ወጣቶች የአመጽ ሰው ከሆነው ኃይል ጋር ምንም አይነት ስምምነት መፍጠር እንደማያስፈልግ እንዲረዱ የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ ምንም እንኳን ንብረታችንን እና ነጻነታችንን የሚያሳጣ ጊዜ የሚመጣም ቢሆን ጦርነቱን መዋጋት እንደምንችል አስተምሩአቸው፤ ጦርነቱ በየዋህነት እና በክርስቶስ መንፈስ መገጠም አለበት፤ እውነት ልክ በክርስቶስ እንዳለ ሆኖ መጠበቅና መታመን አለበት፡፡ ሀብት፣ ክብር፣ ምቾት ወይም ማንኛውም ነገር ቢሆን ሊሰጠው የሚገባው ሁለተኛ ደረጃ ነው፡፡ እውነት መደበቅ፣ መካድ ወይም መሸፋፈን የለበትም፣ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ መታመንና በድፍረት መታወጅ አለበት፡፡ Amh2SM 369.3
እግዚአብሔር ዝም የማይሉና ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚጮሁ፣ ድምጻቸውን እንደ መለከት ከፍ አድርገው የሚያሰሙ እና ለእግዚአብሔር ሕዝብ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን የሚያሳዩ ታማኝ ጠባቂዎች በጽዮን ግንብ ላይ አሉት፡፡ የእውነት ጠላት በአራተኛው ትዕዛዝ ላይ የማያወላዳ ጥቃት እንዲሰነዝር ጌታ ፈቅዶለታል፡፡ በዚህ አማካይነት ለመጨረሻው ዘመን መፈተኛ ስለሆነው ጥያቄ የማያመነታ ፍላጎት ለማነሳሳት አቅዷል፡፡ ይህ የሶስተኛው መልአክ መልእክት በኃይል እንዲታወጅ መንገድ ይከፍታል፡፡ Amh2SM 370.1
አሁን እውነትን የሚያምን ማንም ሰው ዝም አይበል፡፡ አሁን ማንም ቢሆን ግድ የለሽ መሆን የለበትም፣ «ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ” (ዮሐ. 14፡ 13) ያለውን ተስፋ በመያዝ ሁሉም ልመናቸውን ወደ ጸጋው ዙፋን ያቅርቡ፡፡ አሁን ጊዜው የሚባክን ጊዜ አይደለም፡፡ ሰዎች ነጻነት ስላላት የሚኩራሩባት ይህቺ አገር የኃይማኖት ነጻነትን ለመገደብ እና የጳጳሱ ውሸትና ማታለያ ተግባራዊ እንዲሆን ለማስገደድ በሕገ-መንግስቷ ውስጥ የተካተተውን እያንዳንዱን መርህ ለመሰዋት እየተዘጋጀች እስከሆነ ድረስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ልመናቸውን ወደ ታላቁ አምላክ በእምነት ማቅረብ አለባቸው፡፡ በእግዚአብሔር ለሚታመኑት በተስፋዎቹ ውስጥ ሊያበረታታ የሚችል እያንዳንዱ ማደፋፈሪያ አለ፡፡ በግል ሊደርስብን የሚችል አደጋ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሊያሳዝነን አይገባም፣ ነገር ግን የመከራቸው ጊዜ እግዚአብሔር ግልጽ የሆነ ኃይሉን የሚገልጥበት ወቅት ስለሆነ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ብርታትና ተስፋ ማነሳሳት አለበት፡፡ Amh2SM 370.2
ክፉን ለመቃወም ምንም ሳናደርግ እጃችንን አጣጥፈን በዝምታ ጭቆናን እና መከራን እየጠበቅን መቀመጥ የለብንም፡፡ የተባበረው ጩኸታችን ወደ ሰማይ ይላክ፡፡ እየፀለያችሁ ሥሩ፣ እየሰራችሁ ፀልዩ፡፡ ነገር ግን ማንም ቢሆን የሚያደርገውን ነገር በችኮላ አያድርግ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ ሁኔታ ትሁትና የዋህ መሆን እንዳለባችሁ ተማሩ፡፡ በማንም ላይ፣ በግለሰብም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ላይ፣ የምሬት ክስ ማቅረብ የለባችሁም፡፡ ኢየሱስ ከሰዎች አእምሮ ጋር ይሰራ እንደነበረ ለመሥራት ተማሩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጠንከር ያሉ ነገሮች መነገር አለባቸው፤ ነገር ግን ግልጽ የሆነ እውነትን ከመናገራችሁ በፊት የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በውስጣችሁ ስለማደሩ እርግጠኞች ሁኑ፤ የመቁረጥ ሥራ የእናንተ ሥራ ስላልሆነ እርሱ እንዲቆርጥ መፍቀድ አለባችሁ፡፡ Amh2SM 370.3